Monday, 17 December 2018

ስለ ህገ መንግስት አንድ የውይይት ሃሳብ

አሁን ያለን የጎሳል አስተዳደር (ethnic federalism) የግጭት መንስኤ እንደሆነ የ27 ዓመት መረጃ አለን ብዬ ተከራክርያለሁ ከጽሁፎቼ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_89.html)። በህወሓት አገዛዝ የነበሩት የጎሳ እና የድንበር ግጭቶች ህወሓት ብቻውን ያካሄደው፤ የቀሰቀሰው፤ ያስተባበረው ብቻ አልነበሩም። ህወሓት በአስተዳደሩ ምክንያት ያሚመጡትን ችግሮች ለራሱ ጥቅም ያባብስ ነበር እና ያሉ ቅራኔዎችን ያባብስ ነበር እንጂ ችግሮችን ከሀ መፍጠር አቅም አልነበረውም። ዛሬም ለምሳሌ የሲዳማ እና ወላይታ ግጭት ስንመለከት አዎን የህወሓት እና ሌሎች ነበሮች እጅ ቢኖርበትም የጎሳ አገዛዙ መሰረታዊ መንስኤ ነው። በዚህ ምክንያት ዛሬ ያለው የጎሳ አስተዳደር ለሀገራችን ሰላም አይሆንም።

አማራጩ ምንድነው የሚለው ጥያቄ ላይ ጊዜ ብናጠፋ ጥሩ የመስለኛል። በዚህ ጉዳይ የተለያየ አቋም ያለን ኢትዮጵያዊያን ስለዚህ ገና ብዙ መነጋገር አለብን እስካሁን በቂ የተነጋገርን አይመስለኝም። ስንወያይም አብዛኛው ጊዜ የራሳችን አቋም ላይ ነው የምናተኩረው እንጂ በቂ ሌላውን አንረዳም።

ዛሬ አንድ አስተያየት ልስጥ… የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎች ኢትዮጵያ የብሄሮች ስብስብ ነው መሆን ያለበት ነው። የመጀመርያ ማንነታችን ጎሳችን ነው፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነታችን ሁለተኛ ነው ነው የሚሉት። የሀገር ስሜት አለን ነው። ኦሮሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለች ሀገር ናት። ባለቤቷም የኦሮሞ ህዝብ ነው። ግን በታሪክ ምክንያቶች እና ዛሬ ባለው ነባራዊ ሁኔታ አብሮ መኖር ስላለብን ተገንጥለን አንኖርም ብሄሮች እርስ በርስ ውል ይኖራቸዋል ነው። እንደ ብሄር ክልል ወይንም «ትንሽ ሀገር» ከሌለን የሀገራዊ መብታችን ተወሰደ ማለት ነው። ልክ እንደ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ሰው ከኬንያ ጋር በግድ ሙሉለሙሉ ተቀላቅለህ አንድ ሀገር ሁን ቢባል አይ አገርነቴን መጠበቅ እወዳለሁ እንደሚል አማራውም የብሄር ክልል ይቀር ቢባል ማንነቱ እንደተወሰደበት ይሰማዋል ነው። በአጭሩ ይህ አንዱ የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎች አስተሳሰብ ይመስለኛል።

እስቲ ለዚህ አንድ የሚሆን አማራጭ መልስ እንስጥ። ከህገ መንግስቱ «ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች» የሚለውን በሙሉ አውጥተን ግለሰባዊ ብቻ እናድርገው። ግን አሁን ያሉትን ክልሎች እንጠብቅ። ለክልሎች አሁን ካሉት ተጨማሪ መብቶች እንስጥ። ከዛ የኦሮሚያ «ሀገራዊ» ምስልን እንመልከት። በቋንቋ፤ ባህል፤ ማንነት፤ ወዘተ በኦሮሚያ አብዛኛው ኦሮሞ ስለሆነ የሚኖረው ፍላጎቱ እንዲሰፍን ያደርጋል። ይህ የድምጽ ብልጫ ኦሮሚያ ክልልን ከሞላ ጎደል ኦሮሚያ ሀገር ሊያደርገው ይችላል። ግን ሀገር አይባልም እና ኦሮሞ ዘር ያልሆኑ ከኦሮሞዎች እኩል መብት ይኖራቸዋል። ግን አናሳ በመሆናቸው ብዙ ተጽዕኖ አይኖራቸውም።

ለኔ ይህ አካሄድ የጎሳ አስተዳደርን መጥፎ ጎን ያስወግዳል ማለትም ሁሉ ጉዳያችን በጎሳ የተመሰረተ እንዳይሆን ያደርጋል። አንደኛ/ሁለተኛ/ሶስተኛ ዜጋ፤ መፈናቀል፤ የጎሳ ብቻ ፖለቲካ ወዘተ እንዳይኖር ያደርጋል። ግን የጎሳ ወይንም ብሄር መብት ያስከብራል። በዚህ በጎሳ መብት ማስከበር ከጎሳ አስተዳደር ብዙ ልዩነት አይኖረውም።

ይህ አንድ የመሃይም ለውይይት የቀረበ ፕሮፖዛል ነው። የጎሳ ብሄርተኞችን ፍላጎት ያሟላ ይሆን። የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ፍላጎትስ?

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!