Tuesday 6 November 2018

ዲያቆን ዳኒኤል ክብረት ስለ ውጭ ሀገር ጳጳሳት የጻፈውን ለመማርያ እንጠቀም…

(UPDATE) ዛሬ ጥቅምት 21 ይህን ሰማን፤ ከ16 «ውጭ ሀገር ካልተመደብን» አሉ ከተባሉት ጳጳሳት ሁለቱ፤ አቡነ ዮሃንስ እና አቡነ ሚካኤል፤ ሀገር ውስጥ እንሰራለን ብለው ተመድበዋል! ስለዚህ እስካሁን ከ20 ጳጳሳት አራቱ ሀገር ውስጥ፤ ያውም አንዱ ጅጅጋ፤ ለመስራት ተዘጋጅተዋል። ሌሎችም ሊቀጥሉ ይችሉ ይሆናል።

ዲያቆን ዳኒኤል ክብረት በቅርብ ጊዜ ጽሁፉ እንዲህ ይላል፤
«ባለፉት ሦስት ወራት አያሌ ፖለቲከኞች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በሀገር ውስጥ ባለው ፖለቲካ ለመሳተፍ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩም ድጋፍ እየሰበሰቡ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ፖለቲከኞቹ የለቀቋቸውን አሜሪካ፣ አውሮፓና አውስትራልያ ለማጥለቅለቅ ወደ ውጭ እያቀኑ ነው፡፡ 
በተለይም ከውጭ የመጡት ብጹአን አባቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የመመደብ ፍላጎት ፈጽሞ የላቸውም፡፡ በዚህ ረገድ ከ18 ጳጳሳት ሁለት ብቻ ናቸው የተገኙት፡፡ ሌሎቹ ግን በአሜሪካና በአውሮፓ ካልመደባችሁን እንገነጠላለን ብለው የሚያስፈራሩ ሆነዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ መለመንና ማግባባት ሲያቅተው ጳጳሳቱን የደብር አስተዳዳሪዎች አድርጎ እስከ መመደብ ደርሷል፡፡
…»
ጽሁፉ ይቀጥላል። የጽሁፉ ዋና ነጥብ ይህ ነው፤ ለስደተኛው ሲኖዶስ የሚያገለግሉ የነበሩት ጳጳሳት ኢትዮጵያ ውስጥ መመደብ እና መስራት አይፈልጉም።»

የዲያቆን ዳኒኤል ጽሁፍ እንደኚህ አይነት በርካታ ጥያቄዎች ያስከትላል፤

1. እውነትም 16ኡም ጳጳሳት ውጭ ሀገር ካልተሾምን «እንገነጠላለን» ነው ያሉት ወይንም አንዳንዶቹ በነበርንበት ውጭ መመለስ እንወዳለን ነው ያሉት? «ይህ ቢደረግልኝ ነው የምፈልገው» እና «ይህን ካልተደረገልኝ እገነጠላለሁ» የተለያዩ አቋሞች ናቸው።

2. 16ኡም ሁኔታቸውም አቋማቸው እና ሁኔታቸው አንድ ነው? ልምሳሌ አንዳንዶቹ እውነትም አሳሳቢ የጤንነት ችግር እያላቸው ነው ሀገር ውስጥ መስራት አንችልም የሚሉት? ወይንም ከምዕመናኖቻቸው ጋር ያላቸውን ትሥስር ምክንያት መልቀቅ አልፈለጉ ይሆን? ወይንም ሀገር ውስጥ ለመስራት በቂ ብቃት እና ችሎታ የለኝም ብለው በልባቸው የሚያስቡ ይሆናል (አንዳንዱ በቀላሉ ስለተሾሙ)? አንዳንዶቹ ሀገር ውስጥ ለመስራትና ለመኖር መንፈሳዊ ፍርሃት ይኖራቸው ይሆን?

3. ቅዱስ ሲኖዶስ 16ኡም ጳጳሳት ሀገር ውስጥ እንዲሰሩ ይፈልግ ይሆን? ወይንም አንዳንዶቹን ብቻ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ሊመድባቸው ያሰበው?

4. ይህን ተከትሎ እነዚህ 16ኡ ሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ቢመደቡ ቤተ ክርስቲያንን ይጠቅሟት ይሆን?

እነዚህ ጥያቄዎች እስከተረዳሁት ድረስ በዲያቆን ዳኒኤል ጽሁፍ አልተመለሱም። ታድያ እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች ሳይመለሱ እንዴት ነው በ16 ሰው ላይ (የጅምላ) ክስ ማቅረብ የሚቻለው?

ለኔ ይህ ጽሁፍ ለቅራኔ መፍታት (conflict resolution) እና የቅራኔ መፍታት እጦት ጥሩ ትምሕርት ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html)።

ማንኛውም ጹፍ፤ ንግግር፤ ውይይት ወይንም ተግባር ግብ አለው። በተለይ እንደ ዲያቆን ዳኒኤል አይነቱ ታዋቂ እና ባለስልጣን የሆነ ሰው መልዕክት በአንደበትም በጽሁፍም ሲያስተላልፍ ይህን ግብ ጠንቅቆ አስቦ ነው ማድረግ ያለበት።

የዚህ የዲያቆን ዳኔኤል ጽሁፍ ግቡ ምንድነው? እኔ እንደሚመስለኝ 1) ህዝብን የነዚህ ጳጳሳትን ራስ ወዳድነት ወይንም ብቃት ማጣትን ለማሳየት እና 2) ጳጳሳቱን ለመገሠጽ። እነዚህ ግቦች ተገቢ ናቸው ብንልም የዲያኮን ዳኒኤል ጽሁፍ እነዚህን ግቦች ከማሳካት ይልቅ እንዳይሳኩ ያረጋል። እስቲ ጉዳዩን እንመርምረው…

ይህ ጽሁፍ ህዝብን ስለጳጳሳቱ ችግር አያሳውቅም። ለምን?

1) ጽሁፉ የተመሰረተበት ማስረጃ ሙሉ እውነት አይደለም። እንሆ 18 ጳጳሳት ሀገር ውስጥ መሾም አይፈልጉም ተብሎ ነበር ዛሬውኑ 16 ሆነ። ቁጥሩ አሁንም ሊቀንስ ይችላል።

2) ጸሃፌው ዲያቆን ማስረጃ ቢኖሮውም ከጽሁፉ አላቀረበውም። ክሱ ታላቅ ነው ማስረጃው ታናሽ። ስለዚህ አንባቢው በጥርጣሬ ነው የሚያነበው። ከላይ ያነሳኋቸውን ጥያቄዎች ያነሳል። በዚህ ጥርጣሬ መካከል አንባቢው እነዚህ ጳጳሳት እንዲህ አድርገዋል የሚባለውን ለማመን ያስቸግረዋል።

ጽሁፉ ሁለተኛውን የጳጳሳቱን መገሠጽ አላማውንም አያስፈጽምም። ለምን?

1) በሀሰት የተከሰሱት ጳጳሳት፤ ማለትም ሀገር ውስጥ አንሰራም ያላሉት፤ አይመለከታቸውም። ባይመለከታቸውም አብሮ በመከሰሳቸው ዲያቆኑ ላይ ቅሬታ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

2) ጽሁፉ ለተገቢ ምክንያት ሀገር ውስጥ መስራት አንፈልግም ያሉትም ዲያቆን አኒኤል ላይ ቅሬታ እንዲኖራቸው ያደርጋል። የሚያሳስባቸው የጤንነት ችግር አላቸው፤ ህዝባቸውን መትወ አይፈልጉም፤ ሀገር ውስጥ ለመስራት ይፈራሉ ወዘተ ምክንያት ይኖራቸዋል። ዲያቆን ዳኒኤል ሳይጠይቃቸው ሳያነጋግራቸው በደፈናው እንዲህ በመፍረዱ ደስተኛ አይሆኑም። የሱን ተግሣጽ አይቀበሉም።

ስለዚህ የዲያቆን ዳኒኤል ጽሁፍ ሁለቱንም ግቦች አይመተም። ይልቁንስ ቅሬታ ያሰፍናል። ጳጳሳቱ ቅር ይላቸዋል። በርካታ አንባቢ ጽሁፉ የጅምላ ያለማስረጃ ክስ በመሆኑ ቅር ይለዋል። ሌሎች አንባቢዎች ደግሞ ጽሁፉን ቢያምኑት ደግሞ የሀሰት ወይንም ያልተሟላ ክስን አመኑ ማለት ነው እና  እንዲፈርዱ ወይንም ፈራጅ እንዲሆኑ አደረጋቸው። የጽሁፉ መጨረሻ ውጤት አያምርም።

እንዲህ የሆነበት ምክንያት ጽሁፉ መሰረታዊ የአወያየት ስህተቶች ስላሉት ነው። ለምሳሌ፤

1) መፍረድ፤ ማለት ድርጊትን ከመቃውም አድራጊውን መቃወም እና መወንጀል። ልምሳሌ «ጳጳሳት አለ ጥሩ ምክንያት ሀገር ውስጥ መስራት አልፈልግም ማለት ተገቢ አይመስለኝም» ማለት ጥሩ ነው። «እንደዚህ ያሉ ጳጳሳት ካሉ ምክንያታቸው በደምብ ቢታይ ጥሩ ነው» ማለት ተገቢ ነው። ግን «ጳጳሳቱ ምቾት ለምደው ሀገር ውስጥ መስራት አይፈልጉም» ማለት ድርጊትን ሳይሆን ሰው ላይ (ያውም አለማስረጃ) መፍረድ ነው።

2) ማስረጃ አለመስጠት፤ አወያየት እምኔታ ያስፈልገዋል። አንዱ የአምኔታ መስፈርት ማስረጃ ነው። ማስረጃ ከሌለ ጥርጣሬን ነው የሚጋብዘው። ጽሁፉ ጥርጣሬን ያንጸባርቃል።

3) የጅምላ ፍርድ፤ ምናልባት አንዳንዱ ጳጳሳት (ልባቸውን ከፍተን አይተን) መጠን የለሽ ራስ ወዳድ ሆነው ሌሎቹ ግን አይደሉም ክሱም አይመለከታቸውም። ግን አብረው ተፈርጀዋል። የጅምላ ፍርድ የውውት፤ መስማማት፤ እውነት ላይ መድረስ፤ መተማመን ወዘተ ገዳይ ነው።

4) ሀሜት፤ ሰውን ቀጥታ ከመተቸት በተዘዋዋሪ ወይንም በብዙሃን መደረክ መተቸት እንደ ሀሜት ነው። የሚተቸው ሰውን ትችቱን በጥሞና ለመቀበል ይከብደዋል። ተዋረድኩኝ ይላል። ውየንም በሃሰት ተከሰስኩኝ ይላል። በጥሞና ከመቀበል ይልቅ ጥላቻ ያድርበታል።

5) ለሰው አለመቆርቆር፤ በሰው ቦታ ሆኖ ማሰብ የክርስትና ተዕልኮ ነው። ጳጳሱ እውነት እጅግ የሚያማቸው ሆኖ በኢትዮጵያ ህክምና የሚፈሩ ቢሆንስ? በነሱ ቦታ ብንሆን ምን እናደርግ ይሆን? «መነኩሴ ኖት» ማለት ቀላል ነው ግን ተገቢ አይደለም። ለሰው አለመቆርቆር ማለት መወያየት አለመቻል ነው።

6) ስም ማጥፋት፤ የጽሁፉ መንፈስ የስም ማጥፋት መንፈስ አለው ይመስላል። ልምን እንዲህ እላለሁ? እንደገና የጅምላ ፍርድ ያለው እና ግልጽ ማስረጃ የሌለው በመሆኑ ነው።

በነዚህ ምክንያቶች ጽሁፉ ችህግርን ከመፍታት ቅራኔን ያመጣል ወይንም ቅራኔን ያጎለብታል ማለት ይቻላል። እኔ እንደዚህ ነው የሚመስለኝ።

በተጨማሪ ዲያቆን ዳኒኤል የቁጣ መግሥጽ አጻጻፋቸውን ለማስረዳት በመሃበራዊ ሚዲያ ምን አሉ፤ «ጳውሎስ ያን የጻፈው ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ነው። ይህም እንደዚሁ»።

የቅዱሳን አባቶቻችን ትምሕርት ከገባኝ «አትፍረዱ» አንዱ ዋና ትእዛዛችን ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በቁጣ እየፈረዱ ስለጻፉ እኛም እንደዛ ማድረግ አለብን ማለት አይደለም! የተናጋሪው ማንነት ወሳኝ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ የበቃ እረኛ፤ ለእግዚአብሔር እጅግ የቀረበ ሃዋሪያ በመሆኑ ለምዕመናን የሚሰጠው «መድሃኒት» ተገቢው ነው። የምዕመናን ልብን ያውቃል። ምን እንደሚያስፈልገን ያውቃል። ይህ ከቅድስና የሚመጣ ጸጋ ነው። ለዚህ ነው የቅዱሳን አባቶቻችን አንዳንዴ በኃይለኛ ቋንቋ የተናገሩት። ለዚህ ነው እንደ ዮሃንስ አፈወርቅ አይነቱ ህዝብን በጅምላ የገሠጸው። በኢግዚአብሔር ያላቸው ቅርበት ምክንያት እውነትን ይዘው ነው የሚናገሩት በትክክል የሚያስፈልገንን መልዕክት ነው የሚሰጡን። ግን ሌሎቻችን ይህ ደረጃ ላይ ስላልሆንን «አትፍረዱ» የሚለውን ትዛዝ አጥብቀን ይዘን ነው መራመድ ያለብን። እኛ ቅዱስ ጳውሎስ አይደለንም። ዮሃንስ አፈወርቅ አይደለንም። በአነስተኛ የመንፈሳዊ ደረጃችን እንደነሱ እናድርግ ካልን እንሳሳታለን። ወደ መፍረድ፤ ግብዝነት እና ትዕቢት እንድንሄድ ይፈትነናል። አልፎ ተርፎ ቅራኔን ያበዛል።

ይህን ሁሉ ስጽፍ ልብ ካላችሁ የዲያቆን ዳኒኤል ማንነትን አልተቸሁም። ስለ ጻፈው ብቻ ነው የጻፍኩት። ይህ አጻጻፍ ወይንም አነጋገር ገምቢ አይደለም እና ቅራኔ ያንጸባረቃል ነው ያልኩት።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!