Friday 22 February 2019

የጅልነት ፖለቲካ

አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት በተለያየ መንገድ ፍላጎታቸውን በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ መጫን እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። አቋም ከመውሰድ እና ከመናገር አልፎ በተግባር ስራቸውን ሰርተዋል። የአዲስ አበባ «ወጣቶችን» በጅምላ አስረዋል። አዲስ አበባን እናደራጅ ያሉትን አስረው አስፈራርተዋል። ከለገጣፎ አፈናቅለዋል። ወዘተ። እንዲህ በማድረግ አክራሪው ቡድን አቅታጫውን በግልጽ አስቀምቷል። የማስፈራራት ዘመቻውን ቀጥሏል።

ለነገሩ ይህ (ይቅርታ አድርጉልኝ) የጅልነት ፖለቲካ አካሄድ ነው። የሚበጃቸው የነበረው የአዲስ አበባ ህዝብን ሳያስቀይሙ ሳይነሳሱ ቀስ ብለው ውስጥ ለውስት ስራቸውን መስራት ነበር። ግን የጡንቻ አካሄድ መርጠው የአዲስ አበባ ህዝብን ያናድዳሉ እና ተነስቶ እንዲደራጀና መብቱን እንዲያስከበር ያደርጉታል።

ይህ ነው የጅልነት ፖለቲካ። ግን ምና ያመጣሉ ነው ይህን የሚያደርጉት! የአዲስ አበባ ህዝብ እና ጠቅላላ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራው ምን ያመጣል ነው። ስለዚህ ማን ነው ጅሉ። እኛ ነን።

የለገጣፎ «ህገ ወጥነት» የማን ነው?

ሰዎች ከለገጣፎ ገበሬዎች ጋር የውስጥ ውል ተፈራርመው መሬት ገዙ። የእርሻ መሬት መሸጥም መግዛትም ስለማይፈቀድ ይህ ሺያጭ ህገ ወጥ ነበር። ሆኖም ተካሄዷል።

እነዚህ አይነት ሺያጮች ሲካሄዱ የአካባቢው የኦህዴድ (ኦዴፓ) ሹማምንቶች መጀመርያ እንዳላዩ ሆኑ። ቀጥሎ የምዝበራ እድል አይተው ገቡበት። ከገበሬ እየገዙ አትርፈው መሸጥ ጀመሩ። ከገበሬዎች ገዝተው ቤት የሰሩትን ሰዎች ጉቦ ካልሰጣችሁን እናባርራችኋለን፤ መብራት ውሃ እንከለክላችኋለን ወዘተ እያሉ አስፈራሩ። በዚህ መንገድ እራሳቸውን ሃብታም አደረጉ።

የኦዴፓ ላይ ድርስ ያሉ ባለስልጣናት ይህ አይነት ነገሮች አዲስ አበባ ዙርያ እንደሚካሄድ ያውቃሉ። ለነገሩ ሁላችንም እናውቃለን።

ስለዚህ ማን ነው ህገ ወጥ?! መሬት የገዙት ሰዎች? መሬት የሸጡት ገበሬዎች? የመዘበሩ እና በጉቦ ሃብታም የሆኑት የመንግስት ሹማምንቶች? ይህ እንደሚከሰት እያወቀ ዝም ያለው የኦህዴድ አመራር?

ግልጽ ነው፤ በፈቃደኝነት የተስማሙት ሳጭ እና ገዦች በአንጻሩ ንጹህ ናቸው። ማንንም አልጎዱም። ገበሬዎቹ የራሳቸውን መሬት በፈለጉት ዋጋ ሸጡ፤ ገዦችም በተስማሙበት ዋጋ መሬት ገዙ። ይህ ሺያጭ ባይካሄድ የኦህዴድ ሹማምንቶች የገበሬዎቹን መሬት በማይገባ ትንሽ ካሳ ነጥቀው ለኢንቬስተር በውድ ዋጋ እና ጉቦ ሊዝ ያረጉት ነበር።

እነዚህ የኦህዴድ ሹማምንት እና መሪዎች ናቸው ዋና ህግ ወጦች። አዲሱ አረጋ እንዳሉት «ህግ ይከበር» ከሆነ በመጀመርያ ደረጃ የኦህዴድ ሹማምንቶች ነበር መፈተሽ እና መታሰር የነበረባቸው። ሌሎቹ፤ ገንዘብ የተቀበሉት ገበሬዎቹ እና መሬት የገዙት ሰፋሪዎቹ በለዘብተኛ መልኩ መስተናገድ ነበረባቸው።

ለገጣፎ ለሚከሰተው የአዲስ አበባ ህዝብ ሃላፊነት አለብን

ደርግ የ«ከበርቴን» ቤተና ንብረት ሲቀማ በምቀኝነት ተሞልተን አጨበጨብን። እርግጥ ነው አንዳንዱ አላግባብ ብዙ መሬት ይዞ በተከራዮች ይጫወት ነበር። ግን ሌሎች ትንሽ ንብረት የነበራቸው ነበሩ በዚሁ መአበል የተጥለቀለቁ። የሚያከራዩት ሶስት አራት ቤቶች ሲወረሱ ባዶአቸውን ቀሩ። ማንም አላዘነላቸውም። «እንኳን ተነጠቁ» ብለን የጅምላ ፍርድ ላይ ነበርን።

በህወሓት ዘመን ደግሞ ለ«ልማት» እና «ኢንቬስትሜንት» ተብሎ የበርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ንብረት በምንግስት ተነጥቋል። አንዳንዱ ባዶውን ቀረ። አንዳንዱ እጅግ አነስተኛ ካሳ ተሰጥተው። ሌላው ከከተማ ውጭ ባዶ መሬት ላይ ተወረወረ። ይህ ሁሉ ሲከሰት የአዲስ አበባ ህዝብ (በጅምላ ለማውራት) ምንም አላደርገም። እርግጥ መጮህ እና መደራጀት ሊያሳስር እና ሊያስገድል ይችል ነበር። ግን ገንዘብ ሰብስቦ ለተፈናቀሉ ተጎጂዎች መስጠት ምንም ቅጣት አያስቀጥልም ነበር። ከኔ ጀምሮ አንዳችን ይህን አላደረግንም። የባለንጀሮቻችንን ህምም ዝም ብለን ተመለከትን።

ዛሬም እንዲሁ። ለገጣፎ የሚኖሩ ወንድም እህቶቻችን ቤቶቻቸውን እያጡ እያለ ከመጮ ሌላ ምንም አናደርግም። አንረዳቸው፤ አንደራጅ። ትንሽ ጉዳዩ ያናደደን ካለን መንግስት ላይ ጣታችንን እንጠቁማለን!

ከዛ ይልቅ እራሳችን ላይ ነው መፍረድ ያለብን። የአዲስ አበባ ህዝብ ለባለንጀራው በአግባቡ ቢራራ እስካሁን ተደራጅቶ የህ አይነት ግፍ እናይከሰት ማድረግ ይችል ነበር (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2019/02/blog-post_22.html)። ግን አላደረገውም፤ አላደረግነውም።

ስለዚህ ጥፋቱ በዋነኝነት የኛ የአዲስ አበባ ህዝብ ነው። ጣቶቻችንን ሌሎች የማይሰሙን ላይከመጠቆም ስራችንን ሰርተን ተደራጅተን እርስ በርስ ብንጠባበቅ ለሁሉም፤ ለጎጂዎቻችንም ለመላው ሀገራችንም፤ ጠቃሚ ነበር። ለችልተኛችን ንስሃ ገብተን ወደ ስራ እንግባ። ሌላ መፍትሄ የለም!

የአዲስ አበባ ህዝብ ካልተደራጀ ለገጣፎ ይደጋገማል

https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_97.html

የለገጣፎ ነዋሪዎች መፈናቀል ድርጊት በምንም ሚዛን እጅግ አሳፋሪ እና ለሁላችንም ጎጂ መሆኑ ግልጽ ያልሆነለት... ይቅርታ አድርጉልኝ እና የድሮ የፖለቲካ ደንቆሮ ነው።

ሆኖም እንደዚህ አይነት መፈናቀል እና ተመሳሳይ ክስተቶች ለ27 ዓመታት ሲካሄዱ ቆይተዋል። ወደ ኋላ ከሄድንም ደርግ የ«ከበርቴዎችን» ቤት እና መሬት አለ ፍትህ፤ ሚዛን፤ እና ርህራሄ ቀምቷል።

የአዲስ አበባ ህዝብ ይሁን ሁሉ ያትዋል አሳልፏልም። በርካታ ሰለቦች አይተናል። ግን አንዴም ጣታችንን አንስተን እንርዳችሁ፤ ይህ ክስተት እንዳይደገም ተደራጅተን ለእርስ በርሳችን እንቁም ብለን አናቅም። ይሉቅንስ ወይ ተባብረናል፤ አንገታችንን ደፍተናል፤ ወይንም ለተጎጂዎች ከመራራት ፋንታ ፈርደንባቸዋል።

በዚህ ምክንያት አሁንም ባለንጀሮቻችን፤ ጎረቤቶቻችን፤ ወንድም እህቶቻችን እጣ ፈንታቸው ከሆነ መሬት እና ቤቶቻቸውን ይነጠካሉ። ዛሬ ለገጣፎ ነው ነገ ሌላ ቦታ። የኦሮሚያ መንግስት ተወካዮች ይቀጥላል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ህዝብ እንደዚህ አይነት ኢ-ሰባዊ ድርጊቶች እንዲቆሙ ከፈለገ ከመደራጀት በስተቀር ምንም ማድረግ አይችልም። መቾህ፤ ቂም መያዝ፤ ማዘን ወዘተ ብዙ ዋጋ የለውም። አንድ እና አንድ ምርጫ ብቻ ነው ያለው፤ መደራጀት።

ምን ማለት ነው መደራጀት? መቼስ ፖለቲከኞቻችን ሊያውቁ እና ሊያስተምሩን ይገባል ግን እስቲ ለኛ ብዙሃን በምሳሌ መልኩ ልዘርዝረው። ልብ፤ እውቀት፤ እና ገንዘብ ያላቸው «የአዲስ አበባ ዜጎች ድርጅት» የሚባል ያቋቁማሉ። የድርጅቱ ተዕልኮ የአዲስ አበባ ህዝብን ፍላጎትን እና ደህንነትን ለማስከበር መሟገት ይሆናል። ድርጅቱ በየ ቀበሌው፤ በየ ህዝብ ዘርፍ (ነጋዴ፤ ሞያተኛ፤ አስተማሪ፤ እናቶች፤ ወዘተ) አባላት እና ገንዘብ ይመለምላል። ትምሕርት ያስተምራል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ይሰበስባል። እነዚህ አባላት በዬ ህብረተሰብ ክፍል እና መንግስት መስርያቤቶች ያሉ ይሆናሉ እና በይፋም በህቡም ለድርጅቱ እና ለአዲስ አበባ ህዝብ ተጽዕኖ ማድረግ የሚችሉ ይሆናሉ። እንድነ ለገላፍቶ አይነት ክስተት እንደሚካሄድ ሲታወቅ ይህ ድርጅት በሁሉ ዘርፍ ተጽዕኖ ያደርጋል። እንደዚህ አይነት የማፈናቀል እና ሌላ ህዝቡን የሚጎዳ እቅድ እንዳይታሰብ ያደርጋል።

አሁን የደረደርኩት ምሳሌ አዲስ እንዳልሆነ መቼስ ሁላችንም እናውቃለን። ዓለም ዙርያ ለሺ ዓመታት ፖለቲካ በዚህ መልኩ ነው የሚካሄደው። እንኳን የሰላም ፖለቲካ የጦር/ኃይል ፖለቲካም እንዲሁ ተደራጅቶ ነው የሚሰራው። ስለዚህ የአዲስ አበባ ህዝብ ማድረግ ያለበት የተለየ እና በተለየ መልኩ ከባድ ነገር አይደለም። ለአካባቢ ጥቅም መደራጀት ቀላል እና የተለመደ የሰው ልጅ አካሄድ ነው።

ታድያ ለምንድነው የአዲስ አበባ ህዝብ እስካሁን ያላደረገው? በነ ግምት የአዲስ አበባ ህዝብ ይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ (ሀገር) ብሄርተኞች ከ66 አብዮቱ እና ሽብሮቹ እስካሁን አላገገመም። አብዮት ተከታታይ ትውልዶች እንደሚያተፋ ይታወቃል በሀገራችንም እንዲሁ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራውን እርስ በርስ አፋጅቶ ድምጥማጡን አጥፍቷል። ስለዚህ የአዲስ አበባ እና ጠቅላላ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ፖለቲካ አሁንም እጅግ ደካማ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_38.html)።

ይህ እንደሆነ እውነታው የአዲስ አበባ ህዝብ ካልተደራጀ እንደ ለገጣፎ አይነት ኢ-ሰባዊ ክስተቶችን ማቆም እንደማይቻል ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ ደጋግሞ ይረገጣል። ከመደራጀት በቀር ምንም መፍትሄ የለም። ለመድገም ያህል እሮሮ ማሰማት፤ ማልቀስ፤ መርገም፤ መለፍለፍ ወዘተ ዋጋ የለውም። ከባዱ የመደራጀት ስራ ግድ መሰራት አለበት።

Wednesday 13 February 2019

የንስሐ ፖለቲካ በአሜሪካ


በአሜሪካ ይሁን በሌሎች ምዕራባዊ ሀገራት የንስሐ ፖለቲካ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/blog-post_30.html) የተለመደ አይደለም። ፖለቲከኞች የእውነት ይቅርታ ብዙ ጊዜ አይጠይቁም። ይቅርታ ከጠየቁም ለጋራ ወይንም ለሀገር ጥፋት ነው እንጂ እራሳቸው ላደረጉት ስለራሳቸው ይቅርጣ አይጠይቁም። አልፎ ተርፎ ይቅርታ ከጠየቁ የፖለቲካ ጥቅም ካለው ብቻ ነው።

የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዋልተር ጆውንዝ (Walter Jones) ግን የተለዩ ፖለቲከኛ ነበሩ (https://www.theamericanconservative.com/articles/walter-jones-cried-while-the-rest-of-them-lied/)። ዋልተር ጆውንስ እንደ ሁሉም የሪፐብሊካን ፓርቲ ፖለቲከኞች እና አብዛኞች የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች የጆርጅ ቡሽ የኢራቅ የ2003 (እ.አ.አ) ወረራን ደግፈው ነበር። በ2001 በአሜሪካ ላይ የተፈጸመው ሽብር በኋላ የአሜሪካ ህዝብም ፖለቲከኞች ማንኛውም «ጸረ ሽብር» ጦርነትን ይደግፉ ነበር። ዋልተር ጆውንስ በዚህ በኩል አልተለዩም፤ ጭራሽ ጸንፈኛ አቋም ይዘው ነበር። የፈረንሳይ መንግስት ወረራውን አልደግፍም ሲል ጸረ-ፈረንሳይ እርምጆችን ደገፉ። ዋልተር ጆውንስ የሚወክሉት ወረዳ በጣም ጦር ሰራዊት እና ጦርነት የሚደፍግ ህዝብ ያለበት ቦታ ነበር እና አቋማቸው ይህንን አንጸባረቀ።

የአሜሪካ ወታደሮች እበጦርነቱ መሞት ሲጀምሩ እና ዋልተር ጆውንስ ሬሳዎቻቸውን በየቀኑ እና በየሳምንቱ ማየት ሲጀምሩ የ«ጦርነት ወዳጅ» አመለካከታቸውን ተመልሰው ማየት ጀመሩ። ስህተታቸውን ተረዱ። ተጸጸቱ። ወደ ንስሐ ገቡ። እስኪሞቱ ድርስ በተደጋጋሚ ይቅርታ ጠየቁ። ለያንዳንዱ ሃዘኝነቶች የይቅርታ ደብዳቤ ጻፉ! 11,000 ደብዳቤዎች ጻፉ። ደጋግመው ይቅርታ ጠየቁ። አለቀሱ። «ጦርነቱን በመደገፌ 4,000 በላይ አሜሪካኖች እንዲሞቱ አድርጊያለሁ» ብለው ተናገሩ። ለስህተታቸው ምንም ሰበብ አላረጉም። ያደገቱን «ስህተት» አላሉትም፤ «ኃጢአት» ነው ያሉት።

የዋልተር ጆውንስ ንስሐ የካቶሊክ እምነታቸውን እውን በማድረጋቸው እና በተግባር እይሚያምኑ እንደሆነ ያሳያል ይባላል። የሰው ልጅ ክቡር ነደሆነ ተረድተው ምንም ፖለቲካ ከሰው ልጅ እንደማይበልጥ ገባቸው። ሰው ቁጥር ወይንም መሳርያ ሳይሆን የእግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ተረዱ። የአሜሪካ የጦር ኢንዱስትሪ፤ የፖለቲካ ድጋፍ፤ የእስራኤል «ትቅም»፤ ገንዘብ፤ ወዘተ ከሰው ልጅ እንደማይበልጥ ከልባቸው ተረዱ። ለዚህም ይመስላል ጦርነቱን መደገፋቸው እንዲህ ያጸሰታቸው።

ዋልተር ጆውንስ በወሰዱት አቋም ምክንያት ስራቸውን ሊያጡ በጥቂት ተረፉ። ግዙፍ የፖለቲካ ኃይሎች፤ ሎቢዎች፤ እና የራሳቸው የሪፐብሊካን ፓርቲ ዋልተር ጆውንስ በእጩነትም በመርጫም እንዲሸነፉ በዙ ብር አወጡ። አልሆነላቸውም። ዋልተር ጆውንስ ሁለት ቀን በፊት ከዚህ ዓለም ሲለዩ የምክርቤት ወንበራቸውን እንደያዙ ነው የሞቱት።

የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዋልተር ጆውንስ ለሁሉም ፖለቲከኛም ብዙሃንም ታላቅ ምሳሌ ናቸው። ነፍስ ይማር።

እዚህ ላይ እኔም አንድ ንስሐ ልግባ። እኔም በወክቱ የኢራቅን ወረረ ደግፌ ነበር። አሜሪካ ለመቶ ዓመታት አምባገነኖችን ይህን ማንንም የሚጠቅማቸውን እየደገፉ ዛሬ አምባገነኑ ያውሩዱ በሚል እጅግ ደካማ አስተሳሰብ ወረራውን ደገፍኩኝ። ግን ዋና የአስተሳሰቤ ድክመት ፖለቲካን አለመረዳት አይደለም። የሰው ልጅ ማንነቱ ስላልገባኝ ነው። ጦርነት ለኔ ሃሳብ (abstract) ብቻ ነበር። የክፉ መንፈስ ማስተናገጃ እንደሆነ አልቆጠርኩትም። ሰዎች እንደሚሞቱ ባስቅም ብዛው ደረጃ አላውቅም ወይንም አይገባኝም ነበር ማለት ይቻላል። የሰው ልጅ በእግዛአብሔር ምሳሌ በመፈጠሩ ዘንድ ማንኛውም የሰው ልጅን የሚጎዳ እና የሚገል ነገር መቃወምን ግድ ነው። «ሄዶ ይዋጋልኝ (ን)» ማለት እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው። ከሩቅ ሆኘ ለሆነ abstract ሃሳብ ሰው ይሙት ማለት የሰው ልጅ ማንነቱን አለማወቅ እና ሰውን በተዘዋዋሪ መግደል ማለት ነው።

እርግጥ እኔ አንድ ግለሰብ ነኝ። እንደ ዋልተር ጆውንስ የኢራቅ ወረራ እንዲካሄድ የመረጥቁኝ ወይንም የውሰንኩኝ አይደለም። ግን ሃሳቡን በመደገፌ ከሳቸው ምንም እንዳልለይ ያደርገኛል። «ለቀደሙት። አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። 22 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤» (የማቴዎስ ዎንጌል 5:21,22) በሃሳብ የተፈጸመ ኃጢአት ከተገበረ ኃጢአት ብዙ አይለይም። 

የዚህ ትምሕርት ምንድነው? ፖለቲካ ሆኖም ሌላ ነገር ከሰው ልጅ በላይ ካደረግን ሁልጊዜ ወደ ክፋት ነው የምንሄደው። ፖለቲካን ከእግዚአብሔር እና ቃሉ በላይ ካደረግን፤ ፖለቲካን ጣኦት ካደረግን ሁልጊዜ ወደ ክፋት ነው የምናመራው። ስለዚህ ሁሉ አቋሞቻችንን በትህትና እናስተናግድ። ራሳችንን ሁልጊዜ እንመርምር። ሁሌ የሰው ልጅን ማንነት እናስቀድም።

Sunday 10 February 2019

በ«ቤተሰብ ምጣኔ» ስም የሚፈጸመው ጉዳት



 

በ«ቤተሰብ ምጣኔ» ስም በአማራ ክልል እየተፈጸመ የነበረው ማህበረሰባዊ ጉዳት ይህ ደብዳቤ / መመርያ ይገልጻል። አንብቡት።

ከዚህ ደብዳቤ የምንረዳው ዋና ነገሮች እነዚህ ይመስሉኛል፤

፩፤ የመጀመርያ ነጥብ የድርጅቱ አንዱ ግብ (target) የወሊድ መቆጣጠርያ የሚጠቀሙ ሴቶች ቁጥር መጨምር እንደሆነ ግልጽ ያደርጋል። እነዚህ ግቦች የሚመነጩት ደግሞ ከጤና ጥበቃ ቢሮ ብቻ ሳይሆኑ በዋና ደረጃ ከለጋሾቻቸው ማለትም ከተለያዩ የውጭ ሀገር ለጋሾች እንደ ኢዩ እና ዩኤሴይድ (አንድ ምሳሌ፤ http://www.healthpolicyproject.com/index.cfm?ID=country-Ethiopia)። ይህ ማለት የክልሉ መንግስት፤ የጤና ጥበቃ ቢሮ ሃላፊዎች፤ እና የጤና ቢሮ በታቾች ለገንዘብ ብለውም እንደዚህ አይነት ጉዳት የሞላው ፖሊሲ ፈጽመዋል። አዲሱ ቅኝ ግዛት እንዲህ ነው የሚሰራው።

፪፤ እነዚህን ግቦች ለመምታት በጣም ግልጽ የሆኑ ስህተቶች ተፈጽመዋል። ለምሳሌ በሁለተኛ፤ ሶስተኛ እና አምስተኛ ነጥቦች እንደሚገለጸው በረጅም ጊዜ መቆጣጠርያ ላይ የማይሆን ትኩረት ተደርጓል። የጤና ተቋሙ ገንዘቡን ለማምጣት ጸንፈኛ የሆነ አቋም እና ፖሊሲ ለማራመድ ወደኋላ አላለም። ለምሳሌ ሁሉንም ሴቶች የወሊድ መቆጣጠርያ ተጠቃሚ የማድረግ ታርጌት እና ፖሊሲ ከጫፍ የያዙ ጽንፈኝነት በቀር ሌላ ቃል ሊሰጠው ያችልም።

፫፤ ነጥብ ሰባት የጤና ጥበቃ ቢሮው እንደ ተቋምም ሰራቶኞቹም ለገንዘብ ብለው የተለያዩ የወሊድ መቆጣጠርያ እንደሚያስተዋወቁ እና ሴቶች ላይ እንደሚጭኑ በግልጽ ያስረዳል። ፖሊሲው የሚመራው ለህዝቡ ጤንነት ምን ይበጃል በሚለው መርህ ሳይሆን ምን ገንዘብ / ጉቦ ያመጣልናል በሚለው ነው። ስለዚህ የፖለሲው እና የተግባሩ አለቆች እና ወሳኞች የውጭ ሀገር ለገሾች እና የወሊድ መቆጣጠርያ ሳጭ ኩባኒያዎች ናቸው ማለት ነው።

፬፤ ይህ የብሉሹ እና የበሰበሰ አሰራር የጤና ተቋሙ ሚስኪን ሴቶች ላይ የቅስቀሳ ዘመቻ እያካሄዱ የሴቶቹ ስነ ልቦና እና ጤና የሚጎዳ ነገሮች እንዲያደርጉ እንደሚያደርግ ነጥብ ስምንት ያረጋግጣል። የጤና ጥበቃ ቢሮ ቢሮው ገንዘብ እንዲአገኝ፤ ሰራተኞቹም ለግላቸው ገንዘብ / ጉቦ / ስኮላርሺፕ እንዲያገኙ ጉዳት እንደሚፈጽሙ ግልጽ ነው።

፭፤ የአማራ ህዝብ ልሂቃኑን በደምብ መፈተሽ እና ማስተካከል እንዳለበት ግልጽ ነው። ከላይ ደጋግሜ የገንዘብ ሚና እንዴት የአማራ ጤና ጥበቃ ቢሮ የውጭ ሀገር ለጋሾች እና የመድሃኔት ሻጮች መሳርያ እንዲሆን እንዳደረገ ገለጽኩኝ። ገን ከዚም አልፎ ተርፎ በርካቶች በርዕዮት ዓለም ደረጃ በዚህ ጸንፈኛ ፖሊሲ የሚያምኑ የአማራ «የተማሩ» ልሂቃን አሉ። ከሁሉም በላይ ይህ ነው የሚያሳዝነው። ልሂቃኖቻችን በበአድ አስተሳሰብ አዕምሮአቸው ተገዝቷል። ወደ ኋላ ብለው የጠጡትን ፕሮፓጋንዳ መፈተሽም አይችሉም። የህዝብ ቁጥር ምጣኔ ከሌላ አንጻር መመልከትም አይችሉም። ህዝቡ እራሱ የራሱን የቤተሰብ ምጣኔ መወሰን እንደሚችል፤ ሃብታም በሆነ ቁጥር እራሱ የሚወልደውን ቁጥር እንደሚቀንስ፤ የቤተሰብ ምጣኔ የህዝብ ቁጥርም መቀነስ ጉዳይ አለመሆኑ፤ ወዘተ መገንዘብ የማይችል ልሂቃን ተፈጥሯል። የህዝቡን ስነ ልቦና እና ማህበረሰባዊ እሴቶች የማያውቅ ልሂቃን ተፈጥሯል። በዚህ ላይ ብዙ ስራ ሊሰራ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

Thursday 7 February 2019

በህዝብ ቆጠራው ላይ የኦርቶዶክስ አማኝ ቁጥር ከታሰበው በታች ቢሆን ምን እንል ይሆን?

በሚመጣው የህዝብ ቆጠራ ላይ የኦርቶዶክስ አማኝ ቁጥር ከታሰበው ወይንም ከሚፈለገው በታች ቢሆን እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ምን እንል ይሆን? ይህን መረጃ / ሰነድ ስናገኝ ምንድነው ማድረግ ያለብን?

በመጀመርያ ደረጃ ንስሃ ነው መግባት ያለብን። የኦርቶዶክስ አማኝ ቁጥር ከመነመነ ዋናው ጥፋት የኛ የኦርቶዶክስ ምዕመናን ስለሆነ። እምነታችን፤ ክርስቶስም፤ የሃይማኖት አባቶችም አስረግጠው ይነግሩናል፤ እኛ ጥሩ ክርስቲያኖች ከሆንን እንደ ብርሃን ሌሎችን ወደ ብርሃን፤ ወደ ቃሉ፤ ወደ ክርስቶስ እናመጣለን። በአንጻሩ ጥሩ ክርስቲያኖች ካልሆንን፤ ጭለማዎች ከሆንን፤ ሌሎችን ወደ ክርስትና እንዳይመጡ እናደርጋለን። አልፎ ተርፎ ከኛም ያሉትን እንዲወጡ እናደርጋለን።

ይህን እውነት በአጭሩ ለመግለጽ የሩሲያዊው ቅዱስ ሴራፊም (ሱራፌል) ዘ-ሳሮቭ  እንዲህ ብለዋል፤

«መንፈስ ቅዱስ እንዲያድርባችሁ ከፈቀዳችሁ ዙርያችሁ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ይድናሉ።»

በዚህ ጉዳይ ላይ ለተጨማሪ ማብራርያ ይህን የታወቁት የቆጵሮስ (ሊማሱ ከተማ) ጳጳስ አታናሲዮስ ቃለ ምልልስ ያንብቡ፤ http://orthochristian.com/79957.html። «ክርስቶስን የማያውቁ ሰዎች መኖራቸው የኛ (የክርስቲያኖች) ጥፋት ነው» ይላሉ። ይህ መሰረታዊ እምነታችን ነው።

በመንፈሳዊ ህግ ኃጢአት የቦታ እና የጊዜ ግድብ የለውም። የሁላችንም ኃጢአት ሁላችንንም በተለያየ መንገድ ይነካል። ለምሳሌ፤ እንዴ ወንድሜን ከበደክሉኝ ችግሩ ከኔ እና እሱ መካከል ሆኖ አይቀርም። ይተላለፋል። ወንድሜ ተበሳጭቶ ሌሎችን ይበድላል። ቤት ሲሄድ ቤተሰቡ አክሩፎ ያገኙታል። እኔ ስለበደልኩት ህይወቱን በሙሉ ቁስሉን ተሸክሞ በቁስሉ ምክንያት አስተሳሰቡም ድርጊቶቹም ሊሳባ ይችላል። ቂም ሊይዝ ይችላል። ሰውን በጥርጣሬ ሊያይ ይችላል። በዚህ መንገድ የኔ ኃጢአት እንደ ተላላፊ በሽታ ይንሰራጫል።

ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ህግ ኃጢአት ከቦታ ቦታ ብቻ ሳይሆን ዘመናትን ይሸጋገራል ብለን እናምናለን። ይህ ማለት ኃጢአት ለትውልድ ይተላለፋል። ይህ የሃይማኖታችን መሰረታዊ እምነት ነው። የአዳም ኃጢአትን መውረሳችን ይህን ይገልጻል። ለአዳም ኃጢአት ሃላፊነት ባይኖረንም ውጤቱን ወርሰናል። እኛም ኃጢአት በመስራታችን እንዲሁም አስተላልፈንዋል። ለምሳሌ ከወላጆቼ የወረስኩት ችግርን ተሸክሜ ለልጆቼ በትወሰነ ደረጃ አስተላልፋለሁ። ችግሩ በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በደምም (በዲኤኔአችን) ይተላለፋል።

በመንፈሳዊ ህግ ኃጢአት በሀገር ደረጃም ይታወቃል። የእስራኤል ህዝብ ለሀገራዊ ኃጢአታቸው የታዋቁ ናቸው በራሳቸው በኦሪት ታሪክም በወንጌልም ይህ ታሪካቸው ተዘርዝሯል። ሌሎች በርካታ ህዝቦች እንደ ህዝብ ወይንም ሀገር ለኃጢአቶቻቸው ዋጋ ከፍለዋል። ዛሬም እንዲሁ ነው (https://blogs.ancientfaith.com/glory2godforallthings/2015/06/27/dostoevsky-and-the-sins-of-the-nation/)።

ስለዚህ እንደ ግለሰብም እንደሀገርም ኃጢአቶቻችን በቦታ እና ጊዜ ይተላለፋል። ለዚህ ኃጢአቶቻችንን አምነን ንስሃ መግባት አለብን። ይህ መሰረታዊ የክርስትና እምነት ነው። እንኳን በኢትዮጵያ በዓለም ዙርያ ችግር ሲከሰት ወደ ራሳችን ተመልክትን «ምን አድርጌ ወይህም ምን ባለማድረጌ ነው ይህ የሆነው» ብለን እራሳችንን መጠየቅ አለብን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መእመን ቁጥር ከቀነሰ ወይንም ካልጨመረ እሄኑኑ ጥያቄ እራሳችንን መጠየቅ ነው ያለብን። አማራጭ የለንም። እውነቱ ይህ ነው። ለዚህ ችግር ሌሎችን ጥፋተኛ ማድረግ ኢ-ክርቲያናዊ አካሄድ ነው። እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች «ጴንጤዎቹ»፤ «ሙስሊሞቹ»፤ ወይንም «ሴኩላሪስቶቹ» ናቸው ምእመኖቻችንን የወሰዱብን ማለት አንችልም። ወደራሳችን ብቻ ነው መመልከት ያለብን። እኛ ብርሃን ከሆንን ምንም አይሳነንም፤ ዓለም በሙሉ ወደ ክርስቶስ ይመጣ ነበር። እዚህ ላይ ነው ማተኮር ያለብን። ይመስለኛል።