Monday, 30 July 2018

የብሶት ፖለቲካ

የብሶት (grievance) ፖለቲካ በተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን ከ«ጨቛኝ እና ተጨቛኝ» ፖለቲካ አብሮ ወደ ሀገራችን ገብቶ እንሆ ወደ 60 ዓመት ቆይቷል (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/02/blog-post_16.html)። ምንድነው የብሶት ፖለቲካ? ባጭሩ በብሶት፤ ንዴት፤ ቂም፤ ጭቆና፤ በደል ዙርያ የተመሰረተ ፖለቲካ ነው። በአሉታ (negativity) የተመሰረተ ፖለቲካ ነው። በሰለባ ወይንም ተጨቛኝ አስተያየት (victim mentality) የተመሰረተ ነው።

የብሶት ፖለቲካ መፈክሮች እንዲህ ናቸው፤

1. ተበድያለሁ ተጨቁኛለሁ (ማንንም በድዬ አላውቅም)
2. በዳዮቼ ሊክሱኝ ይገባል (እኔ ማንንም ልክስ አይገባም)
3. ዛሬ ላለሁበት ሁኔታ እና ችግር ሙሉ ጥፋተና ሃላፊነት የበዳዮቼ ነው (ዛሬ ላለሁበት ሁኔታ እና ችግር እኔ ምንም ሃላፊነት የለብኝም)
4. የበደሌኝን ማጥፋት ቢቻል ለሁላችንም ይበጀን ነበር
5. መበደሌን ያላመነ እንደ በዳይ ይቆጠር ሊወገዝ ሊጨቆን ይገባዋል

የብሶት ፖለቲካ ምንጭ ምንድነው? በመጀመርያ ደረጃ ምንጩ እውነተኛ ብሶት ነው። የሰው ልጅ በተለያየ ምክንያት ብሶት አለው፤ ይህን መካድ አይቻልም። ለምሳሌ ጭሰኛው መሬቱ ከሱ ወይንም ከአባቱ ወይንም ከአያቱ ተወስዶበት መሬቱን ለወሰደው እንዲገብር ተደርጎ ብሶት ይኖረዋል። ተጨቁኛለሁ ቢል ይገበዋል። የቤት ሰራተኛዋ አለአጋባብ ስራ ሲቆለልባት እንደ ባርያ ስትነዳ ቤተ ክርስቲያንም ለመሄድ ሳይፈቀድላት ሲቆይ ብሶት እየተጠራቀምባት ይሄዳል። ኦሮምኛ ተናጋሪው በቋንቋ ሲቀለድበት እንደ ዝቅተኛ ሰው ሲታይ ብሶት ይይዘዋል።

ግን በኢትዮጵያ የነበረው ያለው ብሶት እንደዚህ አይነቱ ብቻ አይደለም። ሁሉም ሰው በተለያዩ መልኩ ብሶት አለበት። በጎረቤት መካከል ግጭት፤ ቅራኔ እና ብሶት አለ። በአለካ እና ሰራተኛ፤ በአዛዥ እና ታዛዥ፤ በባልደረባዎች መካከል፤ በቤተሰብ መካከል (ምናልባትም ይህ ከሁሉም ይበልጣል) ወዘተ። በሰው ልጅ መካከል ግጭት እስካለ ድረስ ብሶት አለ። ግጭት ደግሞ በተለየዩ መልኩ አይቀርም።

ስለዚህ ጥያቄው ይህን የማይቀረውም ብሶት እንዴት ነው የምናክመው ነው። በርግጠኝነት ይህን ብሶት ወደ ፖለቲካ ምድር ማምጣት ብዙ ጊዜ አደገኛ ነው ፍትሃዊም ላይሆን ይችላል። የኃይለ ሥላሴ ተማሪዎች የተመረዙበት የማርክሲስት ኮምዩኒዝም ፖለቲካ ይህን ነው በመጀመርያ ደረጃ ያደረገው። ዓለምን ወደ «ጨቋኝ እና ተጨቋኝ» ከፋፍሎ ብሶትህን ተወጣ የሚል ፖለቲካ ነው። በዳይህን አጥፋው በማለት ነው። ታላቁ የደቡብ አፍሪካ መሪ ኔልሰን ማንዴላ እንዳሉት "dialectical materialism" (የብሶት ወይንም ጨቋኝ ተጨቋኝ ፖለቲካ መሰረት) ለነፃነት ታጋይ እንደ ፈንጅ ነው»። ይህ ማለት ኃይለኛ መሳርያ ነው ችግሩን የሚፈታ ብቻ ሳይሆን ዙርያውን በሙሉ ድምጥማጡን የሚያጠፋ። የፈንጅ ወርዋሪውይንም፤ ጠቅላላ ህብረተሰቡንም፤ ሌሎች ሀገራትም ሊያጠፋ የሚችል መሳርያ ነው! መቆጣጠር የማይቻል መሳርያ ነው። ያለንን ብሶት ወደ ፖለቲካ አምጥተን በጨቛኝ ተጨቛኝ የብሶት ፖለቲካ እናስተናግደው ከሆነ ሁላችንም ፉንጂ አፈነዳን ማለት ነው። ይህን ነው በሀገራችን ባለፉት 40 ዓመታት ያየነው። ሀገራችንን አፈንድደናል።

በሀገራችን ይህ የብሶት ፖለቲካዊ አሰተሳሰብ በመደብ፤ በጎሳ፤ በሃይማኖት ወዘተ ታይቷል። ዛሬም በሚያሳዝን ሁኔታ እየታየ ነው። አሳዛኝ ነው የምልበት ምክንያት ሁለት ነው፤ 1) ውሸት ነው፤ የሰው ልጅ እራሱን በዋናነት «ተበዳይ» ብሎ ከገለጸ ማንነቱን አጥቷል ማለት ነው። የሰው ልጅ ሊበደል ይችላል ገን «ተበዳይ» ማንነቱ ሊሆን አይገባም። 2) ይህ አስተሳሰብ ቅራኔን፤ ግጭት፤ ማፈናቀል፤ ግድያ ወዘተ ያሰፍናል ሀገርን ያፈርሳል እና ታላቅ እልቂት ያመጣል። እንዴት?

በመጀመርያ የብሶት ፖለቲካ ሁሉንም አቅመቢስ እና ተበዳይ ያደርጋል (victim)። ሁሉም ተበድያለሁ ይላል ማንም በደልኹኝ አይልም። ሁሉም ካሳ ይገባኛል ይላል ማንም የሚክስ አይኖርም። ሁሉም መቀየም ይገባኛል ይላል ማንም ይቅርታ አይልም። ሁሉም እራሱን አቅመ ቢስ (disempowered) አድርጎ ይቆጥራል ማንም እራሱን እንደ ጎለበተ (empowered) ሰው አይቆጥርም። ይህ ማለት ሁሉም ፈላጊ ሆኖ ሰጭ ወይም አቅራቢ የለም። ይህ አስተሳሰብ ግጭትን ያሰፍናል። ተበድያለሁ ሲል አዎን ብሎ ይቅርታ የሚለው ሲያጣ፤ ካሳ ይገባኛል ሲል የሚክሰው ሳይኖር፤ ሰለባ ነኝ ሲል ፍትህ ሳያገኝ፤ አቅም የለኝም ሲል የሚያጎለብተው ሳይኖር፤ ይህ መሬት የኔ ነው ሲል ሌላውም የኔ ነው ሲል ወዘተ የብሶት እሽቅድድም እና ግጭት ይሰፍናል።

ላለፉት 27 ዓመት ከኢትዮጵያ የሰፈነው የጎሳ አስተዳደር ይህን ክስተት በደምብ ያንጸባረቃል። ሁሉም ብሄሮች ተበድያለሁ አሉ። ለምሳሌ ኦሮሞ ብሄርተኛው ለ150 ዓመት ተበድያለሁ አሁን ቢሻሻልም ገና ዴሞክራሲ ያስፈልገናል፤ ካሳ ያስፈልገናል፤ ታሪክ መስተካከል አለበት፤ አዲስ አበባ የኛ ናት ወዘተ ይላል። ትግሬ ብሄርተኛውም እስካሁን በኢትዮጵያ የብሄሮች እስር ቤት ታስረን ነበር አሁን ነው ነፃ የወጣነው ግን አሁንም በነፍጠኛ እና ጠባብ እንጠቃለን ይላል። በደርግ እና ኃይለ ሥላሴ ዘመን የደረሰብን በደል ምክንያት ካሳ ያስፈልገናል ይላሉ። አዲሱ አማራ ብሄርተኛውም በአቅሙ ተበድያለሁ ለ27 ምናልባትም ለ40 ዓመት የተለያዩ ብሄሮች ሰለቦች ሆነናል ይላል። የሀገራችን ችግር በሙሉ በኛ ይሳበባል ያላል። ዘራችን እየጠፋ ነው "genocide" በኛ በተለየ መጠን ተፈጽሟል ይላል። ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ነፍጠኛ እያሉ በየ ቦታው ያሳድዱናል ያፈናቅሉናል። ካሳ ይገባናል ይላሉ አማራ ብሄርተኛው።

ግልጽ ነው፤ ሁሉም ተበዳይ በመሆኑ እርስ በርስ ያጋጫል። ለስልጣን፤ ለጥቅም፤ ለመሬት ወዘተ በብሄር ደረጃ ይወዳደራል፤ ይጣላል፤ ይዋጋል፤ ይገዳደላል። የፖለቲካ ውድድሩ በጎሳ እና በብሶት ብቻ የተመሰረተ ነው። እንደዚህ አይነቱ ውድድር ደግሞ ከርዕዮት ዓለም ውድድር ይልቅ ቶሎ ወደ ግጭት እና ጦር ያመራል። እነዚህ ግጭቶች ደግሞ ሀገሪቷን ወደ መፈረካከስ ይወስዳሉ። መረጃውን ላለፉት ቢያንስ 27 ዓመት አይተነዋል። ልደገመው፤ የምለው «ቴኦሪ» አይደለም የብዙ ዓመት ማስረጃ አለን።

መፍትሄው ምንድነው ታድያ? አንዳንድ የጎሳ ብሄርተኞች ይቅርታ ብንጠየቅ፤ ታሪክ ቢስተካከልልን፤ መሬት ቢመለስልን ሁሉም ያበቃል ይላሉ! ግን እንደማይበቃ እናውቃለን፤ የሰው ልጅ አንዴ የሰለባ አስተያየት (victim mentality) ከሰፈነበት ከራሱ ውጭ የሚመጣ ነገር መቼም ከዚህ እስር አስተሳሰብ አይፈታውም። ከውስጡ ከልቡ ብቻ ነው ከሰለባ ወደ አቅም እና ሃላፊነት ያለው ሰው መቀየር የሚችለው። ምንም ይቅርታ እና ካሳ ይህንን ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። የልብ ለውጥ ነው የሚያስፈልገው።

ይህንን የልብ ለውጥ እንዴት ይመጣል? ምሳሌ 1። የተበደኩኝ ጭሰኛ ከሆንኩኝ በዳዬን ማጥፋት አይደለም ማሰብ ያለብኝ። መበደሌንም ማቆም አይደለም ማሰብ ያለብኝ። ግቤ መሆን ያለበት ፍትሃዊ የሆነ ኑሮ እና ሁኔታ መፍጠር ነው። ግቤ አሉታዊ ሳይሆን ገምቢ መሆን አለበት። እንዲህ ቢሆን ኖር 40 ዓመት በፊት የጭሰኛ ችግር በ«መሬት ለመንግስት» (አሉታዊ - negative) ሳይሆን በ«መሬት ለአራሹ» (ገምቢ - positive) ይፈታ ነበር። ግን በብሶት ፖለቲካ አሉታዊ አስተሳሰብ ለእውነት የሆኑ ችግሮች የውሸት መፍትሄ ያቀርባል።

ምሳሌ 2። በጎሳ ወይንም ቋንቋ ደረጃ እኔ በቋንቋዬ እና ባህሌ መሰረት ነው መኖር የምፈልገው ከሆነ ያንን ነው ግብ ማድረግ። ሌላውን ጨቋኝ ብሎ መሰየም እና ለማጥፋት መነሳት የብሶት ፖለቲካ አካሄድ ነው። የኦሮሞ ብሄርተኛ ኦሮሚያ ለኦሮሞ የሚለው መፈከር አሉታዊ አካሄድ ነው። ኦሮሚያ ለኦሮሞ ማለት ሌላውን ማስወጣት ወይንም ሁለተኛ ዜጋ ማድረግ ስለሆነ። ሌላውን መጉዳት ስለሆነ። ግን ኦሮምኛ ሀገር ዙርያ ይነገር የሀገር ቋንቋ ይሁን ኦሮሞነታችን ሁሉም ውስጥ ይግባ ማለት ገምቢ የሆነ አመለካከት ነው። የብሶት ሳይሆን የገምቢ ፖለቲካ ነው። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ ግጭት ሳይሆን ትብብር የሚጋብዝ ነው።

ስለዚህ ያሉንን በሙሉ ማሀበረሰባዊም ግለሰባዊም ብሶቶች በብሶት ፖለቲካ ሳይሆን በ«ገምቢ ፖለቲካ» ማካሄድ ነው ያለብን። (ጠ/ሚ አብይ «መደመር» ሲሉ ይህን ማለታቸው ይመስለኛል)። የብሶት ፖለቲካ የግጭት እና ህምም ምንጭ በመሆኑ ምክንያት ማስወገድ አለብን። ይህ ማስወገድ የሚጀምረው ከላይም ጠ/ሚ አብይ እንደሚያረጉት ከታችም እኛ ብዙሃን ማደረግ እንዳለብን። ከሁሉም ትምሕርት ደረጃ ይህ የብሶት እና የጨቋኝ ተጨቋኝ አስተሳሰብን አጥፍቶ ወደ ግምቢ አስተሳሰብ መቀየር አለበት። ከአሉታዊ ወደ ገሚቢ መሄድ አለብን። ይህን መልእክት ከሃይማኖት ተቋማትም መንሰራጨት አለበት። የህዝባችን አስተሳሰብ መቀየር አለበት። ወደ ገምቢ ፖለቲካ መምጣት አለብን።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!