ሁላችንም ቄሮ፤ ፋኖ፤ አቢይ፤ ለማ፤ ኦነግ፤ ግንቦት 7 ወዘተ ሲባል ህወሓትን ከስልጣን ማውረድ የተቻለው የ27 ዓመት የተጠራቀመ የግለሰቦች እና የቡድኖች ትግል እንደሆነ እንረሳለን። አንዱ የትግል ዘርፍ ምርጫ 97 ዙርያ በተለይም በአዲስ አበባ የተደረገው ተቃውሞ እና የህዝብ አመጽ ነበር። በዚህ ልጀምርና…
ሁላችንም እንደምናውቀው ለ27 ዓመታት የአዲስ አበባ ህዝብ በፍርሃት ነው የኖረው ማለት ይቻላል። (የብሄር ብሄረሰቦች) ጨቋኝ፤ ገዥ፤ ትምክህተኛ ወዘተ ተብሎ በመንግስት ትርክት ተሰይሟል። ይህ ህዝብ ነገ በጎሳ ብሄርተኞች ተከበን እንወራለን፤ እንገደላለን እና እንፈናቀላለን ብሎ በስጋር ይኖራል። ይህን አይነት ክስተት ደግሞ በተለያየ የኢትዮጵያ ክልሎች ሲከሰቱ አይቷል። አዲስ አበባ ከበየቦታ የተፈናቀሉትን ተቀብሏለችም!
በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባ ህዝብ ይህ በእውነት የተመሰረተ ፍርሃት ምንጭን ለመከላከል ተባብሮ መደራጀት አልቻለም። አዎን በምርጫ 97 ለተወሰነ ጊዜ አሸዋ ላይ ተደራጀ ግን ይህ ወድያው ፈረሰ። አልፎ ተርፎ ህዝቡ ይበልጥ እንዲፈራ እና መደራጀት እንዳይሞክር አደረገ።
ሆኖም የአዲስ አበባ ህዝብ በልቡ መደራጀት እንደሚገባው ያውቃል። የህዝብ ቁጥር እና አቅም እንዳለው ያውቃል። መደራጀት ያልቻለበት ምክንያት የራሱ ድክመት እና ጥፋት መሆኑም በተወሰነ ደረጃ ውስጡ ያውቃል። ጭቆናውን ችሎ መደራጀት እንደነበረበት ያውቃል።
ህወሓት ደጋግሞ እንድተጫወተበትም ያውቃል። ለኔ ስገዱ አለበለዛ ጎሰኞቹን ለቅባችኋለው እያለ ቆዬ። የአዲስ አበባ ህዝብ እራሱን አጠንክሮ ዞርበል ከማለት ፈርተን ዝም አልን። እውነታውን እንመን።
ይህ ነው የአዲስ አበባ ህፍረት የምለው። የተገዛው በትንሽ የምትባል ቡድን (ህወሓት) እንደሆነ ያውቃል። ህወሓት አንድ ለአምስት በሚባለው የቁጥጥር ዘዴ ሲፈጸምበት በራሱ ድክመት እንደሆነ የሚገዛው ህዝቡ አውቋል። ቄሮ እና ፋኖ ሲወራላቸው ዝም ብሎ ቁጭ እንዳለ ያውቃል። ይህ ለአዲስ አበባ ህዝብ ታላቅ የስነ ልቦና ቁስል ሆኗል። የዝቅተኛ መንፈስ እንዲያድርበት፤ አቅም የሌለው እንዲመስለው፤ የተዋረደ እንዲመስለው አድርጓል። ይህ ነው የአዲስ አበባ ህዝብ ሀፍረታችን።
ፍርሃት እና ህፍረት ስላለን ነው በቀደም ኦነግ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ ችግሮች የተፈጠሩት። ህዝቡ ፍርሃቱን በእውን አየው። የሚፈራው የሚፈራቸው ሲገቡ ደንግጧል። በሌላ በኩል ደግሞ እንዳልተደራጀ እና አቅሙን እንዳልሰበሰበ ያውቃል እና ታላቅ insecurity ተሰምቶታል። ሰለዚህም ነው በሰንደቅ አላማ እና አርማ ዙርያ ግጭቶች የነበሩት። ከፍርሃት የመነጨ ምላሽ ነው የአዲስ አበባ ውጣቶች የሰጡት።
እዚህ ላይ አንድ aside ያስፈልጋል። መደራጀት ማለት መዋጋት አይደለም። ውግያ እንዳይኖር ጠንክሮ ስልታማ ሆኖ መገኘት ነው። ግዙፍ አቅም እና ስነ ስረዓት ያላቸው የህዝብን አላማ የሚያስፈጽሙ መዋቅሮችን መፍጠር ማለት ነው። እነዚህ መዋቅሮች ብዙ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ለምሳሌ በከተማ አስተዳደር፤ በምሃበራዊ ኑሮ ጉዳዎች፤ በጸጥታ ዘርፍ፤ በፍትህ ወዘተ። እነዚህ ህዝብን የሚወክሉ መዋቅሮች ቢኖር ሁሉም የአዲስ አበባ ድርጅቶች በህዝብ ፍላጎት እንዲመሩ፤ ተጠያቂነት እና ግልጸኝነትት እንዲኖር ወዘተ ያደርጋሉ። በአጭሩ ህዝቡን አንድ ገልጽ ላይ ያደርጋል። እነዚህ መዋቅሮች ቢኖሩ ኦነግ ሲገባ ህዝቡ ምንም አይመስለውም ነበር። ምንም አይነት ኃይልን መቋቋም የሚችሉ መዋቅሮች እንዳሉት ስለሚያውቅ። ጭራሽ የኦነግ አርማ ይዞ ለመቀበል ይወጣ ነበር! መደራጀት ይህ ማለት ይህ ነው። በአጭሩ አዲስ አበባ በአዲስ አበባ ህዝብ ፍላጎት እንዲመራ ማድረግ ነው።
ዛሬ የአዲስ አበባ ህዝብ እንደ መላው ኢትዮጵያ ህዝብ በፍጥነት በዚህ መልኩ መደራጀት አለበት። የፖለቲካ ፓርቲ መፍጠር አለበት ወይንም እንደ ግንቦት 7 አይነቱ ጋር ተባብሮ ለአዲስ አበባ መዋቅር መዘርጋት አለበት። ሚዲያ መመስረት አለበት። የባህላዊ ድርጅቶችን በአንድ ጃንጥላ ስር ማሰባሰብ አለበት። ህዝቡ የሚወያይበት መዋቅሮች መዘርጋት አለበት። በጥቅልሉ ህዝቡን በአንድ ገልጽ የሚያደርገው መዋቅሮች እና ድርጅቶች መፈጠር አለበት። ነጻነት ማለት እንደዚህ አይነት የፖለቲካ ሃላፊነትን መወጣት ነው።
ግን በመጀመርያ ፍርሃት እና ህፍረታችንን ማመን አለብን። ይህ መደበቅ የለበትም። ስለዚህ በይፋ ማውራት መቻል አለብን። እውነቱ ከሃሰቱ መለየት አለበት። ይህም በውይይት እና መመካከር ነው የሚመጣው። አንዴ ፍርሃት እና ህፍረታችንን ካመንን በኋላ ወደ መፍትሄ ለመሄድ ይቀለናል።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!