Monday 26 March 2018

አማራጭ የፖለቲካ ልሂቃን ቡድን አለ?

በ2017/5አ.አ የተሳፈ ጽሁፍን አማርኛ ትርጉም

English version: https://asfawdarguemeshal.blogspot.ca/2017/05/alternative-political-elite.html

በ1983 ደርግ ፈርሶ ሻዕብያ ህወሓትና ኦነግ ወደ ስልጣን ሲገቡ መዐቱን ፈርተን ነበር። ምክንያቱም ሻዕብያ ህወሓትና ኦነግን እንደ ጎሳ ብሔርተኞች ሺፍቶች አገረን ለማፍረስ ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል የሚመኙ አድርገን ስለቆጠርናቸው።

ዛሬ ከ26 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ከነ በርካታ ችግሮቿ አሁንም አለች! ኤርትራ ብትገኝጠልም ጸንፈኛ የጎሳ አስተዳደር ቢጫንባትም ኢትዮጵያ ተርፋለች። ዋናው የተረፈችበት ምክንያት ብዙሃኗ ድሮም ዛሬም ባብዛኛው የአገር ብሔርተኛ አገርን ከ«ጎሳ» የሚያስቀድም ስለሆነ ነው። ይህ የህዝባችን ባሕሪ የህወሓትን ጸንፈኛ የጎሳ አቋምን ሊቋቋምና መልሶ ሊገፋው አብቅቶታል። እንደ የድሮ የቱርክ መሪ ከማል አታቱክር ህወሓት የአገር ህዝብን ወደ የማያምንበት አስተሳሰብ በግድ ሊጎትተው ፈለገ ግን ሙሉ ለሙሉ አልተሳካም። ህዝቡ የጎሳ ብሔርተኝነትን ህወሓት እንዳለመው ያህል አልተቀበለውም። በህዝቡ መካከል ኢትዮጵያዊነት አሁንም ጠንክራ ትገኛለች!

በእውነቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሓትን አብርዶታል ማለት ይቻላል። ይህን ለመረዳት እስቲ ወደ የኢህአዴግ የመጀመርያ 10 ዓመት ግዛት ወደ ኋላ ሄደን እንመልከት። በዛን ዘመን በተለይ ከኢርትራ ጦርነቱ በፊት «ጠባብ የጎሳ ብሔርተኛ» የሚል አባባል አልነበረም። «ነፍጠኛ» «ትምክህተኛ» በቻ ነበር ህወሓት የሚዘፍነው። ህወሓት ሁሉንም «ጎሳዬ ከኢትዮጵያዊነቴ ይበልጣል» እንዲል ያበረታታ ነበር። «መጀምርያ ኦሮሞ ነኝ ሁለተኛ ኢትዮጵያዊ» ወይም «መጀመርያ ትግሬ ነኝ ሁለተኛ ኢትዮጵያዊ» ማለት የተለመደ ነበር። «ኢትዮጵያዊነት» የሚጠቃ የሚሾፍበት ነበር። አሁን ግን እንደዚህ አይነት ቴአትር ቀንሷል። «ጠባብ» የሚለው ቃል ወደ ፖለኢትካ ቋንቋችን ገባ። ኢህአዴግን ችራሽ ኢትዮጵያዊ እኔና እኔ ብቻ ነኝ ማለት ጀመረ! ህወሓት ድሮ የሚሰብከውን ጸንፈኛ የጎሳ ብሔርተኝነትን ዛሬ እንደ ማነቆ ነው የሚያየው።

ለዚህ ለውጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊመሰገን ይገባል። የህዝባችን ጠንካራ አገር ፍቅርና የአገር ብሔርተኝነት ነው አገሪቷን ከከባድ አደጋ ጠብቆ በህይወት ይሚያኖራት። አስገራሚ ነገር ግን ይህ የህዝባችን ድል አለ ልሂቃን ጎራ በብዙሀኑ ኃይል በቻ መደረጉ ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት በ1983 የፖለቲካ ልሂቃን ሲባል ሻዕብያ ህወሓትና ኦነግ ብቻ ነበሩ ልሂቃንም የወታደር ኃይልም ከነሱ ነበር። ሌላው ወገን የኢትዮጵያ ብሔርተኛ  ወይም «አገር ወዳድ» ጎራ ኃይልም ልሂቃንም አልነበረውም። ይህ ልሂቃን ከአገር ፖለቲካ ጠፍቶ ነበር።

የጠፋው ምክንያት ይህ ልሂቃን ጎራ የረዥም ዓመት የራስ ማጥፋት ዘመቻ አካሄዶ ስለነበር ነው። ከ1950 አካባቢ ጀምሮ የኃይለ ሥላሴ ተማሪዎችና ልሂቃን በእርስ በርስ መተላለቅ በራስ ማጥፋት ምኞት መለከፍ ተጥቅቶ የራሱን ማጥፋት ስራ ብ1983 አብዮቱ አጥናቀቀ። እራሱን አንዴ አድሃሪ አንዴ ፍዩዳል አንዴ ኢህአፓ አንዴ ምኤሶን አንዴ ኢዲዩ አንዴ ደርግ ወዘተ እያለ እርስ በርስ ተፋጅቶ እራሱን ገደለ።

ለዚህም ነው ሽዐብያ ህወሓትና ኦነግ በ1983 በስልጣን ጉዳይ መደራደር ሲጀምሩ የኢትዮጵያ ብሔርተኛ ወቂል የፖለቲካ ወይም የጦር ኃይል ያልነበረው። ለኢትዮጵያ የሚቆምላት ልሂቃን አልነበረም። ልሂቃኑ ይህ ስራን ለብዙሓኑ ተውወው ግን ብዙሃኑ ስራውን በአቅሙ ሰርቷል።

ዛሬም የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ልሂቃን ጎራ ከሞላ ጎደል የለም። ይህ ሊደንቀን አይገባም። የፖለቲካ ልሂቃን ባንዴ አይነሳም፤ የረዝም ዓመትና የትውልድ ውጤት ነው። የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ልሂቃን ጎራ በ1983 የራሱን ማጥፋት ዘመቻ አጠናቅቆ ከዝያ ወዲህ ኢህአዴግ እንዳይነሳ ብቻ ነው ያደረገው። ስለዚህ ይህ ልሂቃን ዛሬ በሽተኛ የቀጨጨ ከወላጆቹ ከአባቶቹ ተለይቶ ምንም ውርስ ግንኙነት ዬሌለው ህጻን ይመስላል።

ለዚህ የልሂቃኑ ችግር ምክንያት ይኢህአዴግ ጭቆና ብቻ ነው? በፍጹም! ቢሆን ኖሮ ቢያንስ በውጭ አገር ኢህአዴግ በማይደርስበት ቦታ ይህ ልሂቃን ጠንክሮ ይገኝ ነበር። ግን የለም። በተጨማሪ የቅንጅት የምርጫ 1997 ቀውስ የተፈጠረው በኢትዮጵያ ብሄርተኛ ልሂቃኑ መሆኑን እናውቃለን። ልሂቃኑ ባለመብሰሉ ምክንያት ያስከተለው የእርስ በርስ ቅራኔ ነው ቅንጅትን ያፈረሰው። ዛሬም አገር ውስጥም ውጭም የቅንጅት ርዥራዞችና ተከታዮቻቸው እየተፋጅን ነው። እነዚህ መረጃዎች ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ልሂቃኑ ድክመት በቂ መረጃ ናቸው።

ስለዚህ የኢህአዴግ ጭቆና ነው የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ልሂቃንን ያደከመው ማለት አይቻልም። ኢህአዴግም ቢጠፋ ይህ ልሂቃን ጠንክሮ ይገኛል ቃልን እራሳችንን ማታለል ነው። የልሂቃኑ ውድቀት ረዝም ዓመት የፈጀ ውስብስብ ታሪክ ነው። በዚህ ረገድ ይህ ልሂቃንን ከሞት ለማስነሳት እንደዚሁ ረዝም ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። አንድ ልሂቃን ጎራ ባንዴ መጎልበት አይቻልም። ግን እስከዛ ብዙሃኑ ልቆ ሄድዋልና መሪ ይፈልጋል።

ስለዚህ ወዴት ነው ማምራት የምንችለው? የጎሳ ብሄርተኝነት እንዲቀንስ፤ ጭቆና ኢፍትሓዊነት፤ የስነ መግባር እጦትና ሙስና በአገራችን እንዳይኖር፤ ፖለቲካና ሌሎች ጉዳዮችን በሰላም የምንወያይበት መድረክ የምንፈልግ ምን እናድርግ? አገራችን ህዝቦቿ በምትወደው በምታከብረው መንግስት እንድትገዛ የምንመኝ ምን እናድርግ? አገር ወዳድ መንግስት የምንፈልግ ምን እናድረግ?

በይፋ ንቅናቄዎች ድርጅቶች ፓርቲዎች ማቋቋም እንደማይሆን ግልጽ ነው! እስር ጽቃይ ሞትም ሊያደርስ ይችላል። በ50 ዓመት እራስ ማጥፋት ዘመቻ ምክንያት የደከመ የተቃዋሚው ልሂቃን እንደዚህ አይነቱን ጭቆና ሊቋቋመው አይችልም። ያለፉት 26 ዓመት ታሪክ ይህን አሳይቶናል። ከዚህ የተለየ የርቀቀ አካሄድ ያስፈልጋል።

ይህ አካሄድ ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ማለትም ኢህአዴግ ውስጥ ገብቶ ውስጥ ሆኖ መታገል ነው። ዛሬ ኢህአዴግ ብቸኛ አቅም ያለው የፖለቲካ መዋቅር ስለሆነ ይህን መዋቅርን ተቆጣጥሮት የለውጥ አጋር ማድረግ ነው ስራችን የሚሆነው።

«አይሆንም» ይላሉ ተስፋ ቆራጮቹ! ህወሓት ይህን መቼም አይፈቅደም ይላሉ በዛው አፋቸው ህወሓት የአገራችን 8% ብቻ ነው የሚወክለው ይላሉ! ግን 8% በጣም ትንሽ ስለሆነ 92% የሆነው ህዝብ ትንሽ ብቃት ቢኖረውም ሁኔታውን ለመቀየር በቂ ነው። እንደ የሩስያ መሪ ቭላዲሚር ፑቲን ከነበረው ሥርዐት ውስጥ ሆነው ማንነታቸውን ደብቀው ሙሉ ስልጣን እስከሚይዙ ፕሬዚደንት ሆኖ ሩሲያን 180 ዲግሬ የቀየራት ኢትዮጵያ ውስጥም እንደዚህ ማድረ ይቻላል። መቼም እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች መሆን ያስፈልጋል! በመጀመርያ ካለው የፖለቲካ አዝማምያ ጋር አብሮ መሄድ ያስፈልጋል። ቀስ በቀስ ራስን ባለማጋለጥ የፖለቲካ ተከታይነትና ኃይል ማከማቸት ያስፈልጋል። በስልጣን ደረጃ ከፍ ባለ ቁጥር ባለው የስልጣን መጠን መጠቀም ፍላጎትን ማስፈጸም ይችላል። በዚሁ ረገድ ህሊና ያለው ሰው የፓርቲውን ፖለቲካ እየተከተለ ሰው ላይ ጉዳት ሳይፈጽም ኢፍትሃዊ ድርጊቶች ሳያደርግ በብልጠት ስራውን መስራት ይችላል። የፖለቲካ ተጎጂዎችንም ሊረዳ ይችላል።

ይህ አይነቱ ስራ ታላቅ የፖለቲካ ብስለትና ሙያ ይጠይቃል ከባድ ስራ ስለሆነ። ግን ለጊዜው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ብቸናው መንገድ ነው። አለበለዛ ቅጭ ብሎ ከእግዚአብሔር መብረቅ መጠበቅ ወይም ህዝባዊ አመጽ መጠበቅ ይሆናል። መቆጣጠር የማይቻል ለአገር ይበልጥ አስጊ የሆነ ችግርን መጠበቅ ይሆናል።

ስለዚህ በኔ አመለካከት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ጥሩ መንገድ ለመምራት ፍላጎት ያላቸው የኢትዮጵያ ብሄርተኛ የሆኑ ግለሰቦች በኢህአዴግ ቀመጠቀም ብዙ አማራጭ የላቸውም። አማራጭ ሊሆን የሚገባው የኢትዮጵያ ብሄርተና ልሂቃን ድርጅት ከ50 ዓመት የራስ ማጥፋት ዘመቻው ገና አልዳነም። ይህ አይነት ድርጅት ወይም ንቅናቄ አጠንክሮ ለማቁቋም እስካሁን አልቻልነውም የረዝም ዓመት ስራ ነው የሚሆነው። ሌሎች አማራጮች እንደ መንግስት ላይ የዓለም አቀፍ ተጽእኖ ማስነሳት ወይም የተቃዋሚ ፓርቲ ማቋቋም እስካሁን አልሰሩምና ውጤታማ አልሆኑም። ስለዚህ ወደ መሳካት የሚችለው ስራ እንግባ፤ ኢህአዴግ ዙርያውን ሰርጎ ገብተን እንቆጣጠረውና በዛ መንገድ ለውጥ እናምጣ።

ቀደም ተከተል

በ«ተቃዋሚዎች» መካከል ስለ አማራ ማንነት አይነቱ ክርር ያለ ጭቅጭቅ ሲነሳ «መጀመሪያ የሁላችንም ጠላት የሆነውን ህወሓትን ከስልጣን መፈንቀል ላይ ተባብረን እናተኩር ፤ ከዛ በኋላ ስለ ሌሎች ጉዳዮች መነጋገር ይቻላል» ይባላል።  ለ27 ዓመት በተደጋጋሚ የሰማነው አሁንም የምንሰማው አባባል ነው።

አዎ ግባችን ህወሓትን ከስልጣን ማውረድ ከሆነ ከማንም ጋር ተባብረን ሌሎች ጉዳዮችንን በሙሉ ዘርግፈን ግባችን ላይ ማተኮር ነው ያለብን። ነገር ግን ይህን ማድረግ አልተቻለም። ለ27 ረዥም ዓመታት አልተቻለም! ተስማምተን ለአላማችን ብለን ተማምነንና ተባብረን አንድ ሆነን መስራት አልቻልንም።

ለምን? ለምን ግባችንን ለመምታት ግድ የሆነውን አንድነት መመስረት አልቻልንም? ያልቻልንበት ምክንያት እኛ «ተቃዋሚዎች» በርካታ የማንስማማባቸው የአገራችን የፖለቲካ ጉዳዮች ስላሉ ነው። በነዚህ ጉዳዮች ስለማንስማማ ተማምነን አብረን መስራት አልቻልንም።

ስለዚህ ይህን ችግር ለመፍታት ቁጭ ብለን መወያየት፣ ጉዳዮቹን ማብሰልሰል፣ መከራከር፤ መስማማት አለብን። ይህን የውይይት ስራችንን እስካሁን በጭራሽ አልሰራንም ማለት ይቻላል። እስካሁን ጊዜአችንን አቅማችንን 95% በኢህአዴግ ማልቀስ 5% በራሳችንን ማጎልበት ነው ያዋልነው! አንድ ላይ መስራት የምንችለው በኢትዮጵያ ያለንን ራዕይ ዙርያ በቂ ውይይታዊ ስራ ካደረግን በኋላ ነው።

ስለዚህ ቀደም ተከተሉ እንደዚህ መሆን አለበት፤ 1ኛ) እርስ በርስ ያለንን ጉዳዮች ተወያይተን ጨምቀን ወደ የምንተመመንበት  የምንስማማበት መድረስ። ይህ ስራ ዓመታት ሊፈጅ ይችላል። 2ኛ) ከዚያ በኋላ የመሰረትነውን መተማመን፣ ስምምነትና አንድነት ተጠቅመን ህወሓትን መፎካከር።

ለማጠቃለል ትኩረታችን ህውሓትን ከስልጣን ማውረድ ከሆነ በመጀመሪያ በመካከላችን አንድነት መፍጠር አለብን። አንድነት ለመፍጠር እርስ በርስ በሁሉም መልኩ እንዳንተማመን፤ እንዳንስማማ እና አንድነት እንዳንፈጥር የሚያደርጉንን ጉዳዮች በደንብ መወያየት አለብን። ከዚያም የገነባነውን አንድነት በመጠቀም ህወሓትን ለማሸነፍ እንችላለን።

ስለዚህ ስለ አማራ ማንነት፤ የጎሳ አስተዳደር፤ የትግል ስልት፤ እና ሌሎች በርካታ የማያስማሙን ወይም ማሻሻል የሚኖሩብን ጉዳዮችን መወያየት ህወሓትን ለማሸነፍ የግድ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ቅድመ ሁኔታ ነው።

እዚህ ላይ ለመጨመር ያህል በኔ እይታ ህወሓትን ከስልጣን ማስወገድ አንደኛ ላማችን ሊሆን አይገባም። አላማችን ሰላም፤ ፍትሕ፤ ፍቅር፤ መልካም አስተዳደር ማምጣት ነው። ሀውሓትንም ማስወገድ የምንፈልገው የነዚህ ተቃራኒ ስለሆነ ነው። ግን ህወሓትን ከስልጣን አባረን የሱን ቢጤ የሆነ መንግስት አንፈልግም። ከላይ የዘረዘርኩት አካሄድ ግን እንደዚህ እንዳይሆን የሚከላከል ነው! ስለ አገራችን ያለንን ራዕይ ላይ ቀድሞ በደምብ ተወያይተን ከተስማማን ከተማመንን አምባገነን ከመካከላችን አምባገነን ሊፈጠር አይችልም አምባገነን የአለመግባባት የአለመስማማት ውጤት ስለሆነ። ስለዚህ ካሁን ወድያ ይህ ዋና ስራችን ላይ እናቶኩር።

Sunday 25 March 2018

ስለ «አማራ» ያከው ውይይት

ስለ አማራ ማንነት ይሆን ወይም በሌላም አርእስት ስነወያይ ነገሮችን በጥራት እንድናይ ለመወያየት ለመከራከር ለመተቻቸት ብቻ ሳይሆን ግብ ለመምታት ከሆነ ከውይይታችን ከአስተሳሰባችን በስተ ጀርባ ዙርያውን ያለውን ሁኔታ አስተሳሰባችን መመልከት አለብን። ይህን ለማድረግ ዘንድ እስቲ እነዚህን ነጥቦች በደምብ እንመልከታቸው።

1. ሁሉም ውይይት "context" (ዐውደ ሁኔታ?) አለው። ዛሬ ያለው ሁኔታ ምንድነው? 60 ዓመት በፉት ይህ ውይይት ይኖር ነበር ቢኖርስ ምን ይመስል ነበር።

2. ለውይይቱ ምን አይነት አመለካከት ርዕዮት ዓለም እምነት ወዘተ ይዘን ነው የምንከራከረው? በጎሰኝነት ("identity") ፒለቱካ እናምናለን? ወይም የአገር ብሄርተኖች ("nationalist") ነን?

3. የምንጠቀምበት ቋንቋ ቃላቶች ምን ትርጉም አላቸው? «ጎሳ» ምንድንደው? «ህዝብ» ምንድነው? «አማራ» ምንድነው? «ማንንነት» ምንድነው?

4. የውይይታችን አላማ ምንድነው? ውይይቱን ማሸነፍ ነው? መስማማት ነው? እውነት ላይ መድረስ ነው?

5. የጠቅላላ አላማችን ምንድነው? ከአገራችን ሽኩቻ አድሎ ኢፍትሃዊነት እንዲጠፋ ሰላምና ፍትህ እንዲኖር ነው? ህወሓትን ከስልጣን ማውረድ ነው? ስልጣን መያዝ ነው? ጥሩ የሚመስለንን ሥርዓትን ማስፈን ነው?

6. ውይይታችን አቋማችን ከህዝቡ ዝንባሌ ጋር በተወሰነ ድረጃ ብቻ ቢሆንም ይሄዳል ወይ? ይህ ታላቅ ጥያቄ ነው። የ«ፌስቡክ» ብቻ ውይይት ነው? የልሂቃን ብቻ ውይይት ነው? የአዲስ አበባ ብቻ ውይይት ነው? የተማሪዎች? ወይም ከብዙኃኑ ምካከል ይህ ጉዳይ እንደ ቁም ነገር ይቆጠር ይሆን?

ሁላችንም እራሳችንን እነዚህን ጥያቄዎች ጠይቀን በአግባቡ መልሰን ነው ፍሬአማ ውይይት ሊኖርን ይሚችለው። 

እስቲ የኔን መልሶች ልስጣችሁ፤

1. ዛሬ የምዕራባዊ የማርክሲዝም የጎሳ ወይም ብሄሮች አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ በደምብ ሰክኗል። በ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ተማሪዎቻችን ወደ ውጭ አገር ትምሕርትቤት ሄድው ያመጡት ርዕዮት ዓለም አገር ውስጥ መሰረት ጥሎ ጭርሽ ህገ መንግስታችንን በክሎታል የፖለቲካ መዋቀራችንን በይኗል። በመሀበረሰብ ደረጀ በፊት ከ«ልሂቃን» ያልወጣ አስተሳሰብ አሁን አማራ ኦሮሞ ሲዳማ ትግሬ ብዙኃኑም ያውቀዋል። ግን በትክክሉ ምንድነው የሚያውቀው? ቋንቋ ነው? «ዘር» ነው? «ቦታ» ነው? ማንነት ነው? የፖለቲካ ክፍል ነው? ብዚህ ዙርያ  የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም አብዛኞቻችን «አማራ» የሚለውን ቃል ድሮ የማንጠቀምበት ዛሬ እንጠቀምበታለን። ድሮ የፖለቲካ ትርጉም ያልነበረው ዛሬ አለው። ዛሬ ሰዎች በአማርነት ይከሰሱበታል። ይወነጀሉበታል። አንዳንዱ አማራ በመሆኔ ተጎጂ ነኝ ብሎ ያስባል። እጨቆናለሁ መብት የለኝም የሚል አለ። ባጭሩ ይህ ሁኔታ ላይ ነው ዛሬ የምንገኘው። 

2. ማንነት የሰው ተፈጥሮ ባህሪ ነው ብዬ አምናለው። በመንደር ካልሆነ በጠቅላይ ግዛት ካልሆነ በጎሳ ካልሆነ በአገር ሁላችንም አንዱ የማንነታችንን ክፍል ይህ ነው። እስቲ አንድ ምሳሌ እናስብ። አንድ ኢትዮጵያዊ አሜሪካ ለ20 ዓመት ኖሮ ዜግነት ተቀብሎ አሜሪካው ነኝ ይላል። ኢትዮጵያዊ ነኝም ይላል። ለምን ኢትዮጵያዊነቱን አይተወውም። ልም ልጆቹን የኢትዮጵያ ቋንቋ ያስተምራል ቢችልም የኢትዮጵያ ትምሕርትቤት ይልካል? ለመሆኑ አሜሪካና ኢትዮጵያ በሆነ ጉዳይ ቢቃረኑ ማንን ይሆን የሚደግፈው? ኢትዮጵያን ቢደፍግ ሌላው አሜሪካዊ ከሃዲ አይለውም ይሆን? ለሌላው አሜሪካዊ «ኢትዮጵያዊ-አመሪካዊ» ማለት ጎሳ ነው። አያችሁ የጎሳ ስሜት እንዴት የተፈጥሮ እንደሆነ። የተፈጥሮ ቢሆንም ብዙ ጎሳዎች ያሉበት አገር ውስት የጎሰኝነት ስሜት ከአገር ብሄርተኝነት ስሜት ከበለጠ የጎሳ ፉክክር ("ethnic competition") በፖለቲካ ምድር ውስጥ ያበዛና ለአገሪቷ ህልውና ለሰላም ለፍትህ አደገኛ ነው ይሚሆነው። ይህን ነው ዛሬ በኢትዮጵያ የምናየው። ይህ ምክነያት የአገር ብሄርተኛ ነኝ። ማለት ለሁላችን ሰላምና ለአገሪቷ ብልጽግና የጎሰኘት ስሜት ከአገር ስሜት በታች መሆን አለበት ብዬ ነው የማምነው። «ኢትዮጵያዊ ነኝ ቀጥሎ ኦሮሞ» ትሩ ነው። «ትግሬ ነኝ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ» ወደ ችግር ይመራል።

3. «ጎሳ» «ህዝብ» «ማንንነት» «አማራ» ለሁላችንም የተለያዩ ትርጉሞች አላቸው። ከላይ እንዳልኩት ለኔ የሰው ልጅ ማንነት ውስጥ አንድ የአገር ወይ ጎሳ ወይ መንደር ወዘተ ክፍል አለ። ስለዚህ ለኔ ይህ የማንነት ክፍል በ«ኢትዮጵያዊነት» ወይም «ኦሮሞነት» ወይም «ኦሮሞ-ኢትዮጵያዊነት» ወይም «ኢትዮጵያ-አማራነት» ወይም «ጎጃምነት» ወይም «አፍሪካነት» ሊሞላ ይችላል። ግን ሰውው «ጎሳ» እና «ህዝብ» እና «አገር» ሲለይ የፖለቲካ አቋምን ነው የሚገልጸው። ለምሳሌ አውሮፓ ከትናንሽ የንጉስ ግዛቶች «ጎሳዎች» ወደ አገሮች ("nation state") ሲቀየር «ጎሳ» የኋላ ቀር ነው ብለው ሰየሙ። ግን በጎስኝነት ዘመን የሚያራምዱት ጥላቻን ጦርነትን አሁን በ«አገር» ደረጃ በከፍ ያለ አቀም አራመዱት! ወደ «አማራ» የምንለው ቃል እንምጣ። የቃላቱ ትርጉም በመቶዎች ዓመታት እነደተቀየሩ ግልጽ ነው። የታሪቅ መጽሐፍቶች የድሮ አጠቃቀም ካሁኑ እንደሚለው ያሳያሉ። በቅርብ ዓመታት እራሱ ለምሳሌ ከሃረር እስከ ሸዋ መካከል «ነባር» ሙስሊም ኦሮሞዎች በቀር ሌላው «ክርስትያን» ነበር የሚባለው። ግን ነገሮች ይቀየራሉ። አሁን ከላይ እንደጠቀስኩት የማርክሲዝም ፖለቲካ ሰፍኖ ሁላችንም አማራ እንላለን ወይም ታግለን እራሳችንን እንቆጥባለን።

4. ስወያይ በተቻለ ቁጥር እውነት ላይ ለመድረስ ነው የምወያየው። አዎን አንድ አንድ ጊዜ ፍተናው ያሸንፈኛልና ትቢት ተሞልቼ ማሸነፍ ፈልጋለው አቋሜ ትክክል ቢሆንም ባይሆንም። ውይም ፈርቼ ወይም ለይሉኝታ መስማማት እፈልጋለሁ ስምምነት በውሸት የተመሰረተ ቢሆንም። ግን ደካማ ወገኔን ትቻ አላማየ እውነት ነው። ባልወደውም። ለምን እውነንት? እውነት ነው ለሁሉም የሚበጀው። አላማ እውነት ነው ማለት ለታክቲክ ወይም ለጊዜያዊ ሰላም ቁስል እስኪድን ወዘተ ተብሎው ዝም አይባልም ወይም አይዋሽም ማለት አይደለም። ገን የመጨረሻ ግቡ እውነት ነው።

5. እኔ ሰላምና ፍትህ ነው የምወደው። (አድሎ ሙስና አይኖር ማለት ፍትህ ይኑር ነው።) ሰው እንዳይጎዳ። ሰው ሌላውን ጉዳ እንዳይባል መጉዳት ከመጎዳት ይበልጥ ጎጂ ነውና። ከዛ ውጭ ማን ይግዛ ምን ሥርዓት ይኖር ግድ የለኝም። እንደ ኦርቶዶክስ ክርስትያንነቴ ወደ ንጉሳዊ አገዛዝ አደላለው ከሰው ወይም ሰዎች ይልቅ እግዚአብሔር መሪ ቢሾም ይሻላል ስለሚመስለኝ። ግን ይህ ሀሳብ ለ«ዘመናዊ» ሰው አይገባውም እንተወው። ለማንኛውም ሰላም ፍቅር ፍትህን የሚያበዛ ትልና ሽኩጫን የሚያሳንስ ሥርዓት ከተባለ ከሞላ ጎደል ምን መምሰል እንዳለበት እናውቃለን። 

6. እውነቱን ለመናገር ይህ ሀአማራ ማንነት ጉዳይ ከዲያስፖራና ፌስቡክ ውች ያን ያህል ትኩረት ያለው አይመስለኝም። በኔ እይታ (በኢህአዴግም ይመስለኛል!) ያለፉት ሶስት አራት ዓመት የህዝብ ተቃውሞ በመጀመርያ ደረጃ አድሎን በተለይ የ«ትግሬ አድሎን» ተመስርቶ ነው። ይህ በአማራ ክልል የተካሄደውን ተቃውሞንም ያካትታል። መፈከሩ ትግሬ አይግዛን ነው እንጂ አማራ ይከበር አይመስለኝም። በግሌ ያየሁት የሰማሁት እንደዚህ ነው። እንደሚመስለኝ ዛሬ አማራ የምንለው ህዝብ አሁንም በጣም ወደ ኢትዮጵያዊነት ያመዝናል ከአማራነት ይልቅ። ነገ አማራ ክልል በንዚን ቢገኝ ለአማራ ክልል ብቻ ይውል የሚል ጥቂት መሰለኝ። ትግሬ ምንም አያገኝ የሚሉ ብዙ ይኖራሉ ያሳዝናል እንጂ። ጥቃት ያመታው ችግር ነው። ግን አብዛኛው አማራ በለጸገች ከማለት ኢትዮጵያ በለጸገች ነው የሚለው።

እሺ በመጨረሻ ለ«ትግሉ» ተብሎ በአማራነት መታገሉ አይሻልም ወይ የሚለው ከመምህር ሐዚም አስራት ወልደየስ ዘመን ጀምሮ ያለ ጥያቄ አለ። ያኔ አልሰራም ከላይ እንደጠቀስኩት «አማራ» የሚባለው ስሜቱ ከአማራነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነት እጅግ ስለሚበልት። አናሳ ብሄርም ስላልሆነ። የተጭቋኝ ስሜትም ስላልነበረው። ዛሬ ሁኔታው ጠቀይሯል በተወሰነ ደረጃ ግን አሁን ስኬታማ የ«አማራ የጎሳ» ትግል ለማካሄድ የህዝቡ ሁኔታ የሚፈቅድ አይመስለኝም።

እውነት ነው እንደዚህ አይነቱ ትግል ያስጎመዣል። እነ ሻዕብያ ህወሓት ኦነግ እንዳረጉት ስኬታማ ትግል ማድረግ ነው። የጎሳን የተፈጥሮ የማሰባሰብ ኃይል መጠቀም ነው። ግን ሁኔታው ካልፈቀደ ህዝቡ ማንነቱ ከዚ አይነት አስተሳሰብ ጋር የማይሄድ ከሆነ አሁንም አይሳካም። ሰከን ብሎ ማሰብ ነው።

በመጨረሻ ላስታውሳችሁ የምወደው ምሳሌዎቹ ወይም "template" የሆኑት እነ ሻዕብያ ህወሓት እጅግ አናሳ ስለሆኑ ለማሸነፍ ጎሰኝነትን ግድ መጠቀም አለብን ብለው ያምኑ ነበር። ግን እስካማውቀው ኢ-ህወሓት የሆንነው ወይም «ተቃዋሚ» የሆንነው የአገሪቷ 90% ወይም 80% ወይም 70% ነን። የጎሰኝነት የፖለቲካ ኃይል መሰብሰብያ "ethnic leverage" አስፈላጊ ነው ልንል አይገባም። ትንሽ የፖልቲካ ብስለት ትብብር አብሮ መስራት መተማመን ጉዳዩን ትላንት ይጨርሰው ነበር።

Thursday 22 March 2018

የመሬት ፖሊሲ በጸንፈኛ ፖለቲከኞቻችን እጅ

English version: https://asfawdarguemeshal.blogspot.ca/2017/05/our-radical-politicians-land-to-ruler.html

በቅርብ ጊዜ ከዚህ ዓለም የተለዩት የኃይለ ሥላሴ የህግ አማካሪ የነበሩት ተሾመ ገብረማርያም በቃለ ምልልስ እነዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፤ «መሬት ለአራሹ» ነበር ያልነው፤ «መሬት ለመንግስት» ሆኖ ቀረ። የ«መሬት ለአራሹ» የሚባለው ፖሊሲ አላማው ከባላባት «ተከራይቶ» የሚያርሰውን መሬት ለጪሰኛው መስጠትና የመረቱ ባለቤት ማድረግ ነበር። የኃይለ ሥላሴ መንግስት ይህን ፖሊሲ ለማጽደቅ ቢሞክር በፖለቲካ በፍትህ በአፈጻጸም ደረጃ ችግሮች ያጋጥሙት ነበር። ሆኖም ለነበረው ኢፍትሃዊ ሥርዓትና ከነበረው የገበሬውችግር አንጻር ይህ «መሬት ለአራሹ» ፖሊሲ ትክክል ተገቢ አስተዋይና መጠነኛ እርምጃ ይሆን ነበር። በተቃራኒው ከደርግ ጀምሮ የዋለው «መሬት ለመንግስት» ፖሊሲ የመሬት ባለቤትነት ሙሉ በሙሉ ለመንግስት ማስተላለፉ ለነበረው የመሬትችግር የከረረና ጸንፈኛ መልሰ ነበር። የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን ተገቢውን መጠነኛውን እርምጃ ከመውሰድ አክራሪና ጸንፈኛውን እርምጃ ወሰዱ።

የሚያሳዝነው ነገር በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን ታሪቅ ልሂቃኖቻችን በቁልፍ ጊዜዎች በተደጋጋሚ ወደ ጸንፍ ማድላታቸው ነው። በተለይ የኃይለ ሥላሴ «ልጆች» የሆኑት በሳቸው ጊዜ ከ1950 ወዲህ የቀለም ትምሕርት የተማሩት ልሂቃን በተደጋጋሚ ጸንፈኛ የፖለቲካ ውሳኔዎች በመወሰን አገራችንን ወደ ከባድ ያልተጠበቁ አደጎች መርተዋታል። ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ለነዚህ አጉል ውሳኔዎች  ዋጋ እየከፈለች ነው።

ከዚህ ጽሁፍ የኢትዮጵያን ህዝብ የጎዳው እስካሁንም እያሰቃየው ያለው የመሬት ባለቤትን መንግስት ያደረገው የፖሊሲ ውሳኔን እንመልከት። ይህ ፖሊሲ ባጭሩ ስድስት ችግሮች ፈጥሯል አባብሷል፡

1. የህዝብ ቁጥርን ባልተጠበቀና በኢተፈትሮ ሁኔታ መናር
2. አሁን ያለውን ታላቅ የገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት
3. ዝቅተኛ «የሰው አቅም» (human capital) በትለይ የግብርና ሙያ በገጠር ቦታዎች
4. ዝቅተኛ የእርሻ ምርት መጠን
5. ከፍተኛ የእህል የምግባ ዋጋ ግሽበት
6. የምግብ ዋስትና እጥሮትና ረኃብ

እነዚህ ችግሮች እንዴት ተፈጠሩ? በመጀመርያ መሬት የመንግስት መደረጉ ገበሬዎች መሬታቸውን መሸጥ መለወጥ ስለከለከላቸው የገጥር ህዝብን ከሞላ ጎደል እስረኛ አድርጓቸዋል። ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው ወደ ከተማ መዘዋወር እንዳይችሉ ከልክሏቸዋል። ይህ እንዴት እንደሆነ በምሳሌ ላስረዳ።

ዐምዴ የሚባል አንድ ገበሬ በ1968 በቂ የሆነ ወደ ሰባት ሄክታር የሚሆን እርሻ ነበረው። ዐምዴ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ከተማ መዘዋወር ይፈልጋል። ግን ይህን ለማድረግ የመቋቋምያና ስራ መጀመርያ ገንዘብ ያስፈልገዋል። ይህን ገንዘብ ለማግኘት መሬቱን በሙሉ ወይም በከፊል መሸጥ አለበት መሬቱ ዋና ንብረቱ ስለሆነ። ያኔም አሁንም የኢትዮጵያ ገበሬዎች ከመሬታቸው ሌላ ብዙ ዋጋ ያለው ንብረቶች የላቸውም።

ግን የዐምዴ መሬት የመንግስት ነው ተብሎ ስለተሰየመ መሸጥ መለወጥ በሱ መበደርም አይችልም። ስለዚህ ለከተማ ኑሮ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት አልቻለም። በተጨማሪ መሬቱን ትቶ ቢሄድ ደግሞ ይወሰድበታል። ስለዚህ በተዘዋዋሪ ዐምዴ ወደ ከተመ መዘዋወር እንዳይችል ተከለከለ ማለት ነው። 1) መሬቱን ሽጦ ወደ ከተማ ለመሄድ ገንዘብ ማግኘት አይችልም። 2) እንደምንም አድርጎ ገንዘብ አግኝቶ ቢሄድም ሀሳቡን ቀይሮ ልመለስ ቢል ምሬቱ ተወስዶበት ነው የሚያገኘው! ይህን ሁሉ ስለሚያውቅ ዐምዴ ወደ ከተማ መሄድን አያስበውም። ሌሎቹም የኢትዮጵያ ገበሬዎች እንደ ዐምዴ ከተማ መሄድ ቢፈልጉም ገጠር ቁች ብለዋል። በዚህ የመሬት ፖሊሲ ምክነያት ከ1975 እስከ ቅርቡ ጊዜ ገበሬዎች በሚገባው ቁጥር ወደ ከተማ አልፈለሱም።

በዐምዴ ታሪክ እንቀጥልና የለት ኑሮው እንዴት ነበር ብለን እንጠይቅ። እንደ አብዛኛው የገጠር ነዋሪ ዐምዴ ብዙ ልጆች ወልዷል። ሰባት ልጆች ወልዷል። በ2000ዓ.ም. በገጠር የሚኖሩ ሴቶች በአማካኝ 6.5 ልጆች ነበር የሚወልዱት በአዲስ አበባ 2.2 ነበር። ይህ በከተማና በገጠር ያለው የልጅ መውለድ መጠን ልዩነት ዓለም አቀፍ ያለ ነው፤ የገጠር በአንጻሩ ብዙ ይወልዳል የከተማ አይወልድም። ደሃ ባንጻሩ ብዙ ይወልዳል ሃብታም አይወልድም። ይህ ዓለም በሙሉ የሚታይ ሁኔታ ነው።

የዐምዴ ልጆች ሲያድጉ መሬቱን ከፋፍሎ ለእያንዳንዳቸው አንድ ሄክታር አወረሰ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ልጆቹም እያንዳንዳቸው ሰባት ልጆች ወለዱና አንድ ሄክታር መሬቶቻቸው ጠበቡ። ይህ ችግር በአገር አቀፍ ደረጃ እየባሰ ሄዷል። ዛሬ በኢትዮጵያ የአማካኝ የእርሻ ይዞታ ከአንድ ሄክታር በታች ነው። የገጠር መሬት ተጨናንቋል።

በ1968 የመሬት አዋጁ ሲታወጅ ከ28 ሚሊዮን የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ 85% የገጠር ነዋሪ ነበር። 40 ዓመት በኋላ በ2008 ከ97 ሚሊዮን ጠቅላላ የህዝብ ቁጥር 80% በገጠር ይኖራል። በ40 ዓመት በገጠር የሚኖረው የህዝብ መጠን ከ85% ወደ 80% በአምስት ብቻ ነው የቀነሰው። ግን የገጠር ነዋሪዎች ከላይ እንደጠቀስኩት በአማካኝ 6.5 ልጅ ስለሚወልዱ ጠቅላላ የገጠር የህዝብ ቁጥር ናረ። ለምን? ለ40 ዓመት ገበሬዎች ሲፈልጉ መሬታቸውን ሽጠው ወደ ከተማ መዘዋወር ስላልቻሉ ከሚገባው በታች ቁጥር ነው ወደ ከተማ የፈለሰው። የመሬቱ ፖሊሲ ባይኖር ኖሮ የገጠሩ ሰው ዓለም ዙርያ እንደሚታየው በራሱ በተፈጥሮና በነፃነት መንገድ ቀስ በቀስ ውደ ከተማ ይፈልስ ነበር። ይህ የተፈጥሮ መጠነኛ ፍልሰት በመሬት ፖሊሲው ምክነያት ባይታገድ ኖሮ የገጥር የህዝብ ቁጥር ዛሬ ከ80% ፋንታ ምናልባት ወደ 65% ወይም ከዛም ዝቅ ብሎ ይወርድ ነበር።

በዚህ መልክ የገጠሩ የህዝብ ቁጥር ቅስ በቅስ እየወረደ ቢሄድ የከተማ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ የአገሪቷ የጠቅላላ የህዝብ ቁጥር እንዳሁኑ አይንርም ነበር። ምክነያቱ የከተማ ሰው እንደ ገጠሬው ያህል አይወልድም። በዐምዴ ምሳሌ ከቀጠልን ወደ ከተመ ቢዘዋወር ኖሮ ልጆቹ እያንዳንዳቸው ሰባት ልጆች ከሚወልዱ ከተማ ስለሚኖሩ እንደሌሎች የከተማ ነዋሪዎች ሁለት ይወልዱ ነበር። ግን ወደ ከተማ እንዳይመጣ «ተከልክሎ» ዐምዴ ከገጠር ታስሮ ቆየ። በዐምዴ ምሳሌ እንደምናየው ይህ «የገጠር እስርቤት» መተንፈስ ስላልቻለ የህዝብ ቁጥሩ በ40 ዓመት ከ24 ሚሊዮን ወደ 77 ሚሊዮን ገባ። ይህ የገጠር/ከተማ የህዝብ መጠን አላግባብ ከፍ ያለ በመሆኑ ነው የኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር በኢተፈጥሮ መንገድ የናረው እስካሁን የሚንረው።

ወደ ዐምዴ ቤተሰብ እንመለስ። ልጆቹ እያንዳንዳቸው ሰባት ልጆች ወልደው የአንድ ሄክታር መሬታቸውን ለሰባቱ መከፋፈል አይችሉም አንድ ሰባተኛ ሄክታር ለአንድ ቤተሰብን በቂ ስላልሆነ። ስለዚህ መሬታቸውን ለአንድ ልጃቸው ያወርሱትና ሌሎቹ ስድስት ልጆቻቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ጨርሰው ግድ ወደ ከተመ መዘዋወር ይኖርባቸዋል። አሁን በአገራችን የምናየው ሁኔታ ይህ ነው። የጠበቅነው ግን መንግስቶቻችን ችላ ያሉት የመሬት መጥበብ ደርሷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎች ለአንድ ወራሽ ብቻ የሚበቃ መሬት ነው ያላቸውና ሌሎች ልጆቻቸው ወደ ከተማ እየፈለሱ ነው። አሁን ያለውን ታላቅ የገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት ይህ ነው ምክነያቱ። ለ40 ዓመት የተጠራቀመ ፍልሰት ነው አሁን ባንዴ የሚታየው። ግና ይቀጥላል።

ከዐምዴ ጋር እንቀጥል። ዐምዴ እግዚአብሔር ይባርከው እንጂ ጎበዝ ገበሬ አይደለም። ሙያውም ፍላጎቱም የለውም ግን ቤተሰቡን ለማስተዳደር ብሎ ያርሳል። ጎረቤቱ ገመቹ ግን እጅግ ጎበዝ ገበሬ ነው። የግብርና ንግዱን ማስፋፋት ይፈልጋል። ግን በመሬት ፖሊሲው ምክነያት እንዴት አድርጎ ተጨማሪ መሬት ይግዛ። ዐምዴ በደስታ መሬቱን ይሸጥለት ነበር ገመቹም ችሎታውን ተማምኖ ጥሩ ዋጋ ይሰጠው ነበር ግን አይፈቀድም። ስለዚህ የሚፈቀደውን አደረጉ ገመቹ ከዐምዴ የተወሰነ መሬት በየዓመቱ እየተከራየ ማረስ ጀመረ። ገመቹ ጉድጓድ መቆፈር ዛፍ መትከልና ተመሳሳይ የረዥም እቅድ ስራዎችና ኢንቬስትሜንቶች ማድረግ ይፈልጋል ግን መሬቱ የሱ ስላልሆነ ኪራዩም በየዓመቱ የሚታደስ ስለሆነ ስለረዥም እቅዶች ማሰብ አይችልም። ገመቹ ከሌሎች ጎረቤቶቹ ተጨማሪ መሬት ገዝቶ ስራውን አስፋፍቶ ምናልባት በትራክተር ማረስ፤ ሙያውንም ማዳበር፤ ስለ ፍራፍሬ ማምረት መማር፤ ወዘተ ያልማል። ግን ችሎታ ቢኖረውም በመሬት ፖሊሲው ምክነያት ምኞቶቹን በተግባር መዋል አልቻለም።

ገመቹ ከዐምዴ በተከራየው መሬት 20 ኪንታል በሄክታር ጠፍ ያመርታል። ዐምዴ 10 ነበር የሚያመርተው። ገመቹ የዐምዴ መሬት ሙሉ በሙሉ ሰባቱንም ሄክታር ገዝቶ ጠፍ ቢተክልበት ኖሮ በዐምዴ 70 ኪንታል የሚያበቅለው መሬት በገመቹ እጅ 140 ኪንታል ያበቅል ነበር። የአካባቢው የምርት መጠን ይጨምር ነበር። ገመቹ ደግሞ የሚያገኘውን ትርፍ ተጠቅሞ መሬቱ ላይ ኢንቬስት አድርጎ የግብርና ንግዱን የምርት መጠኑን ይበልጥ ያሻሽል ነበር። የአካባቢው የጠፍ ምርት ይጨምር ነበር የጤፍ ዋጋ ደግሞ ይቀንስ ነበር። ዐምዴ ከተማ ገብቶ ጠፍ በመጠነኛ ዋጋ ያገኝ ነበር።

ገመቹ ላይ የደረሰው የስራ ክለላ ወይም የማስፋፈትና ማደግ ክለላ የኢትዮጵያ መንግስታት በአገሪቷ ገበሬዎች ላይ ያሳደሩት አሳዛኝ ድርጊት ነው። ገበሬዎች ስራቸውን እርሻቸውን ንግዳቸውን እንዳያሰፋፉ በማገድ መንግስት የገበሬዎቻችን «የሰው አቅም» (human capital) አፍነዋል። ይህ የኤኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የሥነ ልቦና የፖለቲካ የማኅበራዊ ተጽዕኖ ገበሬዎች ላይ አሳድሯል። ከሁሉም የግል ነጋዲዎች ተለይተው ገበሬዎች ነፃነት እንዳይኖራቸው ንግዳቸውን ማስፋፋት እንዳይችሉ ተደርገዋል። በዚህ ምክነያት በሙያ ችሎታም በሙያ ትምሕርትም እንዳይሻሻሉ ተደርገዋል። እንደነበሩት እንዲቆዩ ተደርገዋል። እስቲ አንድ ሜካኒክ ስራውን ንግዱን ከማስፋፋት በህግ ቢከልከል እናስበው። ከአንድ መኪና በላይ የሚችል ቦታ ሊኖርህ አይችልም ቢባል። ይህ ሜካኒክ መቼም የችሎታውን አቅም ሳያሟላ ይቆያል። ወይም አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር ስራ መቀየር አትችልም ከአንድ ርዕስ ውጪ ጥናት ማካሄድ አትችልም ቢባል። ይህ መምህር በሙያው የተም አይደርስምና እራሱን ለማሻሻል አይጥርም። ስራውም እየሰለቸው ይሄዳል። ስለዚህ የመሬት ፖሊሲው ለገበሬዎች ኮምዩኒዝም ለሌሎች ካፒታሊዝም ነው ያደነገገው።

ይባስ ተብሎ መንግስቶቻችን የመንግስት ያልሆኑት ድርጅቶችም (ንጂኦ) ገበሬዎችን ወደታች አድርገው በንቀት ይመለከታሉ። እንደ ሞግዚት የሚያስፈልጋቸው ደንቆሮች ያይዋቸዋል። ከላይ እንዳልኩት ይህ የሆነው ገበሬዎች አቅማቸውን እውቀታቸውን ከማሻሻል ስለተገደቡ ነው። መንግስት እራሱ በነፃነት እንዳይሰሩ ስለከለከላቸው ነው። እንደ ጥሩ ኮምዩኒስቶች መንግስት ዋናውን የምርት ግበዓት የሆነውን መሬት አፍኖ ሌሎችን ግብአቶች እንደ ምርጥ ዘር ማዳበርያ ተባይና አረም ምጥፍያ የ«ኤክስቴንሽን» ትምሕርት ወዘተ በመጨመር የአገሪቷ የምርት መጠንን መጨመር ሞከረ። ግን አልሰራም።

ዛሬም በኢትዮጵያ የሰብል መርት በሄክታር ዝቅተኛ ነው። የምግብ ዋጋ ከሌሎች ታዳጊ ዓገሮች ውድ ነው። ወተት እንቁላል ቂቤ ሥጋ ማር ከአደጉ አገሮች ይልቅ ኢትዮጵያ ይወደዳሉ። የሰብል ዋጋ ውድ ቢሆንም የግብርና የንግድ ክፍል ተስፋፍቶ ያለውን ፍላጎት በአግባብ ማስተናገድ አልቻለም። ፈላጊ እየበዛ ሲሄድ አቅራቢ በቂ ማቅረብ አቅቶታል። ገበሬው ኢንቬስት ማድረግ አልቻለም። ለዚህ ነው የእህል የምግባ የዋጋ ግሽበቱ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሆነውና መንግስትን የሚያስጨንቀው።

ወደ ዐምዴ እንመለስ… ኢትዮጵያ በ10 ዓመት አንዴ የሚደርስባት ድርቅ መጥቶ የዐምዴ ልጆች በአንድ ሄክታሮቻቸው በጣም አነስተኛ መርት ያገኛሉ። ዐምዴ ሰባቱን ሄክታር በሚያአርስበት ጊዜ ድርቅ ቢኖርም የሰባት ሄክታሩ ምርት ብዙ ስለነበር ለድርቅ ጊዜ በቂ የተከማቸ እህል ነበረው። አሁን ግን የዐምዴ ልጆች በአንድ ሄክታር እጅ ወደ አፍ ስለሚኖሩ የአንድ ዓመት ምርታቸው ከቀነሰ በቂ አይኖራቸውም። ስለዚህ ሰባቱም የዐምዴ ልጆችና ቤተሰቦቻቸው ወደ ምግብ እርዳታ ተሸጋሸጉ።

ታሪኩ በዚ ይጠቃለላል፤ የህዝብ ቁጥርን ባልተጠበቀና በኢተፈትሮ ሁኔታ መናር አሁን ያለውን ታላቅ የገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት ዝቅተኛ «የሰው አቅም» (human capital) በትለይ የግብርና ሙያ በገጠር ቦታዎች ዝቅተኛ የእርሻ ምርት መጠን ከፍተኛ የእህል የምግባ ዋጋ ግሽበት የምግብ ዋስትና እጥሮትና ረኃብ። ሁሉም ችግሮች ብያንስ በከፊሉ የ1968 የመሬት አዋጁ ውጤቶች።

የዚህ ፖሊሲ ጎጂ ውጤቶች ያልበሰሉ ጸንፈኛ የፖለቲካ ልሂቃን በችኩልነታቸው አገሪቷ ላይ ሊያመጡ የሚችሉትን ጉዳት ያሳያል። ከጽንፈኝነት መካከለኛውን መንገድ መያዝ ይሻላል። የዛሬም ግዥዎቻችን ከዚህና ሌሎች ታሪኮች ተምረው ሌላውን ጸንፈኛ የአገራችን ፖሊሲ የጎሳ አስተዳደርን እንደገና ቢያስቡበት ይሻላል።

Wednesday 21 March 2018

«ሴኩላሪዝም»

ትንሽ አመታት በፊት አንድ የመንግስት ስራተኛ የሆነ ዘመዴ የኦርቶዶክስ መዝሙር ከመስሪያቤት ኮምፕዩተሩ ላይ ማዳመጥ ክልክል እንደተደረገ ነገረኝ። ለምን ብዬ ስጠይቀው ክርስትያኑም ሙስሊሙም የሚፈልገውን መዝሙር፤ ስብከት፤ ትምሕርት እያዳመጠ እና ኮምፕዩተሩ ላይ ሥዕል እየለጠፈ የሰራተኞች እርስ በርስ ግጭት ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ተከለከለ አለኝ። የሚገርመው ነገር ግን 1) ከመስሪያቤቱ እንደዚህ አይነት ግጭቶች አልነበሩም እና 2) ክልከላው በተራ ትዛዝ ሳይሆን ከከፍ ያለ የአስተዳደር ደረጃ በመመርያ ምልክ የተላለፈ ነበር። የመመርያው ርዕስ ደግሞ «ሴኩላሪዝም» ነበር።

ይህን ታሪክ ስሰማ እጅግ አዘንኩኝ። መቼ ነው መንግስቶቻችን፤ ምሁሮቻችን እና ልሂቆቻችን የምዕራብ ዓለም ርዕዮት ዓለምና ፍልስፍና ይዘው አገራችን ላይ መጫን የሚያቆሙት? ካለፉት የ100 ዓመታት ታሪካችን አይማሩምን?

እስቲ «ሴኩላሪዝም» ባጭሩ ምን እንደሆነ እንመልከት። «ሴኩላሪዝም በዓለማችን እግዚአብሔር የለም/አይሳተፍም ብሎ ማሰብ ነው»። ሴኩላሪዝም እግዚህብሔር ሊኖር ላይኖርም ይችላል ግን ከዓለማችን ከሕይወታችን ከለት ኑሮአችንም አይሳተፍም የሚለው አመለካከት ነው። እግዚአብሔር ካለ እዛው ከዙፋኑ ወይንም ገነቱ ተቀምጦ ይመለከተናል። በሃይማኖት እና በእግዚአብሔር በግል ምርጫችን ልናምንባቸው የምንችል የእምነት ሥርዓቶች ናቸው። በሀሳብ ደረጃ ነው የምናምንባቸው ካላሰኘን ደግሞ ከሀሳባችን እናስወግዳቸዋለን!

ይህ አስተሳሰብ በተለያየ መንገድ ወደ ክርስትያን የሆነውን አስተሳሰብ ገብቷል። «ዓለማዊ» እና «መንፋሳዊ» የምንላቸው ቃላት በተሳሳተ መንገድ እንጠቀማለን። ዓለማዊ ስንል ስራችን፤ ትምሕርታችን፤ ገበያችን፤ ንግዳችን ወዘተ ነው። እግዚአብሔር እነዚ ነገሮች ውስጥ እንዳለ አናምንም። ስለዚህም ነው በነዚህ የህይወት ዘርፎቻችን ኢ-ክርስትያናዊ ነገሮች እያደረግን እያለን አማኞች ነን የምንለው። እሁድ እሁድ ግን ቤተ ክርስትያን ሄደን ወደ መንፈሳዊስ ዓለም እንሸጋገራለን። እዛ ጨዋ ነን፤ ጥሩ ስነ መግባር አለን፤ ጭንቀቶቻችንን አስተንፍሰን ወደ ዓለማችን እንመለሳለን።

ይህ ግን የውሸት ክርስትና ነው። በእምነታችን እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ በሁሉም ነገር አለ። «እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም። ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር።» ኤር 23:23-24።

ስለዚህ ትምሕርት ቤት ብሄድ፤ መስሪያ ቦታ ብሄድ፤ እርሻዬ ላይ ብሆን፤ ትራንስፖርት ላይ ብሆን፤ መጠጥ ቤት ብሄድ፤ በሁሉም ቦታ እግዚአብሔር አለ። ሕይወታችንን እግዚአብሔር ያለበትና የሌለበት ብለን ልንከፋፍለው አንችልም። በሁሉም ቦታ በሁሉ ደቂቃ ከኛ ጋር ነውና።

ይህ የሚያሳየን የሰው ልጅ ክርስትያንም ሴኩላሪስትም አብሮ ሊሆን አይችልም። ብዙዎቻችን ወደዚህ ስህተት ብንገባም ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ለክርስትያኖች እግዚአብሔር ልኬት የለውምና። በተጨማሪ ሴኩላሪዝም እግዚአብሔርን ከለት ኑሮአችን ማጥፋት ስለሚፈልግ የክርስትና ተቃራኒ ብቻ ሳይሆን ጠላት እንደሆነ ግልጽ ነው።

«እናንተ ኦርቶዶክሶች፤ ሙስሊሞች፤ ፕሮቴስታንቶች አብሮ መኖር አትችሉም። ስለዚህም (እግዚአብሔራን ተክቼ!) ከላያችሁ ሆኜ አስተዳድራችኋለሁ» ይላል ሴኩላሪዝም / ሴኩላሪስቱ። «እኔ ነኝ ስልጡኑ፤ ከማንም ጋር የማልጋጨው፤ ከሁሉም ጋር የምግባባው፤ ሁሉንም የማከብረው» ይላል። እውነቱ ግን ሴኩላሪስቱ እንደዚህ ሲል ሁሉንም በሰላም ለመጠበቅ ሳይሆን አላማው ይህን አስመስሎ «እግዚአብሔር የለም» የሚባለውን ሃይማኖትን ለማስፋፋት ነው። እግዚአብሔር ከአዕምሮአችን ብቻ ነው ያለው እንጂ ከስራ ቦታችን፤ ገበያ ቦታችን፤ መንገዶቻችን፤ ሚዲያዎቻችን፤ ከለት ኑሮአችን የለም ብለን ካመንን ቀጥሎ እግዚአብሔር የትም የለም ማለት የሚቀጥለው ቀላል እርምጃ ነውና!

በተጨማሪ እግዚአብሔር ከለት ኑሮአችን ከሌለ የማህበረሰብ የአገራችን ድንጋጌዎች ከየት ሊመጡ ነው? ከሴኩላሪዝም ርዕዮት ዓለም ከ«እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖት ሊመጡ ነው! አያችሁ ሴኩላሪዝም እራሱን ገለልተኛ አድርጎ እንዴት «እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖትን ሰተት ብሎ እንደሚያሰፍን።

ኢትዮጵያ የሃይማኖት አገር ናት። ታሪካችን ትውፊታችን ከዚህ የተያያዘ ነው። ማንነታችን ይህ ነው። ሴኩላሪዝም ደግሞ የህን አፍርሶ «እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖትን ነው ማስፈን የሚፈልገው። ይህ ሂደት እንዴት እንደሚሰራ ለማወቅ የምዕራብ ዓለሙን ያለፈውን 400 መቶ ዓመት ታሪክ መመልከት ነው። ስለዚህ ሴኩላሪዝም ኢ-ኢትይጵያዊ እንደሆነ ተረድተን ወደ አገራችን ሰተት ብሎ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን። በተለይ ደግሞ ወደ ልባችን ሰተት ብሎ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን።

የፖለቲካ ውይይት ስልት፤ «ከጠንካራ ወገኑ ተሟገት»

የኛ የ«ተቃዋሚዎች» የፖለቲካ ችሎታችን፤ ብስለታችን፤ አቅማችን ምን ያህል ደካማ መሆኑን የቅንጅት ታሪክ አጉልቶ ካሳየን 12 ዓመት አልፎታል። አሁንም ደካማ ነን። ብዙኃኑ ንሯል ልሂቃኑ ኋላ ቀርቷል። ምክንያቱ ፖለቲካችንን ለማጠናከር የሚያስፈልጉን ባህሪዎች እንደ መወያየት፤ መተባበር፤ መተማመን፤ መስማማት፤ አብሮ መስራት፤ ቅራኔን መፍታት ወዘተ አሁንም ይጎሉናል። ይህ ጉድለት ነው ለሰላምና ፍትህ ትግላችን ዋና እንቅፋት የሆነው።

ዛሬ በነዚህ ዙርያ አንድ ነጥብ ላይ ማተኮር እወዳለው። ውይይት ሙግት ክርክር የፖለቲካም የማንኛውም የህብረት ስራም መሰረት ነው። የውይይት አንዱ አላማ ሀሳቦችን መፈተንና ማጣራት ነው። የትኛው ትክክል እንደሆነ፤ የትኛው የተሳሳተ እንደሆነ፤ የትኛው ጠቃሚ እንደሆነ፤ የትኛው ተጨማሪ መጠናት እንዳለበት፤ ወዘተ።

ስንወያይ የራሳችን ሀሳብ መናገር ብቻ ከሆነ የምናደርገው እና የሌሎችን ሀሳብ በትክክል የማናዳምጥ ከሆነ ውይይቱ ግቡን እንደማይመታ ግልጽ ነው። እያንዳንዳችን የራሳችን ሀሳብ ብቻ ነው ተቀባይነት የሚገባው ከሆነ ሀሳባችን ሊገመገምና ሊጣራ አይችልም ልንስማማም አንችልም። ሀሳቦቻችን ስላልተገመገሙ ደካማ ይሆናሉ ስላልተስማማን አብረን ደካማ ሆነን እንቀራለን። ስለዚህ ተጠንቅቀን የሌሎችን ሀሳብ ብቻ ሳይሆን አመለካከታቸውንም መረዳት አለብን።

እንደዚህ ለማድረግ የተሟጋቾቻችን ወይም የተቃራኒዎቻችን ሀሳቦች «ጠንካራ ወገንን» መመልከት አለብን። የውይይታችን ዓላማ ማሸነፍ ሳይሆን መገምገምና ማጣራት ስለሆነ። አልፎ ተርፎ የተቃራኒአችን ወይም ተሟጋችን አመለካከትና ሀሳብ ልክ እንደሱ አውቀን መከራከር መቻል አለብን። ከጥንት ዘመን እንደሚባለው ተቃራኒውን ወይም ጠላቱን ያላወቀ ይሸነፋል። ማወቅ ማለት ላይ ላዩን አባባሉን ድርጊቱን ማወቅ ሳይሆን ልከንደሱ ማሰብ ምቻል። ይህን የቻለ ሰው የተቃራኒውን ሀሳብና አቋም ከሱ በተሻለ መንገድ ማሳመን ይችላል! ተቃራኒን በደምብ ማወቅ ማለት ይህ ነው። ከዚህ ብኋላ የተቃራኒውን ሀሳብ በትክክል ሊሟገት ሊያሸንፍ ወይም ሊጠቀምበት ይችላል።

ስለዚህ ጉዳይ ከራሴ አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ። ለረዥም ዓመታት ከ«ጎሰኞች» ጋር ስሟገት የራሴ አቋም እውነት ነው ስነ መግባርና ፍትህ የተሞላ ብቸኛ ሀሳብ ነው ብዬ እነሱን አላዳምጥም ነበር። «ጎሰኝነት ዘረኝነት ነው» እያልኩኝ ከዚህ ሳላልፍ እንደመድም ነበር። ለኔ የሙግቴ አላማ እነሱን የራሴን ሀሳብ ማሳመን ብቻ ነበር። አልሰራም።

አንድ ወቅት ማዳመጥ ጀመኩኝ። እስቲ በነሱ ቦታ ሆኜ ላስበው አልኩኝ። እንደነሱ ሆኜ ከራሴ ጋር መሟገት ጀመርኩኝ። እንደዚህ ሳረግ የነሱ አስተሳሰብ አመጣጥና ሀሳብ እይገባኝ ሄደ። የነሱን አቋም ይዤ መከራከር ቻልኩኝ። ይህ የራሴን አቋም እንዳጠራው ጠቀመኝ። እነሱም እንደማዳምጣቸው ሲረዱ እኔንም ማዳመጥ ጀመሩ። መተማመን ጀመርን እንደ ጥላት መተያየት አቆምን። ብዚህ ምክንያት ጎሰኝነትን አሁን ከድሮ ይልቅ በደምብ እረዳለሁ ማለት እችላለሁ። የጎሰኝነትንም አጉል ወገን እንዴት ማስወገድና ማጥፋት እንደሚቻል ይበልጥ የገባኝ ይመስለኛል።

በተዘዋዋሪ ይህን «ማዳመጥ» ወይም ለሰው መቆርቆርና ራስን በሌላው ቦታ ማድረግ የደረስኩበት ከክርስትና ተልእኮአችን ነው። «አትፍረዱ» «ማሩ» «ራሩ» መሰረታዊ የክርስትና ትምሕርቶች ናቸው። አንዱ ታላቅ ቅዱስ ዮሐንስ «ዘመሰላል» እንደዚህ ብለዋል፤
«አስተዋይ ሰው ወይን ሲበላ የበሰሱትን ይበላል ያልበሰሉትን የሚጎመዝዙትን ይተዋል። እንዲሁም አስተዋይ አዕምሮ በማንድ ሰው የሚያየው (ትንሽም) ጥሩነት ተጠንቅቆ ይመዘግባል። አዕምሮ ቢስ የሆነ ድክመትና መጥፎ ባህሪያትን ይፈልግበታል… ሰው ኃጢአት ሲፈጽም በአይንህም ብታይ አትፍረድ፤ አይኖቻችንም ሊታለሉ ይችላሉና።»
ይህን መንገድ የሚከተል የሌሎችን አስተያየትና አመለካከትን አክብሮ በነሱ ቦቶ እራሱን አስቀምጦ ሁኔታውን ይገመግማል። «አትፍረዱ» «ማሩ» «ራሩ» ማለት እራስን በሌላው ቦታ አድርጎ ማሰብ መቻል ነው!

Monday 19 March 2018

ሊዩ ሺያዎቦ፤ የቻይና ህሊና

ሊዩ ሺያዎቦ (Liu Xiaobo) በቅርብ ከዚህ ዓለም የተለዩ የቻይና ምሁር የሰላምና ፍትህ ተቀናቃኝ የመንግስት ተቃዋሚ ነበሩ። ታሪካቸው ለሁላችንም ኢትዮጵያዊያን እጅግ አስተማሪ ነው። ይህ ጽሑፍ ጠቅለል አድርጎ የሊዩን የፖለቲካ ማንነትን በደምብ የሚገልጽ ይመስለኛል።  

ከሊዩ ሺያዎቦ ግንዛቤዎች መካከል አንዱ አትኩረን ማየት ያለብን የሚመስለኝ ስለ ምዕራቡ ዓለምና ምዕራባዊነት የነበራቸው አመለካከት ነው። ሊዩ በመጀመርያ ምዕራባዊነትንና የምዕራብ አገሮችን አጉል ያደንቁ ነበር። የአገራቸውን የፖለቲካ ችግር ከምዕራብ አገሮች «ዴሞክራሲ» «ፍትህ» «ሰላም» እና ጠቅላላ «ስልጣኔ» ሲያነጻጽሩ የምዕራብ አገሮች ገነት የሆኑ ይመስላቸው ነበር።

ግን እንደ ታላቁ ሩሲያዊ አሌክሳንደር ሶልዠኒትሲን ሊዩ አሜሪካን ሲጎበኙ ይህ አመለካከታቸው የተሳሳተ እንደሆነ ተገነዘቡ። የአሜሪካን ችግር ሲያዩ የምዕራብ አገሮች ገነት አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ግነት በምድር መኖር እንደማይቻልም ተገነዘቡ! ምዕራባዊነትንም እንደ ጣዖት ማየት አቆሙ። አገሬ ቻይና እንደ ምዕራብ አገሮች መሆን አለበት ብለው ማሰብ አቆሙ። የራስችንን ችግር በራሳችን መንገድ ማስተካከል አለበን ብለው አሰቡ።
የምዕራብ ስልጣኔን ፍፁም አድርጌ የማየው የነበረው ምክንያት በአገር ወዳድ ስሜቴ ምዕራቡን ዓለም ለቻይና ተሃድሶ አራአያ ትህናለች ብዬ ነው። ግን ይህ አመለካከቴ የምዕራብ ዓለሙን ግድፈቶችን እንዳላይ አድርጎኛል። የምዕራብ ስልጣኔን አጉል አመልክ ነበር መልካምነቱን አጋንኜ ነበር። የራሴን አስተሳሰብን ትክክልነትም አጋንኜ ነበር። ምዕራብ ዓለሙ ቻይናን የሚያድን ብቻ ሳይሆን የዓለም በሙሉ የሰው ልጅ የመጨረሻ ግብ ይመስለኝ ነበር። የዓለም አገሮች በሙሉ እያደጉ ሲሄዱ እንደ ምዕራብ አገሮች እየመሰሉ ይሄዳሉ ብዬ አስብ ነበር። በተጨማሪ ይህን ቅዠታማ አስተያየቴን ይዤ አገሬን አድናለው ቢየ አስብ ነበር። 
አሁን ግን የገባኝ ይህ ነው፤ የምዕራብ ስልጣኔ ቻይና አሁን ባለችበት ሁኔታ ለማደስ ጥሩ ምሳሌዎች ይኖሩታል ግን ዓለምን የሰው ልጅን ሊያድን አይችልም። 
የምዕራብ ስልጣኔን ራቅ ብለን ሰከን ብለን ከተመለከትነው የሰው ልጅ ቀጥንት እስካሁን ያሉትን ችግሮች አሉት።
ለ30 ዓመት በላይ በቻይና አምባገነናዊ ሥርዓት የኖርኩኝ ሆኜ ስለ የሰው ልጅ ማንነትና ዕጣ ማሰብ ከፈለግኩኝና እውነተኛ መሆን ከፈለግኩኝ ሁለት ትንተኖች ማድረግ ይኖርብኛል፤ 
1. የምዕራብ ስልጣኔን ቻይናን ለመተንተን መጠቀም አለብኝ
2. የራሴን የፈጠራ ሃሳቦችን የምዕራብ ዓለምን ለመተቸት መጠቀም አለብኝ
ሊዩ ሺያዎቦ ከጻፉት መጸሐፎች የታወቀው «ጠላት የለኝም ጥላቻም የለኝም» ነው። ሊዩ ለቻይና መሪዎች የኮምዩኒስት ፓርቲ አባሎች እና ሌሎች ገዞች ጥላቻውን አስወገደ። የሃገሩ ሥርዓት ምክንያት እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ ቻይናዊ ሃላፊነት እንዳለበት ተገንዝበው ሁላችንም መቀየር አለብን ንለው ያምኑ ነበር። ስሜትን የሚያስተስት ለፖለቲካ ምቹ ሃሳብ ባይሆንም ትክክለኛው እውነት የሆነ ሃሳብ ነው።

ለዚህ መሰለኝ ሌሎች ይበልጥ የሚጮሁ (የሚለፈልፉ) መንግስትን የሚተቹ የመንግስት ተቃዋሚዎች ሳይታሰሩ ሊዩ ሺያዎቦ እስኪሞቱ የታሰሩት። ሊዩ ሺያዎቦ እውነቱን ደረሱበት። መንስግትን ብቻ ሳይሆን ላለው ሥርዓት ህዝቡንም ሃላፊነት አለው አሉ። ህዝቡ ቢያዳምጣቸው ደግሞ የእውነት ለውጥ እንደሚመጣ መንግስት ያውቃል።

ሊዩ ሺያዎቦ የምዕራብ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለውጥ ለማምጣት አያስፈልጉንም አሉ። የራሳችን ማንነት ስነ መግባር ፍትህ ህሊና ይበቃናል። ሊዩ በየ ምዕራብ መገናኛ ብዙኃን እየዞረ ቃለ ምልልስ አይሰጥም ነበር። ሌሎች ይህን የሚያደርጉ ሳይታሰሩ ታሰረ። የቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ ምን እውነት እንደሆነና ምን አይነት አስተሳሰብ ከስልጣን እንደሚያወርዱ በደምብ ያውቃል። ስለዚህ ሰላማዊው ሊዩ ሺያዎቦ ታሰረና ሞተ። ታላቅ ምሳሌ ናቸው።

Friday 16 March 2018

ስለ ትህትና

እግዚአብሔር ክፉ መናፍስትን የማስወጣት ጸጋ የሰጣቸው አንድ ባሕታዊ ነበሩ። በአንድ ወቅት ጋኔኖቹን የሚያስፈራቸውና ከሰዎች እንዲለቁ የሚያደርጋቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት ፈልገው ጠየቁ።

«ጾም ይሆን?» ብለው አንዱን ጠየቁት።

«እኛ መቼም አንበላም አንጠጣምም» ብሎ ክፉ መንፈሱ መለሰላቸው።

«የለሊት ሙሉ ጸሎት ይሆን?»

«እኛ አንተኛ።»

«ዓለምን ትቶ መመንን?»

«ይህ እንደ ትልቅ ነገር ይቆጠራል። ግን እኛ አብዛኛው ጊዜአችንን በየ በርሃው እየዞርን ነው የምናጠፋው።»

«ታድያ ምንድነው ይዞ ሊቆጣጠራችሁ የሚችለው፤ እባካችሁ ንገሩኝ» ብለው ታላቁ አባት ደግመው ጠየቁ።

ክፉ መንፈሱ በተአምራዊ ኃይል ጥያቄውን እንዲመልስ ተገደደ፤ «ትህትና ነው። ይህን መቼም ልናሸንፍ አንችልምና።»

ቤተክርስቲያን የፈውስ ቦታ ናት

«ወደ ቤተክርስቲያን ግባ እና ከኃጢአትህ ታጠብ። ቤተክርስቲያን የፈውስ ቦታ እንጂ የዳኛ ፍርድ ቤት አይደለችም እና። ወደ ቤተክርስቲያን በመግባትህ አትፈር። ኃጢአት ሰርተህ ንሰሐ ባለመግባትህ ግን እፈር።»

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

Thursday 8 March 2018

ዴሞክራሲ

ስለ ዴሞክራሲ ብዙ ተጽፏል። በንደፈ ሐሳቡ ደረጃ ምንም መጨመር አልፈልግም። በዚህ ጽሁፍ አሁን ባለን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ዙርያ ስለ«ዴሞክራሲ» ያለን አመለካከት ምን ቢሆን ይበጀናል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ነው የምወደው።

እንደ እስክንድር ነጋ አይነቶቹ በርካታ (ጀግና) የነፃነት ታጋዮቻችን የችግራችን መፍትሄ ዴሞክራሲ ነው ይላሉ። በአንድ ወቅት እኔም እንደዚሁ ይመስለኝ ነበር። ግን ጉዳይ ከዛ እጅግ ውስብስብ እንደሆነ ተረድችያለሁ።

ዛሬ ባለን ህገ መንግስትና ጠቅላላ የመንግስታዊ አወቃቀር የነፃ ምርጫ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቢካሄድ ችግሮቻችን ይፈታሉ ብለን እንገመታለን? አሸናፊዎቹ፤ ተሸናፊዎቹ፤ ጦር ሰራዊቱ፤ የክልል መንግስታት ወዘተ ውጤቱን ተቅብለው ተስማምተው ይሰራሉ ብለን መገመት ኢንችላለን? አዲሱም መንግስት ሰላምና ፍትህ ያመጣል ወይም የፓርላማ ስልጣንና ኃይሉን ተጠቅሞ ግፍና ጭቆና ያሰፍን ይሆን? ህገ መንግስቱን ይቀየር የምንለውሳ? በቂ ድምጽ ካለን አናሳ ድምጽ ያላቸውን የራሳችሁ ጉዳይ ብለን በዚህ ድምጽ ኃይል እንቀይረውና አዲስ ህገ መንግስት እንጭንባቸው ይሆን? ዛሬ እነዚህ አይነቶቹ ከባድ ጥያቄዎች ጥሩና የተሟላ መልስ አላቸው ብዬ እርግጠኛ መሆን አልችልም። ለእነዚህ ጥያቄዎች በሚገባው መልስ ሳይኖረን ወደ ዴሞክራሲ የምንለው ምርጫ ከገባን ደግሞ አደጋ ነው የሚሆነው።

ስለዚህ እንደኔ እንደኔ በመጀመርያ ሰፊ ውይይት በተለያዩ ደረጃዎች ያስፈልጋሉ። የዚህ ውይይት ግብ በርካታ ባለጉዳዮቹ ከብዙሃን እስከ ልሂቃን የአገራችን ማንነትና ፖለቲካ ምን መምሰል አለበት በሚለው ጥያቄና መልስ አንድ ገጽ ላይ እንዲሆኑ ነው። ሰፊ ስምምነት እንድውል ነው። አሁን ያለንበት ደረጃ አገር መገንባት ላይ ነው። በህዝቡም በልሂቃኑም የፖለቲካ መተማመንና መሰረታዊ ስምምነት የለምና። ከላይ የጠቀስኳቸው አይነቶች መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎች እንኳን ሊመለሱ አልተጠየቁም አልተወያየንባቸውም። ይህን የውይይት ሂደት ሳንጨርስና መሰረታዊ ስምምነት ላይ ሳንደርስ ወደ ምርጫ መሄድ አደገኛ ይመስለኛል። እንደ ግብጽ፤ ኢራቅ፤ እና ሌሎች ምርጫ ያላቸው ወይም የነበራቸው ግን ሰላምና ፍትህ የሌላቸው አገሮች እንድንሆን አይፈለግምና።

እሺ፤ በርካታና አስፈላጊዎቹ ባለጉዳዮች አንድ ገጽ ላይ መሆናቸውና ስምምነት ላይ መድረሳቸው እንዴት ልናውቅ እንችላለን? አንዱ ዋና ምልክት የሚመስለኝ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በስል ማለት ነው። ጠንከር ያለ ተቃዋሚ ፓርቲ ከሌለ ወይም ፓርቲዎቹ በጎሳ ብቻ የተመሰረቱ ከሆነ ይህ ጥሩ ምልክት አይመስለኝም። ተመሳሳይ የሆኑ አቋም ያላቸው ተቃዋሚዎች የመዋኸድን ሂደት ለማሟለት ብቃት ከሌላቸው ጥሩ ምልክት አይሆንም። ይህን ያልቻሉ እንዴት አብረው መንግስት ይሆናሉ ወይም እንዴት የአስተዳደሩን ህግ ያከብራሉ? የጎሳ ፓሪቲ ብቻ ካለ ደግሞ እንዴት ነው ፖለቲካ ስረአቱ የማይቀረውን የጎሳ ውድድሩን በሰላም ማስተናገድ የሚችለው? አሁንም ከባድ ጥያቄዎች። እንደምናየው ወደ ምርጫ ከመግባታችን በፊት ብዙ ስራ አለ ቀድመሁኔታዎችም መሟላት አለባቸው።

ይህን ካልኩኝ በኋላ እስቲ ይህን ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ ዴሞክራሲ ቢኖር ሰላምና ፍትህ ይኖራል ማለት ነው? እስቲ አንድ አንድ እውነታዎች እንመልከት። በዓለም ታላቅ የሚባለው ዴሞክራሲ አሜሪካ ነው። በጦሩ ኃይል በርካታ የዴሞክራሲ አገርዎች በሰላም እጠብቃለሁ እሸከማለሁ ባይ ነው። ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አሜሪካ ወደ 20 ሚሊዮን ሰዎች በተለያዩ ጦርነቶች ገድሏል ይባላል። አጭር ትዝታ ያለን መቼም ስለ ኢራቅ፤ ሊብያ፤ ሶርያ እናውቃለን። ኢህአዴግ  ከዚህ ጋር ሲወዳደር መለአክ ነው ማለት ይቻላል! ግን አሜሪካ ለኑሮ ጥሩ አገር ነው። ገንዘብ አለ፤ ከሞላ ጎደል ፍትህ አለ፤ የተወሰነ ነፃነት አለ። ሁላችንም ወደዛ ለመሄድ እንሻለን። ግን ገንዘቡ ባይኖር በአሜሪካ ምን ይሆን ነበር?

ምናልባት አውሮፓ ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን ለምን አሜሪካን እንደ ምሳሌ ትጠቀማለህ ትሉ ይሆናል። ሰላማዊዋ ስዊድንሳ? እውንቱን ለመናገር የስዊድን የጦር መሳርያዎች በዓለም ዙርያ ምን ያህል ሰው እንደተገደለ የተቆጠረ አይመስለኝም። ግን ትንሽ አይመስለኝም። ደግሞ ከሳውዲ አራቢያ ያላቸው ጓደኝነታቸው እንዴት ፍቅር የተሞላ ነው?!

ዴሞክራሲ ለሰላምና ፍትህ ሊበጅ ይችላል፤ ይህ ጥያቄ የለውም። ግን ሰላምንና ፍትህን ለማስፈን ሥርዓቱ በራሱ አይበቃም።  ብዙሃኑም ልሂቃኑም ቀድሞ በትወሰኑ መሰረታዊ ጉዳዮችና አስተሳሰብ መስማማት አለባቸው። ከህግና የሂደት ደምብ አስተሳሰብ ይቀድማል። አሰተሳሰቡ ካለ ህጉ ይመጣል በሚገባውም ይተገበራል። ህጉ ካለን አስተሳሰቡ ከሌለ ዋጋ የለውም። ብዙ ነገር በጽሁፍ ላይ የዋለ ህገ ደምቦች ሊካታቱ ይችላሉ ግን አስተሳሰብ በጽሁፍ ሳይሆን በልብ ውስጥ የሚሰክን ባህል ነው መሆን ያለበት። ከዛ በኋላ እንቅፋት ሲያጋጥም ይህ አስተሳሰብ፤ ስምምነትና አንድነት ናቸው ከወረቀት ላይ ከሰፈረው ህግ ይልቅ ወደ መፍትሄ የሚመሩን።

ስለዚህ ዴሞክራሲን እንደ ዋና ግብ ወይንም እንደ ጣዖት አንመልከተው። ዋናው ግብ ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ ነው። እነዚህ እንዲሰፍኑ ዴሞክራሲ አንዱ መሳርያ ሊሆን ይችላል። በዴሞክርሲ ዘንድ ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ ሊሰፍኑ ይችላሉ። ግን ቀድሞ ዝግጅቶች ካልተደረጉ፤ ግባችን እነዚህ እንደሆኑና ዴሞክራሲ መንገድ ወይም ሂደት ባቻ እንደሆነ ካልተረዳን ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ የሌለው ዴሞክራሲ ሊሰፍን ይችላል። እንደዚህ አይነቱ ዴሞክራሲ ደግሞ በበርካታ አገራት ልምድ እንደምናየው አይበጅም።

Monday 5 March 2018

እውነት አማኞች

ስለ ታላቁ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ካህን አባ አርሴኒ በተጻፈው አንዱ መጸሃፍ አቭሴንኮቭ የሚባል ባለ ታሪክ አለ። አባ አርሴንይ ለሁለተኛ ጊዜ ጉላግ የሚባለው የሶቪዬት የሞት እስርቤት ገብተው እያለ የመንግስት ባለስልጣንና ዳኛ የነበረው የኮምዩኒስት ፓርቲ አባል አቭሰንኮቭ ታስሮ ወደሳቸው እሰር ቤት ይገባል። እንዴት እንደ አቭሴንኮቭ አይነቱ ከፍተኛ ባለ ስልጣን ታሰራ። ወቅቱ እንደ የኢትዮጵያ ቀይ ሽብር ነበር። የሰው ስልጣን ወይም ስራ ለመቀማት፤ ሰው በመጠቆም ሹመት ለማግኘት፤ የሚጠሉትን ሰው ለመጉዳት፤ ጥቅም ለማግኘት ወዘተ ምክንያቶች ፖለቲከኞችም ብዙሃንም እርሰ በርስ እየተጠቋቆሙ እስር ቤቶቹንና መቃብሮቹን እየሞሉ ነበር። በዚህ ሂደት በርካታ ባለ ስልጣኖችም ታስረዋል ተገድለዋልም። አቭሴንኮቭ አንዱ ከታሰሩት ነበር

አቭሴንኮቭ ሶቪየቶች «እውነት አማኝ» ኮምዩኒስት ከሚሏቸው አንዱ ነበር። ይህ ማለት በኮምዩኒስም ርዕዮተ ዓለም፤ በፓርቲውና በአስተዳደሩ በእውነት ያምን ነበር። «ባለጥቅም» ከሚባሉት ለስልጣ፤ ለገንዘብ፤ ለሹመት፤ ለጥቅም፤ ሰው በማሰርና በማስጨረስ ብሶቱን ለመወጣት ወዘተ አልነበረም የኮምዩኒስት ፓርቲ አባልና ባለ ስልጣን የሆነው። በእውነት የኮምዩኒዝምን መሰረተ ሐሳቦች ያምን ነበር። ለዚ ለሚያምንበት ርዕዮተ ዓለም ለማሳሰር ለመፍረድና በሞት ፍርድ ለመፍረድ ዝግጁ ነበር።

ግን እንደ ማንኛውም ድርጅት ወይም ፖለቲካ ፓርቲ የኮምዩኒስት ፓርቲም በርካታ «እውነት አማኝ» ያልሆኑ አባላት በበረው። እነዚህ ቅድም እንደጠቀስኩት ለስልጣን፤ ለገንዘብ፤ ብሶት ለመወጣት፤ ጥቅም ለማግኘት ወዘተ ፓርቲ ውስጥ የገቡ ናቸው። አንዱ እንደዚህ አይነቱ የአቭሴንኮቭ የከፍተኛ ዳኛ ስልጣንን ለመቀማት ብሎ ቀስ ብሎ ሴራ ፈጥሮ አቭሴንኮቭን ከስሶ ወደ ጉላግ የሞት እሰርቤት እንዲላክ አደረገ።

አቭሴንኮቭ እስር ቤት እንደገበ መታሰሩን እንደ የአስተዳደር ስህተት ነበር የቆጠረው። በኮምዩኒዝምም በመንግስቱና አስተዳዳሪዎቹና መዋቅሮ እምነቱ እንዳለ ሆኖ በስህተት ነው የታሰርኩትና ከትንሽ ጊዜ በኋላ ስህተቱ ተደርሶበት እፋታለው ብሎ ይጠብቅ ነበር። በእውነት አማኞች ዘንድ ይህ የተለመደ አስተሳሰብ ነበር። የእምነታቸው ጥንካሬ የፓርቲውንና የመንግስቱን መሰረታው ሐሳቦች በጥያቄ ውስት ማድረግ እንዳይችሉ ያረጋቸው ነበር።

ግን አቭሴንኮቭ በእስር ቤቱ በቆየ ቁጥር መቀየር ጀመረ። እንደ አባ አርሴኒ አይነቱን በጸረ አብዮትነት የተሳሩትን ባልደረቦቹን ሲመለከት፤ ስነ መግባራቸው፤ እምነታቸው፤ ትህትናቸው፤ ፍቅራቸውን ሲመለከት ንፁሃን እንደሆኑ ቀስ በቀስ መረዳት ጀመረ። ከእስር ቤት አስተዳዳሪዎችና አዛጆቻቸው የሚመነጨው ክፋትን ሲአይ ደግሞ ያምንበት የነበረውን የፖለቲካ መዋቅሩን መጠራጠር ጀመረ። አቭሴንኮቭ ቀስ በቀስ የመንግስቱንና ርዕዮተ ዓለሙን ክፋት እየተረዳ ሄደ፤ ወደ አባ አርሴኒ አይነቱን እያየ ወደ ክርስትና መለወጥ ጀመረ። መጨረሻ ላይ የአባ አርሴኒ ንሰሀ ልጅ ሆኖ ነበር እድለኛ ሆኖ ከእስር ቤት ሳይሞት የወጣው።

ቅድም እንደጠቀስኩት ማንኛውም የፖለቲካ ሥርዓት ወስጥ እውህነት አማኞችና ባለጥቅሞች አሉ። ሁለቱም አይነቶች አሉ። ብዙዎቻችን እውነት አማኞችን እናከብራለን ባለጥቅሞችንን እንንቃለን። ግን እንደዚህ መሆን አለበትን? ማን ነው በርካታ ጉዳት ሊአይደርስ የሚችለው፤ እውነት አማኙ ወይም ባለ ጥቅሙ? ማን ነው ይበልጥ ክፉ መሆን የሚችለው?

አቭሴንኮቭ ረስቷቸው ነበር እንጂ እሱ ነበር አባ አርሴኒን ፈርዶባቸው ወደ ሞት እስር ቤት የላካቸው። የኮምዩኒዝምና የሶቪዬት ህዝብ ጠላት ናቸው ብሎ። ሌሎችም በርካታ ሰዎችን ወደ እስር ቤትና ሞት ሲልክ ለሚያመልከው ርዕዮተ ዓለም ስለሆነ ሰው መሆናቸው ረስቶ ልቡን ደንድኖ ድርጊቱን በቀላሉ አደረገው። እውነት አማኞች እጅግ አደገኛና ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ። የሚያምኑበት አካዬድ መጥፎ ከሆነ ይህን መጥፎነት በሙሉ እምነትና አቅማቸው ስለሚያራምዱ በርካታ ጉዳት ይፈጽማሉ። እውነት አማኝ በጥሩና ትክክለኛ ነገር ካመነ በጣም ጥሩ ውጤት ይኖረዋል። በመጥፎ ነገር ካመነ ደግሞ መጣም ከባድ ጉዳት ያደርሳል።

ባለጥቅሙ ግን ልቡ በሙሉ ስለማያምንበት የሚፈጽመው ጉዳት አናሳ ሊሆን ይችላል። ከጥሩም ከመጥፎም ወገን ቢሰለፍ ውጤቱ መካከለኛ ነው የሚሆነው። ክፉ ስርዓት ውስጥ ከተሳተፈ የሚያመጣው ጉዳት እንደ እውነት አማኙ ላይሆን ይችላል። ጥሩ ስርዓት ውስጥም ቢሳተፍ ወጤቱ እንደ እውነት አማኙ ያህል አይሆንም።

ስለዚህ እውነት አማኞችን ከባለጥቅሞች ይበልት ልናከበራቸው አይገባም። የአብዛኛው ጸንፈኛ የፖለቲካ ንቅናቄዎች መሰረት ጠንካራ የእውነት አማኝ ቡድን እንደሆነ መርሳት የለብንም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙርያ ከተመለከትን የግራ ርዕዮተ ዓለም ትከታይ የሆነው የተማሪ ንቅናቄ የደረሰበት ደረጃና ያደረሰው ጉዳት አለ እውነት አማኞች አይሆንም ነበር። ላይ ያሉት መሪዎች መካከል በርካታ ባለጥቅሞች ቢኖሩም አለ ጠንካራ የእውነት አማኝ አምድ የትም አይደርሱም ነበር። እነ ህወሓትና ሻብያም የእውነት ዓማኝ አምዳቸው ነው እዚህ ያደረሳቸው አንዳይታደሱም የሚከለክላቸው።

ለኛ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳታፊዎች ይህ ታላቅ ትምህርት ሊሆነን ይገባል። «አምኖበት ነው ያእደረገው» «ለአቋሙ የቆመ ነው» «ፕሪንሲፕለድ ነው» «ለአገር ብሎ ነው ያደረገው» አይነቱን አባባሎቻችንን መተው አለበን። አንድ ሰው የሚያራምደው ርዕዮተ ዓለም ክፋት የሚጎትት ከሆነ እውነት ዓማኝ መሆኑ «ፕሪንሲፕልድ» መሆኑ ምን አይጠቅምም። ጭራሽ ጉዳት ነው። በደምብ ስለሚያምንበት ይበልጥ ጉዳት ያደርሳልና። ዋናው አላማችን በተሳሳተ ርዕዮተ ዓለም ወይም አቋም አለማመን። በተቻለ ቁጥር ማንኛውም ርዕዮተ ዓለም ወይም የፖለቲካ አመለካከት ከሰው በላይ አለማረግ። ዋናው ነገር ሰው ነው። ለሰው የሚያስፈልገው ፍቅርና ፍትህ ነው። ሌላው በሙሉ እነዚህን ማግኛ ዘዴ ነው። የምናምንበት ርዕዮተ ዓለም ጭራሽ ጥላቻና ጉዳት እያደረሰ ካየን የተሳሳተ መሆኑን ቶሎ ተረድተን መተው መቻል አለብን። ጣዖታችን ሊሆን አይገባም። ከኢግዚአብሔር በቀር ለምንም የእውነት አማኞች መሆን የለብንም።

Friday 2 March 2018

የምዕራባዊያን አገራት አምልኮ

የአባቴ ትውልድ የምዕራባዊያን አገሮችን የሚተቹባቸው በርካታ ጉዳዮች ነበሩ። ዘረኛ ናቸው። ታላቂቷ ምዕራባዊ አገር አሜሪካ አሁንም በጥቁር ዜጎቿ ታላቅ ግፍ እያደረሰችባቸው ነው። ዓለምን በቅኝ ግዛት አሰቃይተዋል። ቅኝ ግዛታቸውን እየተውዉ ቢሆንም አሁንም በ«አዲሱ ቅኝ ግዛት» መርህ ዘንድ ጥቅማቸውን የማያስከብሩ መንግስታትን በመፈንቀለ መንግስትና የተለያዩ ዘዴዎች ያፈርሳሉ።

የአሁኑ ትውልድ ደግሞ የምዕራባዊያን አገሮችን እንደ ጣዖት የሚያመልክ ይመስላል። ነፃነት ከነሱ ጎራ ነው የሚገኘው። ተራማጅነት ከነሱ ነው። ሀብት ከነሱ። ዴሞክራሲ ከነሱ። ቴክኖሎጂ ከነሱ። ስነ መግባር ከነሱ። ወዘተ።

በኔ ኢይታ ይህ አምልኮ ለአገራችን ለያንዳንዳችንም አደገኛ ነው። ለምን ብትሉኝ ይህ አመለካከት ከባህላችን፤ ትውፊታችን፤ ማንነታችን ነጥቆ እንደ ስሩ የተነቀለ አትክልት ነው የሚያደርገን።

ስለዚህም ቢዚህ ርእስ ዙርያ የተወሰኑ ጽሁፎች ለማዘጋጀት አቅጅያለሁ። የኢትዮጵያዊነት፤ የሰውነት፤ የማንነት ጉዳይ የተሳሰረበት ርእስ ነው። የምዕራባዊው ፕሮፓጋንዳ እጅግ ከባድ ነው። በመሰረታዊ አስተሳሰባችንን፤ አስተያየታችንን፤ አስተነፋፈሳችንንም ታላቅ ሚና ተጫውቷል። መሰራታዊ ሃሳቦቻችንና ቋንቋችንም ቀይሯል መቀየሩንም አናውቀውም! ይህ ሁሉ በደምብ ልናየው ይገባል።

ጽሁፎቼን ስጽፍ በተለምዶ በመጀመርያ እንደ ክርስቲያን በማቀው ክርስቲያናዊ አመለካከት ነው የምጽፋቸው። እምነቴ በሁሉ ነገር ኢግዚአብሔር አለ ብሎ ሰለሚያስተምር እንቋን የማንነት ጉዳይ ምንም ነገር ከዚህ መነጽር ውጭ ማየት አይቻልም።

ለጽሁፎቼ እንደ መግብያና ሀሳብ ማንሸራሸርያ እስቲ እነዚህን ቃላቶችን እናስባቸው፤

ዘመናዊነት (modernity)
መሻሻል ወይም እድገት (progress)
ዴሞክራሲ (democracy)
ነፃነት (freedom)
ሰው (Man)
ፍትህ (justice)
ልማት (development)
አገር (nation)
ጎሳ (tribe - in the neutral sense)
ተፈጥሮ (nature)
ፍቅር (love)
ስልጣኔ (civilization)
ሴኩላሪዝም (secularism)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

ይህንን የምጽፈው ሊህቃኖቻችንም እኛ ብዙሃንም አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ትክክለኛ የሚመስለኝን ግንዛቤ እንዲኖረን ነው። በዛ ግንዛቤ ተመስርቶ ትክክለኛውን ሃሳብና ስራ በተግባር እንዲያውል ነው።

ዛሬ የፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በርካቶች ከሚያስቡት ተቃራኒ አስተዋሶ ነው የሚኖረው። የነጻነትን እንቅስቃሴውን ይጠቅማል እንጂ አይጎዶም።

ለማስታወስ ያህል ባለፉት ዓመታት ያየነው የህዝብ ተቃውሞና የኢህአዴግ የስልጣን መገለባበጥ በአንድ ጊዜ የምነጣ አይደለም። ለረዥም ዓመታት እየተንከባለለ የመጣ አዝማሚያ ነው። የህዝብ ብሶትና የአስተዳደሩ መሰረታዊ ችግር ያመታው ተቃውሞ ነው። የጎሳ አስተዳደርና የአውራ ፓርቲ የልማታዊ መንግስት አስተዳደር እንደ እሳትና ጭድ የሆኑ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች በመሆናቸው ኤኮኖሚው ምንም ቢያድግም የህዝብ ቁታ እንዲንር አድርጓል። ይህ አገዛዝ ያመጣው በህዝቡ መካከል ያለው የአድሎ ግንዛቤ ህዝቡን እጅግ አምሮት ለዓመታት የማያቋረት ሰላማዊም አመጻዊም ሰልፍ እንዲካሄድ አድርጓል።

ይህን አዝማሚያ እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምንም ሊያቆመው አይችልም። ያለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጀ እንዳላቆመው እናስታውስ! ትልቅ የፖለቲካ ለውጥ ብቻ ነው የህዝቡን ቅሬታ መመለስ የሚችለውና መሰረታዊ የፖለቲካ ብልሽቶችን ማስተካከል የሚችለው።

ምናልባት አንዳንድ ተቃዋሚዎች ስለኢህአዴግ ያላቸው ግንዛቤ የተጋነነ ስለሆነ በቀላሉ የተስፋ ምቁረጥ ባህሪ አላቸው። ይህ አዋጅ የህዝቡን ተቃውሞ ያቆመዋል ያከሽፈዋልና ከምርጫ 97 በኋላ እንደሆነው ለበርካታ ዓመታት የኢህአዴግ አገዛዝ ይቀጥላል ብለው ያምናሉ። ይህ ምን ያህል የተሳሰት እንደሆነ የሚያሳየው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችንም ስለማያስቡት ነው! ስልጣናቸው እንደተነጋ ለሁሉም ግልጽ ነው። የሚሉትም ነገሮች፤ የሚወጣው ሚስጥሮች፤ የሚያደርጉት ድርጊቶች ሁሉ ይህንን ይመሰክራል። እስረኞችን የፈቱት ብርሀን ስላዩ አይደለም። ተሃድሶ እያሉ እርስ በርስ የሚፋጁት ከንቱ አይደለም። እነ ለማ መገርሳ እራሳቸውን ከፍ ያደረጉት አለ ምክንያት አይደለም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈለገውም ክንያት አለው! የህዝቡ ተቃውሞ ጋብ ይል ይሆናል ማለትም አለበት ግን ቀስ በቀስ ይቀጥላል ለውጥ እስኪመጣ።

ሌላው ማስተካከል የምወደው የተሳሳተ የሚመስለኝ አመለካከት ስለ ጦር ስራዊቱ ነው። የጦር መሪዎቹ ባብዛኛው የህወሓት አባሎች ቢሆኑም ጦሩ እራሱ ባብዛኛው አይደለም። ጠመንጃ የያዘው ኦሮሞ፤ አማራ፤ ሲዳማ ወዘተ ነው። ጦር ሰራዊት ውስጥ የታወቀ የፖለቲካ ክፍፍል አለ። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወታደሩ ብዙ ቅራኔዎች ካላጋጠሙትና ባብዛኛው ሰላማዊ የፍተሻና የሚመሳሰል የማያስጨንቅ ስራ የሚሰራ ከሆነ ይህ ክፍፍል ብዙ ላይታይ ይችላል። ግን ኃይለኛ አመጽ ከተነሳና በርካታ ቅራኔና ግድያ ከተከሰተ የወታደሩ የውስጥ የፖለቲካ ክፍፍል - በዘር ምክንያት - መውጣት ይጀምራል። ጦር ሰራዊቱን ወደ መከፋፈል ይገፋዋል። የጦር ሰራዊት መሪዎች ደግሞ ይህንን "risk" እጅግ ይፈራሉና ይሸሻሉ። ግን የአቸኳ አዋጁ በቆየ ቁጥር ይህ የመከሰቱ እድል እየጨመረ ስለሚሄድ የጦር ሰራዊቱ መሪዎችም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቶሎ እንዲቋረጥ ነው የሚፈልጉት።

ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብዙ ሌከርም አይችልም። ጊዜ መግዣ ነው። የአገሪቷ መንገዶችና ንግዶች እንዲንቀሳቀሱና ሰውዉ ለተወሰነ ጊዜ ቢሆንም ወደ ዘውትር ኑሮ እንዲመለስ ነው። ፖለቲከኞቹ ማቀዳቸውንና ውይይታቸውን እንዲቀጥሉ ነው። አይከፋም። የአገሪቷ የፖለቲካ ጠቅላላ አዝማሚያውን አይቀይርም ሊቀይርም አይችልም። ኢህአዴግ ባለበት አወቃቀር ከስጣን መውረዱ አቀርም። ወይ ለጉድ ይቀየራል ወይም ከስልጣን ይወርዳል። ጉዳዩ አልቋል። አሁን የጭዋታው መጨረሻ ("end-game") ላይ ነን። ስለዚህ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጨነቅ ይልቁኑ እኛ ተቃዋሚዎች በርካታ የተጠራቀመ የቤት ስራችንን እንስራ። ጊዜውን እንጠቀምበት።