Tuesday, 14 August 2018

ተረት ተረት፤ «ጎሰኝነት ዘረኝነት ነው»

ይህም ከፊል እውነታ አለው። አማራ ማየት አማርኛ መስማት የሚጠሉ ጸንፈኛ ኦሮሞ ብሄርተኞች አሉ። ግን ጎሰኝነትን «ዘረኝነት» ብሎ መሰየሙ ችግሩን በትክክል አይገልጸውም ወደ መፍትሄም ለመምጣት አይረዳም። ላስረዳ…

«ዘረኝነት» የሚለው ቃል ብዙ ትርጉም ያለው፤ የተወሳሰበ፤ ኃይል ያለው ቃል ነው። የምንጠቀምበት አንድ ነገርን ወይንም ሰውን ክፉ መጥፎ ነው ብለን ለመሰየም ነው። ከክፉ ጋር ውይይት የለም ድርድር የለም። «ዘረኝነት» ብለን ሰይመን ከዚህ ሀሳብ ጋር ውይይትም ድርድርም አያስፈልግም ነው የምንለው «ዘረኛ» ስንለው። ትክክለኛ አካሄድ አይደለም።

ጎሰኝነትን እስቲ እንደዚህ ብናየው ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዳል ጎሰኝነትን ለመቀነስ ለማጥፋትም ምን ማድረግ እንዳለብን እንድንረዳ ይረዳናል። ጎሰኝነት ገና ሲጀመር በውይይት፤ በማስረዳት እና በማስተማር ማጥፋት ይቻላል። ግን ጎሰኝነት አንድ ደረጃ ካለፈ ውይይት ከሞላ ጎደል አይሰራም።

ለምሳሌ ጎሰኛው ኦሮሞነቱ እጅግ አይሎ ኢትዮጵያዊነቱ እጅግ ከመነመነ ስለ ታሪክ እና ፖለቲካ ምን ብትሰብከው ለውጥ ሃሳቡን አይቀይርም። «ዘረኛ» ብትለውም ፋይዳ የለውም። ይህ ስወ ዘረኛ ሳይሆን ማንነቴ ሙሉ በሙሉ «ኦሮሞ» ነው ብሎ ወስኗል። ሀገሬ ኦሮሞ ነው ኢትዮጵያ አይደለም ነው የሚለው። ኢትዮጵያን ይጠላ አይጠላ አይደለም ዋናው ጉዳይ። ኦሮሞ ነኝ ማለቱ ነው። ልክ እንደ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የተለያዩ ሀገሮች እንደሆኑ ሱዳናዊው በኢትዮጵያ ያለው መብት ውስን እንደሆነ እንዲሁም በተገላቢጦሽ ለኦሮሞ ብሄርተኛው በኦሮሚያ እና ኢትዮጵያ ያለው ልዩነት እንዲሁ ነው። ሌላ ሀገር ንኝ ነው የሚለው። ይህን የማንነት ስሜቱን ደግሞ ልንከለክለው አንችልም። «ዘረኛ» ማለቱ ዋጋ የለውም ምናልባትም ማባባስ ነው።

ታድያ ጎሰኝነት ይህ ከሆነ ምን ችግር አለው ትሉ ይሆናል? የሀገሩ ማንነት መምረጥ የሰው ልጅ «መብት» ከሆነ ምን ክፋት አለው? «ዘረኝነት» ካላልነው መጥፎነቱን እንዴት እንግለጽ? መልሱ ቀላል ነው፤ ጎሰንኘት «መብት» ቢሆንም የታላቅ ግጭት ምንጭ ነው። በአንድ ሀገር ጎሰኝነት በተለይም ጎሰኝነት እና ብሶት (grievance) አብረው ሲኖሩ ከፉ ግጭቶች ይኖራሉ። ይህ በቴኦሪ ወይንም በሌሎች ሀገራት ብቻ የሚታይ ሳይሆን ለ27 ዓመት በኢትዮጵያ የታየ ነው። ለግጭቶች ደግሞ በመንግስት አምባገንነት አናሳብብ፤ መንግስት ያልተሳተፈበት ግጭቶች ብዙ ነበሩ አሁንም አሉ። አልፎ ተርፎ መንግስት በግጭቶቹ ቢሳተፍባቸውም ባለ ክፍተት ነው እየገባ እየበጠበጠ የነበረው እንጂ የሌላ ልዩነት የመፍጠር አቅም አልነበረውም።

ስለዚህ ጎሰኝነት ወይንም የጎሳ እና ሀገር ሚዛን ከልክ በላይ ወደ ጎሳ ሲያመዝን ችግሩ ጎሰኝነት «ዝረኝነት» መሆኑ ሳይሆን የግጭት ምንጭ መሆኑ ነው። መፍትሄውም የግጭት ምንጭ ነው ብለን ጎሳን እንደ ጽንሰ ሀሳብ ከሀገሪቷ ህገ መንግስት ማውጣት እና በ«ቋንቋ እና ባህል» ጽንሰ ሀሳቦች መተካት ነው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!