Showing posts with label ethnic cleansing. Show all posts
Showing posts with label ethnic cleansing. Show all posts

Thursday, 27 September 2018

ለምንድነው የቡራዩን ክስተት የጎሳ ማጥፋት (ethnic cleansing) ክስተት የሚባለው?

ይህን ቪዲዮ እዩት።


እንዲሁ በርካታ የቡራዩ ሰለቦች እና ምስክሮች የዘር ማጥፋት ክስተት እንደሆነ ገልጸዋል። መረጃዎቹ ቀላል ናቸው፤ ወንጀለኞቹ በአንደበታቸው ዘር እየመረጡ ነው የገደሉት እና የግድያ እና ወንጀል አየነቶቹ ማለትም ማረድ እና መድፈር የዘር ጥላቻ ያለበት የዘር ማጥፋት ዘመቻን ያመለክታሉ። ይህ ምንም ጥርጥር የሌለው እውነታ ነው።

ኦሮሞዎችም ተገድለዋል ተጎድተዋል ይባላል። ይህ የዘር ማጥፋት ክስተ መሆኑን አያስቀርም። በግርግር መሃል ይህም ተከስቶ ይሆናል። መንጋው በመጠጥም በደምም ሰክሮ ብዙ ሊያደርግ ይችላል። ግን ከመንጋ ውስጥ ዘር መርጠው እየገደሉ እንደነበሩ ሃቅ መሆኑን መሰረዝ አይቻልም።

ቅጥረኞች ናቸው ያደረጉት ይባላል። እውነት ሊሆን ይችላል። ያስኬዳልም። ቢሆንም 1) ጥላቻ የሌለባቸው ፕሮፌሽናል ቅጥረኞች የዘር ማጥፋት ምልክቶች ያሉት ግድያ እና ጭቆና ማድረግ አይችሉም! 2) «ቄሮ ነን እያላችሁ ግደሉ» ተብለው የታዘዙ ቅጥረኞች ቢሆኑ ደግሞ ኦሮሞን አይገሉም ነበር። ይልቁንስ አማራን እና ኦሮሞን ለማጣላት የተቀነጀ ሴራ በመሆኑ ከጋሞ ይልቅ አማራ ላይ ነበር የሚያተክሩት።

ስለዚህ እነዚህ ቅጥረኞች ፕሮፌሽናል ሳይሆኑ የአካባቢው ሰው እና አንዳንድ ከውጭ የሜጡ መሪዎች ናቸው። የቅጥረኛ ሴራው በአካባቢው በነበረ የጎስ ቅሬታ እሳት እና በንዚን ማቀጣጠል ነው።

ለቡራዩ ክስተት የኦሮሞ ህዝብም ይሁን ቄሮም መፈረጅ እንደሌለበት ለማንም የሰው ልጅ ግልጽ እንደሆነ እናውቃለን። አንዳንድ ክፉ አሸባሪዎች ወይንም አላዋቂ ቀንደኞች በቀር እንደዚህ አይነት ነገር አያስቡም እንኳን መናገር።

ስለዚህ ለምንድነው የቡራዩ ክስተት የዘር ማጥፋት የሚባለው? ስለነበር ነው! እውነት ስለሆነ ነው! ልክ እንደ ከሶማሌ የተፈናቀሉት ኦሮሞዎች የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሰለቦችህ እንደነበሩት። በአዋሳ ዎላይታዎች ላይ እንደደረሰው እኩል። ጊኬኦ ላይ እንደደረሰው። አኗክ ላይ እንደደረሰው። አማራ ላይ በየቦታው እንደደረሰው። የ27 ዓመት የዘር ማጥፋት ክስተቶች ረዥም ዳታቤስ አለ። የቡራዩ ክስተት ትንሿ ናት። ልድገመው፤ ትንሿ ናት። በሶማሌ ግጭቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ነው ገቤታቸው የተባረሩት! (በነገራችን እኛ ኢትዮጵያዊነት ወዳጆች ጎፉንድሚ ለነዚህ አድርገናልን?)

ይህ የሚያሳየው የጎሳ ፌደራሊዝም የግጭት ምንጭ እንደሆነ ነው። ጎሳ በፖለቲካ ሲካተት ጸንፈኝነትን እና ግጭትን ነው የሚያመጣው። ይህ ሃቅ በዓለም ዙርያም ብኢትዮጵያም ይመሰከርለታል።

አልፎ ተርፎ ሁሉም አይነት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አናምንበትም ቢሉም አምነውበታል! ሁሉም ፖለቲከኞቻችን በርካታ ጊዜአቸውን የጎሳ ግጭት አሳሳቢ ነው አብሮ መኖር አለብን በመስበክ ይውላሉ! ከነ ኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች! የጎሳ ግጭት የሀገራችን ዋና ፖለቲካዊ ችግር መሆኑን ከዚ በላይ የሚገልጽ የለም!

ስለዚ የጎሳ ብሄርተኝነት እና የጎሳ ፌደራሊዝም መርዝ እንደመዋት መብት ቢሆንም ይገላል!

Friday, 21 September 2018

የተረሳው ጉዳያችን፤ የመሬት ፖሊሲ ሚና በጎሳ ፖለቲካ

ከዚህ በፊት ደጋግሜ ስለ የኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲ ችግር ጽፍያለሁ (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_47.html)። መሬት የግል ወይንም የአካባቢ ("local community" ለምሳሌ ወረዳ) ከመሆኑ ፋንታ የመንግስት መሆኑ ለህዝባችን እጅግ ጎጂ ፖሊሲ ነው ብዬ ነው የማምነው። ለዝርዝሩ ከላይ የጠቀስኩትን ጽሁፍ አንብቡ፤ ግን በአጭሩ መሬት የመንግስት መሆኑ የፈጠረው ችግሮች እንዲህ ናቸው፤

1. ገበሬው ለ«ጎበዝ ገበሬ» የሆነው ጎረቤቱ መሬቱን ሽጦ ወደ ከተማ መሄድ ባለመቻሉ ገጠር ቀርቶ በገጠር የመውለድ መጠን (birth rate፤ በገጠር አማካኙ ከስድስት ልጅ በላይ ነው) ልጅ ወለደ። ከተማ ቢሄድ ኖሮ ሁለት ልጅ (ሁለት አማካኙ ነው ለከተማ ነዋሪ) ይወልድ ነበር። ይህ ማለት የህዝብ ቁጥርን ባልተጠበቀና በኢተፈጥሮዊ (artificial) መንገድ ንሯል። ኢተፈጥራዊ ማለት ህዝቡ ወደ ከተማ እንዳይሄድ ነፃነቱ በመገደብ የጠፈጠረ ሁኔታ ስለሆነ ነው። ከግዳጅ የመጣ ክስተት ስለሆነ ነው።

2. የገጠር ህዝብ ቁጥር ንሮ የገበሬ መሬት አንሶ ልጆች የሚወርሱት አጥተው አሁን ታላቅ የገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት ተከስቷል። ለ40 ዓመት ቀስ በቀስ ፍልሰት ከመሆኑ ፋንታ የገጠሩ ሰው ለ40 ዓመታት ከገጠር ተጠራቅሞ አሁን ባንዴ ወደ ከተሞች እየመጣ ነው። ይህ ሁኔታ ከተሞቻችንን አስጨንቋል።

3. ገበሬዎች ቢጎብዙም ገንዘብ ቢኖራቸውም መሬት መግዛት ባለመቻላቸው የግብርና ስራውን ማስፋፋት አልቻለም። ማደግ አልተፈቀድለትም። በዚህ ምክንያት «የሰው አቅማቸው» (human capital) እንዳያድግ ተደርጓል። ለምሳሌ እንደ የግብርና የሙያ፤ የንግድ ሙያ፤ የአስተዳደር ችሎታ አይነቱን እንዳያዳብር ተደርጓል።

4. ገበሬው ሽጦ መሄድ ባላመቻሉ መሬቱን ለትውልድ እያከፋፈለ መሸንሸን ሆነበት። መሬቱ ተሸንሽኖ የያንዳንዱ ገበሬ መሬት አንሶ አንድ ቤተሰብም ማስተዳደር የማይችል ሆኗል። በዚህ ምክንያት ገበሬዎች ለድርቅ እና ርሃብ ተጋለጡ። የምግብ ዋስትና እጥረት እንዳለ ነው።

5. ጎበዝ ገበሬዎች መሬት ገዝተው መስፋፋት ባለመቻላቸው እና ደካማ ገበሬዎች ለጎበዞቹ መሸጥ ባለመቻላቸው የእርሻ ውጤት ዝቅተኛ ሆኖ ቈርቷል። ይህ ደግሞ የእህልና የምግባ ዋጋ ግሽበት አምጥቷል።

ከላይ የጠቀስኳቸው ባብዛኛው በኤኮኖሚ ዙርያ የሆኑ ነጥቦች ናቸው። ግን የመሬት ፖሊሲው ሌላ ታላቅ የፖለቲካ እና ማህበረሰባዊ ተጽዕኖ አለው።

ባጭሩ፤ የመሬት ፖሊሲው አንዱ የጎሳ አስተዳደሩ ምሶሶ ነው። መሬት የ«ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች» ነው ሲባል ለ27 ዓመት የተተረጎመው የአማራ ክልል መሬት የ«አማራ ብሄር» ነው፤ የኦሮሚያ ክልል መሬት የ«ኦሮሞ ህዝብ» ነው ወዘተ እየተባለ ነው። ትርጉሙም የህገ መንግስቱን ጽሁፍም መንፈስም የተከተለ ነው።

«መጤ» እና «ነባር» የሚሉት ጽንሰ ሃሳቦች በማህበረሰቡ በዚህ መሬት ፖሊሲ ይደገፋሉ። የ27 ዓመታት የመፈናቀል ዘመቻዎች የተካሄዱትም በዚህ ምክንያት ነው። ግን ህጉ የመሬት ባለቤትነት የግለሰብ ወይንም የቅርብ አካባቢ ሰዎች ቢያደርግ ኖሮ የ«መጤ» እና «ነባር» አስተሳሰብን ይቀንስ ነበር ነአ ቀስ በቀስ ያጠፋ ነበር። ለዚህ አስተሳሰብ የህግ ሽፋን እንዳይኖረው ያደርጋል። ተፈናቃዮች ለመብታቸው በፍርድ ቤት መታገል እንዲችሉ ያደርጋቸው ነበር።

ስለዚህ ዛሬ ያለውን ጎሰኝነትን ለመታገል እና ቀስ ብሎ ከጎሳ ፌደራሊዝም ወደ ህብረ ባህላዊ አገዛዝ ለመሄድ ይህን የመሬት ፖሊሲ መመልከትና መቀየር ጠቃሚ ይመስለኛል።

Wednesday, 19 September 2018

ታላቅ ጥላቻ ባይኖር የከቡራዩ እልቂት አይከሰትም ነበር

ስለቡራዩ የዘር ማጥፋት እልቂት ብዙ ይባላል። ጸንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች የቀሰቀሱት እና ያስተባበሩት ነው ይባላል። በተለያዩ የኦሮሞ ሚዲያዎች በተለይም ኦኤምኤን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የተቀሰቀሰው ነው ይባላል። ሁከት ለመፍጠር እና ኦሮሞ እና አማራን «ለማጣላት» የህወሓት ሰዎች ናቸው ያደረጉት ይባላል። ህወሓት ከያኮረፉት ኦህዴዶች እና ጸንፈኛ ብሄርተኞች አብሮ ያስተባበረው ነው ይባላል። አሁን ደግሞ አንዳንድ የህወሓት ጸንፈኞች እና የኦሮሞ ብሄርተኞች የጎሳ ብሄርተኝነትን የጥላ እሸት ለመቀባት ተብሎ ግንቦት ሰባት ያሴረው ክስተት ነው ይላሉ። ብዙ ይባላል መንግስት ቀስ ብሎ እውነታውን በይፋ እንደሚያወጣው ተስፋ አለኝ።

ይህ ሁሉ ሲባል አንድ እውነታን መካድ አይቻልም። ይህን የህዝብ ማጥፋት እልቂትን የፈጸሙት ሰዎች በዘር ጥላቻ የተሞሉ መሆናቸው ግልጽ ነው። ሰለቦችም መስካሪዎችም የመሰከሩት የዘር ማጥፋትን ነው። ገዳዮቹ ዘርን እየሰደቡ፤ ውነድ ልጅን ለመግደል እየፈላለጉ፤ ሴቶችን እየደፈሩ፤ ጥይት ወይንም ድብደባ ሳይሆን አጸያፊ የግድያ መንገዶች እየተጠቀሙ ወዘተ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ክስተት መሆን የሚቻለው በዘር ጥላቻ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ክስተቱ ሙሉ በሙሉ ግልጽ የሆነ የዘር ማጥፋት (ethnic cleansing) በሃሪ ነው ያለው።

ዝም ብሎ ቅጥረኛ ገዳይ ይህንን አይነት ድርጊት ማድረግ አይችልም። ቅጥረኛ ገዳይ በቀጥታ ነው ተግባሩን የሚፈጽመው። ግደል እና ዝረፍ ከሆነ ይገላል ይዘርፋል እንጂ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ያለው ክስተት ሊፈጽም አይችልም።

በተዘዋዋሪ በሌሎች በኢትዮጵያ ስፍራዎችም ያየናቸው የዘር ማጥፋት ዘመቻዮች እንዲሁ በዘር ጥላቻ ያላቸው ኃይሎች እንደተፈጸመ ግልጽ ነው። በጊዴኦ/ጉጂ፤ ኦሮሞ/ሶማሌ፤ አማራ/ቤኒሻንጉል የተከሰቱት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ምክልቶች (pattern) አላቸው። ምንም የፖለቲካ እና የገንዘብ ኃይል ከበስተጀርባቸው ቢኖርም አለዘር ጥላቻ መፈጸም የማይችሉ ተግባሮች ናቸው።

ስለዚህ ዋናው ችግር የዘር ጥላቻው ነው! እና የዘር ጥላቻን የሚያራግቡ ናቸው! ገንዘቡ፤ ሴራው፤ ወዘተ ባለው የዘር ጥላቻ ላይ ነው ስራውን የሚሰራው። ችግሩን ለመፍታት ሴራውን የሚሰሩት እና የሚያቀናበሩትን ማስቆም ያስፈልጋል። ግን ይህ መሰረታዊ ችግሩን አይፈታም። በዋናነት የዘር ጥላቻን የሚያራግቡትን ማስቆም ያስፈልጋል። ቀጥሎ በህዝብ መካከል ያለውን ጥላቻ ማጥፋት ያስፈልጋል።

እንዴት ነው በህዝቡ መካከል ያለው የዘር ጥላቻን ማጥፋት የሚቻለው። መንግስት ትህምህርት ቤትን፤ ሚዲያን እና ሌሎች ተመሳሳይ መዎቅሮችን በተገቢ ሁኔታ መቆጣጠር አለበት። የ27 ዓመታት የዘር ጥላቻ ፕሮፓጋንዳን ለመመለስ ሙሉ ዘመቻ ማድረግ አለበት። ጉዳዩ አስርት ዓመታት ይፈጃል ግን አማራጭ የለም። ሌላው የዚህ ዘመቻ ዋና ተግባር ደግሞ ህዝብ እንዲ ቀላቀል ማድረግ ነው። የእርስ በርስ ቋንቋ እንዲማር እና እንዲጋባ እና እንዲዋህድ ማድረግ ነው። ዘላቂው መፍትሄ ይህ ነው።

Tuesday, 18 September 2018

ኦኤምኤንን ከመክሰስ ሌላ ሚዲያ አቋቁመን እንብለጠው

በርካታ ጽሁፎቼ ስ«ለሃላፊነት» መውሰድ ነው። የሰው ልጅ ችግሮች ሲያጋጥሙን ሌሎችን ከመውቀስ እኛ ምን ብናደርግ ነው፤ ምን ብንሳሳት ነው፤ ምን ቀድሞ ዝግጅት ባናደርግ ነው ብለን እራሳችንን መጠየቅ አለብን። በዚህ አካሄድ ብቻ ነው ችግሮቻችንን መፍታት የምንችለው።

ሌሎችን መውቀሱ ዋጋ የለውም። ለምን ብትሉ ችግርን የሚፈጥሩ ሰዎች አውቀው የሚያደርጉት ከሆነ የኛ እነሱን መውቀስ በሃሪና ተግባራቸውን አይቀየርም። ይቀየራሉ ብለን ስንጠብቅ ችግሮቻችንን እያባባሱ ይቀጥላሉ! እኛ እየተጠቃን እንቀጥላለን። በራሳችን ያለን መተማመን እየቀነሰ ይሄዳል። የሰለባ አስተሳሰብ (victim mentality) እና የዝቅተኝነት መንፈስ (inferiority complex) እያደረግን እየጠነከረብን እንሄዳለን። አሉንታዊ እና ብሶታዊ ሰዎች እንሆናለን።

ግን ችግር ሲያጋጥመን ሃላፊነት ወስደን ምን ብናደርግ ባናደርግ ነው ይህ ችግር ያጋጠመን ካልን እራሳችንን የችግሩ መፍትሄ እናደርጋለን። እራሳችንን እናጎለብታለን (empower)። ችግሩን ሰፋ አድርገን እናያለን። ኃይል እንዳለን ይገባናል እና በራሳችን እንድንተማመን (confidence) ያደርገናል። አዎንታዊ እርምጃዎች ወስደን ከችግራችን እራሳችንን እናወጣለን። ደግሞ ችግር እንዳይገጥመን ደግሞ እራሳችንን እናጠነክራለን። ለደህንነታችን ሌሎችን መለመን እንደማያስፈልገን ይገባናል ስለዚህም በማንነታችን በተገቢው እንኮራለን።

በቅርቡ በቡራዩ እና ዙርያ በተከሰተው የጎሳ ማጥፋት (ethnic cleansing) ክስተት በርካቶች ኦኤምኤን ተለቪዥን ጣብያን እንደ አንድ ጥፋተኛ ከሰዋል። ኦኤሜን ላይ የሚቀርቡ ተንታኞች የዘር ማጥፋት ቅስቀሳ ስለሚያደርጉ ነው አንዱ ምክንያት እንደዚህ አይነት ክስተት የሚከሰተው ይባላል። ኦኤምኤን ነው ችግራችን እና ይዘጋ ወይንም እስከሚስተካከል ይታገድ ይባላል።

ጥሩ ነው። አጥፊ አጥፊ ነው ተብሎ መንግስትን ህግን አስከብሩ ማለትም የዘር ማጥፋት ቅስቀሳን አቁሙ ማለት ተገቢ ነው። ግን በዚ ላይ ብቻ ማተኮር እራስን አቅመ-ቢስ ማድረግ ነአ ማዋረድ ነው። አንዴ መንግስት ተነግሯል፤ መንግስት ያውቃል፤ ይበቃል። ኦኤምኤንን ደጋግሞ መክሰስ ኦኤምኤንን ማጎልበት ነው። በኛ ላይ ብዙ ኃይል አለህ እና ጫና መፍጠር ትችላለህ ማለት ነው። እኛ የአንተ ሰለቦች ነን ብሎ ማለት ነው። ይህ አካሄድ ኦኤምኤንን ያጎለብታል እኛን ደግሞ አቅመ-ቢስ ያደርጋል። የሰለባ እና የዝቅተኝነት ስሜት እንዲአድርብን ያደርጋል። በዋናነቱ ደግሞ ችግሩ እንዲቀጥል እንዲባባስ ያደርጋል።

መሆን ያለበት አንዴ መልዕክታችንን ለመንግስት ካስተላለፍን በኋላ እና ለህዝቡ የኦኤምኤንን ጥፋት ካገለጽን በኋላ ወደ ራሳችን ስራ መግባት ነው። 10% ጊዜአችን ስለ ኦኤምኤን እውነቱን መናገር ካጠፋን 90% ጊዜአችንን እራሳችን በራሳችን መፍትሄ በማግኝነት ነው ማድረግ ያለብን።

በዚህ በሚዲያ የዘር ማጥፋት ጉዳይ ምንድነው እኛ ማድረግ የምንችለው? ብዙ ነገሮች አሉ ግን አንዱ ቀላሉ ጠንካራ የኦሮምኛ ሚዲያ ማቋቋም ነው። ይህን ነው ኢሳት ረዥም ዓመታት በፊት የመከረው ግን ይህ ሙከራ አቅሙ እጅግ ደካማ ነው። ስለዚህ ያልንን አቅም (resources) ሰብስበን ኦኤምኤንን የሚበልጥ ሚዲያ በማቋቋም መስራት አለብን። ይህን ካደረግን እና ከተሳካ ግማሹ ችግር ይጠፋል። ስለ ኦኤምኤን ማልቀስ ይቀራል። ይህ አካሄድ አሉታዊ ከመሆን አዉንታዊ ያደርገናል።

ሁሉ ጉዳዮቻችንን በዚህ መልኩ ብናያቸው ጥሩ ይመስለኛል። ጣት ከመጠቆም እራስን ማየት እና እራስን አጎልብቶ መፍትሄ በራስ ባግኘት። እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ቢኖረን ኖሮ ስንት ያለፍንባቸው ችግሮች አይኖሩም ነበር። በጥቂት ድጋፍ ያለው ህወሓትም አንገዛም ነበር! ስለዚህ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ እናተኩር፤ ከህጻንነት ወደ ሃላፊነት የምንወስድ አዋቂዎች እንቀየር።