Monday, 17 September 2018

መርዝ መጠጣት መብት ቢሆንም ይገላል፤ እንዲሁም የጎሳ ብሄርተኝነት መብት ቢሆንም ህዝብን ያጠፋል

ለማንም ሰው በ«ጎሳ ብሄርተኝነት» እና የፖለቲካ ዘመዱ በ«ጎሳ አስተዳደር» ማመን መብቱ ነው። አንድ ሰው እንዲህ «ኢትዮጵያዊ አይደለሁም፤ ኦሮሞ ነኝ። ኢትዮጵያ ህዝቤን ለዓመታት ጨቁናለች ቅኝ ገዝታለችም። ማንነቴ ኦሮሞ ነው። መኖር የምፈልገው በኦሮሞ ሀገር ነው እንጂ ኢትዮጵያ አይደለም» ቢል መብቱ ነው። እንዲህ አታስብ ማለት ልክ አይደለም። ካልንም መብት ገፈናል ግጭትንም ጋብዘናል ማለት ነው (ይህንን ጥንቅቃችሁ እንድታነቡ እጠይቃለሁ http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2017/11/whats-ethnic-nationalism-again.html)።

ይህን ተከትሎ በርካታ ሰዎች እንዲህ አይነት የጎሳ ብሄርተኝነት አመለካከት ካላቸው እና የፖለቲካ ፍላጎታቸው ይህ ከሆነ ጥያቄአቸው በሰላማዊ መንገድ መስተናገድ ይኖርበታል። ለምሳሌ የአንድ ክፍለ ሀገር ወይንም ክልል 70% ህዝብ «ነፃነት» ወይንም ሌላ የፖለቲካ አስተዳደር እፈልጋለሁ ካለ በድርድር መልክ መስተናገድ አለበት። አለበለዛ መብታቸውን አላከበርንም ማለት ነው። እንዲህ አይነት አካሄድ ደግሞ ወደ ግጭት እና ጦርነት ማምራቱ የታወቀ ነው።

የጎሳ ብሀሄርተኝነት መብት ነው ብለናል። ታድያ ለምንድነው የምንቃወመው? መልሱ ቀላል ነው፤ የጎሳ ብሄርተኝነት የግጭት ምንጭ ስለሆነ ነው። በተለይ በብሶት ማንነት የተመሰረተ (grievance based identity) የጎሳ ብሄርተኝነት በ«ጭቋኝ ተጨቛኝ» አስተሳሰብ የተሞላ ስለሆነ ሁልጊዜ ግጭት ያመጣል። ተጨቁኛለሁ ጨቋኜን ማጥቃት አለብኝ ይላል። ብድር መመለስ አለብኝ ይላል። መሬቴን መመለስ አለብኝ ይላል። «መጤዎችን» ማባረር አለብኝ ይላል። ሰውን እንደ ሰው ከማየት እንደ ቡድን ያያል። የመንጋ አስተሳሰብ ይጋብዛል። ወዘተ። ታሪኩ ዓለም ዙርያ የታወቀ ነው።

የጎሳ ብሄርተኝነት ግጭት እንደሚጋብዝ የሚታወቀው በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር ባለፉት 27/40 ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ ያየነው ነው። ግጭቶቹ የህወሓት ስራ ናቸው እንጂ የጎሳ ስረዓቱ አይደለም ማለትም አይቻልም። አብዛኞቹ ግጭቶቹ ህወሓት እንደ ተጋጭ አልተሳተፈባቸውምና። ግጭቶቹ የህወሓት እጅ ቢኖርባቸውም ህወሓት በባዶ መሬት ያስነሳቸው አልነበሩም። ህወሓት የነበሩ የጎሳ ቅራኔዎችን ነበር የሚጭረው እንጂ ቅራኔዎችን ከስር አልፈጠረም። ስለዚህ ባለፉት ዓመታት ያየናቸው የጎሳ ግጭቶች የጎሳ ብሄርተኝነት እና አስተዳደር ውጤት ናቸው ማለት ይቻላል።

በቅርብ ታሪካችን እንደሚመሰክረው የፖለቲካዊ፤ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበረሰባዊ ግጭቶች ሁሉ በ«ጎሳ ፖለቲካዊ ውድድር» ዙራይ (ethnic political competition) ነው የሚከሰቱት። ይህ ውድድር በመሬት፤ የፖለቲካ ስልጣን፤ ንብረት ክፍፍል ወዘተ ሊሆን ይችላል። «ይህ መሬት የኛ ነው»፤ «ይህ ስልጣን ለኛ ይገባል»፤ «ይህ መዓድን ውጤት ለኛ ነው መሆን ያለበት» ወዘተ እየተባለ ወደ አጉል ውድድር፤ ፉክክር እና ግጭት ይኼዳል። ይህን በተግባር አይተናል እያየንም ነው።

በምንድነው ይህ የጎሳ ውድድር ከሌሎች ፖለቲካዊ ውድድሮች የሚለየው? በምን መንገድ ነው ከአካባቢ፤ ርዕዮት ዓለም፤ መደብ፤ ጥቅም ወዘተ የፖለቲካ ውድድሮች የሚለየው? ለምንድነው ጤናማ ያልሆነው? ልዩነቱ ጎሳ ከሰው ማንነት ጋር የተቆራኘ እና በቀላሉ መቀየር የማይቻል ነገር ስለሆነ ነው። አካባቢ፤ ርዕዮት ዓለም፤ መደብ፤ ጥቅም ይቀያየራሉ። ዛሬ አዲስ አበባ ነገ አምቦ መኖር ይቻላል። ዛሬ ማርክሲስት ነጋ ካፒታሊስት መሆን ይቻላል። ዛሬ ድሃ ነገ ሃብታም መሆን ይቻላል (ሳይቻል ሲቀር ደግሞ ይህም ኃይለኛ ግጭት የመጣል)። እነዚህ መስፈርቶች የሰው ልጅ ማንነት ላይ ሚና ቢኖራቸውም ሚናው መጠነኛ ነው። መቀየር ይቻላል ብዙ ጊዜም እንቀይራቸዋለን። ግን ጎሳ ወይንም ሃይማኖት የማንነት ታላቅ ክፍል ናቸው እና ባብዛኛው አይቀየሩም። ጎሳ በዚህ መልኩ ከሰው ልጅ ማንነት ጋር አጥብቆ ስለተያያዘ በጎሳ በኩል የሚመጣ ውድድር እጅግ የከረረ እና አከፋፋይ ነው የሚሆነው።

አልፎ ተርፎ የጎሳ ልዩነት እና የጎሳ ብሄርተኝነት በበዛበት ስፍራ ሁሉ ጥያቄዎች/ውድድሮች «የጎሳ መልክ» ይይዛሉ። ለምሳሌ የጎሳ ብሄርተኝነት በሌለበት ቦታ በአንድ ድርጅት እና የሰራተኛ ማህበር ግጭት ካለ ግጭቱ በኩባኒያው እና ሰራተኛ ማህበር መካከል ሆኖ ይቀራል። ምናልባት ሌሎች ቁባንያዎች ከጓድ ኩባኒያቸው ጋር ይወግኑ ይሆን እና ሌሎች የሰራተኛ ማህበራት ከጓድ ከሰራተኛ ማህበራቸው ጋር ይወግኑ ይሆናል። የከረረ ጎሰኝነት ባለበት ቦታ ግን ኩባንያውም የሰራተኛ ማህበሩም በጎሳ ይሰየማሉ እና ጎሳዎች ከኋላቸው ይሰለፋሉ። ለምሳሌ የኩባንያው ባለቤት ኦሮሞ ከሆነ ኦሮሞዎች ከሱ ጋር ይሰለፋሉ ሰራተኞቹ ደግሞ ባብዛኛው ጉራጌ ከሆኑ ጉራጌዎች ከነሱ ጋር ይሰለፋሉ። ግጭቱ ከሰራተኛ መብት አልፎ ወደ ጎሳ ግጭት ይቀየራል። ወደ ከረረ ግጭት ይገባል። ጎሰኝነት ወይንም የጎሳ ብሄርተኝነት በአንድ ሀገር ሲበዛ ይህ ነው አንዱ አደጋ እና የግጭት መብዛት መንጭ።

ግን ይህ አደጋ እንዳለ ሆኖ ከላይ እንዳልኩት አንድ ሰውን የጎሳ ማንነትህን ተው ማለት አይቻልም። መብቱ ነው ማንነቱ ነው ምንም ትክክል ባይመስለን ወይንም በሃሰት የሆነ ሃሳቦች የተመሰረተ ነው ብንልም የሌላ ሰው ማንነትን አስገድዶ መቀየር አይቻልም (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_34.html)። አልፎ ተርፎ ሰውን በማንነቱ ጥንቃቄ በሌለው መንገድ ከተቸነው ይበልት እንዲከርር ነው የምናደርገው። በተለይም የጎሳ ማንነቱ በብሶት የተመሰረተ ከሆነ። ካልተጠነቀቅን አክራሪ ያልሆነውንም ወደ አክራሪነት እንገፈዋለን። ለምሳሌ «እኔ ኦሮሞ መጀመርያ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ ነኝ» የሚለው ኦሮሞ ማንነቱን ከተቸነው ወይንም ከተከራከርነው በማንነቴ አትምጡብኝ ብሎ ጭራሽ ኢትዮጵያዊነቱን ትቶ ወደ ኦሮሞነት ብቻ ሊያመራ ይችላል። ይህ የሚሆነው በስሜት ደረጃ ነው። «ይህ አደጋ ነው እና ኦሮሞ ብቻ ነኝ አትበል ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ነኝ በል» ማለት ሁኔታውን ያባብሳል ጎሰኝነቱን ይጨምራል።

ጥንቃቄ ያስፈልጋል ስንል ግን እውነት አይነገር አይደለም። ግን «ኦሮሞ አትሁን» አይነቱን አሉታዊ አስተያየት ከመሰንዘር ይልቅ በአዉንታዊው ማተኮር ነው። አዎን የጎሳ ብሄርተኝነት አደጋ እንደሆነ በግልጽ መናገር ጠቃሚ ነው። ግን ከዚህ ጋር አብሮ የጎሳ ማንነቱ እንዴት አለ ጎሳ ብሄርተኝነት (nationalism) ማስተናገድ እንደሚቻል መግለጽ ይኖርብናል። ማንነቱ በኢትዮጵያዊነት እንዲንጸባረቅ ማድረግ እንደሚቻል ማሳየት አለብን። ለምሳሌ አንድ እንደዚህ አይነት አውንታዊ ሃሳብ ኦሮምኛ ከአማርኛ እኩል የፌደራል መንግስት ቋንቋ ማድረግ ጥሩ ነው የሚለው አቋም ነው። ይህ አቋም የሚልከው መልእክት «አንተ ኦሮሞ ነህ፤ ኢትዮጵያም ኦሮሞ ናት» የሚል ነው። ማንነትህ በኢትዮጵያዊነት ተታክቷል ማለት ነው። እንዲህ አይነት አውንታዊ መርህ እና መልእክቶች ናቸው ሰው ወደ ጎሳ ብሄርተኝነት እንዳይገባ የሚረዳው ወይንም ከጎሰኝነት ወደ ኢትዮጵያዊነት እንዲያመዝን የሚያደርገው።

በሌላ በኩል ስለምናስተላልፈው መልዕክቶች መጠንቀቅ ያለብን እንዲህ ነው። ብዙ ጊዜ የጎሳ ብሄርተኝነት «ጥላቻ»፤ «ዘረኝነት»፤ «ጠባብነት»፤ «የፖለቲካ ነጋዴዎች ጭዋታ» ወዘተ ተብሎ ይሰየማል። እነዚህ በሙሉ የተወሰነ እውነታ አላቸው። ግን ሙሉ እውነታው አይደለም። በድፍኑ እንዲህ ማለቱ በርካታ ለዘብተኛ የሆኑ የጎሳ ብሄርተኞች ወይንም ገና አቋማቸውን ያልወሰኑ በመሃል የሚንሳፈፉ ሊያስቀይም እና ይበልጥ ወደ ጎሰኝነት ሊገፋቸው ይችላል። «ማንነቴ ኦሮሞ ነው ስላልኩኝ ዘረኛ ነኝ እንዴ» ብሎ ይበሳጫል። እንዳልኩት የጎሳ ማንነት በጣም ስሜታዊ ነገር ነው እና መተቸት አይወድም። ስለዚህ ስንተቸው በትክክል እና precise መንገድ መሆን አለበት። ለመልሶ ትችት የማይመች መሆን አለበት። ስለዚህ ዘረኛ አመለካከት ስንሰማ ይህን አመለካከት ዘረኛ ነው ማለት ተገቢም አስፈላጊም ነው። ወደ ኋላ ማለት እና መሸማቀቅ ጎጂ ነው። ግን በጅምላ ዘረኞች ናችሁ ካለን ሁኔታዎች ያባብሳል። በጠቅላላ የጎሳ ብሄርተኝነትን መቀነስ የምንፈልግ የማስተላልፈው ምልዕክቶአችንን ተጠንቅቀን ማርቀቅ አለብን። ልድገመው፤ የሰው ልጅ ማንነቱ ሲተችበት አይወድም።

ለማጠቃለል ያህል፤ የጎሳ ብሀኢርተኝነትን አቋም መያዝ መብት ነው። ግን የጎሳ ብሄርተኝነት እና የጎሳ ፌደራሊዝም የግጭት እና ሁከት ምንጮች ናቸው። በዚህ ምክንያት ነው የምንቃወማቸው።  በመሰረቱ ክፉ፤ ዘረኛ፤ ጠባብ ወዘተ ስለሆነ ሳይሆን የግጭት ምንች ስለሆነ ነው። ይህን በጽንሰ ሃሳብም በተግባር አይተነዋል። የጎሳ ብሄርተኝነትን ለመቀነስ ትጠንቅቀን መስራት አለብን በተለይ በምናስተላልፈው መልዕክቶቻችን ትክክለኛ እውነት ግን በጅምላ የማይፈርጅ እንዲሆኑ ማድረግ አለብን። የሰው ማንነትን አክብረን ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ውስት ይህ ማንነት በድምብ እንዲካተት በአውንታዊ መልክ መስራት አለብን።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!