ኢትዮጵያዊነትን የምናራምድ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ባለፉት 60 ዓመታት በተደጋጋሚ እርስ በርስ መጣላት ሀገራችንን አደጋ ላይ መጣላችን ይታወቃል (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_15.html)። መቼም በዚህ እፍረታችን ምክንያት የሀገራችንን ችግሮች በሌሎች (ጎሳ ብሄርተኞች፤ የውጭ ኃይሎች ወዘተ) ማሳበብ ሱስ ቢሆብንም እውነቱ የኛ ጥፋት መሆኑን መቀበል ግዴታችን ነው። ለሀገራችን ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች አንድነት እና ታላቅ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑ የታወቀ ነው።
ከዚህ ጽሁፍ ትምሕርት እንዲሆነን እና ወደ ፊት ስህተቶቻችንን እንዳንደግም ዘንድ ወደ ኋላ ሄጄ እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች እርስ በርስ የተፋጀንበት ታሪኮችን ማስታወስ እወዳለሁ። ዛሬ በሀገራችን ፖለቲካ ታላቁ ጉዳይ የጎሳ ብሄርተኝነት ስለሆነ እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ከታሪካችን ተምረን ለሚመጣው የፖለቲካ ሂደት በደምብ መዘጋጀት አለብን። አሁን ያለንን የታሪክ እድል መጠቀም ግድ ነው። እግዚአብሔር ከዚ በኋላ ሌላ እድል ላይሰጠን ይችላልና።
እንሆ ላለፉት 60 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሄርተኞች እርስ በርስ መጣላት ታሪክ ዝርዝር፤
1. የነ መንግስቱ ነዋይ እና ግርማሜ ነዋይ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ (1953)፤ አስፈላጊ ለውጦችን ለማምጣት ባለው መዋቀር ውስጥ በትእግስት ከመስራት ፋንታ ግርማሜ በውጭ ሀገር በተማረው «ማርክሲዝም» ፍልስፍና ተመስርቶ ወደ «ስር ነቀል ለውጥ» ወይንም አብዮት አመራ። ይህ የተከሰተው ኃይለ ሥላሴ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ ገና 18 ዓመት ካላፈ በኋላ ነው። ኢትዮጵያ ገና አቅም የሌላት ደሃ ሀገር ነበረች። ግርማሜ እና ደጋፊዎቹ ኃይለ ሥላሴ ወደ ውጭ ሀገር እንዲማሩ ከላኳቸው ተማሪዎች ነበሩ። ይህ ነበር የመጀመርያው ጊዜ የኃይለ ሥላሴ የፈረንጅ ትምሕርት ፖሊሲ በራሳቸው ላይ ጥቃት ያመጣባቸው። የኃይለ ሥላሴ መንግስት ከዚህ ተምሮ አስፈላጊ ለውጦችን ከማድረግ ፋንታ ስልጣንን ይበልት ሰበሰባ ለሰላማዊ የፖለቲካ መፍትሄ ከፍተቶችን ዘጋ።
2. የተማሪዎች ንቅናቄ፤ ከነመንግስቱ ነዋይ ግልበጣ ሙከራ በኋላም የኃይለ ሥላሴ መንግስት ተማሪዎችን ለትምሕርት ወደ ውጭ ሀገር መላክ አላቆመም። የኢትዮጵያን ባህል እና ትውፊት ከማስተማር ፋንታ የምዕራባዊ ፍልስፍና እና ሶሺያል ሳየንስ እንዲማሩ አደረገ። እነዚህ ተማሪዎች ኢ-ኢትዮጵያዊ አስተሳሰቦች ይዘው ወደ ኢትዮጵያ መንግስት እና ሌሎች መስርያቤቶች ገቡ። የቀለም ትምሕርት አለአግባብ በመደነቁ ምክንያት «የተማረ ይግደለኝ» የሚለው አባባል ተፈጠረ (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/12/blog-post_7.html)። ይህ እሳት እየተለኮሰም መንግስት በትምሕርትም ደረጃ በፍትህ በተለይም በመሬት ፍትህ ዘርፍ ምንም አላደረገም። የኃይለ ሥላሴ መንግስት የኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት መርዝ የሚሆናት ትውልድ እና ባህል ፈጠረ። የ«ጨቋኝ ተጨቋኝ» አስተሳሰብ እንዲሰፍን አደረገ። የመደብ እና የጎሳ ጦርነት እንዲጀምር አደረገ። ዛሬ የዚህን "legacy" ነው የወረስነው።
3. የደርግ አብዮት፤ በኃይለ ሥላሴ መንግስት ተሃድሶ የሚፈልጉ በርካቶች ነበሩ ግን እድሉ ሳይደርሳቸው የተማሪዎች ንቅናቄ የሚፈልገው ስር ነቀል አብዮት መጣ እና ሀገሪቷን አፈነዳ። በርካታ ልሂቃን ተገደሉ ተሰደዱ። ለኢትዮጵያ ብቻ ስያሆን ለማንም ሀገር የማይሆን የፖለቲካ ፍልስፍና ሰፈነ። መሰረታዊ ነገር እንደ «መሬት ለአራሹ» ወደ «መሬት ለመንግስቱ» ሆኖ ቀረ። ኢትዮጵያ በደምብ ቁልቁል መውረድ ጀመረች። የደርግ በኃይል የተመሰረተ ጨቋኝ አገዛዝ ለጎሳ ብሄርተኞች በንዚን ሆናቸው እና በደምብ መንቀሳቀስ ጀመሩ። ድሮ በቀላሉ በትናንሽ ሰላማዊ ለውጦች መስተካከል የሚችሉት የጎሳ ጉዳዮች ወደ ጦር ሜዳ ገቡ።
4. የኢዲዩ መፈራረስ፤ ማርክሲስት ያልሆኑት የደርግ ተቃዋሚዎች በኢዲዩ ድርጅት ስር ለመታገል ወደ ሱዳን ገቡ። ከሞላ ጎደል አንድ አቋም እና አንድ አመጣጥ ኖሯቸውም እርስ በርስ መስማማት ባለመቻላቸው ከትንሽ ጊዜ በኋላ ተበታተኑ። ይህ በአንድ አቋም ያላቸው ኢትዮጵያ ብሄርተኞች መካከል እርስ በርስ መጣላት ታሪክ እስካሁን እየተደጋገመ ነው።
5. የኢህአፓ፤ መኢሶን፤ ደርግ ግጭት፤ እንዴ ማንኛውም የማርክሲስት አብዮት አብዮተኞ የፍልስፍና፤ የጥቅም እና የስልጣን ልዩነቶቻቸውን በተብ መንጃ ነው እነ ኢህአፓ፤ መኢሶን፤ ደርግ እና ሌሎች የተወጡት። የእነዚህ ድርጅቶች አብዛኛው አባላት በ«አንድ ኢትዮጵያ» የሚያምኑ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ነበሩ። እነ ኢህአፓ በመገንጠል እናምናለን ቢሉም ብዙ ኤርትራ እና ትግራይ ብሄርተኞች ቢኖሯቸውም አብዛኞቻቸው ኢትዮጵያ ብሄርተኞች ነበሩ። መኢሶንም የኦሮሞ ብሄርተኞች ቢኖሩትም አብዛኛው በአንድነት ያሚያምን ነበር። ደርግም እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ስፍራ ነበር። ሆኖም የነዚህ ድርጅቶች መፋጃጀት ለጎሳ ብሄርተኞች ታላቅ ድል ሆነ። የኢትዮጵያ ብሄርተኛው እርስ በርስ ሲተላለቅ የጎሳ ብሄርተኛ እየቀረ ሄደ ካስፈለገ ወደ ሻዕብያ፤ ህወሓት እና ኦነግ ገባ። ቀይ ሽብሩ ካበቃ በኋላ የተቆሳሰለች ኢትዮጵያ ናት የቀረችው። በጎሳ ብሄርተኞች ለመገዛት ዝግዱ የሆነች ደካማ ኢትዮጵያ ናት የቀረችው። ደርግ ከስልጣን ሲወርድ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ልሂቃን ራሱን አጥፍቶ ርዝራዡ ብቻ ነው የቅረው። ብዙሃኑም የፖለቲካ ልቡ ተስብሮ እየተንገዳገደ ነበር። የኢትዮጵያ የወደፊት የጎሰኝነት ዘመን ተወሰነላት።
6. የመላው አማራ እና መላው ኢትዮጵያ ፓርቲዎች ግጭት፤ ደርግ ኤኮኖሚውን ገድሎ፤ ህዝቡን አጥፍቶ፤ የሶቪየት ህብረት ሲፈርስ ገንዘብ አጥቶ እነ ሻዕብያ እና ህወሓትን ወደ መንግስት አስገባ። የኢትዮጵያ ብሄርተኛው ጎራ እራሱን አትፍቶ ሜዳውን ሙሉ በሙሉ ለጎሳ ብሄርተኞቹ ተወ። እነሱም ደንግጠውም ቢሆን ያልጠበቁትም ቢሆን ሜዳውን ለመቆጣጠር ቶሎ ስራ ጀመሩ። የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራው ከድንጋጤው በኋላ ልደራጅ ሲል የለመደው አብሮ መስራት አለመቻል እርስ በርስ መጣላት በሽታው እንደገና ተነሳበት። «መላው ኢትዮጵያ» ይህን ወይንም «መላው አማራ» ይሁን አውራ ፓርቲአችን በሚለው ጥያቄ የኛ «ወታደሮች» በ«ጠላት ሜዳ» ላይ እርስ በርስ መጣላት ጀመሩ! ላለመስማማት መስማማት እና በጋራ ጥቅም አብሮ መስራት ፋንታ አንዳችን ብቻ ነው የሚቀረው ብለው እርስ በርስ ተፋጁ እና ሁለቱንም ድርጅቶች («መላው ኢትዮጵያም» «መላው አማራም») አደከሙ። የጎሳ ብሄርተኞች ከዳር ሆነው በሳቅ ሞቱ። ግን አሁንም እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ጥፋታችንን ከማመን እነ ከመፍታት ፋንታ የጎሳ ብሄርተኞች ጥፋት ነው እነሱ ናቸው ያከፋፈሉን ብለን እንደ ህጻናት አሳበብን። እንሆ ችግራችንን ስላላመንን አልፈታነውም። አልፎ ተርፎ ይህን ስህተትን ወደፊት ለመድገም እራሳችንን አዘጋደን!
7. የቅንጅት ግጭት፤ ወደ ምርጫ 97 ስንገባ ጠ/ሚ መለስ ዘናዊ በተለያዩ ምክንያቶች ነጻ ምርጫ እናሸንፋለን ዓለም ያከብረናል ብለው ነጻ ምርጫ አወጁ። ድንቅ ውሳኔ ነበር አሁንም ይደንቃል። ግን በዛን ግዜ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራው በራሱ ካመጣው ቁስሎቹ ገና አልዳነም ነበር። ጠንካራ ድርጅት ከሀገር ውስጥም ውጭም አልነበረም። የእርስ በርስ ጥሉ እንዳለ ነበር። በዚህም ምክንያት ነው የኢትዮጵያ ብሄርተኛው ወደ አንድ ስምምነት (ቅንጅት) የገባው በመጨራሻው ደቂቃ ከምርጫው ሶስት ወር በፊት! ግን አርፍዶ ቢዘጋጅም እንደምንም አድርጎ የኢትዮጵያ ብሄርተኛው ጎራ በምርጫው ተሳትፎ በሚደንቅ ሁኔታ አሸነፈ። ካሸነፈ ብኋላ የምናውቀው ፈተናዎች አጋጠሙት። እነዚህን ፈተናዎች በደምብ አድርጎ ወደቀ። በሰው የተፈጥሮ ባህሪ ጓዶች አብረው ሲታሰሩ ፍቅራቸው እና ትብብራቸው ይጨምራል። የቅንጅት መሪዎች ሲታሰሩ ጭራሽ እርስ በርስ ተጣሉ!ድርጅቱም ምን ያህል ባዶ እንደነበረ ታየ። ከላይ የተወሰኑ መሪዎች በ100 የሚቆጠሩ ነበሩ ከዛ በታች ግን መዋቅር የሚባል ነገር አልነበረም። መዋቅር ስል በይፋ ብቻ ሳይሆን በልብም አልነበረም። ስለዚህ መንግስት ቅንጅትን ሲያጠቃ በምርጫው 70% እንዳሸነፈ ድርጅት ጥቃቱን ጠንክሮ ከመቋቋም ይልቅ እንደ ምንም ድጋፍ የሌለው ድርጅት ቀለጠ። ቅንጅት አሸዋ ላይ የተገነባ ቤት መሆኑን አየን። ግን ለዚህ ሽንፈት ምክንያት እንደነበረ እንገንዘብ። የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ልሂቃን ከዛ በፊት ለ30 ዓመታት እርስ በርስ መፋጀት ታሪክ ምክንያት በጣም ሳስቶ ነበር። ለዚህም ነው ቅንጅት በተንሽ ግፊት የፈራረሰው። መሪዎቹ "cream of the crop" ሳይሆኑ ካለፈው 30 ዓመት የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ጎራ እርስ በርስ መጨራረስ የተራረፉ ነበሩ። ታሪካችን ምን ያህል እንደ ጎዳን አየን።
8. ዛሬ፤ አሁንም የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ጎራ እጅግ ደካማ ነው። አሁንም ሀገር ውስጥም ውጭም ብዙሀኑን በሚገባው የሚወክል ድርጅት የለውም። ግን ብዙሃኑ አለ ልሂቃን እየታገለ እንደሆነ የሚያሳየው እንደ ጠ/ሚ አብይ አህመድ አይነቱን ሰዎች ከዚህ ብዙሃን መውለዳቸው ነው። እንጂ ከ27 ዓመት የጎሳ ብሄርተኝነት በኋላ ኢትዮጵያ እውነትም የብሄር ብሄረሰቦች እስር ቤት ብትሆን እና በርካታ የሀገር ብሄርተኛ ባይኖራት እንደ አብይ አይነቱ አይፈጠርም ነበር እንቋን ወደ ስልጣን መግባት። ግን ይህ ብዙሃን ልሂቃን ያስፈልገዋል። እነ ጠ/ሚ አብይ በርካታ እገዛ ያስፈልጋቸዋል። ቢያንስ እንቅፋት አያስፈልጋቸውም!
አንድ እንቅፋት ሊሆን የሚችለው አዲሱ የ«አማራ ብሄርተኝነት» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/06/blog-post_14.html) ነው። የአማራ ብሄርተኝነት በኢትዮጵያዊነት አምናለው ይላል ግን የኢትዮጵያ ብሄርተኛውን ጎራ የመከፋፈል እና የማድከም አዝማምያ አለው። የአስተያየት ልዩነት መልካም ነው በአንድ አንድ ነገር ሳይስማሙ አብሮ መስራት ይቻላል። ግን አሁን የሚታየው የአብሮ መስራት አዝማምያ ሳይሆን የጥሎ ማለፍ መንፈስ ነው። የአማራ ብሄርተኛው ጎራ አንዱ መፈከሩ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ድርጅቶች ዋጋ የላቸውም ነው። ከኢትዮጵያ ብሄርተኛ ድርጅቶች ጋር አብሮ ከመስራት ያጣጥልዋቸዋል። ያው የነ ሻዕብያ፤ ህወሓት፤ ኦነግ ፎቶኮፕይ ማለት ነው። የህዝብን ብሶት በጎሳ ቤንዚን ለኩሶ የፖለቲካ ኃይል ማግኘት ነው። ልክ ህወሓት በመጀመርያ ነባር የጥግራይ ልሂቃንን እንዳጠፋ አንድ አንድ የአማራ ብሄርተኞች የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ድርጅቶችን ማጥፋት ይፈልጋሉ። እንደነ ኢህአፓ/መኢሶን/ደርግ የማርክሲስት ዜሮ ድምር ፖለቲካ ማለት ነው።
ይህ የሚመስልኝ ታሪክን መድገም ነው። የኢትዮጵያ ብሄርተኞች እንደገና እርስ በርስ ሲፋጁ የጎሳ ብሄርተኖች ስልጣን ይቆጣጠራሉ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ብዙሃን እንደገና መሪ አልባ ሆኖ ይጠቃል። ከታሪካችን ብንማር ይበጀናል። በዛሬው የፖለቲካ ለውጥ እግዚአብሔር የማይገባንን እድል ሰጥቶናል። እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ልሂቃን ምንም የሚጠቅም ነገር ሳናደርግ ከኢህአዴግ መሃል የለማ ቡድን ተነስቶ ለአንድነት መንፈስ ቆሟል። ታላቁ «ኢትዮጵያዊ» ዶናልድ ለቪን ደጋግመው እንዳሉት በርካታ እድሎቻችንን አበላሽተናል (https://scholarworks.wmich.edu/ijad/vol1/iss1/3/)። ይህን እድል ደግሞ ካበላሽን ታሪክ ለዘለዓለም ይወቅሰናል።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!