Sunday 15 July 2018

የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ጥፋታችንን ካላመንን ካላስተካከልን ኢትዮጵያን ዳግም እንሸጣታለን

ያለፉት 60 ዓመት የኢትዮጵያ ብሄርተኛ የፖለቲካ ጎራው ታሪክ እጅግ አሳዛኝ እና አሳፋሪ ነው። ከዛ በፊት እስከ ወደ 1955 ሀገራችን ዓለም ዙርያ የተከበረች ነበረች። በዲፕሎማሲ፤ በሀገራዊ ኃይል ወዘተ ከአቅሟ በላይ የምትሰራ ነበረች። አንድ አንድ ምሳሌዎች፤

1. የበርካታ የዓለም ሀገሮች ተቃውሞ በላቀ የዲፕሎማሲ ስራ አሸንፋ ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ መለሰች። ይህ የዲፕሎማሲ ድል ከሀገራችን ከአቅማችን አስር እጥፍ በላይ ነበር ግን አደረግነው።

2. የአፍሪካ ቁንጮ ሆንን ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት እኛን እንደ ምሳሌ ያይን ነበር። በዲፕሎማሲ እና ሀገር ኃይል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በታሪክ እና ባህል። ይህ ክብሬታ ለኢትዮጵያ ብዙ ጠቅሟታል።

3. በዓለም ዙርያ ያሉት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያኖች ስብሰባ አቀደች የኦሪዬንታል ኦርቶዶክስ ስብሰባውን አከናወነች ስምምነቶች አስፈጸመች።

ከ1955 አካባቢ በኋላ ግን እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኖች እርስ በርስ በመጣላት ሀገራችንን ድራሹን አጥፍተናል። መጀመርያ አስፈላጊ የፖለቲካ ለውጦች ባለማድረግ ቀጥሎ ልዩነቶቻችንን በጡንቻ በማካሄድ ሀገራችንን አሳልፈን ለጎሳ ብሄርተኞች ሰጠን። የመጨረሻ ውጤት ምን ሆነ ሻዕብያ እና ወያኔ የሀገራችን 10%ን ወክለው ኢትዮጵያን ተቆጣጠሩት። ይህ ለኛ 90% እጅግ አሳፋሪ ክስተት ነበር አሁንም ነው።

ይህ ታሪክ እንዳለ ሆኖ አሁን ያለፉትን ስህተቶቻችንን ለማርም የሀገራችን ሆደ ሰፊ ብዙሃን እና እግዚአብሔር ዳግም ለማረም እድሉን ሰጥተውናል። ሆንም አንታረምም ብለናል። ዋናው እና መሰረታዊ ችግራችን ያለፉትን አሳፋሪ ድርጊታችንን አለማመናችን ነው ሰው ችግሩን ካላመኑ መፍትሔ አያገኝምና። ጥፋቶቻችንን ላለማምን እና ለመደበቅ ብለን ይመስለኛል ሁል ጊዜ ለችሮቻችን ወያኔ፤ ሻዕብያ፤ ኦነግ፤ «አሜሪካ»፤ ሩሲያ፤ ኤርትራ፤ «አራብ ሀገራት» ወዘተን የምንወቅሰው። እኛ የገዛ ቤታችንን በር ከፍተን እነዚህ ደብተው እንደፈለጉት ሲያደርጉ በራችንን እንዴት ተከፈተ እንዝጋው ከማለት ለሚን ይገባሉ ብለን መጮህ! ዋናው ጣፍቱ የኛ እንደሆነ እናውቃለን ግን እፍረታችን ከባድ ነው መሸሽ ብቻ ነው የምንፈልገው።

ለማስተዋስ ያህል ባለፈው ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አንድ የኤርትራ የጦር አዛዥ ያለው ነገር አለ። አንድ ኤርትራዊ አስር ኢትዮጵያዊ ዋጋ አለው ብሎ ፎከረ። ይህ አዲስ ፉከራ አልነበረም በደርግ ጦርነት ላይ የተመሰረተ ነው። የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ምን ያህል እንደተናቁ ነው የሚያሳየው። ድሮ ኤርትራ በሰላም ያጠቃለልን ዛሬ ይቀልዱምን ጀመረ። እስከ ዛሬ በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የፖለቲካ ዋይንም የንግድ ዘርፎች በሙሉ ኤርትራዊዎችም ትግሬዎችም እደዚህ ያስባሉ። እኛ ደደብ አህዮች እነሱ አስር እጥፍ ጎበዝ። ከኢትዮጵያዊዎች ብልጥ፤ ጠንካራ፤ የተማርን ወዘተ ነን ብለው ያስባሉ። ይህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ግን የነሱ ጥፋት አይደለም። በፍፁም የነሱ ጥፋት አይደለም። እኛ እርስ በርስ ተጨራርሰን እራሳችንን ከታላቅ ህዝብ እና ሀገር ወደ ደካማ ለማኝ ስላወረድን እነሱ የሚያዩትን እውነታ ነው የሚናገሩት። ይህ ለኛ እጅግ አሳፋሪ ነው።

የሰው ልጅ ግን እፍረቱ ስለሚያሳምመው ሊደብቀው ይፈልጋል። ለችግሮቹ ሃላፊነት ከመውሰድ ሁል ጊዜ በውነትም በውሸትም ሌሎችን ይወነጅላል። እኛም አሳፋሪ ድርጊቶቻችንን እና ውድቀታችንን ለመደበቅ ያህል ለ27 ዓመት መጀመርያ ሻዕብያን፤ ኦነግን፤ ወያኔን ወዘተ እየወቀስን ቆይተናል። አሁንም እግዚአብሔር የማይገባንን ጠንካራ የድሮ ዘመን አይነት ኢትዮጵያዊ መሪ ልኮልን አሁን ላሉን ችግሮች ህወሓትን እንወቅሳለን! እንደ ወቀሳችን መጠን ህወሓት ማንም የማይሳነው ግዙፍ ኃይል እንዲመስለን አድርገናል! (ግን 6% ነው የሚወክለው እንላለን!) የራሳችንን ድክመንት ለመሸፈን ላለማየት ለህወሓት የሌለውን አቅም ፈጠርንለት የሌለውን ጥንካሬ ሰየምንለት።

አሁንም እዛው ላይ ነን። አሁንም ከኢትዮጵያ ብሄርተኛ ፖለቲከኛ ተንታኝ አስር ጽሁፎች ካነበብን አስሩም ስለ «ሌሎች»፤ ወያኔ፤ ጎሰኞች፤ ኦነጎች ወዘተ ለቅሶ ነው። እንጂ አንድም ስለራሳችን ጥፋቶች እና ማረምያኦች የሚናገር የሚጽፍ የለም። ኢሳትን ከተመለከትን ስለ«ጠላት» ለቅሶ ነው። ጋዜቶች ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁ። የኛ የ«ተፎካካሪ» ድርጅቶች ወሬም እንዲሁ ምናላባትም ይብሳል። እንደ ሚና እና አቅም የሌላው ተጨቋኞች ማልቀስ፤ ማልቀስ፤ ማልቀስ።

እንደዚህ በማድረግ ለራሳችን ጥልቅ የሆነ የእፍረት ጉድጓድ ቆፍረናል። የራሳችን ህልውና በራሳችን ሳይሆን በሌሎች የተቆጣጠረ ነው ብለናል። እነዚህ ሌሎች ደግሞ ከኛ እጅግ አናሳ የሆኑ ናቸው። ይህ አስተሳሰብ ግልጽ የሆነ የዝቅተኝነት መንፈስ እንዲያድርብን አድርጓል። እውነት ነው በተፈጥሮ ሻ'ዕብያዎች፤ ወያኔዎች፤ ኦነጎች ወዘተ ከኛ ይሻላሉ ይበልጣሉ ብለን አምነናል! ይህን የተሳሳተ እምነት የገባንበት ለችግሮቻችን በሙሉ እነሱን ፈላጭ ቆራች እራሳችንን አቅመ ቢስ ስለምናደርግ ነው። ይህ የዝቅተኝነት መንፈስ የሚፈጥረውን እፍረት ለመሸፈን ደግሞ እንደገና እነሱ ላይ እንወርዳለን ከእፍረታችን ለመሸሽ ብለን። ይህ "vicious cycle" ሆኖናል ማቆም ያልቻልነው ሱስ ሆኖናል። የድሮ መሪዎቻችን (ከነ ስህተቾቻቸው) ይህን ቢያዩ ኢትዮጵያዊ መሆናችንን የሚያምኑ አይመስለኝም።

እግዚአብሔር ችር ነው እና አሁን በራሱ የሚኮራ፤ ሃላፊነት የሚወስድ፤ ጥፋቱን የሚያምን፤ ለጥፋቶቹ ንስሃ ገብቶ ይቅርታ የሚጠይቅ፤ ሌሎችን ለራሱ ጥፋቶች እና ችግሮች ከመውቀስ እራሱን በተገቢው ወቅሶ መፍትሔውን ፈልጎ አግኝቶ ስራ ላይ የሚያውል ጀግና መሪ ሰጥቶናል። ለኛ ለኢትዮጵያ ብሄርተኞች ምሳሌ ሊሆን የሚገባን መሪ። ከ60 ዓመት ጥፋታችን በኋላ አሁንም እራሳችንን ለማረም እድል ተሰጥቶናል። ይገርማል!

አሁን የ60 ዓመት ጥፋታችን ውጤት ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ተዝናንተን አድሃሪ፤ ተራማጅ፤ ደርግ፤ ኢዲኡ፤ ኢህአፓ፤ ሜሶን ወዘተ እየተባባልን ተጨራረስን። ባቃጠልነው ባዶ ሜዳ የጎሳ ብሄርተኞች ገቡ። አሁንም የሀገራችን ታላቅ የፖለቲካ ችግር የጎሳ ብሄርተኝነት ነው ብለን እናምናለን ላለፉት 27 ዓመት ያመጣውን ግጭቶች አይተናልና። ስለዚህ የእርስ በርስ መጣላታችን የመስማማት እና አብሮ መስራት አለመቻላችን ምን አይነት ውጤት እንደሚያመጣ እናውቃለን። በዚህ ምክንያት ጎሰኝነትን ለመቀነስ ለማጥፋት ከፈለግን እኛ የሀገር ብሄርተኞች አንድ መሆነ እንዳለብን የእርስ ብሰር ችግሮቻችንን መፍታት መችሃል እንዳለብን ለጋራ ጥቅም አብሮ መሰለፍ እንዳለብን ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። ግልጽ ብቻ ሳይሆን ብቸኛ መንገዳችን እንደሆነ ሊገባን ይገባል። አማራጭ የለንም።

ካሁን ወድያ ከማህላችን ጣት መጠቆም ስለ ሻዕብያ፤ ወያኔ፤ ጎሰኞች ወዘተ ማልቀስ ክልክል ይሁን! ክልክል ይሁን! ይህ አስተሳሰብ ነው ወደ ኋላ የሚጎትተንና። እንደ ጠ/ሚ አብይ ችግር ሲያጋጥምን እራሳችንን ምን አድርገን ነው ይህ ችግር የገጠመን ነው ማለት ያለብን። ወሬዎቻችንን፤ አነጋገራችንን፤ አስተሳሰባችንን፤ ጽሁፎቻችንን እንቀይር። ሌሎች አጎልብተን ስለነሱ በኛ ያላቸውን ሚና ከማውራት እራሳችንን አጎልብትን እንገኝ እራሳችን ለራሳችን አለቃ ነን ችግር ካለን እንፈታለን እንበል። ያህን አይነት ባህል ማዳበር አለብን የ60 ዓመት የውድቅ ልምድ ለመቀየር። ታላቅ ስራ ነው ግን እድለኛ ነን እንደ አብይ አይነቱ የጎላ ምሳሌ ሰጥቶናል።

በመጨረሻ አንድ የጠ/ሚ አቢይ ምሳሌ ልጥቀስላችሁ። ከኢሳያስ ጋር ያለውን ግንኝነት እንየው። እራሱን እንደ ታናሽ ወንድም ትሁት አድርጎ ነው የሚያሳየው። እራሱን ዝቅ ያደርጋል ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲመጣ እራሱ ጠቅላይ ሚኒስጤር ሆነ ይቀበላል። የ100 ሚሊኦን ህዝብ መሪ ሆኖ ወደ ስድስት ሚሊዮንዋ ኤርትራ መጀመርያ እሱ ነው የሄደው። ለምን። ይህን ማድረግ የሚችሉ በራሱ ስለሚተማመን ነው። ሁኔታውን እራሱ እንደሚቆጣጠር ስለሚያውቀው የራሱን አጀንዳ ማስረገጥ እንደሚችል ስለሚያውቅ እራሱን ዝቅ ማድረግ ምንም አይመስለውም። በራሱ የሚኮራ ብቻ ነው እራሱን ዝቅ ማድረግ የሚችለው። ሌሎቻችን በራሳችን የምናፍር ሰውው ገበናችንን ያቅብናል ብለን የውሸት ጭምብል አድርገን እንኮፈሳለን። አያችሁ እንዴት በራስ ሃላፊነት መውሰድ ሌሎችን ለራስ ችግር ሌሎችን አለመወንጀል እራስን እንደሚያጎለብት። ሌላው መንገድ እራስን አቅመ ቢስ ያደርጋል። ለራስ ሃላፊነት መውሰድ ግን ያጎለብታል። ዶ/ር አብይም የፖለቲካውን ጉልበት ከዚህ ነው የሚያገኘው። እስቲ ትንሽም እንማር!

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!