Showing posts with label citizenship politics. Show all posts
Showing posts with label citizenship politics. Show all posts

Wednesday, 7 November 2018

የጎሳ አስተዳደርን አደገኝነት አለመረዳት ትንሽ ግትርነት ይመስለኛል

ከዚህ ገንቢ ውይይት (https://www.youtube.com/watch?v=tVqQW7Sh_G0) ስለ ጎሳ አስተዳደር (ፌደራሊዝም) ብዙ ጊዜ የሚነሳ ነጥብ ተነስቶ ነበር። ይህም፤

«የጎሳ ፌደራሊዝም በትክክሉ አልተሞከረም። እስካሁን ዴሞክራሲ አልነበረም፤ የአምባገነናዊ ጭቆና ነበር። የህዝቡ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅምም አልተከበረም። ለዚህ ነው ፖለቲካዊ ችግሮች የሚታዩት። ዴሞክራሲ፤ የኤኮኖሚ እና ማህበራው ፍትህ ሲኖሩ የጎሳ አስተዳደር በደምብ ይሰራል።»

አንዱ ተንጣኝ ይህንን አቋም ለመግለጽ "You can't judge a philosophy by its abuse" አይነት አባባል ተናግረዋል።

መቼስ ስለ ኮምዩኒዝምም እንዲህ ማለት ይቻላል! በትክክል ቢፈጸም ገነትን ያመጣልን ነበርና።

የጎሳ አስተዳደር ችግሮች ለማንኛውም አጉል risk ወይንም የራቀ እና ጸንፍ የያዘ ፍልስፍና ማቀፍ ለማይፈልግ ሰው ግልጽ የሆነ ይመስለኛል። ምክንያቶቹ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_89.html)፤

1. ደጋግሞ እንደሚባለው የትም ሀገር የጎሳ አስተዳደር የለም። ይህ በራሱ የጎሳ አስተዳደር እጅግ ጸንፍ የያዘ አስተዳደር እንደሆነ ይገልጻል።

2. በተለያዩ ሀገራት የጎሳ አስተዳደር የሌላቸውም ግን በተለያየ በፖለቲካ ክፈተቶች ጎሰኝነት ሲሰፍን ያለው ጉዳት አይተናል። የጎሰኝነት ችግር አንዳንድ ሀገሮች እስከ የጎሳ ፓርቲዎችም መከልከል አድርሷቸዋል።

3. የ27/22 ዓመት የሀገራችን የጎሳ አስተዳደር ተለምዶ ለጎሳ አስተዳደር አደገኝነት በቂ ማስረጃ ነው። አዎን ዴሞክራሲ አልነበረም ግን የጎሳ ተኮር ግጭቶች እና ቅራኔዎች በዴሞክራሲ እጦት ማሰበብ አይቻልም። መቼም ማንም reasonable ሰው እንዲህ የሚያየው አይመስለኝም። ምንም አይነት ችግሮች በጎሳ ግጭት መልኩ እራሳቸውን የሚገልጹ ከሆኑ ጎሰኝነት ነው ችግሩ ማለት
 ነው! አልፎ ተርፎ አሁን ዴሞክራሲ እየመጣ ግጭቶቹ ቀጥለዋል ወይንም በዝተዋል!

እነዚህን ግልስ የሆን ማስረጃዎች እያለን እና ግጭቶች እየበዙ እያሉ አሁንም የጎሳ አስተዳደር experimentአችንን እንቀጥል ማለት የሰከነ አስተያየት ነው? ይቅርታ አድርጉልኝ እና አይመስለኝም።

ይህን ስል የጎሳ አስተዳደርን የሚፈልጉት ሰዎችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ማስተናገድ አንዳለብን ይገባኛል። አማራጭ ሊኖር ይገባል። አለ ጎሳ አስተዳደር እንዴት ነው የጎሳ መብቶች (እነዚህ መብቶች አይነታቸው አከራካሪ ቢሆንም) ማስከበር የሚቻለው።

መልሱ ቀላል ነው እና እንደ ጎሳ አስተዳደር አዲስ ፈጠራ ውስጥ እንድንገባ አያስገድደንም።
ከኢትዮጵያ አስር እጥፍ በላይ የጎሳ መብቶች (ቋንቋ፤ ባህል፤ አስተዳደር) የሚያስከብሩ ሀገራት አሉ። ህንድ፤ ስዊትዘርላንድ፤ ካናዳ ወዘተ። እነዚህ ሀገራት ሁሉም ሀገ መንግስታቸውን በዜግነት ነው የመሰረቱት። የጎሳ መብቶች በክፍለ ሀገር አቀራረጽ፤ የቋንቋ ህጎች፤ ለክፍለ ሀገር የሚሰጠው የማስተዳደር መብት ወዘተ ያስከበራሉ። ግን መሰረቱ ዜግነት ነው። እነዚህን እንደ ምሳሌ ወስዶ መጠቀም ነው።

ለመዝጋት አንድ አጭር ምሳሌ ልስጥ። ዛሬ ከህገ መንግስቱ «ብሄር፤ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች» የሚለው ጥቅስ ከህገ መንግስቱ አወጣን እንበል። የክልል ቋንቋ በክልል ህዝብ ነው የሚወሰነው እንበል። ኦሮሚኛ የፌደራል ቋንቋ አደረግን እንበል። ይህ ሁኔታ (scenario) በርካታ የጎሳ መብት ያስከብራል። ኦሮሚያ ውስጥ በድምጽ ብልጫ የክልል ቋንቋ ኦሮምኛ ሆኖ ይቀራል። ይህ ማለት የምንግስት መስሪያቤት፤ ትምሕርት ቤት ወዘተ። የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርም በኦሮሞ ባህል እንዲሆን በድምጽ ብልጫ ይፈጸማል። ወዘተ። ይህ አንድ ምሳሌ ነው። አለ ጎሳ አስተዳደር በርካታ የጎሳ መብቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ።

ስለዚህ ወደ ህልም፤ ጸንፍ፤ አጉል ሙከራ አንሂድ። ቀላሉን መንገድ እንውሰድ። እንደ ኮምዩኒስቶቹ ህልማችንን እስከ መቃብራችን አቅፈን አንቆይ!

Sunday, 21 October 2018

የዜግነት ፖለቲካ ከባድ ነው!

አንታለል፤ የዜግነት ፖለቲካ ከባድ ነው። የንጉሳዊ አገዛዝ እና ማርክሲዝምን የለመደ ህብረተስብን ወደ ዜግነት ፖለቲካ ማስገባት ግዙፍ ሸክም መጎተት ማለት ነው። የዜግነት ፖለቲካ እንደ ጎሳ ፖለቲካ ተጨቁነናል፤ ተንቀናል፤ ደምና አጥንታትችን አንድ ነው፤ ሀገሪቷ ችግር ውስጥ አለች እና እየተጠቃን ነው ስለዚህ ወደኛ ተሸግሸጉ፤ ወዘተ ብሎ ድጋፍ መሰብሰብ ያችልም።

1. የዜግነት ፖለኢትካ primordial አይደለም። ህዝብን ሆ! ብሎ መሰብሰብ አይችልም። ስልት ያስፈልገዋል። ስልት አያስፈልገኝም እና በstreet ፖለቲካ ልሳተፍ ማለት አይችልም። ይህ ውድቅ የነ አካሄድ ነው።

2. የዜግነት ፖለቲካ ከጎሳ ፖለቲካ ጋር ያለው ግንኝነት asymmetric ነው። ከጎሳ ፖለቲካ ጋር በተመሳሳይ ታክቲክ ፊትለፊት ግብ ግብ ልግባ ካለ ይሸነፋል። ምክንያቱ የጎሳ ፖለቲካ የስሜታዊ advantage አለው። ለምሳሌ 1) የጎሳ ፖለቲካ ከተተቸ «ጎሳዬ እየተጠቃ ነው» ብሎ ይጮሃል። እንዲህ ሲጮህ ለዘበተኞቹንም ወደሱ ሊያመጣ ይችላል። 2) የሀገሪቷ ጠቅላላ ሁኔታ (ፖለቲካ፤ ኤኮኖሚ፤ ጸትታ ወዘተ) እየተበላሸ ከሄደ የጎሳ ፖለቲካ «የነሱ የጠላቶቻችን ጥፋት ነው» ይላል። «ወደኛ ተሸሸጉ» ይላል። እንዲህ በማለት ተከታይ ይሰበስባል። ስለዚህ ይህን asymmetric ሁኔታ ተገንዝበን ተገቢውን ስልት መጠቀም አለብን።
ሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከቅራኔ መፍታት ዘገምተኝነት በሽታ ይጠቃል (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html)። ምቀኝነት፤ በግልጽ አለመነጋገር፤ አለመቆርቆር (empathy)። መጠርጠር። ሃሳብ እና ግለሰብን ማቆራኘት። ወገናዊነት። ስም ማጥፋት። ቂም። ግትርነነት ወዘተ። በነዚህ ምክንያት በርካታ ጊዜ የራሳችንን ጥቅምንም እንጎዳለን ሌላውን ለማጥቃት ስንል! በዚህ ምክንያት ነው አብሮ መስራት፤ ቅራኔ መፍታት እና win-win ሁኔታዎችን ማየት እና መፍጠር የሚያቅተን። ይገ ዜግነት ፖለቲካም የጎሳ ፖለቲካም እነዚህን ችግሮችን ማሸነፍ አለባቸው። ግን ለጎሳ ፖለቲካ ይቀላል። «ጠላት አለን» የሚባለው ነገር ሰውን ሳይፈልግም እንዲተባበር ያደርጋል። የሚአይተባበሩ ደግሞ ሀውሓት፤ ሻዕቢያ፤ ኦነግ ሌሎች የጎሳ ድርጅቶች እንዳሳዩት በቀላሉ ይረሸናሉ። የ 'survival' ጉዳይ ነው ተብሎ ይሳበባል። የዜግነት ፖለቲካ ግን ይህን አማራጭ የለውም። ከባድ የሆነውን የፖለቲካ ባህል ለውጥ ስራን ግድ መስራት አለበት።

3. የዜግነት ፖለቲካ ለዘብተኛ እና መካከለኛውን መንገድ መውሰድ አለበት። ጽንፈኝነት በጎሰኞቹ ተቆጣጥሯልና። የዜግነት ፖለቲካ ሁሉንም አይነት ፍላጎት በተቻለ ቁጥር ሚዛን ላይ አድርጎ ማስተናገድ አለበት። «ትልቅ ዛንጥላ» መሆን አለበት፤ አቃፊ መሆን አለበት። የዜግነት ፖለቲካ የማስወገድ፤ የመግደል፤ የመረሸን፤ የመጨቆን፤ የማጥቃት ወዘተ አማራጭ የለውን። እንዲዚህ ነገር ውስጥ ከገባ የዜግነት ፖለቲካ ማንነቱን ያጣልና የጎሰኝነት ፖለቲካውን ይሆናል። በጎሳ ፖለቲካው ይሸነፋል። ምሳሌ ልስጥ፤ ዛሬ ዜግነት ፖለቲካ ደጋፊዎች ሁለት አይነት አስተሳሰብ አለ ስለ ጎሳ ፖለቲካ። የአንዱ አቋም «ህገ መንግስቱ ዛሬውኑ ካልተቀየረ አቃቂ ዘራፍ» የሚል ነው። ብዚህ ጉዳይ ድርድር የለም ይላል። ሌላው ጎራ ደግሞ «ህገ መንግስቱ መቀየር አለበት ግን ይህን ለማድረግ ገና አሁን ወቅቱ አይደለም፤ መጀመርያ ንግግር እና ድርድር ማድረግ አለብን» ይላል። ሁለተኛው ነው ለዘብተኛውም ሚዛናዊውም መንገድ። ይህ ለዜግነት ፖለቲካ ግድ ነው።

4. ችግር እና ሁከት የዜግነት ፖለቲካን ይጎዳል የጎሳ ፖለቲካን ያጠነክራል። (ያው ይህ ይሚያስኬደው እንደ ኢትዮጵያ አይነት የጎሳ ፖለቲካ ያለበት ሀገር ነው።) ችግር ሲኖር ሰው ወደ ጎሳ የመሸግሸግ ባህሪ አለው። የደርግ ሁከት እነ ሻዕቢያ፤ ህወሓት እና ኦነግን በጣም አጠነከረ። ዛሬም አማራ ላይ ጥቃት ሲፈጸም የአማራ ብሄርተኝነት ንቅናቄ እየጠነከረ ይሄዳል። ስለዚህ የዜግነት ፖለቲካ በአብዮት መምጣት አይችልም አብዮት ሁከት ነውና። ብዙዎቻችን ኢህአዴግ በአብዮት («ስር ነቀል ለውጥ») መገልበጥ አለበት ስንል የአብዮቱ ውጤት የዜግነት ፖለቲካ ይሆናል ብለን አስበን ነበር። ይህ ታላቅ ስህተት ነው። ዛሬም የዜግነት ፖለቲካ ጭላንጭል ማየት የቻልነው ለውጡ አለ አብዮት ስለመጣ ነው። አለ ሁከት ስለመጣ ነው።

5. ሁላችንም እንደምናውቀው የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች እስካሁን ታሪካችን ጥሩ አይደለም። ፖለቲከኞቻችን፤ ጋዜጠኞቻችን አክቲቪስቶቻችንም አብሮ መስራት አልቻሉም። የቅንጅት ታሪክ ይህን ታላቅ ሽንፈታችንን በድምብ ይገልጻል። ይህ በመሆኑ ዛሬ የዜግነት ፖለቲካ ድርጅቶች እጅግ ደካማ ናቸው። የዜግነት ፖለቲካ የሚደግፈው ብዙሃን ብዙ ነው፤ ይህ የቅንጅት ታሪክም ይመሰክራል። ግን ይህ ግዙፍ ብዙሃን በድርጅት፤ ልሂቃን እና ፖለቲከኛ በአግባቡ አልተወከለም። ስለዚህ ዛኢረ የዜግነት ፖለቲካ የመጀመርያ ግብ መዋቅር ማለትም ድርጅትን ማጠንከር ነው መሆን ያለበት። አለ በቂ መደራጀት ምንም ማድረግ አይቻልምና። ሁሉም የዜግነት ፖለቲካ ተቀናቃኞች ሙሉ አቅማቸውን (resources) በዚህ ጉዳይ ላይ ማዋል አለባቸው። ምርጫ የለም። ሌሎች የጊዜያዊ ስራዎች ውሃ ቀዳ ውሃ ድፋ ነው የሚሆነው። ለዜግነት ፖለቲካ strong organizations are a precondition to any success።

6. የዜግነት ፖለቲካ ገና መደራጀት ላይ ስለሆነ ጠላትን ማፍራት የለበትም። እንደ ጠ/ሚ አቢይ ሁሉንም ማቀፍ መቻል አለበት። ጠላት ካፈራ የመደራጀት ስራው ይደናቀፋል። ስለዚህ ሌሎችን በአግባቡ በጥሩ ሁኔታ ይዞ የራሱን ስራ መስራት ነው ያለበት። ይህ basic ፖለቲካ ነው ግን አንዳንዶቻችን ፖለቲካን እንደ ሃይማኖት ጥቁር እና ነጭ አድርገን ስለምናይ ወደ ቀላል ስህተት እንገግባለን። ገና ሳንደራጅ፤ ገና ሳንጠነክር ወደ ጦርነት ካልገባን እንላለን። ይህ ለዜግነት ፖለቲካ አይሆንም።

7. «የወሬ ፖለቲካ» ለዜግነት ፖለቲካ አይሆንም። የወሬ ፖለቲካ ማለት ተቃራኒዎችን በወሬ ዘመቻ ማጥቃት እና የራስን ወገን እንደ ሰለባ አድርጎ ማውራት። የጥላቻ ፖለቲካ ማለት ነው። የወረ ፖለቲካ አላማው ህዝቡ ተናዶ እንዲነሳ ማድረግ ነው። ካላይ እንዳስረዳሁት ህይ አይነት አካሄድ ለጎሳ ፖለቲካ ነው የሚጠቅመው እንጂ የዜግነት ፖለቲካ (ስሜታዊ ስላልሆነ) እንዲህ አይሰራም። ለዚህ ደግሞ የ27 ዓመት ማስረጃ አለን። ለ27 ዓመት እኛ ተቃዋሚዎች ወያኔ ሴጣን ነው ብለን ብንቾህ ምንም አልሰራም። ለውጡ የመጣው ህዝቡ የትግሬ የባላይነት በተግባር ሰልችቶት ነው እንጂ ኢሳት ስለነገረው አይደለም። ለ27 ዓመት ስለ ወያኔ ከማውራት አቅማችንን በመደራጀት ስራ ብናውል ወያኔ ገና ድሮ ወርዶ ነበር።

8. አንዱ ከላይ ከጠቀስኳቸው የፖለቲካ «ጎጂ ባህሎች» የሁሉም አሸናፊ (win-win) ውጤት አለማወቅ ነው። ይህ እንዳልኩት የዜግነት ፖለቲከኞች እና ተቀናቃኞች ይበልጥ የሚጠቁበት በሽታ ነው። (የጎሳ ፖለቲከኞች በጎሳ ስሜት ስለሚቆጣጠሩ ይህ ችግር ቢኖራቸውም አነስተኛ ነው።) ይህ በቅንጅት እና ቀጥሎ ባለው ታሪክ በደምብ ይታያል። ገና ትንካሬ ሳይሰበሰብ ስለ ፖለቲካ ክፍፍል ማሰብ፤ ስለ ስልጣን ማሰብ። ትንሽ ስልጣን በግዙፍ መዋቀር ከሚኖረኝ ትልቅ ስልጣን በባዶ መዋቀር ይሻላል የሚል አስተሳሰብ ነው። ይህን ማስወገድ ማለት አለብን። አብሮ ከሰራን ትልቁን ውጤት አምጥተን ለሁላችንም በቂ ስልጣን ይኖራል (ፖለቲከኞች)።

9. ባለፉት የ50 ዓመት የፖለቲካ ታሪካችን በተለይም አብዮት እና ሁከት የዜግነት ፖለቲካ ወይንም የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ልሂቃን ጎራ ተገድሎ፤ ተሰድዶ፤ እርስ በርስ ተፋጅቶ ቁጥሩ መንኗል (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_38.html)። የዜግነት ፖለቲካ መዋቅሮቻችን የደከሙበት ምክነያት አንዱ ይህ ነው። እነ ኃይሉ ሻውል፤ ብርሃኑ ነጋ እና ልደቱ አያሌው የቅንጅት ዋና መሪዎች ሆነው ሲገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ልሂቃን ሞትዋል፤ ተሰዷል ወይን ፖለቲካ ኮሬንቲ ነው ብሎ ትቶታል። ስለዚህ እነ ብርሃኑ ነጋ ከዚህ የተረፉት ጥቂቶች ናቸው። እነሱ ሲደናቀፉ የሚደግፋቸው ወይንም ቦታቸውን የሚወስድ ማንም አልነበረም። የህ የልሂቃኑ መመንመን ዛሬም ሚና ይጫወታል። ሁለት የዜግነት ፖለቲካ ልሂቃን ትውልድ ነው ያጣነው። አዲሱ ትውልድም «አለ አሳዳጊ» ነው ያደገው። ይህን ችግር ተገንዝብን የሚያስፈልገውን የአካሄድ ለውጦች ማድረግ ይኖርብናል።

10. እውናትዊ የዜግነት ፖለቲካ ለብዙ አይነት ሃሳቦች መቆርቆር አለበት (empathy)። ሚዛናዊ መሆን ስላለበት። አንዱ የብዙ የዜግነት ፖለቲካ ተከታዮች ችግር ለጎሳ ፖለቲካ ምንም አለመቆርቆር ነው። የጎሳ ፖለቲካ ከዘረኝነት ውጭ ምን እንደሆነ አይገባንም ወይንም ሊገባን አንፈልግም። ይህ ታልቅ ድክመት ነው። ሌላውን አለማወቅ፤ ተቃራኒውን በአግባቡ አለማወቅ ታልቅ ሽንፈትን ያመጣል። የጎሳ ፖለቲካ ዓለም ዙርያ ያለ ነገር ነው ከነ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ። «ዘረኝነት ነው» ብሎ መሰየሙ የውሸት ማቅለልያ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2017/11/whats-ethnic-nationalism-again.html)። እውነት ነው በርካታ ዘረኞች የሆኑ ጎሳ ብሄርተኞች አሉ። ግን «ዘረኝነት» የጎሳ ፖለቲካን ሙሉ በሙሉ አይገልጸውም። የጎሳ ብሄርተኝነት ጎሳውን እንደ ሀገር (nation) ማየት ማለት ነው። ይህ ደግሞ ስሜት ነው፤ ማንነት ነው። እንደዚህ አይነት ነገር በlogical ሙግት አይቀየርም። ስልት ያስፈልጋል። ለዘብተኞቹን ማቀፍ ያስፈልጋል። ህዝብን በመቀላቀል አንዱ የሌላውን ቋንቋ እንዲያውቅ ብማድረግ የሃገር ውስጥ መዘዋወር እንዲጨምር በማድረግ ህዝብ እንዲወሃድ መባድረግ ነው ችግሩ የሚፈታው። ዝም ብሎ መጮህ ጉዳት ነው የሚያመጣው። የለዘብተኛ (moderate) አስተሳሰብ ነው እንዲህ አይነቱን ነገር ሊገነዘብ የሚችለው።

Friday, 19 October 2018

የወሬ ፖለቲካ

እኛ ኢትዮጵያ ብሄርተኞች ለ27 ዓመት ወያኔን ከመውቀስ ሌላ ስራ ባለመስራታችን የወያኔን ለሩብ ክፍለ ዘመን እንዲገዛ አደረግን። በቂ ጸረ-ወያኔ ፕሮፓጋንዳ ካሰራጨን ህዝቡ በአመጽ ይነሳል ብለን ገምተን ይሆናል ግን አልሆነም። በመጨረሻ አመጹን ያስነሳው ህዝቡ በእውን የትግሬ አድሎ በዝቶበት ነው። የትግሬ አድሎ አለ ብሎ በነ ኢሳት ስለተነገረ ሳይሆን ህዝቡ በለት ኑሮው ስላየው ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/10/ethnic-federalism-kills-meles.html)።

ስለዚህ የወሬ ፖለቲካ እንደማይሰራ የ27 ዓመት ማስረጃ አለን። እኛ ኢትዮጵያ ብሄርተኞች 100% ጊዜአችንን ስለ ወያኔ በማልቀስ ከማዋል ፋንታ 50%ኡን ህዝብ እና ልሂቃንን በማደራጀት ብናውለው የት ደርሰን ነበር።

አሁንም አንዳንድ ጓዶቻችን የወሬ ዘመቻ በጎሳ ብሄርተኞች እና አሁን በ ጠ/ሚ አቢይ ማካሄድ ጠቃሚ ይመስላቸዋል። የድሮውን ስህተት መድገም። ለ27 ዓመት ያልሰርዋን መቀጠል። ምን ማለት ነው የማይሰራን ነገር መደጋገም?

ምን አልባት ውስጣችን ማደራጀት እና ሌሎች የእውነት የፖለቲካ ስራዎች ከባድ እንደሆኑ ስለምናውቅ ወሬ ላይ በማተኮር ማምለጥ እንፈልግ ይሆን። ወይንም ሻዕብያ እና ህወሓት ግዙፍ በህዝባቸው ጽናት ግዙፍ ድርጅቶች ሆነው ሲገኙ እኛ ኢትዮጵያ ብሄርተኞች የነሱን 1% የሚያክል ድርጅት መመስራት ስላቃተን አፍረን ይህንን ላለማየት ይሆን ወደ ወሬ ፖለቲካ የምንሸሸው። የዝቅተኛ ስሜት አድሮብን ይሆን 6% ድጋፍ ያለው ወያኔ ለ27 ዓመት ሲገዛን አንድ ጠንካራ ድርጅት መፍጠር ባለመቻላችን?

ምክንያቱ ምንም ቢሆን የወረ ፖለቲካ አይሰራም እና ካሁኑኑ አቅማችንን ከዛ ወደ ከባድ ስራው ወደ መደራጀት ማሸጋሸግ አለብን። ይህ ማለት ካሁን ወድያ ወሬ ሳይሆን ስራ መስራት። መሳደብ ሳይሆን ብልጥ ሆኖ ትብብሮችን መፍጠር ለጊዜውም ቢሆን እስከንደራጅ። ድልዲዮችን ከማቃጠል መጠቀም። እንደ ጠ/ሚ አቢይ አይነቱን ከማራቅ ማቀፍ እና መጠቀም። ይህ ነው ፖለቲካ። እንጂ ዝም ብሎ ማውራት መገዛት ማለት ነው።

Don't make enemies before you can fight!

ቆቅ ሞቷን ጠራች ይባላል።

የኢትዮጵያ ብሄርተኞች በቂ እንዳልተደራጀን የታወቀ ነገር ነው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያላቸው ድርጅቶች ሊኖርን ይገባል ግን የለንም። በርካታ ሚሊዮኖች ብዙሃን አለን ግን ልሂቃን፤ መሪ እና ድርጅት ላይ እጅግ ደካማ ነን።

በተዘዋዋሪ የጎሳ ድርጅቶች ያው የጎሳ በመሆናቸው ትብብር እና አንድነት ስላላቸው ጠንካራ ናቸው። ሁከት እና ችግር ስለሚያጎለብታቸው እየጠነከሩም እየሄዱ ነው።

በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ዋና ስራ መደራጀት እንደሆነ ግልጽ ነው። የህልውና ጉዳይ ነው። የዜግነት ፖለቲካችንን ካላራመድን እና ግዙፍ ድርጅቶች ካልፈጠርን እኛም ሀገራችንም እንጠፋለን። ጠ/ሚ አቢይ ቢፈልግም ይህን ሊያደርግልን አይችልም። እኛ የራሳችንን ድርሻ ካልሰራን እሱም አቅም ያጣል። ለነገሩ እስከ ዛሬም ሀገራችን ላሳለፈችው ችግር ዋና ምክንያት የኛ በሚገባው አለመደራጀት ነው።

በዚህ ሁኔታ፤ ደካማ ሆነን፤ ዋና ስራችን እራሳችንን ማጎልበት እና ማደራጀት በሆነበት ጊዜ ጠላቶች ማፍራት ጅልነት ነው። አሁን ሁሉንም የማቀፍ ጊዜ ነው። የጊዜ መግዥያ ጊዜ ነው። ጠ/ሚ አቢይ፤ የጎሳ ብሄርተኞች፤ ህወሓት ወዘተ ሁሉንም ተጠንቅቀን ይዘን ወዳጅ መስለን መገኘት አለብን። የመደራጀት ስራችንን መስራት ነው ያለብን። ብልህ ፖለቲካ ማለት ይህ ነው።

ለምሳሌ የአዲስ አበባ ሲቪክ ድርጅት ለማቋቋም ሲጀመር ስለ ከንቲባው አለማንሳት። ወይንም ማሞገስ። ጽሁፍ እና ፖስተሮች በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በኦሮምኛም ማዘጋጀት። አዲስ አበባ ለአዲስ አበቤዎች አይነት መፈክር ትቶ በቀላሉ «ለአዲስ አበባ ነዋሪ ሁሉ መብት ማስከበር» ነው ተልዕኯችን ማለት ነው! ወዘተ። ሀሳቡ ግልጽ ይመስለኛል።

ግን ይህን ከማረግ ፋንታ እንደ ቆቛ እንጮሃለን! ምንም ሳይኖረን አፍ ብቻ እንሆናለን። ባለን ጊዜ አንዴ ከጎሳ ብሄርተኞች ጋር አሁን ደግሞ አንዳንዶቻችን ከጠ/ሚ አቢይ ጋር ግብ ግብ እንገባለን። ገና ለመታገል አቅም ሳይኖረን ጠላቶች እናፈራለን። ይህን ማቆም አለበን፤ የህልውና ጉዳይ ነው። የ50 ዓመት የፋራ ፖለቲካችንን ማቆም ካላቆምን ሌላ እድል የሚኖረን አይመስለኝም።

አካሄዳችን መሆን ያለበት መጀመርያ ኃይልን መሰብሰብ። ይህን ለማድረግ ባይጥመንም የሚያስፈልገውን ነገር ማድረግ። ከሁሉም ጋር አብሮ መስራት ያስፈልጋል። እራስን አለማጋለጥ ያስፈልጋል። ኃይልን ከሰበሰብን በኋላ ደፈር ያሉ አቋሞች መያዝ እና ስራዎች መስራት።

በመጨረሻ ማለት የምፈልገው... ምን አልባት በመጮህ፤ መተቸት እና በመውቀስ ህዝባችን እንዲማረር እና እንዲቆጣ አድርገን በቀላሉ ይደራጃል ብለን እናስብ ይሆናል? ለዚህ ይሆን ብዙዎቻችን ዋናው የመደራጀቱን ስራ ትተን 100% ጊዜአችንን በመተቸት እና መወንጀል የምናጠፋው?

ይህ ከሆነ በጣም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። አካሄድ ውድቅ እንደሆነ የ27 ዓመት ማስረጃ አለን! ለ27 ዓመት ህወሓት እና የጎሳ ብሄርተኞች ሲረግጡን ያሁሉ ሚሊዮን ህዝብ ሆነን አንዳች ግዙፍ ድርጅት ማቋቋም አልቻልንም። የወሬ፤ ጩሀት እና ትችት ፖለቲካ አልሰራም።

ህወሓት ከስልጣን የወረደው እነ ኢሳት ህዝቡ ሀውሓትን እንዲጠላ ስላደረጉ አይደለም። ህዝቡ በለቱ ኑሮ አይቷቸው ጠልቷቸዋልና! አልፎ ተርፎኦ ይህ ጸረ-ህወሓት ዘመቻ ምንም አይነት ጠንካራ ድርጅት አልፈጠረም። ያሁሉ ዓመታት ጩሀት በኋላ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ትንሿ ግንቦት 7ን ብቻ ነው ያፈራነው።

ስለዚህ የጩሀት ፖለቲካ አይሰራም። ህዝቡን በፕሮፓጋንዳ አማርሮ ማደራጀት እንደማይቻል አይተናል። ህዝቡ በእውን በኑሮው ተማርሯል። የፖለቲከኞች ስራ ይበልጥ ተማረሩልኝ ማለት ሳይሆን ማደራጀት እና ለምሬቱ ትክክለኛ መስመር ማብጀት ነው። የኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች የፖለቲካ ልሂቃን ይህን ማድረግ አልቻልንም። እስቲ አሁን እንሞክር።