Showing posts with label infighting. Show all posts
Showing posts with label infighting. Show all posts

Thursday, 16 December 2021

ከንቱ መከፋፈልን ቀንሰናል፤ አሁን እናጥፋው

ሁላችንም የምናውቀው የድሮ ከንቱ መከፋፈል ባህሪአችን እየቀነሰ እያየነው ነው። የከንቱ እርስ በርስ መጣላትና መከፋፈል ባህሪአችን አደጋ ላይ እንደጣለን እና ከምድር እንድንጠፋ ጫፍ እንዳደረሰን እየገባን ነው። ህወሓትም በዚህ ምክነያት አናሳና ትንሽ ሆኖ እንደገዛን ገብቶን እያመንን ነው። 

መቼስ የመንቃታችን አንዱ ምክነያት ያየነው አደጋና የጦርነት ውጤት ቢሆንም መንቃታችን ጥሩ ነው። ግን በፍጹም መዘናጋት የለብንም። የከንቱ መከፋፈል ባህሪአችን ከውስጣችን ጨርሶ እስኪጠፋ ተግተን መታገል አለብን። አማራጭ እንደሌለን ከልባችን ማመን አለብን። 

አንዱ ማድረግ ያለብን ነገር አንድነትን ዋና መግባር ማድረግ ነው። ከእውነት፤ ጽናት፤ ታማኝነት ወዘተ እኩል የሆነ መግባር መሆን አለበት። ትቢትና አውቃለሁ ባይነትን ነውር ማድረግ። ውሳኔዎችን በጋራ አድርጎ በጋራ መቀበልን ዋና መግባር ማድረግ። የክፍፍልንና እርስ በርስ መጣላትን፤ የጋራ ውሳኔን አለማክበርን ነውር ማድረግ። የህልውና ጉዳይ ነው።

Monday, 1 April 2019

የህፃንነት ፖለቲካ

ላለፉ 50 ዓመታት፤ ከደርግ አቢዮት ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጎራው በህፃንነት የፖለቲካ አስትሳሰብ ተለክፏል። ተመልከቱ...

በአንድ በኩል ኃይል ያለው የጎሰኛ ጎራ አለ። ኃይል ማለት ኃይለ ቃል አይደለም አንዳንዶች ሁለቱ አንድ ይመስላቸዋልና። «ከተሳደብኩኝ ተሟገትኩኝ» ብሎ የሚያስብ አለ እንጂ። ኃይል ማለት ጎሰኛው በየ መንግስት መዋቅሩ ተሰግስጓል። ገንዘብ አለው። ሚዲያ አለው። መዋቅሮች አለው። ጦር አለው። አካላዊ እና ንብረታዊ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ፍላጎቱን በተለያየ መንገዶች ሊያስፈጽም ይችላል። መንግስት ውስጥ የተሰገሰገው በዛ አቅሙ ይጠቀማል። ጦር ያለው በሱ ይጠቀማል። ሚዲያው እንዲሁ። «ኃይል» ማለት ይህ ነው። ጎሰኛው ተጨባጭ (tangible) ኃይል አለው።

የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ወይን አንድነት ጎራው ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ኃይል የለውም። መንግስት መስሪያቤት ውስጥ ያለው ቁጥሩ ትንሽ ነው መንግስት የኢህአዴግ ስለሆነ። ጦር የለውም። ሚዲያው ደካማ ነው። ምንም መዋቅር የለውም። ገና እየተደራጁ ያሉ እነ ግንቦት 7 እና ባልደራስ ነው ያሉት። ሌላ ነገር የለም። ሰለዚህ ይህ ጎራ ፍላጎቱን ለማስፈጸም አቅም የለውም። የራሱን መከላከልም አቅም የለውም። መዋቅር እና ኔትወርክ አልዘረጋም። ከሞላ ጎደል ኃይሉ እጅግ አነስተኛ ነው። አልፎ ተርፎ ይህ ጎራ ዋናው hobbyው እርስ በርስ መጠላለፍ እና መጣላት ነው።

ይህ እንደሆን እነ ጠ/ሚ ዓቢይ የሚፈሩት ማንን ነው፤ ጎሰኛውን ነው የኢትዮጵያ ብሄርተኛው? ጎሰኛውን ነው። ገጀራን ዝም ብለው ባልደራስን የሚተቹት ለምንድነው? ባለ ገጀራው ኃይል አለው ባልደራስ የለውም። ግልጽ ነው።

በዚህ ሁኔታ ጠ/ሚ ዓቢይ ላይ መውረድ ምን ዋጋ አለው?! ቢፈልግም ገጀራውን ዝም ብሎ መደምሰስ አይችልም። በዘዴ መሆን አለበት፤ ጊዜ ይፈጃል። እያሳሳቀ ነው ሊያጠፋው የሚችለው። አንዳንዶች እንደሚሉት ከባለ ገጀሮቹ አንዱ ከሆነ ጠ/ሚ ዓቢይ መነጫነጫችን ዋጋ የለውም ማለት ነው።

መፍትሄው አንድ ብቸኛው ነው፤ የአንድነት ኃይሉ «ኃይል» ማጠራቀም አለበት። ከባለ ገጀራው እጥፍ ኃይል ከሌላው ዋጋ የለውም። ይህን ኃይል እስኪያጠራቅም ደግሞ ወደ ጸብ መግባት የለበትም፤ ይህ ቀላል የፖለቲካ ስልት ነው። አንገት ደፍቶ ሁሉንም እንደ አጋር አስመስሎ የኃይል ማጠራቅም ስራውን መስራት አለበት። እንጂ ገና ምንም ኃይል ሳይኖረው ሌሎችን አምበረግጋለሁ ማለት እራስን መጥለፍ ማለት ነው።

ስለዚህ ጠ/ሚ ዓቢይ ላይ የምትወርዱበት፤ ጩሀታችሁ ዋጋ የልውም፤ ጭራሽ ዋጋ ያስከፍላል። እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ተጨባጭ ኃይል እስኪኖረን እሱ ላይ መጮህ፤ እርስ በርስ ጸጉር መሰንጠቅ ዋጋ የለውም። መጀመርያ ተደራጅተን መዋቅሮች እና ኔትዎርኮች ዘርግተን ከዛ ብኋላ ወደ ሙግት።

(ለምን «ባለ ገጀራ» የሚለውን አሉታዊ አነጋገር ተጠቀምኩኝ? የዚህ ጽሁፍ audience የጎሳ ብሄርተኞች ላይ ኃይለ ቃል የሚጠቀሙ የአንድነት ሰዎች ናቸው። ለአንባቢው የሚመች ቃላቶችን ተጠቀምኩኝ። እነ ለማ መገርሳ ለርዥም ዓመታት «ኦነግ በሽፋን» የሆነውን የኦህዴድ ካድሬዎችን ሲያነጋግሩም እንዲሁ ብትረዷቸው ጥሩ ይመስለኛል።)

የቅንጅት ታሪክ ሊደገም ነው?

ታሪኩን ለማታስታውሱ ወጣቶች፤ የቅንጅት «ፓርቲ» አመራሮች ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ኃይለኛ የእርስ በርስ የፖለቲካ ጦርነት አካሄዱ። ዋና አቋሞቻቸው አንድ ነበር፤ የኢህአዴግ/ህወሓት አምባገነን አገዛዝን ማስቆም እና «ዴሞክራሲ» እና የዜግነት ፖለቲካን ማምጣት። እንደዚህ አይነት ግዙፍ እና ዋና ጉዳዮች ላይ የሚጋሩ ቢሆንም ሁለቱ የቅንጅት ወገኖች አብሮ ለመስራት አልፈለጉም፤ መጨራረስን መረጡ። ጥላቸው እየከረረ ሲሄድ እርስ በርስ ያላቸው ጥላቻ ለኢህአዴግ ካላቸው ጥላቻ በልጦ ተገኘ! የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እና ዴሞክራሲ ትግል እንደገና ፈራረሰ ተበታተነም (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html)።

ዛሬም ይህን ታሪክ ካልደገምን እያልን ይመስላል። የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ነኝ፤ የዜግነት ፖለቲካ ደጋፊ ነኝ፤ ዴሞክራሲን እደግፋለሁ፤ ጎሰኝነት ይውደም፤ የምን ሆነን እነዚህ የጋራ ፍላጎት እና ጥቅማችን አብሮ በመስራት ከማስከበር ፋንታ በትናንሽ የሚለያዩን ጉዳዮች እንፋለማለን!! የጉድ ጉድ ነው። ይህ ሁሉ የምንጋራው ዋና ነገሮች እያሉ እንጣላለን። ምን ማለት ነው?

ለምሳሌ ግንቦት 7ን መሳደብ። አዴፓን መሳደብ። የእስክንር ነጋን ንቅናቄ ማጥላላት። ምን ማለት ነው? በሰለጠነ ፖለቲካ እነዚህ ሁሉ ጠንካራ አጋሮች መሆን ይኖርባቸው ነበር። ትናንሽ የታክቲች እና ስትራቴጂ ልዩነቶች አላቸው። በመነጋገር እና መናበብ እርስ በርስ መጠቃቀም እና መደጋገር ይችላሉ። ለነገሩ የበሰለ አብንም እንዲሁ የዜግነት ፖለቲካ ነው የምፈልገው ሰለሚል። ግን የለም። 100% ካልተስማማን ወይንም የግል ጸብ ካለን ከምንተባበር ኦነግ ቢያሸንፍ ይሻላል ነው አመለካከታችን።

የቅንጅት እርስ በርስ ጦርነት እንደ ባቡር ግጭት ለረዥም ጊዜ እንደሚከሰት እያየን ምንም ማረግ ሳንችል የተከሰተ እልቂት ነበር። አሁንም ይህ ባቡር ይተየኛል፤ የግጭት ጉዞውን ጀምሯል።


Thursday, 6 December 2018

የ «መጠላለፍ» ፖለቲካ

በቅርብ ጊዜ ነው የ«መጠላለፍ ፖለቲካ» የሚለውን አባባል ያወቅኩት። በጣም የወደድኩት አባባል ነው፤ ችግሩን በሚአምር መንገድ የሚገልጽ።

የመጠላለፍ ፖለቲካ ሲባል የሚታየኝ የአንድ የኳስ ቡድን ተጨዋቾች በግጥሚአ መሃል እርስ በርሳቸው ላይ «ፋውል» ሲሰሩ እና ሲጠላለፉ ነው! የሌላው ቡድን ተጨዋቾች ገርሟቸው በንቀት ያመለከቷቸዋል!

አንድ ተጨዋች ከአሸናፊ ቡድን መሆን ይጠቅመዋል። የተጨዋቹን ዋጋ ማለትም ደሞዝ እንዲጨምር ያደርጋል። ስለዚህ የእያንዳንዱ ተጨዋች ጥቅሙን የሚያስከብረው ቡድኑ እንዲያሸንፍ በማድረግ ነው። ግን ተጨዋቾቹ ይህን አይገነዘቡም። ምናልባት ከባልደረቦቻቸው ጋር ትናንሽ ጸቦች አላቸው። በነዚህ ትናንሽ ጸቦች ምክንያት ያላቸው ንዴትን ለመወጣት ብለው ጥቅማቸውን ይጎዳሉ። ቡድናቸው እንዳያሸንፍ ያደርጋሉ!

ፖለቲካችንም እንዲሁ። እጅግ የሚያማርረኝ የፖለቲካ ታሪካችን የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ፖለቲካ በተለይ ከ1967 በኋላ ነው። ብዙ ጽሁፎች ስለኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች አሳዛኝ ታሪክ ጽፍያለሁ። ከኢዲዩ ጀምሮ እስከ ቅንጅት ከዛም አልፎ ታሪካችን የ«መጠላለፍ ፖለቲካ» ነው። ከሁሉም ታሪክ በላይ ይህንን በደምብ የሚገልጸው የቅንጅት ታሪክ ነው። የቅንጅት አመራርም ተከታዮችም እስክንቆሳሰል ተጠላለፍን! በአስርት ሚሊዮን ሰው የተደገፈውን ድርጅት አፈረስን።

ብዙዎቻችን ደጋግመን ከነህ ከመጠላለፍ ታሪካችን እንማር እንላለን። መቼም አይደገም እንላለን። በመጠላለፍ ኢትዮጵያን ወደ አደጋ ጫፍ አድርሰናታል። እግዚአብሔር ጥፋት ይበቃችኋል ብሎ አቢይ አህመድን ልኮልናል። የህን የመጨራሻ እድላችንን በአግባቡ እንጠቀምበት።

https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html