Monday, 13 August 2018

አጸያፊ ግጭቶች ለተወሰነ ጊዜ ይቀጥላሉ

ብዙዎቻችን ለ27 ዓመታት በየ ክልሉ በዘውትር የሚካሄደውን የምናውቅ አይመስለኝም። የቤተሰቦቼ ሀገር ጨርጨር (ምዕራብ ሀረርጌ) እንደ ምሳሌ ተጠቅሜ ላስረዳ። ኢህአዴግ ስልጣን ክተቆጣጠረ ጀምሮ በየጊዜው «ነባሮቹን» (የጨርጨር ሙስሊም ኦሮሞዎች) እንወክላለን የሚሉ ጸንፈኛ ጎሰኛ እና ሙስሊም ተነስተው «መጤዎቹን» (ሙስሊም ኦሮሞ ያልሆኑት አማራ፤ ጉራጌ፤ ሶማሌ ወዘተ) በግድ ሙስሊም ሁኑ፤ ከሀገራችን ውጡ ወዘተ እያሉ ይነሳሉ። በሳውዲዎች ገንዘብ የሚደገፉ «ማድራሳዎች» (የጸንፈኛ እስልምና ትምሕርትቤትዎች) ይከፈታሉ ጽንፈኛ እስልምና ያስፋፋሉ። ጸንፈኛ ጎሰኝነት በስውር በየመንግስት መስሪያቤቱም ይንቀሳቀሳል «መጤውን» አባሩ ግደሉ ብሎ ይሰብካል። ይህ ጸንፈኝነት በየወቅቱ «መጤዎች» ላይ ጫና ይፈጠራል እስከ ሞት ያህል ጉዳት በየጊዜው ይደርሳል። እንደዚህ አይነት ክስተቶች ሲበዙ ፌደራል ፖሊስ ወይንም መከላከያ ይመጡና ጸንፈኞቹን አድነው አግኝነተው ያስሯቸዋል ግን አብዛኛው ጊዜ ይረሽኗቸዋል። ምርመራ፤ ፍርድ ቤት ወዘተ የለም። ዋና አቀነባባሪዎቹን ፈልገው ያጠፏቸዋል። ከዛ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ሁኔታው ይረጋጋል «መጤው» ትንሽ ሰላም ያገኛል። ግን ከትወሰነ ጊዜ በኋላ ጸንፈኞቹ እንደገና ይነሳሉ። አላለፉት 27 ዓመት ይህ ነበር የሚደጋገመው።

ከዚም አልፎ ተርፎ በለት ኑሮዋቸው «መጤዎች» ስለ ደህንነታቸው በትወሰነ ደረጃ ሁል ጊዜ ይጨንቃሉ። አባቶቻቸው ጭቋኝ የነበሩ ያማይፈለጉ «እንግዶች» እንደሆኑ እንዲሰማቸው ይደረጋል። እንደ ሁለተኛ ዜጋ ነው የሚታዩት። ማህበራዊ ችግር ከተፈጠረ ወይንም የህግ አስከባሪ ጉድለት ከመጣ ጉዳት ይደርስብናል ብለው ነው «መጤዎቹ» የለት ኑሮዋቸውን የሚኖሩት። በስጋት ነው የሚኖሩት። የከፋ ጊዜ ከመጣ ፌደራል ፖሊስ ወይንም መከላከያ ነው የሚያድንን ብለው ነው የሚያስቡት።

የህወሓት አሰራር እንዲህ ነበር በኦሮሚያ፤ ደቡብ፤ ቤኒሻንጉል፤ ሶማሌ ወዘተ ክልሎች። ፖሊሲአቸውን «ያዝ ለቀቅ» ብሎ መሰየም ይቻላል። ጎሰኝነትን በፖሊሲ ደረጃም ያራምዳሉ ጸንፈኛ ጎሰኝነት እንዲፈጠር እንዲኖር ያደርጋሉ። ግን ከቁጥጥራቸው ሲወጣ የወለዷቸውን ጸንፈኞች ያጠፏቸዋል እና እራሳቸውን እንደ የ«መጤው» ጠባቂ አድርገው ያቀርባሉ። «መጤውም» ምርጫ የለውም ለደህንነቱ ሁልጊዜ ወደ ፌደራል መንግስት ይመለከታል። ህወሓት የኖረው ይህን ክፉ ሚዛን ገንብቶ በመጠበቅ ነው።

አሁን በነ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ዘመን ይህ አካሄድ አብቅቷል። በመጀመርያ ደረጃ ጎሰኝነትን ለመቀነስ ተነስተዋል። ሁለተኛ ደግሞ ሰላም፤ ፍቅር እና ፍትህ እንዲመጣ ነው የረዥም እቅዳቸው። በዚህ መሰረት ወንጀሎች እና ግጭቶች ሲፈጠሩ እንደ ድሮ የህወሓት አገዛዝ ገብተው አይረሽኑም። በህጋዊ መንገድ ጉዳዩን አጣርተው ፍትህ እና መፍትሄ በትክክሉ መንገድ ማድረስ ነው የሚፈልጉት። በዚህ መካከል ጸንፈኞች ፍርሃታቸው ቀንሶ ድሮ የማይደፍሩትን ያደርጋሉ። ወንጀሎች እና ግጭቶች ወዲያው አይቋረጡም መፍትሄ ቀስ ብሎ ይሆናል የሚገኝላቸው። በቅርቡ በሶማሌ፤ ቤኒሻንጉል፤ ሻሸመኔ ወዘተ የምናየው ይህ ነው። አልፎ ተርፎ በጠ/ሚ አብይ የግድያ ሙከራ ወይንም በስመኘው በቀለ ግድያ ዙርያም እንዲሁም ወደያው የፈጣን መልስ አልተገኘለትም። በህጋዊ ስነ ስርዓት እየተጣራ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_6.html)።

ከዚህ ሁሉም መካከል ደግሞ የአዲሱ ስርዓት አቅምን ማወቅ አለብን። የድሮ የህወሓት ርዝራዦች ገና ከመንግስት፤ መከላከያ፤ ፌደራል ፖሊስ፤ በተለይም ደህንነት ገና አልጸዱም ለማጽዳትም ረዥም ጊዜ ይፈጃል። እንኳን ሌላ የጠ/ሚ አብይን ደህንነት መጠበቅ እራሱ ከባድ ሆኗል። ስለዚህም ነው እነ አብይ በማንኛውም ስራ እንቅፋቶች እያገጠማቸው የሚሰሩት።

ስለዚህ ባሁኑ ጊዜ ከህወሓት የጠብ መንጃ ፍትህ-ቢስ አገዛዝ ወደ ጠ/ሚ አብይ አገዛዝ መሸጋገርያ ወቅት ገና ብዙ ወንጀል፤ ዘር ማጥፋት ሙከራዎች፤ ህዝባዊ ግጭቶች፤ ግድያዎች፤ ወዘተ ሳይቀጥሉ አይቀሩም። የጠ/ሚ አብይ መንግስት እስኪጠነክር ድርስ፤ የክልል ፖሊሶች እስኪጠነክሩ ድርስ፤ ህዝቡ እስኪረጋጋ ድርስ፤ ፖለቲከኞች እና ሌሎች መሪዎች እስኪረጋጉ እና ለጥያቄዎች መልስ እና አቅታጫ ማስያዝ እስኪችሉ ድርስ ይቀጥላል። የድሮ እንቅፋቶች እስኪነሱ ድርስ በርካታ ጉዳቶች ያጋጥሙናል። ከመታገስ እና አዲሱን መንግስት ባለን አቅም በተለይ በአቅም ግንባታ ደረጃ ከመርዳት በቀር ምንም ማድረግ አይቻልም።

ለተጎዱት ለተገደሉት በሙሉ ጸሎታችን ከነሱ ጋር ይሁን። የሁላችንም የተከማቸ የረዥም ዓመታት ኃጢአት ነውና ሀገራችንን በዚህ ሁኔታ እንድትሆን ያደረገው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!