Showing posts with label communication. Show all posts
Showing posts with label communication. Show all posts

Sunday, 21 April 2019

ገንቢ ውይይት ከአንዷለም አራጌ ጋር

ስዩም ተሾመ በጣም ጥሩ ቃለ ምልልሶች እያረገ ነው፤ አጠያየቁንም ወድጄዋለሁ። እንግዶቹን ከነ መልእክቶቻቸው ያከብራል። የተንዛዛ ንግግሮች እንዲያደርጉ አይፈቅድም ግን መልዕክቶቻቸውን በደምብ እንዲገልጹ ይገፋፋቸዋል። በበቂም ይሟገታቸዋል  የሚናገሩትን ለማጥራት ዘንድ።

ለማንኛውም አንድ ሁለት ነጥብ ከዚህ ውይይት... በመጀመርያ አንዱእዓለም ስለ «ሃላፊነት ፖለቲካ» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_30.html) አስረግጦ ተናገረ። የሀገራችን ፖለቲካዊ ይሁን ሌሎች ችግሮች በዋናኝነት የህወሓት ጥፋት ሳይሆኑ የያንዳንዶቻችን ጥፋት ናቸው። በድርጊታችን ወይንም በዝምታችን እያንዳንዶቻችን ጥፋተኛ ነን። (እኔ የምለው) አልፎ ተርፎ ህወሓትንም የወለድነው እኛው ነን (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_21.html)። ይህን ሃላፊነት ካልወሰድን መቼም ልንድን አንችልም። ትክክለኛ መልዕክት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ አንዱእዓለም ስለ ጎሳ ፖለቲካ ሲይወራ የጎሳ ፖለቲካ አግላይ እና ዘረኛ አድርጎ ያቀረበው መሰለኝ፡፡ እወንተ ነው፤ ብዙ ጊዜ እነኝህን ባህሪአት ይንፀባርቃል፡፡ ግን ተገቢ ጥያቄዋችም እናስሜቶች አሉት። እነዚህን ተገቢ ትያቄዎችን በመጀመርያ ካልተቀበልን መወያየት አይችልም። Don't reduce ethnic nationalism to 'racism' (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_6.html)፡፡ 

<<የጎሳ አስተዳደር (ethnic federalism) ዋና ችግር የግጭት መንስኤ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም የ28 ዓመታት ማስረጃ አለን። የቋንቋ፤ ባህል፤ አካባቢ መስተዳደር (local autonomy) ፍላጎቶች ተገቢ ናቸው ግን ከጎሳ አስተዳደር ሌላ በሆነ አስተዳደር ነው በተገቢው እና ሰላማዊ መንገድ የሚመለሱት፡፡>> መልእክታችን ይህ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ እንጂ ዘረኝነት ነው በማለት ካተኮርን የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡

Monday, 4 March 2019

የጎሳ ፌደራሊዝም ችግር አንድ ነው፤ የግጭት መንስኤ ነው!

ዛሬ አንድ ሁለት ውይይቶች ስለ ሀገራችን «የጎሳ ፌደራሊዝም» ተመልክቼ ነበር። ውይይቶቹ ያተኮሩት በጎሳ ፌደራሊዝም እንደ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ተናጋሪዎቹ ታሪክን እና ርዕዮት ዓለምን ፈትሸው የጎሳ ፌደራሊዝም ለሀገራችን ይበጃል ወይንም አይበጅም ብለው ተከራከሩ። Of course ውይይት/ክርክሩ የትም አልደረስም። The participants, as usual, talked right past each other።

በመጀመርያ ደረጃ አንዱ የሌላውን ፍላጎት የማይረዳበት ውይይት ውይይት አይደለም። ስለ ጎሳ ፌደራሊዝም የሉን ውይይቶች እንዲህ ናቸው። እኛ አቋማችንን እንናገራለን ሌላውም እንዲሁ አንድ ሌላው አይገባውም ውይይቱም ባለመግባባት ያልቃል።

ይህ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት የውይይት እና ቅራኔ መፍታት ስልት በማጣት ነው። ግን አሁን ማተኮር የምፈልገው እዚህ ላይ አይደለም። ሁለተኛው ምክንያት ነው፤ ይህ ደግሞ የጎሳ እና ማንነት ጉዳይ ስሜታዊ በመሆኑ ለውይይት አይመችም። አይሆምም ማለት ይቻላል። «እኔ መጀመርያ ኦሮሞ ነኝ ቀጥሎ (ምናልትባት) ኢትዮጵያዊ» ሲል አንዱ ሌላው «እንዴት እንዲህ ትላለህ» ብሎ ሁለቱም በስሜታቸው ይመራሉ። አንዱ ሌላውም ማሳመን አይችልም።

ለዚህ ነው በጎሳ ፌደራሊዝም ጉዳይ ታሪክን እና ርዕዮት ዓለምን ፈትሸን መከራከር የትም የማያደርሰን። በጎሳ ፌደራሊዝም የሚያምን እና የጎሳ ፌደራሊዝምን የሚጠላው ሁለቱም ምክንያቶች በመሰረቱ ስሜታዊ የማንነት ናቸው። እነዚህን በርዕዮት ዓለም እና ታሪክ (in the eye of the beholder) ማስታረቅ አይቻልም።

ሁለቱን ጎራዎች ለማግባበት ወደ ሌላ level መሄድ ያስፈልጋል። ይህ ደረጃ እንዲህ ነው፤ እኔ የጎሳ ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ አይሆንም የምልበት ምክንያት ታሪክ እና ርዕዮት ዓለም ሳይሆን በ evidence ምክንያት ነው። የ24 ዓመት ታሪክ ከነ ያለፈው አንድ ዓመት የለውጥ ዘመን ታሪክ የሚያሳየው የጎሳ ፌደራሊዝም የግጭት መንስኤ መሆኑ ነው። የጎሳ ፌደራሊዝም በጎሳዎች መካከል በርካታ ግጭቶች እንዲኖሩ አድርጓል። ሰዎች በጎሳቸው ምክንያት የሚጎዱበት ዘመን አምጥቷል። ይህ ጉዳት ለተወሰኑ ጎሳዎች ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሩ ነው። ለዚህ በርካታ የ25 ዓመት evidence አለ።

ለዚህ ነው የጎሳ ፌደራሊዝም መቀየር አለበት ብለን መከራከር ያለብን። የ24 ዓመት የጭቆና እና የአንድ ዓመት የአንጻራዊ ነጻነት መረጃ የሚያሳየን የጎሳ ፌደራሊዝም ህግ እና መንፈስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን እንደጎዳ ነው። ሶማሌ በሶማሌነቱ፤ ኦሮሞ በኦሮሞነቱ፤ ጊዴኦ በጊዴኦነቱ፤ አማራ በአማራነቱ፤ አንዋክ በአንዋክነቱ፤ ወላይታ በወላይታነቱ፤ ስዳማ በሲዳማነቱ፤ ወዘተ ተጎድቷል። የጉዳት ፈጻሚዎቹም እንዲሁ የተለያዩ ናቸው። «ህወሓት» ወይንም የህወሓት አሽከሮች ብቻ አይደሉም ጨቋኞቹ። ህዝቡ እራሱ ይጭቋቆናል። ለዚህ በርካታ መረጃ አለን።

አንድ ታካቅ መራጀ ደግሞ የሁሉም ጎራ ፖለቲከኞች «ካልተጠነቀቅን እርስ በርስ እንፋጃለን» ማለታቸው ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/blog-post.html)! የጎሳ ፌደራልዚምን የሚደግፉትም የማይደግፉትም የጎሳ እልቂት is right around the corner ብለው ደጋግመው ይነግሩናል። ለጎሳ ፌደራሊዝም ከዚህ የባሰ indictment የለም!

ስለዚህ ለ«ዜግነት ፖለቲካ» ደጋፊዎች እና ሌሎች የዚህ የጎሳ ፖለቲካ የሚጠሉ ሰዎችን የምመክረው፤ ስሜትን በሃሳብ አትከራከሩ፤ የትም አትደርሱም። በመሰረቱ የጎሳ ፌደራሊዝም ሰውን የሚጎዳ ባይሆን ምን ችግር አለው? ምንም። የጎሳ ፌደራሊዝም ኢትዮጵያን በሰላም ቢያስተዳደር እኔ የሚጀመርያ ደጋፌው ሆን ነበር። ግን አይደለም። ሃቁ ይህ ነው። የጎሳ ፌደራሊዝም የምንጠላው የግጭት እና ጭቆና መንስኤ ስለሆነ ነው። ይህ ደግሞ በመረጃ የተመሰረተ statement ነው። ክርክራችን በታሪክ እና ርዕዮት ዓለም የተገደባ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ መረጃ የተመሰረተ ነው። ይህ መከራከርያ መንገድ ነው አዋጪ ብዬ የማስበው።

Thursday, 11 October 2018

መልዕክት ለኢሳቶች…

አቤቱታ፤ ማማረር፤ ማልቀስ፤ complaining ህዝብን ተስፋ እንዲቆርት ያደርጋል። ይህ ከኢሳት ተዕልኮ የሚጻረር ነው።

እንደ አንድ ተራ ዜጋ ምክሬ እንዲህ ነው፤ ስለ ችግሮች ለ10 ደቂቃ ካወራችሁ ስለ መፍትሄ እና አማራጭ መንገዶች ለ20 ደቂቃ ተወያዩ። አዋጪው መንገድ ይህ ይመስለኛል።

Wednesday, 10 October 2018

የቅራኔ መፍታት (conflict resolution) ጉድለታችን

አንዱ ከብዙ የጠ/ሚ አብይ አህመድ ልዩ የሚያረጋቸው ችሎታዎች የቅራኔ መፍታት አቅማቸው ነው። ትዕቢት፤ ቂም፤ አሉታዊነት፤ ትቶ የሁሉንም ትቅም የሚያስከብር ለሁሉም ተመራጭ የሆነ ግባ ላይ በማተኮር ችግሮችን ፈትተዋል አሁንም እየፈቱ ይገኛሉ። ይህ አቅማቸው ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መሪዎች ለዘመናት ታይቶ አይታወቅም (https://ethsat.com/2018/10/ethiopia-soldiers-show-up-unannounced-at-national-palace-pm-orders-pushups/)።

@Samuel Abebe (በዚህ ትችት ላይ https://www.facebook.com/abdurahman.ahmedin.7/posts/2120966214582614?comment_id=2121015731244329) ሁላችንም በውስጣችን የምናስበውን ታላቅ ጥያቄ ጠየቀዋል፤

«መለወጥ ስህተትን ከመቀበል ይጀምራል ይባላል ትልቅ ስህተት ተፈጽሞም ከቅንጅት አመራሮች ስህተቱን ተቀብሎ እዚህ ላይ ይህን ባንሳሳት ኑሮ የሚል አመራር እንዴት ይጠፋል? ሁሉም ወደ ሌላ ሰዉ ጣቱን ይቀስራል፡ እኛስ የትኛዉን አምነን የትኛዉን እንቀበል?»

ዋና እና ተገቢ ጥያቄ ነው። ብስለት እና እውቀት የሞላው። በማንኛውም ቅራኔ አንድ ጥፋተኛ እና ሌላው ንፁሃን የለም (there are two or more sides to any conflict)። ይህን ሃቅ ማንኛውም ስለቅራኔ የሚያውቅ ባለሙያ፤ ማንኛውም የካህን፤ ማንኛውም አስተዳዳሪ፤ ማንኛውም ወላጅ የሚያውቀው ነው። ግን ብናውቀውም እንዳማናውቀው አድርገን ነው የምንኖረው። ቅራኔ ውስጥ በተገኘን ቁጥር እራሳችንን ፍፁም ንፁህ ሌላው ፍፁም ጥፋተኛ አድርገን ነው የምንቆጥረው።

ይህ ከገባን በቅንጅት ቅራኔ ህሉም ተሳታፊዎች የተወሰነ ሚና መጫወታቸውን ሊገባን ይገባል። የፈረደበት ልደቱ ጥፋት ብቻ ሊሆን አይችልም። ዋናው ችግር የሱ ነው ቢባልም ያንን ችግር ማስተናገድ አለመቻል በራሱ ትልቅ ድክመት ነው! መታመን ያለብት እና ይቅርታ የሚጠየቅበት ድክመት ነው። ታላቅ መማርያ የሚሆን ድክመት ነው።

እንደ ቅንጅት አይነት ታላቅ ድርጅት፤ እጅግ ግዙፍ የሆነ የሀገር ሃላፊነት ያለው ድርጅት ሲፈርስ ሁሉም በአመራር ያሉት በመፍረሱ ሚና ተጫውተዋል እና ሁሉም ድክመታቸውን አምነው ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል። እኛም ደጋፊዎቻቸው እንዲሁም። ያደረግነውን ስህቶቻችንን ካመንን በኋላ ብቻ ነው መማር የምንችለው እና እንዳንደግማቸው ማድረግ የምንችለው።

የቅንጅት ታሪክ ከብዙ የሀገራችን ፖለቲካ የቅራኔ መፍታት አለመቻል ታሪኮቻችን አንዱ ነው። እንዳውም በኔ እምነት የፖለቲካ እና ማህበራዊ ችግሮቻችን ዋና ጎልቶ የሚታየው ምክንያት «የቅራኔ መፍታት (conflict resolution) ጉድለታችን» ነው። በዚህ ዙርያ ብዙ ተጽፏል እና ተነግሯል ግን በቂ አልተደረገም። ዛሬም የምናያቸው ነገሮች አሉ፤

1. አንድ «አቋም»፤ ርዕዮት ዓለም፤ አስተያየት ኖሮን አብሮ መስራት አለመቻል
2. የራሳችንን ጥቅም ጎድተን ቂማችንን ለመወጣት የምናደርጋቸው ስህተቶች
3. የጋራ ማሸነፍን ከመፈለግ (አሁንም የራሳችንን ጥቅም ቢጎዳም) ሌላው እንዲሸነፍ መመኘት እና መስራት
4. ፖለቲካን እንደ ሃይማኖት ፍፁም እውነት እንዳለው መቁጠር።

የፖለቲካ አካሄዳችን እንዲሻሻል ከተፈለገ ስለነዚህ ጉዳዮች መያየት እና መፍትሄ ማግኘት ግድ ነው።

ቅራኔ መፍታት ለኛ ኢትዮጵያዊያን አዲስ ነገር አይደለም። የድሮ ንጉሶቻንን አድርገውታል። ይህን የሚያስፈጽሙ በርካታ ባህላዊ መንገዶች አሉን። ከሃይማኖታችን ደግሞ መሰረታዊ ቅራኔ መፍታት ምክንያቶችንም ዘዴዎችም አሉ። ለምሳሌ በክርስትና «ንስሃ» ማለት ማለት 1) ስተትን ማመን 2) እንዳይደገም 3) ሌላው እንዲገባው 4) እራስን ለማረም 5) እራስን ለማወቅ ወዘተ። ውየንም «አለመፍረድ» ማለት 1) ለሌላው መቆርቆር (empathy) 2) የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ችኩሎ አለመድረስ 3) ጣት ጠኩሞ የራስን ችግር መርሳት ወዘተ።

ስለዚህ አሁን ማድረግ ያለብን እነዚህን (ምናልባት የተረሱ) ባህላዊ እሴቶችን እንደገና ማስነሳት እና ማሰራጨት ነው። ከባድ ስራ ነው ግን ምርጫ የለንም!

http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html

Monday, 17 September 2018

መርዝ መጠጣት መብት ቢሆንም ይገላል፤ እንዲሁም የጎሳ ብሄርተኝነት መብት ቢሆንም ህዝብን ያጠፋል

ለማንም ሰው በ«ጎሳ ብሄርተኝነት» እና የፖለቲካ ዘመዱ በ«ጎሳ አስተዳደር» ማመን መብቱ ነው። አንድ ሰው እንዲህ «ኢትዮጵያዊ አይደለሁም፤ ኦሮሞ ነኝ። ኢትዮጵያ ህዝቤን ለዓመታት ጨቁናለች ቅኝ ገዝታለችም። ማንነቴ ኦሮሞ ነው። መኖር የምፈልገው በኦሮሞ ሀገር ነው እንጂ ኢትዮጵያ አይደለም» ቢል መብቱ ነው። እንዲህ አታስብ ማለት ልክ አይደለም። ካልንም መብት ገፈናል ግጭትንም ጋብዘናል ማለት ነው (ይህንን ጥንቅቃችሁ እንድታነቡ እጠይቃለሁ http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2017/11/whats-ethnic-nationalism-again.html)።

ይህን ተከትሎ በርካታ ሰዎች እንዲህ አይነት የጎሳ ብሄርተኝነት አመለካከት ካላቸው እና የፖለቲካ ፍላጎታቸው ይህ ከሆነ ጥያቄአቸው በሰላማዊ መንገድ መስተናገድ ይኖርበታል። ለምሳሌ የአንድ ክፍለ ሀገር ወይንም ክልል 70% ህዝብ «ነፃነት» ወይንም ሌላ የፖለቲካ አስተዳደር እፈልጋለሁ ካለ በድርድር መልክ መስተናገድ አለበት። አለበለዛ መብታቸውን አላከበርንም ማለት ነው። እንዲህ አይነት አካሄድ ደግሞ ወደ ግጭት እና ጦርነት ማምራቱ የታወቀ ነው።

የጎሳ ብሀሄርተኝነት መብት ነው ብለናል። ታድያ ለምንድነው የምንቃወመው? መልሱ ቀላል ነው፤ የጎሳ ብሄርተኝነት የግጭት ምንጭ ስለሆነ ነው። በተለይ በብሶት ማንነት የተመሰረተ (grievance based identity) የጎሳ ብሄርተኝነት በ«ጭቋኝ ተጨቛኝ» አስተሳሰብ የተሞላ ስለሆነ ሁልጊዜ ግጭት ያመጣል። ተጨቁኛለሁ ጨቋኜን ማጥቃት አለብኝ ይላል። ብድር መመለስ አለብኝ ይላል። መሬቴን መመለስ አለብኝ ይላል። «መጤዎችን» ማባረር አለብኝ ይላል። ሰውን እንደ ሰው ከማየት እንደ ቡድን ያያል። የመንጋ አስተሳሰብ ይጋብዛል። ወዘተ። ታሪኩ ዓለም ዙርያ የታወቀ ነው።

የጎሳ ብሄርተኝነት ግጭት እንደሚጋብዝ የሚታወቀው በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር ባለፉት 27/40 ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ ያየነው ነው። ግጭቶቹ የህወሓት ስራ ናቸው እንጂ የጎሳ ስረዓቱ አይደለም ማለትም አይቻልም። አብዛኞቹ ግጭቶቹ ህወሓት እንደ ተጋጭ አልተሳተፈባቸውምና። ግጭቶቹ የህወሓት እጅ ቢኖርባቸውም ህወሓት በባዶ መሬት ያስነሳቸው አልነበሩም። ህወሓት የነበሩ የጎሳ ቅራኔዎችን ነበር የሚጭረው እንጂ ቅራኔዎችን ከስር አልፈጠረም። ስለዚህ ባለፉት ዓመታት ያየናቸው የጎሳ ግጭቶች የጎሳ ብሄርተኝነት እና አስተዳደር ውጤት ናቸው ማለት ይቻላል።

በቅርብ ታሪካችን እንደሚመሰክረው የፖለቲካዊ፤ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበረሰባዊ ግጭቶች ሁሉ በ«ጎሳ ፖለቲካዊ ውድድር» ዙራይ (ethnic political competition) ነው የሚከሰቱት። ይህ ውድድር በመሬት፤ የፖለቲካ ስልጣን፤ ንብረት ክፍፍል ወዘተ ሊሆን ይችላል። «ይህ መሬት የኛ ነው»፤ «ይህ ስልጣን ለኛ ይገባል»፤ «ይህ መዓድን ውጤት ለኛ ነው መሆን ያለበት» ወዘተ እየተባለ ወደ አጉል ውድድር፤ ፉክክር እና ግጭት ይኼዳል። ይህን በተግባር አይተናል እያየንም ነው።

በምንድነው ይህ የጎሳ ውድድር ከሌሎች ፖለቲካዊ ውድድሮች የሚለየው? በምን መንገድ ነው ከአካባቢ፤ ርዕዮት ዓለም፤ መደብ፤ ጥቅም ወዘተ የፖለቲካ ውድድሮች የሚለየው? ለምንድነው ጤናማ ያልሆነው? ልዩነቱ ጎሳ ከሰው ማንነት ጋር የተቆራኘ እና በቀላሉ መቀየር የማይቻል ነገር ስለሆነ ነው። አካባቢ፤ ርዕዮት ዓለም፤ መደብ፤ ጥቅም ይቀያየራሉ። ዛሬ አዲስ አበባ ነገ አምቦ መኖር ይቻላል። ዛሬ ማርክሲስት ነጋ ካፒታሊስት መሆን ይቻላል። ዛሬ ድሃ ነገ ሃብታም መሆን ይቻላል (ሳይቻል ሲቀር ደግሞ ይህም ኃይለኛ ግጭት የመጣል)። እነዚህ መስፈርቶች የሰው ልጅ ማንነት ላይ ሚና ቢኖራቸውም ሚናው መጠነኛ ነው። መቀየር ይቻላል ብዙ ጊዜም እንቀይራቸዋለን። ግን ጎሳ ወይንም ሃይማኖት የማንነት ታላቅ ክፍል ናቸው እና ባብዛኛው አይቀየሩም። ጎሳ በዚህ መልኩ ከሰው ልጅ ማንነት ጋር አጥብቆ ስለተያያዘ በጎሳ በኩል የሚመጣ ውድድር እጅግ የከረረ እና አከፋፋይ ነው የሚሆነው።

አልፎ ተርፎ የጎሳ ልዩነት እና የጎሳ ብሄርተኝነት በበዛበት ስፍራ ሁሉ ጥያቄዎች/ውድድሮች «የጎሳ መልክ» ይይዛሉ። ለምሳሌ የጎሳ ብሄርተኝነት በሌለበት ቦታ በአንድ ድርጅት እና የሰራተኛ ማህበር ግጭት ካለ ግጭቱ በኩባኒያው እና ሰራተኛ ማህበር መካከል ሆኖ ይቀራል። ምናልባት ሌሎች ቁባንያዎች ከጓድ ኩባኒያቸው ጋር ይወግኑ ይሆን እና ሌሎች የሰራተኛ ማህበራት ከጓድ ከሰራተኛ ማህበራቸው ጋር ይወግኑ ይሆናል። የከረረ ጎሰኝነት ባለበት ቦታ ግን ኩባንያውም የሰራተኛ ማህበሩም በጎሳ ይሰየማሉ እና ጎሳዎች ከኋላቸው ይሰለፋሉ። ለምሳሌ የኩባንያው ባለቤት ኦሮሞ ከሆነ ኦሮሞዎች ከሱ ጋር ይሰለፋሉ ሰራተኞቹ ደግሞ ባብዛኛው ጉራጌ ከሆኑ ጉራጌዎች ከነሱ ጋር ይሰለፋሉ። ግጭቱ ከሰራተኛ መብት አልፎ ወደ ጎሳ ግጭት ይቀየራል። ወደ ከረረ ግጭት ይገባል። ጎሰኝነት ወይንም የጎሳ ብሄርተኝነት በአንድ ሀገር ሲበዛ ይህ ነው አንዱ አደጋ እና የግጭት መብዛት መንጭ።

ግን ይህ አደጋ እንዳለ ሆኖ ከላይ እንዳልኩት አንድ ሰውን የጎሳ ማንነትህን ተው ማለት አይቻልም። መብቱ ነው ማንነቱ ነው ምንም ትክክል ባይመስለን ወይንም በሃሰት የሆነ ሃሳቦች የተመሰረተ ነው ብንልም የሌላ ሰው ማንነትን አስገድዶ መቀየር አይቻልም (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_34.html)። አልፎ ተርፎ ሰውን በማንነቱ ጥንቃቄ በሌለው መንገድ ከተቸነው ይበልት እንዲከርር ነው የምናደርገው። በተለይም የጎሳ ማንነቱ በብሶት የተመሰረተ ከሆነ። ካልተጠነቀቅን አክራሪ ያልሆነውንም ወደ አክራሪነት እንገፈዋለን። ለምሳሌ «እኔ ኦሮሞ መጀመርያ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ ነኝ» የሚለው ኦሮሞ ማንነቱን ከተቸነው ወይንም ከተከራከርነው በማንነቴ አትምጡብኝ ብሎ ጭራሽ ኢትዮጵያዊነቱን ትቶ ወደ ኦሮሞነት ብቻ ሊያመራ ይችላል። ይህ የሚሆነው በስሜት ደረጃ ነው። «ይህ አደጋ ነው እና ኦሮሞ ብቻ ነኝ አትበል ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ነኝ በል» ማለት ሁኔታውን ያባብሳል ጎሰኝነቱን ይጨምራል።

ጥንቃቄ ያስፈልጋል ስንል ግን እውነት አይነገር አይደለም። ግን «ኦሮሞ አትሁን» አይነቱን አሉታዊ አስተያየት ከመሰንዘር ይልቅ በአዉንታዊው ማተኮር ነው። አዎን የጎሳ ብሄርተኝነት አደጋ እንደሆነ በግልጽ መናገር ጠቃሚ ነው። ግን ከዚህ ጋር አብሮ የጎሳ ማንነቱ እንዴት አለ ጎሳ ብሄርተኝነት (nationalism) ማስተናገድ እንደሚቻል መግለጽ ይኖርብናል። ማንነቱ በኢትዮጵያዊነት እንዲንጸባረቅ ማድረግ እንደሚቻል ማሳየት አለብን። ለምሳሌ አንድ እንደዚህ አይነት አውንታዊ ሃሳብ ኦሮምኛ ከአማርኛ እኩል የፌደራል መንግስት ቋንቋ ማድረግ ጥሩ ነው የሚለው አቋም ነው። ይህ አቋም የሚልከው መልእክት «አንተ ኦሮሞ ነህ፤ ኢትዮጵያም ኦሮሞ ናት» የሚል ነው። ማንነትህ በኢትዮጵያዊነት ተታክቷል ማለት ነው። እንዲህ አይነት አውንታዊ መርህ እና መልእክቶች ናቸው ሰው ወደ ጎሳ ብሄርተኝነት እንዳይገባ የሚረዳው ወይንም ከጎሰኝነት ወደ ኢትዮጵያዊነት እንዲያመዝን የሚያደርገው።

በሌላ በኩል ስለምናስተላልፈው መልዕክቶች መጠንቀቅ ያለብን እንዲህ ነው። ብዙ ጊዜ የጎሳ ብሄርተኝነት «ጥላቻ»፤ «ዘረኝነት»፤ «ጠባብነት»፤ «የፖለቲካ ነጋዴዎች ጭዋታ» ወዘተ ተብሎ ይሰየማል። እነዚህ በሙሉ የተወሰነ እውነታ አላቸው። ግን ሙሉ እውነታው አይደለም። በድፍኑ እንዲህ ማለቱ በርካታ ለዘብተኛ የሆኑ የጎሳ ብሄርተኞች ወይንም ገና አቋማቸውን ያልወሰኑ በመሃል የሚንሳፈፉ ሊያስቀይም እና ይበልጥ ወደ ጎሰኝነት ሊገፋቸው ይችላል። «ማንነቴ ኦሮሞ ነው ስላልኩኝ ዘረኛ ነኝ እንዴ» ብሎ ይበሳጫል። እንዳልኩት የጎሳ ማንነት በጣም ስሜታዊ ነገር ነው እና መተቸት አይወድም። ስለዚህ ስንተቸው በትክክል እና precise መንገድ መሆን አለበት። ለመልሶ ትችት የማይመች መሆን አለበት። ስለዚህ ዘረኛ አመለካከት ስንሰማ ይህን አመለካከት ዘረኛ ነው ማለት ተገቢም አስፈላጊም ነው። ወደ ኋላ ማለት እና መሸማቀቅ ጎጂ ነው። ግን በጅምላ ዘረኞች ናችሁ ካለን ሁኔታዎች ያባብሳል። በጠቅላላ የጎሳ ብሄርተኝነትን መቀነስ የምንፈልግ የማስተላልፈው ምልዕክቶአችንን ተጠንቅቀን ማርቀቅ አለብን። ልድገመው፤ የሰው ልጅ ማንነቱ ሲተችበት አይወድም።

ለማጠቃለል ያህል፤ የጎሳ ብሀኢርተኝነትን አቋም መያዝ መብት ነው። ግን የጎሳ ብሄርተኝነት እና የጎሳ ፌደራሊዝም የግጭት እና ሁከት ምንጮች ናቸው። በዚህ ምክንያት ነው የምንቃወማቸው።  በመሰረቱ ክፉ፤ ዘረኛ፤ ጠባብ ወዘተ ስለሆነ ሳይሆን የግጭት ምንች ስለሆነ ነው። ይህን በጽንሰ ሃሳብም በተግባር አይተነዋል። የጎሳ ብሄርተኝነትን ለመቀነስ ትጠንቅቀን መስራት አለብን በተለይ በምናስተላልፈው መልዕክቶቻችን ትክክለኛ እውነት ግን በጅምላ የማይፈርጅ እንዲሆኑ ማድረግ አለብን። የሰው ማንነትን አክብረን ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ውስት ይህ ማንነት በድምብ እንዲካተት በአውንታዊ መልክ መስራት አለብን።