Friday 25 January 2019

የሮማኒያው እስር ቤት…


ቀሲስ ጊኦርጊስ ካልቹ በቅርብ ጊዜ ያረፉ ታላቅ የሮማኒያ ኦርቶዶክስ ካህን ናቸው። ከዚህ ቪዲዮ የሳቸውን እና የሌሎች በሮማኒያ የቀድሞው ስረአት የተሰቃዩ ሰዎች ታሪክን ይናገራል…

Thursday 24 January 2019

በረከት ስመዖን፤ የድክመታችን መለክያ

ሃብታሙ አያሌው እንዳለው ፍትህ መታየቱ ጥሩ ነው። ሆኖም ለበረከትም፤ ለቤተሰቦቹም፤ ለኢትዮጵያም አዝናለሁ።

እንደ ኢትዮጵያዊ አፍራለሁ። እንደ ሀገር እንደ በረከት፤ ታደሰ፤ አዲሱ፤ መለስ ወዘተ አይነት አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎችን ማፍራታችን ያሳፍራል። መቶ እጥፍ የሚያሳፍረው ግን እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎችን መሪዎቻችን እንዲሆኑ መፍቀዳችን ነው።

ሌላ ላይ መፍረድ ቀላል ነው ግን ልክ አይደለም አዋጪም አይደለም። ሃላፊነት የወሰደ ብቻ ነው ህይወቱን በትክክል መምራት የሚችለው። እኛም እንደ ኢትዮጵያዊያን በነ በረከት መኖር እና ስልጣን መያዝ ሃላፊነት መውሰድ አለብን። በተለይም የፖለቲካ መደባችን ከጃንሆይ ዘመን ጀምሮ ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥፋቶችን አይተን፤ አምነን፤ ህፍረታችንን አምነን፤ ተቀብለን፤ ንስሃ መግባት አለብን።

ከበረከት ስመዖን መማር የሚገባኝ ይህ ነው ብዬ አምናለሁ።

Tuesday 22 January 2019

ስለ የውጭ ሀገር «የበጎ አድራጎት ድርጅቶች» ማስታወሻ

የኤንጂኦዎችን ችግር የታወቀ ነው ግን ከፕሮፓጋንዳ እና ገንዘብ ውግያ አንጻር ችግራቸውን ደጋግሞ ማስታወስ ጥሩ ይመስለኛል። ይህን እንድታነቡ እጋብዛለሁ፤

https://www.theamericanconservative.com/articles/how-a-foreign-reporter-got-jaded-over-the-united-nations/

Friday 18 January 2019

Unraveling NAMA's "Intellectual Cover"

የአማራ ብሄርተኝነት በመሰረቱ የብሶት ፖለቲካ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_30.html) ነው። የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) መሪዎችም ተከታዮችም በትርክታቸው የሚያተኩሩት ስለአማራ ላይ የደረሰው የ27/44 ዓመት በደል ነው። አማራ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ተለይቶ ተበድሏል ይላሉ። አልፎ ተርፎ ካሳም ይገባዋል ይላሉ። ከፖለቲካዊ ፕሮፓጋንዳዎቻቸው ምናልባት 80%ኡ ስለዚህ ስለ አማራው መጨቆን ነው። ይህ የአማራ ብሄርተኝነት በመሰረቱ በብሶት የሚመራ ንቅናቄ መሆኑን ያስረዳል።

ሆኖም እንደ ማንኛውም ፖለቲካ ንቅናቄ የአማራ ብሄርተኝነት ትርክት እና ፖለቲካዊ ጽንሰ ሃሳብ (theory) ያስፈልገዋል። ይህ intellectual cover (የምሁራን ሽፋን ልበለው?) የአብን ምሁራኖች በደምብ ሰርተውበታል። ዋናው የዚህ ሽፋን መልእክት እንዲህ ነው፤

«የአማራ ብሄርተኝነት የሚያስፈልገው የሌሎች (ያጠቁን) የጎሳ ብሄርተኝነቶችን በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዳያመዝኑ ማድረግ ነው። የአማራ ብሄርተኝነት የሌሎች የጎሳ ብሄርተኝነቶችን balance በማድረግ የአማራንም የኢትዮጵያንም ህልውና ይጠብቃል።»

ማንኛውም ትንሽም ስለፖለቲካ/ታሪክ የሚያውቅ ሰው ይህ ትክርት እጅግ የተሳሳተ እንደሆነ ያውቃል። በርካታ ጎሳዎች ወይንም ክልሎች ባሉባቸው ሀገራት የስልጣን ውድድር በመሃል እና በክልሎቹ እንደሆነ የታወቀ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/on-nama-strategies.html)። ስልጣን ከምሃሉ (ኢትዮጵያዊነት) ወደ ልልሎች (ጎሳ ብሄርተኝነት) ቁጥር ሁሉም ጎሳ ብሄርተኞች ይጠነክራሉ። የጎሳ ብሄርተኞቹ ከእርስ በርስ ይልቅል የሚሟገቱት ከመሃሉ (ከኢትዮጵያዊነት) ነው። ዋናው አላማቸው መሃሉ ማድከም ነው። በዚህ ጋራ አላማቸው ይተባበራሉ። መሃሉ መንምኖ ሲያበቃው ስልጣን በሙሉ በጎሳ ብሄርተኞች እጅ ይሆናል። ከዛ እነዚህ የጎሳ ብሄርተኞች (ለምሳሌ ህወሓት፤ ኦነግ፤ አብን፤ ወዘተ)እርስ በርስ መደራደር አይችሉም። በጎሳ እና ብሶት የተመሰረቱ ስለሆነ የጋራ ማንነት እና ጥቅም ስለማይታያቸው የሚደራደሩት በባዶ ድምር (zero sum) አቋም ነው። ወጤቱ ጦርነት እና መለያየት ነው የሚሆነው። ሰለባው በየክልሉ የሚኖር አማራ፤ አማራ ክልል፤ መላው ኢትዮጵያዊ ነው የሚሆነው። መሃሉ ሲመነምን እና ጎሳ ብሄርተኞች ሲጠነክሩ ውጤቱ ይህ ነው።

እስቲ በዚህ ረገድ አንዳንድ የአብን አስተሳሰብ የውስጥ ተቃርኖዎች (inconsistencies) እንመልከት። በአንድ በኩል የጎሳ አስተዳደርን (ethnic nationalism) እንቃወማለን፤ የዜጋ ፖለቲካ ነው የሚያስፈልገው ያላሉ። በጎሳ የተደራጀነው ነባራዊው ሁኔታ አስገድዶን ነው እንጂ የጎሳ አስተዳደር ይቁም ይላሉ። የጎሳ አስተዳደር መኖር የለብትም ሲሉ ደግሞ ምክንያቱ አንድ ሀገር በጎሳ ሲስተዳደር ግጭቶች ይበዛሉ ነው። ኦሮሚያ የሚኖሩ አማሮች ይጠቃሉ፤ ነባር እና መጤ ግጭት። ጠረፍ ላይ ግጭት ይኖራል፤ የመሬት ግጭት። በሁሉም የፖለቲካም የማህበረሰብም መስክ ሰው ጎሳውን አስቀድሞ ኢ-ፍትሃዊነት ያራምዳል፤ የፍትህ ግጭት። ለዚህ ነው የጎሳ አስተዳደር የግጭት ምንጭ ነው እና ይቅር የሚባለው። በሌላ አባባል ፖለቲካ በጎሳ ብሄርተኝነት ሲመራ ግጭት ይመጣል ነው። እንዲህ ከሆነ ኢንዴት ነው አብን እንደሚለው የአማራ፤ የኦሮሞ፤ የትግራይ ወዘተ ብሄርተኞች ኢትዮጵያዊነትን አፍርሶ እንደገና በድርድር መገንባት የሚችሉት! የጎሳ ብሄርተኞች መደራደር አይችሉም ተብሏል። አሁን ደግሞ መደራደር ይችላሉ። ሃሳቦቹ ይቃረናሉ።

አልፎ ተርፎ «የኢትዮጵያ የብሄር (ጎሳ) እስር ቤት ናት፤ ሰለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጎሳው ይሰብሰብ እና እነዚህ የጎሳ ብሄርተኛ ስብስቦች አንዲስ ኢትዮጵያ ይመስርቱ» የሚለው ሃሳብ በ1950/60ዎቹ በማርክሲስት የተማሪ ንቅናቄው የተወለደ ነው። እስከ ዛሬም እነ ህወሓት፤ ኦነግ እና ሌሎች ጎሳ ብሄርተኞች ይህንን አቋም ነው የያዙት። በ1983 ህወሓት ስልጣን ሲይስዝም ይህን ነው አሰምሮ የተናገረው። «እንዳንተ «አንድነቶች» ኣናንተ «አማሮች»፤ እምዬ ኢትዮጵያ ከማለት በጎሳችሁ ተሰብሰቡ እና ተደራደሩ» እያሉ መሃይም ጥሩምባቸውን ይነፉ ነበር። ይህ ሃሳብ ወድቅ መሆኑ የገባን ደግሞ የጎሳ ብሄርተኞች ስብስብ ጦርነት እንጂ ሰላም አያመጣም ነበር። እንሆ ውጤቱን አየነው። ፖለቲካ በጎሳ ሲሆን ጸብ ብቻ ነው የሚኖረው። የጎሳ ፖለቲካ በተፈጥሮ የዜሮ ድምር አስተሳሰብን ይከተላልና።

ስለዚህ አብን ይህንን ታሪክ አውቆ እንዴት ነው ወደ ጎሳ ፖለቲካ እንመለስ የሚለው? አይገባኝም። እኔ እንደሚመስለኝ የሚገባ ብሶት እና ቅሬታቸውን የምሁራን ልብስ (intellectual cover) ለማልበስ ብለው የአብን ልሂቃን እራሳቸውን ወደ የማይሆን ትምዝምዝ ውስጥ አስገበተዋል። የአማራ ብሄርተኝነት በዚህ መልኩ ምንም አይነት ምሁራዊ ድጋፍ የለውም እና ሊፈጥሩ ለት አይችሉም። የብሶት የጎሳ ብሄርተኝነት ነው፤ ሌላ ነገር አንፍጠርለት። አንዴ ይህንን ካመንን በኋላ እንዴት ነው የህዝቡን ብሶት እና በደል በሚጠቅመው ሁኔታ ማስተናገድ የሚቻለውን የፖለቲካ ጥያቄን ለመመለስ እንስራ።

Thursday 17 January 2019

የጎሳ አስተዳደር አንድ እና አንድ ችግር ነው፤ የግጭት ምንጭ ነው

ፖለቲካ በሃሳብ ብቻ ነው ምሆነ ያለበት እንጂ በጎሳ መሆን የለበትም ሲባል ዋናው ምክንያቱን አጥብቀን ማስረዳት አለብን። ምክንያቱ የብሄር ፖለቲካዊ ጥያቄ ስለሌለ አይደለም፤ ጎሳዎች ስላልተጨቆኑ አይደለም፤ የርዕዮት ዓለም ጉዳይ አይደለም። መሰረታዊ ምክንያቱ፤

«ጎሳ ወደ በፖለቲካ ሲገባ የግጭት ምንጭ ይሆናል ነው»።

ይህ ደግሞ የርዕዮት ዓለም ወይንም የቴኦሪ አመለካከት ሳይሆን በተግባር empirically በሀገራችን (ሌሎችን ሀገራት ምሳሌ ትተን) የያእነው እያየን ያለው ነው። በህወሓት ዘመን የጎሳ አስተዳደር የግጭት ምንጭ ነበር። ግጭቶቹ ሀውሓት የሰራቸው ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ሌሎች ነበሩ። በዴሞክርሲ እጦት ሳይሆን በሌላ ምክንያቶች የተነሱ ነበሩ።

አሁን ደግሞ «ነፃነት» ባለበት የጠ/ሚ ዓቢይ ዘመን የጎሳ ግጭቶች እየቀጠሉ ነው። ይህ አስምሮ የሚያሳየው የጎሳ አስተዳደር ወይንም የጎሳ ፖለቲካ በነፃነት እና ዴሞክራሲያዊ አገዛዝም ግጭቶች የመጣል ነው።

ስለዚህ የጎሳ ፖለቲካ/አስተዳደር የግጭት ምንጭ ነው። መብት ነው። ጥያቄዎችን ያስተናግዳል። ግን ግጭት እና ጦርነት ያመጣል።

አማራጩ ምንድነው። የጎሳ ጥያቄዎች በጎሳ አስተዳደር ሳይሆን በሌላ መልኩ ይመለሱ። ለምሳሌ «የአካባቢዬ ባህል አይናድ» ከሆነ በአካባቢ ፖለቲካዊ መብቶች ይመለስ። «ቋንቋዬ ይስፈን» ከሆነ በአካባቢ ፖለቲካ እና በብሄራዊ ዴሞክራሲ መንገድ ይመለስ። ወዘተ። የጎሳ ጥያቄዎች በዚህ መልኩ ሊመለሱ ይችላሉ። እንኳን እንደ ኦሮሞ አይነት የግዙፍ ጎሳ ጥያቄ የአናሳዎችም በዚህ መልኩ ይመለሳል።

Wednesday 16 January 2019

የድሮ ስረአት ናፋቂ ነኝ!

የአብን አመራሮች ክርስቲያን ታደለ እና በለጠ ሞላ እራሳቸውን «ትምክሕተኞች» ነን ካሉ እኔም እውነቱን ለመናገር በአቅሚቲዬ «የድሮ ስረአት ናፋቂ» ነኝ ማለት የምችል ይመስለኛል። የኃይለ ሥላሴ መንግስት ከስልጣን ሲወድቅ እድሜዬ ገና ሁለት ዓመት ቢሆንም ታሪክ በመስማት ስሜቴ ያንን ዘመን እንድናፍቀው አድርጎኛል።

ግን ዘመኑም አገዛዙም በርካታ ችግሮች ነበራቸው። የፍትህ እጦት፤ አድሎአዊነት፤ ወዘተ ነበረ። ሁላችንም እንደምናውቀው በርካታ ጪሰኞች እነሱ ወይንም አባት አያቶቻቸው ከመሬታቸው ተፈናቅለው በኢፍትሃዊ አሰራር ባላባቶችን ያገለግሉ ነበር። እንደዚህ አይነት ችግሮች እንደነበሩ እያወኩኝ እንዴት ያዘመን ይበልጥ ያስረአት ይናፍቀኛል።

ለቤተሰቦቼ ያዘመንን ጥሩ ነበር። ችግሩ እነሱን በቀጥታ አላጠቃም እና እነሱ በሰላም እና ብልጽግና ይኖሩ ነበር። ደርግ ሲመጣ ግን ችግር እየመጣ ጀመረ። የፖለቲካ ቀሱም ቤታችን ላይ ሊያንኳኳ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደርግን ጠላሁ የጃንሆይ መንግስትን ናፈኩኝ። እንደ ማንኛውም ልጅ የራሴ ህይወት እና ልምድ (experience) አመለካከቴን ወሰነው።

መቼም አሁን ይህ አመለካከት የተሟላ እንዳልሆነ ይገባኛል። እኔ እና ቤተሰቦቼ ሰላም ስለነበራቸው ያዘመን እና ስረአት ጥሩ ነበር ማለት እንዳልሆነ ይገባኛል! ግን አሁንም ይናፍቀኛል። ለምን? ያኔ እኛ ኢትዮጵያዊያን የቆፈርነው ጉድጓድ ገና ብዙ ጥልቅ አልነበረም! ማለትም በርካታ ችግሮቻችንን በቀላሉ በአንዳንድ ትናንሽ ማስተካከያዎች ልናስወግድ እንችል ነበር። የኔ መሬት በሽ ነበር፤ ደን ነበር፤ ልሂቃኖቻችን ብዙ በማርክሲዝም አልተዋጡም ነበር፤ ጎሰኝነት አልሰፈነም ነበር። ተስፋ ቅርብ ነበር።

አሁን ግን ተጨማሪ ሌላ የ50 ዓመት የጉድጓድ ቁፈራ አካሄደናል። ጥልቅ የሆነ ጉድጓድ ውስጥ ነን። አሁንም ተግተን ሰርተን መውጣት እንችላለን ግን ስራው ከበፊቱ ይልቅ እጅግ ከባድ ነው። ብዙ በጣም የተመላሹ ነገሮች አሉ።

ስለዚህ አዎን የድሮ ስረአት ናፋቂ ነኝ። ግን የምናፍቀው ምክንያት ያኔ ችግሮች ቢኖሩም እንደ ዛሬ ያህል ለማስተካከል አይከብዱም ነበር ብዬ ስለማምን ነው። እንጂ የጃንሆይ ዘመን እና ስረአት ችግሮች አልነበረባቸውም ለማለት አይደለም!

Monday 14 January 2019

ስለ ራያ ማንነት ውይይት፤ ዳር ዳሩን ከማለት ወደ ቁምነገሩ ካልገባን ችግሮችን አንፈታም


ይህን ስለ ራያ ማንነት ጉዳይ ቃለ ምልልስ ስመለከት ጠያቂውም እንግዶቹም ስለ ህግ አፈጻጸም እና ሂደታዊ (procedural) ጉዳዮች ከዓንድ ሰዓት በላይ ተወያይተው ዋናው መሰረታዊ የሆነው ጉዳይ ላይ ምናልባት 10 ደኪካ ነው ያዋሉት። «በግልጽ እንነጋገር ከተባለ…» ማለቱ ለምን ያስፈልጋል፤ መጀመሪያኑ በግልጽ ስለ መሰረታዊ ጉዳዩ መነጋገር ነው።

በግጭት መፍታት (conflict resolution) መሰረታዊ ችግር እንዳለ መገንዘብ፤ ከዛ ችግሩን ማወቅ፤ ከዛ ችግሩን ለመፍታት መስራት አብዛኛው ጊዜ የግድ የሆነ አስፈላጊ ሂደት ነው። አለበለዛ የችግሮቹ ውጤቶች ላይ እየተተኮረ እሳት እየተለኮሳ እሳት እያጠፋን እንቀጥላለን። መሰረታዊ ችግሩ እየተባባሰ ይሄዳል። እርግጥ የግጭቱ አካሎች ስለ መሰረታዊ ጉዳዩ ማውራት ማሰብም አይወዱ ይሆናል ግን አማራጭ የለም። ክስ ብሎ አለስልሶ ወደዛ መግባት ግድ ነውና።

የራያ መሰረታዊ ጉዳይ የራያ ማንንነት ኮሚቴ(ዎች) መቼ አመለከቱ ለማን አመለከቱ አይደለም። ይህ ሁለተኛ ጉዳይ ነው እና ብዙ የውይይት ጊዜ ሊፈጅ አይገባም። መሰረታዊ ችግር እና ጥያቄው እንደገባኝ ከሆነ እንዲህ ነው፤

1) እኛ ከትግሬ የተለየ የራያ ማንነት አለን እና አለፍላጎታችን በትግሬ ክልል ተካለልን፤
2) ሰባዊ መብታችን በትግራይ ክልላዊ መንግስት ለ27 ዓመት ትጥሷል እና ተጭቁነናል፤
3) መጀመሪያውኑ የጎሳ አስተዳደር ባይሆን ኖሮ ይህ የማንነት ጉዳያችን በዚህ መልኩ አይነሳም ኖሮ፤
4) አማራ ክልል ብንገባ መብታችን እና ሰላማችን ይከበራል እና የአምባገናን ትግራይ ክልልውስጥ መሆን አንፈልግም።

በርካታው የውይይቱ ጊዜ በነዚህ ጥያቄዎች ዙርያ መሆን ነበረበት ብዬ አስባለው። በዛሬው የፖለቲካ ሁኔታ ጥያቄዎቹ እጅግ ከባድ ናቸው እና ብዙ ውይይት ያስፈልጋቸዋል። ይህን ትቶ ስለ ደብዳቤ እና ግልባጭ ማውራት ትንሽ priority ማጣት ይመስለኛል።

ክርስቲያን ታደለን ተውት፤ የመጠላለፍ ፖለቲካ ባህልን ካላቆምን ሁላችንም አብረን እንጠፋለን!

ሰሞኑን የአብን አመራር የሆነው ክርስቲያን ታደለ የህአዴግ አባል ስለነበር ስሙን ለማጥፋት የሚሯሯጡ የ«አንድነት» ደጋፊዎች አይተናል። እጅግ ያሳዝናል። አሁን ሀገራችን ባለችበት ከባድ የፖለቲካዊ እና ማህበራው ችግር፤ የግብረ ገብ እና ስነ መግባር እጦት፤ አሁን ባለንበት አደገኛ ጊዜ እንዲህ ያነት ርካሽ እና ጎጂ የፖለቲካ ሽኩቻ ሀገራችንን ወደ ማጥፋት ይመራናል።

እረ ከታሪካችን እንማር! የጃንሆይን መግስት የጣሉ ከራሳቸው መንግስት ያሉት አብረው ተስማምተው መስራት ባለመቻላቸው ነው። ደርግ እና ህወሓት በስልጣን ላይ ቆይተው ሀገሪቷን ማተራመስ የቻሉት አንድ አቋም ያላቸው ተቃዋሚዎች አብረው በስነ ስርአት መስራት ባለመቻላቸው ነው። እንደ ቅንጅት አይነት ተስፋ የነበረው ድርጅት/መንገስ የጠፋው አብሮ መስራትን እንደ ሽንፈት ስላየነው ነው። አብሮ ሰርቶ፤ win-win ሁኔታዎች ላይ አተኩሮ፤ long term ጥቅማችን ላይ አቶኩረን ከመስራት ፋንታ በርካሽ እና ጠቃሚ ያልሆነ ግብ-ግብ ላይ ተደምደን ሀገርን ለማፍረስ ሰራን!

ኢትዮጵያ አሜሪካ አይደለችም! እንደነሱ ርካሽ ፖለቲካ ጸቦችን አሽከርክረን ከምርጫ በኋላ የምንስማማበት ሁኔታ የለንም። አሁን ሀገር ግንባታ ላይ ነን እንጂ የአሜሪካ ምርጫ ላይ አይደለንም። ሀገር ግንባታ ርካሽ ሳይሆን ውድ እና ዘላቂ አቋም፤ ግንኙነት እና ግንባታ ነው የሚያስፈልገው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/02/blog-post_20.html)።

ክርስቲያን ታደለ እንደ ሁላችንም ስህተቶች አድርጓል። ምናልባት ከኢህአዴግ መስራቱ ጠቅሞም ይሆናል (እንደነ ቲም ለማ እና ሌሎች በርካቶች)። አልፎ ተርፎ ክርስቲያን ታደለ ልጅ ነበር አሁንም ነው። «በአንድ ወቅት ክርስቲያን ታደለ የኢህአዴግ አባል ነበር አሁን ግን አቋሙን ቀይሯል» ማለት ተገቢ ነው። የክርስቲያን የሚያራምደውን አስተሳሰብ በሚገባው መግጠም እና መሟገት ተገቢ ነው። ጨዋ እና በቂ አካሄድ ነው። ግን ከዛ አልፎ መሳደብ ነውርነት፤ ርካሽነት እና ግብዝነት ነው። ርህራሄ ማጣት ነው። እነዚህን የሀገራችን ፖለቲካ ለዓመታት እያተራመሱት ያሉት ባህሪዎችን የሚያንጸባርቅ አካሄድ ነው። ዛሬውኑ ይቁም (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_31.html)!

አሁን በሀገራችን የጎሰኝነት ችግር አለ። የህወሓት እና ሌሎች ነባሮች የሽብር ችግር አለን። የገብረ ገብ እጦት አለን። የመተማመን፤ አርቆ ማየት፤ የራስን የሩቅ ጥቅም መገንዘብ፤ የመራራት፤ የመተባበር ወዘተ ታላቅ እጦት አለን። Emergency ላይ ነን። ታሪካችንን አንድገም። ነውርነትን አቁመን ከጠ/ሚ ዓቢይ ተምረን አውንታዊ መንገድ እንያዝ ብሄ እለምናለሁ።

Thursday 10 January 2019

በምሁራችን ተስፋ እንቁረጥ?

እስቲ ይህን የምጸሃፍ ትችት ያንብቡ፡ https://www.ethiopiaobserver.com/2019/01/06/book-review-overcoming-agricultural-and-food-crises-in-ethiopia/

የመጸሃፉ ጸሃፊ የኢትዮጵያ የእርሻ ምርት ችግር የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ነው ይላል? ምሁራኖቻችን ከዚህ የፈረንጅ ማርክሲስት የ60 ዓመት በፊት አስተሳሰብ መውጣት አቅቷቸዋልን? ያሳዝናል።

ለ40 ዓመታት ኢትዮጵያ የተመራቸው በዚህ አይነት አስተሳሰብ ነው። የእርሻ ምርታችን እንደወረደ ነው። ታድያ አሁንም ምክንያቱ ቤተ ክርስቲያን ነው? እስቲ ምሁራን ትንሽ indoctrinate ካደረጋችሁ መጸሃፍት ውጡ እና imaginative ሁኑ። ምናልባት ወደ ወጋችን ብትመለሱ እና እሴቶቻችንን ብትመለከቱ መናባችሁ መስራት ይጀምር ይሆናል።

እስቲ ገበሬዎቻችንን እግዚአብሔር የሰጣቸውን ነጻነት እንስጣቸው። ከ43 ዓመት በፊት የነጠቅናቸውን መሬት እንመልስላቸው። ባለቤት እናንተ ናችሁ እንበል። ከዛ እንተዋቸው ድጋር ካስፈለጋቸው እንርዳቸው። እርስ በርስ መሻሻጥ ከፈለጉ ያድርጉት። ህበረቶች መፍጠፍ ከፈለጉ ያድርጉ። መንግስት/ወረዳ/ቀበሌ ጉዳያቸውስጥ አይግባ። እስቲ በዚህ እንጀምር።

ገቤሮዎቻችን የባህል እስረኞች አይደሉም። ለ43 ዓመት የመንግስት የማርክሲዝም የሞደርኒዝም እስረኞች ሆነው ቆይተዋል። በራሳቸው መሬት እና ክህሎት ኢንቬስት እንዳያደርጉ ተደርግዋል። ምሁራኖቻችን በትዕቢት የራሳቸውን ፍላጎት ጭነውባቸዋል። ከዛ ደግሞ ባህላቸውን እና ወጋቸውን ይተቻሉ! ህም።

ግብዝነት ያጠፋል

"Correct faith does not benefit anything, when life is corrupted."

St. John Chrysostom

ከቤተ ክርስቲያን ሰው ካፈነገጠ፤ እምነት ካጣ፤ ከብርሃን ወደ ጭለማ ከገባ፤ ለነዚህ ሁሉ ዋና ምክንያት የኛ የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን እና አመራር ግብዝነት ነው። ቤተ ክርስቲያን ባለእንጀራህን ክርስቶስ እንደሚወዳችሁ ውደዱ ብላ ታስተምራለች። እኛ ግን በተለያየ ደረጃ ይህን እውነታዊ ትዕዛዝ አንፈጽምም። «ግብዞች» ነን። ይህን ባለማድረጋችን ወንድም እህቶቻችን ቤተ ክርስቲያንን እንዳያምኑ እና ወደ ፈተና እንዲገቡ እናረጋለን። ለዚህም ነው ክርስቶስ ግብዝነትን ለይቶ የወቀሰው። ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። ግን ግብዝነታችን በበዛ ቁጥር እራሳንን (ቤተ ክርስቲያንን) እጅግ እየጎዳን እንሄዳለን ሰውንም እናሳስታለን። (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2017/11/blog-post.html)

ይህንን ትምሕርት ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ የራስ ማጽዳት ዘመቻውን አጠንክሮ እና እንደ ዋናው እና መጀመርያ ስራቸው ይያዙት ብዬ በአቅሜ እለምናለሁ። ዛሬ ሚሊዮኖች አማኝ ናቸው። ቤተ ክርስቲያኖች ይገነባሉ። ነገ በግብዝነታችን ምክንያት ሁሉም ሌጠፋ ይችላል። ይህ እንዳይሆን እራሳችንን እናጽዳ።

እስቲ ግብዝነትን በሌላ ምሳሌ እንመልከተው… በሀገራችን መሃበረሰብ ማመንዘርም ማስገደድ/መስረቅም ኃጢአት እና ነውር ነው። ሆኖም የሃገራችን ሴቶች በተለይ ከተማ ዙርያ አንዳንድ ወንዶች ሲያመነዝሩ፤ ከኛ ጋር ካልወታሽ መስርያቤቱ እንዳይቀጥርሽ አደርጋለው ሲሉ፤ ሚስቶቻቸውን ሲደበድቡ ወዘተ ይሰማሉ ወይንም ያያሉ። ይህ ሁሉ በባህላችን በወጋችን ክፉ የሚባሉ ነገሮች ሆነው ግን ይከሰታሉ። ይህን እያየች ያደገች ሴት በቀለም ትምሕርት ገፍታ ሄዳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አንዱ የ«ፌሚኒዝም» ፍልስፍናን አቅፋ ጣኦት ታደርጋለች። ለምን በዚህ ታምኛለሽ ካልናት ባህላችን በጅምላ ጭፍጭፍ ታደርጋለች። ለምን? ግብዝ የሆነ የራሱን እሴቶች የማያከብር ህብረተሰብ መካከል ስላደገች። ልክ ያንን «ተቃራኒ» ስታገኝ ሮጣ አቀፈችው።

አያችሁ የግብዝነት ጉዳት። እንታገለው። ወደ ማንነታችን ወደ እውነት የሆኑት እሴታችን እንመለስ። አለበለዛ ሀገራችንንም ማንነታችንንም እናጣለን።

አቶ አበረ አዳሙን አዳምጡት!


https://www.youtube.com/watch?v=43jAqrS4F_g

«(አብዛኛው ያየኋቸው የሀገራችን ፖለቲከኞች) የሚናገሯቸው እና የሚያስተላለፉት መልእክቶች ተመሳሳይ ሆነው ከአንድ መጸሃፍ የተቀዱ ሆነው ግን ደግሞ ምን እንደሚአላያቸው በማይገባህ መንገድ እርስ በርሳቸው ሲለያዩ ታያለህ።»

«ከነ አቢይ ቡድን (ቲም ለማ) በቀር የኢትዮጵያን ተጭባጭ ሁኔታ እና ታሪካዊ እሴቶቿን የተረዳ ያለ (ፖለቲከኛ) ያለ አይመስለኝም።»

Friday 4 January 2019

የአብን መሪዎች ትምክሕተኛ ናቸው!

https://www.facebook.com/seyoum.teshome/videos/1916214778447833/

ሙሉውን ቃለ ምልልስ አላየሁትም ግን… የአብን መሪዎች ክርስቲያን ታደለ እና በለጠ ሞላ ትምክተኛ ነን ሲሉ ይታያል። እስቲ ከዚህ ጥርውን ወገን ልውሰድ…

ባለፉት ረዥም ረዥም ዓመታት የጎሳ ብሄርተኞች አማራ ወይንም «የአማራ ግዥ መደብ» ዋና ጨቋኝ ነው ብለው ሲሰብኩ አብሮ ቋንቋችንን መርዘዋል። «አድሃሪ»፤ «ነፍጠኛ»፤ «ትምክሕርተኛ»፤ «ጠባብ» የሚሉትን ቃላቶች ለአሉታዊ እና ሃሰተኛ ትርክት ተጠቅመዋል። የ«ጨቋኝ ተጨቋኝ» ትርክትን ሽጠውልናል።

የትርክቱን ሃሰትነት ለማስረገጥ እግረ መንገዳችን እነዚህ ቃላቶችን መልሰን ማዳን አለብን። ማሸማቀቅያ እንዲሆኑ መፍቀድ የለብንም። አንዳንድ አማራዎች በተለይም ወደ አብን የሚሳቡት ለረዥም ዓመታት እነዚህን ስድቦች ሲሰሙ ስሜታቸው እጅግ ተነክቷል። የበታችነት እንዲሰማቸው ተደርጓል። ለዚህም ነው አዎ በአማራነቴ እመካለሁ የሚሉት። አላፍርበትም ነው። ካሁን ወድያ ይህ ቃል ኃይል የለውም ነው። ልድገመው፤ ካሁን ወድያ ይህ ቃል ኃይል የለውም ነው።

ይህ ጥሩ ነገር ነው። አብኖች፤ ቀጥሉበት! (ግን የውሃ ልክ አይነት ያልሆነ ነገር ተውው!)

ይህን ሁሉ ስል በአብን የአማራ ብሄርተኝነት እና በበርካታ የሚሪዎቻቸው አቋም ጭራሽ አልሳማማም። ግን ዛሬ እረፍት ልስጣቸው እና ጥሩ ወገኑን ልጥቀስ።

Thursday 3 January 2019

ከብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች ፌደራሊዝም ደጋፊዎች አንዱ የምጋራበት ነገር…

ሁልጊዜ ጥሩውን ነገር መውሰድ ነው… ደካማውን ወገን ትቶ…

የጎሳ አስተዳደር (ፌደራሊዝም) ደጋፊዎች ባህል፤ ቋንቋ እና ሌላ ማንነታችን ለራሳችን ተትቶ እውቅና ይኖረው ይላሉ። የጨርጨር ኦሮሞ የራሱን ማንነት ጠብቆ በሰላም ለመኖር ለዓመታት ታግዷል። የምኒሊክ ጦር 150 ዓመት በፊት መጥቶ አስተአደር እና ባህል ከሌላ ቦታ አምጥቶ የጨርጨር ኦሮሞ ማንነቱን ጠብቆ መኖር አልቻልም ነው። ለኔ ይህ አመለካከት የተወሰነ እውነታ አለው። ለሰው ልጅ የአካባቢ (local) ማንነቱ የተፈጥሮአዊ አስፈላጊነት አለው። የሰው ልጅ በተፈጥሮ ቤተሰብ እና መንደር ያስፈልገዋል። ይህ ተፈጥሮ ነው ብዬ አምናለሁ የሰው ልጅ ታሪክም ይህንን ይመሰክራል። አንዳንድ የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎች ይህን አስተዳደር የምንፈልገው የጎሳ ወይንም ይበልጥ የአካባቢ ማንነቴ እንዳይወረር ነው ሲሉ ይገባኛል። ተገቢ አመለካከት ይመስለኛል።

የማልስማማበት ነገር ግን የአካባቢ ማንነት በህግ ደረጃ የጎሳ ውየን የ«ብሄር ብሄርተሰቦች እና ህዝቦች» ይሁን በሚለው ነው። የምቃወምበት ምክንያቶችም ሁለት ቀላል እና ግልጽ ምክነያቶች ናቸው፤ 1) የአካባቢ ማንነት በጎሳ ከተመሰረተ አግላይ ነው፤ ሰውን በደም እና አጥንት ምክንያት ከአካባቢው በእኩልነት እንዳይቀላቀል ይከልላል እና 2) በጎሳ ከተመሰረተ ግጭት ያመጣል፤ ይህንን ደግሞ በቴኦሪም በ27 ዓመት ታግባር አይተነዋል አሁንም እያየነው ነው።

ስለዚህ እንዴት ነው የጨርጨር ኦሮሞ ባህሉን፤ ቋንቋውን እና የአካባቢ ማንነቱን የሚጠብቀው አስተዳደሩ የጎሳ ካልሆነ? ማለት የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎችን ግብ ለማሳካት እንምራ፤ ግቡን እናሳካ ግን በሌላ መንገድ። የአካባቢ ማንነት እንዲሰፍን እናድርግ ግን አለ ጎሳ አስተዳደር። እንዴት እናድርገው? አንድ ቀላል አማራጭ የዛሬውን ህገ መንግስትን ብዚህ መልኩ መቀየር ነው። «ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች» የሚለውን በዜጋ ይቀየር። የክልል አወቃቀሩ እንዳለ ይሁኑ እንበል። ህገ መንግስቱ ላይ ለክልል ግን እጅግ ይበልጥ ለዞን እና ለወረዳ በርካታ ኃይሎች ይስጥ። ዛሬ ካለው ይልቅ አብዛኛው የመንግስት ኃይል ወደ ዞን እና ወረዳ ይውረድ። ይህ ከተደረገ የአካባቢ ማንነት በዘላቂነት ይጠበቃል።

ለምሳሌ አንድ ዞን አካባቢ አስተዳደር ቋንቋ እና የትምሕርትቤት ቋንቋ የመወሰን መብት ይኑረው። ምናልባትም የመሬት ፖሊሲ መብት ይኑረው። የአስተዳደር ዘዴ መብትም ይኑረው። ወዘተ። ብዙ መብቶች ወደ ታች ወደ ዞን እና ወረዳ መውረድ ይችላል። ይህን በማድረግ አካባቢዎች ኃይል እና ስልጣን እንዲኖራቸው ይደረጋል። መአከላዊ እና ክልላዊ መንግስቶች የራሳቸውን ፍላጎት እና ተጽዕኖ ዞን እና ወረዳዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና ማድረግ ያችልም። የአካባቢ ባህል፤ ቋንቋ እና ማንነት በደምብ ይጠበቃል። መዓከላዊ እና ክልላዊ መንግስቶች እነዚህ ነገሮችን መንካት አይችሉም። የአካባቢ ማንነት autonomy ይጠበቃል።

አንዳንድ የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎች ይህ አሰራር የአከባቢ ማንነትን ሊያስከብር ያችልም ትሉ ይሆናል። በተለያየ መንገድ አዲስ አበባ፤ የምአከላዊ መንግስት፤ የክልል መንግስት ወዘተ በባህልም በሌላም ተጽዖን አድርጎ ማንነቱን ሊቀይር ይችላል ትሉ ይሆናል። ምናልባት። ግን እንዲህ ከሆነ የጎሳ አስተዳደርም ይሄንን ሊከላከል አይችልም! ጨርጨር የአካባቢ ማንነቱን ከክልሉ በጎሳ መልክ የሚቀበል ከሆነ ተቀባይ ነው ዴሞክራሲያዊ አይደለም። ስለዚህ ነጻነት የለውም። ግን ነጻነቱ ቢሰጠው እና በጎሳ ይልቅ በአካባቢ ቢሆን የጨርጨር ኦሮሞ አብዛኛ በመሆኑ አካባቢው በራሱ ባህል ይቀርጸዋል። እዛ የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑትም እኩል ዜጋ ስለሆን ደም እና አጥንታቸው ስለማይቆጠር ይህንን የአካባቢ ማንነት ይደግፉታል እና ይሳተፋሉ። Win-win ሁኔታ ነው።

እስቲ ይህን ሃሳብ አስቡበት። አውቃለሁ የኢትዮጵ ምሁራን የተማሩት በtextbook የምዕራባዊ ፍልስፍና ነውና ስለ localism፤ communitarianism ወዘተ ብዙ አስበንም ገብቶንም አናውቅም። የጎሳ መብት እንላለን ግን አሁንም ከላይ ወደ ታች መጫን ነው ፍላጎታችን። ሌላ አስተሳሰብ ግን ዞሮ ዞሮ ከላይ ወደታች። ግን እስቲ ለአካባቢዎች እውነተኛ ነጻነት እንስጣቸው። ማንም እንዳይጎዳ የዜግነት መንብት እንዲሰፍን አድርገን ግን በርካታ መብቶች ወደ ታች እናውርድ። ይህ ሃሳብ የጎሳ አስተአደር እና የዜግነት አስተዳደር ደጋፊዎችን የሚያስማማ ይመስለኛል።

(ለስህተቶች ይቅርታ በችኮላ ነው የጻፍኩት!)

አንዳንድ ሃሳቦች፤ የአንድነት አና የአማራ ብሄርተኝነት ፖለቲካ

ከአብርሃም ጮራ ገንቢ ጽሁፍ (https://www.facebook.com/abrham.tibebu/posts/10155875239026471) ተከትሎ አንዳንድ ሃሳቦች፤

1. የአንድነት አቋም እና ድርጅት/ደጋፊ/ሰው እንለይ። አቋም እና ሰው እንለይ። እንደማንኛውም ፍሬያማ ውይይት ሃሳብ እና ሰውን መለየት ያስፈልጋል። ይህ ባለመሆኑ አንዳንድ ሰዎች እንደ ግንቦት 7 አይነቱን የማይወዱትን የ«አንድነት ኃይል» ለመኮነን የአንድነት ጽንሰ ሃሳቡንም ይኮንናሉ። እንደሚገባኝ አብን (ለምሳሌ) ሁለት ግብ ነው ያለው፤ 1) የአማራ ህዝብ መብትን ለማስከበር 2) ኢትዮጵያ ዙርያ የጎሳ አስተዳደር የንዲፈርስ እና የዜግነት ፖለቲካ እንዲሰፍን። ስለዚህ አብን በ«አንድነት» ያምናል። ግን አንዳንድ የአብን ደጋፊዎች ግንቦት 7ን ወይንም ሌሎች የማይወዱትን ለመኮነን እራሳቸው የሚያምኑበት የአንድነት ወይንም የዜግነት ፖልቲካን ይኮንናሉ!

2. ሃላፊነት እንውስድ፤ ሁላችንም የአማራ ብሄርተኞችም (ሁሉ አይነት የአማራ ብሄርተኞች) የተወሰነ ዓመታት በፊት የአንድነት ኃይሉ አካል ነበርን። ለምሳሌ የቅንጅት ደጋፊ ነበርን። ወይንም የመኢአድ ደጋፊ፤ ወይንም እድሜአችን ጠና ከሆነ የኢዲዩ ደጋፊ። ወዘተ። ስለዚህ የአንድነት አስተሳሰብንም የአንድነት ድርጅቶችንም እንደ ባይተዋር አንመልከታቸው። እራሳችን ከነሱ ነበርን/ነን።

3. የምዕራባዊያን/ማርክሲስት/ወዘተ ጨቋኝ ተጨቁኝ ውየንን us vs them ሃሰተኛ ትርክት እናቁም! አሁን ያለው የሃሳብ ግጭት ነው። ለምሳሌ፤ የ«አንድነት ኃይሉም» «አማራ ብሄርተኛውም» በአንድነት/ዜግነት ፖለቲካ ያምናል። ያሁኑ ህገ መንግስት ፈርሶ ጎሳ/ዘር የሌለበት ሀገ መንግስት መኖር አለበት ያልሉ ሁለቱም አንድነቶቹም አማራ ብሄርተኞችም። ታድያ ልዩነቱ ምንድነው? የስልት (strategy) ምናልባትም የታክቲክ ነው። አንድ አቋም እያለን በአካሄድ ከሆነ ልዩነታችን መቦጫጨቁ ሁለታችንንም እንደሚጎዳ ግልጽ ነው። ታሪክ መድገም ነው የሚሆነው።

4. ልጅ የሆኑት የአማራ ብሄርተኞች እኛ የ60ዎቹ ተቃራኒ ነን ይላሉ። ግን ይህ us vs them dialectical ትርክት የ60ዎቹ መሰረታዊ አካዬድ ነው!! ከሃሳብ ይልቅ ሰው/ቡደን ላይ ማተኮር ይ60ዎቹ አካሄድ ነው። በስልታዊ ልዩነት መፋጀት የ60ዎቹ «ሌጋሲ» ነው። ፌው ከዛፉ ርቆ አይወድቅም። የአባቶቻን ስህተት አንድገም። የ60ዎቹ የ«ጠላት/ወዳጅ» ፖለቲካ የተጠቀሙት በቀላሉ ተከታዮች በስሜት ለማሰባሰብ ነው፤ እንደ ህወሓት ማለት ነው። ለዚህ ግብ ይህ ጠላት/ወዳጅ ትርክት ማንዴላ እንዳለው ጥይት/መድፍ ነው። ስልጣን ያመጣል ግን ሀገር ያፈርሳል።

5. Counterforce ጥሩ ይመስላል ግን አይሰራም። ነገ አማራ ተደራጅቶ ከነ ህወሓት እጥፍ ድርብ ጠንካራ ሆነ hard እና soft powerኡን በገንዘብ፤ በinfluence፤ በኔትዎርክ ወዘተ ሌሎች ክልሎች ላይ ጫና መፍጠር ይችላል ነው የcounterforce ሃሳብ። ይህን ለማድረግ መሃሉን መያዝ (capture the centre) አለበት ልክ ህወሓት እንዳደረገው። በዛሬ ነባራዊ ሁኔታ አማራም ሌላም የጎሳ ብሄርተኝነት ይህን ማድረግ እንደማይችል መቼም ለሁሉም ግልጽ ይሆናል ብሄ እገምታለሁ። ሌሎች ጎሳዎች ምንም ያህል ከአማራው ደካማ ቢሆኑም ይህን አይፈቅዱም። ሁከት እና ሽብር ይሻላቸዋል። አማራው ይበልጥ ለአማራ ብቻ በቆመ ቁጥር እነሱም ወደ ራሳቸው ይሸገሸጋሉ። ጠንካራ የአማራ ብሄርተኝነት የአማራ ክልልን ልዋላዊነት ያስከብራል ብዬ አምናለሁ። ግን ከሌሎች ጎሳ ድርጅቶች ጋር መስማማት አይችልም።

6. ህወሓት ከሌሎች ጎሳዎች ጋር መተባበር የቻለው ለምን አማራ ብሄርተኛው አይችልም ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ህወሓት መቼ ቻለ! ለጊዜው (27 ዓመት) አማራን ጥላት በማድረግ ጎሰኝነትን በማስፈን ከጎሰኞች ጋር ህብረት ፈጠረ። በሌላው በኩል ጸንፈኛ ጎሰኞች እንዳይመጡብህ እጠብቅሃለው ብሎ ሌላውን በፍርሃት ያዜ። ግን ሁሉም አሻጥር የማይሆን ከጥላቻ ወይንም ከአሉታዊነት ውጭ የሌላው መሰረት ነበር። ዛሬ ጠንካራ አማራ ብሄርተኛው ይህን ላድርግ ቢል ማን እንደሚተባበረው አይታየኝም።

7. በአጭሩ ጠንካራ አብን (የዛሬው ሳይሆን እንደሚፈልገው ስራውን ሰርቶ የጠነከረ እና የአማራ ክልል ሙሉ ድጋፍ ያለው) ከሌሎች የጎሳ ድርጅቶች ጋር መወየየት አይችልም። የጎሳ ስብስብ ተወያይቶ መስማማት አይችልም። ሁልጊዜ ወደ ግጭት ያመራል። ምርጫው ሀገሪቷን መከፋፈል ነው የሚሆነው። ይህም በብዙ ደም ነው የሚካሄደው ብየቦታው minorityዎች ወደ «ቦታቸው» መመለስ ስለሚኖርባቸው።

8. በህብረ ጎሳዊ ሀገር force/counterforce በጎሳዎች መካከል ቀውስን ነው የሚያመጣው። ስንሰ ሃሳቡን ትተን empirically በኢትዮጵያም አይተነዋል እያየነው ነው። በህበረ ጎሳዊ ሀገር ታላቁ force/counterforce በመሃሉ እና በጎሳዎቹ መካከል ያለው ነው። መሃሉ በጠነከረ ቁጥር ሰላም እየሰፈነ ይመጣል ጎሳዎችን አለፍላጎታቸው ካልጨፈለቀ ድርስ። ጎሳዎቹ እየጠነከሩ መሃሉ በላላ ቅጥር ጎሳዎቹ እርስ በርስ ያላቸው ልዩነት እየከረረ ይሄዳል ማለት ነው። ልዩነታቸው ጨመረ አንድነታቸው ቀነሰ። ይህ የግጭት መንስኤ ነው። አንዱ ጎሳ ከሌላው ምንም ያህል ቢጠነክር በኃይል ይሁን በድርድር ሰላምን ሊያመጣ አይችልም።

9. ስለዚህ አብን ለሌሎች ጎሰኞች counterforce መሆን ለግቤ ይጠቅማል ብሎ ማሰብ የለበትም። ለኔ ዋናው የአብን ስትራቴጂካል ጥቅም (ሌሎች ቢኖሩም) የአማራ ክልልን ከህወሓት ናፋቂዎች፤ ክሙስና፤ ከሞራል ዝቅተት ወዘተ ለማዳን መስራት ነው። ያለውን የአማራ ብሄርተኝነት ስሜትን ወደዚህ አይነት አውንታዊ አቅጣጫ ማሰማራት ነው። አማራ ክልልን rehabilitate ማድረግ ነው።

10. እንጂ አብን የአማራ ብሄርተኝነትን አስፋፍቼ የአንድነት ፖለቲካን አጥፍቼ እንደገነ ገነባለሁ ከሆነ ለአማራ ህዝብም ለሁሉም ቀውስ ነው የሚያመጣው።

11. የአማራ ብሄርተኝነትን እንደ መሳርያ ተጠቅሜ በኋላ ተወዋለሁ ማለትም አይቻልም! አንዴ የፖለቲካ ውጤት ካመጣ ማንም ፖለቲከኛ አይተወውም። «ሱስ ይሆናል»! ይህ መቼም የታወቀ የፖለቲካ ሃቅ ነው።

12. የአንድነት ፖለቲካ መሰረታዊ ችግሩ የመጠላለፍ ፖለቲካ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html) ነበር አሁንም ነው። በጃንሆይ ዘመንም መንግስታቸው ውስጥ የነበረው የእርስ በርስ ሹኩቻ ነው መንግስታቸውን አድክሞ ለውጦች አንዳያደርግ እና እንዲፈርስ ያደረገው። የተማሪ ንቅናቄውንም የፈጠረው። ከዛ ኢዲዩ፤ መድህን፤ ግራኞቹ (ኢህአፓ፤ መኢሶን፤ ወዘተ)፤ መኢአድ፤ ቅንጅት ወዘተ ቁም ነገር ላይ መድረስ ያልቻሉት በመጠላለፍ ፖለቲካ ባህል ምክንያት ነው በመሰረቱ። ይህ ችግር ግን የአንድነት ወይንም የዜግነት ፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ሳይሆን የፖለቲካ ባህል ችግር ነው።

13. በሁለተኛ ደረጃ ነው የነ ቅንጅት ችግር የ«ነፍጠኛ ነህ» ክስ። ይህን ክስ ለማስቆም እና ከራሱ የጎሳ መጨፍለቅ ሃሳብ ለማውጣት ብሎ ነው የአንድነት ፖለቲካው አማራ ያልሆኑትን በተጨማሪ ማቀፍ የፈለገው። ለመድገም ያህል ሁለት ምክንያት፤ 1) አማራ ብቻ ነህ እናይባል እና 2) ኢትዮጵያ multicultural መሆን የለባትም የሚሉትን ከማህሉ ለማውጣት። ግን ይህን በማድረግ፤ ለምሳሌ መድረክን በመፍጠር፤ የአንድነት ኃይሉ የተወሰን መሻሻል ቢያሳይም መጠንከር አልቻለም። ለምን፤ ከላይ ያልኩት መሰረታዊው የመጠላለፍ ፖለቲካ ባህል ስላለቀቀው። ያበደምብ address አልተደረገም።

14. ታድያ ለምንድነው እነ አብን፤ ህወሓት እና ሌሎች የጎሳ ፓርቲዎች ይህ የመጠላለፍ ፖለቲካ ባህል የማያጠቃቸው? ያው ጎሰኝነት ስሜታዊ አንድነት ስለሚያመጣ ትብብርን ይጨምራል፤ የታወቀ ነገር ነው። የጎሰኝነትን ግን ትክክለኛ ጽንሰ ሃሳብ አያደርገውም!! የጎሳ ፖለቲካ ድርጅት በ mobilization ዋና ቢሆንም ለጭኮና እና ግጭትም ዋና ነው። ህወሓት መጀመርያ የማይስማሙትን ትግሬዎች አጠፋ። በኃይለ ጎሳ ትግራይን ተቆጣጠረ ጠላት አለህ ብሎ እይሰበከ። ስለዚህ ጎሰኝነት ለፖለቲከኞች attractive ቢሆንም መጨረሻ ላይ ግጭት ነው የሚያመጣው። ስለዚህ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አንድነት ኃይሎች ባይደነባበሩም ጥሩ አያደርጋቸውም። የአንድነት/ዜግነት ፖለቲካ ከባድ ቢሆንም ለሰላም ግዴታ ነው። ለዚህም ነው አብን የዜግነት ህገ መንግስት እንደ ግብ ያስቀመጠው።

ቃለ ሕይወት ያሰማለን

ቆንጆ ትምህርት ከሩሲያዊ ቄስ አንድሬይ ካችዬቭ፤

https://russian-faith.com/explaining-orthodoxy/how-god-will-judge-those-who-dont-know-christ-n1980

Tuesday 1 January 2019

የአማራ «ልሂቃን» እና የአማራ ህዝብ ቅነሳ

ማንም በማይክድበት ደረጃ በአማራ ክልል የተካሄደው የወሊድ ቅጥጥር (በተዘዋዋሪ የህዝብ ቁጥር ቅነሳ) ዘመቻ ከሁሉም ክልል በላይ በደምብ «ተሳክቷል»። ማለት የህዝብ ቁጥር ጭማሬ በደምብ እንዲቀንስ አድርጓል።

ይህ ለኔ እጅግ የሚያሳዝን ክስተት ነው። የአማራ ክልላዊ መንግስት በአማራ ልሂቃን ተደግፎ ያልተሟላ እና ኋላ ቀር የህዝብ ብዛት መጥፎ ነው የሚል ፍልስፍና ተሸክሞ የአማራ ክልልን ህዝባዊ አቅምን መንምኖታል። ህዝቡም በመርፌ የሚወገ የወሊድ መቆጣጠርያ መድሃኔት በmarketing እና coercion ኃይል እንዲጠቀም በማድረግ ከባህሉ፤ ከጤንነቱ እና ከራሱ (ከህሊናው) ጋር እንዲጣላ አድርጓል። ሌሎቹ ክልሎች ይህንን መርዛማ አካሄድ ላለመከተል ሲታገሉ የአማራ መንግስት እና ልሂቃን አዋቂ እና ተምረናል ባዮች ሙሉ በሙሉ capitulate አደረጉ። እውነትም «የተማረ ገደለን» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/12/blog-post_7.html)።

ዛሬ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር የህዝብ ብዛት አይደለም። ከመሰረታዊ ችግሮች መካከል የመሬት ፖሊሲው (መሬት የመንግስት መሆኑ) እንደ ችግር ይበልጠዋል። የህዝብ ብዛት እንዲህ እንዲጨምር ያደረገው ገበሬው መሬቱን ሽጦ ወደ ከተማ መምጣት ስለማይችል የኢትዮጵያ ህዝብ ለ40 ዓመታት artificially ገጠር እንዲቆይ ተደርጓል። ገበሬው በነጻነት መሬት መሸጥ መለወት ቢችል ኖሮ ዛሬ 80-85% የገጠር ነዋሪ ከሚሆን ወደ 60% ደርሰን ይሆን ነበር። የገጠር ህዝብ ስድስት ልጅ ይወልዳል የአዲስ አበባ ህዝብ ሁለት ልጅ ይወልዳል። 40% የከተማ ነዋሪ ሆኖ ከስድስት ፋንታ ሁለት ልጅ በአማካኝ ሲወልድ የህዝብ ቁጥራችን እንዲህ አይጨምርም ነበር። ስለዚህ ልክ እንደ ቻይና በማኦ ዘመን የመሬት ፖሊሲው ነው የዝብ ቁጥራችንን artificially እንዲንር ያደረገው። አሁን ታድያ መሰረታዊ ችግሩን አምኖ ለመቅረፍ ከመሞከር symptomኡን ለማከም እንሞክራለን። ይህ ታላቅ ጥፋት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ አንድ ህዝብ የሚወልደውን ልጅ መጠን እራሱ የራሱን ጥቅም አይቶ በholistic እና organic መንገድ ቢቆጣጠር ነው የሚሻለው (በስነ ልቦና እና ማህበራዊ ሰላም ደረጃ)። ከተሜ ሲሆን፤ ቆይቶ ሲያገባ፤ ወዘተ እራሱ አስቦ መወሰን ይጀምራል። በመንግስት እና ኤንጂኦ ኃይል በግፊት እና ጫና በቅኝ ግዛት መልክ ከተመጣበት ችግሩን በደምብ ሳያውቀው ወደ አደገኛ የወሊድ ቁጥጥር ይገባበታል። ከዛ ዛሬ የምናየው backlash ይመጣል። ሴቶች መውለድ አቃተን ይላሉ። ልጆች ጠፉ ይባላል። ወዘተ። የብአድ መፍትሄ ብዙ ጊዜ መፍትሄ አይደለም።

ሶስተኛ፤ መላ ኢትዮጵያም አማራም ለህዝብ ቁጥር እድገት በቂ ቦታ አላት። አልተጨነቀችም። ሌሎች የመንግስት ፖሊሲዎች ናቸው ችግሮቹ። አልፎ ተርፎ አንዱ ላለፉት አመታት የኤኮኖሚ እድገት ያመጣው ግበአት የህዝብ ብዛት ነው። የ100 ሚሊዮን ገበያ እና ሰራተኛ ኃይል ቀላል አይደለም። ጥቅም አለው። ይህ በአማራ ክልል እና ልሂቃን የታሰበበት አይመስለኝም። ውሳኔዎችን በ one track mind ሆነው ነው የወሰኑት።

አራተኛ፤ በዛሬው የጎሳ ችግር ሁኔታ ዴሞግራፊ ወሳኝ ነገር ነው። የአማራ ክልል ህዝብ ቁጥር ቀነሰ ማለት በአንድነት የሚያምነው ህዝብ ቁጥር ቀነሳ ማለት ነው (አማራው ከሞላ ጎደል እንዳለ ከአንድነት ኃይሉ ውስጥ ስለሆነ)። ዛሬ ይህን ሃቅ መካድ አይጠቅምም። ይህ ፖለቲካዊን ይቀይራል። መሃሉን ያደክማል ጎሰኝነትን የሚያራምድ ፖለቲካን ያጠነክራል። ፖለቲካው ይዛባል። የአማራ ክልል መንግስት እና ልሂቃን ይህን እንደ አንድ ግበአት አለማሰባቸው እጅግ ያሳፍራል። ወይ ክፋት ወይንም ጅልነት ነው፤ ይቅርታ አድርጉልኝ። ነባራዊ እውነታን አለመቀበል ነው። ለጎሳ ፖለቲካ ተብሎ የህዝብ ቁጥር እንዲንር ይደረግ ማለቴ እንዳልሆነ መችሄስ ግልጽ ይመስለኛል። ግን ሁሉ ነገር መታየት አለበት እና ሚዛናዊው መንገድ መከተል አለብን ነው የምለው።

መፍትሄው ምንድነው? የወሊድ መቆጣጠርይ ይከልከል ወዘተ አይነት የማይሆን ነገር አደለም የምለው፤ ከአንዱ ጸንፍ ወደ ሌላው! መንግስት ለወሊድ መቆጣጠርያ marketing እና እርዳታ ይተው ነው የምለው። በዚህ ዘርፍ የሚሰሩ ኤንጂኦዎች ይከልከሉ። የታወቁ ጉዳታቸው ያነሰ የወሊድ መቆጣጠርያ መንገዶች ይሸጡ ግን ህዝቡ ላይ አይጫኑ። ህዝቡ አለ ጫና እና ግፊት በorganic እና holistic መንገድ የራሱን ግላዊ ውሳኔ ያድረግ። አለ ጫና እና ግፊት። ይህ መፍትሄ ሁለት ግቦች ይኖሩታል፤ 1) የህዝቡ ስነ ልቦና እና የማህበረሰቡ ስነ ልቦና ይገጋጋል እና ይጠበቃል እና 2)  የህዝብ ቁጥር ጭማሬ ከፍ ይላል፤ ወደ naturally መሆን ያለበት ደረጃዎች ይሄዳል እና ከሌሎች ክልሎች ብዙ አያንስም። በአጭሩ የክልሉ ፖሊሲ ከጫፍ ወደ ሚዛን ይመለሳል ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/04/blog-post_6.html)።