Showing posts with label discussion. Show all posts
Showing posts with label discussion. Show all posts

Thursday, 14 March 2019

ገንቢ ውይይት ከስዩም ተሾመ እና መንግስቱ አሰፋ

ይህን ገንቢ ውይይትን ተመልከቱ። ስዩም ተሾመ እና መንግስቱ አሰፋ ይህን ውይይታቸውን ዘውትር ቢያደርጉት ጥሩ ይመስለኛል። በተለይ የተለያዩ የህገ መንግስት ቅያሬዎችን ቢያሰላስሉ ጥሩ ይመስለኛል። ወደ እንደዛ አይነት ተግባራዊ ውይይት ሲገባ ደግሞ የተለያዩ እውነታዎች እና አስተያየቶች ይወጣሉና።

Monday, 14 January 2019

ስለ ራያ ማንነት ውይይት፤ ዳር ዳሩን ከማለት ወደ ቁምነገሩ ካልገባን ችግሮችን አንፈታም


ይህን ስለ ራያ ማንነት ጉዳይ ቃለ ምልልስ ስመለከት ጠያቂውም እንግዶቹም ስለ ህግ አፈጻጸም እና ሂደታዊ (procedural) ጉዳዮች ከዓንድ ሰዓት በላይ ተወያይተው ዋናው መሰረታዊ የሆነው ጉዳይ ላይ ምናልባት 10 ደኪካ ነው ያዋሉት። «በግልጽ እንነጋገር ከተባለ…» ማለቱ ለምን ያስፈልጋል፤ መጀመሪያኑ በግልጽ ስለ መሰረታዊ ጉዳዩ መነጋገር ነው።

በግጭት መፍታት (conflict resolution) መሰረታዊ ችግር እንዳለ መገንዘብ፤ ከዛ ችግሩን ማወቅ፤ ከዛ ችግሩን ለመፍታት መስራት አብዛኛው ጊዜ የግድ የሆነ አስፈላጊ ሂደት ነው። አለበለዛ የችግሮቹ ውጤቶች ላይ እየተተኮረ እሳት እየተለኮሳ እሳት እያጠፋን እንቀጥላለን። መሰረታዊ ችግሩ እየተባባሰ ይሄዳል። እርግጥ የግጭቱ አካሎች ስለ መሰረታዊ ጉዳዩ ማውራት ማሰብም አይወዱ ይሆናል ግን አማራጭ የለም። ክስ ብሎ አለስልሶ ወደዛ መግባት ግድ ነውና።

የራያ መሰረታዊ ጉዳይ የራያ ማንንነት ኮሚቴ(ዎች) መቼ አመለከቱ ለማን አመለከቱ አይደለም። ይህ ሁለተኛ ጉዳይ ነው እና ብዙ የውይይት ጊዜ ሊፈጅ አይገባም። መሰረታዊ ችግር እና ጥያቄው እንደገባኝ ከሆነ እንዲህ ነው፤

1) እኛ ከትግሬ የተለየ የራያ ማንነት አለን እና አለፍላጎታችን በትግሬ ክልል ተካለልን፤
2) ሰባዊ መብታችን በትግራይ ክልላዊ መንግስት ለ27 ዓመት ትጥሷል እና ተጭቁነናል፤
3) መጀመሪያውኑ የጎሳ አስተዳደር ባይሆን ኖሮ ይህ የማንነት ጉዳያችን በዚህ መልኩ አይነሳም ኖሮ፤
4) አማራ ክልል ብንገባ መብታችን እና ሰላማችን ይከበራል እና የአምባገናን ትግራይ ክልልውስጥ መሆን አንፈልግም።

በርካታው የውይይቱ ጊዜ በነዚህ ጥያቄዎች ዙርያ መሆን ነበረበት ብዬ አስባለው። በዛሬው የፖለቲካ ሁኔታ ጥያቄዎቹ እጅግ ከባድ ናቸው እና ብዙ ውይይት ያስፈልጋቸዋል። ይህን ትቶ ስለ ደብዳቤ እና ግልባጭ ማውራት ትንሽ priority ማጣት ይመስለኛል።

Monday, 17 December 2018

ስለ ህገ መንግስት አንድ የውይይት ሃሳብ

አሁን ያለን የጎሳል አስተዳደር (ethnic federalism) የግጭት መንስኤ እንደሆነ የ27 ዓመት መረጃ አለን ብዬ ተከራክርያለሁ ከጽሁፎቼ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_89.html)። በህወሓት አገዛዝ የነበሩት የጎሳ እና የድንበር ግጭቶች ህወሓት ብቻውን ያካሄደው፤ የቀሰቀሰው፤ ያስተባበረው ብቻ አልነበሩም። ህወሓት በአስተዳደሩ ምክንያት ያሚመጡትን ችግሮች ለራሱ ጥቅም ያባብስ ነበር እና ያሉ ቅራኔዎችን ያባብስ ነበር እንጂ ችግሮችን ከሀ መፍጠር አቅም አልነበረውም። ዛሬም ለምሳሌ የሲዳማ እና ወላይታ ግጭት ስንመለከት አዎን የህወሓት እና ሌሎች ነበሮች እጅ ቢኖርበትም የጎሳ አገዛዙ መሰረታዊ መንስኤ ነው። በዚህ ምክንያት ዛሬ ያለው የጎሳ አስተዳደር ለሀገራችን ሰላም አይሆንም።

አማራጩ ምንድነው የሚለው ጥያቄ ላይ ጊዜ ብናጠፋ ጥሩ የመስለኛል። በዚህ ጉዳይ የተለያየ አቋም ያለን ኢትዮጵያዊያን ስለዚህ ገና ብዙ መነጋገር አለብን እስካሁን በቂ የተነጋገርን አይመስለኝም። ስንወያይም አብዛኛው ጊዜ የራሳችን አቋም ላይ ነው የምናተኩረው እንጂ በቂ ሌላውን አንረዳም።

ዛሬ አንድ አስተያየት ልስጥ… የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎች ኢትዮጵያ የብሄሮች ስብስብ ነው መሆን ያለበት ነው። የመጀመርያ ማንነታችን ጎሳችን ነው፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነታችን ሁለተኛ ነው ነው የሚሉት። የሀገር ስሜት አለን ነው። ኦሮሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለች ሀገር ናት። ባለቤቷም የኦሮሞ ህዝብ ነው። ግን በታሪክ ምክንያቶች እና ዛሬ ባለው ነባራዊ ሁኔታ አብሮ መኖር ስላለብን ተገንጥለን አንኖርም ብሄሮች እርስ በርስ ውል ይኖራቸዋል ነው። እንደ ብሄር ክልል ወይንም «ትንሽ ሀገር» ከሌለን የሀገራዊ መብታችን ተወሰደ ማለት ነው። ልክ እንደ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ሰው ከኬንያ ጋር በግድ ሙሉለሙሉ ተቀላቅለህ አንድ ሀገር ሁን ቢባል አይ አገርነቴን መጠበቅ እወዳለሁ እንደሚል አማራውም የብሄር ክልል ይቀር ቢባል ማንነቱ እንደተወሰደበት ይሰማዋል ነው። በአጭሩ ይህ አንዱ የጎሳ አስተዳደር ደጋፊዎች አስተሳሰብ ይመስለኛል።

እስቲ ለዚህ አንድ የሚሆን አማራጭ መልስ እንስጥ። ከህገ መንግስቱ «ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች» የሚለውን በሙሉ አውጥተን ግለሰባዊ ብቻ እናድርገው። ግን አሁን ያሉትን ክልሎች እንጠብቅ። ለክልሎች አሁን ካሉት ተጨማሪ መብቶች እንስጥ። ከዛ የኦሮሚያ «ሀገራዊ» ምስልን እንመልከት። በቋንቋ፤ ባህል፤ ማንነት፤ ወዘተ በኦሮሚያ አብዛኛው ኦሮሞ ስለሆነ የሚኖረው ፍላጎቱ እንዲሰፍን ያደርጋል። ይህ የድምጽ ብልጫ ኦሮሚያ ክልልን ከሞላ ጎደል ኦሮሚያ ሀገር ሊያደርገው ይችላል። ግን ሀገር አይባልም እና ኦሮሞ ዘር ያልሆኑ ከኦሮሞዎች እኩል መብት ይኖራቸዋል። ግን አናሳ በመሆናቸው ብዙ ተጽዕኖ አይኖራቸውም።

ለኔ ይህ አካሄድ የጎሳ አስተዳደርን መጥፎ ጎን ያስወግዳል ማለትም ሁሉ ጉዳያችን በጎሳ የተመሰረተ እንዳይሆን ያደርጋል። አንደኛ/ሁለተኛ/ሶስተኛ ዜጋ፤ መፈናቀል፤ የጎሳ ብቻ ፖለቲካ ወዘተ እንዳይኖር ያደርጋል። ግን የጎሳ ወይንም ብሄር መብት ያስከብራል። በዚህ በጎሳ መብት ማስከበር ከጎሳ አስተዳደር ብዙ ልዩነት አይኖረውም።

ይህ አንድ የመሃይም ለውይይት የቀረበ ፕሮፖዛል ነው። የጎሳ ብሄርተኞችን ፍላጎት ያሟላ ይሆን። የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ፍላጎትስ?

Tuesday, 23 October 2018

ብስለት የሞላው ውይይት

ይህንን ውይይት ጠንቅቃችሁ አዳምጡት ብዬ እለምናለሁ።

https://www.youtube.com/watch?v=PY9RFsmu_ks

የተነሱት ዋና ዋና ነጥቦች፤

1.ዛሬ ያለንበት ፓለቲካዊ እና ማህበረሰባዊ ሁኔታ እና ችግሮች 27 ወይን 44 ወይን 50 ዓመት የፈጠረው አይደለም። ከዛ በፊት ያለን የረዥም ዓመታት ታሪክም አስተዋጾ ያለው ነው። ይህን አውቀን ነው ወደ እውነት እና ትክክለኛ መፍትሄ ምድረስ የሚቻለው።

2. ራስን መመርመር ግድ ነው። ችግሮቻችን በመንግስት እና በፖለቲከኞች ምክንያት ነው የመጣው ማለት ልክ አይደለም። እውነት አይደለም። ሁሉም ዜጋ በራሱ በኩል ሚና ተጫውቷል እና ላለፈውም ለወደፊቱም ሃላፊነት መውሰድ አለበት።

3. ፖለቲካ አንድ የማህበረሰባዊ ኑሮ ክፍል ነው። በመሆኑ ሁሉ ዜጋ በአቅሙ እና በአግባቡ መሳተፍ አለበት። እናት እንደ እናት፤ አባት እንደ አባት፤ ልጅ እንደ ልጅ፤ ሃይማኖት መሪ እንደ ሃይማኖት መሪ፤ ምሁር እንደ ምሁር፤ ሰራተኛ እንደ ሰራተኛ ወዘተ።

4. የግብረ ገብ እጦት ታላቅ ችግር ነው እና ሊሰራበት ይገባል። እንደማንኛውም ችግር ይህ ችግር የሚፈታው መጀመርያ አመጣጡ፤ ምክንያቱ እና ምንጩ ሲታወቁ እና ሲታመኑ ነው።

5. ለውጥ ማለትም ወደ የተሻለ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ሁኔታ መቀየር ጊዜ ይፈጃል። ትዕግስት ይጠይቃል። ምርጫ እና ተመሳሳይ ስርዓቶች አለ ቅድመ ዝግጅት እና የአስተሳሰብ ለውጥ ጎጂ ነው የሚሆኑት።

6. ዛሬ ከሞላ ጎደል የፖለቲካ «ነፃነት» አለ። ቋሱ በኛ በህዝቦቹ ሜዳ ነው ያለው። ችግር ካለ መፍታት የኛ ሃላፊነት ነው። ሃላፊነታችንን እንደ ዜጎች መቀበል ግድ ነው። በሌላ ለምሳሌ በመንግስት ባሳበብ አብቅቷል።

Saturday, 15 September 2018

ህዝብ ፉት የፒለቲካ ውይይቶች ዛሬውኑ ይጀመሩ

ማሳሰብያ፤ ኢቢሲ በአስቸቋይ ተከታታይ የፖለቲካ ውይይቶችን አሁኑኑ ማዘጋጀት መጀመር አለበት።

1. «ፖለቲከኞቻችን» እራሳቸውን ህዝብ ፉት ማጋለጥ አለባችው። ዙርያ ጥምጥም ቀርቶ ማንነታቸውን ማየት አለብን።

2. አቋሞቻቸውንም ከመደበቅ ይልቅ ማስፈትሽ አለባቸው።

3. ፖለቲከኞቻችን ከዝግ በር ኋላ ለማሰብ 27 ዓመት ተሰጥተዋል። ያጡት ይሄን ሳይሆን የህዝቡን ሃሳብ እና ዝንባሌን ማወቅ ስለሆነ አሁኑኑ ህዝብ ፉት ይቅረቡ።

4. መጀመርያ ፕሪግራም እንቅረጽ ማለት ተገቡ አይደለም። ይህ ሂደት ፕሪግራም እንዱቀርጹ ይረዳቸዋል ያስፈልጋቸዋልና።

5. ህዝቡ ውይይትን ይልመድ። እንደ ቅንጅት ጊዜ የአንድ ወር ውይይት ሳይሆን የዓመት ዓመታት ነው የሚያስፈልገን።

6. ፖለቱከኞቻችን በሆዳቸው ውስጥ የደበቁት በተለይ ጸንፈኛ ሃሳቦች ይታዩ። ስለ ምኒልክ ሃኡልት፤ ባንዲራ፤ የጊሳ አስተዳደር፤ ጎሰኝነት፤ ጨቋኝ ተጨቋ፤ እንዴት አብረው እንደሙሰሩ ወይንም እንደሙፋጁ ይጠየቁ። ይጋለጡ ይታወቁ።

7. የሚከሰሱት እራሳቸውን ከማስረዳት እድሉ ይሰጣቸው ሳይሰሹ ይጠቀሙበት።

8. ጎሳዬን ወክዬ እደራደራለሁ የሚለውን እስቱ የመደራደር አቅሙን እንይ። ወይንም የመጋጨት አቅሙን።

9. ፖለቲከኞቻችን በዚህ መልኩ ለረዥም ጊዙእ ሳይፈተሹ ምርጫ ከተጠራ ታላቅ አደጋ ይጠብቀናል።

Monday, 20 August 2018

ከሰው ማንነት ጋር መከራከር ያስቸግራል

ድሮ ከኤርትራዊያን፤ ትግራይ፤ ኦሮሞ ብሄርተኞች ጋር ስንከራከር እንዲህ አይነቱ ነጥቦችን እናነሳ ነበር፤

  • ሁላችንም ኢትዮጵያዊ ነን ማንም ከማንም በላይ አልተጠቀመም አልተጨቆነም
  • መንግስት በጎሳ ወይም ብሄር አድሎ አድርጎ አያውቅም
  • ከሁሉም ጎሳ የፖለቲካ መሪዎች አሉ ታላላቅ መሪዎቻችን ብዙ የተለያየ የጎሳ ደም አላቸው
  • የሁላችንም ጥቅም አብሮ ከመሆን የተያያዘ ነው
  • ጎሰኝነት የጋራችንንም የያንዳንድ ጎሳችንንም ጥቅም ይጎዳል ግጭት እንዲሰፍን ያደርጋል
    ወዘተ

እነዚህን አይነት ፍሬአማ ነጥቦች ላይ ከተወያየን ብኋላ ሁልጊዜ መጨረሻ ላይ ወደ አንድ ነጥብ እንመለሳለን። ኤርትራዊያኖች «እኛ ኤርትራዊያን ነን ኢትዮጵያዊ አይደለንም» ትግራዮውቹ «እኛ መጀመርያ ትግራይ ነን» ኦሮሞ ብሄርተኞች «እኛ ኦሮሞ ነን ኢትዮጵያዊ አይደለንም» ብለው ውይይታችንን ያቆማሉ። የአባባላቸው ትርጉም ግልጽ ነበር፤ ማንነታችን ይህ ነው እና ስለ ማንነታችን ምንም ማለት አይቻልም ነው። ጉዳዩ ሌላ አይደለም፤ ጥቅም እና ጉዳትም አይደለም፤ «ማንነት» ነው።

እንዲሁም አሁን ከአማራ ብሄርተኝነት ደጋፊዎች ይህንን ነው የማየው። ባለፉት 45 ዓመት የፖለቲካ ችግሮቻች (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_15.html) ምክንያት የተወሰነው የአማራ ህብረተሰብ ውስጥ አዲስ የአማራ ማንነት (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_17.html) ተፈጥሯል። ይህ ማንነት የአማራ ብሄርተኝነት ንቅናቄ መሪ @  የጻፉት በደምብ የሚገልጸው ይመስለኛል፤

«አማራ ነኝ ፣ አማራ ነን ፤ እንደአማራነት የተሰነዘረብኝን ጥቃት በአማራነት ተደራጅቼ እመክታለሁ ፤ በዚህም ህልዉናዬን፣ ፍላጎቶቸንና ዘላቂ ጥቅሞችን አስከብራለሁ»
(https://www.facebook.com/photo.php?fbid=1934811083224914&set=a.308423195863719&type=3)

ጉዳዩ የማንነት ስለሆነ ምንም አይነት «ሎጂካል» ሙግት ማንነትን እንደሚያጣጥል ሊቆተር ይችላል። ውይይት ቶሎ ወደ ቅራኔ ይወሰዳል። ለምሳሌ እንደ እኔ አይነቱ በኢትዮጵያዊነት መደራጀትን የሚያምን «የአማራ ጥቅምን የሚያሟላው በኢትዮጵያዊነት መደራጀት ነው» ብል ለአማራ ብሄርተኛው ማንነቱን የተቸትኩኝ ይመስለዋል እና መልሱ ከጉዳዩ ጋር ሳይሆን ከማንነቱን መከላከል ጋር የተያያዘ ይሆናል። «ይህን ሁሉ ጥቃት ደርሶብን እንዴት በአማራነት አትደራጁ ትላለህ» ይባላል። «ድሮስ እናንተ በኛ ትነግዱ ትጫወቱ ነበር አህን ያበቃል» ይባላል። «ሌሎች የጎሳ ብሄርተኞችን ለምን አትተቹም?» ይባላል። ወዘተ።

የነ ጃንሆይ፤ ደርግ፤ ኢህአፓ፤ መኢሶን፤ መላው አማራ/ኢትዮጵያ፤ ቅንጅት፤ ግንቦት ሰባት ወዘተ ኃጢአቶች በሙሉ በ«አንድነት ድርጅቶች» እና በ«ኢትዮጵያዊነት» ርዕዮተ ዓለም ላይ ይለጠፋሉ! ይህ ሁሉ የማይሆኑ («ኢሎጊካል») መልሶች የሚሰነዘሩት ጉዳዩ በዋናነት የማንነት ስለሆነ ነው።

አንዴ በበሶት እና «ጭቁንነት» የተመሰረተ ማንነት ስር ከሰደደ በሎጂክ የተመሰረተ ሙግት ምንም መቀየር አይቻልም። ወይ ከነሱ ጋር ነህ ወይንም ጠላት ነህ።

እዚህ ላይ አንድ መናገር የምፈልገው ነገር አለ። በነዚህ የአማራ ብሄርተኞች ምንም ምንም አልፈርድም። ያወረስናቸው ኢትዮጵያ እጅግ ህመምተኛ እና ደካማ ናት (አሁንም እንዳ አብይ አህመድ አይነት ጀግና መውለድ ብትችልም)። ያወረስናቸው የፖለቲካ ባህል ጥላቻ የቶሞለው ስልት-ቢስ የሆነ ነው። በጃንሆይ ዘመን በሰላም ነገሮችን ከማስተካከል ሀገሪቷን ወደ ገደል ወሰድናት (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_15.html)። ለዚህ ማንም ላይ ጣቴን አልጠቁምም። እንደ በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ የኔ ጥፋት ነው ብዬ ሃላፊነት እወስዳለሁ። ይቅርታም እተይቃለሁ።

ይህን ካልኩኝ በኋላ የአማራ ብሄርተኞችን እንደ ኦርሞ ብሄርተኞች ተጠንቅቆ መያዝ ያስፈልጋል እላለው። እርግጥ የአማራ ብሄርተኞች በአብዛኛው በጎሳ ብሄርተኝነት አናምንም ስትራቴጂ ነው ወይንም ሌሎቹ በጎሳ ስለተደራጁ ግዴታ ሆኖብን ነው ይላሉ። በኢትዮጵያዊነት እናምናለን ይላሉ። ነገ ህገ መንግስቱ ቢቀየር እኛም በጎሳችን መደራጀት እናቆማለን ይላሉ። አቃፊ ብሄርተኞች ነን ይላሉ።

ሆኖም የጎሳ ማንነት በደምብ ገብቶባቸዋል። መጀመርያ አማራ ነን ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ የሚሉ አሉ። ኢትዮጵያዊነት ጠፍቷል የሚሉ አሉ። አንቀጽ 39 ጥሩ ነው የሚሉ አሉ። በመታወቅያ ላይ ጎሳ ቢኖር ጥሩ ነው የሚሉ አሉ። አማራ ብሄርተኛ ያልሆነ አማራ አይደለም የሚሉ አሉ። ወዘተ።

ስለዚህ ይህን ማንነት በዘዴ መያዝ ይኖርብናል። ከሙግት ይልቅ empathy ወይን መቆርቆር ነው የሚያስፈልገው። ከሙግት በፊት መተማመንን መፍጠር ያስፈልጋል (አንድ የሆንን እና የምንተማመን መስሎኝ ነበር ግን ለካ የማላውቀው ብዙ ግጭት እና ቁስል አለ በአምራ ብሄርተኞች እና «አንድነት ኃይሎች»)። ትክክለኛ መተማመን ጋር ከደረስን በኋላ ብቻ ነው ወደ ውይይት እና ሙግት መግባት ያሚቻለው።

የ27 ዓመት ጥቃትን አናጣጥል። የብዙ አማራ «ሞራል» ተሰብሯል። ጥቂት ትግሬ ገዝቶን ነበር ብለው የሚያስቡ ብዙ አሉ። ትክክለኛውን ሚዛናዊውን ግንዛቤ ላይ ከመድረስ በራስ አለመተማመን እና የ«ጭቁን» ስሜት ብዙዎቻችን ላይ አድሯል። ይህን እኔ በበኩሌ አልተገነዘብኩትም ነበር። ምን ያህል ስር እንደሰደደ አልገብኛም ነበር። ድሮ ኩሩ የነበረው አማራ ምን ያህል ሞራሉ እንደተጎዳ እና ወደ ጎሳ ብሄርተኝነት ማዘንበል እንደሚችል አልገባኝም ነበር። አሁን ግን ትንሽ የገባኝ ይመስለኛል። ከተሳሳትኩኝ አርሙኝ።