Monday, 1 April 2019

የቅንጅት ታሪክ ሊደገም ነው?

ታሪኩን ለማታስታውሱ ወጣቶች፤ የቅንጅት «ፓርቲ» አመራሮች ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ኃይለኛ የእርስ በርስ የፖለቲካ ጦርነት አካሄዱ። ዋና አቋሞቻቸው አንድ ነበር፤ የኢህአዴግ/ህወሓት አምባገነን አገዛዝን ማስቆም እና «ዴሞክራሲ» እና የዜግነት ፖለቲካን ማምጣት። እንደዚህ አይነት ግዙፍ እና ዋና ጉዳዮች ላይ የሚጋሩ ቢሆንም ሁለቱ የቅንጅት ወገኖች አብሮ ለመስራት አልፈለጉም፤ መጨራረስን መረጡ። ጥላቸው እየከረረ ሲሄድ እርስ በርስ ያላቸው ጥላቻ ለኢህአዴግ ካላቸው ጥላቻ በልጦ ተገኘ! የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እና ዴሞክራሲ ትግል እንደገና ፈራረሰ ተበታተነም (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html)።

ዛሬም ይህን ታሪክ ካልደገምን እያልን ይመስላል። የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ነኝ፤ የዜግነት ፖለቲካ ደጋፊ ነኝ፤ ዴሞክራሲን እደግፋለሁ፤ ጎሰኝነት ይውደም፤ የምን ሆነን እነዚህ የጋራ ፍላጎት እና ጥቅማችን አብሮ በመስራት ከማስከበር ፋንታ በትናንሽ የሚለያዩን ጉዳዮች እንፋለማለን!! የጉድ ጉድ ነው። ይህ ሁሉ የምንጋራው ዋና ነገሮች እያሉ እንጣላለን። ምን ማለት ነው?

ለምሳሌ ግንቦት 7ን መሳደብ። አዴፓን መሳደብ። የእስክንር ነጋን ንቅናቄ ማጥላላት። ምን ማለት ነው? በሰለጠነ ፖለቲካ እነዚህ ሁሉ ጠንካራ አጋሮች መሆን ይኖርባቸው ነበር። ትናንሽ የታክቲች እና ስትራቴጂ ልዩነቶች አላቸው። በመነጋገር እና መናበብ እርስ በርስ መጠቃቀም እና መደጋገር ይችላሉ። ለነገሩ የበሰለ አብንም እንዲሁ የዜግነት ፖለቲካ ነው የምፈልገው ሰለሚል። ግን የለም። 100% ካልተስማማን ወይንም የግል ጸብ ካለን ከምንተባበር ኦነግ ቢያሸንፍ ይሻላል ነው አመለካከታችን።

የቅንጅት እርስ በርስ ጦርነት እንደ ባቡር ግጭት ለረዥም ጊዜ እንደሚከሰት እያየን ምንም ማረግ ሳንችል የተከሰተ እልቂት ነበር። አሁንም ይህ ባቡር ይተየኛል፤ የግጭት ጉዞውን ጀምሯል።


No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!