Showing posts with label conflict resolution. Show all posts
Showing posts with label conflict resolution. Show all posts

Friday, 11 November 2022

ቅራኔአችሁን እንፍታላችሁ!

በተለይ ከ1997 ከቅንጅት ዘመን በኋላ ምእራባውያን ማለትም መንግስታት፤ ኤንጂኦዎች፤ ወዘተ ኢትዮጵያዊያን የግትርነት እና የቅራኔ ማባባስ ባህል አላቸው ብለው ያወሩ ነበር። በአንጻሩ እኛ ምእራባውያን በጠቅላላ የፖለቲካ ስልጣኔ በተለይም በቅራኔ መፍታት conflict resolution ጎበዝ ስለሆንን እናንተን ኢትዮጵያውያን እናስተምራችሁ አሉ። በርካታ ስብሰባዎች ትምሕርቶች በብዙ ገንዘብ ወጪ ተካሄዱ። ውጤቱ....

(በነገራችን ላይ እኔም በግሌ ይህ ባህላዊ ችግር አለን ብዬ አምኜ የፈረንጆቹን እርዳታ እንጠቀም ከሚሉት አንዱ ነበርኩኝ።)

ባህል ውስብስብ ነገር ነው። የእገሌ ባህል እንዲህ ነው የእገሌ ባህል እንዲያ ነው በደፈናው ማለት አይቻልም። ሁኔታዎች ሁሉንም ግለሰብም ቡድኖችንም ይቀይራል። እንሆ እነዚህ የቅራኔ መፍታት ባለሙያዎች ምእራባውያን ዛሬ ትክክለኛ ግትርነት ምን እንደሆነ እያሳዩን ነው። በከንቱ ዓለምን ንዩክሊየር ጦርነት ጫፍ ላይ አድርሰዋልና!

እኛ ኢትዮጵያውያን ወዲህ ወድያ ከማየት እራሳችንን ከምእራባውያን ይሁን ከምስራቃውያን ከማነጻጸር ወደ ራሳችን ተመልክተን በራሳችን እሴቶች ተጠቅመን እራሳችን ላይ ብንሰራ ይበጃል። ከሌሎች ጥሩ ነገር መማር ጥሩ ነው ተፈጥርዋዊም ነው። ግን ብዙ ጊዜ ይህ ከጥሩ ነገር መማር አልፎ ወደ ማነጻጸር ይሻገራል እና ሁለት «ኮምፕሌክሶች» ያሳድራል፤ 1) ሌሎች በደፈናው ይበልጡናል ብሎ ማሰብ 2) የራስን እሴቶችን አለማየት። እና ማነጻጸር አደገኛ ልምድ ይሆናል ከእውነታ እንድንርቅ ያደርገናል። ስለዚህ ብዙ ግራ ከኝ ሳንመለከት ችግራችንን በራሳችን በቂ የሆኑ እሴቶች መፍታት ጥሩ አካሄድ ይመስለኛል።

Friday, 5 July 2019

«መፈንቀለ መንግስት»

ፌደራል መንግስት «መፈንቀለ መንግስት» ያለው ጉዳዩን ለማካበድ እና የሚያደርገውን ኃይል እርምጃዎችን ሽፋን ለመስጠት ነው። ተገቢ ይመስለኛል።

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት አቅሙን እጅግ ውስን ነው። የክልሎች መንግስታትም እንዲሁም። ኦነግ ባንክ ሲዘርፍ የቆየው መንግስት «ሆደ ሰፊ» ሆኖ ሳይሆን ለማስቆም አቅም ስለሌለው ነው። እርምጃ ከወሰደ ከውስጡ አቢዮት ሊነሳል ስለሚችል ብዙ የፖለቲካ ስራ በመስራት ቆይቷል። ሆኖም የሰመኑ ግድያዎች መንግስት ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ያሳያል።

ለዚህ አይነት የደከመ መንግስት «መፈንቀለ መንግስት» የሚመጣው በdeath by a thousand cuts ነው። አሳምነው አማራ ክልልን ይቆጣጠራል። የመንግስት ደካማነት ያሳያል። መንግስት ውስጥ ያሉት ለምክዳት ዳር ያሉት ድፍረት ያገኛሉ። በሌሎች ቦታዎች አመጽ ይነሳል። ሁከት ይበዛል። እንዲህ እያለ መንግስት ይፈራርሳል። እንሆ መፈንቀለ መንግስት።

መንግስት ታላቅ የሰው ኃይል እጥረት አለው፤ ይህ ሁላችን የምናውቀው ነው። የህ የ50 ዓመት ውጤት ነው። የዓቢይ ፍላጎት ወደታች በደምብ አይደርስም። መሰረታዊ ችግር ነው። በዚህ ውክት ሁሉም ብሶተኛ ይህን ድክመት ተጠቅሞ ሁከት ማስነሳት ይሞክራል። ይህ ነው ያለፈው ዓመት ታሪክ። አሁንም ይቀጥላል።

መንግስት አሁን ስልቱን ገምግሞ ወደ ይበልጥ ኃይል እርምጃ እየገባ ይሆን ይሆናል። የአቢዮት እና ሁከት ምንጮችን አሳዶ ማስቆም ሂደቱ ሰባዊ ጉዳት ቢኖረውም። ማህበራዊ ሚዲያን ማገድ፤ ኢንተርኔትን ሳይሆን ማህበራዊ ሚዲያን። ይህ ስልት ይሰራ አይሰራ አላውቅም፤ ጉዳይ መሃል ውስጥ እና መረጃ ያላቸው እነ ዓቢይ ነው የሚያውቁት።

ግን ኢግዚአብሔር በሰላም መንግስት ሁከተኞችን ለሞቆጣጠር ይርዳቸው። መንግስት የ«ሁከተኞችን» ችግር እና ብሶት ደግሞ dismiss ከማድረግ ማዳመጥ እና ፍትህ መስጠት እንዲችል ይርዳው።

Thursday, 18 April 2019

ገንቢ ትምሕርት ክሙስታፋ ምሐመድ ዑመር

ይህንን ቪዲዮ እንድትመለከቱ በትህትና እጠይቃለሁ። ሙስጠፋ መሐመድ ዑመር (የሱማሌ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር)  ታላቅ የመሪ ትህምሕርት በሚገባ ቋንቋ ነው የሰጡት።

ሁለት ዋና ዋና ነጥቦች፤

፩) በፖለቲካ ፍፁምነት የለም። ፍፁም እውነት እና ፍፁም ውሸት የለም። ፖለቲካ እንደ ሃይማኖት አይደለም። የሁሉም ሃሳብ የተወሰነ እውነት ሊኖረው ይችላል። ስለዚህም የሌላውን ሃሳብ እና አቋም በደምብ መረዳት አለብን። እራሳችንን በሌሎች ቦታ አድርገን በርህራሄ ማሰብ አለብን። ምናልባት ልክ ሊሆኑ ይችላሉ ብለን ማሰብ አለብን። መገተር የለብንም። ለመስማማት መወያየት እና መደራደር አለብን። ይህን ተመልክቶ «ፖለቲካ ሃይማኖት አይድለም» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/10/blog-post.html) የሚለውን ጽሁፍ ያንብቡ።

በተዘዋዋሪ በፖለቲካ ተደራድሮ ተስማምቶ መኖር ሲቻል በሃይማኖት ረገድ አይቻልም ብለው ሲአስረዱ በሃይማኖት ግን ተቻችሎ፤ ላለመስማማት ተስማምቶ አብሮ መኖር ይቻላል ብለዋል። ግን «ተቻችሎ» ብቻ ሳይሆን ተፋቅሮ መኖር ይቻላል። «ሃይማኖታዊ መቻቻል» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/04/blog-post_3.html) የሚለውን ጽሁፍ ያንብቡ።

፪) ይህንን ተከትሎ ርዕዮት ዓለምን እንደ ፍፁም ማየት የለብንም። ርዕዮት ዓለም ሰው ስራሽ ነው እና ስህተቶች እንዳሉት ማወቅ አለብን። ርዕዮት ዓለምን እንደ ጣኦት ካመለክን ወደ እልቂት እናመራለን። አቶ ሙስታፋ ብዙዎቻችን «የምናመልከው» ዴሞክራሲም እንደ ጣኦት ከተቆጠረ ታላቅ አደጋ እንደሚያስከትል አስረዳ። በዚህ ዙርያ «ዴሞክራሲ» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_8.html) የሚለውን ጽሁፍ ያንብቡ።

አልፎ ተርፎ በርዕዮት ዓለም ፍፁም እውነት ወይንም ፍፁም ስህተት የለም ስንል ይህን አባባል በኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ስንተገብር አንዱ መደምደምያ የጎሳ ብሄርተኝነት ፍፁም ስህተት አይደለም የሚለው ይሆናል። እኔ የጎሳ ብሄርተኝነት በተለይ የጎሳ ፌደራሊዝም ባልወድም የጎሳ ብሄርተኝነት እና ፌደራሊዝም «ክፋት» ናቸው አራማጆቹም «ክፉ» ናቸው ማለት ተገቢ አይደለም። በነሱ ቦታ ሆኖ አስቦ ተቆቁሮ ነው ወደፊት መራመድ የሚቻለው። በዚህ ረገድ «ተረት ተረት፤ ጎሰኝነት ዘረኝነት ነው» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_6.html) የሚለው ጽሁፍ ይመልከቱ።

፫) በመጨረሻ የጎሰኝነትን አደጋ (ይህ የሀገር ብሄርተኝነትንም ሊመለከት ይችላል) «የኔ ጎሳ ሰዎች ንጹ የሌሎች ክፉ» አድርገን መቁጠር ምን ያህል ሃሰት እንደሆነ አቶ ሙስታፋ አስተማሩ። በኔም በሌላም ጎሳ ደጎች እና ክፉዎች እንዳሉ ለማንም ግልጽ ነው። ጥሩ እና ክፉን የሚለየው መስመር በጎሳዎች መካከል አይደለም የሚሄደው፤ በጎሳዎች ውስጥ ነው።

አቶ ሙስታፋ እዚህ ላይ አቆሙ፤ በሃሳቡ አልቀጠሉበትም። መሰረታዊው ነጥብ ይህ ነው፤ ጥሩን እና ክፉን የሚለየው መስመር የሚያልፈው በጎሳዎች መካከል ሳይሆን በያንዳንዶቻችን ልብ መሃል ነው። እነዚህን ሁለት ጽሁፎች ያንብቡ፤ https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/blog-post_21.html እና https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_30.html

Sunday, 24 March 2019

የመጠላለፍ ፖለቲካ ቁጥር 1,999,999

መቼስ እኛ ጎሰኝነትን እንጠላለን ህገ መንግስቱ ይቀየር የምንለው የመጠላለፍ ፖለቲካ ባለሙያዎች ነን። ህወሓት የሀገራችን 6%ም የማይሆን ድጋግ ይዞ ለ27 ዓመት ሲገዛን እንኳን መታገል መደራጀትም አቅቶን ቆየን። በተለይ አማራ ክልል ውስጥ የህወሓት ሰዎች አንድ ለመቶ ሺ ሆነው እንደፈለጉት ሲጫወቱብን ማንም ሳናደርግ ቆየን። በዲያስፖራ ያለነውም ከሳንቲሞች በቀር ማዋጣት አልቻልንም ምንም ቁም ነገር ያለው ድርጅትም አልነበረንም። ለማስታወ ያህል የነ ሻቢያ እና ህወሓት ዲያስፖራዎች በዓመት በአስርት ሚሊዮን ዶላር ነበር ለአቋማቸው የሚያዋጡት።

ዛሬም አክራሪ ጎሰኛው ህልውናችንን አደጋ ላይ እያደረገ እኛ እርስ በርስ እንጠላለፋለን። አሁንም የአማራ ብሄርተኞች እና «አንድነት ኃይል» ወዘተ ፉክክር አልበረደም። አቋማችን አንድ ሆኖ፤ «ህገ መንግስቱ ይቀየር» «ጎሰኝነት ይቅር»፤ እንኳን መተባበር በሰላም አብረን መኖር አልቻልንም። ስለ isolated attack አይደለም የማወራው። በየ አይነቱ ሰው አለ። እንደዚህ አይነት ነገሮች ይከሰታሉ። አብን አደረገው አይባልም። ሆኖም እንደዚህ አይነት ድርጊቶች pattern ሆኖዋል። በሁለቱም ወገን ያለው የአለመተባበርን መንፈስ የሚያንጸባርቅ መንፈስ።

አንዱ መፍትሄ ቀላል ነው፤ እንዲህ አይነት ክስተት ሲፈጠር ሁሉም ወገኖች በይፋ ጮክ ብለው ማውገዝ አለባቸው። ይህ ፖለቲካ 101 ይመስለኛል። ደጋፊዎችህ መስመር እንዳይስቱ፤ ሌሎች ባንተ እንዲተማመኑ የሚደረግ ነገር ነው። የጸብ መንፈስን በህብረት መንፈስ መተካት ነው። ማውገዝ ድርጊቱን እኔ ነኝ ያደረግኩት ብሎ ማመን አይደለም፤ ይህ የታወቀ ነገር መሆኑ ሁላችንም እንደምንረዳ ተስፋ አለኝ። ደግሞ ስለተወገዘ ደጋፊ አጣለhu የሚል እንደሌላ ተስፋ አለኝ። አብንን ማንም outflank የሚያደርግ ድርጅት የለም። ማለት አብን ያወገዘው የትም መሄጃ የለውም። ስለዚህ አብን እንደዚህ አይነት ድርጊቶችን ቶሎ ብሎ ማውገዝ አይጎዳውም እጅግ ይጠቅመዋል።

የአንድነት ኃይል ደጋፊዎችም እነ አብንን እንተው። ማለት ከተቸን ወንድማዊ ምክር በያዘ መልኩ ነው እንጂ መበሻሸቁ ያብቃ። አሁን ቁልፍ ጊዜ ነው፤ እንደ ጥንት አባቶቻችን የሰለጠነ እና የሰከነ ፖለቲካ አሁን ግድ ነው። የዓመታት ህጻንነታችን ለውቅቱ አይበጅም።


Thursday, 3 January 2019

ከብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች ፌደራሊዝም ደጋፊዎች አንዱ የምጋራበት ነገር…

ሁልጊዜ ጥሩውን ነገር መውሰድ ነው… ደካማውን ወገን ትቶ…

የጎሳ አስተዳደር (ፌደራሊዝም) ደጋፊዎች ባህል፤ ቋንቋ እና ሌላ ማንነታችን ለራሳችን ተትቶ እውቅና ይኖረው ይላሉ። የጨርጨር ኦሮሞ የራሱን ማንነት ጠብቆ በሰላም ለመኖር ለዓመታት ታግዷል። የምኒሊክ ጦር 150 ዓመት በፊት መጥቶ አስተአደር እና ባህል ከሌላ ቦታ አምጥቶ የጨርጨር ኦሮሞ ማንነቱን ጠብቆ መኖር አልቻልም ነው። ለኔ ይህ አመለካከት የተወሰነ እውነታ አለው። ለሰው ልጅ የአካባቢ (local) ማንነቱ የተፈጥሮአዊ አስፈላጊነት አለው። የሰው ልጅ በተፈጥሮ ቤተሰብ እና መንደር ያስፈልገዋል። ይህ ተፈጥሮ ነው ብዬ አምናለሁ የሰው ልጅ ታሪክም ይህንን ይመሰክራል። አንዳንድ የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎች ይህን አስተዳደር የምንፈልገው የጎሳ ወይንም ይበልጥ የአካባቢ ማንነቴ እንዳይወረር ነው ሲሉ ይገባኛል። ተገቢ አመለካከት ይመስለኛል።

የማልስማማበት ነገር ግን የአካባቢ ማንነት በህግ ደረጃ የጎሳ ውየን የ«ብሄር ብሄርተሰቦች እና ህዝቦች» ይሁን በሚለው ነው። የምቃወምበት ምክንያቶችም ሁለት ቀላል እና ግልጽ ምክነያቶች ናቸው፤ 1) የአካባቢ ማንነት በጎሳ ከተመሰረተ አግላይ ነው፤ ሰውን በደም እና አጥንት ምክንያት ከአካባቢው በእኩልነት እንዳይቀላቀል ይከልላል እና 2) በጎሳ ከተመሰረተ ግጭት ያመጣል፤ ይህንን ደግሞ በቴኦሪም በ27 ዓመት ታግባር አይተነዋል አሁንም እያየነው ነው።

ስለዚህ እንዴት ነው የጨርጨር ኦሮሞ ባህሉን፤ ቋንቋውን እና የአካባቢ ማንነቱን የሚጠብቀው አስተዳደሩ የጎሳ ካልሆነ? ማለት የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎችን ግብ ለማሳካት እንምራ፤ ግቡን እናሳካ ግን በሌላ መንገድ። የአካባቢ ማንነት እንዲሰፍን እናድርግ ግን አለ ጎሳ አስተዳደር። እንዴት እናድርገው? አንድ ቀላል አማራጭ የዛሬውን ህገ መንግስትን ብዚህ መልኩ መቀየር ነው። «ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች» የሚለውን በዜጋ ይቀየር። የክልል አወቃቀሩ እንዳለ ይሁኑ እንበል። ህገ መንግስቱ ላይ ለክልል ግን እጅግ ይበልጥ ለዞን እና ለወረዳ በርካታ ኃይሎች ይስጥ። ዛሬ ካለው ይልቅ አብዛኛው የመንግስት ኃይል ወደ ዞን እና ወረዳ ይውረድ። ይህ ከተደረገ የአካባቢ ማንነት በዘላቂነት ይጠበቃል።

ለምሳሌ አንድ ዞን አካባቢ አስተዳደር ቋንቋ እና የትምሕርትቤት ቋንቋ የመወሰን መብት ይኑረው። ምናልባትም የመሬት ፖሊሲ መብት ይኑረው። የአስተዳደር ዘዴ መብትም ይኑረው። ወዘተ። ብዙ መብቶች ወደ ታች ወደ ዞን እና ወረዳ መውረድ ይችላል። ይህን በማድረግ አካባቢዎች ኃይል እና ስልጣን እንዲኖራቸው ይደረጋል። መአከላዊ እና ክልላዊ መንግስቶች የራሳቸውን ፍላጎት እና ተጽዕኖ ዞን እና ወረዳዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና ማድረግ ያችልም። የአካባቢ ባህል፤ ቋንቋ እና ማንነት በደምብ ይጠበቃል። መዓከላዊ እና ክልላዊ መንግስቶች እነዚህ ነገሮችን መንካት አይችሉም። የአካባቢ ማንነት autonomy ይጠበቃል።

አንዳንድ የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎች ይህ አሰራር የአከባቢ ማንነትን ሊያስከብር ያችልም ትሉ ይሆናል። በተለያየ መንገድ አዲስ አበባ፤ የምአከላዊ መንግስት፤ የክልል መንግስት ወዘተ በባህልም በሌላም ተጽዖን አድርጎ ማንነቱን ሊቀይር ይችላል ትሉ ይሆናል። ምናልባት። ግን እንዲህ ከሆነ የጎሳ አስተዳደርም ይሄንን ሊከላከል አይችልም! ጨርጨር የአካባቢ ማንነቱን ከክልሉ በጎሳ መልክ የሚቀበል ከሆነ ተቀባይ ነው ዴሞክራሲያዊ አይደለም። ስለዚህ ነጻነት የለውም። ግን ነጻነቱ ቢሰጠው እና በጎሳ ይልቅ በአካባቢ ቢሆን የጨርጨር ኦሮሞ አብዛኛ በመሆኑ አካባቢው በራሱ ባህል ይቀርጸዋል። እዛ የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑትም እኩል ዜጋ ስለሆን ደም እና አጥንታቸው ስለማይቆጠር ይህንን የአካባቢ ማንነት ይደግፉታል እና ይሳተፋሉ። Win-win ሁኔታ ነው።

እስቲ ይህን ሃሳብ አስቡበት። አውቃለሁ የኢትዮጵ ምሁራን የተማሩት በtextbook የምዕራባዊ ፍልስፍና ነውና ስለ localism፤ communitarianism ወዘተ ብዙ አስበንም ገብቶንም አናውቅም። የጎሳ መብት እንላለን ግን አሁንም ከላይ ወደ ታች መጫን ነው ፍላጎታችን። ሌላ አስተሳሰብ ግን ዞሮ ዞሮ ከላይ ወደታች። ግን እስቲ ለአካባቢዎች እውነተኛ ነጻነት እንስጣቸው። ማንም እንዳይጎዳ የዜግነት መንብት እንዲሰፍን አድርገን ግን በርካታ መብቶች ወደ ታች እናውርድ። ይህ ሃሳብ የጎሳ አስተአደር እና የዜግነት አስተዳደር ደጋፊዎችን የሚያስማማ ይመስለኛል።

(ለስህተቶች ይቅርታ በችኮላ ነው የጻፍኩት!)

Tuesday, 6 November 2018

ዲያቆን ዳኒኤል ክብረት ስለ ውጭ ሀገር ጳጳሳት የጻፈውን ለመማርያ እንጠቀም…

(UPDATE) ዛሬ ጥቅምት 21 ይህን ሰማን፤ ከ16 «ውጭ ሀገር ካልተመደብን» አሉ ከተባሉት ጳጳሳት ሁለቱ፤ አቡነ ዮሃንስ እና አቡነ ሚካኤል፤ ሀገር ውስጥ እንሰራለን ብለው ተመድበዋል! ስለዚህ እስካሁን ከ20 ጳጳሳት አራቱ ሀገር ውስጥ፤ ያውም አንዱ ጅጅጋ፤ ለመስራት ተዘጋጅተዋል። ሌሎችም ሊቀጥሉ ይችሉ ይሆናል።

ዲያቆን ዳኒኤል ክብረት በቅርብ ጊዜ ጽሁፉ እንዲህ ይላል፤
«ባለፉት ሦስት ወራት አያሌ ፖለቲከኞች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በሀገር ውስጥ ባለው ፖለቲካ ለመሳተፍ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩም ድጋፍ እየሰበሰቡ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ፖለቲከኞቹ የለቀቋቸውን አሜሪካ፣ አውሮፓና አውስትራልያ ለማጥለቅለቅ ወደ ውጭ እያቀኑ ነው፡፡ 
በተለይም ከውጭ የመጡት ብጹአን አባቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የመመደብ ፍላጎት ፈጽሞ የላቸውም፡፡ በዚህ ረገድ ከ18 ጳጳሳት ሁለት ብቻ ናቸው የተገኙት፡፡ ሌሎቹ ግን በአሜሪካና በአውሮፓ ካልመደባችሁን እንገነጠላለን ብለው የሚያስፈራሩ ሆነዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ መለመንና ማግባባት ሲያቅተው ጳጳሳቱን የደብር አስተዳዳሪዎች አድርጎ እስከ መመደብ ደርሷል፡፡
…»
ጽሁፉ ይቀጥላል። የጽሁፉ ዋና ነጥብ ይህ ነው፤ ለስደተኛው ሲኖዶስ የሚያገለግሉ የነበሩት ጳጳሳት ኢትዮጵያ ውስጥ መመደብ እና መስራት አይፈልጉም።»

የዲያቆን ዳኒኤል ጽሁፍ እንደኚህ አይነት በርካታ ጥያቄዎች ያስከትላል፤

1. እውነትም 16ኡም ጳጳሳት ውጭ ሀገር ካልተሾምን «እንገነጠላለን» ነው ያሉት ወይንም አንዳንዶቹ በነበርንበት ውጭ መመለስ እንወዳለን ነው ያሉት? «ይህ ቢደረግልኝ ነው የምፈልገው» እና «ይህን ካልተደረገልኝ እገነጠላለሁ» የተለያዩ አቋሞች ናቸው።

2. 16ኡም ሁኔታቸውም አቋማቸው እና ሁኔታቸው አንድ ነው? ልምሳሌ አንዳንዶቹ እውነትም አሳሳቢ የጤንነት ችግር እያላቸው ነው ሀገር ውስጥ መስራት አንችልም የሚሉት? ወይንም ከምዕመናኖቻቸው ጋር ያላቸውን ትሥስር ምክንያት መልቀቅ አልፈለጉ ይሆን? ወይንም ሀገር ውስጥ ለመስራት በቂ ብቃት እና ችሎታ የለኝም ብለው በልባቸው የሚያስቡ ይሆናል (አንዳንዱ በቀላሉ ስለተሾሙ)? አንዳንዶቹ ሀገር ውስጥ ለመስራትና ለመኖር መንፈሳዊ ፍርሃት ይኖራቸው ይሆን?

3. ቅዱስ ሲኖዶስ 16ኡም ጳጳሳት ሀገር ውስጥ እንዲሰሩ ይፈልግ ይሆን? ወይንም አንዳንዶቹን ብቻ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ሊመድባቸው ያሰበው?

4. ይህን ተከትሎ እነዚህ 16ኡ ሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ቢመደቡ ቤተ ክርስቲያንን ይጠቅሟት ይሆን?

እነዚህ ጥያቄዎች እስከተረዳሁት ድረስ በዲያቆን ዳኒኤል ጽሁፍ አልተመለሱም። ታድያ እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች ሳይመለሱ እንዴት ነው በ16 ሰው ላይ (የጅምላ) ክስ ማቅረብ የሚቻለው?

ለኔ ይህ ጽሁፍ ለቅራኔ መፍታት (conflict resolution) እና የቅራኔ መፍታት እጦት ጥሩ ትምሕርት ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html)።

ማንኛውም ጹፍ፤ ንግግር፤ ውይይት ወይንም ተግባር ግብ አለው። በተለይ እንደ ዲያቆን ዳኒኤል አይነቱ ታዋቂ እና ባለስልጣን የሆነ ሰው መልዕክት በአንደበትም በጽሁፍም ሲያስተላልፍ ይህን ግብ ጠንቅቆ አስቦ ነው ማድረግ ያለበት።

የዚህ የዲያቆን ዳኔኤል ጽሁፍ ግቡ ምንድነው? እኔ እንደሚመስለኝ 1) ህዝብን የነዚህ ጳጳሳትን ራስ ወዳድነት ወይንም ብቃት ማጣትን ለማሳየት እና 2) ጳጳሳቱን ለመገሠጽ። እነዚህ ግቦች ተገቢ ናቸው ብንልም የዲያኮን ዳኒኤል ጽሁፍ እነዚህን ግቦች ከማሳካት ይልቅ እንዳይሳኩ ያረጋል። እስቲ ጉዳዩን እንመርምረው…

ይህ ጽሁፍ ህዝብን ስለጳጳሳቱ ችግር አያሳውቅም። ለምን?

1) ጽሁፉ የተመሰረተበት ማስረጃ ሙሉ እውነት አይደለም። እንሆ 18 ጳጳሳት ሀገር ውስጥ መሾም አይፈልጉም ተብሎ ነበር ዛሬውኑ 16 ሆነ። ቁጥሩ አሁንም ሊቀንስ ይችላል።

2) ጸሃፌው ዲያቆን ማስረጃ ቢኖሮውም ከጽሁፉ አላቀረበውም። ክሱ ታላቅ ነው ማስረጃው ታናሽ። ስለዚህ አንባቢው በጥርጣሬ ነው የሚያነበው። ከላይ ያነሳኋቸውን ጥያቄዎች ያነሳል። በዚህ ጥርጣሬ መካከል አንባቢው እነዚህ ጳጳሳት እንዲህ አድርገዋል የሚባለውን ለማመን ያስቸግረዋል።

ጽሁፉ ሁለተኛውን የጳጳሳቱን መገሠጽ አላማውንም አያስፈጽምም። ለምን?

1) በሀሰት የተከሰሱት ጳጳሳት፤ ማለትም ሀገር ውስጥ አንሰራም ያላሉት፤ አይመለከታቸውም። ባይመለከታቸውም አብሮ በመከሰሳቸው ዲያቆኑ ላይ ቅሬታ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

2) ጽሁፉ ለተገቢ ምክንያት ሀገር ውስጥ መስራት አንፈልግም ያሉትም ዲያቆን አኒኤል ላይ ቅሬታ እንዲኖራቸው ያደርጋል። የሚያሳስባቸው የጤንነት ችግር አላቸው፤ ህዝባቸውን መትወ አይፈልጉም፤ ሀገር ውስጥ ለመስራት ይፈራሉ ወዘተ ምክንያት ይኖራቸዋል። ዲያቆን ዳኒኤል ሳይጠይቃቸው ሳያነጋግራቸው በደፈናው እንዲህ በመፍረዱ ደስተኛ አይሆኑም። የሱን ተግሣጽ አይቀበሉም።

ስለዚህ የዲያቆን ዳኒኤል ጽሁፍ ሁለቱንም ግቦች አይመተም። ይልቁንስ ቅሬታ ያሰፍናል። ጳጳሳቱ ቅር ይላቸዋል። በርካታ አንባቢ ጽሁፉ የጅምላ ያለማስረጃ ክስ በመሆኑ ቅር ይለዋል። ሌሎች አንባቢዎች ደግሞ ጽሁፉን ቢያምኑት ደግሞ የሀሰት ወይንም ያልተሟላ ክስን አመኑ ማለት ነው እና  እንዲፈርዱ ወይንም ፈራጅ እንዲሆኑ አደረጋቸው። የጽሁፉ መጨረሻ ውጤት አያምርም።

እንዲህ የሆነበት ምክንያት ጽሁፉ መሰረታዊ የአወያየት ስህተቶች ስላሉት ነው። ለምሳሌ፤

1) መፍረድ፤ ማለት ድርጊትን ከመቃውም አድራጊውን መቃወም እና መወንጀል። ልምሳሌ «ጳጳሳት አለ ጥሩ ምክንያት ሀገር ውስጥ መስራት አልፈልግም ማለት ተገቢ አይመስለኝም» ማለት ጥሩ ነው። «እንደዚህ ያሉ ጳጳሳት ካሉ ምክንያታቸው በደምብ ቢታይ ጥሩ ነው» ማለት ተገቢ ነው። ግን «ጳጳሳቱ ምቾት ለምደው ሀገር ውስጥ መስራት አይፈልጉም» ማለት ድርጊትን ሳይሆን ሰው ላይ (ያውም አለማስረጃ) መፍረድ ነው።

2) ማስረጃ አለመስጠት፤ አወያየት እምኔታ ያስፈልገዋል። አንዱ የአምኔታ መስፈርት ማስረጃ ነው። ማስረጃ ከሌለ ጥርጣሬን ነው የሚጋብዘው። ጽሁፉ ጥርጣሬን ያንጸባርቃል።

3) የጅምላ ፍርድ፤ ምናልባት አንዳንዱ ጳጳሳት (ልባቸውን ከፍተን አይተን) መጠን የለሽ ራስ ወዳድ ሆነው ሌሎቹ ግን አይደሉም ክሱም አይመለከታቸውም። ግን አብረው ተፈርጀዋል። የጅምላ ፍርድ የውውት፤ መስማማት፤ እውነት ላይ መድረስ፤ መተማመን ወዘተ ገዳይ ነው።

4) ሀሜት፤ ሰውን ቀጥታ ከመተቸት በተዘዋዋሪ ወይንም በብዙሃን መደረክ መተቸት እንደ ሀሜት ነው። የሚተቸው ሰውን ትችቱን በጥሞና ለመቀበል ይከብደዋል። ተዋረድኩኝ ይላል። ውየንም በሃሰት ተከሰስኩኝ ይላል። በጥሞና ከመቀበል ይልቅ ጥላቻ ያድርበታል።

5) ለሰው አለመቆርቆር፤ በሰው ቦታ ሆኖ ማሰብ የክርስትና ተዕልኮ ነው። ጳጳሱ እውነት እጅግ የሚያማቸው ሆኖ በኢትዮጵያ ህክምና የሚፈሩ ቢሆንስ? በነሱ ቦታ ብንሆን ምን እናደርግ ይሆን? «መነኩሴ ኖት» ማለት ቀላል ነው ግን ተገቢ አይደለም። ለሰው አለመቆርቆር ማለት መወያየት አለመቻል ነው።

6) ስም ማጥፋት፤ የጽሁፉ መንፈስ የስም ማጥፋት መንፈስ አለው ይመስላል። ልምን እንዲህ እላለሁ? እንደገና የጅምላ ፍርድ ያለው እና ግልጽ ማስረጃ የሌለው በመሆኑ ነው።

በነዚህ ምክንያቶች ጽሁፉ ችህግርን ከመፍታት ቅራኔን ያመጣል ወይንም ቅራኔን ያጎለብታል ማለት ይቻላል። እኔ እንደዚህ ነው የሚመስለኝ።

በተጨማሪ ዲያቆን ዳኒኤል የቁጣ መግሥጽ አጻጻፋቸውን ለማስረዳት በመሃበራዊ ሚዲያ ምን አሉ፤ «ጳውሎስ ያን የጻፈው ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ነው። ይህም እንደዚሁ»።

የቅዱሳን አባቶቻችን ትምሕርት ከገባኝ «አትፍረዱ» አንዱ ዋና ትእዛዛችን ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በቁጣ እየፈረዱ ስለጻፉ እኛም እንደዛ ማድረግ አለብን ማለት አይደለም! የተናጋሪው ማንነት ወሳኝ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ የበቃ እረኛ፤ ለእግዚአብሔር እጅግ የቀረበ ሃዋሪያ በመሆኑ ለምዕመናን የሚሰጠው «መድሃኒት» ተገቢው ነው። የምዕመናን ልብን ያውቃል። ምን እንደሚያስፈልገን ያውቃል። ይህ ከቅድስና የሚመጣ ጸጋ ነው። ለዚህ ነው የቅዱሳን አባቶቻችን አንዳንዴ በኃይለኛ ቋንቋ የተናገሩት። ለዚህ ነው እንደ ዮሃንስ አፈወርቅ አይነቱ ህዝብን በጅምላ የገሠጸው። በኢግዚአብሔር ያላቸው ቅርበት ምክንያት እውነትን ይዘው ነው የሚናገሩት በትክክል የሚያስፈልገንን መልዕክት ነው የሚሰጡን። ግን ሌሎቻችን ይህ ደረጃ ላይ ስላልሆንን «አትፍረዱ» የሚለውን ትዛዝ አጥብቀን ይዘን ነው መራመድ ያለብን። እኛ ቅዱስ ጳውሎስ አይደለንም። ዮሃንስ አፈወርቅ አይደለንም። በአነስተኛ የመንፈሳዊ ደረጃችን እንደነሱ እናድርግ ካልን እንሳሳታለን። ወደ መፍረድ፤ ግብዝነት እና ትዕቢት እንድንሄድ ይፈትነናል። አልፎ ተርፎ ቅራኔን ያበዛል።

ይህን ሁሉ ስጽፍ ልብ ካላችሁ የዲያቆን ዳኒኤል ማንነትን አልተቸሁም። ስለ ጻፈው ብቻ ነው የጻፍኩት። ይህ አጻጻፍ ወይንም አነጋገር ገምቢ አይደለም እና ቅራኔ ያንጸባረቃል ነው ያልኩት።

አንድ የሊሂቃን ንስሃ፤ ዶ/ር ታደሰ ወልዴ

ይህንን ቪዲዮ ብትመለከቱ ጥሩ ይመስለኛል።

https://youtu.be/qSPFi8xsbBo?t=1696

ረዥም ከአንድ ሰአት በላይ የሚወስድ ቢሆንም ከላይ ባስቀመትኩት ሊንክ ጀምሮ ብታዩት ስለ ንስሃ ታላቅ ትምሕርት በተለይም ታላቅ ምሳሌ ታያችሁ።

አቶ ታደሰ ወልዴ፤ ታላቅ የኦክስፎርድ መምህር፤ ለኛ ሁሉ ንስሃ ለመግባት ምሳሌ በመሆኖ እግዚአብሔር ይስጦት።

Friday, 19 October 2018

የአለክሳንደር ሶልዠኒትሲን መልዕክት ለኢትዮጵያ

ታላቁ የሩሲያ ደራሲ አለክሳንደር ሶልዠኒትሲን ያሉትን በደምብ ሊገባን ይገባል፤
«ከእስርቤታችን አልጋ የሆነው የበሰበሰው ገለባ ላይ ጋደም ብዬ ነው ለመጀመርያ ከውስጤ የበጎ መንፈስ የተሰማኝ። ቀስ በቀስ መረዳት የጀመርኩት ይህ ነው፤ ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር በሀገሮች፤ መደቦች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መካከል አይደለም የሚያልፈው፤ ይህ መስመር የሚያልፈው በያንዳንዱ የሰው ልብ መኻል ነው። መስመሩ እድሜአችን በሙሉ ከውስጣችን ወደፊት ወደኋላ ይላል። በክፉ የተሞሉ ልቦችም ቢያንስ ቅንጣት ያህል ጥሩነት ይኖራል፤ ከሁሉም ጥሩ ከሚባለውም ልብ ከአንድ ጥጓ ትንሽ ክፉነት ይኖራል።
በየቦታው እየዞሩ ያሉ ክፉ ስራ የሚሰሩ ክፉ ሰዎች ቢኖሩና እነሱን ከኛ መለየትና ማጥፋት ብቻ ቢሆን ኖሮ እንዴት ቀላል ነበር? ግን ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር ከያንዳንዱ የሰው ልጅ ልብ መካከል ነው የሚያልፈውና ማን አለ ከራሱ ልብ ቁራጭ ቆርጦ ለማጥፋት ፈቃደኛ ይሆነ?»

Wednesday, 10 October 2018

የቅራኔ መፍታት (conflict resolution) ጉድለታችን

አንዱ ከብዙ የጠ/ሚ አብይ አህመድ ልዩ የሚያረጋቸው ችሎታዎች የቅራኔ መፍታት አቅማቸው ነው። ትዕቢት፤ ቂም፤ አሉታዊነት፤ ትቶ የሁሉንም ትቅም የሚያስከብር ለሁሉም ተመራጭ የሆነ ግባ ላይ በማተኮር ችግሮችን ፈትተዋል አሁንም እየፈቱ ይገኛሉ። ይህ አቅማቸው ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መሪዎች ለዘመናት ታይቶ አይታወቅም (https://ethsat.com/2018/10/ethiopia-soldiers-show-up-unannounced-at-national-palace-pm-orders-pushups/)።

@Samuel Abebe (በዚህ ትችት ላይ https://www.facebook.com/abdurahman.ahmedin.7/posts/2120966214582614?comment_id=2121015731244329) ሁላችንም በውስጣችን የምናስበውን ታላቅ ጥያቄ ጠየቀዋል፤

«መለወጥ ስህተትን ከመቀበል ይጀምራል ይባላል ትልቅ ስህተት ተፈጽሞም ከቅንጅት አመራሮች ስህተቱን ተቀብሎ እዚህ ላይ ይህን ባንሳሳት ኑሮ የሚል አመራር እንዴት ይጠፋል? ሁሉም ወደ ሌላ ሰዉ ጣቱን ይቀስራል፡ እኛስ የትኛዉን አምነን የትኛዉን እንቀበል?»

ዋና እና ተገቢ ጥያቄ ነው። ብስለት እና እውቀት የሞላው። በማንኛውም ቅራኔ አንድ ጥፋተኛ እና ሌላው ንፁሃን የለም (there are two or more sides to any conflict)። ይህን ሃቅ ማንኛውም ስለቅራኔ የሚያውቅ ባለሙያ፤ ማንኛውም የካህን፤ ማንኛውም አስተዳዳሪ፤ ማንኛውም ወላጅ የሚያውቀው ነው። ግን ብናውቀውም እንዳማናውቀው አድርገን ነው የምንኖረው። ቅራኔ ውስጥ በተገኘን ቁጥር እራሳችንን ፍፁም ንፁህ ሌላው ፍፁም ጥፋተኛ አድርገን ነው የምንቆጥረው።

ይህ ከገባን በቅንጅት ቅራኔ ህሉም ተሳታፊዎች የተወሰነ ሚና መጫወታቸውን ሊገባን ይገባል። የፈረደበት ልደቱ ጥፋት ብቻ ሊሆን አይችልም። ዋናው ችግር የሱ ነው ቢባልም ያንን ችግር ማስተናገድ አለመቻል በራሱ ትልቅ ድክመት ነው! መታመን ያለብት እና ይቅርታ የሚጠየቅበት ድክመት ነው። ታላቅ መማርያ የሚሆን ድክመት ነው።

እንደ ቅንጅት አይነት ታላቅ ድርጅት፤ እጅግ ግዙፍ የሆነ የሀገር ሃላፊነት ያለው ድርጅት ሲፈርስ ሁሉም በአመራር ያሉት በመፍረሱ ሚና ተጫውተዋል እና ሁሉም ድክመታቸውን አምነው ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል። እኛም ደጋፊዎቻቸው እንዲሁም። ያደረግነውን ስህቶቻችንን ካመንን በኋላ ብቻ ነው መማር የምንችለው እና እንዳንደግማቸው ማድረግ የምንችለው።

የቅንጅት ታሪክ ከብዙ የሀገራችን ፖለቲካ የቅራኔ መፍታት አለመቻል ታሪኮቻችን አንዱ ነው። እንዳውም በኔ እምነት የፖለቲካ እና ማህበራዊ ችግሮቻችን ዋና ጎልቶ የሚታየው ምክንያት «የቅራኔ መፍታት (conflict resolution) ጉድለታችን» ነው። በዚህ ዙርያ ብዙ ተጽፏል እና ተነግሯል ግን በቂ አልተደረገም። ዛሬም የምናያቸው ነገሮች አሉ፤

1. አንድ «አቋም»፤ ርዕዮት ዓለም፤ አስተያየት ኖሮን አብሮ መስራት አለመቻል
2. የራሳችንን ጥቅም ጎድተን ቂማችንን ለመወጣት የምናደርጋቸው ስህተቶች
3. የጋራ ማሸነፍን ከመፈለግ (አሁንም የራሳችንን ጥቅም ቢጎዳም) ሌላው እንዲሸነፍ መመኘት እና መስራት
4. ፖለቲካን እንደ ሃይማኖት ፍፁም እውነት እንዳለው መቁጠር።

የፖለቲካ አካሄዳችን እንዲሻሻል ከተፈለገ ስለነዚህ ጉዳዮች መያየት እና መፍትሄ ማግኘት ግድ ነው።

ቅራኔ መፍታት ለኛ ኢትዮጵያዊያን አዲስ ነገር አይደለም። የድሮ ንጉሶቻንን አድርገውታል። ይህን የሚያስፈጽሙ በርካታ ባህላዊ መንገዶች አሉን። ከሃይማኖታችን ደግሞ መሰረታዊ ቅራኔ መፍታት ምክንያቶችንም ዘዴዎችም አሉ። ለምሳሌ በክርስትና «ንስሃ» ማለት ማለት 1) ስተትን ማመን 2) እንዳይደገም 3) ሌላው እንዲገባው 4) እራስን ለማረም 5) እራስን ለማወቅ ወዘተ። ውየንም «አለመፍረድ» ማለት 1) ለሌላው መቆርቆር (empathy) 2) የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ችኩሎ አለመድረስ 3) ጣት ጠኩሞ የራስን ችግር መርሳት ወዘተ።

ስለዚህ አሁን ማድረግ ያለብን እነዚህን (ምናልባት የተረሱ) ባህላዊ እሴቶችን እንደገና ማስነሳት እና ማሰራጨት ነው። ከባድ ስራ ነው ግን ምርጫ የለንም!

http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html

Tuesday, 20 February 2018

ታሪክን አንድገም፤ ሀገርን እንገንባ

አሳፋሪና አገር አፍራሽ ታሪካችንን እንዳንደግም ነው ይህን ጽሁፍ የምጽፈው። ታሪክ እንደመዘገበው ከኢህአዴግ ውጭ ያለነው ምሁራን፤ ፖለቲከኞችና ብዙሃን በፖለቲካ ረገድ ቁም ነገር ለማድረግ እድል ባጋጠመን ቁጥር እልዳችንን አበላሽተናል። በተደጋጋሚ ጊዜ ለአገራችን የፖለቲካ መስተካከል ከኢህአዴግም ይበልጥ እንቅፋት ሆነን ተገኝተናል።  ይህን ደፍሬ መናገር የምችል ይመስለኛል።

አንዱ የድክመታችን ምክንያት ተልዕኮአችንን አለማወቃችን ወይም መርሳታችን ነው። ተልዕኮአችን የአገር ፖለቲካ ግንባታ ነው እንጂ የፖለቲካ ውድድር አይደለም። የአገር ፖለቲካ ስርዓት ግንባታ ሲባል ሁላችንም ስለ ህገ መንግስትን ማርቀቅ ነው የምናስበው። ግን ከዚህ ህገ መንግስት ማርቀቅ ስራ በፊት  የልብ ለልብ መተዋወቅ፤ በተወሰነ ደረጃ መተማመን፤ መግባባትና መስማማት ያስፈልጋል። እነዚህ ለአገር ግንባታ የፖለቲካ ድርድር ቀድሞ ሁኔታዎች ናቸውና። አለነዚህ ማንኛውም በወረቀት ያለ ህግ፤ ምንም አይነት ወርቅ የሆነ ህግ ቢሆነም፤ በስራ ሊተገበር አይችልም

ቀጥሎ በነዚህ ተመስርቶ ህገ መንግስትና ሌሎች የርዓይና የህግ ሰነዶች ይደነገጋሉ። ቅራኔ ወይም አለመግባባት ካለ በህግ መሰረት ይፈታል ህጉ ደግሞ በቂ ካልሆነ ያለው መተማንና ስምምነት ለፍትህ ይረዳል። የአገር የፖለቲካ ግንባታ ሂደት እንደዚህ ነው መሆን ያለበት።

የፖለቲካ ውድድር ደግሞ የሚጀምረው የፖለቲካ ስረዓቱ ከተዋቀረ በኋላ የሚመጣው የፖለቲከኞችና ሌሎች ለመሪነት እርስ በርስ በህጉ መሰረት መወዳደር ነው። በምእራብ «ዴሞክራሲዎች» እንደዚህ አይነቱ ውድድር በርካታ ክርክር፤ ክስ፤ ዘለፋም ወዘተ ያካትታል። የህጉን ገደብ ዳር ዳር እየነኩ ግን ሳያልፉ እነዚህን አይንቶች ባህሪዎችን ያንጸባርቃሉ። ይህ ስልጣን ለመያዝ ሊበጃቸው ይችላል ግን ምንም አይገነባም። እርግጥ መተማመንንና ውይይትን ይጎዳል ግን ከምርጫው በኋላ የደረሰውን ጉዳት ይጠግኑና የአገር ማስተዳደር ስረአቸውን ይጀምራሉ። ይህ ነው በተለምደው የምናውቀው የፖለቲካ ውድድር።

የፖለቲካ ውድድር ደግሞ የፖለቲካ ስርዓቱ ከተዋቀረ በኋላ የሚከተለው የፖለቲከኞችና ሌሎች ለመሪነት እርስ በርስ በህጉ መሰረት መወዳደር ነው። በምእራብ «ዴሞክራሲዎች» እንደዚህ አይነቱ ውድድር በርካታ ክርክር፤ ክስ፤ ዘለፋ ወዘተ ያካትታል። የህጉን ገደብ ዳር ዳር እየነኩ ግን ሳያልፉ እነዚህን አይንቶች ባህሪዎችን እያንጸባርቁ ይወዳደራሉ። ይህ ስልጣን ለመያዝ ሊበጃቸው ይችል ይሆናል ግን አገርን አይገነባም ይጎዳልም። ሰልዚህም ነው ውድድሩ ምርጫው ካለፈ አሸናፊዎቹ ውድድሩ ያደረሰውን ንዴት፤ ቂምና ጉዳት ይጠግን ዘንድ ትሸናፊዎቹንም መላው የአገሪቷን ህዝብ አንድ የሚያረግ እርቃዊ ንግግርና ተግባር የሚአደርጉት። ይህ ነው በተለምዶ የምናውቀው የፖለቲካ ውድድር።

ስለዚህ አገርን መገንባትና የፖለቲካ ውድድር የተለያዩ ባህሪያት፤ ተግባራትና ልምድ ያስፈልጋቸዋል። የአገር ግንባታ ሂደት እንደ መተማመን፤ ስምምነት፤ አንድነት፤ መግባባት፤ ህብረት፤ ቅራኔን መፍታት፤ ውይይት ወዘተ አይነቱ ባህሪያትና ልምዶች ያስፈልጉታል። የፖለቲካ ውድድር ግን ክርክር፤ ውድድር፤ ፉክክር፤ መካሰስ፤ ህግና ስረዓትን ዳር ዳሩን መጣስ፤ ወዘተ አይነቱን ልምዶች ያካትታል። በአገር ግንባታ ሂደት መካከል እነዚህን የፖለቲካ ውድድር ባህሪያትና ልምዶች ይዘን ከገባን አገርን መገንባት ሳይሆን ማፍረ ነው የምናደርገው።

ለዚህ ደግሞ በርካታ ታሪካዊ ምሳሌዎች አሉን። እስቲ ወደ 15 ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሰን የ«ተቃዋሚ» ምሁራን፤ ጋዜጠኛና ፖለቲከኞች እያደረጉ፤ እየተናገሩ፤ እየጻፉ ምን እንደነበር እናስታውስ። ስራቸውን ባጭሩ ለመግለጽ «እርስ በርስ መበላላት» ማለት ይቻላል! ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ ከሚተቹት ይበልጥ እርስ በርስ ነበር የሚፋጁት። ጋዜጣ ላይ ቁም ነገር ሳይሆን ስድብና የመንደር ወሬ ነበር የሰፈነው። ከሞላ ጎደል ስራቸው 90% አፍራሽ 10% ገምቢ ነበር። ስለዚህም ነው ተቃዋሚው ጎራ ምርጫ '97 በግንቦት ሆኖ እሰከ የካቲት አካባቢ የትብብር መዋቅሮች ያላደራጀው! ለዚህም ነው ከምርጫው በኋላ ተቃዋሚዎች በቀላሉ የተበታተኑት። በበፊቱ ዓመታት እዱሉ እያለን ቅስ ብለን በትብብር ጉዳይ ተወያይቶ ትብብርን ከመፈጸምና ጠንካራ መሰረት የሆነ መዋቅርን ከመገንበት እንደ ምርጫ ተዋዳዳሪዎች እየተሰዳደብን ዋልን። ችግር ሲመጣ ለመቋቋም አቅሙ አልነበረንም። እርስ በርስ ተፋጅተን አለቅን። የግንባታ ስራ ያልተሰራባቸው ቅንጅትና ህብረት በቀላሉ ፈረሱ። የፖለቲካ መዋቅር ግንባታንና የፖለቲካ ውድድርን መለየት ያልቻሉትም ከፖለቲካ ወጡ። የህዝብም ትዝብት አደረባቸው።

በርካታዎቻችን በምዕራብ የሚዲያ ዜና፤ ትምህርትና ፕሮፓጋንዳ ስላደግን የነዚህ አገራት ፖለቲካ ስናይ ፖለቲካ እንደዛ መሆን እንዳለበት ይመስለናል። የናየው ደግሞ የፖለቲካ ውድድራቸውን ነው። ክርክሩን፤ ዘለፋውን፤ ስድቡን፤ ሴራውን ወዘተ። እኛም እንደነሱ ማድረግ እንወዳለን መሰለኝ። ግን ኢትዮጵያ ያለችበት ቦት፤ ለረዥም ዓመታት ያለችበት ቦታ፤ ገና የአገር ፖለቲካ ግንባታ ላይ ናት። ብዙሃኑም ልሂቃኑም የፖለቲካ መደቦቻችን እስካሁን በእምነት የተመሰረተ አገራቷን ምን መምሰል አለበት የሚል ሰፊ ስምምነት ላይ አልደረስንም። አሁንም ያለው ዋና ስራችን የህ ነው። አዎን ህገ መንግስት አለን ግን ሰፊው ርአይና ስምምነት የለንም። ነገ ኢህአዴግ ከስልጣን ቢወርድም ይህ ስምምነቱ ስለሌለ ሁከትና አብዮት ይከተላል።

በዚህ ምክንያት ሁላችንም፤ ምሁራን፤ ብዙሃን፤ ፖለቲከኛ፤ የመንግስት ሰራተኛ፤ ወዘተ ትኩረታችን ወደ አገር ግንባታ መቀየር አለበት። ይህ ማለት ከታች የተጠቀሱትን ለአገር ግንባታ አስፈላጊ የሆኑትን ብሃሪያት፤ ተግባሮችና ልምዶች ከራሳችን ጋር መዋሃድና በዚህ አስተሳሰብ ወደ ፊት መራመድ።

ስምምነት፤ አንድነት፤ መግባባት፤ ህብረት፤ መተማመን፤ በስነ ስረዓት መነጋገር፤ ውይይት፤ ቅራኔን መፍታት።

የሚቀጥለው ጊዜ አንድ ሰውን ወይም ቡድንን መዝለፍ ወይም መስደብ ካሰኘን ቆመን እናስብ። የፖለቲካ ውድድር ውስጥ አይደለንም። እንደዚህ አይነቱ ባህሪያት ታሪካችን እንደሚያረጋግጠው ሁላችንንም ጠርጎ ገደል ውስጥ ያስገባል አገራችንን ያፈርሳል። በሰላም እየተከባበርን እየተማመንን ነው መወያየት ያለብን። ይህ የሁላችንንም ጥቅም ያስከብራልና። ይህንን ብቻ ተግባራዊ ካደረግን አለ ምንም ጥርጣሬ ታላቅ አገር እንገነባለን ጠላት የምንላቸውም ምንም ሊጎዱንም አይችሉም።

Tuesday, 25 October 2016

An Exercise in Empathy

2009/2/15 (Ethiopian calendar)
2016/10/25 (European calendar)

(pdf)

[Note: An Amharic version of this post will appear sometime!]

In the next few posts, I will attempt, just attempt, an exercise in empathy. I will try and put myself in the shoes of Ethiopia's various political groups and constituencies and describe the truth about Ethiopian politics how they see it – from their perspective. I will start with either Oromo ethnic nationalists or the EPRDF, or maybe just the TPLF. And I'll keep going as much as I can.

Why this exercise? I'll first answer from within the 'conflict resolution' paradigm. Empathy – trying to grasp the point of view, the feelings, the thoughts, etc of others – is an important tool, perhaps the most important, in conflict resolution. The idea is that if you can empathize, you can communicate better, that is you can communicate in a way that your opponents can understand, and of course you can better envision solutions that your opponents can accept. Empathy also builds trust and understanding, which needless to say are important for living together peacefully.

Second, as this blog is written from an Orthodox Christian perspective, I'll explain from this point of view as well. Empathy is basic Christianity. Our fundamental belief is that Christ came and died for us out of compassion – to share our suffering and redeem it. This is similar to empathy, but greater, as it involves not only sharing the Other's experience, but doing so with the hope of bring about something better. Further, avoiding judgement is a basic teaching of the Church. “To judge sins is the business of one who is sinless, but who is sinless except God?... To judge a man who has gone astray is a sign of pride, and God resists the proud.” says St Dorotheus of Gaza. So, following Christ's example of compassion and his command not to judge, a Christian as a matter of course must try to be empathetic.

I hope my little exercise will help shed some light on solutions for Ethiopia's problems. So, I'll give it a try over my next few articles. Your feedback as always is much appreciated.