Friday, 30 September 2016

ጥፋት አለብኝ ብዬ ካላመንኩኝ «ወያኔ» ነኝ!

2009/1/19 ዓ.ም. (2016/9/29)

ከዲያስፖራ እየኖርኩኝ ስጋዊ ምቾቴን አጠናቅቄ ህሊናዬ እየወቀሰኝ ሀገር ቤት ያሉትን ወንድሞች እህቶቼን ታገሉ እላለሁ። ሀግሬን እወዳለሁ እላለውንጂ ያሳደገችኝ ብትሆንም ለሷ ያለኝን ሃላፊነት ከተውኩኝ ቆይቻለሁ። ክጃታለሁ ጥያታለሁም። ሆኖም ግን ሀገሬን መበደሌ አይታየኝም። ስለሌሎችን ኅጢአትና በደል እጮሀለው እንጂ። ከአይኔ ያለውን ግንድ አላየውም የሌላውን ጉድፍ ብቻ ነው የሚታዬኝ።

ምሬቴ ትንሽ በመሆኗ ምክንያት አጥሬን መግፋት መብቴ ነው እላለሁ! ገፈዋለሁ፤ ከጎረቤት ጋርም እጣላለሁ፤ መንገድንም አጠባለሁ። ለሰፈሩ ችግር እያመጣሁኝ ነው። ግን የእለት ወሬዬ ስለ ቀበሌአችን ሹማምንት የምስና ባህሪ ነው። አይኔ ውስጥ ግንድ የለም።

እውነት ነው፤ ሲያስፈልግ ጉቦ ሰጣለሁ። መብቴን ለማስከበር ብቻ ሳይሆን የማይገባኝን ለማግኘትም። ምን ይደረግ፤ የሀገራችን እውነታ ነው ብዬ እራሴን አታልላለው። ግን መሪዎቻችን እንዴት ሞራል ቢስ ናቸው ብዬ አማርራለሁ።

አንዱ የኦርቶኦክስ መሰረታዊ እምነት ሁላችንም ለሁሉም ሰው ኅጢአት በተወሰነ ደረጃ አስተዋጾ እድርገናልና ሃላፊነት አለብን የሚል ነው። ኅጢአቶቻችን የተገናኙም የተወራረሱም ናቸው። ይህንን ለማብራራት ያህል የታወቀው ሩሲያዊ ደራሲ ፊኦዶር ዶስቶኤቭስኪ በ«ካራማዞቭ ወንድማማቾች» የጻፈውን ጥቅስ እንመልከት። ታላቁ የሃይማኖት አባት ዞሲማ ልጆቻቸውን ሲመክሩ እንደዚህ አሉ፤
«አንድ ሰው በዚህ ዓለም ከሚኖሩት በሙሉ የባሰ ኅጢአተኛ እንደሆነ ሲያምን፤ በተጨማሪም ከሁሉም ሕዝብ ፊት ጥፋተኛ እንደሆነ...፤ ለዓለምም ለያንዳንዱ ሰውንም ኅጢአት እና ጥፋት እንዳለበት ስያምን ነው የ(ክርስቲያናዊ) አንድነት ድላችንን ማስመዝገብ የምንችለው..።
«ሁላችሁም ልባችሁን በደምብ አዳምጡና ለራሳችሁ ሳትሰለቹ ንስሐ ግቡ። እስከ ተጸጸታችሁ ድረስ ኅጢአታችሁ የጎላ ቢመስላችሁም አትፍሩት...።
«በጸሎታችሁ እንደዚህ አስታውሷቸው፤ «አምላካችን ሆይ የሚጸልይላቸው የሌሏቸውንም ላንተ መጸለይ የማይፈልጉትንም አድናቸው» ብላችሁ ጸልዩ። እንደዚህም ቀጥሉ «አምላኬ ሆይ እኔ ከሁሉም የባሰ ርኩስ ነኛ፤...»»
በተጨማሪ ባለፈው ጽሁፌ የጠቀስኩት በጾቪዬት እስር ቤት የተሰቃዩት አለክሻንደር ሶልዠኒትሲን ከእስር ቤት ሆነው የጻፉትን እንደገና ልጥቀስ፤

ከእስርቤታችን አልጋ የሆነው የበሰበሰው ገለባ ላይ ጋደም ብዬ ነው ለመጀመርያ ከውስጤ የበጎ መንፈስ የተሰማኝ። ቀስ በቀስ መረዳት የጀመርኩት ይህ ነው፤ ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር በሀገሮች፤ መደቦች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መካከል አይደለም የሚያልፈው፤ ይህ መስመር የሚያልፈው በያንዳንዱ የሰው ልብ መኻል ነው። መስመሩ እድሜአችን በሙሉ ከውስጣችን ወደፊት ወደኋላ ይላል። በክፉ የተሞሉ ልቦችም ቢያንስ ቅንጣት ያህል ጥሩነት ይኖራል፤ ከሁሉም ጥሩ ከሚባለውም ልብ ከአንድ ጥጓ ትንሽ ክፉነት ይኖራል።
«በየቦታው እየዞሩ ያሉ ክፉ ስራ የሚሰሩ ክፉ ሰዎች ቢኖሩና እነሱን ከኛ መለየትና ማጥፋት ብቻ ቢሆን ኖሮ እንዴት ቀላል ነበር? ግን ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር ከያንዳንዱ የሰው ልጅ ልብ መካከል ነው የሚያልፈውና ማን አለ ከራሱ ልብ ቁራጭ ቆርጦ ለማጥፋት ፈቃደኛ ይሆነ?»
ሶልዠኒትሲን በመታሰራቸው፤ በእስር ቤት ለደረሰባቸው በደልና ስቃይ፤ ያሰሯቸውን የዘመኑን መንግስት መሪዎች፤ የፍርድ ቤት ዳኞች፤ የደህንነት አዛዦች፤ ወዘተ ብቸኛ ጥፋተኛ አድርገው ሊቆትሩ ይችሉ ነበር። ማንናችንም ደካሞች በሳቸው ቦታ ብንሆን እንደዛ ነበር የምናስበው።

ግን እየተሰቃዩም ቢሆን ይህን ቀላሉ የውሸት መንገድን ከመከተል እውነትን መረጡ። እውነትን ፈለገው ህሊናቸውን ተጠንቅቀው መርምረው የራሳቸውም ግድፈት እንዳለ ተገነዘቡ። ከነዛ ክፉዎች እንደማይሻሉ አመኑ።

ሶልዠኒትሲን በሁለተኛ ዓለም ጦርነት ጀግና ወትደር ነበሩ። ሀገሬን እንደዚህ አገልግዬ እንዴት በማግስቱ ለማይረባ ምክንያት እታሰራለሁ ነበር በመጀመርያ ያሰቡት። ግን ህሊናቸውን ሲመረምሩ ከጦር ሜዳ የሰሩትንና ሲሰራ አይተው ዝም ያሉትን ግፍ አስታወሱ። ሀገርን በመከላከል አሳበው ህሊናቸውን እንዴት እንደሸጡ አስተዋሉ። አብረዋቸው የታሰሩትንን የመንግስት ሰለቦች ሲመለከቱም ምንም ንጹ የሚመስሉትም በተወሰነ ደረጋ ተመሳሳይ የህሊና ሽያጭ እንዳካሄዱ ተገነዘቡ።

ከዝ ቀጥሎ የበደሏቸውን ሲመለከቱ በፊት የነበራቸው እነሱ ክፉ እኔ ንጹ የሚለው አስተሳሰባቸው ውሸት እንደሆነ ገባቸው። በዳዮቻቸውም እንደራሳቸው በተለላየ አታላይና የማይረባ ምክንያት ህሊናቸውን ሽተዋል። ስንቱ ናቸው በስመ ሀገር ወዳድነት እንደ ሶልዠኒትሲን አይነቱን የሀገር ከሃዲ ብለው ያሳሰሩት። እነዚህ «እውነት አማኞች» ርዕዮት ዓለማቸውን እንደ ሃይማኖት አድረገው የሚያምኑበት ስለሱ ምንም ለማድረግ ወደኋላ አይሉም ነበር። ሶልዠኒትሲን እነሱን ሲያዩ እራሳቸውን አዩ።

የመጨረሻ ግንዛቤአቸው ንስሃ መግባት እንዳለባቸው ነበር። ንስሃ ቢገቡ በራሳቸው ብቻ ሳይሆን በባልደረቦቻቸው በሙሉ የደረሰው እንደማይደርስ ገባቸው። በሶቪዬት ህብረት የሚገኙት ሀገራት በሙሉም ሰላምና እውነታዊ መንግስት ሊያገኙ የሚችሉት በዚህ አይነት መንገድ ብቻ እንደሆነ ተገነዘቡ። ሌሎቻችንም እንደዚህ አድርገን እንድናስብ ጋበዙን።

እሺ፤ የምጨረሻ ጥቅስ ከአባ ዶሮቴዎስ፤
«አንድ ሰው በእግዚአብሔርን ፊት እራሱን በደምብ ቢመረመረ ለሚደርስበት ያለው በደል ባተግባር፤ በሃሳብ፤ በንግግር፤ በፀባይ፤ ወይም በባህሪይ ሃላፊነት እንዳለበትና ከፊል ተጠቅያቂ እንደሆነ ይገለጽለታል።»
እንዲሁም ለኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ፤ የፖለቲካ ችግር ተጨምሮ፤ ሁላችንም ኢትዮጵያኖች አስተዋጾ አድርገናል ሃላፊነትም አለብን ብለን ማመን አለብን። ቀጥሎ ይህን ሃላፊነት ብንወታው ችግሩ ይፈታል ብለን ማመን አለብን። አባ ዶሮቴዎስ እንዳሉት እራሳችንን ተጠንቅቀን በኢግዚአብሔር ፊት እንመርምር። ይህ ወደ ሰላምና እውነት ብጨኛው መንገድ ነው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!