Showing posts with label conflict. Show all posts
Showing posts with label conflict. Show all posts

Tuesday, 16 April 2019

በስመ አብ! አሁንም ምሁሮቻችን ይህን ስርዓት «multiculturalism» ይሉታል

ይህ ውይይት ገንቢ ይመስለኛል፤ ተመልከቱት። ግን አሁንም በርካታ ሰዎች የሚሳሳቱትን ስህተት ሰርተዋል። አሁን ያለውን multinational federalism (ይጎሳ አስተዳደር) "multiculturalism" ብለው ይጠሩታል። ይህ መሰረታዊ የቃል እና ሃሳብ አጠቃቅም ስህተት ነው።

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በዓለም ብቸኛ እና ጸንፈኛ የሚያደርገው በጎሳ፤ በ«ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች»፤ የተመሰረተ ነው። ይህ ሌላ ሀገር የለም። የጎሳ ፖለቲካ እና የጎሳ ምብት ሌሎች ሀገራት አሉ፤ ግን የህገ መንግስታቸው መሰረት አይደለም። እንደ ካናዳ፤ ህንድ፤ ወዘተ የጎሳ ፍላጎት፤ መብት፤ ጥያቄ፤ ወዘተ፤ የባህል እና ቋንቋ ብዝሃነት፤ የማንነት ምዝያነት ወዘተ ከኢትዮጵያ በተሻለ መንገድ ያስተናግዳሉ። ግን ይህን የሚያደርጉት የባህል እና እቋንቋ ብዝሃነት የሚያስተናግድ የዜግነት ህገ መንግስት ተጠቅመው ነው እንጂ ቀጥታ የጎሳ ሀገ መንግስት ተጠቅመው አይደለም።

ልዩመንት ምንድነው? የኢትዮጵያ ባለቤቶች ጎሳዎች ናቸው። ስለዚህ እንደ ቤኒሻንጉል አይነቱ ክልል ክልሉ የተወሰኑ ብሄር ተወላጆች ንብረት ነው ብለው በህግ መደንገግ ይችላሉ። የሌላ ብሄር ተወላጅ ቤኒሻንጉል ሲኖር እንደ ሁለተኛ ዜጋ ነው። የዜግነቱ መብቶች ከቤኒሻንጉል ጎሳ መቶች በታች ነው። ይህ ዜጋ መሬትና ቤት ካለው ከቤኒሻንጉል ጎሳዎች የተከራየው ነው። ወዘተ፤ ሁለተኛ ዜጋ ነው።

በነ ህንድ አይነቱ ሀገር ክፍለ ሀገሮቹ የተከለሉት ከሞላ ጎደል ጎሳን ታስቦ ነው። ስለዚህ በያንዳንዱ ክልል ብዙ ቁጥር ያለው ጎሳ የጎሳ መብቱን ያስፈጽማል። ለምሳሌ ቋንቋውን እና ባህሉን የክልሉ ቋንቋእና ባህል ያደርጋል። ወዘተ። ግን እዛ የሚኖር የማንኛውም ጎሳ ተወላጅ ሙሉ መብት አለው! ይህ ነው ልዩነቱ። «መጤ» አይደለም። የክልሉ እኩል ባለቤት ነው።

ይህ ልዩነት ውጤቱ ምንድነው? በጎሳ ፌደራሊዝም ጎሳ ከሁሉም በላይ ስለሆነ ግጭት ይበዛዋል። ይህን በኢትዮጵያ በደምብ አይተነዋል እያየነውም ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2019/03/blog-post_4.html)። የቋንቋ እና ባህል ብዝሃነት ያለው የዜግነት ፌደራሊዝም ግን ግጭት ቢኖርም ዜግነት ከሁሉም በላይ ስለሆነ ግጭቶቹ እጅግ አነስተኛ ናቸው።

ስለዚህ እንደገና... ቁንቋችንን እናስተካከል። ይህ ህገ መንግስት multiculturalism አይደለም ያመጣው። Multinationalismን ነው ያመጣው። የትም ሀገር የሌለ ጸንፈኛ experiment ነው የሚያደርገው። ይህ ሙከራ ኢትዮጵያን የግጭቶች ምህዳር አርገዋታል። አሁን የሚያስፈልገን ወደ ለዘብተኛ መንገድ ተመልሶ ወደ የቋንቋ እና የባህል ብዝሃነት ያለው በተዘዋዋሪ የጎሳ ፋልጎቶችን የሚያስተናግድ የዜግነት አስተዳደር ነው የሚያስፈልገን።


Monday, 1 April 2019

የቅንጅት ታሪክ ሊደገም ነው?

ታሪኩን ለማታስታውሱ ወጣቶች፤ የቅንጅት «ፓርቲ» አመራሮች ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ኃይለኛ የእርስ በርስ የፖለቲካ ጦርነት አካሄዱ። ዋና አቋሞቻቸው አንድ ነበር፤ የኢህአዴግ/ህወሓት አምባገነን አገዛዝን ማስቆም እና «ዴሞክራሲ» እና የዜግነት ፖለቲካን ማምጣት። እንደዚህ አይነት ግዙፍ እና ዋና ጉዳዮች ላይ የሚጋሩ ቢሆንም ሁለቱ የቅንጅት ወገኖች አብሮ ለመስራት አልፈለጉም፤ መጨራረስን መረጡ። ጥላቸው እየከረረ ሲሄድ እርስ በርስ ያላቸው ጥላቻ ለኢህአዴግ ካላቸው ጥላቻ በልጦ ተገኘ! የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እና ዴሞክራሲ ትግል እንደገና ፈራረሰ ተበታተነም (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html)።

ዛሬም ይህን ታሪክ ካልደገምን እያልን ይመስላል። የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ነኝ፤ የዜግነት ፖለቲካ ደጋፊ ነኝ፤ ዴሞክራሲን እደግፋለሁ፤ ጎሰኝነት ይውደም፤ የምን ሆነን እነዚህ የጋራ ፍላጎት እና ጥቅማችን አብሮ በመስራት ከማስከበር ፋንታ በትናንሽ የሚለያዩን ጉዳዮች እንፋለማለን!! የጉድ ጉድ ነው። ይህ ሁሉ የምንጋራው ዋና ነገሮች እያሉ እንጣላለን። ምን ማለት ነው?

ለምሳሌ ግንቦት 7ን መሳደብ። አዴፓን መሳደብ። የእስክንር ነጋን ንቅናቄ ማጥላላት። ምን ማለት ነው? በሰለጠነ ፖለቲካ እነዚህ ሁሉ ጠንካራ አጋሮች መሆን ይኖርባቸው ነበር። ትናንሽ የታክቲች እና ስትራቴጂ ልዩነቶች አላቸው። በመነጋገር እና መናበብ እርስ በርስ መጠቃቀም እና መደጋገር ይችላሉ። ለነገሩ የበሰለ አብንም እንዲሁ የዜግነት ፖለቲካ ነው የምፈልገው ሰለሚል። ግን የለም። 100% ካልተስማማን ወይንም የግል ጸብ ካለን ከምንተባበር ኦነግ ቢያሸንፍ ይሻላል ነው አመለካከታችን።

የቅንጅት እርስ በርስ ጦርነት እንደ ባቡር ግጭት ለረዥም ጊዜ እንደሚከሰት እያየን ምንም ማረግ ሳንችል የተከሰተ እልቂት ነበር። አሁንም ይህ ባቡር ይተየኛል፤ የግጭት ጉዞውን ጀምሯል።


Monday, 4 March 2019

የጎሳ ፌደራሊዝም ችግር አንድ ነው፤ የግጭት መንስኤ ነው!

ዛሬ አንድ ሁለት ውይይቶች ስለ ሀገራችን «የጎሳ ፌደራሊዝም» ተመልክቼ ነበር። ውይይቶቹ ያተኮሩት በጎሳ ፌደራሊዝም እንደ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ተናጋሪዎቹ ታሪክን እና ርዕዮት ዓለምን ፈትሸው የጎሳ ፌደራሊዝም ለሀገራችን ይበጃል ወይንም አይበጅም ብለው ተከራከሩ። Of course ውይይት/ክርክሩ የትም አልደረስም። The participants, as usual, talked right past each other።

በመጀመርያ ደረጃ አንዱ የሌላውን ፍላጎት የማይረዳበት ውይይት ውይይት አይደለም። ስለ ጎሳ ፌደራሊዝም የሉን ውይይቶች እንዲህ ናቸው። እኛ አቋማችንን እንናገራለን ሌላውም እንዲሁ አንድ ሌላው አይገባውም ውይይቱም ባለመግባባት ያልቃል።

ይህ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት የውይይት እና ቅራኔ መፍታት ስልት በማጣት ነው። ግን አሁን ማተኮር የምፈልገው እዚህ ላይ አይደለም። ሁለተኛው ምክንያት ነው፤ ይህ ደግሞ የጎሳ እና ማንነት ጉዳይ ስሜታዊ በመሆኑ ለውይይት አይመችም። አይሆምም ማለት ይቻላል። «እኔ መጀመርያ ኦሮሞ ነኝ ቀጥሎ (ምናልትባት) ኢትዮጵያዊ» ሲል አንዱ ሌላው «እንዴት እንዲህ ትላለህ» ብሎ ሁለቱም በስሜታቸው ይመራሉ። አንዱ ሌላውም ማሳመን አይችልም።

ለዚህ ነው በጎሳ ፌደራሊዝም ጉዳይ ታሪክን እና ርዕዮት ዓለምን ፈትሸን መከራከር የትም የማያደርሰን። በጎሳ ፌደራሊዝም የሚያምን እና የጎሳ ፌደራሊዝምን የሚጠላው ሁለቱም ምክንያቶች በመሰረቱ ስሜታዊ የማንነት ናቸው። እነዚህን በርዕዮት ዓለም እና ታሪክ (in the eye of the beholder) ማስታረቅ አይቻልም።

ሁለቱን ጎራዎች ለማግባበት ወደ ሌላ level መሄድ ያስፈልጋል። ይህ ደረጃ እንዲህ ነው፤ እኔ የጎሳ ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ አይሆንም የምልበት ምክንያት ታሪክ እና ርዕዮት ዓለም ሳይሆን በ evidence ምክንያት ነው። የ24 ዓመት ታሪክ ከነ ያለፈው አንድ ዓመት የለውጥ ዘመን ታሪክ የሚያሳየው የጎሳ ፌደራሊዝም የግጭት መንስኤ መሆኑ ነው። የጎሳ ፌደራሊዝም በጎሳዎች መካከል በርካታ ግጭቶች እንዲኖሩ አድርጓል። ሰዎች በጎሳቸው ምክንያት የሚጎዱበት ዘመን አምጥቷል። ይህ ጉዳት ለተወሰኑ ጎሳዎች ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሩ ነው። ለዚህ በርካታ የ25 ዓመት evidence አለ።

ለዚህ ነው የጎሳ ፌደራሊዝም መቀየር አለበት ብለን መከራከር ያለብን። የ24 ዓመት የጭቆና እና የአንድ ዓመት የአንጻራዊ ነጻነት መረጃ የሚያሳየን የጎሳ ፌደራሊዝም ህግ እና መንፈስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን እንደጎዳ ነው። ሶማሌ በሶማሌነቱ፤ ኦሮሞ በኦሮሞነቱ፤ ጊዴኦ በጊዴኦነቱ፤ አማራ በአማራነቱ፤ አንዋክ በአንዋክነቱ፤ ወላይታ በወላይታነቱ፤ ስዳማ በሲዳማነቱ፤ ወዘተ ተጎድቷል። የጉዳት ፈጻሚዎቹም እንዲሁ የተለያዩ ናቸው። «ህወሓት» ወይንም የህወሓት አሽከሮች ብቻ አይደሉም ጨቋኞቹ። ህዝቡ እራሱ ይጭቋቆናል። ለዚህ በርካታ መረጃ አለን።

አንድ ታካቅ መራጀ ደግሞ የሁሉም ጎራ ፖለቲከኞች «ካልተጠነቀቅን እርስ በርስ እንፋጃለን» ማለታቸው ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/blog-post.html)! የጎሳ ፌደራልዚምን የሚደግፉትም የማይደግፉትም የጎሳ እልቂት is right around the corner ብለው ደጋግመው ይነግሩናል። ለጎሳ ፌደራሊዝም ከዚህ የባሰ indictment የለም!

ስለዚህ ለ«ዜግነት ፖለቲካ» ደጋፊዎች እና ሌሎች የዚህ የጎሳ ፖለቲካ የሚጠሉ ሰዎችን የምመክረው፤ ስሜትን በሃሳብ አትከራከሩ፤ የትም አትደርሱም። በመሰረቱ የጎሳ ፌደራሊዝም ሰውን የሚጎዳ ባይሆን ምን ችግር አለው? ምንም። የጎሳ ፌደራሊዝም ኢትዮጵያን በሰላም ቢያስተዳደር እኔ የሚጀመርያ ደጋፌው ሆን ነበር። ግን አይደለም። ሃቁ ይህ ነው። የጎሳ ፌደራሊዝም የምንጠላው የግጭት እና ጭቆና መንስኤ ስለሆነ ነው። ይህ ደግሞ በመረጃ የተመሰረተ statement ነው። ክርክራችን በታሪክ እና ርዕዮት ዓለም የተገደባ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ መረጃ የተመሰረተ ነው። ይህ መከራከርያ መንገድ ነው አዋጪ ብዬ የማስበው።

Thursday, 17 January 2019

የጎሳ አስተዳደር አንድ እና አንድ ችግር ነው፤ የግጭት ምንጭ ነው

ፖለቲካ በሃሳብ ብቻ ነው ምሆነ ያለበት እንጂ በጎሳ መሆን የለበትም ሲባል ዋናው ምክንያቱን አጥብቀን ማስረዳት አለብን። ምክንያቱ የብሄር ፖለቲካዊ ጥያቄ ስለሌለ አይደለም፤ ጎሳዎች ስላልተጨቆኑ አይደለም፤ የርዕዮት ዓለም ጉዳይ አይደለም። መሰረታዊ ምክንያቱ፤

«ጎሳ ወደ በፖለቲካ ሲገባ የግጭት ምንጭ ይሆናል ነው»።

ይህ ደግሞ የርዕዮት ዓለም ወይንም የቴኦሪ አመለካከት ሳይሆን በተግባር empirically በሀገራችን (ሌሎችን ሀገራት ምሳሌ ትተን) የያእነው እያየን ያለው ነው። በህወሓት ዘመን የጎሳ አስተዳደር የግጭት ምንጭ ነበር። ግጭቶቹ ሀውሓት የሰራቸው ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ሌሎች ነበሩ። በዴሞክርሲ እጦት ሳይሆን በሌላ ምክንያቶች የተነሱ ነበሩ።

አሁን ደግሞ «ነፃነት» ባለበት የጠ/ሚ ዓቢይ ዘመን የጎሳ ግጭቶች እየቀጠሉ ነው። ይህ አስምሮ የሚያሳየው የጎሳ አስተዳደር ወይንም የጎሳ ፖለቲካ በነፃነት እና ዴሞክራሲያዊ አገዛዝም ግጭቶች የመጣል ነው።

ስለዚህ የጎሳ ፖለቲካ/አስተዳደር የግጭት ምንጭ ነው። መብት ነው። ጥያቄዎችን ያስተናግዳል። ግን ግጭት እና ጦርነት ያመጣል።

አማራጩ ምንድነው። የጎሳ ጥያቄዎች በጎሳ አስተዳደር ሳይሆን በሌላ መልኩ ይመለሱ። ለምሳሌ «የአካባቢዬ ባህል አይናድ» ከሆነ በአካባቢ ፖለቲካዊ መብቶች ይመለስ። «ቋንቋዬ ይስፈን» ከሆነ በአካባቢ ፖለቲካ እና በብሄራዊ ዴሞክራሲ መንገድ ይመለስ። ወዘተ። የጎሳ ጥያቄዎች በዚህ መልኩ ሊመለሱ ይችላሉ። እንኳን እንደ ኦሮሞ አይነት የግዙፍ ጎሳ ጥያቄ የአናሳዎችም በዚህ መልኩ ይመለሳል።

Monday, 17 December 2018

ስለ ህገ መንግስት አንድ የውይይት ሃሳብ

አሁን ያለን የጎሳል አስተዳደር (ethnic federalism) የግጭት መንስኤ እንደሆነ የ27 ዓመት መረጃ አለን ብዬ ተከራክርያለሁ ከጽሁፎቼ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_89.html)። በህወሓት አገዛዝ የነበሩት የጎሳ እና የድንበር ግጭቶች ህወሓት ብቻውን ያካሄደው፤ የቀሰቀሰው፤ ያስተባበረው ብቻ አልነበሩም። ህወሓት በአስተዳደሩ ምክንያት ያሚመጡትን ችግሮች ለራሱ ጥቅም ያባብስ ነበር እና ያሉ ቅራኔዎችን ያባብስ ነበር እንጂ ችግሮችን ከሀ መፍጠር አቅም አልነበረውም። ዛሬም ለምሳሌ የሲዳማ እና ወላይታ ግጭት ስንመለከት አዎን የህወሓት እና ሌሎች ነበሮች እጅ ቢኖርበትም የጎሳ አገዛዙ መሰረታዊ መንስኤ ነው። በዚህ ምክንያት ዛሬ ያለው የጎሳ አስተዳደር ለሀገራችን ሰላም አይሆንም።

አማራጩ ምንድነው የሚለው ጥያቄ ላይ ጊዜ ብናጠፋ ጥሩ የመስለኛል። በዚህ ጉዳይ የተለያየ አቋም ያለን ኢትዮጵያዊያን ስለዚህ ገና ብዙ መነጋገር አለብን እስካሁን በቂ የተነጋገርን አይመስለኝም። ስንወያይም አብዛኛው ጊዜ የራሳችን አቋም ላይ ነው የምናተኩረው እንጂ በቂ ሌላውን አንረዳም።

ዛሬ አንድ አስተያየት ልስጥ… የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎች ኢትዮጵያ የብሄሮች ስብስብ ነው መሆን ያለበት ነው። የመጀመርያ ማንነታችን ጎሳችን ነው፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነታችን ሁለተኛ ነው ነው የሚሉት። የሀገር ስሜት አለን ነው። ኦሮሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለች ሀገር ናት። ባለቤቷም የኦሮሞ ህዝብ ነው። ግን በታሪክ ምክንያቶች እና ዛሬ ባለው ነባራዊ ሁኔታ አብሮ መኖር ስላለብን ተገንጥለን አንኖርም ብሄሮች እርስ በርስ ውል ይኖራቸዋል ነው። እንደ ብሄር ክልል ወይንም «ትንሽ ሀገር» ከሌለን የሀገራዊ መብታችን ተወሰደ ማለት ነው። ልክ እንደ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ሰው ከኬንያ ጋር በግድ ሙሉለሙሉ ተቀላቅለህ አንድ ሀገር ሁን ቢባል አይ አገርነቴን መጠበቅ እወዳለሁ እንደሚል አማራውም የብሄር ክልል ይቀር ቢባል ማንነቱ እንደተወሰደበት ይሰማዋል ነው። በአጭሩ ይህ አንዱ የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎች አስተሳሰብ ይመስለኛል።

እስቲ ለዚህ አንድ የሚሆን አማራጭ መልስ እንስጥ። ከህገ መንግስቱ «ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች» የሚለውን በሙሉ አውጥተን ግለሰባዊ ብቻ እናድርገው። ግን አሁን ያሉትን ክልሎች እንጠብቅ። ለክልሎች አሁን ካሉት ተጨማሪ መብቶች እንስጥ። ከዛ የኦሮሚያ «ሀገራዊ» ምስልን እንመልከት። በቋንቋ፤ ባህል፤ ማንነት፤ ወዘተ በኦሮሚያ አብዛኛው ኦሮሞ ስለሆነ የሚኖረው ፍላጎቱ እንዲሰፍን ያደርጋል። ይህ የድምጽ ብልጫ ኦሮሚያ ክልልን ከሞላ ጎደል ኦሮሚያ ሀገር ሊያደርገው ይችላል። ግን ሀገር አይባልም እና ኦሮሞ ዘር ያልሆኑ ከኦሮሞዎች እኩል መብት ይኖራቸዋል። ግን አናሳ በመሆናቸው ብዙ ተጽዕኖ አይኖራቸውም።

ለኔ ይህ አካሄድ የጎሳ አስተዳደርን መጥፎ ጎን ያስወግዳል ማለትም ሁሉ ጉዳያችን በጎሳ የተመሰረተ እንዳይሆን ያደርጋል። አንደኛ/ሁለተኛ/ሶስተኛ ዜጋ፤ መፈናቀል፤ የጎሳ ብቻ ፖለቲካ ወዘተ እንዳይኖር ያደርጋል። ግን የጎሳ ወይንም ብሄር መብት ያስከብራል። በዚህ በጎሳ መብት ማስከበር ከጎሳ አስተዳደር ብዙ ልዩነት አይኖረውም።

ይህ አንድ የመሃይም ለውይይት የቀረበ ፕሮፖዛል ነው። የጎሳ ብሄርተኞችን ፍላጎት ያሟላ ይሆን። የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ፍላጎትስ?

Thursday, 6 December 2018

የ «መጠላለፍ» ፖለቲካ

በቅርብ ጊዜ ነው የ«መጠላለፍ ፖለቲካ» የሚለውን አባባል ያወቅኩት። በጣም የወደድኩት አባባል ነው፤ ችግሩን በሚአምር መንገድ የሚገልጽ።

የመጠላለፍ ፖለቲካ ሲባል የሚታየኝ የአንድ የኳስ ቡድን ተጨዋቾች በግጥሚአ መሃል እርስ በርሳቸው ላይ «ፋውል» ሲሰሩ እና ሲጠላለፉ ነው! የሌላው ቡድን ተጨዋቾች ገርሟቸው በንቀት ያመለከቷቸዋል!

አንድ ተጨዋች ከአሸናፊ ቡድን መሆን ይጠቅመዋል። የተጨዋቹን ዋጋ ማለትም ደሞዝ እንዲጨምር ያደርጋል። ስለዚህ የእያንዳንዱ ተጨዋች ጥቅሙን የሚያስከብረው ቡድኑ እንዲያሸንፍ በማድረግ ነው። ግን ተጨዋቾቹ ይህን አይገነዘቡም። ምናልባት ከባልደረቦቻቸው ጋር ትናንሽ ጸቦች አላቸው። በነዚህ ትናንሽ ጸቦች ምክንያት ያላቸው ንዴትን ለመወጣት ብለው ጥቅማቸውን ይጎዳሉ። ቡድናቸው እንዳያሸንፍ ያደርጋሉ!

ፖለቲካችንም እንዲሁ። እጅግ የሚያማርረኝ የፖለቲካ ታሪካችን የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ፖለቲካ በተለይ ከ1967 በኋላ ነው። ብዙ ጽሁፎች ስለኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች አሳዛኝ ታሪክ ጽፍያለሁ። ከኢዲዩ ጀምሮ እስከ ቅንጅት ከዛም አልፎ ታሪካችን የ«መጠላለፍ ፖለቲካ» ነው። ከሁሉም ታሪክ በላይ ይህንን በደምብ የሚገልጸው የቅንጅት ታሪክ ነው። የቅንጅት አመራርም ተከታዮችም እስክንቆሳሰል ተጠላለፍን! በአስርት ሚሊዮን ሰው የተደገፈውን ድርጅት አፈረስን።

ብዙዎቻችን ደጋግመን ከነህ ከመጠላለፍ ታሪካችን እንማር እንላለን። መቼም አይደገም እንላለን። በመጠላለፍ ኢትዮጵያን ወደ አደጋ ጫፍ አድርሰናታል። እግዚአብሔር ጥፋት ይበቃችኋል ብሎ አቢይ አህመድን ልኮልናል። የህን የመጨራሻ እድላችንን በአግባቡ እንጠቀምበት።

https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html

Thursday, 15 November 2018

ማን ነው የሚተርፈው?

አሉ የኢሳት ተንታኞች። በኢህአዴግ ዘመን የተከሰቱ የጭካኔ እና ሙስና ወንጀሎች ክር መተርተር ሲጀምር ማን ከኢህአዴግ እና ዙርያ ይተርፋል? ማን ያላጠፋ አለ?

ወይ ሁሉንም ማሳሰር ነው ወይንም እንደ ደቡብ አፍሪካ የእርቅ ስርዓት አቋቁሞ ፍትህ በእርቅ እንዲመጣ ማድረግ ነው ተባለ። ከነዚህ ደግሞ ሁለተኛው የእርቅ ስርዓት መንገዱ ጥሩ እና እውነት የያዘ አማራጭ ነው።

ለኔ ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ዋናው ጓይ ይህ ነው፤ ማን ይተርፋል ብለን ስንጠይቅ ለምንድነው ስለኢህአዴግ እና ሌሎች ብቻ የምናወራው? «እኛሳ»? ጥፋት በማድረግም ባለባድረግም ነው ልንከሰስ ይገባል።

አዎን መስረቅ ጥፋት ነው። ግን የሚጎዳን አለመርዳትም እንዲሁ ጥፋት ነው። ስንቶቻችን «ብዙሃን» ባልደረቦቻችን በተለያየ መንገድ የፖለቲካ እና ማህበረሰባዊ ጥቃት ሲደርስባቸው ዝም ያልነው እና ያልረዳናቸው? ጎረቤታችን ተቸግሮ ቢያንስ «ይሄው 100ብር፤ ስለተቸገርክ ስለተጎዳህ አዝናለሁ» ያልን ስንቶቻችን ነን? እርግጥም ስንቶቻችን ነን ከጎረቤትና ባልደሮቦቻችን የከፋ ግጭት እና ቅራኔ ያለን። እርስ በርስ ተከፋፍለን ለከፋፍሎ መግዛት መንግስት እራሳችንን ያመቻቸን?!

የፖለቲካ እና ማህበራዊ ጥፋቶች የማህበሩ ማለትንም የእያንዳንዶቻችን ነው። No man is an island። ጥፋታችንን አምነን ወደ ንስሃ ከገባን ብቻ ነው እርፍት እይሚኖረን። እንጂ ዎንጀሎችን አስረን ሰላም ይመጣል ማለት ታሪክን አለማወቅ እና እራስን ማታለል ነው።

ታዋቂው ሩሲያዊ የፖለቲካ እስረኛ እንዳሉት፤
«ከእስርቤታችን አልጋ የሆነው የበሰበሰው ገለባ ላይ ጋደም ብዬ ነው ለመጀመርያ ከውስጤ የበጎ መንፈስ የተሰማኝ። ቀስ በቀስ መረዳት የጀመርኩት ይህ ነው፤ ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር በሀገሮች፤ መደቦች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መካከል አይደለም የሚያልፈው፤ ይህ መስመር የሚያልፈው በያንዳንዱ የሰው ልብ መኻል ነው። መስመሩ እድሜአችን በሙሉ ከውስጣችን ወደፊት ወደኋላ ይላል። በክፉ የተሞሉ ልቦችም ቢያንስ ቅንጣት ያህል ጥሩነት ይኖራል፤ ከሁሉም ጥሩ ከሚባለውም ልብ ከአንድ ጥጓ ትንሽ ክፉነት ይኖራል።
በየቦታው እየዞሩ ያሉ ክፉ ስራ የሚሰሩ ክፉ ሰዎች ቢኖሩና እነሱን ከኛ መለየትና ማጥፋት ብቻ ቢሆን ኖሮ እንዴት ቀላል ነበር? ግን ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር ከያንዳንዱ የሰው ልጅ ልብ መካከል ነው የሚያልፈውና ማን አለ ከራሱ ልብ ቁራጭ ቆርጦ ለማጥፋት ፈቃደኛ ይሆነ?»
https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_30.html

Wednesday, 7 November 2018

የጎሳ አስተዳደርን አደገኝነት አለመረዳት ትንሽ ግትርነት ይመስለኛል

ከዚህ ገንቢ ውይይት (https://www.youtube.com/watch?v=tVqQW7Sh_G0) ስለ ጎሳ አስተዳደር (ፌደራሊዝም) ብዙ ጊዜ የሚነሳ ነጥብ ተነስቶ ነበር። ይህም፤

«የጎሳ ፌደራሊዝም በትክክሉ አልተሞከረም። እስካሁን ዴሞክራሲ አልነበረም፤ የአምባገነናዊ ጭቆና ነበር። የህዝቡ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅምም አልተከበረም። ለዚህ ነው ፖለቲካዊ ችግሮች የሚታዩት። ዴሞክራሲ፤ የኤኮኖሚ እና ማህበራው ፍትህ ሲኖሩ የጎሳ አስተዳደር በደምብ ይሰራል።»

አንዱ ተንጣኝ ይህንን አቋም ለመግለጽ "You can't judge a philosophy by its abuse" አይነት አባባል ተናግረዋል።

መቼስ ስለ ኮምዩኒዝምም እንዲህ ማለት ይቻላል! በትክክል ቢፈጸም ገነትን ያመጣልን ነበርና።

የጎሳ አስተዳደር ችግሮች ለማንኛውም አጉል risk ወይንም የራቀ እና ጸንፍ የያዘ ፍልስፍና ማቀፍ ለማይፈልግ ሰው ግልጽ የሆነ ይመስለኛል። ምክንያቶቹ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_89.html)፤

1. ደጋግሞ እንደሚባለው የትም ሀገር የጎሳ አስተዳደር የለም። ይህ በራሱ የጎሳ አስተዳደር እጅግ ጸንፍ የያዘ አስተዳደር እንደሆነ ይገልጻል።

2. በተለያዩ ሀገራት የጎሳ አስተዳደር የሌላቸውም ግን በተለያየ በፖለቲካ ክፈተቶች ጎሰኝነት ሲሰፍን ያለው ጉዳት አይተናል። የጎሰኝነት ችግር አንዳንድ ሀገሮች እስከ የጎሳ ፓርቲዎችም መከልከል አድርሷቸዋል።

3. የ27/22 ዓመት የሀገራችን የጎሳ አስተዳደር ተለምዶ ለጎሳ አስተዳደር አደገኝነት በቂ ማስረጃ ነው። አዎን ዴሞክራሲ አልነበረም ግን የጎሳ ተኮር ግጭቶች እና ቅራኔዎች በዴሞክራሲ እጦት ማሰበብ አይቻልም። መቼም ማንም reasonable ሰው እንዲህ የሚያየው አይመስለኝም። ምንም አይነት ችግሮች በጎሳ ግጭት መልኩ እራሳቸውን የሚገልጹ ከሆኑ ጎሰኝነት ነው ችግሩ ማለት
 ነው! አልፎ ተርፎ አሁን ዴሞክራሲ እየመጣ ግጭቶቹ ቀጥለዋል ወይንም በዝተዋል!

እነዚህን ግልስ የሆን ማስረጃዎች እያለን እና ግጭቶች እየበዙ እያሉ አሁንም የጎሳ አስተዳደር experimentአችንን እንቀጥል ማለት የሰከነ አስተያየት ነው? ይቅርታ አድርጉልኝ እና አይመስለኝም።

ይህን ስል የጎሳ አስተዳደርን የሚፈልጉት ሰዎችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ማስተናገድ አንዳለብን ይገባኛል። አማራጭ ሊኖር ይገባል። አለ ጎሳ አስተዳደር እንዴት ነው የጎሳ መብቶች (እነዚህ መብቶች አይነታቸው አከራካሪ ቢሆንም) ማስከበር የሚቻለው።

መልሱ ቀላል ነው እና እንደ ጎሳ አስተዳደር አዲስ ፈጠራ ውስጥ እንድንገባ አያስገድደንም።
ከኢትዮጵያ አስር እጥፍ በላይ የጎሳ መብቶች (ቋንቋ፤ ባህል፤ አስተዳደር) የሚያስከብሩ ሀገራት አሉ። ህንድ፤ ስዊትዘርላንድ፤ ካናዳ ወዘተ። እነዚህ ሀገራት ሁሉም ሀገ መንግስታቸውን በዜግነት ነው የመሰረቱት። የጎሳ መብቶች በክፍለ ሀገር አቀራረጽ፤ የቋንቋ ህጎች፤ ለክፍለ ሀገር የሚሰጠው የማስተዳደር መብት ወዘተ ያስከበራሉ። ግን መሰረቱ ዜግነት ነው። እነዚህን እንደ ምሳሌ ወስዶ መጠቀም ነው።

ለመዝጋት አንድ አጭር ምሳሌ ልስጥ። ዛሬ ከህገ መንግስቱ «ብሄር፤ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች» የሚለው ጥቅስ ከህገ መንግስቱ አወጣን እንበል። የክልል ቋንቋ በክልል ህዝብ ነው የሚወሰነው እንበል። ኦሮሚኛ የፌደራል ቋንቋ አደረግን እንበል። ይህ ሁኔታ (scenario) በርካታ የጎሳ መብት ያስከብራል። ኦሮሚያ ውስጥ በድምጽ ብልጫ የክልል ቋንቋ ኦሮምኛ ሆኖ ይቀራል። ይህ ማለት የምንግስት መስሪያቤት፤ ትምሕርት ቤት ወዘተ። የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርም በኦሮሞ ባህል እንዲሆን በድምጽ ብልጫ ይፈጸማል። ወዘተ። ይህ አንድ ምሳሌ ነው። አለ ጎሳ አስተዳደር በርካታ የጎሳ መብቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ።

ስለዚህ ወደ ህልም፤ ጸንፍ፤ አጉል ሙከራ አንሂድ። ቀላሉን መንገድ እንውሰድ። እንደ ኮምዩኒስቶቹ ህልማችንን እስከ መቃብራችን አቅፈን አንቆይ!

Tuesday, 6 November 2018

አንድ የሊሂቃን ንስሃ፤ ዶ/ር ታደሰ ወልዴ

ይህንን ቪዲዮ ብትመለከቱ ጥሩ ይመስለኛል።

https://youtu.be/qSPFi8xsbBo?t=1696

ረዥም ከአንድ ሰአት በላይ የሚወስድ ቢሆንም ከላይ ባስቀመትኩት ሊንክ ጀምሮ ብታዩት ስለ ንስሃ ታላቅ ትምሕርት በተለይም ታላቅ ምሳሌ ታያችሁ።

አቶ ታደሰ ወልዴ፤ ታላቅ የኦክስፎርድ መምህር፤ ለኛ ሁሉ ንስሃ ለመግባት ምሳሌ በመሆኖ እግዚአብሔር ይስጦት።

Wednesday, 17 October 2018

ኢትዮጵያን የሚገላት የአንድነት ኃይሉ ነው (ክፍል 1)

ባለፈው ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የኤርትራ ዲያስፖራ እንደልማዳቸው እየተሯሯጡ ለሀገራቸው ገንዘብ እያዋጡ ነበር። ምን ያህል አዋጡ? ልምሳሌ ያህል፤ በአንድ ቀን ከአንድ ከተማ ሲአትል (ዋሺንግተን ስቴት) አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አዋጥተዋል! ከዋሺንግተን ዲሲ አይነቱ ብዙ ኤርትራዊ ያለበት ከተማ ምን ያህል እንደተዋጣ ባላውቅም መገመት ይቻላል።

ተወዳጁ «ኢትዮጵያዊነትን» የወከለው ቅንጅት ለሰላም እና ዴሞክራሲ ፓርቲ መሪዎቹ ከተፈቱ በኋላ ሰሜን አሜሪካ መጥተው ለወራት ቆዩ። ከመላው ሰሜን አሜሪካ የሚኖር ኢትዮጵያዊያን ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በታች ሰብስበው (እና እርስ በርስ ተጣልተው) ተመለሱ!

የአንድነት ኃይሉ እርስ በርስ አለመስማማት እና አለመደራጀት ኢትዮጵያን ይገላል።

Wednesday, 19 September 2018

ታላቅ ጥላቻ ባይኖር የከቡራዩ እልቂት አይከሰትም ነበር

ስለቡራዩ የዘር ማጥፋት እልቂት ብዙ ይባላል። ጸንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች የቀሰቀሱት እና ያስተባበሩት ነው ይባላል። በተለያዩ የኦሮሞ ሚዲያዎች በተለይም ኦኤምኤን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የተቀሰቀሰው ነው ይባላል። ሁከት ለመፍጠር እና ኦሮሞ እና አማራን «ለማጣላት» የህወሓት ሰዎች ናቸው ያደረጉት ይባላል። ህወሓት ከያኮረፉት ኦህዴዶች እና ጸንፈኛ ብሄርተኞች አብሮ ያስተባበረው ነው ይባላል። አሁን ደግሞ አንዳንድ የህወሓት ጸንፈኞች እና የኦሮሞ ብሄርተኞች የጎሳ ብሄርተኝነትን የጥላ እሸት ለመቀባት ተብሎ ግንቦት ሰባት ያሴረው ክስተት ነው ይላሉ። ብዙ ይባላል መንግስት ቀስ ብሎ እውነታውን በይፋ እንደሚያወጣው ተስፋ አለኝ።

ይህ ሁሉ ሲባል አንድ እውነታን መካድ አይቻልም። ይህን የህዝብ ማጥፋት እልቂትን የፈጸሙት ሰዎች በዘር ጥላቻ የተሞሉ መሆናቸው ግልጽ ነው። ሰለቦችም መስካሪዎችም የመሰከሩት የዘር ማጥፋትን ነው። ገዳዮቹ ዘርን እየሰደቡ፤ ውነድ ልጅን ለመግደል እየፈላለጉ፤ ሴቶችን እየደፈሩ፤ ጥይት ወይንም ድብደባ ሳይሆን አጸያፊ የግድያ መንገዶች እየተጠቀሙ ወዘተ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ክስተት መሆን የሚቻለው በዘር ጥላቻ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ክስተቱ ሙሉ በሙሉ ግልጽ የሆነ የዘር ማጥፋት (ethnic cleansing) በሃሪ ነው ያለው።

ዝም ብሎ ቅጥረኛ ገዳይ ይህንን አይነት ድርጊት ማድረግ አይችልም። ቅጥረኛ ገዳይ በቀጥታ ነው ተግባሩን የሚፈጽመው። ግደል እና ዝረፍ ከሆነ ይገላል ይዘርፋል እንጂ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ያለው ክስተት ሊፈጽም አይችልም።

በተዘዋዋሪ በሌሎች በኢትዮጵያ ስፍራዎችም ያየናቸው የዘር ማጥፋት ዘመቻዮች እንዲሁ በዘር ጥላቻ ያላቸው ኃይሎች እንደተፈጸመ ግልጽ ነው። በጊዴኦ/ጉጂ፤ ኦሮሞ/ሶማሌ፤ አማራ/ቤኒሻንጉል የተከሰቱት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ምክልቶች (pattern) አላቸው። ምንም የፖለቲካ እና የገንዘብ ኃይል ከበስተጀርባቸው ቢኖርም አለዘር ጥላቻ መፈጸም የማይችሉ ተግባሮች ናቸው።

ስለዚህ ዋናው ችግር የዘር ጥላቻው ነው! እና የዘር ጥላቻን የሚያራግቡ ናቸው! ገንዘቡ፤ ሴራው፤ ወዘተ ባለው የዘር ጥላቻ ላይ ነው ስራውን የሚሰራው። ችግሩን ለመፍታት ሴራውን የሚሰሩት እና የሚያቀናበሩትን ማስቆም ያስፈልጋል። ግን ይህ መሰረታዊ ችግሩን አይፈታም። በዋናነት የዘር ጥላቻን የሚያራግቡትን ማስቆም ያስፈልጋል። ቀጥሎ በህዝብ መካከል ያለውን ጥላቻ ማጥፋት ያስፈልጋል።

እንዴት ነው በህዝቡ መካከል ያለው የዘር ጥላቻን ማጥፋት የሚቻለው። መንግስት ትህምህርት ቤትን፤ ሚዲያን እና ሌሎች ተመሳሳይ መዎቅሮችን በተገቢ ሁኔታ መቆጣጠር አለበት። የ27 ዓመታት የዘር ጥላቻ ፕሮፓጋንዳን ለመመለስ ሙሉ ዘመቻ ማድረግ አለበት። ጉዳዩ አስርት ዓመታት ይፈጃል ግን አማራጭ የለም። ሌላው የዚህ ዘመቻ ዋና ተግባር ደግሞ ህዝብ እንዲ ቀላቀል ማድረግ ነው። የእርስ በርስ ቋንቋ እንዲማር እና እንዲጋባ እና እንዲዋህድ ማድረግ ነው። ዘላቂው መፍትሄ ይህ ነው።

Monday, 17 September 2018

የአዲስ አበባ ህዝብ፤ ፍርሃት እና ህፍረት

ሁላችንም ቄሮ፤ ፋኖ፤ አቢይ፤ ለማ፤ ኦነግ፤ ግንቦት 7 ወዘተ ሲባል ህወሓትን ከስልጣን ማውረድ የተቻለው የ27 ዓመት የተጠራቀመ የግለሰቦች እና የቡድኖች ትግል እንደሆነ እንረሳለን። አንዱ የትግል ዘርፍ ምርጫ 97 ዙርያ በተለይም በአዲስ አበባ የተደረገው ተቃውሞ እና የህዝብ አመጽ ነበር። በዚህ ልጀምርና…

ሁላችንም እንደምናውቀው ለ27 ዓመታት የአዲስ አበባ ህዝብ በፍርሃት ነው የኖረው ማለት ይቻላል። (የብሄር ብሄረሰቦች) ጨቋኝ፤ ገዥ፤ ትምክህተኛ ወዘተ ተብሎ በመንግስት ትርክት ተሰይሟል። ይህ ህዝብ ነገ በጎሳ ብሄርተኞች ተከበን እንወራለን፤ እንገደላለን እና እንፈናቀላለን ብሎ በስጋር ይኖራል። ይህን አይነት ክስተት ደግሞ በተለያየ የኢትዮጵያ ክልሎች ሲከሰቱ አይቷል። አዲስ አበባ ከበየቦታ የተፈናቀሉትን ተቀብሏለችም!

በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባ ህዝብ ይህ በእውነት የተመሰረተ ፍርሃት ምንጭን ለመከላከል ተባብሮ መደራጀት አልቻለም። አዎን በምርጫ 97 ለተወሰነ ጊዜ አሸዋ ላይ ተደራጀ ግን ይህ ወድያው ፈረሰ። አልፎ ተርፎ ህዝቡ ይበልጥ እንዲፈራ እና መደራጀት እንዳይሞክር አደረገ።

ሆኖም የአዲስ አበባ ህዝብ በልቡ መደራጀት እንደሚገባው ያውቃል። የህዝብ ቁጥር እና አቅም እንዳለው ያውቃል። መደራጀት ያልቻለበት ምክንያት የራሱ ድክመት እና ጥፋት መሆኑም በተወሰነ ደረጃ ውስጡ ያውቃል። ጭቆናውን ችሎ መደራጀት እንደነበረበት ያውቃል።

ህወሓት ደጋግሞ እንድተጫወተበትም ያውቃል። ለኔ ስገዱ አለበለዛ ጎሰኞቹን ለቅባችኋለው እያለ ቆዬ። የአዲስ አበባ ህዝብ እራሱን አጠንክሮ ዞርበል ከማለት ፈርተን ዝም አልን። እውነታውን እንመን።

ይህ ነው የአዲስ አበባ ህፍረት የምለው። የተገዛው በትንሽ የምትባል ቡድን (ህወሓት) እንደሆነ ያውቃል። ህወሓት አንድ ለአምስት በሚባለው የቁጥጥር ዘዴ ሲፈጸምበት በራሱ ድክመት እንደሆነ የሚገዛው ህዝቡ አውቋል። ቄሮ እና ፋኖ ሲወራላቸው ዝም ብሎ ቁጭ እንዳለ ያውቃል። ይህ ለአዲስ አበባ ህዝብ ታላቅ የስነ ልቦና ቁስል ሆኗል። የዝቅተኛ መንፈስ እንዲያድርበት፤ አቅም የሌለው እንዲመስለው፤ የተዋረደ እንዲመስለው አድርጓል። ይህ ነው የአዲስ አበባ ህዝብ ሀፍረታችን።

ፍርሃት እና ህፍረት ስላለን ነው በቀደም ኦነግ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ ችግሮች የተፈጠሩት። ህዝቡ ፍርሃቱን በእውን አየው። የሚፈራው የሚፈራቸው ሲገቡ ደንግጧል። በሌላ በኩል ደግሞ እንዳልተደራጀ እና አቅሙን እንዳልሰበሰበ ያውቃል እና ታላቅ insecurity ተሰምቶታል። ሰለዚህም ነው በሰንደቅ አላማ እና አርማ ዙርያ ግጭቶች የነበሩት። ከፍርሃት የመነጨ ምላሽ ነው የአዲስ አበባ ውጣቶች የሰጡት።

እዚህ ላይ አንድ aside ያስፈልጋል። መደራጀት ማለት መዋጋት አይደለም። ውግያ እንዳይኖር ጠንክሮ ስልታማ ሆኖ መገኘት ነው። ግዙፍ አቅም እና ስነ ስረዓት ያላቸው የህዝብን አላማ የሚያስፈጽሙ መዋቅሮችን መፍጠር ማለት ነው። እነዚህ መዋቅሮች ብዙ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ለምሳሌ በከተማ አስተዳደር፤ በምሃበራዊ ኑሮ ጉዳዎች፤ በጸጥታ ዘርፍ፤ በፍትህ ወዘተ። እነዚህ ህዝብን የሚወክሉ መዋቅሮች ቢኖር ሁሉም የአዲስ አበባ ድርጅቶች በህዝብ ፍላጎት እንዲመሩ፤ ተጠያቂነት እና ግልጸኝነትት እንዲኖር ወዘተ ያደርጋሉ። በአጭሩ ህዝቡን አንድ ገልጽ ላይ ያደርጋል። እነዚህ መዋቅሮች ቢኖሩ ኦነግ ሲገባ ህዝቡ ምንም አይመስለውም ነበር። ምንም አይነት ኃይልን መቋቋም የሚችሉ መዋቅሮች እንዳሉት ስለሚያውቅ። ጭራሽ የኦነግ አርማ ይዞ ለመቀበል ይወጣ ነበር! መደራጀት ይህ ማለት ይህ ነው። በአጭሩ አዲስ አበባ በአዲስ አበባ ህዝብ ፍላጎት እንዲመራ ማድረግ ነው።

ዛሬ የአዲስ አበባ ህዝብ እንደ መላው ኢትዮጵያ ህዝብ በፍጥነት በዚህ መልኩ መደራጀት አለበት። የፖለቲካ ፓርቲ መፍጠር አለበት ወይንም እንደ ግንቦት 7 አይነቱ ጋር ተባብሮ ለአዲስ አበባ መዋቅር መዘርጋት አለበት። ሚዲያ መመስረት አለበት። የባህላዊ ድርጅቶችን በአንድ ጃንጥላ ስር ማሰባሰብ አለበት። ህዝቡ የሚወያይበት መዋቅሮች መዘርጋት አለበት። በጥቅልሉ ህዝቡን በአንድ ገልጽ የሚያደርገው መዋቅሮች እና ድርጅቶች መፈጠር አለበት። ነጻነት ማለት እንደዚህ አይነት የፖለቲካ ሃላፊነትን መወጣት ነው።

ግን በመጀመርያ ፍርሃት እና ህፍረታችንን ማመን አለብን። ይህ መደበቅ የለበትም። ስለዚህ በይፋ ማውራት መቻል አለብን። እውነቱ ከሃሰቱ መለየት አለበት። ይህም በውይይት እና መመካከር ነው የሚመጣው። አንዴ ፍርሃት እና ህፍረታችንን ካመንን በኋላ ወደ መፍትሄ ለመሄድ ይቀለናል።

መርዝ መጠጣት መብት ቢሆንም ይገላል፤ እንዲሁም የጎሳ ብሄርተኝነት መብት ቢሆንም ህዝብን ያጠፋል

ለማንም ሰው በ«ጎሳ ብሄርተኝነት» እና የፖለቲካ ዘመዱ በ«ጎሳ አስተዳደር» ማመን መብቱ ነው። አንድ ሰው እንዲህ «ኢትዮጵያዊ አይደለሁም፤ ኦሮሞ ነኝ። ኢትዮጵያ ህዝቤን ለዓመታት ጨቁናለች ቅኝ ገዝታለችም። ማንነቴ ኦሮሞ ነው። መኖር የምፈልገው በኦሮሞ ሀገር ነው እንጂ ኢትዮጵያ አይደለም» ቢል መብቱ ነው። እንዲህ አታስብ ማለት ልክ አይደለም። ካልንም መብት ገፈናል ግጭትንም ጋብዘናል ማለት ነው (ይህንን ጥንቅቃችሁ እንድታነቡ እጠይቃለሁ http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2017/11/whats-ethnic-nationalism-again.html)።

ይህን ተከትሎ በርካታ ሰዎች እንዲህ አይነት የጎሳ ብሄርተኝነት አመለካከት ካላቸው እና የፖለቲካ ፍላጎታቸው ይህ ከሆነ ጥያቄአቸው በሰላማዊ መንገድ መስተናገድ ይኖርበታል። ለምሳሌ የአንድ ክፍለ ሀገር ወይንም ክልል 70% ህዝብ «ነፃነት» ወይንም ሌላ የፖለቲካ አስተዳደር እፈልጋለሁ ካለ በድርድር መልክ መስተናገድ አለበት። አለበለዛ መብታቸውን አላከበርንም ማለት ነው። እንዲህ አይነት አካሄድ ደግሞ ወደ ግጭት እና ጦርነት ማምራቱ የታወቀ ነው።

የጎሳ ብሀሄርተኝነት መብት ነው ብለናል። ታድያ ለምንድነው የምንቃወመው? መልሱ ቀላል ነው፤ የጎሳ ብሄርተኝነት የግጭት ምንጭ ስለሆነ ነው። በተለይ በብሶት ማንነት የተመሰረተ (grievance based identity) የጎሳ ብሄርተኝነት በ«ጭቋኝ ተጨቛኝ» አስተሳሰብ የተሞላ ስለሆነ ሁልጊዜ ግጭት ያመጣል። ተጨቁኛለሁ ጨቋኜን ማጥቃት አለብኝ ይላል። ብድር መመለስ አለብኝ ይላል። መሬቴን መመለስ አለብኝ ይላል። «መጤዎችን» ማባረር አለብኝ ይላል። ሰውን እንደ ሰው ከማየት እንደ ቡድን ያያል። የመንጋ አስተሳሰብ ይጋብዛል። ወዘተ። ታሪኩ ዓለም ዙርያ የታወቀ ነው።

የጎሳ ብሄርተኝነት ግጭት እንደሚጋብዝ የሚታወቀው በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር ባለፉት 27/40 ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ ያየነው ነው። ግጭቶቹ የህወሓት ስራ ናቸው እንጂ የጎሳ ስረዓቱ አይደለም ማለትም አይቻልም። አብዛኞቹ ግጭቶቹ ህወሓት እንደ ተጋጭ አልተሳተፈባቸውምና። ግጭቶቹ የህወሓት እጅ ቢኖርባቸውም ህወሓት በባዶ መሬት ያስነሳቸው አልነበሩም። ህወሓት የነበሩ የጎሳ ቅራኔዎችን ነበር የሚጭረው እንጂ ቅራኔዎችን ከስር አልፈጠረም። ስለዚህ ባለፉት ዓመታት ያየናቸው የጎሳ ግጭቶች የጎሳ ብሄርተኝነት እና አስተዳደር ውጤት ናቸው ማለት ይቻላል።

በቅርብ ታሪካችን እንደሚመሰክረው የፖለቲካዊ፤ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበረሰባዊ ግጭቶች ሁሉ በ«ጎሳ ፖለቲካዊ ውድድር» ዙራይ (ethnic political competition) ነው የሚከሰቱት። ይህ ውድድር በመሬት፤ የፖለቲካ ስልጣን፤ ንብረት ክፍፍል ወዘተ ሊሆን ይችላል። «ይህ መሬት የኛ ነው»፤ «ይህ ስልጣን ለኛ ይገባል»፤ «ይህ መዓድን ውጤት ለኛ ነው መሆን ያለበት» ወዘተ እየተባለ ወደ አጉል ውድድር፤ ፉክክር እና ግጭት ይኼዳል። ይህን በተግባር አይተናል እያየንም ነው።

በምንድነው ይህ የጎሳ ውድድር ከሌሎች ፖለቲካዊ ውድድሮች የሚለየው? በምን መንገድ ነው ከአካባቢ፤ ርዕዮት ዓለም፤ መደብ፤ ጥቅም ወዘተ የፖለቲካ ውድድሮች የሚለየው? ለምንድነው ጤናማ ያልሆነው? ልዩነቱ ጎሳ ከሰው ማንነት ጋር የተቆራኘ እና በቀላሉ መቀየር የማይቻል ነገር ስለሆነ ነው። አካባቢ፤ ርዕዮት ዓለም፤ መደብ፤ ጥቅም ይቀያየራሉ። ዛሬ አዲስ አበባ ነገ አምቦ መኖር ይቻላል። ዛሬ ማርክሲስት ነጋ ካፒታሊስት መሆን ይቻላል። ዛሬ ድሃ ነገ ሃብታም መሆን ይቻላል (ሳይቻል ሲቀር ደግሞ ይህም ኃይለኛ ግጭት የመጣል)። እነዚህ መስፈርቶች የሰው ልጅ ማንነት ላይ ሚና ቢኖራቸውም ሚናው መጠነኛ ነው። መቀየር ይቻላል ብዙ ጊዜም እንቀይራቸዋለን። ግን ጎሳ ወይንም ሃይማኖት የማንነት ታላቅ ክፍል ናቸው እና ባብዛኛው አይቀየሩም። ጎሳ በዚህ መልኩ ከሰው ልጅ ማንነት ጋር አጥብቆ ስለተያያዘ በጎሳ በኩል የሚመጣ ውድድር እጅግ የከረረ እና አከፋፋይ ነው የሚሆነው።

አልፎ ተርፎ የጎሳ ልዩነት እና የጎሳ ብሄርተኝነት በበዛበት ስፍራ ሁሉ ጥያቄዎች/ውድድሮች «የጎሳ መልክ» ይይዛሉ። ለምሳሌ የጎሳ ብሄርተኝነት በሌለበት ቦታ በአንድ ድርጅት እና የሰራተኛ ማህበር ግጭት ካለ ግጭቱ በኩባኒያው እና ሰራተኛ ማህበር መካከል ሆኖ ይቀራል። ምናልባት ሌሎች ቁባንያዎች ከጓድ ኩባኒያቸው ጋር ይወግኑ ይሆን እና ሌሎች የሰራተኛ ማህበራት ከጓድ ከሰራተኛ ማህበራቸው ጋር ይወግኑ ይሆናል። የከረረ ጎሰኝነት ባለበት ቦታ ግን ኩባንያውም የሰራተኛ ማህበሩም በጎሳ ይሰየማሉ እና ጎሳዎች ከኋላቸው ይሰለፋሉ። ለምሳሌ የኩባንያው ባለቤት ኦሮሞ ከሆነ ኦሮሞዎች ከሱ ጋር ይሰለፋሉ ሰራተኞቹ ደግሞ ባብዛኛው ጉራጌ ከሆኑ ጉራጌዎች ከነሱ ጋር ይሰለፋሉ። ግጭቱ ከሰራተኛ መብት አልፎ ወደ ጎሳ ግጭት ይቀየራል። ወደ ከረረ ግጭት ይገባል። ጎሰኝነት ወይንም የጎሳ ብሄርተኝነት በአንድ ሀገር ሲበዛ ይህ ነው አንዱ አደጋ እና የግጭት መብዛት መንጭ።

ግን ይህ አደጋ እንዳለ ሆኖ ከላይ እንዳልኩት አንድ ሰውን የጎሳ ማንነትህን ተው ማለት አይቻልም። መብቱ ነው ማንነቱ ነው ምንም ትክክል ባይመስለን ወይንም በሃሰት የሆነ ሃሳቦች የተመሰረተ ነው ብንልም የሌላ ሰው ማንነትን አስገድዶ መቀየር አይቻልም (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_34.html)። አልፎ ተርፎ ሰውን በማንነቱ ጥንቃቄ በሌለው መንገድ ከተቸነው ይበልት እንዲከርር ነው የምናደርገው። በተለይም የጎሳ ማንነቱ በብሶት የተመሰረተ ከሆነ። ካልተጠነቀቅን አክራሪ ያልሆነውንም ወደ አክራሪነት እንገፈዋለን። ለምሳሌ «እኔ ኦሮሞ መጀመርያ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ ነኝ» የሚለው ኦሮሞ ማንነቱን ከተቸነው ወይንም ከተከራከርነው በማንነቴ አትምጡብኝ ብሎ ጭራሽ ኢትዮጵያዊነቱን ትቶ ወደ ኦሮሞነት ብቻ ሊያመራ ይችላል። ይህ የሚሆነው በስሜት ደረጃ ነው። «ይህ አደጋ ነው እና ኦሮሞ ብቻ ነኝ አትበል ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ነኝ በል» ማለት ሁኔታውን ያባብሳል ጎሰኝነቱን ይጨምራል።

ጥንቃቄ ያስፈልጋል ስንል ግን እውነት አይነገር አይደለም። ግን «ኦሮሞ አትሁን» አይነቱን አሉታዊ አስተያየት ከመሰንዘር ይልቅ በአዉንታዊው ማተኮር ነው። አዎን የጎሳ ብሄርተኝነት አደጋ እንደሆነ በግልጽ መናገር ጠቃሚ ነው። ግን ከዚህ ጋር አብሮ የጎሳ ማንነቱ እንዴት አለ ጎሳ ብሄርተኝነት (nationalism) ማስተናገድ እንደሚቻል መግለጽ ይኖርብናል። ማንነቱ በኢትዮጵያዊነት እንዲንጸባረቅ ማድረግ እንደሚቻል ማሳየት አለብን። ለምሳሌ አንድ እንደዚህ አይነት አውንታዊ ሃሳብ ኦሮምኛ ከአማርኛ እኩል የፌደራል መንግስት ቋንቋ ማድረግ ጥሩ ነው የሚለው አቋም ነው። ይህ አቋም የሚልከው መልእክት «አንተ ኦሮሞ ነህ፤ ኢትዮጵያም ኦሮሞ ናት» የሚል ነው። ማንነትህ በኢትዮጵያዊነት ተታክቷል ማለት ነው። እንዲህ አይነት አውንታዊ መርህ እና መልእክቶች ናቸው ሰው ወደ ጎሳ ብሄርተኝነት እንዳይገባ የሚረዳው ወይንም ከጎሰኝነት ወደ ኢትዮጵያዊነት እንዲያመዝን የሚያደርገው።

በሌላ በኩል ስለምናስተላልፈው መልዕክቶች መጠንቀቅ ያለብን እንዲህ ነው። ብዙ ጊዜ የጎሳ ብሄርተኝነት «ጥላቻ»፤ «ዘረኝነት»፤ «ጠባብነት»፤ «የፖለቲካ ነጋዴዎች ጭዋታ» ወዘተ ተብሎ ይሰየማል። እነዚህ በሙሉ የተወሰነ እውነታ አላቸው። ግን ሙሉ እውነታው አይደለም። በድፍኑ እንዲህ ማለቱ በርካታ ለዘብተኛ የሆኑ የጎሳ ብሄርተኞች ወይንም ገና አቋማቸውን ያልወሰኑ በመሃል የሚንሳፈፉ ሊያስቀይም እና ይበልጥ ወደ ጎሰኝነት ሊገፋቸው ይችላል። «ማንነቴ ኦሮሞ ነው ስላልኩኝ ዘረኛ ነኝ እንዴ» ብሎ ይበሳጫል። እንዳልኩት የጎሳ ማንነት በጣም ስሜታዊ ነገር ነው እና መተቸት አይወድም። ስለዚህ ስንተቸው በትክክል እና precise መንገድ መሆን አለበት። ለመልሶ ትችት የማይመች መሆን አለበት። ስለዚህ ዘረኛ አመለካከት ስንሰማ ይህን አመለካከት ዘረኛ ነው ማለት ተገቢም አስፈላጊም ነው። ወደ ኋላ ማለት እና መሸማቀቅ ጎጂ ነው። ግን በጅምላ ዘረኞች ናችሁ ካለን ሁኔታዎች ያባብሳል። በጠቅላላ የጎሳ ብሄርተኝነትን መቀነስ የምንፈልግ የማስተላልፈው ምልዕክቶአችንን ተጠንቅቀን ማርቀቅ አለብን። ልድገመው፤ የሰው ልጅ ማንነቱ ሲተችበት አይወድም።

ለማጠቃለል ያህል፤ የጎሳ ብሀኢርተኝነትን አቋም መያዝ መብት ነው። ግን የጎሳ ብሄርተኝነት እና የጎሳ ፌደራሊዝም የግጭት እና ሁከት ምንጮች ናቸው። በዚህ ምክንያት ነው የምንቃወማቸው።  በመሰረቱ ክፉ፤ ዘረኛ፤ ጠባብ ወዘተ ስለሆነ ሳይሆን የግጭት ምንች ስለሆነ ነው። ይህን በጽንሰ ሃሳብም በተግባር አይተነዋል። የጎሳ ብሄርተኝነትን ለመቀነስ ትጠንቅቀን መስራት አለብን በተለይ በምናስተላልፈው መልዕክቶቻችን ትክክለኛ እውነት ግን በጅምላ የማይፈርጅ እንዲሆኑ ማድረግ አለብን። የሰው ማንነትን አክብረን ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ውስት ይህ ማንነት በድምብ እንዲካተት በአውንታዊ መልክ መስራት አለብን።

Monday, 20 August 2018

ከሰው ማንነት ጋር መከራከር ያስቸግራል

ድሮ ከኤርትራዊያን፤ ትግራይ፤ ኦሮሞ ብሄርተኞች ጋር ስንከራከር እንዲህ አይነቱ ነጥቦችን እናነሳ ነበር፤

  • ሁላችንም ኢትዮጵያዊ ነን ማንም ከማንም በላይ አልተጠቀመም አልተጨቆነም
  • መንግስት በጎሳ ወይም ብሄር አድሎ አድርጎ አያውቅም
  • ከሁሉም ጎሳ የፖለቲካ መሪዎች አሉ ታላላቅ መሪዎቻችን ብዙ የተለያየ የጎሳ ደም አላቸው
  • የሁላችንም ጥቅም አብሮ ከመሆን የተያያዘ ነው
  • ጎሰኝነት የጋራችንንም የያንዳንድ ጎሳችንንም ጥቅም ይጎዳል ግጭት እንዲሰፍን ያደርጋል
    ወዘተ

እነዚህን አይነት ፍሬአማ ነጥቦች ላይ ከተወያየን ብኋላ ሁልጊዜ መጨረሻ ላይ ወደ አንድ ነጥብ እንመለሳለን። ኤርትራዊያኖች «እኛ ኤርትራዊያን ነን ኢትዮጵያዊ አይደለንም» ትግራዮውቹ «እኛ መጀመርያ ትግራይ ነን» ኦሮሞ ብሄርተኞች «እኛ ኦሮሞ ነን ኢትዮጵያዊ አይደለንም» ብለው ውይይታችንን ያቆማሉ። የአባባላቸው ትርጉም ግልጽ ነበር፤ ማንነታችን ይህ ነው እና ስለ ማንነታችን ምንም ማለት አይቻልም ነው። ጉዳዩ ሌላ አይደለም፤ ጥቅም እና ጉዳትም አይደለም፤ «ማንነት» ነው።

እንዲሁም አሁን ከአማራ ብሄርተኝነት ደጋፊዎች ይህንን ነው የማየው። ባለፉት 45 ዓመት የፖለቲካ ችግሮቻች (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_15.html) ምክንያት የተወሰነው የአማራ ህብረተሰብ ውስጥ አዲስ የአማራ ማንነት (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_17.html) ተፈጥሯል። ይህ ማንነት የአማራ ብሄርተኝነት ንቅናቄ መሪ @  የጻፉት በደምብ የሚገልጸው ይመስለኛል፤

«አማራ ነኝ ፣ አማራ ነን ፤ እንደአማራነት የተሰነዘረብኝን ጥቃት በአማራነት ተደራጅቼ እመክታለሁ ፤ በዚህም ህልዉናዬን፣ ፍላጎቶቸንና ዘላቂ ጥቅሞችን አስከብራለሁ»
(https://www.facebook.com/photo.php?fbid=1934811083224914&set=a.308423195863719&type=3)

ጉዳዩ የማንነት ስለሆነ ምንም አይነት «ሎጂካል» ሙግት ማንነትን እንደሚያጣጥል ሊቆተር ይችላል። ውይይት ቶሎ ወደ ቅራኔ ይወሰዳል። ለምሳሌ እንደ እኔ አይነቱ በኢትዮጵያዊነት መደራጀትን የሚያምን «የአማራ ጥቅምን የሚያሟላው በኢትዮጵያዊነት መደራጀት ነው» ብል ለአማራ ብሄርተኛው ማንነቱን የተቸትኩኝ ይመስለዋል እና መልሱ ከጉዳዩ ጋር ሳይሆን ከማንነቱን መከላከል ጋር የተያያዘ ይሆናል። «ይህን ሁሉ ጥቃት ደርሶብን እንዴት በአማራነት አትደራጁ ትላለህ» ይባላል። «ድሮስ እናንተ በኛ ትነግዱ ትጫወቱ ነበር አህን ያበቃል» ይባላል። «ሌሎች የጎሳ ብሄርተኞችን ለምን አትተቹም?» ይባላል። ወዘተ።

የነ ጃንሆይ፤ ደርግ፤ ኢህአፓ፤ መኢሶን፤ መላው አማራ/ኢትዮጵያ፤ ቅንጅት፤ ግንቦት ሰባት ወዘተ ኃጢአቶች በሙሉ በ«አንድነት ድርጅቶች» እና በ«ኢትዮጵያዊነት» ርዕዮተ ዓለም ላይ ይለጠፋሉ! ይህ ሁሉ የማይሆኑ («ኢሎጊካል») መልሶች የሚሰነዘሩት ጉዳዩ በዋናነት የማንነት ስለሆነ ነው።

አንዴ በበሶት እና «ጭቁንነት» የተመሰረተ ማንነት ስር ከሰደደ በሎጂክ የተመሰረተ ሙግት ምንም መቀየር አይቻልም። ወይ ከነሱ ጋር ነህ ወይንም ጠላት ነህ።

እዚህ ላይ አንድ መናገር የምፈልገው ነገር አለ። በነዚህ የአማራ ብሄርተኞች ምንም ምንም አልፈርድም። ያወረስናቸው ኢትዮጵያ እጅግ ህመምተኛ እና ደካማ ናት (አሁንም እንዳ አብይ አህመድ አይነት ጀግና መውለድ ብትችልም)። ያወረስናቸው የፖለቲካ ባህል ጥላቻ የቶሞለው ስልት-ቢስ የሆነ ነው። በጃንሆይ ዘመን በሰላም ነገሮችን ከማስተካከል ሀገሪቷን ወደ ገደል ወሰድናት (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_15.html)። ለዚህ ማንም ላይ ጣቴን አልጠቁምም። እንደ በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ የኔ ጥፋት ነው ብዬ ሃላፊነት እወስዳለሁ። ይቅርታም እተይቃለሁ።

ይህን ካልኩኝ በኋላ የአማራ ብሄርተኞችን እንደ ኦርሞ ብሄርተኞች ተጠንቅቆ መያዝ ያስፈልጋል እላለው። እርግጥ የአማራ ብሄርተኞች በአብዛኛው በጎሳ ብሄርተኝነት አናምንም ስትራቴጂ ነው ወይንም ሌሎቹ በጎሳ ስለተደራጁ ግዴታ ሆኖብን ነው ይላሉ። በኢትዮጵያዊነት እናምናለን ይላሉ። ነገ ህገ መንግስቱ ቢቀየር እኛም በጎሳችን መደራጀት እናቆማለን ይላሉ። አቃፊ ብሄርተኞች ነን ይላሉ።

ሆኖም የጎሳ ማንነት በደምብ ገብቶባቸዋል። መጀመርያ አማራ ነን ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ የሚሉ አሉ። ኢትዮጵያዊነት ጠፍቷል የሚሉ አሉ። አንቀጽ 39 ጥሩ ነው የሚሉ አሉ። በመታወቅያ ላይ ጎሳ ቢኖር ጥሩ ነው የሚሉ አሉ። አማራ ብሄርተኛ ያልሆነ አማራ አይደለም የሚሉ አሉ። ወዘተ።

ስለዚህ ይህን ማንነት በዘዴ መያዝ ይኖርብናል። ከሙግት ይልቅ empathy ወይን መቆርቆር ነው የሚያስፈልገው። ከሙግት በፊት መተማመንን መፍጠር ያስፈልጋል (አንድ የሆንን እና የምንተማመን መስሎኝ ነበር ግን ለካ የማላውቀው ብዙ ግጭት እና ቁስል አለ በአምራ ብሄርተኞች እና «አንድነት ኃይሎች»)። ትክክለኛ መተማመን ጋር ከደረስን በኋላ ብቻ ነው ወደ ውይይት እና ሙግት መግባት ያሚቻለው።

የ27 ዓመት ጥቃትን አናጣጥል። የብዙ አማራ «ሞራል» ተሰብሯል። ጥቂት ትግሬ ገዝቶን ነበር ብለው የሚያስቡ ብዙ አሉ። ትክክለኛውን ሚዛናዊውን ግንዛቤ ላይ ከመድረስ በራስ አለመተማመን እና የ«ጭቁን» ስሜት ብዙዎቻችን ላይ አድሯል። ይህን እኔ በበኩሌ አልተገነዘብኩትም ነበር። ምን ያህል ስር እንደሰደደ አልገብኛም ነበር። ድሮ ኩሩ የነበረው አማራ ምን ያህል ሞራሉ እንደተጎዳ እና ወደ ጎሳ ብሄርተኝነት ማዘንበል እንደሚችል አልገባኝም ነበር። አሁን ግን ትንሽ የገባኝ ይመስለኛል። ከተሳሳትኩኝ አርሙኝ።

Monday, 13 August 2018

አጸያፊ ግጭቶች ለተወሰነ ጊዜ ይቀጥላሉ

ብዙዎቻችን ለ27 ዓመታት በየ ክልሉ በዘውትር የሚካሄደውን የምናውቅ አይመስለኝም። የቤተሰቦቼ ሀገር ጨርጨር (ምዕራብ ሀረርጌ) እንደ ምሳሌ ተጠቅሜ ላስረዳ። ኢህአዴግ ስልጣን ክተቆጣጠረ ጀምሮ በየጊዜው «ነባሮቹን» (የጨርጨር ሙስሊም ኦሮሞዎች) እንወክላለን የሚሉ ጸንፈኛ ጎሰኛ እና ሙስሊም ተነስተው «መጤዎቹን» (ሙስሊም ኦሮሞ ያልሆኑት አማራ፤ ጉራጌ፤ ሶማሌ ወዘተ) በግድ ሙስሊም ሁኑ፤ ከሀገራችን ውጡ ወዘተ እያሉ ይነሳሉ። በሳውዲዎች ገንዘብ የሚደገፉ «ማድራሳዎች» (የጸንፈኛ እስልምና ትምሕርትቤትዎች) ይከፈታሉ ጽንፈኛ እስልምና ያስፋፋሉ። ጸንፈኛ ጎሰኝነት በስውር በየመንግስት መስሪያቤቱም ይንቀሳቀሳል «መጤውን» አባሩ ግደሉ ብሎ ይሰብካል። ይህ ጸንፈኝነት በየወቅቱ «መጤዎች» ላይ ጫና ይፈጠራል እስከ ሞት ያህል ጉዳት በየጊዜው ይደርሳል። እንደዚህ አይነት ክስተቶች ሲበዙ ፌደራል ፖሊስ ወይንም መከላከያ ይመጡና ጸንፈኞቹን አድነው አግኝነተው ያስሯቸዋል ግን አብዛኛው ጊዜ ይረሽኗቸዋል። ምርመራ፤ ፍርድ ቤት ወዘተ የለም። ዋና አቀነባባሪዎቹን ፈልገው ያጠፏቸዋል። ከዛ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ሁኔታው ይረጋጋል «መጤው» ትንሽ ሰላም ያገኛል። ግን ከትወሰነ ጊዜ በኋላ ጸንፈኞቹ እንደገና ይነሳሉ። አላለፉት 27 ዓመት ይህ ነበር የሚደጋገመው።

ከዚም አልፎ ተርፎ በለት ኑሮዋቸው «መጤዎች» ስለ ደህንነታቸው በትወሰነ ደረጃ ሁል ጊዜ ይጨንቃሉ። አባቶቻቸው ጭቋኝ የነበሩ ያማይፈለጉ «እንግዶች» እንደሆኑ እንዲሰማቸው ይደረጋል። እንደ ሁለተኛ ዜጋ ነው የሚታዩት። ማህበራዊ ችግር ከተፈጠረ ወይንም የህግ አስከባሪ ጉድለት ከመጣ ጉዳት ይደርስብናል ብለው ነው «መጤዎቹ» የለት ኑሮዋቸውን የሚኖሩት። በስጋት ነው የሚኖሩት። የከፋ ጊዜ ከመጣ ፌደራል ፖሊስ ወይንም መከላከያ ነው የሚያድንን ብለው ነው የሚያስቡት።

የህወሓት አሰራር እንዲህ ነበር በኦሮሚያ፤ ደቡብ፤ ቤኒሻንጉል፤ ሶማሌ ወዘተ ክልሎች። ፖሊሲአቸውን «ያዝ ለቀቅ» ብሎ መሰየም ይቻላል። ጎሰኝነትን በፖሊሲ ደረጃም ያራምዳሉ ጸንፈኛ ጎሰኝነት እንዲፈጠር እንዲኖር ያደርጋሉ። ግን ከቁጥጥራቸው ሲወጣ የወለዷቸውን ጸንፈኞች ያጠፏቸዋል እና እራሳቸውን እንደ የ«መጤው» ጠባቂ አድርገው ያቀርባሉ። «መጤውም» ምርጫ የለውም ለደህንነቱ ሁልጊዜ ወደ ፌደራል መንግስት ይመለከታል። ህወሓት የኖረው ይህን ክፉ ሚዛን ገንብቶ በመጠበቅ ነው።

አሁን በነ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ዘመን ይህ አካሄድ አብቅቷል። በመጀመርያ ደረጃ ጎሰኝነትን ለመቀነስ ተነስተዋል። ሁለተኛ ደግሞ ሰላም፤ ፍቅር እና ፍትህ እንዲመጣ ነው የረዥም እቅዳቸው። በዚህ መሰረት ወንጀሎች እና ግጭቶች ሲፈጠሩ እንደ ድሮ የህወሓት አገዛዝ ገብተው አይረሽኑም። በህጋዊ መንገድ ጉዳዩን አጣርተው ፍትህ እና መፍትሄ በትክክሉ መንገድ ማድረስ ነው የሚፈልጉት። በዚህ መካከል ጸንፈኞች ፍርሃታቸው ቀንሶ ድሮ የማይደፍሩትን ያደርጋሉ። ወንጀሎች እና ግጭቶች ወዲያው አይቋረጡም መፍትሄ ቀስ ብሎ ይሆናል የሚገኝላቸው። በቅርቡ በሶማሌ፤ ቤኒሻንጉል፤ ሻሸመኔ ወዘተ የምናየው ይህ ነው። አልፎ ተርፎ በጠ/ሚ አብይ የግድያ ሙከራ ወይንም በስመኘው በቀለ ግድያ ዙርያም እንዲሁም ወደያው የፈጣን መልስ አልተገኘለትም። በህጋዊ ስነ ስርዓት እየተጣራ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_6.html)።

ከዚህ ሁሉም መካከል ደግሞ የአዲሱ ስርዓት አቅምን ማወቅ አለብን። የድሮ የህወሓት ርዝራዦች ገና ከመንግስት፤ መከላከያ፤ ፌደራል ፖሊስ፤ በተለይም ደህንነት ገና አልጸዱም ለማጽዳትም ረዥም ጊዜ ይፈጃል። እንኳን ሌላ የጠ/ሚ አብይን ደህንነት መጠበቅ እራሱ ከባድ ሆኗል። ስለዚህም ነው እነ አብይ በማንኛውም ስራ እንቅፋቶች እያገጠማቸው የሚሰሩት።

ስለዚህ ባሁኑ ጊዜ ከህወሓት የጠብ መንጃ ፍትህ-ቢስ አገዛዝ ወደ ጠ/ሚ አብይ አገዛዝ መሸጋገርያ ወቅት ገና ብዙ ወንጀል፤ ዘር ማጥፋት ሙከራዎች፤ ህዝባዊ ግጭቶች፤ ግድያዎች፤ ወዘተ ሳይቀጥሉ አይቀሩም። የጠ/ሚ አብይ መንግስት እስኪጠነክር ድርስ፤ የክልል ፖሊሶች እስኪጠነክሩ ድርስ፤ ህዝቡ እስኪረጋጋ ድርስ፤ ፖለቲከኞች እና ሌሎች መሪዎች እስኪረጋጉ እና ለጥያቄዎች መልስ እና አቅታጫ ማስያዝ እስኪችሉ ድርስ ይቀጥላል። የድሮ እንቅፋቶች እስኪነሱ ድርስ በርካታ ጉዳቶች ያጋጥሙናል። ከመታገስ እና አዲሱን መንግስት ባለን አቅም በተለይ በአቅም ግንባታ ደረጃ ከመርዳት በቀር ምንም ማድረግ አይቻልም።

ለተጎዱት ለተገደሉት በሙሉ ጸሎታችን ከነሱ ጋር ይሁን። የሁላችንም የተከማቸ የረዥም ዓመታት ኃጢአት ነውና ሀገራችንን በዚህ ሁኔታ እንድትሆን ያደረገው።