Thursday 25 October 2018

የሀገራችን የኢትዮጵያ ድህነት «የንስሐ ፖለቲካ» ነው!

የንስሐ ፖለቲካ ምን ማለት ነው? «ንስሐ» በመጀመርያ ስህተትን መገንዘብ እና ማመን ማለት ነው። «ተሳስቻለሁ»፤ «አውቄም ሳላውቅም አጥፍቻለሁ»፤ «በድያለሁ»፤ «የውሸት መንገድ ተከትያለሁ» ብሎ ማመን ነው የመጀመርያ የንስሐ ተግባር።

ይህ ስህተትን ማመን ብዙ ጥቅም አለው። በመጀመርያ እውነትን እንድናውቅ እና እንድናምን ያደርጋል። ለምሳሌ አንድ ፖለቲከኛ በማርክሲዝም አምኖ ሰዎችን «ጸረ አብዮት» ናችሁ ብሎ ጨቁኗል እንበል። ይህ ሰው መሳሳቱን ሲያምን አብሮ ማርኪስዝም ውሸት ነው፤ እውነቱ ስብዓዊነት ነው ብሎ ያምናል ማለት ነው። ንስሐው እውነትን እንዲረዳ እና እንዲቀበል አደረገው።

ሌላው የንስሐ ጥቅም የመንፈስ እርካታ ነው። የስህተት እና ሓጢአት ሸክም ከባድ ነው። ይቅርታ ስንጠይቅ ይህ ግዙፍ ሸክምን እናወርዳለን ማለት ነው። ሸክሙ ሲወርድልን ስራችንን በአግባቡ እንድንሰራ ይጠቅመናል።

ሶስተኛ የንስሐ ትቅም ተጎጂን ማጽናናት ነው። የሰው ልጅ «ይቅርታ አድርግልኝ» ሲባል ልቡ ይለሰልሳል እና ይረካል። ከበቀል ወደ ሰላም ይመለሳል። ይህ የልብ እርካታ እዚህ ላይ አይቆምም። በዳዩ ይቅርታ ሲጠይቀው ተበዳዩም የራሱን ስህተቶች እንዲገነዘብ ይረደዋል። የራሱን ስህተቶች እንዲያምን እና ይቅርታ እንዲጠይቅ ይገፋፈዋል። በዚህ መንገድ የይቅርታ፤ መግባባት እና ቅራኔ መፍታት መንፈስ በማህበረሰቡ ይንሰራጫል።

ሌላው የንስሐ ትቅም ስህተትን አውቆ ማረምያውንም ማወቅ ነው። አንዴ ስህተታችንን ካመንን ለችግሩ መፍትሄውን ማግኘት እንችላለን። በተቃራኒው ስህተታችንን ካላመንን ችግራችንን መፍታት አንችልም። ይህ ሁላችንም የምናውቀው ነገር ነው። አንድ መሪ የተሳሳተ እርምጃዎች እየወሰደ እና ችግሮችን እያመጣ እያለ ስህተቱን ካላወቀ እና ካላመነ ችግሩ መቼም አይፈታም። ስህተትን ማመን የችግር መፍታት ቅድመ ሁኔታ ነው። ስለዚህ ስህተታችንን ካመንን መፍትሄ ይመጣል።

ስለዚህ የንስሐ ሁለተኛ ተግባር ለስህተታችን የፈጠረው ችግሩ መፍትሄ አግኝቶ በተግባር መዋል ነው። ይቅርታ ከጠየቅን እና ስህታችንን ላለመድገም ከማልን በኋላ እንደ ሁኔታው ካሳ እንሰጣለን። ካሳ ማለት የተፈጠረውን ችግር ማስተካከል ማለት ነው። ከሰረቅኩኝ መመለስ። ከጎዳሁኝ ማደስ። ከዋሸሁኝ እውነቱን መናገር፤ ካበላሸሁኝ ማስተካከ፤ ወዘተ። አልፎ ተርፎ እንደዚህ አይነት ስህተትን ደግሜ እንዳልሰራ ተገቢውን ጸሎት፤ ተግባር፤ ትምሕርት ወዘተ ማድረግ እና መፈጸም ነው ያለብኝ። ይህ ነው ችግሩን መፍታት ማለት፤ ማስተካከል እና እንዳይደገም የሚያስፈልገውን ነገሮችን ማድረግ።

ይህ ካደረግን በጠቅላላው የተበላሸውን አስተካከልን ማለት ነው። ወደ እውነት መመለስ ነው። «ወደ ራስ (እውነት ማለት ነው) መመለስ ነው»።

ንስሐን በዚህ መልኩ ከተረዳነው «የንስሐ ፖለቲካ» ጥቅሙን እና አስፈላጊነቱን መገንዘብ ቀላል ይመስለኛል። በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል፤ ንስሐ መግባት የችግርን መፍታት ቁንጮ ነው። ፖለቲካችንም የመሃበራዊ ሁኔታችንም በርካታ የምናውቃቸውም የማናውቃቸውም ችግሮች አሏቸው። እነዚህን ችግሮችን ምንጮቻቸውን ሳናውቅ ወይን ሳናምን እንፈታቸዋለን ማለት ሃሰት ነው። ችግሮቹ የሚፈቱት መጀመርያ ችግር እንደሆኑ ካመንን፤ የራሳችንን ድርሻ ካመንን፤ ይቅርታ ከጠየቅን፤ መፍትሔ ከፈለግን እና እራሳችንን ከቀየርን ነው። ሌላ መንገድ በሙሉ አይሰራም። አልፎ ተርፎ ይህንን መንገድ ካልተከተልን ችግሮቻችን ይቀጥላሉ እየባሱም ይሄዳሉ።

የንስሐ ፖለቲካ በተግባር በታላቅ የፖለቲካ መድረክ ያየነው በጠ/ሚ አብይ አህመድ ስራዎች ነው። ጠ/ሚ አብይ ለአለፉት የኢህአዴግ ጥፋቶች «እንደ ግለሰብ» ተሳስችያለሁ ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል። ንስሐ ገቡ ማለት ነው። ይህ በማድረጋቸው በርካታ ስኬቶች አምጥተዋል፤

1. ስህተታቸውን ተገነዘቡ እና አመኑ። ችግሮችን በአግባቡ ስለተረዱ ወደ መፍትሄ መሄድ ችለዋል።

2. ተጎጂውን በሙሉ ይቅርታ በመጠየቃቸው ህዝቡ የመንፈስ እርካታ እንዲያገኝ አድርገዋል። ብሶት እና ቂም በመጠኑ መቀነስ ችለዋል።

3. ሌሎቻችንም ለራሳችን ጥፋቶች ይቅርታ እንድንጠይቅ አስተምረውናል። ስህተታችንን አምነን የጎዳናቸውን አዝናንተን ወደ መፍትሄ እንድንሄድ ገፋፍተውናል። መሪአችን እንዲህ ካደረገ እኛም እንችላለን ነው።

4. አንጻራዊ የብሄራዊ ሰላም አምጥተዋል። ጠ/ሚ አብይ ይቅርታ በመጠየቃቸው አብዮት እና ሁከት እንዳይመጣ አድርገዋል። ሰው ይቅርታ ጠይቆ ይቅር ብሎ በሰላም እንዲኖር ገፋፍተዋል። የ«እውነት እና እርቅ» (truth and reconciliation) አይነት ሂደት ወደፊት እንዲጀመር ሜዳውን አብጅተዋል።

5. ይቅርታ፤ ትህትና እና ሃላፊነት መውሰድን በማንጸባረቃቸው የህዝብን እምኔታ አገኝተዋል።

የጠ/ሚ አብይ የ«ንስሐ ፖለቲካ» ከሞላ ጎደል በታላቁ ስኬታማ ሆኗል። አንድ ወይንም ሁለት ዓመት በፊት የአምባገነናዊ አገዛዛችን በዚህ መልኩ አለ አብዮት እና አለ ሁከት ይቀየራል ብንባል ሁላችንም አናምንም ነበር። የማሆን ነገር ነው እንል ነበር። ይህ ያልጠበቅነው ታላቅ ድል አለ «ንስሐ ፖለቲካ» አይሳካም ነበር።

እንደሚመስለኝ ከዚህ ታላቅ ትምሕርት መማር ያለብን «ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት»፤ «አንድነት» ወይን የ«ዜግነት ፖለቲካ» የምናራምደው ጎራ ነን። ደጋግሜ እንደጻፍኩት ይህ የፖለቲካ ጎራ በርካታ የሀገራችን ፖለቲካ ችግርን ያመጣ ነው። በጃንሆይ ዘመን ተሃድሶ ማድረግ ባለመቻሉ፤ ግማሹ ማርክሲስት ሆኖ አብዮት እና ሁከት በማምጣቱ፤ እርስ በርስ በመጨራረሱ፤ በኢህአዴግ ዘመን አብሮ ስርቶ ተገቢ የተቃዋሚ ኃይል ማደራጀት ባለመቻሉ፤ ወዘተ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_15.html)። እስከ ዛሬ የ«ኢትዮጵያዊነት ኃይሉ» መቢገባን ደረጃ መደራጀት አልቻልንም። ግንቦት 7 ነው ያለው ግን እሱም ከሚገባው እጅግ ትንሽ እና አቅም ያነሰው ድርጅት ነው። የሀገራችን እምብዛም ብዙሃን በ«ኢትዮጵያዊነት» የሚያምን ሲሆን ልሂቃኑ እና ፖለቲከኛው ይህን ብዙሃን ወክሎ ሊያደራጅ አልቻልም። የልሂቃኑ የክሽፈት ታሪኩ ተጭኖታልና።

የንስሐ ፖለቲካ ይህን የተጫነውን መንፈስ ያወርድላታል ብዬ አምንዳለው። ልክ እንደ ለነ ጠ/ሚ አብይ እንዳረገው። እንደ ግንቦት 7 አይነቱ ድርጅት ወደ ኋላ ሄደው እንደ ድርጅት፤ መሪዎቻቸው እንደ ግለሰብ፤ እራሳቸውን ፈትሸው ያደረጉትን ስህተቶች አምነው በይፋ ቢናገሩ ይበጃል። ስህተቱ ትንሽም ሊሆን ይችላል፤ ቅራኔን መፍታት አለመቻል ይሆናል። ግን ይህ ፍተሻ እጅግ ጠቃሚ ነው የሚሆነው። መማርያ ይሆናል።

ታሪክን በአግባቡ ፈትሾ ያሉን ችግሮች ከየት እንደተነሱ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ይህ ሲደረግ የሁላችንም ጥፋት ይታያል። ችግሩን በህወሓት ብቻ መለጠፍ ተገቢ አይደለም እውነትም አይደለም። እንደዚህ አይነት የህጻን አስተያየት ነው ችግሮቻችን በአግባቡ እንዳይታወቁ እና እንዳይፈቱ የሚያደርገው። የራስ ሃላፊነትን ማምለጫ መንገድ ነው። ለሀገራችን ችግር ሁላችንም ትልቅ ሚና ተጫውተናል፤ በመስራትም ማለመስራትም። ይህ መታመን እና መነገር ያለበት ይመስለኛል። ይህን ካደረግን ችግሮቻችንን በደምብ አውቀን ትክክለኛውን መፍትሄዎችን እናገኛለን። በህዝቡም እምኔታ እናገኛለን። ከስህተት መማር እና መሻሻል ባህል እናደብራለን። የትህትና ባህል እናደብራለን። የሃላፊነት መውሰድ ባህል እናዳብራለን። ጠ/ሚ አብይ እንደሆኑት ስኬታማ እንሆናለን።

አልፎ ተርፎ የ«ንስሐ ፖለቲካ» ከባህል እና ከወጋችን አብሮ የሚሄድ በመሆኑ ድል የመሳካት እድሉ ከፍ ያለ ነው። «ህዝባችን የዴሞክራሲ ባህል የለውም» ይላሉ የዘመኑ ምሁራናችን። «ገና መማር አለብን እና የስነ ልቦና ለውጥ ያስፈልጋል» ይባላል። ለኔ ይህ አስተያየት የሚመነጨው ከሀገራችን ባህላዊ እሴቶችን በአግባቡ አለማወቅ እና አለመፈተሽ ነው። ከ«ምዕራብ ዓለም» የጫነብን ፕሮፓጋንዳ ማመን ነው ይህ አስተያየት የሚመጣው። ግን የጢ/ሚ አብይ ስኬታማ ስራ የሚያሳየው የኛ የትህትና፤ የይቅርታ፤ የንስሐ፤ እሴቶች በፖለቲካችን ታላቅ አውንታዊ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ነው። ሌላ (የምዕራብም) ሀገር መፈጸም የማይቻል ድል ነው የጠ/ሚ አብይ አካሄድ ያመጣው! የት ሀገር ነው መሪ ለሌላ የፈጸመው ሳይሆን ለራሱ ስህተቶች ይቅርታ የሚጠይቀው? የት ሀገር ነው እንደዚህ በቀላሉ ህዝቡ ይቅርታውን የሚቀበለው?! የት ሀገር ነው ትህትና ያሚያንጸባርቅ መሪ የሚወደደው? ይህ አካሄድ ሀገራችን የሰራው ምክንያት ከሃይማኖቶቻችን ቀጥታ የመጡ እሴቶችንም ስለተጠቀመ ነው። ስለዚህ የንስሐ ፖለቲካ በመሰረታዊ ደረጃ ኢትዮጵያዊ አካሄድ ነው። የኢትዮጵያዊነት ፓርቲዎች፤ ይህን የንስሐ ፖለቲካ እንስራበት!

Tuesday 23 October 2018

ብስለት የሞላው ውይይት

ይህንን ውይይት ጠንቅቃችሁ አዳምጡት ብዬ እለምናለሁ።

https://www.youtube.com/watch?v=PY9RFsmu_ks

የተነሱት ዋና ዋና ነጥቦች፤

1.ዛሬ ያለንበት ፓለቲካዊ እና ማህበረሰባዊ ሁኔታ እና ችግሮች 27 ወይን 44 ወይን 50 ዓመት የፈጠረው አይደለም። ከዛ በፊት ያለን የረዥም ዓመታት ታሪክም አስተዋጾ ያለው ነው። ይህን አውቀን ነው ወደ እውነት እና ትክክለኛ መፍትሄ ምድረስ የሚቻለው።

2. ራስን መመርመር ግድ ነው። ችግሮቻችን በመንግስት እና በፖለቲከኞች ምክንያት ነው የመጣው ማለት ልክ አይደለም። እውነት አይደለም። ሁሉም ዜጋ በራሱ በኩል ሚና ተጫውቷል እና ላለፈውም ለወደፊቱም ሃላፊነት መውሰድ አለበት።

3. ፖለቲካ አንድ የማህበረሰባዊ ኑሮ ክፍል ነው። በመሆኑ ሁሉ ዜጋ በአቅሙ እና በአግባቡ መሳተፍ አለበት። እናት እንደ እናት፤ አባት እንደ አባት፤ ልጅ እንደ ልጅ፤ ሃይማኖት መሪ እንደ ሃይማኖት መሪ፤ ምሁር እንደ ምሁር፤ ሰራተኛ እንደ ሰራተኛ ወዘተ።

4. የግብረ ገብ እጦት ታላቅ ችግር ነው እና ሊሰራበት ይገባል። እንደማንኛውም ችግር ይህ ችግር የሚፈታው መጀመርያ አመጣጡ፤ ምክንያቱ እና ምንጩ ሲታወቁ እና ሲታመኑ ነው።

5. ለውጥ ማለትም ወደ የተሻለ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ሁኔታ መቀየር ጊዜ ይፈጃል። ትዕግስት ይጠይቃል። ምርጫ እና ተመሳሳይ ስርዓቶች አለ ቅድመ ዝግጅት እና የአስተሳሰብ ለውጥ ጎጂ ነው የሚሆኑት።

6. ዛሬ ከሞላ ጎደል የፖለቲካ «ነፃነት» አለ። ቋሱ በኛ በህዝቦቹ ሜዳ ነው ያለው። ችግር ካለ መፍታት የኛ ሃላፊነት ነው። ሃላፊነታችንን እንደ ዜጎች መቀበል ግድ ነው። በሌላ ለምሳሌ በመንግስት ባሳበብ አብቅቷል።

Sunday 21 October 2018

የዜግነት ፖለቲካ ከባድ ነው!

አንታለል፤ የዜግነት ፖለቲካ ከባድ ነው። የንጉሳዊ አገዛዝ እና ማርክሲዝምን የለመደ ህብረተስብን ወደ ዜግነት ፖለቲካ ማስገባት ግዙፍ ሸክም መጎተት ማለት ነው። የዜግነት ፖለቲካ እንደ ጎሳ ፖለቲካ ተጨቁነናል፤ ተንቀናል፤ ደምና አጥንታትችን አንድ ነው፤ ሀገሪቷ ችግር ውስጥ አለች እና እየተጠቃን ነው ስለዚህ ወደኛ ተሸግሸጉ፤ ወዘተ ብሎ ድጋፍ መሰብሰብ ያችልም።

1. የዜግነት ፖለኢትካ primordial አይደለም። ህዝብን ሆ! ብሎ መሰብሰብ አይችልም። ስልት ያስፈልገዋል። ስልት አያስፈልገኝም እና በstreet ፖለቲካ ልሳተፍ ማለት አይችልም። ይህ ውድቅ የነ አካሄድ ነው።

2. የዜግነት ፖለቲካ ከጎሳ ፖለቲካ ጋር ያለው ግንኝነት asymmetric ነው። ከጎሳ ፖለቲካ ጋር በተመሳሳይ ታክቲክ ፊትለፊት ግብ ግብ ልግባ ካለ ይሸነፋል። ምክንያቱ የጎሳ ፖለቲካ የስሜታዊ advantage አለው። ለምሳሌ 1) የጎሳ ፖለቲካ ከተተቸ «ጎሳዬ እየተጠቃ ነው» ብሎ ይጮሃል። እንዲህ ሲጮህ ለዘበተኞቹንም ወደሱ ሊያመጣ ይችላል። 2) የሀገሪቷ ጠቅላላ ሁኔታ (ፖለቲካ፤ ኤኮኖሚ፤ ጸትታ ወዘተ) እየተበላሸ ከሄደ የጎሳ ፖለቲካ «የነሱ የጠላቶቻችን ጥፋት ነው» ይላል። «ወደኛ ተሸሸጉ» ይላል። እንዲህ በማለት ተከታይ ይሰበስባል። ስለዚህ ይህን asymmetric ሁኔታ ተገንዝበን ተገቢውን ስልት መጠቀም አለብን።
ሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከቅራኔ መፍታት ዘገምተኝነት በሽታ ይጠቃል (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html)። ምቀኝነት፤ በግልጽ አለመነጋገር፤ አለመቆርቆር (empathy)። መጠርጠር። ሃሳብ እና ግለሰብን ማቆራኘት። ወገናዊነት። ስም ማጥፋት። ቂም። ግትርነነት ወዘተ። በነዚህ ምክንያት በርካታ ጊዜ የራሳችንን ጥቅምንም እንጎዳለን ሌላውን ለማጥቃት ስንል! በዚህ ምክንያት ነው አብሮ መስራት፤ ቅራኔ መፍታት እና win-win ሁኔታዎችን ማየት እና መፍጠር የሚያቅተን። ይገ ዜግነት ፖለቲካም የጎሳ ፖለቲካም እነዚህን ችግሮችን ማሸነፍ አለባቸው። ግን ለጎሳ ፖለቲካ ይቀላል። «ጠላት አለን» የሚባለው ነገር ሰውን ሳይፈልግም እንዲተባበር ያደርጋል። የሚአይተባበሩ ደግሞ ሀውሓት፤ ሻዕቢያ፤ ኦነግ ሌሎች የጎሳ ድርጅቶች እንዳሳዩት በቀላሉ ይረሸናሉ። የ 'survival' ጉዳይ ነው ተብሎ ይሳበባል። የዜግነት ፖለቲካ ግን ይህን አማራጭ የለውም። ከባድ የሆነውን የፖለቲካ ባህል ለውጥ ስራን ግድ መስራት አለበት።

3. የዜግነት ፖለቲካ ለዘብተኛ እና መካከለኛውን መንገድ መውሰድ አለበት። ጽንፈኝነት በጎሰኞቹ ተቆጣጥሯልና። የዜግነት ፖለቲካ ሁሉንም አይነት ፍላጎት በተቻለ ቁጥር ሚዛን ላይ አድርጎ ማስተናገድ አለበት። «ትልቅ ዛንጥላ» መሆን አለበት፤ አቃፊ መሆን አለበት። የዜግነት ፖለቲካ የማስወገድ፤ የመግደል፤ የመረሸን፤ የመጨቆን፤ የማጥቃት ወዘተ አማራጭ የለውን። እንዲዚህ ነገር ውስጥ ከገባ የዜግነት ፖለቲካ ማንነቱን ያጣልና የጎሰኝነት ፖለቲካውን ይሆናል። በጎሳ ፖለቲካው ይሸነፋል። ምሳሌ ልስጥ፤ ዛሬ ዜግነት ፖለቲካ ደጋፊዎች ሁለት አይነት አስተሳሰብ አለ ስለ ጎሳ ፖለቲካ። የአንዱ አቋም «ህገ መንግስቱ ዛሬውኑ ካልተቀየረ አቃቂ ዘራፍ» የሚል ነው። ብዚህ ጉዳይ ድርድር የለም ይላል። ሌላው ጎራ ደግሞ «ህገ መንግስቱ መቀየር አለበት ግን ይህን ለማድረግ ገና አሁን ወቅቱ አይደለም፤ መጀመርያ ንግግር እና ድርድር ማድረግ አለብን» ይላል። ሁለተኛው ነው ለዘብተኛውም ሚዛናዊውም መንገድ። ይህ ለዜግነት ፖለቲካ ግድ ነው።

4. ችግር እና ሁከት የዜግነት ፖለቲካን ይጎዳል የጎሳ ፖለቲካን ያጠነክራል። (ያው ይህ ይሚያስኬደው እንደ ኢትዮጵያ አይነት የጎሳ ፖለቲካ ያለበት ሀገር ነው።) ችግር ሲኖር ሰው ወደ ጎሳ የመሸግሸግ ባህሪ አለው። የደርግ ሁከት እነ ሻዕቢያ፤ ህወሓት እና ኦነግን በጣም አጠነከረ። ዛሬም አማራ ላይ ጥቃት ሲፈጸም የአማራ ብሄርተኝነት ንቅናቄ እየጠነከረ ይሄዳል። ስለዚህ የዜግነት ፖለቲካ በአብዮት መምጣት አይችልም አብዮት ሁከት ነውና። ብዙዎቻችን ኢህአዴግ በአብዮት («ስር ነቀል ለውጥ») መገልበጥ አለበት ስንል የአብዮቱ ውጤት የዜግነት ፖለቲካ ይሆናል ብለን አስበን ነበር። ይህ ታላቅ ስህተት ነው። ዛሬም የዜግነት ፖለቲካ ጭላንጭል ማየት የቻልነው ለውጡ አለ አብዮት ስለመጣ ነው። አለ ሁከት ስለመጣ ነው።

5. ሁላችንም እንደምናውቀው የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች እስካሁን ታሪካችን ጥሩ አይደለም። ፖለቲከኞቻችን፤ ጋዜጠኞቻችን አክቲቪስቶቻችንም አብሮ መስራት አልቻሉም። የቅንጅት ታሪክ ይህን ታላቅ ሽንፈታችንን በድምብ ይገልጻል። ይህ በመሆኑ ዛሬ የዜግነት ፖለቲካ ድርጅቶች እጅግ ደካማ ናቸው። የዜግነት ፖለቲካ የሚደግፈው ብዙሃን ብዙ ነው፤ ይህ የቅንጅት ታሪክም ይመሰክራል። ግን ይህ ግዙፍ ብዙሃን በድርጅት፤ ልሂቃን እና ፖለቲከኛ በአግባቡ አልተወከለም። ስለዚህ ዛኢረ የዜግነት ፖለቲካ የመጀመርያ ግብ መዋቅር ማለትም ድርጅትን ማጠንከር ነው መሆን ያለበት። አለ በቂ መደራጀት ምንም ማድረግ አይቻልምና። ሁሉም የዜግነት ፖለቲካ ተቀናቃኞች ሙሉ አቅማቸውን (resources) በዚህ ጉዳይ ላይ ማዋል አለባቸው። ምርጫ የለም። ሌሎች የጊዜያዊ ስራዎች ውሃ ቀዳ ውሃ ድፋ ነው የሚሆነው። ለዜግነት ፖለቲካ strong organizations are a precondition to any success።

6. የዜግነት ፖለቲካ ገና መደራጀት ላይ ስለሆነ ጠላትን ማፍራት የለበትም። እንደ ጠ/ሚ አቢይ ሁሉንም ማቀፍ መቻል አለበት። ጠላት ካፈራ የመደራጀት ስራው ይደናቀፋል። ስለዚህ ሌሎችን በአግባቡ በጥሩ ሁኔታ ይዞ የራሱን ስራ መስራት ነው ያለበት። ይህ basic ፖለቲካ ነው ግን አንዳንዶቻችን ፖለቲካን እንደ ሃይማኖት ጥቁር እና ነጭ አድርገን ስለምናይ ወደ ቀላል ስህተት እንገግባለን። ገና ሳንደራጅ፤ ገና ሳንጠነክር ወደ ጦርነት ካልገባን እንላለን። ይህ ለዜግነት ፖለቲካ አይሆንም።

7. «የወሬ ፖለቲካ» ለዜግነት ፖለቲካ አይሆንም። የወሬ ፖለቲካ ማለት ተቃራኒዎችን በወሬ ዘመቻ ማጥቃት እና የራስን ወገን እንደ ሰለባ አድርጎ ማውራት። የጥላቻ ፖለቲካ ማለት ነው። የወረ ፖለቲካ አላማው ህዝቡ ተናዶ እንዲነሳ ማድረግ ነው። ካላይ እንዳስረዳሁት ህይ አይነት አካሄድ ለጎሳ ፖለቲካ ነው የሚጠቅመው እንጂ የዜግነት ፖለቲካ (ስሜታዊ ስላልሆነ) እንዲህ አይሰራም። ለዚህ ደግሞ የ27 ዓመት ማስረጃ አለን። ለ27 ዓመት እኛ ተቃዋሚዎች ወያኔ ሴጣን ነው ብለን ብንቾህ ምንም አልሰራም። ለውጡ የመጣው ህዝቡ የትግሬ የባላይነት በተግባር ሰልችቶት ነው እንጂ ኢሳት ስለነገረው አይደለም። ለ27 ዓመት ስለ ወያኔ ከማውራት አቅማችንን በመደራጀት ስራ ብናውል ወያኔ ገና ድሮ ወርዶ ነበር።

8. አንዱ ከላይ ከጠቀስኳቸው የፖለቲካ «ጎጂ ባህሎች» የሁሉም አሸናፊ (win-win) ውጤት አለማወቅ ነው። ይህ እንዳልኩት የዜግነት ፖለቲከኞች እና ተቀናቃኞች ይበልጥ የሚጠቁበት በሽታ ነው። (የጎሳ ፖለቲከኞች በጎሳ ስሜት ስለሚቆጣጠሩ ይህ ችግር ቢኖራቸውም አነስተኛ ነው።) ይህ በቅንጅት እና ቀጥሎ ባለው ታሪክ በደምብ ይታያል። ገና ትንካሬ ሳይሰበሰብ ስለ ፖለቲካ ክፍፍል ማሰብ፤ ስለ ስልጣን ማሰብ። ትንሽ ስልጣን በግዙፍ መዋቀር ከሚኖረኝ ትልቅ ስልጣን በባዶ መዋቀር ይሻላል የሚል አስተሳሰብ ነው። ይህን ማስወገድ ማለት አለብን። አብሮ ከሰራን ትልቁን ውጤት አምጥተን ለሁላችንም በቂ ስልጣን ይኖራል (ፖለቲከኞች)።

9. ባለፉት የ50 ዓመት የፖለቲካ ታሪካችን በተለይም አብዮት እና ሁከት የዜግነት ፖለቲካ ወይንም የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ልሂቃን ጎራ ተገድሎ፤ ተሰድዶ፤ እርስ በርስ ተፋጅቶ ቁጥሩ መንኗል (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_38.html)። የዜግነት ፖለቲካ መዋቅሮቻችን የደከሙበት ምክነያት አንዱ ይህ ነው። እነ ኃይሉ ሻውል፤ ብርሃኑ ነጋ እና ልደቱ አያሌው የቅንጅት ዋና መሪዎች ሆነው ሲገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ልሂቃን ሞትዋል፤ ተሰዷል ወይን ፖለቲካ ኮሬንቲ ነው ብሎ ትቶታል። ስለዚህ እነ ብርሃኑ ነጋ ከዚህ የተረፉት ጥቂቶች ናቸው። እነሱ ሲደናቀፉ የሚደግፋቸው ወይንም ቦታቸውን የሚወስድ ማንም አልነበረም። የህ የልሂቃኑ መመንመን ዛሬም ሚና ይጫወታል። ሁለት የዜግነት ፖለቲካ ልሂቃን ትውልድ ነው ያጣነው። አዲሱ ትውልድም «አለ አሳዳጊ» ነው ያደገው። ይህን ችግር ተገንዝብን የሚያስፈልገውን የአካሄድ ለውጦች ማድረግ ይኖርብናል።

10. እውናትዊ የዜግነት ፖለቲካ ለብዙ አይነት ሃሳቦች መቆርቆር አለበት (empathy)። ሚዛናዊ መሆን ስላለበት። አንዱ የብዙ የዜግነት ፖለቲካ ተከታዮች ችግር ለጎሳ ፖለቲካ ምንም አለመቆርቆር ነው። የጎሳ ፖለቲካ ከዘረኝነት ውጭ ምን እንደሆነ አይገባንም ወይንም ሊገባን አንፈልግም። ይህ ታልቅ ድክመት ነው። ሌላውን አለማወቅ፤ ተቃራኒውን በአግባቡ አለማወቅ ታልቅ ሽንፈትን ያመጣል። የጎሳ ፖለቲካ ዓለም ዙርያ ያለ ነገር ነው ከነ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ። «ዘረኝነት ነው» ብሎ መሰየሙ የውሸት ማቅለልያ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2017/11/whats-ethnic-nationalism-again.html)። እውነት ነው በርካታ ዘረኞች የሆኑ ጎሳ ብሄርተኞች አሉ። ግን «ዘረኝነት» የጎሳ ፖለቲካን ሙሉ በሙሉ አይገልጸውም። የጎሳ ብሄርተኝነት ጎሳውን እንደ ሀገር (nation) ማየት ማለት ነው። ይህ ደግሞ ስሜት ነው፤ ማንነት ነው። እንደዚህ አይነት ነገር በlogical ሙግት አይቀየርም። ስልት ያስፈልጋል። ለዘብተኞቹን ማቀፍ ያስፈልጋል። ህዝብን በመቀላቀል አንዱ የሌላውን ቋንቋ እንዲያውቅ ብማድረግ የሃገር ውስጥ መዘዋወር እንዲጨምር በማድረግ ህዝብ እንዲወሃድ መባድረግ ነው ችግሩ የሚፈታው። ዝም ብሎ መጮህ ጉዳት ነው የሚያመጣው። የለዘብተኛ (moderate) አስተሳሰብ ነው እንዲህ አይነቱን ነገር ሊገነዘብ የሚችለው።

Friday 19 October 2018

የአለክሳንደር ሶልዠኒትሲን መልዕክት ለኢትዮጵያ

ታላቁ የሩሲያ ደራሲ አለክሳንደር ሶልዠኒትሲን ያሉትን በደምብ ሊገባን ይገባል፤
«ከእስርቤታችን አልጋ የሆነው የበሰበሰው ገለባ ላይ ጋደም ብዬ ነው ለመጀመርያ ከውስጤ የበጎ መንፈስ የተሰማኝ። ቀስ በቀስ መረዳት የጀመርኩት ይህ ነው፤ ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር በሀገሮች፤ መደቦች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መካከል አይደለም የሚያልፈው፤ ይህ መስመር የሚያልፈው በያንዳንዱ የሰው ልብ መኻል ነው። መስመሩ እድሜአችን በሙሉ ከውስጣችን ወደፊት ወደኋላ ይላል። በክፉ የተሞሉ ልቦችም ቢያንስ ቅንጣት ያህል ጥሩነት ይኖራል፤ ከሁሉም ጥሩ ከሚባለውም ልብ ከአንድ ጥጓ ትንሽ ክፉነት ይኖራል።
በየቦታው እየዞሩ ያሉ ክፉ ስራ የሚሰሩ ክፉ ሰዎች ቢኖሩና እነሱን ከኛ መለየትና ማጥፋት ብቻ ቢሆን ኖሮ እንዴት ቀላል ነበር? ግን ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር ከያንዳንዱ የሰው ልጅ ልብ መካከል ነው የሚያልፈውና ማን አለ ከራሱ ልብ ቁራጭ ቆርጦ ለማጥፋት ፈቃደኛ ይሆነ?»

የወሬ ፖለቲካ

እኛ ኢትዮጵያ ብሄርተኞች ለ27 ዓመት ወያኔን ከመውቀስ ሌላ ስራ ባለመስራታችን የወያኔን ለሩብ ክፍለ ዘመን እንዲገዛ አደረግን። በቂ ጸረ-ወያኔ ፕሮፓጋንዳ ካሰራጨን ህዝቡ በአመጽ ይነሳል ብለን ገምተን ይሆናል ግን አልሆነም። በመጨረሻ አመጹን ያስነሳው ህዝቡ በእውን የትግሬ አድሎ በዝቶበት ነው። የትግሬ አድሎ አለ ብሎ በነ ኢሳት ስለተነገረ ሳይሆን ህዝቡ በለት ኑሮው ስላየው ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/10/ethnic-federalism-kills-meles.html)።

ስለዚህ የወሬ ፖለቲካ እንደማይሰራ የ27 ዓመት ማስረጃ አለን። እኛ ኢትዮጵያ ብሄርተኞች 100% ጊዜአችንን ስለ ወያኔ በማልቀስ ከማዋል ፋንታ 50%ኡን ህዝብ እና ልሂቃንን በማደራጀት ብናውለው የት ደርሰን ነበር።

አሁንም አንዳንድ ጓዶቻችን የወሬ ዘመቻ በጎሳ ብሄርተኞች እና አሁን በ ጠ/ሚ አቢይ ማካሄድ ጠቃሚ ይመስላቸዋል። የድሮውን ስህተት መድገም። ለ27 ዓመት ያልሰርዋን መቀጠል። ምን ማለት ነው የማይሰራን ነገር መደጋገም?

ምን አልባት ውስጣችን ማደራጀት እና ሌሎች የእውነት የፖለቲካ ስራዎች ከባድ እንደሆኑ ስለምናውቅ ወሬ ላይ በማተኮር ማምለጥ እንፈልግ ይሆን። ወይንም ሻዕብያ እና ህወሓት ግዙፍ በህዝባቸው ጽናት ግዙፍ ድርጅቶች ሆነው ሲገኙ እኛ ኢትዮጵያ ብሄርተኞች የነሱን 1% የሚያክል ድርጅት መመስራት ስላቃተን አፍረን ይህንን ላለማየት ይሆን ወደ ወሬ ፖለቲካ የምንሸሸው። የዝቅተኛ ስሜት አድሮብን ይሆን 6% ድጋፍ ያለው ወያኔ ለ27 ዓመት ሲገዛን አንድ ጠንካራ ድርጅት መፍጠር ባለመቻላችን?

ምክንያቱ ምንም ቢሆን የወረ ፖለቲካ አይሰራም እና ካሁኑኑ አቅማችንን ከዛ ወደ ከባድ ስራው ወደ መደራጀት ማሸጋሸግ አለብን። ይህ ማለት ካሁን ወድያ ወሬ ሳይሆን ስራ መስራት። መሳደብ ሳይሆን ብልጥ ሆኖ ትብብሮችን መፍጠር ለጊዜውም ቢሆን እስከንደራጅ። ድልዲዮችን ከማቃጠል መጠቀም። እንደ ጠ/ሚ አቢይ አይነቱን ከማራቅ ማቀፍ እና መጠቀም። ይህ ነው ፖለቲካ። እንጂ ዝም ብሎ ማውራት መገዛት ማለት ነው።

Don't make enemies before you can fight!

ቆቅ ሞቷን ጠራች ይባላል።

የኢትዮጵያ ብሄርተኞች በቂ እንዳልተደራጀን የታወቀ ነገር ነው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያላቸው ድርጅቶች ሊኖርን ይገባል ግን የለንም። በርካታ ሚሊዮኖች ብዙሃን አለን ግን ልሂቃን፤ መሪ እና ድርጅት ላይ እጅግ ደካማ ነን።

በተዘዋዋሪ የጎሳ ድርጅቶች ያው የጎሳ በመሆናቸው ትብብር እና አንድነት ስላላቸው ጠንካራ ናቸው። ሁከት እና ችግር ስለሚያጎለብታቸው እየጠነከሩም እየሄዱ ነው።

በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ዋና ስራ መደራጀት እንደሆነ ግልጽ ነው። የህልውና ጉዳይ ነው። የዜግነት ፖለቲካችንን ካላራመድን እና ግዙፍ ድርጅቶች ካልፈጠርን እኛም ሀገራችንም እንጠፋለን። ጠ/ሚ አቢይ ቢፈልግም ይህን ሊያደርግልን አይችልም። እኛ የራሳችንን ድርሻ ካልሰራን እሱም አቅም ያጣል። ለነገሩ እስከ ዛሬም ሀገራችን ላሳለፈችው ችግር ዋና ምክንያት የኛ በሚገባው አለመደራጀት ነው።

በዚህ ሁኔታ፤ ደካማ ሆነን፤ ዋና ስራችን እራሳችንን ማጎልበት እና ማደራጀት በሆነበት ጊዜ ጠላቶች ማፍራት ጅልነት ነው። አሁን ሁሉንም የማቀፍ ጊዜ ነው። የጊዜ መግዥያ ጊዜ ነው። ጠ/ሚ አቢይ፤ የጎሳ ብሄርተኞች፤ ህወሓት ወዘተ ሁሉንም ተጠንቅቀን ይዘን ወዳጅ መስለን መገኘት አለብን። የመደራጀት ስራችንን መስራት ነው ያለብን። ብልህ ፖለቲካ ማለት ይህ ነው።

ለምሳሌ የአዲስ አበባ ሲቪክ ድርጅት ለማቋቋም ሲጀመር ስለ ከንቲባው አለማንሳት። ወይንም ማሞገስ። ጽሁፍ እና ፖስተሮች በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በኦሮምኛም ማዘጋጀት። አዲስ አበባ ለአዲስ አበቤዎች አይነት መፈክር ትቶ በቀላሉ «ለአዲስ አበባ ነዋሪ ሁሉ መብት ማስከበር» ነው ተልዕኯችን ማለት ነው! ወዘተ። ሀሳቡ ግልጽ ይመስለኛል።

ግን ይህን ከማረግ ፋንታ እንደ ቆቛ እንጮሃለን! ምንም ሳይኖረን አፍ ብቻ እንሆናለን። ባለን ጊዜ አንዴ ከጎሳ ብሄርተኞች ጋር አሁን ደግሞ አንዳንዶቻችን ከጠ/ሚ አቢይ ጋር ግብ ግብ እንገባለን። ገና ለመታገል አቅም ሳይኖረን ጠላቶች እናፈራለን። ይህን ማቆም አለበን፤ የህልውና ጉዳይ ነው። የ50 ዓመት የፋራ ፖለቲካችንን ማቆም ካላቆምን ሌላ እድል የሚኖረን አይመስለኝም።

አካሄዳችን መሆን ያለበት መጀመርያ ኃይልን መሰብሰብ። ይህን ለማድረግ ባይጥመንም የሚያስፈልገውን ነገር ማድረግ። ከሁሉም ጋር አብሮ መስራት ያስፈልጋል። እራስን አለማጋለጥ ያስፈልጋል። ኃይልን ከሰበሰብን በኋላ ደፈር ያሉ አቋሞች መያዝ እና ስራዎች መስራት።

በመጨረሻ ማለት የምፈልገው... ምን አልባት በመጮህ፤ መተቸት እና በመውቀስ ህዝባችን እንዲማረር እና እንዲቆጣ አድርገን በቀላሉ ይደራጃል ብለን እናስብ ይሆናል? ለዚህ ይሆን ብዙዎቻችን ዋናው የመደራጀቱን ስራ ትተን 100% ጊዜአችንን በመተቸት እና መወንጀል የምናጠፋው?

ይህ ከሆነ በጣም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። አካሄድ ውድቅ እንደሆነ የ27 ዓመት ማስረጃ አለን! ለ27 ዓመት ህወሓት እና የጎሳ ብሄርተኞች ሲረግጡን ያሁሉ ሚሊዮን ህዝብ ሆነን አንዳች ግዙፍ ድርጅት ማቋቋም አልቻልንም። የወሬ፤ ጩሀት እና ትችት ፖለቲካ አልሰራም።

ህወሓት ከስልጣን የወረደው እነ ኢሳት ህዝቡ ሀውሓትን እንዲጠላ ስላደረጉ አይደለም። ህዝቡ በለቱ ኑሮ አይቷቸው ጠልቷቸዋልና! አልፎ ተርፎኦ ይህ ጸረ-ህወሓት ዘመቻ ምንም አይነት ጠንካራ ድርጅት አልፈጠረም። ያሁሉ ዓመታት ጩሀት በኋላ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ትንሿ ግንቦት 7ን ብቻ ነው ያፈራነው።

ስለዚህ የጩሀት ፖለቲካ አይሰራም። ህዝቡን በፕሮፓጋንዳ አማርሮ ማደራጀት እንደማይቻል አይተናል። ህዝቡ በእውን በኑሮው ተማርሯል። የፖለቲከኞች ስራ ይበልጥ ተማረሩልኝ ማለት ሳይሆን ማደራጀት እና ለምሬቱ ትክክለኛ መስመር ማብጀት ነው። የኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች የፖለቲካ ልሂቃን ይህን ማድረግ አልቻልንም። እስቲ አሁን እንሞክር።

Disarmed! አለች ርዕዮት ዓለሙ

በዛሬ እለታዊ ፕሮግራም የርዕዮት ዓለም አስተያየትን (https://www.youtube.com/watch?v=b1OuvNmwxeY) በተመለከተ...

ነጥቧ ከሞላ ጎደል እንዲህ ነው፤ እነ «ቲም ለማ» ከመጀመርያዉኑ በጭፍን አምነን መከተል («መደገፍ») አልነበረብንም። ለ«ዴሞክራሲ» መታገል መቀጠል ነበረብን እና እነ «ቲም ለማ» እውነትም ዴሞክራቶች ቢሆኑ መሃል መንገድ እንገናኛለን ነው። ዛሬ እነ ጠ/ሚ አብይ አድሎ እያሳዩ እየሆነ የፈራሁት ሁኔታ እየተከሰተ ነው ግን አሁን እኛ ለዴሞክራሲ የምንታገለው ቡድን እራሳችንን "disarm" አድርገናል። በተወሰነ ደረጃ "its' too late" ነው የምትለው።

ምን መሳርያ ኖሮን ነው "disarm" ያረግነው ነው ጥያቄው! እኛ ኢትዮጵያ ብሄርተኞች ከሁሉም ፖለቲካ ኃይሎች የመጨረሻ ደካማ ነበርን ዓመት በፊት ዛሬም እንዲሁ። ምንም "disarm" አላረግንም። ነው ግንቦት 7 ሀገር መግባት አልነበረበትም ወይንም ጥጥቁን መፍታት አልነበረበትም ነው? ዓመት በፊት በኦሮሚያ የነበረው ሁኔታ ይታወቃል። በኦህዴድ ያለው ሁኔታ ይታወቃል። «ጠባቦች» በርካታ ነበሩ አሁንም ናቸው። እንደ አብይ በነሱ ላይም ከነሱ ጋርም ነው የመንግስት ግልበጣ ያደረጉት። እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ኢሚንት ነው ያደረግነው።

ታድያ ዛሬ ጠ/ሚ አቢይ ፈልገውም ባይፈልጉም ኦሮሞ ብሄርተኞቹን ወድያው መቆጣጠር ባይችሉ ምን ይገርማል። የኢትዮጵያ ብሄርተኛው ቡድን ለ50 ዓመት መደራጀት ያልቻለው ዛሬም ስላልቻለ ነው ይህ የሚከሰተው። የአዲስ አበባ ህዝብ ገና ድሮ ቢደራጅ ኖር (ዋጋውን ከፍሎ) ይህ ሁሉ አይሆንም ነበር። ዛሬም ባለፉት ስድስት ወራት መደራጀት ይችል ነበር። አሁንም ይችላል። ላለመቻሉ እነ ጠ/ሚ አቢይን መውቀስ ተገቢ አይደለም። በፍፁም ተገቢ አይደለም። እንደልማዳችን የራሳችንን ችግር ሌላ ላይ እየለጠፍን ነው።

እኛ መጀመርያ ተደራጅተን ታክቲካል አላያንስ ከነ ጠ/ሚ አቢይ ጋር መፍጠር ነው። አሁን ላለውን ችግር እሱ ላይ ከመለጠፍ ፋንታ ስራችንን ሰርተን ብልህ ፖለቲከኞች ሆነን እራሳችንን አጎልብትን መገኘት ነው። ሀውሓት ያደረገው፤ ኦሮሞ ብሄርተኞች ያደረጉትን እኛ ሊያቅተን አይገባም።

ይቅርታ አድርጉልኝ ግን የኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ፖለቲካ በመደራጀት ብቻ ሳይሆን በስልትም እጅግ ደካማ ይመስለኛል። የህዝብ/ብዙሃን ቁጥር አለን ግን ድርጅት የለንም። ስለዚህም አቅመ-ቢስ ነን። ልሰዚህ ይህ ጊዜ የማጎልበት ነው እንጂ የጠላት መፍጠር አይደለም!! እነ ጠ/ሚ አቢይን ጓደኛ አድርጎ፤ የጎሳ ብሄርተኞችን ዝም ብሎ፤ ወሬ ሳናበዛ ለመደራጀት እና ለመጎልበት እራሳችንን ጊዜ መስጠት አለብን። ይህ ነው ብቸኛ አማራጭ።

Thursday 18 October 2018

የአዲስ አበባ ህዝብ መደራጀት፤ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ

ትላንት ሁለት የአዲስ አበባ ሰዎች በማይሆን ክስ ታስረዋል። ከሱም እንደገባኝ ከሆነ ወጣቶችን በ«አዲስ አበባ በከተማው ተወላጅ ነው መመራት ያለበት» መፈክር ዙርያ ማደራጀት ነው። ለዚህም አደረጃጀት ከፍልስቴም ኮንሱሌት ጋር ተባብረዋል ነው ሌላው ክስ። እነዚህ ስራዎች በፍፁም ህገ ወጥ አይደሉም እና መታሰር እንደሌለባቸው ግልጽ ነው። ሆኖም ትላንት እነዚህ እስረኞች በጭለማ ቤት እየተሰቃዩ (torture) ይገኙ ነበር። ዛሬ ደህና ፍርድ ሳያገኙ አይቀርም። መከራ ለነሱ ቢሆንም መሻሻል ነው።

በዚህ ግዳይ በርካቶች አቤቱታ እያቀረቡ ነው። ጥሩ ነው፤ እንደዚህ አይነት የማይሆን እስርን መቃወም አለብን። ግን እንደምናውቀው ፖለቲካችን ከመቃወም ወደ መስራት መሻገር አለበት። Proactive politics beats reactive politics anytime።

መሰራት ያለበት ስልታዊ አደረጃጀት ነው። በመጀመርያ ለምንድነው «ወጣቶችን» የምናደራጀው? ሰራተኛው የት አለ? ወዝ አደሩ የት አለ? የቢሮ ሰራተኛው የት አለ? ወላጆች የት አሉ? ጡረተኞች የት አሉ? መከከለኛ መደቡ የት አለ? ሃብታሙ የት አለ? «የተማረው» የት አለ? ምሁራኑ የት አለ? ልሂቃኑ የት አለ? ለምንድነው «ወጣቱ» (እውነቱን ለመናገር ስራ የሌለው ወጣት) ሸክሙን መሸከም ያለበት?

ይህ «ወጣትን» ማደራጀት ዘላቂነት እንደሌለው ይታወቃል። ሁሉም ህዝብ መሳተፍ አለበት ለእውነተኛ የዜግነት ፖለቲካ ወይንም የሲቪክ አደረጃጀት። ወጣቱ ተሳትፎ ሌላው ከሸሸ ዋጋ የለውም ብቻ ሳይሆን ጎጂም ሊሆን ይችላል። እንደ ሜኪናን በአራተኛ ማርሽ ማስጀመር ማለት ነው።

ሌላው ችግር ገና መደራጀቱ በተገቢው ሁኔታ አይጀምር እራስን ለጥቃት ማጋለጥ ነው። እኔ እንደሚገባኝ የአዲስ አበባ መደራጀት አላማ «የአዲስ አበባ ህዝብ መብቱ እንዲከበር» ነው። ከንቲባው የአዲስ አበባ ትውልድ ይሁን አይሁን አይደለም። የአዲስ አበባ ህዝብ መብት ከተጠበቀ ምርጫ ይኖራል እና ህዝቡ የፈለገውን ይመርጣል። ግቡ እንዲህ ግልጽ ሆኖ ካየነው እና ግቡ ላይ ካተኮርን 1) ስራችንን በትክክሉ እንሰራለን እና ይሳካልናል 2) ለጥቃት እራሳችንን አናጋልጥም!

አካሄዱ እንደሚመስለኝ እንዲህ ነው መሆን ያለበት፤

1) በጣም ሰፊ ተዕልኮ (vision and mission) ያለው ድርጅት ማቋቋም፤ ለምሳሌ «የአዲስ አበባ ህዝብ መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚሰራ» ድርጅት ማለት ነው። ሀ) ሰፊ ተዕልኮ ስለሆነ ለመጠቃት መጋለጡ አነስተኛ ነው የሚሆነው። ለ) ብዙ ሰዎችን በተለይም «መደራጀት» ሲባል የማይገባቸው ወይንም የሚፈሩትን ይጋብዛል። እናቶች፤ ወላጆች፤ መካከለኛ መደቡን። ሃብታሙን ወዘተ ይጋብዛል።

2) ከመፈክር በፊት መደራጀት። መጀመርያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከፋይ አባላት ይኖረው። ከዛ በኋላ ነው መንቀሳቀስ። እንቅስቃሴው ከአቅም ጋር አብሮ መሄድ አለበት! እንቅስቃሴው ከአቅም ጋር አብሮ መሄድ አለበት! አቅም ሳይጎለበት መራመዱ ጥቃትን መጋበዝ ነው። የቅንጅት ታሪክ ይህን ነው የሚያስተምርን። ቅንጅት በመቶ የሚቆጠሩ መሪዎች እና አባላት ነበረው ከዛ ቀጥሎ እስከ ብዙሃኑ ድረስ ከሞላ ጎደል ባዶ መዋቅር ነበር። ጥቂት መሪዎች እና ብዙ ብዙሃን። መሃሉ ባዶ ነው። እነዚህ ጥቂት መሪዎች ሲጠቁ እና እርስ በርስ ሲጣሉ ማን ይተካቸው። መዋቅሩ እስከ ታች ባዶ ነበርና። ስለዚህ መጀመርያ መጠንከር ከዛ ወደ ዋና ስራ መግባት ነው ትክክለኛ አሰራር። ይመስለኛል።

የአዲስ አበባ ህዝብ ወይንም ጠቅላላ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ ወኪላዊ ድርጅቶች መደራጀት አለበት (በዜግነት ፖለቲካ ካመንን)። አለበለዛ ያው የጎሳ ፖለቲካ ማለትም የግጭት ፖለቲካ ነው የሚቀረን። ለሀገራችን ህልውና ቅድመ ሁኔታ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ይህን ዋና ስራ በሙሉ ተሳትፎ በሰከን ያለ ብልጥ መንገድ እንስራው። ህዝብ በሙሉ እንዲሳተፍ እናድርግ።

«እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።»

ኢትዮጵያን የሚገላት የአንድነት ኃይሉ ነው (ክፍል 4)

በ1983 ደርግ ሲፈርስ እና ሻዕብያ፤ ህወሓት እና ኦነግ ስልጣን ሲይዙ እኛ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኞች («አንድነት ኃይሎች») ደነገጥን። ሁለት በፍፁም ያልተበቅናቸው ክስተቶች፤ አጥፊው ደርግ ፈራረሰ እና የትም አይደርሱም የሚባሉት «ሺፍቶቹ» ስልጣን ያዙ! እኛ በአብዮት እና ሽብር የተጎሳቆልን ተመልካቾች (debilitated bystanders) ሆነን ቀረን።

ሆኖም የተወሰነ ነፃነት ሰፍኗል ብለን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጀመርን። ያው የእርስ በርስ አለመስማማት ጠባያችን እንደገና እንቅፋት ሆነን። EDU, COEDF, AAPO, AEUP, MEDHIN, ቅንጅት, Ethiopian Review, Ethiopian Register, Ethiopolitics, EEDN፤ ሁሉም በእርስ በርስ ግጭት ተንገላተው የፈረሱ ተቋሞች።

እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኖች ተባብረን የዜግነት መዋቅሮች መዘርጋት ባለመቻላችን ሜዳውን ለሌሎች ተውን። ግን ጥልቁ ችግር በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ህዝብ ብዙ መኖሩ ነው። ይህ ብዙሃን ባይኖር እና ሁሉም በጎሳ ድርጅቶች ቢወከል ሁሉም ተወክሏል እና መዋቅራት አሉት ማለት ይቻላል። ግን እንዲህ አይደለም። በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ብዙሃኑ ብዙ ልሂቃኑ እና ተቋሙ ትንሽ እና ደካማ። ይህ ነው የኢትዮጵያ distorted ፖለቲካ።

Wednesday 17 October 2018

ኢትዮጵያን የሚገላት የአንድነት ኃይሉ ነው (ክፍል 3)

በደርግ ዘመን ብዙ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስራ ከሀገር ውጭ (በዲያስፖራ) ነበር የሚደረገው ሀገር ውስጥ በነፃነት መስራት ስለማይቻል።

በዚህ ጊዜ ሻዕብያ እና ህወሓት ከዲያስፖራ በርካታ ገንዘብ እና ሌላ ድጋር እየሰበሰቡ ግዙፍ ተቋማት ሆነው ኢትዮጵያን አንቀጠቀጡ።

የ«ኢትዮጵያዊነት» ኃይል ግን «ዴሞክራት» (ኢዲዩ) እና «ማርክሲስት» (ኢህአፓ፤ መኢሶን፤ ደርግ ወዘተ) ሆኖ ተከፋፍሎ ቆየ። ኤዲዩ እርስ በርስ ተከፋፍሎ እና ተጣልቶ በፍጥነት እራሱን ከፖለቲካ ዓለም አባረረ! ማርክሲስቶቹ እርስ በርስ ተፋጁ፤ ሀገሪቷን አሰቃዩ እና ፈትፍተው ለጎሳ ብሄርተኞቹ አጎረሱ።

እኛ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኞች አንድ አላማ ኖሮን መተማመን፤ መስማማት፤ አብሮ መስራት፤ መተባበር እና መደራጀት አለመቻል በሽታችን አሁንም አንቆ ይዞናል።

ኢትዮጵያን የሚገላት የአንድነት ኃይሉ ነው (ክፍል 2)

ወኪሎች ማፍራት ያልቻለ ህዝብ ይጠፋል።

አዲስ አበባ የአምስት ሚሊዮን በ«ኢትዮጵያዊነት» የሚያምን ህዝብ ከተማ ነው። ቅንጅት በ100% መርጧል። ግን ይህ ህዝብ አንድም የፖለቲካ እና ማህበራው መብቱን የሚከራከርለት፤ የሚሟገትለት፤ የሚወክለው ድርጅትን ማቋቋም አልቻለም። አንድም!

ታድያ መብቶች ሲገፈፉ፤ ፍትህ ሳይኖር፤ ሰላም ሲጠፋ ምንድነው ምክንያቱ? ትብብር እና ድርጅት የሌለው ህዝብ እንዴት ፍትህ እና ሰላም ይኖረዋል? ማን መብቱን ያስከብርለታል እራሱ ካላስከበረ?!

ወኪሎች ማፍራት ያልቻለ ህዝብ ይጠፋል።

አንድ ምሁራን እንዲህ ብልዋል፤  “When people realize things are going wrong, there are two questions they can ask. One is, ‘What did we do wrong?’ and the other is, ‘Who did this to us?’ The latter leads to conspiracy theories and paranoia. The first question leads to another line of thinking: ‘How do we put it right?’”

ኢትዮጵያን የሚገላት የአንድነት ኃይሉ ነው (ክፍል 1)

ባለፈው ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የኤርትራ ዲያስፖራ እንደልማዳቸው እየተሯሯጡ ለሀገራቸው ገንዘብ እያዋጡ ነበር። ምን ያህል አዋጡ? ልምሳሌ ያህል፤ በአንድ ቀን ከአንድ ከተማ ሲአትል (ዋሺንግተን ስቴት) አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አዋጥተዋል! ከዋሺንግተን ዲሲ አይነቱ ብዙ ኤርትራዊ ያለበት ከተማ ምን ያህል እንደተዋጣ ባላውቅም መገመት ይቻላል።

ተወዳጁ «ኢትዮጵያዊነትን» የወከለው ቅንጅት ለሰላም እና ዴሞክራሲ ፓርቲ መሪዎቹ ከተፈቱ በኋላ ሰሜን አሜሪካ መጥተው ለወራት ቆዩ። ከመላው ሰሜን አሜሪካ የሚኖር ኢትዮጵያዊያን ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በታች ሰብስበው (እና እርስ በርስ ተጣልተው) ተመለሱ!

የአንድነት ኃይሉ እርስ በርስ አለመስማማት እና አለመደራጀት ኢትዮጵያን ይገላል።

«አትፍረዱ»

"Once on Mount Athos there was a monk who lived in Karyes. He drank and got drunk every day and was the cause of scandal to the pilgrims. Eventually he died and this relieved some of the faithful who went on to tell Elder Paisios that they were delighted that this huge problem was finally solved.

Father Paisios answered them that he knew about the death of the monk, after seeing the entire battalion of angels who came to collect his soul. The pilgrims were amazed and some protested and tried to explain to the Elder of whom they were talking about, thinking that the Elder did not understand.

Elder Paisios explained to them: "This particular monk was born in Asia Minor, shortly before the destruction by the Turks when they gathered all the boys. So as not to take him from their parents, they would take him with them to the reaping, and so he wouldn't cry, they just put raki into his milk in order for him to sleep. Therefore he grew up as an alcoholic. There he found an elder and said to him that he was an alcoholic. The elder told him to do prostrations and prayers every night and beg the Panagia to help him to reduce by one the glasses he drank.

After a year he managed with struggle and repentance to make the 20 glasses he drank into 19 glasses. The struggle continued over the years and he reached 2-3 glasses, with which he would still get drunk."

The world for years saw an alcoholic monk who scandalized the pilgrims, but God saw a fighter who fought a long struggle to reduce his passion.

Without knowing what each one is trying to do what he wants to do, what right do we have to judge his effort?"

-A story of St. Paisios, translated by John Sanidopoulos

Tuesday 16 October 2018

የለቅሶ ፖለቲካ አሳፋሪ ነው፤ ያብቃ!

ኢሳት ለበርካታ ስዓት ስለ የታፈሱ የአዲስ አበባ «ወጣቶች» ዜና እና አስተያየት እያቀረበ ነው (https://www.youtube.com/watch?v=4KugoBLSfFY)።

እኔ እስካየሁት ድረስ ኢሳት አንዲት ደቂቃ ስለ መሰረታዊ ችግሩ ውይይት አላቀረበም። መሰረታዊ ችግሩ የአዲስ አበባ ህዝብ እና በመላው ኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊነት የምናምነው የኢትዮጵያ ብሄርተኞች በበቂ ደረጃ አለመደራጀታችን ነው።

አስቡት… የአምስት ሚሊዮን ህዝብ ከተማ አንዳች ይሄ ነው የሚባል ህዝብ ወኪል ተቋም የለውም! ይህ ነው ጉዱ።

ይህን ጉድ አምነን ወደ መፍትሄ ከመሄድ ወደ መደራጀት ከመሄድ ጊዜአችንን «በለቅሶ ፖለቲካ» እናጠፋለን። እንደ ክብር የሌለን ሰዎች የራሳችን ገበና ሳናስተካክል ሌሎችን «አትግዱን» ብለን 24 ሰዓት እንለምናለን። በራሳችን ድክመት ስለምናፍር ይመስለኛል ሁል ጊዜ ጣታችንን ወደ ሌሎች የምንጠቁመው። እነሱ ደግሞ እኛ እራሳችንን ካላልጎለበትን ምንም አያደርጉልንም።

አንድ ምሁራን እንዲህ ብልዋል፤  “When people realize things are going wrong, there are two questions they can ask. One is, ‘What did we do wrong?’ and the other is, ‘Who did this to us?’ The latter leads to conspiracy theories and paranoia. The first question leads to another line of thinking: ‘How do we put it right?’”

የኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ምሁራን እና ልሂቃን አሁንም «ማን ነው የሚያጠቃን» የሚለው ላይ ነን። በጃንሆይ ዘመን በ«አለመተባበር ብሽታችን» ምክንያት በየቀኑ ለዳኝነት ወደ ጃንሆይ እንሄድ ነበር። ከዛ አድሃሪ/ተራማጅ እየተባባልን ተገዳደልን። የተረፉት «አድሃሪዎቹም» ኢዲዩ መስርተው አብሮ መስራት አቅቷቸው ፈራረሱ። ማርክሲስቶቹ ከመተባበር እርስ በርስ ተፋጁ። ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ እራሳችንን «ተቃዋሚ» ብለን ሰይመን ይሄ ነው የሚባል ተቋም ማደራጀት አቃተን። ወዘተ። የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ደጋግሞ መውደቅ ረዥም ታሪክ ነው። ግን አሁንም ይህን ድምከት ላይ ከማተኮር ይልቅ ሌሎችን እባካችሁን አድኑን ብለን እንለምናለን!

Monday 15 October 2018

አንድ የቅዱስ ዮሃንስ አፈወር ጥቅስ

«ስፖርት የሚከታተሉ ሰዎች የታወቀ ስፖርተኛ ከመንደራችሁ መጥቷል ከተባለ ይህን ስፖርተኛ፤ ችሎታውን እና ጥንካሬውን ለማየት ብለው ወዳለበት ይሮጣሉ። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች የተሞሉ ስታዲየሞች አሉ። እነዚህ ተመልካቾች አንዳች ነገር እንዳያመልጣቸው ብለው እስኪደክማቸው ድርስ አያናቸውንም አዕምሮአቸውንም አትኩረው ስፖርቱን ይመለከታሉ። እንዲሁም የታወቀ ዘፋኝ ከመንደራቸው እንደሚገኝ ከሰሙ ሰዎች ያላቸውን አንገብጋቢም የሆነ ጉዳዮቻቸውን ሁሉ ትተው ዘፋኙን ለማየት ይሄዳሉ። ዜማውን እና ግጥሙን ተጠንቅቀው ያዳምጣሉ። ለታዋቂ ተናጋሪም ሰው እንዲሁ ያደርጋሉ በጭብጨባ እና እልልታ ይቀበሉታል እና ያስተናግዱታል። ታድያ ተናጋሪዎችን፤ ዘፋኞችን እና ስፖርተኞችን ሰዎች እንዲህ አትኩረው የሚከታተል ከሆነ ምን አይነት ቅንዓት እና ጽናት ሊኖረን ይገባ ይሆን ሰው በኢግዚአብሔር ፀጋ ከገነት ሆኖ ሲያስተምርን?»

ቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅ፤ «የዮሃንስ ወንጌል ትርጓሜ» ክፍል 1

"People who watch sports, when they hear that a famous athlete is in town, run to watch him, and all his skill and strength. And there are stadiums full of ten of thousands, all straining their eyes and minds so that they don't miss anything. Or if a famous musician passes through their area, people drop everything, even necessities and urgent business, to sit listening attentively to the words and the music. People will do the same thing for a renown speaker and receive them with clapping hands and cheering. And if in the case of rhetoricians, musicians, and athletes, people pay such close attention, what degree of zeal and earnestness should we display when a man is speaking from heaven with the Grace of God on his tongue?"

St. John Chrysostom (+407AD), On the Gospel of John, Homily 1

የአዲስ አበባ ወጣቶቻችን፤ Nameless and faceless

ዛሬ በመሃበራዊ ሚዲያ ለ«ታፈሱት የአዲስ አበባ ወጣቶች» ፍትህ መጠየቂአ ቀን ይመስላል። ጥሩ እቅድ ነው።

ግን ማናቸው እነዚህ «ወጣቶች»? መስላቸው የት አለ? ስማቸውስ? ቤተሰቦቻቸው የት አሉ? ልጆች አላቸው ይሆን? ወላጆቻቸው የት ናቸው? እየተፈለጉ ነው ወይ? ማን ስለነሱ በየቤቱ እያለቀሰ ነው?

እኔ እስከመቀው ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ የለንም። ለምን የለንም? እንዴት በመቶዎች ወይንም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታፍሰው ወደ ወታደራዊ ካምፕ ሲወሰዱ ምስላቸው፤ ስማቸው፤ ቤተሰቦቻቸው አይመዘገቡም? አዲስ አበባ የአምስት ሚሊዮን ህዝብ ከተማ ናት። ልጆቿ እንዲህ አይነት ነገር ሲደርስባት እንዴት ዝርዝሩን አናውቅም? ኤንዴንት ቤተሰቦቻቸው ወይንም ወኪሎቻቸው በተለያየ ሚዲያ ወጥተው እንዲታዩ ወይንም እንዲናገሩ አይደረግም? ለምንድነው faceless ሆነው የሚቀሩት?

ለነዚህ ጥያቄዎች መሰረታዊ ምክንያቱ የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ህዝብ እንደዚህ አይነት ጥቃቄዎችንም የሚያስተናግድ እና የሚመልሱ አቅም ያላቸው የፖለቲካ እና ማህበራዊ ተቋሞች ስለሌለው ነው! እነዚህ ወጣቶች ከተታፈሱ በኋላ ሁላቸውም ከነ ምስላቸው፤ ስማቸው እና ቤተሰቦቻቸው ተመዝግበው እንደ አግባቡ በሚድያ መቅረብ ነበረባቸው። ወጣቶቹን የሚመዘግብ፤ ሁኔታቸውን የሚከታተል፤ ሰለነሱ የሚሟገት እና የአዲስ አበባ ህዝብን ሰለ ጉዳያቸው የሚያሳውቅ ድርጅት ሊኖር ይገባ ነበር! የአምስት ሚሊዮን ከተማ ነው፤ ይህ ሊሳነው አይገባም።

ስለዚህ ይህ ነው መሰረታዊ ችግሩ/ችግራችን። አልተደራጀንም። መደራጀት ለህልውናችን ግድ ነው። ይህ መሰረታዊ ችግር ካልተፈታ ህመሞቻችን ይቀጥላሉ! (If we don't address the fundamental cause we'll keep running after the symptoms and never catch up)።

ስለዚህ ጉዳይ ሌላ ነገር ላንሳ። እስቲ ስንቶቻችን ነን የነዚህ ወጣቶችን ቤተሰቦች አይዝዋችሁ እያልን የምንገኘው? የሚያስፈልጋቸው እርዳታ ካለ የምናረግላቸው? ለባለንጀራዬ ካላሰብኩኝ ለምን ሌላው ያስባል ብዬ አስባለሁ። በችግር ጊዜ ካልደረስኩለት ምን አይነት መተማመን እና ትብብር ይኖረናል? ይህ ሌላ መሰረታዊ ችግር ነው። የእርስ በርስ ግንኙነታችን (social capital) መንኗል። ፍትህ እና ሰላም ከፈለግን ይህ መታደስ አለበት።

https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_14.html

https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_97.html

On NAMA Strategies

One of the National Movement of Amhara's (NAMA) strategies seems to be to out-ghetto Oromo nationalists, so to speak. That is, to demonstrate political positions and attitudes that are as radical or even more radical than Oromo nationalists. Simple examples - NAMA leadership and intellectuals have made statements in support of Article 39 and of maintaining ethnic identification on kebele id cards. And apparently at a recent NAMA meeting, supporters publicly voiced the idea of evicting Oromos living on Oromia zones in Amhara Region.

The idea behind this strategy, it seems to me, is that taking extreme positions, which, by the way, have no acceptance from the Amhara masses, will help neutralize Oromo and other ethnic nationalists by restoring the political balance. The NAMA view is that Oromo nationalists have been 'coddled' for too long and now have too much political power now, and one of the ways for NAMA to counteract that is by showing strength through extremism. Basic tit-for-tat strategy.

The problem with this is that it is based on an erroneous and simplistic understanding of the phenomenon of ethnic nationalism in a multi-ethnic nation. The goal of ethnic nationalism is to tear away at the centre, weaken it, and take power away from it to the periphery, which is various ethnic nationalisms. Adding 'another' ethnic nationalism to this actually further weakens the centre and strengthens all ethnic nationalist movements.

A further factor that NAMA doesn't seem to consider is the asymmetric nature of ethnic relations in Ethiopia. The Amhara live in large numbers in various regions, while the Oromo do not.

Given this, Oromo nationalists would much rather have a weak or empty centre and deal with a strong Amhara nationalist movement. This is their perfect scenario, in which all Oromos, including moderate ones, will congregate to Oromo nationalism, making it the only game in Oromia, so to speak. They will negotiate tit for tat agreements with Amhara nationalism and have their Oromo homeland.

What about issues that Oromo nationalists and Amhara nationalists do not agree on, such as Amharas in Oromia, and the case of Addis Ababa? With all Oromos on board, Oromo nationalists will not give an inch on this, and there will be conflict, either overt or covert. The main victims, given the population distribution I mentioned above, will be Amharas and other ethnic groups in Oromia and in Addis Ababa. And if NAMA has a vision of being able to carry out a TPLF 2.0 and forcing itself on the whole country, well, I think we all realize how realistic that is.

Now, I think we should take a step back and ask ourselves 'why'. Why does NAMA exist and why does it take the positions and attitudes in does? In order to reach any kind of understanding and solution to the issues at hand, this question has to be the focus. As I've written about this in my blog, for me, there are two major reasons: 1) The upheaval and resulting weakness of Ethiopian nationalism (or 'the centre') over the past 50 years, and 2) accumulated resentment for the treatment of the Amhara, including by Amhara 'traitors', over the past 27 years, and the resulting grievance and inferiority complex. NAMA is simply an outgrowth of this. The second factor we can do little about - time will heal wounds. But the first we must work hard with all our might to correct, as fixing that - strengthening the centre tangibly via political parties and institutions - is a sine qua non for the survival of Ethiopia.

Thursday 11 October 2018

መልዕክት ለኢሳቶች…

አቤቱታ፤ ማማረር፤ ማልቀስ፤ complaining ህዝብን ተስፋ እንዲቆርት ያደርጋል። ይህ ከኢሳት ተዕልኮ የሚጻረር ነው።

እንደ አንድ ተራ ዜጋ ምክሬ እንዲህ ነው፤ ስለ ችግሮች ለ10 ደቂቃ ካወራችሁ ስለ መፍትሄ እና አማራጭ መንገዶች ለ20 ደቂቃ ተወያዩ። አዋጪው መንገድ ይህ ይመስለኛል።

«ኢሳት ስለ ችግር አውርተው ሰማይ ተገለበጠ ብለው ያቆማሉ»

ዛሬ «ኢሳት ስለ ችግር አውርተው ሰማይ ተገለበጠ ብለው ያቆማሉ» አለችኝ እናቴ። ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ላይ ለምን ያተኩራሉ አለች። እውነቷን ነው። ከኢሳት ተዕልኮ ጋር ይጋጫል። ሆኖም…

ኤርሚያስ ለገሰ በትላንቱ የኢሳት እለታዊ ፕሮግራም (https://youtu.be/mzQqTD-D2SM?t=2162) እንዳለው የወታደሮቹ አለ ቀጠሮ ወደ ቤተ መንግስት መሄዳቸው የህግ ወጥነት፤ ችልተኝነት፤ ስርዓትን አለማክበር፤ ስራ አለማክበር ወዘተ በሀገር እና መንግስት መብዛቱን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ነው። ችግር አለ ይቀጥላልም።

1. የ27/44 ወዘተ ዓመት ችግሮችን ለመፍታት እና ለማስተካከል ዓመታት ይፈጃል።
2. ስርዓትን በግዳጅ እና በፍርሃት ማቅበር የለመደ ሰው ግዳጁ እና ፍርሃቱ ሲቀሩ ልቅ ይሆናል።
3. የተለያዩ የህብረተሰባችን ክፍሎች ከነ ወታደሮች፤ አስተማሪዎች፤ ሰራተኞች ወዘተ ጥያቄዎቻቸው ለረዥም ዓመታት ተዳፍኖ በመቆየቱ አሁን ባንዴ ይፈነዳሉ።
4. አዲሱ መንግስት የማስፈራራት እና መረሸን ፍላጎት እንደሌለው ስለሚታወቅ የተለያዩ የህዝብ ክፍሎች ልቅ ሆነዋል።

ስለዚህ ተወያይቶ የተለያዩ መፍትሄዎች ማቅረቡ ጥሩ እና ገንቢ ነገር መሰለኝ። ከማማረር ይልቅ ተግባር!

የፌደራል መንግስት ዘመን አቆጣጠራችን (calendar) ይቀየር ይላሉ አቶ አብዱ አሊ ሂጅራ?!

ብስመ አብ! የፌደራል መንግስት ዘመን አቆጣጠራችን (calendar) ይቀየር ይላሉ አቶ አብዱ አሊ ሂጅራ?!

ከመአዛ አሸናፊ ጋር 10 ቀን በፊት ያደረጉትን ቋሚ ቃለ ምልልስ አሁን አዳመጥኩት (https://www.youtube.com/watch?v=s-ve5RiImNc)። ባጭሩ የቀን መቁጠርያችን እንደ ባህል እንጠብቀው፤ ለምሳሌ አዲስ አመትን አሁን እንደሚደረገው በመስከረም 1 ይከበር፤ ግን official ወይንም የመንግስት የቀን አቆጣጠር ወደ «ፈረንጁ» (Georgian calendar) አቆጣጠር ይቀየር። ምክነያቱ አብዛኛው ሀገራት በፈረንጁ አቆጣጠር ስለሚጠቀሙ በኢትዮጵያ አቆጣጠር መጠቀም ለበርካታ ስራ አይመችም። ሁልጊዜ ከአንዱ ወደ አንዱ መቀየር (convert) ስራን ያስተጓድላል አሉ አቶ አብዱ አሊ።

ይህ በብዞዎች ተቀባይነት ያለው አስተሳሰብ ነው። ግን ትክክል አይደለም… አይመስለኝም። ማንኛውም ትውፊታዊ ነገር እንደ ቀን መቁጠርያ እንደ «ባህል» ብቻ ይዘን በስራ ላይ ካልዋለ ቀስ ብሎ ይጠፋል! ለዚህም ነው ሀገራት የራሳቸውን ቋንቋ የሚጠብቁት። ከጃፓንኛ ወደ እንግሊዘኛ መከያየር ከባድ ስራ ነው። አብዛኛው የቴክኖሎጂ ነክ ነገሮች በእንግሊዘኛ ናቸው። ሆኖም ጃፓን በጃፓንኛ ቀልቋል። ያን ሁሉ ቴክኖሎሂ ነክ ስራዎችም ሲሰራ በጃፓንኛ ነው ያደረጉት። ድሮ የኮምፕዩተር ስራ በሌላ ቋንቋ መስራት በጣም ከባድ በሆነበት ዘመንም በጃፓንኛ ነበር የሰሩት። የማንነት ጉዳይ ስለሆነ እንደ ባህል አልትውትም። ሰሩበት አሁንም ይሰሩበታል። ይህ አስተያየት ለቋንቋ ብቻ ሳይሆን ለቀን መቁጠርያም ይሆናል።

በተዘዋዋሪ ኤርትራ የመንግስት የቀን መኩጠርያውን ሲቀይር እጅግ አዝኜ ነበር። ውጤቱ ዛሬ እና ነገ ይታያል እነ እንቁጣጣሽም እየተረሱ ይሄዳሉ።

ትንሽ ቃል ስለ ሃሳቡ ጠቅላላ መንፈስ ልጻፍ… ጣልያን ሀገር ብትሄዱ ሰንበት ሱቅ መከፈት የለበትም፤ እንደነ «ዎልማርት» አይነት ግዙፍ ሱቆች ሊኖሩ አይገባም፤ አማዞን ገደለን ወዘተ ይባላል። እነዚህ ነገሮች በማህበራዊ ኑሮ (including social capital)፤ ግለኝነት እና ብቸኝነት (individiualism and loneliness)፤ የትናንሽ ከተማ እና ሰፈር ህልውና፤ ወዘተ ላይ ያላቸው ሚና ይተቻሉ። ሁሉን ነገር 'rationalise' ማድረግ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳትም እንዳሉእው ይታወቃል። በዚህ ምክንያት localism የሚባለው ርዕዮት ዓለም ባለፉት አስርት ዓመታት ወደ ልሂቃን መገናኛ ተመልሷል። ስለዚህ እንደዚህ አይነቱን ጉዳይ ላይላዩን ሳይሆን ጠልቀን መመርመር ይኖርብናል።

Wednesday 10 October 2018

የቅራኔ መፍታት (conflict resolution) ጉድለታችን

አንዱ ከብዙ የጠ/ሚ አብይ አህመድ ልዩ የሚያረጋቸው ችሎታዎች የቅራኔ መፍታት አቅማቸው ነው። ትዕቢት፤ ቂም፤ አሉታዊነት፤ ትቶ የሁሉንም ትቅም የሚያስከብር ለሁሉም ተመራጭ የሆነ ግባ ላይ በማተኮር ችግሮችን ፈትተዋል አሁንም እየፈቱ ይገኛሉ። ይህ አቅማቸው ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መሪዎች ለዘመናት ታይቶ አይታወቅም (https://ethsat.com/2018/10/ethiopia-soldiers-show-up-unannounced-at-national-palace-pm-orders-pushups/)።

@Samuel Abebe (በዚህ ትችት ላይ https://www.facebook.com/abdurahman.ahmedin.7/posts/2120966214582614?comment_id=2121015731244329) ሁላችንም በውስጣችን የምናስበውን ታላቅ ጥያቄ ጠየቀዋል፤

«መለወጥ ስህተትን ከመቀበል ይጀምራል ይባላል ትልቅ ስህተት ተፈጽሞም ከቅንጅት አመራሮች ስህተቱን ተቀብሎ እዚህ ላይ ይህን ባንሳሳት ኑሮ የሚል አመራር እንዴት ይጠፋል? ሁሉም ወደ ሌላ ሰዉ ጣቱን ይቀስራል፡ እኛስ የትኛዉን አምነን የትኛዉን እንቀበል?»

ዋና እና ተገቢ ጥያቄ ነው። ብስለት እና እውቀት የሞላው። በማንኛውም ቅራኔ አንድ ጥፋተኛ እና ሌላው ንፁሃን የለም (there are two or more sides to any conflict)። ይህን ሃቅ ማንኛውም ስለቅራኔ የሚያውቅ ባለሙያ፤ ማንኛውም የካህን፤ ማንኛውም አስተዳዳሪ፤ ማንኛውም ወላጅ የሚያውቀው ነው። ግን ብናውቀውም እንዳማናውቀው አድርገን ነው የምንኖረው። ቅራኔ ውስጥ በተገኘን ቁጥር እራሳችንን ፍፁም ንፁህ ሌላው ፍፁም ጥፋተኛ አድርገን ነው የምንቆጥረው።

ይህ ከገባን በቅንጅት ቅራኔ ህሉም ተሳታፊዎች የተወሰነ ሚና መጫወታቸውን ሊገባን ይገባል። የፈረደበት ልደቱ ጥፋት ብቻ ሊሆን አይችልም። ዋናው ችግር የሱ ነው ቢባልም ያንን ችግር ማስተናገድ አለመቻል በራሱ ትልቅ ድክመት ነው! መታመን ያለብት እና ይቅርታ የሚጠየቅበት ድክመት ነው። ታላቅ መማርያ የሚሆን ድክመት ነው።

እንደ ቅንጅት አይነት ታላቅ ድርጅት፤ እጅግ ግዙፍ የሆነ የሀገር ሃላፊነት ያለው ድርጅት ሲፈርስ ሁሉም በአመራር ያሉት በመፍረሱ ሚና ተጫውተዋል እና ሁሉም ድክመታቸውን አምነው ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል። እኛም ደጋፊዎቻቸው እንዲሁም። ያደረግነውን ስህቶቻችንን ካመንን በኋላ ብቻ ነው መማር የምንችለው እና እንዳንደግማቸው ማድረግ የምንችለው።

የቅንጅት ታሪክ ከብዙ የሀገራችን ፖለቲካ የቅራኔ መፍታት አለመቻል ታሪኮቻችን አንዱ ነው። እንዳውም በኔ እምነት የፖለቲካ እና ማህበራዊ ችግሮቻችን ዋና ጎልቶ የሚታየው ምክንያት «የቅራኔ መፍታት (conflict resolution) ጉድለታችን» ነው። በዚህ ዙርያ ብዙ ተጽፏል እና ተነግሯል ግን በቂ አልተደረገም። ዛሬም የምናያቸው ነገሮች አሉ፤

1. አንድ «አቋም»፤ ርዕዮት ዓለም፤ አስተያየት ኖሮን አብሮ መስራት አለመቻል
2. የራሳችንን ጥቅም ጎድተን ቂማችንን ለመወጣት የምናደርጋቸው ስህተቶች
3. የጋራ ማሸነፍን ከመፈለግ (አሁንም የራሳችንን ጥቅም ቢጎዳም) ሌላው እንዲሸነፍ መመኘት እና መስራት
4. ፖለቲካን እንደ ሃይማኖት ፍፁም እውነት እንዳለው መቁጠር።

የፖለቲካ አካሄዳችን እንዲሻሻል ከተፈለገ ስለነዚህ ጉዳዮች መያየት እና መፍትሄ ማግኘት ግድ ነው።

ቅራኔ መፍታት ለኛ ኢትዮጵያዊያን አዲስ ነገር አይደለም። የድሮ ንጉሶቻንን አድርገውታል። ይህን የሚያስፈጽሙ በርካታ ባህላዊ መንገዶች አሉን። ከሃይማኖታችን ደግሞ መሰረታዊ ቅራኔ መፍታት ምክንያቶችንም ዘዴዎችም አሉ። ለምሳሌ በክርስትና «ንስሃ» ማለት ማለት 1) ስተትን ማመን 2) እንዳይደገም 3) ሌላው እንዲገባው 4) እራስን ለማረም 5) እራስን ለማወቅ ወዘተ። ውየንም «አለመፍረድ» ማለት 1) ለሌላው መቆርቆር (empathy) 2) የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ችኩሎ አለመድረስ 3) ጣት ጠኩሞ የራስን ችግር መርሳት ወዘተ።

ስለዚህ አሁን ማድረግ ያለብን እነዚህን (ምናልባት የተረሱ) ባህላዊ እሴቶችን እንደገና ማስነሳት እና ማሰራጨት ነው። ከባድ ስራ ነው ግን ምርጫ የለንም!

http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html

Sunday 7 October 2018

የ«ኢትዮጵያዊነት» ጎራው በቂ አለመደራጀቱ ነው የሀገራችን ፖለቲካ መሰረታዊ ችግር!

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ገደል የገባው በኃይለ ሥላሴ ዘመን አስፈላጊ ለውጦች ባለመደረጋቸው ማርክሲዝም እና አብዮት በሀገራችን መስፈኑ ነው። በዚህ ሂደት በሀገራዊ ብሄርተኝነት የሚያምነው የፖለቲካ ልሂቃን ተከፋፍለው እና እርስ በርስ ተፋጀተው የሀገራችን ፖለቲካ በጎሳ ብሄርተኞች እንዲወረር ተው።

ይህ የፈጠረው ሁኔታ ይህ ነው፤ የጎሳ ብሄርተኝነትን የሚከተለው ብዙሃን በፖለቲካ ድርጅት፤ ኃይል እና ልሂቃን ደረጃ በአግባቡ ተወክሏል። በአንጻሩ በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የሚያምነው ብዙሃን አልተወከለም ማለት ይቻላል። ከ100 ሚሊዮን ህዝብ ቢያንስ ግማሹ ጠንካራ ኢትዮጵያ ብሄርተኛ ነው። ግን ይህ ግዙፍ የሆነው ህዝብ ብዛቱ የሚገባው ድርጅት የለውም። ግንቦት 7 ነው ያለው አቅሙ ግን የ50 ሚሊዮን ህዝብ የሚወክል ድርጅት ያህል አይደለም። ቅርቡም አይደለም።

ይህ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋና እና መሰረታዊ ችግር። በታም ግዙፍ የሆነ የብዙሃኑ ክፍል የልሂቃን፤ ምሁራን፤ እና የፖለቲካ መደብ ውክልና የለውም። ይህ የተዛባ (distorted) ሁኔታ ፖለቲከኞቻችን የተዛባ ውሳኔዎች እንዲወስዱ ያደርጋል እና ሀገሪቷን ግጭት በግጭት የደርጋል።

አልፎ ተርፎ በአግባቡ ያልተወከለ ግዙፍ ብዙሃን አንድ ቀን ይፈነዳልና ወደ አብዮት ያመራል። የአማራ ብሄርተኝነት ማደግ ይህን ያመለክታል። በዜግነት መደራጀት ስላቃተን በጎሳ እንደራጅ ነው የአማራ ብሄርተኝነት መሰረታዊ ግፊቱ። ይህ ሁኔታ በዚ አቅጣጫ ከቀጠለ ምሃል ሀገሩ (centre) ባዶ ቀርቶ የፖለቲካ ኃይል በሙሉ ከጠረፎቹ (periphery) ይሆናል። ይህ ደግሞ እንደምናውቀው የጎሳ ውድድር፤ ከዛ ግጭት፤ ከዛ ጦርነት ያመጣል። ለዚህ የ27 ዓመት መረጃ አለን።

ስለዚህ የፖለቲካችን ችግር ለመፈታት ዘንድ የኢትዮጵያ ብሀኢርተኝነት ጎራው በአግባቡ መደራጀት ግድ ነው። ቅድመ ሁኔታ (necessary precondition) ነው። በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠረው የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ብዙሃኑ ቁጥሩን የሚመጥን ፖለቲካዊ ውክልና ያስፈልገዋል። የመሃል እና ጠረፍ (centre and periphery) ሚዛን መስተካከል አለበት። ይህ ከሆነ የፖለቲካ መደቡ በእውነታ የተመሰረተ ድርድር ማድረግ ይችላል። ሁሉም ህዝብ በተወከለበት ማለት ነው።

ይህን ነጥብ እንዴት አጠንክሬ ማስደምደም እንደምችል አላውቅም! የኢትዮጵያዊነት ጎራው በአግባቡ አለመደራጀቱ ነው እስካሁን ያለውን የፖለቲካ ችግር የሚቀጥለው። ካሁን በኋላም ካልተደራጀ ፖለቲካችን ወደ ቀውስ እና ሁከት መሄዱ አይቀርም።

Wednesday 3 October 2018

«የዜግነት ፖለቲካ ይስፈን» ብለን እንጮሃለን ግን አልተደራጀንም!

መቼም «ከእንቁላል ውስጥ» ያሉት እነ ጠ/ሚ አብይ በሙሉ አቅማቸው ኢትዮጵያዊነትን ለማጠንከር እየጣሩ ነው። በዚህ መንገድ እንደሚቀጥሉም ይታወቃል።

አሁን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለው ትልቅ ጉድለት ነገር በኢትዮጵያዊነት የምናምን ፖለቲከኛ፤ ልሂቃን እና ብዙሃን በአግባቡ አለመደራጀቱ ነው። «የዜግነት ፖለቲካ ይስፈን» ብለን እንጮሃለን ግን አልተደራጀንም!! እንኳን በሚሊዮኖች የምቆጥር በመቶ ሺዎች የሚቆጥር አባል ያለው ድርጅት የለንም። ታድያ ሌሎች የዜግነት ፖለቲካ አይሰራም ብለው እንዲያምኑ የሚያደርጋቸው እኛ ነን ማለት ነው!

እነ ግንቦት 7 ስሙ። ቶሎ ብላችሁ የዜግነት ፖለቲካ አራምዱ። አባላት እና መሪዎች በሰፊው መልምሉ። የመዋቅር መዘርጋት ስራ ካሁኑኑ ጀምሩ። ጊዜ ይፈጃል ግን ጊዜ የለንምና።

Tuesday 2 October 2018

መሬት የግል ቢሆን ባለሃብት ይገዘዋል የሚባለው ሃሰት ነው

መሬት የግል መሆን አለበት ሲባል እንዱ በተለምዶ የሚሰነዘረው ተቃውሞ ገበሬዎች አግባብ ባልሆነ ርካሽ ዋጋ መሬታቸውን ይሸጣሉ እና ባለሃብት ብቻ መሬቱን ይገዛሉ። መሬት በሙሉ የባለሃብት ይሆናል ወደ «ፍዩዳል» ዘመን ከነችግሩ እንመለሳለን።

ይህ እጅግ የተሳሳተ አመለካከት ለመሆኑ ተጨባጭ መረጃ አለ። ላለፉት በርካታ ዓመታት መንግስት በሊዝ (የ55 ዓመት ሊዝ ለምሳሌ) በርካታ ትላልቅ መሬቶች ማከራየት ሞክሯል። በየክልሉ መርጥ የሆኑ ህዝብ ያለበትም የሌለበትም ለእርሻ አመቺ የሆኑ ቦታዎች ለሊዝ ኪራይ ቀርበዋል። ዋጋቸውም እጅግ ረካሽ ነበር። ለምሳሌ በጋምቤላ በዓመት 100,000 ብር አካባቢ ለመቶዎች ዬክታር ይከራያል።

ይህም ሆኖ ጥቂት ባለ ሃብቶች እና ኩባኒያዎች ናቸው ወደ እርሻ የገቡት። የቁጥር ሰነድ በእጄ የለኝም ግን ሊገን ይችላል። ግን አሁንም የሊዝ ቦታ በርካሽ ዋጋ መኖሩ የእርሻ መሬቱ ብዙ ፈላጊ እንዳልነበረው ያሳያል።

ዛሬ ባለሃብቶች በርካሽ ዋጋ ምርጥ የእርሻ መሬት ሊዝ ማድረግ ያልፈለጉ ከግል ገበሬዎች የደከመ የተበጣጠሰ መሬት ይገዛል ብለን ማሰብ አንችልም። ገበሬው መሬትን መሸጥ ቢችልም አብዛኛው ጊዜ ባለሃብት አይገዛውም።

የሚገዛው ጎረቤቱ ነው የሚሆነው። ዛሬ በየአመቱ በእኩል የሚከራየው ጎረቤት ገበሬ ከምከራይ ልግዛ ብሎ ይጠይቃል። የጎበዝ ገበሬው ይዞታ ይሰፋል የመሬት ጠቅላላ ምርቱም ይጨምራል። ጎበዝ ገበሬው በዚህ መንገድ እየተስፋፋ ታዳጊ ገበሬ ይሆናል። ይህ የሃገራችንን ጠቅላላ ምርት ይጨምራል።

(http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_47.html)

The Black Swan - አንብቡት!

ተሳስቼ ይሆናል እንጂ የኢትዮጵያዊ ምሁራን ባብዛኛው ከምዕራብ ዓለም ዘወትር ትምሕርት ነው (mainstream academia) የሚማሩት። የሚነከሩበት ልበል?

ለማንኛውም በዚህ ምክንያት ይህን «ብላክ ስዋን» ("Black Swan") የሚባለው መፀሃፍን ብዙዎች ያነበቡት አይመስለኝም። አንብቡት! እጅግ አስተማሪ ነው። ያው እንደማንኛውም ነገር ዘሩን ከእንክርዳዱ መለየት ያስፈልጋል ግን አንብቡት!

እኔ ያነበብኩት ገና ሲወጣ ወደ 11 ዓመት በፊት ነው። የገረመኝ ነገር ምን ያህል ከኢትዮጵያ ባህላዊ አስተሳሰብ እንደሚሄድ ነው። ጸሃፊው ሊባኖሳዊ አሜሪካዊ ሆኖ አስተሳሰቡ በኦርቶዶክስ ሃይማኖቱ የተገራ ይመስላል። መጸሃፉ ስለ ሳይንስ እና ፍልስፍና ቢሆንም ይህንን ዝንባሌ በደምብ ያሳያል።

አንብቡት!

https://www.amazon.com/Black-Swan-Improbable-Robustness-Fragility/dp/081297381X/ref=sr_1_1?s=books&ie=UTF8&qid=1538495240&sr=1-1&keywords=black+swan&dpID=41w4yuUG1mL&preST=_SY344_BO1,204,203,200_QL70_&dpSrc=srch

የአዲስ አበባ ተፈናቃዎች

የኛ የአዲስ አበባዎች አንዱ (ከብዙ) ድክመቶቻችን በዚህ ቪዲዮ ይገለጻል፤

https://www.youtube.com/watch?v=fhKBwe1wF2Y

ይህ ድክመት ከመሬታቸው የተፈናቀሉት ወንድሞች እይቶቻችን ጎረቤቶቻችንን ዞር ብለን አለማየት ነው። በመቶ ሺዎች «የብሎኬት ካሳ» ተሰጥተው ከቤታቸው ወደ ዳር ከተማ ባዶ የሆነ 70 ካራሜትር ተባርረዋል።

ሰፈር ከነ ማህበራዊ ኑሮ ተበታትነዋል። አብዮተኛ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ማለት ይቻላል። ይህ ለተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆን ለመላው የአዲስ አበባ ህዝብ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ ይታወቃል። "Social capital" ከሰረ፤ መተባበር ጠፋ፤ መተዋወቅ ጠፋ፤ መደጋገፍ ጠፋ፤ ማህበራዊ ግብረ ገብ ጠፋ፤ ኢ-ማህበራዊነት በዛ፤ ወንጀል በዛ ወዘተ።

አንዱ ለችግሩ መፍትሄ የመሬት ፖሊሲውን መቀየር ነው።

1. ካሁን ወድያ መንግስት መሬት መውሰድ የሚችለው ለመንግስት ጥቅም እንደ መብራት፤ ውሃ፤ መንገድ ወዘተ ይሁን። ካሳውም የ«ብሎኬት ዋጋ» ሳይሆን የመሬቱ ከነቤቱ የገበያ ዋጋ መሆን አለበት።

2. መሬት ለግል ጉዳይ እንደ ኢንቬስትሜንት ከተፈለገ ኢንቬስተሩ በግል ከመሬት ባለቤቶቹ መሬቱን ተደራድሮ ይግዛ። መንግስት ጣልቃ አይግባ። ገዥ እና ሻጭ ከተስማሙ ሁለቱም ደስተኛ ይሆናሉ። ኢንቬስተሩ የገበያ ዋጋ ስለከፈለ በመሬቱ አይቀልድም አዋጪ ነገር ላይ ያውለዋል። ሻጩም ተበድያለሁ አይልም በራሴ የወሰንኩትን አገኘሁኝ ብሎ ያምናል።

የሚጠቀም ሶስተኛ ወገኖችም አሉ። መላው የአዲስ አበባ ህዝብ ከመፈናቀል የሚያመጣው ጠቅላላ ህምሞች ይተርፋል። የመንግስት ሰራተኞችም ከሙስና ፈተና ይድናሉ። ማፈናቀል ወይንም የመሬት ፖሊሲው በጠቅላላ ካድሬዎች በረካሽ አፈናቅለው በውድ ለኢንቬስተር በመስጠት ሙስና የጋበዘ ስርዓት ነበር። ፖሊሲው ከተቀየረ ሁላችንም ከዚህ ሁሉ እንተርፋለን።

Monday 1 October 2018

በሌሎች መፍረድ

ሁል ጊዜ ሌሎች ሰዎችን ጥሩ ካልሆናችሁ ብለን የምንጠብቀው የራሳችንን ድክመት በነሱ ላይ እየጫንን ስለሆነ ነው። እራሳችን ጥሩ መሆን እንፈልጋለን። ግን ባለመቻላችን ምክንያት ሌሎችን ጥሩ ካልሆናችሁ ብለን እንጫናለን። ይህን አስተሳሰብ ተከትለን አብዛኛው ጊዜ እንጨነቃለን፤ በሌሎች እንበሳጫለን እና እንፈርዳለን። ሆኖም ሁሉንም ነገር በፀሎት ማሸነፍ ይቻላል።

ቅዱስ ፖርፎሪዮስ
Elder St Porphyrios, 'Wounded by Love'

የጎሳ አስተዳደር ጎጂ መሆኑን ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች አምነዋል!

የጎሳ አስተዳደር የኢትዮጵያ ግጭት ምንጭ መሆኑ ሁሉም ፖለቲከኞቻችን ልሂቃኖቻችንም እንዳመኑበት እናውቃለን?!

1. እነ ህወሓት ከነ ቀድሞ መሪአቸው መለስ ዜናዊ ደጋግመው በሀገራችን የጎሳ እልቂት እንዳይፈጠር ያስጠነቅቁ ነበር። እንደ «ርዋንዳ» ልንሆን እንችላለን ይሉ ነበር አሁንም ይላሉ።

2. ኦሮሞ ብሄርተኞችም እንዲህ ደጋግመው ጎሳዎች በሰላም እርስ በርስ ተማምነው ተፋቅረው መኖር አለባቸው ብለው ይሰብካሉ። ካልተከባበርን የጎሳ እልቂት ሊመጣ ይችላል ብለው ያስጠነቅቃሉ። የጎሳ ግጭት እና እልቂት አንድ የሀገራችን ዋናው potential ችግር መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።

3. የለማ ቡድን ከነ ጠ/ሚ አብይ አህመድም ደጋግሞ የጎሳ አብሮ መኖር አስፈላጊነት እና የጎሳ ግጭት አደጋን ደጋግመው ይቀልጻሉ።

4. የ«ኢትዮጵያዊነት» ጎራውም ደጋግሞ ስለ በጎሳዎች የሚያስፈልገው ፍቅር እና ሰላም ይሰብካል። ይህን «የመጨረሻ» የፖለቲካ እድል ካጣን ወደ ጎሳ እልቂት ልንገባ እንችላለን ይላሉ።

እንሆ በሁሉም ጎራ ያሉት ፖለቲከኞቻችን ለኢትዮጵያን ህልውና ዋና አስጊ ነገር የጎሳ ግጭት እንደሆነ እንደሚያምኑ አሳይተዋል።

ታድያ በጎሳ አስተዳደር (ethnic federalism) እና በጎሳ ብሄርተኝነት ከዚህ በላይ ፍርድ አለ! ሀገራችን የጎሳ ግጭት አደጋ ላይ ናት ከሆነ ምክንያቱ ለ27 ዓመት የነበረን የጎሳ አስተዳደር መዋቅር ነው ማለት ነው! ብያንስ ይህ ጎሳ አስተዳደር አልሰራም ግጭቶችን አባብስዋል ማለት ነው! የጎሳ አስተዳደር የግጭት ምንጭ መሆኑ ሁላችንም አይተነዋል። ማመን ብቻ ነው የቀረን።

በመጨረሻ ማለት የምፈልገው አንዳንድ የጎሳ ብሄርተኞች የጎሳ አስተዳደር ቢቀር ታላቅ ፍርሃት አላቸው። ማንነታችን ይዋጣል ይላሉ። በፍፁም። ሀገራችን ህብረ ባህላዊ ህብረ ቋንቋዊ ነው መሆን ያለበት። ኦሮምኛ በሀገራችን በሙሉ ይነገር ነው የምንለው በኦሮሚያ ብቻ አይነገር። አዲስ አበባም ኦሮሚያም የሁላችንም ነው የምንለው የኦሮሞውች ብቻ አይደለም። ሌላውም ኢትዮጵያ የኦሮሞ ነው ነው የምንለው። ይህ እንዲሆን የሚያስፈልገው ህብረ ባህላዊ/ቋንቋዊ ስርዓት ነው ንጂ የጎሳ የክልል የአጥር አስተዳደር አይደለም።