ለመጀመርያ ጊዜ በአማራ ስም ፋንታ በኢትዮጵያ ስም ብትደራጁ አይሻልም ወይ ብዬ የአማራ ብሄርተኞችን ስጠይቅ ያገኘሁት መልሶች (ስድቦቹን ትተን) አስገራሚ ነበር። ምናልባት 80% ስለ አማራ ላይ ባለፉት 27/40 ዓመት የደረሰበት በደል እና ጭቆና ነው። የአማራ ህዝብ ጥቅም ይበልጥ የሚከበረው በአማራነት በመደራጀት ነው ወይንም በኢትዮጵያዊነት በሚለው ዙርያ ከመወያየት ፋንታ ስለ አማራ መጨቆን የጭቆና ቆጠራ ውስጥ ገባን። ይህን ስል አማራው አልተጨቆነም ማለቴ አይደለም ከሌሎች ይልቅ በመንግስት ብቻ ሳይሆን በግለ ሰብ እና በቡድን በአማራነቱ ተጭቁኗል «መጤም» እየተባለ በትውልድ ሀገሩ ባይተዋር ሆኗል። ይህ ሁሉም የሚያቀው ነው። ግን ይህ በፍፁም የአማራ ማንነት መግለጫ መሆን የለበትም። ላስረዳ…
እንደገባኝ ይህ የ27 ዓመት ጭቆና የዛሬው የአማራ ማንነት መሰረት ሆኗል። እስቲ ስለ አማራ እና አማራነት ንገረኝ ሲባል የዘመኑ አማራ ላለፉት አመታት «እጅግ የተጨቆነ፤ የተበድለ፤ የተፈናቀለ፤ የተዋረደ፤ ባሁሉ የተሰደበ፤ ማንነቱ የተገፈፈ» ወዘተ ነው የሚለው። የድሮ አማራ ይህንን ቢሰማ እጅግ ግራ ነበር የሚገባው። ማን ነው አማራ ምንድነው አማራነት ብለህ የድሮ አማራን ብትጠይቀው 3000 ዓመት ታሪክ ያለው፤ ሃይማኖት ያለው፤ ስልጣኔ ያለው፤ የአፍሪካ ቁንጮ፤ የሰው ልጅ ቁንጮ፤ ፍርሃ እግዚአብሔር ወዘተ ነው የሚለው! ልዩነቱን አያችሁ። አማራ በወጉ መሰረት እራሱን የሚሰይመው ማንነቱን የሚገልጸው በአዎንታዊ መንገድ ነው። ዛሬ ግን እድሜ ለረዥም ዓመት ጫና እና የጎሳ ብሄርተኝነት እና የማርክሲዝም ፕሮፓጋንዳ አማራው ማንነቱን ስቷል።
የዛሬ አማራ የበታችነትን ስሜት (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_30.html) መቀበል ብቻ ሳይሆን የማንነቱ መሰረት ያደረገው ይመስላል። የሰለባ አመለካከት (victim complex)፤ የበታችነት ስሜት (inferiority complex) አጥቅቶናል። እንደ ጥቁር አሜሪካኖች ወይንም ሌሎች በጭቆና ምክንያት ማንነታቸውን ሙሉ በሙሉ ለ«ጭቁን ነው ማንነቴ» የሚለው አስተሳሰብ እራሳችንን ሰጥተናል።
በራሳችን መተማመን እና መኩራት ቀርቷል። ጣልያን ለአምስት ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ ቆይቶ ተጭቁነናል ተገዝተናል ብለን አናውቅም። የድሮ አማራ ምንም ያህል ቢጭቆን እራሱን «ተጨቋኝ ነኝ» ብሎ አይሰይምም። ጦርነት ላይ ነኝ ነው የሚለው። እንደ አያቶቼ አሸንፋለው ነው የሚለው። እንጂ እጁን ለበታችነት ስሜት አይሰጥም ምን እንደሆነም አያቅም። ለዚህ ነው እስከ ዛሬ ጣልያን ገዝቶናል አንልም። ውግያ ላይ ነበርን ነው የምንለው። ይህ ነበር የድሮ እና ትክክለኛ ተውፊተኛ የአማራ ስለራሱ ማንነት አስተሳሰብ።
ዛሬ ግን ይህ ባለመሆኑ ብዙ አማራ በተለይ ወጣቱ «ጭቁን ብሄረሰብ» ነኝ የሚለው አስተሳሰብ አምኖበት ውጦታል (internalize) ተዋህዶታል። ስለዚህ ይመስለኛል የ«አማራ ብሄርተኝነት» ድሮ ታይቶ የማይተወቀው ዛሬ እንደዚህ መነሳት የጀመረው። በጎሳ ብሄርተኝነት የማናምነው ወንድሞች እና እህቶች ይህ የአማራ ብሄርተኝነት ፖለቲካ ለአማራ ህዝብ ያዋጣል ወይ በሚለው እንነጋገር ስንል ብዙ ጊዜ ስሜታዊ መልስ እና ስድብ ነው የሚጠብቀን። ምክንያቱ የአማራ ብሄርተኛውን ማንነት ጥያቄ ውስጥ ስላደረግን ነው። ማንነቱ «ጭቁን አማራ» ሆኗል። አንድ ሰው ይህ ነው ማንኔቴ ብሎ ከሰየመ አልፎ ተርፎ ቁስል ያለው ከሆነ በዚህ ዙራይ መወያየት አይችልም። ውይይቱ በሃሳብ ሳይሆን በማንነት ስለሆነ በዚህ መደራደር የለም። ስሜት እና ቁጣ ብቻ ነው።
ይህ ክስተት እነ ሻዕቢያ፤ ህወሓት፤ እና ኦነግ ሲመሰረቱ አይተነዋል። ወደነዚህ የሚያዘንብሎ ሰዎችን ድሮ ስናናገር አንዴ እንዲሁም እንዴት ማንነቴን በጥያቄ መልክ ታቀርበዋለሁ ብለው ይናደዱ ነበር። በማንነት ድርድር የለም ይሉ ነበር። መገንጠል አይበጅም ኢትዮጵያዊ ናችሁ ወዘተ አይነት ነበር በፍፁም መስማት ብቻ ሳይሆን ስለዚህ መነጋገርም አይፈልጉም። አንዴ ማንነት ከተቀየረ በአጭር ጊዜ ምንም ማድረግ አይቻልም።
ስለዚህ አሁን ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ብዙ በተለይ ልጅ የሆኑ አማራ እህት እና ወንድሞቻችን ባለፈው 27 ዓመት የጎሰኝነት፤ ፀረ አማራ፤ ማርክሲዝም ፕሮፓጋንዳ ቶሞልተው የአማራ ማንነታቸው ተቀይሯል። «ጭቁን» ነኝ ብለው አምነዋል። ለዚህ ጭቆና መልሱ ወደ «አማራነት» ከ«ኢትዮጵያዊነት» ማስቀደም ነው ብለው አምነዋል። ይህን በሰላም መተቸት ማንነትን መተቸት ሆኗል።
ጉዳዩ እንደዚህ ባይሆን እና የበታችንነት እና የ«ጭቁን» አስተሳሰብ ባይህኖር መርሰረታዊ ጥያቄውን በአማራ ስም ነው ወይም በኢትዮጵያ ስም ነው መደራጀት የሚበጀን መወያየት እንችል ነበር። አሁን ግን ለብዙዋች ውይይት አቻልም ስሜት ይነካልና ማንነትን ይነካልና።
አንድ ማረግ የምንችለው የአማራ ባህል እና ወግ በትክክሉ ማስተማር ነው። የአማራ 3000 ዓመት ታሪክ በራሱ መኩራት እና መተማመን ነው። ፍርሃት የለውም። እንደ ጠ/ሚ አብይ (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_10.html) ማንም አይነት ሰውን አቅፎ ይዞ እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምኖ ወደ ትክክለኛ መንገድ ማምጣት ነው ባህላችን። ወደዛ ለመመለስ እንጥራ። መሰረታዊ ማንነቱን ያጣ ህብረተሰብ ይወድቃል።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!