Friday 6 April 2018

የህዝብ ብዛት

የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በዝቷል በተለያዩ መንገዶች የህዝብ ቁጥር እድገትን መቀነስ አለብን ሲባል እጅግ አዝናለሁ። በተለይ የኛ ምሁራን ልሂቃን እንደዚህ ሲሉ ስለ ሀገራችን ህልውና እሰጋለሁ። ሀገራችን ብዙ የፖለቲካ የኤኮኖሚ የመሐበረሰብ ችግሮች አሉትና ከነዚህ ሁሉ የሰው ቁትር መብዛት «ችግር» ከተባለም ትንሹ ነው። የሰው ቁጥር አለ አግባብ ጨምሯል ከተባለም ምክንያቱ የእርግዝና መከላከያ እጦት ሳይሆን ሌሎች የኤኮኖሚና የፖለቲካ ችግሮች ናቸው።

እስቲ አንዳንድ እውነታዎች እንመልከት፤

1. በገጠር ሴቶች በአማካይ ስድስት ልጆች ይወልዳሉ። በአዲስ አበባ በአማካይ ሁለት ልጆች ይወልዳሉ። ላለፉት 43 ዓመት የመንግስታችን የመሬት ፖሊሲ ህዝባችን ከገጥር እንዳይወጣ አድርጓል። ምክንያቱም አንድ ገበሬ ገጠርን ትቶ ወደ ከተማ መምጣት ከፈለገ መሬቱን መሸጥ ስለማይችል ከሞላ ጎደል ባዶ እጁን ወደ ከተመ መምጣት ስለሚሆንበት አያደርገውም። በዚህ ምክንያት 43 ዓመት በፊት የህዝባችን 85% የገጠር ነዋሪ ነበር አሁንም ወደ 80% የገጠር ነዋሪ ነው። የመሬት ፖሊሲው ባይኖር ይህ ቁጥር ዛሬ ምናልባት 60% ይሆን ነበር። እንደዚህ ቢሆን ኖር 80% ፋንታ 60% ነበር ስድስ ልግ የሚወልድው 20% ፋንታ 40% ሁለት ልግ ይወልዳል። በዚህ ምክንያት የጠቅላላ የህዝብ ቁጥር እድገት ይቀንስ ነበር።

2. ሀብት ምቾት ድሎት ከትመት (urbanization) በጠቅላላ ብልጽግና (development) በጨመረ ቁጥር የቤተሰብ መጠን ይቀንሳል። ይህ ንድፈ ሐሳብ (theory) ሳይሆን ያለፈው የ100 አመት የዓለም ታሪክ የመሰከረው እውነታ ነው። በሀገርም በህብረተሰብም ደረጃ ይህ እውነታ ይታያል። ሀብታም ሀገሮች ብዙ አይወልዱም ከነሱም የሚወልዱት ካልበለጸጉ ሀገሮች የመጡ መጤዎች ናቸው። ማንኛውም ሀገር አማካይ ሀብቱ በጨመረ ቁጥር የቤተሰብ መጠኑ ይቀንሳል። ስለዚህ በኢትዮጵያም «ብልጽግና» በጨመረ ቁጥር የሚወለደው ቁጥር ይቀንሳል። ስለዚህ አሁን እንቀንሰው ብሎ መርሯሯጥ አያስፈልግም።

3. የህዝብ ብዛት ሀብት ነው። የምዕራብ ሀገሮች ፍልሰትን (immigration) የሚጋብዙት ምክንያት የሰው እጥረት ስላላቸው ኤኮኖሚያቸው እየተጎዳ ስለሆነ ነው። የአዲስ አበባ ኤኮኖሚ የሚንርበት አንዱ ምክንያት ከገጠር ወደ ከተማ ያለው ፍልሰት ነው። የሰው ኃይልና የሸማች (consumer) ቁጥር በመጨመረ ቁጥር የኤኮኖሚ እንቅሳሴ ይጨምራል። በውጭ ግንኙነት አንጻርም ብዙ ህዝብ ያለው ሀገር በዓለም ላይ ያለው ኃይልና ሚና ይጨምራል። የኢትዮጵያ የዝብን ቁጥር በአባይ ግድብ ላይ ያለው ሚና ትንሽ አይደለም። ስለዚህ የህዝብ ብዛት እንደ እንቅፋት ብቻ መታየት የለበተም።

4. ኢትዮጵያ ገና ብዙ የህዝብ ቁጥር ማስተናገድ የምትችል ሀገር ናት። ካላት ለም መሬትና ሌሎች የተፈጥሮ ምንጮች አንጻር ምናልባት እስከ 200 ሚሊዮን ትችላለች። ጃፓን የኢትዮጵያ አራት እጥፍ ሰው በካሬ ኪሎሜትር አላት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ትጨናነቃለች ብለን ልንሰጋ አይገባም።

ከዚህ አልፎ ተርፎ እንደ ኦርቶዶክስ ክርትያን የህዝብ ቁጥርን «መቆጣጠር» የሚባለው ነገር ያሳስበኛል። በተለይ የወሊድ መቆጣጠርን ማስፋፋት ያሳስበኛል። እንደዚህ አይነት ጉዳይ ውስጥ መግባት ትዕቢትን ነው የሚጋበዘው። እራሳችንን እንደ አምላክ እንድናይ ይፈትነናል። ከእግዚአብሔር የሰጠንን የተፈጥሮ ተልእኮ እንድንወጣ ይፈትነናል። ለዚህም ነው የሃይማኖት አባቶቻችን በሙሉ የቃወሙታ። ይህን መጠቀም ከሰው ተልእኮና ማንነት ይጋጫል ማጣት ነው ይላሉ። እርግጥ ካህናት በእረኝነት ሚናቸው በአንዳንድ አጋጣሚዎች የሃይማኖት ልጆቻቸውን እንዲጠቀሙ ሊፈቅዱ ይችላሉ ግን በጠቅላላ ከተቻለ አይመከርም። የስጋ ግንኙነትና መውለድ በተፈጥሮ የተገናኙ ናቸው ማለያየት ለሰው ልጅ ጎጂ ነውና።

ይህን እያወቅን የህዝብ ቁጥር እድገት እንዲቀንስ ተግባራዊ ስራዎች እናካሄድ ማለት ይከብደኛል። በተለይ በወሊድ መቆጣጠርያን በመጠቀም እንቀንስ ማለት ይከብደኛል። ለተጠቃሚው መንፈስ ጎጂ ነው ብዬ የማምነው ነገርን ማስፋፋት ህሊናዬ አይፈቅድልኝም። ሰዎች በገዛ ፍቃዳቸው ቢጠቀሙ ልፈርድባቸው አይገባም አልችልም «መብታቸው» ነው። ግን እንደ መንግስት መርህ ይህን ማስተዋወቅና ማስፋፋት ጎጂ ነው ብዬ ነው የማምነው። የቤተሰብ መጠንን ይቀንሳል ግን የመንፈሳዊ ጉዳቱ በምዕራቡ ዓለም የምናየው ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት አልፈልግም። አዎ ዛሬ በሀገራችን በደምብ ተስፋፍቷል ግን መንግስት ከዚህ ጉዳይ እራሱን ቢያወጣ እወዳለሁ።

አልፎ ተርፎ ከላይ እንደጠቀስኩት በኔ እምነት የህዝብ ቁጥራችን አሳሳቢ ጉዳይም አይደለም። ክትመት ብልጽግና በጨመሩ ቁጥር የህዝብ ቁጥር እድገት ይቀንሳል። ቻይና ለ40 አመት ህዝቧ እንዳይወልዱ አድርጋ አሁን የህዝብ ቁጥራችን አንሶ አሳስቦናል ትላለች! እንማር!

ሀገራችን ገና «አልሞላችም»። ስለዚህ ትኩረታችንን ወደ ሌሎች የኤኮኖሚ የፖለቲካ የመሐበረሰብ ጉዳዮች ይሁን። እነዚህን ጉዳዮች በማሸነፍ የህዝብ ብዛት ጉዳያችንም በራሱ ይስተካከላል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!