Showing posts with label Addis Ababa. Show all posts
Showing posts with label Addis Ababa. Show all posts

Sunday, 24 March 2019

የመጠላለፍ ፖለቲካ ቁጥር 1,999,999

መቼስ እኛ ጎሰኝነትን እንጠላለን ህገ መንግስቱ ይቀየር የምንለው የመጠላለፍ ፖለቲካ ባለሙያዎች ነን። ህወሓት የሀገራችን 6%ም የማይሆን ድጋግ ይዞ ለ27 ዓመት ሲገዛን እንኳን መታገል መደራጀትም አቅቶን ቆየን። በተለይ አማራ ክልል ውስጥ የህወሓት ሰዎች አንድ ለመቶ ሺ ሆነው እንደፈለጉት ሲጫወቱብን ማንም ሳናደርግ ቆየን። በዲያስፖራ ያለነውም ከሳንቲሞች በቀር ማዋጣት አልቻልንም ምንም ቁም ነገር ያለው ድርጅትም አልነበረንም። ለማስታወ ያህል የነ ሻቢያ እና ህወሓት ዲያስፖራዎች በዓመት በአስርት ሚሊዮን ዶላር ነበር ለአቋማቸው የሚያዋጡት።

ዛሬም አክራሪ ጎሰኛው ህልውናችንን አደጋ ላይ እያደረገ እኛ እርስ በርስ እንጠላለፋለን። አሁንም የአማራ ብሄርተኞች እና «አንድነት ኃይል» ወዘተ ፉክክር አልበረደም። አቋማችን አንድ ሆኖ፤ «ህገ መንግስቱ ይቀየር» «ጎሰኝነት ይቅር»፤ እንኳን መተባበር በሰላም አብረን መኖር አልቻልንም። ስለ isolated attack አይደለም የማወራው። በየ አይነቱ ሰው አለ። እንደዚህ አይነት ነገሮች ይከሰታሉ። አብን አደረገው አይባልም። ሆኖም እንደዚህ አይነት ድርጊቶች pattern ሆኖዋል። በሁለቱም ወገን ያለው የአለመተባበርን መንፈስ የሚያንጸባርቅ መንፈስ።

አንዱ መፍትሄ ቀላል ነው፤ እንዲህ አይነት ክስተት ሲፈጠር ሁሉም ወገኖች በይፋ ጮክ ብለው ማውገዝ አለባቸው። ይህ ፖለቲካ 101 ይመስለኛል። ደጋፊዎችህ መስመር እንዳይስቱ፤ ሌሎች ባንተ እንዲተማመኑ የሚደረግ ነገር ነው። የጸብ መንፈስን በህብረት መንፈስ መተካት ነው። ማውገዝ ድርጊቱን እኔ ነኝ ያደረግኩት ብሎ ማመን አይደለም፤ ይህ የታወቀ ነገር መሆኑ ሁላችንም እንደምንረዳ ተስፋ አለኝ። ደግሞ ስለተወገዘ ደጋፊ አጣለhu የሚል እንደሌላ ተስፋ አለኝ። አብንን ማንም outflank የሚያደርግ ድርጅት የለም። ማለት አብን ያወገዘው የትም መሄጃ የለውም። ስለዚህ አብን እንደዚህ አይነት ድርጊቶችን ቶሎ ብሎ ማውገዝ አይጎዳውም እጅግ ይጠቅመዋል።

የአንድነት ኃይል ደጋፊዎችም እነ አብንን እንተው። ማለት ከተቸን ወንድማዊ ምክር በያዘ መልኩ ነው እንጂ መበሻሸቁ ያብቃ። አሁን ቁልፍ ጊዜ ነው፤ እንደ ጥንት አባቶቻችን የሰለጠነ እና የሰከነ ፖለቲካ አሁን ግድ ነው። የዓመታት ህጻንነታችን ለውቅቱ አይበጅም።


Tuesday, 12 March 2019

የአዲስ አበባ ህዝባዊ ድርጅት

በጄት፤ 100 ሚሊዮን ብር
አባል ቁጥር፤ አንድ ሚሊዮን
አደረጃጀት፤ አንድ ለአምስት
አካሄድ፤ ስልታዊ
ውጤት፤ ሰላም

የሰከነ አስተያየት ስለ ዓቢይ እና ኦዴፓ

ስሜታዊ መሆን አይበጅም... ይህን የፍፁም ፈቃዱ ትክክለኛ ትንታኔ ያንብቡ።

(https://www.facebook.com/fitsum.fikadu.96/posts/2138544319567816)

ቁምነገሩ ጦርነቱን ማሸነፍ ነው

በቅድምያ በአደጋው ለተጎዳነው ሁሉ ፈጣሪ መፅናናት ይሁነን እላለሁ።አዎ እርሱው ፈጣሪ ኢትዮጵያዬን እንዲህ ካለው ሃዘን ሁሌም ይጠብቅልን እያልኩ በሰሞኑ የፖለቲካችን ፈተና ዙሪያ እንዲህ እንደሚከተለው ልል ወድጃለሁ።

የዶ/ር አብይ ቡድን ማለቴ ቲም ለማ ሃገርን አንድ ለማድረግ ከፍተኛ ትግልና ውጥረት ውስጥ ሆኖ ይታየኛል።ጁሃር (ኦነግ፣ ቄሮ) እነርሱን (ማለትም ቲም ለማን) ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ለማጣላት ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አምናለሁ። እነርሱም ይህ ስለገባቸው ህውሃትን ቀስ በቀስ ድባቅ የመቱበትን ያንኑ የተለመደ ለዘብተኛ የሚመስል ግን ውስጠ ወይራ አካሄዳቸውን እየተገበሩበት ይገኛሉ። እነዚህ ብልህ መሪዎች መሬት እስከሚይዙ ድረስ ለህውሃት ተገዢና ተልመጥማጭ መስለው እንዴት አዘናግተው በጡረታ ስም ገሸሽ በማድረግ ከዚያም ጊዜ ጠብቀው እነዛኑ አይነኬ መሣይ የህውሃት መሪዎች ወደ ማሰር ውስጥ እንደገቡ ሳስብ፤ ይሄ በስሜት የሚነዳው ህዝባችን በሚፈልገው ፍጥነት ባለመሄድ ውስጥ ውጤት እንዳለ ያሳዩኛል።የእነዚህ ሰዎች አካሄድ ልክ እንደ ሺቭ ኬራ አባባል ዓይነት ነው።ማለትም፦ አሸናፊነት ማለት እያንዳንዱን የጦር ግንባር ማሸነፍ ማለት ሳይሆን ጦርነቱን ማሸነፍ ማለት ነውና።

ጁሃር በዚህም በእዛም ብሎ፤ "እኛ ከየኦሮሞ ህዝብ ጥቅምና አጀንዳ ይልቅ የምናስቀድመው የኢትዮጵያ ህዝብን አጀንዳና ጥቅም ነው" ብለው ዛሬውኑ በአደባባይ እንዲናገሩ ለማድረግ ያልወጋጋቸው ቦታ የለም። ም/ቱም ለእርሱ እንዲህ ማስባል ማለት እነርሱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስካሁንም በጥርጣሬ እያያቸው ካለው ከቄሮና ፅንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች ጋር ሙሉ ለሙሉ ማቆራረጥ እናም ቦታቸውን (ምርጫ ባስፈለገ ጊዜም ሆነ በአዘቦቱ ጊዜ) በኦነግ ማስቀማት ብሎም የእራሱን ርካሽ ተወዳጅነት በአክራሪ ኦሮሞ ብሄርተኞቹ መካከል ያለስጋት ማስፈን መሆኑን ስለሚያውቀው ነው።በከፍተኛ ፈተናና ጫና ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያውያኑ ብልሆቹ መሪዎች ግን ገብቷቸዋልና፤ ቪዥናቸውን ከዳር ማድረስ እንዳለባቸው ስለሚያውቁ መረጋጋት ያለበትን በማረጋጋትና ባላንስ በመስራት ስራ ላይ ናቸው።

ኢትዮጵያውያኑ መሪዎች አዲስ አበባን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ብቻ በእኩል እንድትሆን እንደሚመኙ ግልፅ ማሳያው እኮ፤ መጀመሪያውኑ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ማውጣታቸው ነው።ከዚህ በተጨማሪም አገር ሰላም ብሎ የኮንዶሚኒየም እጣ ያወጣው ደግሞ የኦዴፓ አባላቸው ማለትም ታከለ ሆኖ ሳለ ወዲያውኑ የጁሃር ጫጫታ ወደ ደም ማፋሰስ ሊሻገር መሆኑ ሲገባቸው፤ ፅንፈኞቹን ለማረጋጋትና የኦሮሞን ህዝብ ለማሳመኛ የሚሆናቸውን ጊዜ ለመግዛት የሆነ ዓይነት መግለጫ "በሌላኛው" የኦዴፖ ገፅ አውጥተው ጉዳትን ተከላክለዋል። ዳሩ ግና በስሜት የሚንቀለቀለው የህዝባችን አካል ጠረጠራቸው። እነርሱ ግን ምንተዳቸው፤ ግባቸው የብሄር ፖለቲካን ከኢትዮጵያ ምድር ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት ነውና፤ ይኸው ውጥናቸው ሲሳካ ለሁሉ ምላሽ ይሆነናል በሚል ተስፋ አሁንም ዋና ስራቸው ላይ ናቸው። አዎ በብሄር ፖለቲካ ሃገራቸውን እንዲህ ቁምስቅሏን በማሳየት እያንገላታት ያለውን ኢህአዴግንም ሆነ ኦዴፓቸውን ፍርስርስ አድርገው በህብረብሄራዊ ፓርቲ መተካት ደግሞ፤ የለዘብተኛ መሳይ አካሄዳቸው የመጨረሻ ግብ በዚያውም የጁሃርም ሆነ የኦነግ አሊያም የወላጃቸው የህውሃት ወይም ደግሞ የሌሎች ዘረኛ መሰሎቻቸው ሁሉ ሃሳቦች ግብአተ መሬት እንዲሁም የኢትዮጵያዬ ትንሳዔ መሆኑ ገብቷቸዋልና፤ ለስኬቱ ትግልና ጫና ውስጥ ናቸው። እኛስ የት ነን?

Sunday, 10 March 2019

ለማ መገርሳ ልክ ነው፤ የዴሞግራፊ ለውጥ ግድ ነው

ከዚህ በፊት እንደጻፍኩት የጎሳ ብሄርተኝነትን ከፖለቲካችን ለመቀነስ እና ለማጥፋት የዴሞግራፊ ለውጦች ማምጣት ግድ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/curbing-ethnic-nationalism-via_26.html)። ምከንያቱ ባጭሩ እንዲህ ነው...

የጎሳ ብሄርተኝነት ህዝብ ውስጥ በተለይ የኦሮሞ ህዝብ ውስጥ በደምብ እንደገባ ሁላችንም ገብቶናል። በልሂቃን ደረጃ ብቻ ሳይሆን በብዙሃን ደረጃም። ይህን ጎሰኝነት በስብከት እና ልመና ማጥፋት አይቻልም። የተም ሀገር የጎሳ ብሄርተንኘት አንዴ ከሰፈነ የሚቅንሰው ነገር ፖለቲካዊ ድርድር ሳይሆን የዴሞግራፊያዊ ለውጥ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው የዴሞግራፊ ለውጥ በኦሮሞ እና ሌላው ኢትዮጵያዊ መካከል መቅላቀል እና ውህደት (integration and assimilation) ነው። ህዝቡ ተቀላቅሎ ተጋብቶ ተዋልዶ የቅይጥ ባህል እና ህዝብ መጨመር አለበት። በዚህ መንገድ የጎሳ ብሄርተኛው ጎራ እያነሰ ይሄዳል የፖለቲካ ኃይሉም ይመነምናል። ይህን የሚያስፈጽም አንድ ፖሊሲ ኦሮምኛ የህገር ሙሉ ቋንቋ ማድረግ ነው። ይህ ኦሮሞዎች ከኦሮሚያ ወደ ሌላው ኢትዮጵያ እንዲፈልሱ ይጋብዛል። ለምሳሌ ኦሮምኛ ለማስተማር ወደ አማራ ክልል ይመጣሉ። ይህ ፈልስት መቀላቀልን እና መወሃድን ያመጣል። ከላይ የጠቀስኩት ጽሁፍ ባጭሩ ይህን ነው የሚለው።

በቅርቡ ለማ መገርሳ ስለኦሮሞ ህዝብ ወደ ከተማ መፍለስ እናለበት ያሉት ነገር ከዚህ ጋር አብሮ ይሄዳል። ለምሳሌ አዲስ አበባ ዙርያ የሚኖረው ባብዛኛው ኦሮሞ ነው። አዲስ አበባ ባደገች ቁጥር በሜትሮፖሊታን ከተማው ያለው የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። ከላይ በጻፍኩት አንጻር ይህ የኦሮሞ ህዝብ በአዲስ አበባ መብዛት አይቀሬም ብቻ ሳይሆን እንደ ጥሩ ነገር ነው መታየት ያለበት። ከተማው ህዝቡን ይቀላቅለዋል እና ያዋህደዋል። ይህ ውህደት የጎሳ ብሄርተኝነትን ይቀንሳል። ስለዚህ ኦሮሞዎችን ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች እንዲፈልሱ ያለው የኦዴፓ እቅድ ጥሩ ነው ማለት ይቻላል።

አሁን ከኛ ከኢትዮጵያ ብሄርተኞች ጎራ የሚጠበቀው ይህ እቅድ በምንፈልገው በአውንታዊ መስመር እንዲካሄድ ነው። «የጎሳ ጌቶዎች» ወይንም የአንድ ጎሳ ሰፈሮች እንዳይፈጠሩ፤ እውነታዊ ውህደት እንዲኖር፤ ሌላው ህብረተሰብ ኦሮምኛ እንዲማር፤ አድሎዋዊነት እንዳይኖር፤ ወዘተ መስራት አለብን። ሌላው ከኛ የሚጠበቀው ነገር የኦሮሞዎች መብት እና ፍላጎት በአዲስ አበባ እንደሚከበረው የሌሎች ዜጎች መብት እና ፍላጎት በኦሮሚያ እንዲከበር መሟገት እና ማስፈጸም ነው። አልፎ ተርፎ ኦሮሙማ (የኦሮሞ ባህል) በአዲስ አበባ እና መላው ኢትዮጵያ እንዲንጸባረቅ በመስማማት in exchange የጎሳ ፌደራሊዝም ሀገ መንግስቱ እንዲቀየር መሟገት እና መደራደር አለብን። ይህን ለማድረግ ታላቅ አቅም እና መደራጀት ይጠበቅብናል።

ነገሮችን ሁሉ በአውንታዊ መልኩ እንደ opportunity ማየት የአሸናፊነት ምልክት ነው። ኦዴፓ ኦሮሞን ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድ እናበረታታለን ሲል እኛ እሰየው ብለን በሂደቱ ተሳትፈን እኛ የምንፈልገው መልክ እንዲይዝ ማድረግ አለብን። ከውጭ እያየን በፍርሃት ከማልቀስ ጉዳይ ውስጥ ገብተን መምራት ነው ያለብን።

ስለዚህ ለማ መገርሳ ልክ ነው፤ የዴሞግራፊ ለውጥ ግድ ነው። በዚህ መንገግድ ብቻ ነው መቀላቀል እና መዋሃድ የሚመጣው። በዚህ መንገድ ብቻ ነው አሁን በህብረተሰባችን የሰፈነው ጎሰኝነት ከረዥም ዓመታት በኋላ እንዲቀንስ እና እንዲጠፋ ማድረግ የሚቻለው።

Saturday, 9 March 2019

የአዲስ አበባ ህዝብ መደራጀት ምን ይመስላል?

ይዽርጅጥ ጽም፤ «የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ድርጅት»

ተእልኮ፤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚሰራ ድርጅት።

መሰረታዊ አቋሞች፤ ፩) አዲስ አበባ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ነው መገዛት ያለበት ፪) አዲስ አበባ ከጎረቤት ኦሮሚያ ክልል በተገቢው መልካም እና ገንቢ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል ፫) የአዲስ አበባ ህዝብ መብቶች መከበር አለበት ፬) መካከለኛው እና ለዘብተኛው መንገድ መቅደም አለበት፤ ጸንፈኝነት ለአዲስ አበባ ህዝብ ጎጂ ነው።

የአደረጃጀት ሂደት፤ ፩) 100 የአዲስ አበባ ባለሃብቶች ሰብስቦ ከያንዳንዱ 10 ሚሊዮን ሰብስቦ መሰረት ማድረግ ፪) ሰፊ የንቃት እና የአባል መለምለም ሂደት አካሄዶ አንድ ሚሊዮን አባላት ማግኘት ፫) አዲስ አበባን በአንድ ለአምስት አሰራር ሁሉንም የህብረተሰብ እና ኤኮኖሚ ክፍል መቆጣጠር።

ስልቶች፤ ፩) አንድነት፤ የሃሳብ ልዩነቶች በአግባቡ ተንሸራሽረው መፍትሄ ይገኛሉ። ድርጅቱ ጸብ፤ ቂም፤ ሹክሹክታ ወዘተ ይጸየፋል ፪) ግልጽነት፤ ሚስጥርነት ድክመትን ያመጣል። የድርጅቱ ስራ በሙሉ የግልጽነትን ፈተና መቋቋም አለበት፤ ሚስጥር ከወጣ የሚጎዳ ድርጅት መሆን የለበትም ፫) ተሳታፊነት፤ ድርጅቱ አባላት እንዲሳተፉ መጣር አለበት አባሉ የድርጅቱ ባለበትነት እንዲሰማው።

የሰለጠነ እና የሰከነ ፖለቲካ መንፈስ፤ ለቅዋሜ የሚይመች አቋም፤ ድርጅቱ ኢ-ስሜታዊ ሆኖ የሚወስደው አቋም እና የሚያንጸባርቀው ሃሳብ ማንኛውንም ፈተና የሚቋቋሙ መሆን አለበት። ምሳሌዎች፤

፩) ልዩ ጥቅም ጉዳይ፤ «እንዴት ለኦሮሞ/ኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ይኑር ትላላችሁ» ከማለት ምንድነው ልዩ ጥቅም ብሎ ወደ ውይይት መግባት። የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች የአዲስ አበባ አገልግሎትን ማግኘት ይችላሉ፤ የኦሮሚያ ነጋዴዎች በአዲስ አበባ እንደ ነዋሪ መነገድ ይችላሉ፤ ወዘተ አይነቱ ልዩ ጥቅም እንደ ማንኛውም ሜትሮፖሊታን ከተማ ተገቢ ነው። እስቲ ሌላ ምን ልዩ ጥቅም አለ ብሎ መወያየት ነው የድርጅቱ መንገስ።

፪) ኦሮሙማ በአዲስ አበባ፤ ከቋንቋ በላይ ኦሮሙማ የለም። ስለሆንም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በመከበቧ ኦሮምኛ የከተማዋ ሁለተኛ ቋንቋ ብትሆን መልካም ነው። በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች አማርኛ እንደሚሰራው በአዲስ አበባ ኦሮምኛ ሊሰራ ይገባል።

፫) «የአዲስ አበባ ባልቤት ኦሮሚያ ነው»፤ ይህ አባባል ኢ-ዴሞችራሲያዊ ነው። የማንኛውም ቦታ ባለቤት ነዋሪው ነው። አዲስ አበባም ይሁን ልዩ ዞኖቹ ነዋሪዎቻቸው ናቸው የፖለቲካ ባለቤቶቹ። አለበለዛ ወደ አምባገነነት ገባን ማለት ነው።

፬) ተፈናቃዮች፤ የኦሮሞ ገበሬም ሌሎች የአዲስ አበባ እና ዙርያ ተፈናቃዮች በሙሉ ጉዳያቸው ይታይ። ማን ተፈናቀለ ምን ያህል ካሳ ተሰጠው ማን ካድሬ/መሪ በምዝበራ ተጠቀመ። ከምርመራው በኋላ እርምቶች ይደረጉ። አልፎ ተርፎ መሬት የግል ይሁን የሚለውን አቋም ድርጅቱ ያራምድ። መሬት የግል ቢሆን ኖሮ መፈናቀል የሚባል አጸያፊ ነገር አይኖርም ነበር። አልፎ ተርፎ አዲስ አበባ ዙርያ ያለው ኦሮሞ እና ሌሎች ገበሬዎች እጅግ ሃብታም ይሆኑ ነበር መሬ ታቸውን በመሸጥ። መንግስት 100,000 ብር ካሳ የሚሰጠው ግለሰብ የገበያ ዋጋውን አንድ ሚሊዮን ብር ሊሰጠው ይችላል።

የአዲስ አበባ ህዝብ ማለት...

በሩን ከፍቶ የሚያድር ሰው ዘራፊው ሲመጣበት እባክህ አትዝረፈኝ ብሎ የሚለምን።

ሳያርስ ሳይዘራ የክረመ ገበሬ አዝመራ ሳይኖረው እግዚአብሔርን የሚያማርር።

አትንቶ የማያውቅ ተማሪ ፈተናውን ሲወድቅ አስተማሪውን የሚወቅስ።

ወዘተ።

የአዲስ አበባ ህዝብ (ከነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ) ለዓመታት በትንሿ ህወሓት የተገዛው የራሱን የቤት ስራ ስላልሰራ ነው። ይህ የቤት ስራ ተደራጅቶ ለራስ መብት መቆም ነው።

ካሁን ወድያ የአዲስ ህዝብ ካልተደራጀ ለሚደርስበት ጉድ ከራሱ በቀር ማንም ጥጠያቂ አይኖርም። የአምስት ሚሊዮን ህዝብ ከተማ መቶ ሚሊዮን ብር በጀት፤ አንድ ሚሊዮን አባል ያለው ድርጅት ማቋቋም ካልቻለ በቅኝ ግዛት መገዛት ይገባዋል አይቀርለትምም።

Monday, 4 March 2019

ተረት ተረት፤ አዲስ አበባ የኦሮሞ ገቤሬዎችን አፈናቅሏል

1. የአዲስ አበባ ህዝብ ምንም ፖለቲካዊ ውሳኔ አድርጎ አያውቅም። በኢህአዴግ (ከነ ኦህዴድ) የተገዛ ህዝብ ነበር። ስለዚህ የአዲስ አበባ ህዝብ ማንንም አላፈናቀለም። አፈናቃይ ካለ ኢህአዴግ ከነ ኦህዴድ ነው።

2. ከአዲስ አበባ የተፈናቀሉት ባብዛኛው ኦሮሞ ቢሆንም የተወሰኑ አማሮች እና የሌላ ጎሳ አባላት ነበሩ።

3. ካአዲስ አበባ ውስጥ የተፈናቀሉት ደግሞ ከሁሉም ጎሳ ነበሩ። እነዚህ የአዲስ አበባ ተፈናቃዮች ከአዲስ አበባ ዙርያ የተፈናቀሉት ገበሬዎች ይበልጥ ተበድለዋል በደልን በገንዘብ ከተረጎምነው። ከካዛንቺስ 50 ካሪሜትር ቦታው የተፈናቀለው ምናልታብት ሁለት ሶስት ሚሊዮን ብር ነው ያጣው። ከቡልቡላ የተፈናቀለው ገበሬ የዚህ ሩብም አልከሰረም።

4. ገበሬዎች እና ሌሎች «ተፈናቀሉ» ስንል መንግስት የማይመጥን ትንሽ ካሳ ሰጥቷቸው በግድ ከመሬታቸው አስነሳቸው ነው። አድግራጊው የአዲስ አበባ ህዝብ ያልመረጠው የአዲስ አበባ መንግስት ውየንም አብዛኛው ጊዜ የኦህዴድ መንግስት ነው። ገበሬውን አነስተኛ ካሳ ሰጥቶት ለኢንቬስተር በከፍተኛ ዋጋ ሽጦ ትርፉን ኪስ አስገብቷል። ለዚህ የአዲስ አበባ ህዝብ ትጠያቂ አይደለም፤ ኢህአዴግ እና ኦህዴድ ናቸው።

5. ታላቁ ግን ማንም የማያነሳው ጉዳይ የሀገራችን የመሬት ፖሊሲ ነው። መሬት የመንግስት በመሆኑ ነው ገበሬዎችም ሌሎችም የሚፈናቀሉት እና «ተፈናቀሉ» የሚባለው። አዲስ አበባ ሲሰፋ (እንደ ከተማ ይሁን እንደ metropolis) ዙርያ ያሉት ገበሬዎች ዋና ተጠቃሚ ነበር መሆን ያለባቸው፤ ይሆኑም ነበር መሬት የግል ቢሆን። አዲስ አበባ ዙርያ ያሉት ገበሬዎች ከተማው እየሰፋ ስለሄደ መሬታቸውን በእጅግ ውድ ዋጋ ሊሸጡ እና ሊጠቀሙ ይችላሉ። ቡልጋ ያለው ገበሬ የመሬቱ ዋጋ አንድ ብር በካሬ ቢሆን ይው መሬት አዲስ አበባ ዙርያ መቶ ብር ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ ነው የትም ሀገር ከተማ ሲሰፋ ዙራይ ያሉት ገበሬዎች ሎተሪ እንዳሸነፉ የሚቆጠረው። ግን ኢትዮጵያ ገበሬው መረቱን መሸት ስለማይፈቀድ እና መንግስት ሲፈልግ መንጠቅ ስለሚችል ከተማ ዙርያ ያለ ገበሬ ጭራሽ ይሰጋ! ስለዚህ በዚምህ ረገድ ጥፋቱ የአዲስ አበባ ህዝብ ሳይሆን የኢህአዴግ እና ኦህዴድ የመሬት ፖሊሲ ነው። አዲስ አበባ ዙርያ ያሉ ገበሬዎች በኢህአዴግ/ኦህዴድ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጥር ብር አጥቷልና!

Friday, 1 March 2019

የአዲስ አበባ ጉዳይ እና የሃላፊነት ፖለቲካ

በተለያዩ ጽሁፎቼ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሰረታዊ ችግር የ«ኢትዮጵያዊነት» ጎራው ለራሱ እጣ ፈንታ ሃላፊነት አለመውሰዱ ነው ብያለሁ። ላለፉት 50 ዓመታት ተደራጅቶ ፍላጎቶቹን አጣርቶ ከማስከበር ይልቅ ህልውናውን ለሌሎች ትቷል። ሃላፊነት ለሌሎች መታው ባህል አድርጎታል። ይህ አካሄድ የ«ለቅሶ ፖለቲካ» ብሄ ሰይምዬዋለሁ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/blog-post_16.html)።

ይህ ሁኔታ ምክንያት አለው፤ የኢትዮጵያዊነት ጎራው በአብዮቱ ጀምሮ እርስ በርስ ተገዳድሎ ልሂቃኑ እራሱን አጥፍቶ እስካሁን አላገገመም። (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/1.htmlhttps://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/2.htmlhttps://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/3.htmlhttps://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/4.html)። ቢሆንም በዚህ አካሄድ መቀጠል አይቻልም። ሌሎችን «ፍላቶእ እና መብታችንን አስከብሩልን» ብለን እየለመንን መቀጠል አይቻልም።

አሁን የሚያስፈልገን ከ«ለቅሶ ፖለቲካ» ወጥተን፤ ከህጻንነት እና ብሽተኝነት ወትጠን ወደ «ሃላፊነት ፖለቲካ» መግባት አለብን። ግድ ነው፤ አማራጭ የለም። እነ ለማ ይሁን አቢይ ይሁን ህወሓት ይሁን ግንቦት 7 ይሁን አብን ወዘተ እንዲህ አድርጉልን ብለን መለመን አይቻልም። ካሁን በኋላ ሁላችንም «ይህ ይሁን»፤ «ይህ ይደረግ»፤ «እከለ ይውደም» ወዘተ ከማለት ወደ «እኔ ይህን አደርጋለው» የሚለው አመለካከት መግባት አለብን። ልመና በቃ፤ የራሴን እጣ ፈንታ እራሴ ወስነዋለው ወደሚለው መግባት አለብን።

የአዲስ አበባ ጉዳይ የዚህ የአስተሳሰብ እና ተግባር ለውጥ አስፈላጊነት በደምብ ይገልጻል (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_97.html)። ልሂቃኖቻችን እስካሁን እነ ኢህአዴግን፤ ህወሓትን፤ ኦዴፓን፤ የኦሮሞ ብሄርተኞችን፤ አዴፓን፤ ጥ/ሚ አቢይን፤ ፕሬዚደንት ለማን፤ ወዘተ እባካችሁ እንዲህ እንዲያ አድርጉ አታድርጉ እያሉ ለው ዓመት ይጮሃሉ። ግን አንድ የሚባል የአዲስ አበባ ህዝብን ጥቅም የሚያንጸባርቅ እና ለማስከበር የሚሯሯት ድርጅት የለም? የአዲስ አበባ ህዝብ ህልውናውን ለሌሎች ሰጥቶ ሌሎቹ የሚፈልጉትን ሲአደርጉ ልሂቃኑ ያለቅሳል! ይህ ምን ማለት ነው? የአዲስ አበባ ህዝብ እራሱን አደራጅቶ ፍላጎቱን እና መብቱን ዘርዝሮ ማስከበር ካልቻለ እነዚህ የማይወክሉት ተቋሞች የፈለጉትን ያደርጋሉ። ይህ እኮ እጅግ basic የሆነ ነገር ነው።

እስከ ዛሬ የኛ ልሂቃን እና ሚዲያ ይህን መሰረታዊ ጉዳይ ትተው በማልቀስ እና መለመን ነው የዋሉት። የራሳችንን ጥፋት (አለመደራጀት) ላለማየት ትብሎ ህልውናችንን አደጋ ውስጥ ከትተናል! ይህ ሁሉ ችግር ስላልተደራጀን ነው እና እንደራጅ ከማለት ሌሎች ስለሚያደርጉት እናለቅሳለን። ይህ ለቅሶ ምንም ለውጥ አላመጣም አያመጣምም። ህዝባችን በንዴት እንዲደራጅ አላደረገም። ይባስ ሌሎች ላይ ጣት በመጠቆም የራሳችንን ጥፋት እንዳናይ ስበብ ሆኖናል። ጉርጓዳችንን ይበልጥ እንድንቆፍር አድርጎናል።

አሁን ግን አንዳንዶች መራራ የሆነውን መድሃኒት ውጠን ወደ ፊት መራመድ እንዳለብን የገባቸው ይመስላል።


ከዚህ ከኢሳት ዝግጅት የአዲስ አበባ ህዝብ መዋናነት መደራጀት አለበት ትባለ። ያለመደራጀታችን ጥፋታችንን አመንን ማለት ነው፤ ይህን ማመን ነው መራራው መድሃኔት። ካመንን በኋላ ሙሉ አቅማችንን ወደ መደራጀት ስራ ማሰለፍ ነው ያለብን። ካሁን ወድያ አንዳች የልሂቃን እና ሚዲያ ደቂቃ በእሮሮ፤ ለቅሶ፤ እና ልመና መጥፋት የለበትም። ሙሉ አቅማችን ወደ መደራጀት።

ምን ማለት ነው የመደራጀት ስራ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/blog-post_18.html)? ብዙ ሚስጥር የለውም፤ የህዝብ የማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መደራጀት ለሺዎች ዓመታት የተደረገ ነገር ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ «የአዲስ አበባ ህዝቦች ድርጅት» ያስፈልገዋል። የዚህ ድርጅት (ድርጅቶች) ተእልኮ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ጥቅም ማስከበር ነው። ቀላል ተእልኮ ነው፤ ሌላ ጣጣ አያስፈልገውም። ድርጅቱ በርካታ (በመቶ ሺዎች የሚቆጠር) አባላት ያስፈልጉታል። ባለ ሃብቱ በደምብ መሳተፍ አለበት። ስብሰባ፤ ሰርቬ፤ ምርጫ፤ ወዘተ የሚያካሄድ መሆን አለበት። አባላቶቹ በየ ማህበራዊ ዘርፍ፤ በየ መስርያቤት፤ በዬ ሰፈሩ የሚሰሩ እና የሚኖሩ መሆን አለባቸው። ድርጅቱ ሰፊ ኔትወርክ ኖሮት «የሚፈራ» ማለትም አቅም ያለው መሆን አለበት። በተለያዩ የከተማው ጉዳዮች፤ መብራት፤ ውሃ፤ መንገድ፤ ደህንነት፤ ጤንነት፤ መፈናቀል፤ ውክልና፤ ወዘተ የሚሰራ መሆን አለበት። በዴሞክራሲያዊ መልኩ የአባላቱን ፍላቶ የሚያውቅ፤ የሚያስከበር እና የሚወክል መሆን አለበት።

ይህ ድርጅት ሲኖር፤ ዛሬ ቢኖር ስለ አዲስ አበባ ያለው ጭቅጭቅ አይኖርም ነበር። ሁሉም ተሳታፊዎች የአዲስ አበባ ህዝብ ፍላጎትን አበጥረው ያውቃሉ። የሁሉም አቋም ሰልሚታወቅ የፖለቲካ ድርድሮች በግልጽ እና በጽጋ ይካሄዱ ነበር። የለገጣፎ ሰዎች አይፈናቀሉም ነበር። ጉዳዩ ገና ሲነሳ ድርጅቱ ተሳትፎበት ድርድር ተደርጎበት በሰላም በሁሉም የሚያስማማ መልኩ ይፈታ ነበር። የኦሮሚያ «ልዩ ጥቅም» ጉዳይም እንዲሁ። ወካይ ድርጅት ቢኖርን «ልዩ ጥቅም» ብለን አናለቅስም ነበር። ድሮውኑ ተደራድረን የልዩ ጥቅም ትርጉም ላይ ተስማምተን ነገሩ በሰላም ይወሰን ነበር። ወዘተ።

የአዲስ አበባ ችግር የመጣው በህወሓት ምክንያት አይደለም። በኦሮሞ ብሄርተኞች ምክንያት አይደለም። መሰረታዊ ችግሩ የአዲስ አበባ ህዝብ እርስ በርስ ተስማምቶ አለመደራጀቱ ነው። ይህን አምነን አንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለቅሶ እና ልመናችንን ትተን ሙሉ አቅማችንን ወደ መደራጀት ማዋል አለብን። አለበለዛ በየበታችንነት እና ተገዥነት ስሜት እንደተገዛን እንቀጥላከን። መገዛት ማለት የራስን እጣ ፈንታ ለሌሎች መተው እና በራስ ህይወት ሃላፊነት አለመውስውድ ነው። ይህ ላለፉት በርካታ ዓመታት ጉዞአችንን ይገልጻል።

Friday, 22 February 2019

የጅልነት ፖለቲካ

አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት በተለያየ መንገድ ፍላጎታቸውን በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ መጫን እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። አቋም ከመውሰድ እና ከመናገር አልፎ በተግባር ስራቸውን ሰርተዋል። የአዲስ አበባ «ወጣቶችን» በጅምላ አስረዋል። አዲስ አበባን እናደራጅ ያሉትን አስረው አስፈራርተዋል። ከለገጣፎ አፈናቅለዋል። ወዘተ። እንዲህ በማድረግ አክራሪው ቡድን አቅታጫውን በግልጽ አስቀምቷል። የማስፈራራት ዘመቻውን ቀጥሏል።

ለነገሩ ይህ (ይቅርታ አድርጉልኝ) የጅልነት ፖለቲካ አካሄድ ነው። የሚበጃቸው የነበረው የአዲስ አበባ ህዝብን ሳያስቀይሙ ሳይነሳሱ ቀስ ብለው ውስጥ ለውስት ስራቸውን መስራት ነበር። ግን የጡንቻ አካሄድ መርጠው የአዲስ አበባ ህዝብን ያናድዳሉ እና ተነስቶ እንዲደራጀና መብቱን እንዲያስከበር ያደርጉታል።

ይህ ነው የጅልነት ፖለቲካ። ግን ምና ያመጣሉ ነው ይህን የሚያደርጉት! የአዲስ አበባ ህዝብ እና ጠቅላላ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራው ምን ያመጣል ነው። ስለዚህ ማን ነው ጅሉ። እኛ ነን።

ለገጣፎ ለሚከሰተው የአዲስ አበባ ህዝብ ሃላፊነት አለብን

ደርግ የ«ከበርቴን» ቤተና ንብረት ሲቀማ በምቀኝነት ተሞልተን አጨበጨብን። እርግጥ ነው አንዳንዱ አላግባብ ብዙ መሬት ይዞ በተከራዮች ይጫወት ነበር። ግን ሌሎች ትንሽ ንብረት የነበራቸው ነበሩ በዚሁ መአበል የተጥለቀለቁ። የሚያከራዩት ሶስት አራት ቤቶች ሲወረሱ ባዶአቸውን ቀሩ። ማንም አላዘነላቸውም። «እንኳን ተነጠቁ» ብለን የጅምላ ፍርድ ላይ ነበርን።

በህወሓት ዘመን ደግሞ ለ«ልማት» እና «ኢንቬስትሜንት» ተብሎ የበርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ንብረት በምንግስት ተነጥቋል። አንዳንዱ ባዶውን ቀረ። አንዳንዱ እጅግ አነስተኛ ካሳ ተሰጥተው። ሌላው ከከተማ ውጭ ባዶ መሬት ላይ ተወረወረ። ይህ ሁሉ ሲከሰት የአዲስ አበባ ህዝብ (በጅምላ ለማውራት) ምንም አላደርገም። እርግጥ መጮህ እና መደራጀት ሊያሳስር እና ሊያስገድል ይችል ነበር። ግን ገንዘብ ሰብስቦ ለተፈናቀሉ ተጎጂዎች መስጠት ምንም ቅጣት አያስቀጥልም ነበር። ከኔ ጀምሮ አንዳችን ይህን አላደረግንም። የባለንጀሮቻችንን ህምም ዝም ብለን ተመለከትን።

ዛሬም እንዲሁ። ለገጣፎ የሚኖሩ ወንድም እህቶቻችን ቤቶቻቸውን እያጡ እያለ ከመጮ ሌላ ምንም አናደርግም። አንረዳቸው፤ አንደራጅ። ትንሽ ጉዳዩ ያናደደን ካለን መንግስት ላይ ጣታችንን እንጠቁማለን!

ከዛ ይልቅ እራሳችን ላይ ነው መፍረድ ያለብን። የአዲስ አበባ ህዝብ ለባለንጀራው በአግባቡ ቢራራ እስካሁን ተደራጅቶ የህ አይነት ግፍ እናይከሰት ማድረግ ይችል ነበር (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2019/02/blog-post_22.html)። ግን አላደረገውም፤ አላደረግነውም።

ስለዚህ ጥፋቱ በዋነኝነት የኛ የአዲስ አበባ ህዝብ ነው። ጣቶቻችንን ሌሎች የማይሰሙን ላይከመጠቆም ስራችንን ሰርተን ተደራጅተን እርስ በርስ ብንጠባበቅ ለሁሉም፤ ለጎጂዎቻችንም ለመላው ሀገራችንም፤ ጠቃሚ ነበር። ለችልተኛችን ንስሃ ገብተን ወደ ስራ እንግባ። ሌላ መፍትሄ የለም!

የአዲስ አበባ ህዝብ ካልተደራጀ ለገጣፎ ይደጋገማል

https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_97.html

የለገጣፎ ነዋሪዎች መፈናቀል ድርጊት በምንም ሚዛን እጅግ አሳፋሪ እና ለሁላችንም ጎጂ መሆኑ ግልጽ ያልሆነለት... ይቅርታ አድርጉልኝ እና የድሮ የፖለቲካ ደንቆሮ ነው።

ሆኖም እንደዚህ አይነት መፈናቀል እና ተመሳሳይ ክስተቶች ለ27 ዓመታት ሲካሄዱ ቆይተዋል። ወደ ኋላ ከሄድንም ደርግ የ«ከበርቴዎችን» ቤት እና መሬት አለ ፍትህ፤ ሚዛን፤ እና ርህራሄ ቀምቷል።

የአዲስ አበባ ህዝብ ይሁን ሁሉ ያትዋል አሳልፏልም። በርካታ ሰለቦች አይተናል። ግን አንዴም ጣታችንን አንስተን እንርዳችሁ፤ ይህ ክስተት እንዳይደገም ተደራጅተን ለእርስ በርሳችን እንቁም ብለን አናቅም። ይሉቅንስ ወይ ተባብረናል፤ አንገታችንን ደፍተናል፤ ወይንም ለተጎጂዎች ከመራራት ፋንታ ፈርደንባቸዋል።

በዚህ ምክንያት አሁንም ባለንጀሮቻችን፤ ጎረቤቶቻችን፤ ወንድም እህቶቻችን እጣ ፈንታቸው ከሆነ መሬት እና ቤቶቻቸውን ይነጠካሉ። ዛሬ ለገጣፎ ነው ነገ ሌላ ቦታ። የኦሮሚያ መንግስት ተወካዮች ይቀጥላል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ህዝብ እንደዚህ አይነት ኢ-ሰባዊ ድርጊቶች እንዲቆሙ ከፈለገ ከመደራጀት በስተቀር ምንም ማድረግ አይችልም። መቾህ፤ ቂም መያዝ፤ ማዘን ወዘተ ብዙ ዋጋ የለውም። አንድ እና አንድ ምርጫ ብቻ ነው ያለው፤ መደራጀት።

ምን ማለት ነው መደራጀት? መቼስ ፖለቲከኞቻችን ሊያውቁ እና ሊያስተምሩን ይገባል ግን እስቲ ለኛ ብዙሃን በምሳሌ መልኩ ልዘርዝረው። ልብ፤ እውቀት፤ እና ገንዘብ ያላቸው «የአዲስ አበባ ዜጎች ድርጅት» የሚባል ያቋቁማሉ። የድርጅቱ ተዕልኮ የአዲስ አበባ ህዝብን ፍላጎትን እና ደህንነትን ለማስከበር መሟገት ይሆናል። ድርጅቱ በየ ቀበሌው፤ በየ ህዝብ ዘርፍ (ነጋዴ፤ ሞያተኛ፤ አስተማሪ፤ እናቶች፤ ወዘተ) አባላት እና ገንዘብ ይመለምላል። ትምሕርት ያስተምራል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ይሰበስባል። እነዚህ አባላት በዬ ህብረተሰብ ክፍል እና መንግስት መስርያቤቶች ያሉ ይሆናሉ እና በይፋም በህቡም ለድርጅቱ እና ለአዲስ አበባ ህዝብ ተጽዕኖ ማድረግ የሚችሉ ይሆናሉ። እንድነ ለገላፍቶ አይነት ክስተት እንደሚካሄድ ሲታወቅ ይህ ድርጅት በሁሉ ዘርፍ ተጽዕኖ ያደርጋል። እንደዚህ አይነት የማፈናቀል እና ሌላ ህዝቡን የሚጎዳ እቅድ እንዳይታሰብ ያደርጋል።

አሁን የደረደርኩት ምሳሌ አዲስ እንዳልሆነ መቼስ ሁላችንም እናውቃለን። ዓለም ዙርያ ለሺ ዓመታት ፖለቲካ በዚህ መልኩ ነው የሚካሄደው። እንኳን የሰላም ፖለቲካ የጦር/ኃይል ፖለቲካም እንዲሁ ተደራጅቶ ነው የሚሰራው። ስለዚህ የአዲስ አበባ ህዝብ ማድረግ ያለበት የተለየ እና በተለየ መልኩ ከባድ ነገር አይደለም። ለአካባቢ ጥቅም መደራጀት ቀላል እና የተለመደ የሰው ልጅ አካሄድ ነው።

ታድያ ለምንድነው የአዲስ አበባ ህዝብ እስካሁን ያላደረገው? በነ ግምት የአዲስ አበባ ህዝብ ይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ (ሀገር) ብሄርተኞች ከ66 አብዮቱ እና ሽብሮቹ እስካሁን አላገገመም። አብዮት ተከታታይ ትውልዶች እንደሚያተፋ ይታወቃል በሀገራችንም እንዲሁ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራውን እርስ በርስ አፋጅቶ ድምጥማጡን አጥፍቷል። ስለዚህ የአዲስ አበባ እና ጠቅላላ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ፖለቲካ አሁንም እጅግ ደካማ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_38.html)።

ይህ እንደሆነ እውነታው የአዲስ አበባ ህዝብ ካልተደራጀ እንደ ለገጣፎ አይነት ኢ-ሰባዊ ክስተቶችን ማቆም እንደማይቻል ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ ደጋግሞ ይረገጣል። ከመደራጀት በቀር ምንም መፍትሄ የለም። ለመድገም ያህል እሮሮ ማሰማት፤ ማልቀስ፤ መርገም፤ መለፍለፍ ወዘተ ዋጋ የለውም። ከባዱ የመደራጀት ስራ ግድ መሰራት አለበት።

Thursday, 18 October 2018

የአዲስ አበባ ህዝብ መደራጀት፤ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ

ትላንት ሁለት የአዲስ አበባ ሰዎች በማይሆን ክስ ታስረዋል። ከሱም እንደገባኝ ከሆነ ወጣቶችን በ«አዲስ አበባ በከተማው ተወላጅ ነው መመራት ያለበት» መፈክር ዙርያ ማደራጀት ነው። ለዚህም አደረጃጀት ከፍልስቴም ኮንሱሌት ጋር ተባብረዋል ነው ሌላው ክስ። እነዚህ ስራዎች በፍፁም ህገ ወጥ አይደሉም እና መታሰር እንደሌለባቸው ግልጽ ነው። ሆኖም ትላንት እነዚህ እስረኞች በጭለማ ቤት እየተሰቃዩ (torture) ይገኙ ነበር። ዛሬ ደህና ፍርድ ሳያገኙ አይቀርም። መከራ ለነሱ ቢሆንም መሻሻል ነው።

በዚህ ግዳይ በርካቶች አቤቱታ እያቀረቡ ነው። ጥሩ ነው፤ እንደዚህ አይነት የማይሆን እስርን መቃወም አለብን። ግን እንደምናውቀው ፖለቲካችን ከመቃወም ወደ መስራት መሻገር አለበት። Proactive politics beats reactive politics anytime።

መሰራት ያለበት ስልታዊ አደረጃጀት ነው። በመጀመርያ ለምንድነው «ወጣቶችን» የምናደራጀው? ሰራተኛው የት አለ? ወዝ አደሩ የት አለ? የቢሮ ሰራተኛው የት አለ? ወላጆች የት አሉ? ጡረተኞች የት አሉ? መከከለኛ መደቡ የት አለ? ሃብታሙ የት አለ? «የተማረው» የት አለ? ምሁራኑ የት አለ? ልሂቃኑ የት አለ? ለምንድነው «ወጣቱ» (እውነቱን ለመናገር ስራ የሌለው ወጣት) ሸክሙን መሸከም ያለበት?

ይህ «ወጣትን» ማደራጀት ዘላቂነት እንደሌለው ይታወቃል። ሁሉም ህዝብ መሳተፍ አለበት ለእውነተኛ የዜግነት ፖለቲካ ወይንም የሲቪክ አደረጃጀት። ወጣቱ ተሳትፎ ሌላው ከሸሸ ዋጋ የለውም ብቻ ሳይሆን ጎጂም ሊሆን ይችላል። እንደ ሜኪናን በአራተኛ ማርሽ ማስጀመር ማለት ነው።

ሌላው ችግር ገና መደራጀቱ በተገቢው ሁኔታ አይጀምር እራስን ለጥቃት ማጋለጥ ነው። እኔ እንደሚገባኝ የአዲስ አበባ መደራጀት አላማ «የአዲስ አበባ ህዝብ መብቱ እንዲከበር» ነው። ከንቲባው የአዲስ አበባ ትውልድ ይሁን አይሁን አይደለም። የአዲስ አበባ ህዝብ መብት ከተጠበቀ ምርጫ ይኖራል እና ህዝቡ የፈለገውን ይመርጣል። ግቡ እንዲህ ግልጽ ሆኖ ካየነው እና ግቡ ላይ ካተኮርን 1) ስራችንን በትክክሉ እንሰራለን እና ይሳካልናል 2) ለጥቃት እራሳችንን አናጋልጥም!

አካሄዱ እንደሚመስለኝ እንዲህ ነው መሆን ያለበት፤

1) በጣም ሰፊ ተዕልኮ (vision and mission) ያለው ድርጅት ማቋቋም፤ ለምሳሌ «የአዲስ አበባ ህዝብ መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚሰራ» ድርጅት ማለት ነው። ሀ) ሰፊ ተዕልኮ ስለሆነ ለመጠቃት መጋለጡ አነስተኛ ነው የሚሆነው። ለ) ብዙ ሰዎችን በተለይም «መደራጀት» ሲባል የማይገባቸው ወይንም የሚፈሩትን ይጋብዛል። እናቶች፤ ወላጆች፤ መካከለኛ መደቡን። ሃብታሙን ወዘተ ይጋብዛል።

2) ከመፈክር በፊት መደራጀት። መጀመርያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከፋይ አባላት ይኖረው። ከዛ በኋላ ነው መንቀሳቀስ። እንቅስቃሴው ከአቅም ጋር አብሮ መሄድ አለበት! እንቅስቃሴው ከአቅም ጋር አብሮ መሄድ አለበት! አቅም ሳይጎለበት መራመዱ ጥቃትን መጋበዝ ነው። የቅንጅት ታሪክ ይህን ነው የሚያስተምርን። ቅንጅት በመቶ የሚቆጠሩ መሪዎች እና አባላት ነበረው ከዛ ቀጥሎ እስከ ብዙሃኑ ድረስ ከሞላ ጎደል ባዶ መዋቅር ነበር። ጥቂት መሪዎች እና ብዙ ብዙሃን። መሃሉ ባዶ ነው። እነዚህ ጥቂት መሪዎች ሲጠቁ እና እርስ በርስ ሲጣሉ ማን ይተካቸው። መዋቅሩ እስከ ታች ባዶ ነበርና። ስለዚህ መጀመርያ መጠንከር ከዛ ወደ ዋና ስራ መግባት ነው ትክክለኛ አሰራር። ይመስለኛል።

የአዲስ አበባ ህዝብ ወይንም ጠቅላላ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ ወኪላዊ ድርጅቶች መደራጀት አለበት (በዜግነት ፖለቲካ ካመንን)። አለበለዛ ያው የጎሳ ፖለቲካ ማለትም የግጭት ፖለቲካ ነው የሚቀረን። ለሀገራችን ህልውና ቅድመ ሁኔታ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ይህን ዋና ስራ በሙሉ ተሳትፎ በሰከን ያለ ብልጥ መንገድ እንስራው። ህዝብ በሙሉ እንዲሳተፍ እናድርግ።

«እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።»

Wednesday, 17 October 2018

ኢትዮጵያን የሚገላት የአንድነት ኃይሉ ነው (ክፍል 2)

ወኪሎች ማፍራት ያልቻለ ህዝብ ይጠፋል።

አዲስ አበባ የአምስት ሚሊዮን በ«ኢትዮጵያዊነት» የሚያምን ህዝብ ከተማ ነው። ቅንጅት በ100% መርጧል። ግን ይህ ህዝብ አንድም የፖለቲካ እና ማህበራው መብቱን የሚከራከርለት፤ የሚሟገትለት፤ የሚወክለው ድርጅትን ማቋቋም አልቻለም። አንድም!

ታድያ መብቶች ሲገፈፉ፤ ፍትህ ሳይኖር፤ ሰላም ሲጠፋ ምንድነው ምክንያቱ? ትብብር እና ድርጅት የሌለው ህዝብ እንዴት ፍትህ እና ሰላም ይኖረዋል? ማን መብቱን ያስከብርለታል እራሱ ካላስከበረ?!

ወኪሎች ማፍራት ያልቻለ ህዝብ ይጠፋል።

አንድ ምሁራን እንዲህ ብልዋል፤  “When people realize things are going wrong, there are two questions they can ask. One is, ‘What did we do wrong?’ and the other is, ‘Who did this to us?’ The latter leads to conspiracy theories and paranoia. The first question leads to another line of thinking: ‘How do we put it right?’”

Monday, 15 October 2018

የአዲስ አበባ ወጣቶቻችን፤ Nameless and faceless

ዛሬ በመሃበራዊ ሚዲያ ለ«ታፈሱት የአዲስ አበባ ወጣቶች» ፍትህ መጠየቂአ ቀን ይመስላል። ጥሩ እቅድ ነው።

ግን ማናቸው እነዚህ «ወጣቶች»? መስላቸው የት አለ? ስማቸውስ? ቤተሰቦቻቸው የት አሉ? ልጆች አላቸው ይሆን? ወላጆቻቸው የት ናቸው? እየተፈለጉ ነው ወይ? ማን ስለነሱ በየቤቱ እያለቀሰ ነው?

እኔ እስከመቀው ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ የለንም። ለምን የለንም? እንዴት በመቶዎች ወይንም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታፍሰው ወደ ወታደራዊ ካምፕ ሲወሰዱ ምስላቸው፤ ስማቸው፤ ቤተሰቦቻቸው አይመዘገቡም? አዲስ አበባ የአምስት ሚሊዮን ህዝብ ከተማ ናት። ልጆቿ እንዲህ አይነት ነገር ሲደርስባት እንዴት ዝርዝሩን አናውቅም? ኤንዴንት ቤተሰቦቻቸው ወይንም ወኪሎቻቸው በተለያየ ሚዲያ ወጥተው እንዲታዩ ወይንም እንዲናገሩ አይደረግም? ለምንድነው faceless ሆነው የሚቀሩት?

ለነዚህ ጥያቄዎች መሰረታዊ ምክንያቱ የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ህዝብ እንደዚህ አይነት ጥቃቄዎችንም የሚያስተናግድ እና የሚመልሱ አቅም ያላቸው የፖለቲካ እና ማህበራዊ ተቋሞች ስለሌለው ነው! እነዚህ ወጣቶች ከተታፈሱ በኋላ ሁላቸውም ከነ ምስላቸው፤ ስማቸው እና ቤተሰቦቻቸው ተመዝግበው እንደ አግባቡ በሚድያ መቅረብ ነበረባቸው። ወጣቶቹን የሚመዘግብ፤ ሁኔታቸውን የሚከታተል፤ ሰለነሱ የሚሟገት እና የአዲስ አበባ ህዝብን ሰለ ጉዳያቸው የሚያሳውቅ ድርጅት ሊኖር ይገባ ነበር! የአምስት ሚሊዮን ከተማ ነው፤ ይህ ሊሳነው አይገባም።

ስለዚህ ይህ ነው መሰረታዊ ችግሩ/ችግራችን። አልተደራጀንም። መደራጀት ለህልውናችን ግድ ነው። ይህ መሰረታዊ ችግር ካልተፈታ ህመሞቻችን ይቀጥላሉ! (If we don't address the fundamental cause we'll keep running after the symptoms and never catch up)።

ስለዚህ ጉዳይ ሌላ ነገር ላንሳ። እስቲ ስንቶቻችን ነን የነዚህ ወጣቶችን ቤተሰቦች አይዝዋችሁ እያልን የምንገኘው? የሚያስፈልጋቸው እርዳታ ካለ የምናረግላቸው? ለባለንጀራዬ ካላሰብኩኝ ለምን ሌላው ያስባል ብዬ አስባለሁ። በችግር ጊዜ ካልደረስኩለት ምን አይነት መተማመን እና ትብብር ይኖረናል? ይህ ሌላ መሰረታዊ ችግር ነው። የእርስ በርስ ግንኙነታችን (social capital) መንኗል። ፍትህ እና ሰላም ከፈለግን ይህ መታደስ አለበት።

https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_14.html

https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_97.html

Tuesday, 2 October 2018

የአዲስ አበባ ተፈናቃዎች

የኛ የአዲስ አበባዎች አንዱ (ከብዙ) ድክመቶቻችን በዚህ ቪዲዮ ይገለጻል፤

https://www.youtube.com/watch?v=fhKBwe1wF2Y

ይህ ድክመት ከመሬታቸው የተፈናቀሉት ወንድሞች እይቶቻችን ጎረቤቶቻችንን ዞር ብለን አለማየት ነው። በመቶ ሺዎች «የብሎኬት ካሳ» ተሰጥተው ከቤታቸው ወደ ዳር ከተማ ባዶ የሆነ 70 ካራሜትር ተባርረዋል።

ሰፈር ከነ ማህበራዊ ኑሮ ተበታትነዋል። አብዮተኛ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ማለት ይቻላል። ይህ ለተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆን ለመላው የአዲስ አበባ ህዝብ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ ይታወቃል። "Social capital" ከሰረ፤ መተባበር ጠፋ፤ መተዋወቅ ጠፋ፤ መደጋገፍ ጠፋ፤ ማህበራዊ ግብረ ገብ ጠፋ፤ ኢ-ማህበራዊነት በዛ፤ ወንጀል በዛ ወዘተ።

አንዱ ለችግሩ መፍትሄ የመሬት ፖሊሲውን መቀየር ነው።

1. ካሁን ወድያ መንግስት መሬት መውሰድ የሚችለው ለመንግስት ጥቅም እንደ መብራት፤ ውሃ፤ መንገድ ወዘተ ይሁን። ካሳውም የ«ብሎኬት ዋጋ» ሳይሆን የመሬቱ ከነቤቱ የገበያ ዋጋ መሆን አለበት።

2. መሬት ለግል ጉዳይ እንደ ኢንቬስትሜንት ከተፈለገ ኢንቬስተሩ በግል ከመሬት ባለቤቶቹ መሬቱን ተደራድሮ ይግዛ። መንግስት ጣልቃ አይግባ። ገዥ እና ሻጭ ከተስማሙ ሁለቱም ደስተኛ ይሆናሉ። ኢንቬስተሩ የገበያ ዋጋ ስለከፈለ በመሬቱ አይቀልድም አዋጪ ነገር ላይ ያውለዋል። ሻጩም ተበድያለሁ አይልም በራሴ የወሰንኩትን አገኘሁኝ ብሎ ያምናል።

የሚጠቀም ሶስተኛ ወገኖችም አሉ። መላው የአዲስ አበባ ህዝብ ከመፈናቀል የሚያመጣው ጠቅላላ ህምሞች ይተርፋል። የመንግስት ሰራተኞችም ከሙስና ፈተና ይድናሉ። ማፈናቀል ወይንም የመሬት ፖሊሲው በጠቅላላ ካድሬዎች በረካሽ አፈናቅለው በውድ ለኢንቬስተር በመስጠት ሙስና የጋበዘ ስርዓት ነበር። ፖሊሲው ከተቀየረ ሁላችንም ከዚህ ሁሉ እንተርፋለን።

Monday, 17 September 2018

የአዲስ አበባ ህዝብ፤ ፍርሃት እና ህፍረት

ሁላችንም ቄሮ፤ ፋኖ፤ አቢይ፤ ለማ፤ ኦነግ፤ ግንቦት 7 ወዘተ ሲባል ህወሓትን ከስልጣን ማውረድ የተቻለው የ27 ዓመት የተጠራቀመ የግለሰቦች እና የቡድኖች ትግል እንደሆነ እንረሳለን። አንዱ የትግል ዘርፍ ምርጫ 97 ዙርያ በተለይም በአዲስ አበባ የተደረገው ተቃውሞ እና የህዝብ አመጽ ነበር። በዚህ ልጀምርና…

ሁላችንም እንደምናውቀው ለ27 ዓመታት የአዲስ አበባ ህዝብ በፍርሃት ነው የኖረው ማለት ይቻላል። (የብሄር ብሄረሰቦች) ጨቋኝ፤ ገዥ፤ ትምክህተኛ ወዘተ ተብሎ በመንግስት ትርክት ተሰይሟል። ይህ ህዝብ ነገ በጎሳ ብሄርተኞች ተከበን እንወራለን፤ እንገደላለን እና እንፈናቀላለን ብሎ በስጋር ይኖራል። ይህን አይነት ክስተት ደግሞ በተለያየ የኢትዮጵያ ክልሎች ሲከሰቱ አይቷል። አዲስ አበባ ከበየቦታ የተፈናቀሉትን ተቀብሏለችም!

በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባ ህዝብ ይህ በእውነት የተመሰረተ ፍርሃት ምንጭን ለመከላከል ተባብሮ መደራጀት አልቻለም። አዎን በምርጫ 97 ለተወሰነ ጊዜ አሸዋ ላይ ተደራጀ ግን ይህ ወድያው ፈረሰ። አልፎ ተርፎ ህዝቡ ይበልጥ እንዲፈራ እና መደራጀት እንዳይሞክር አደረገ።

ሆኖም የአዲስ አበባ ህዝብ በልቡ መደራጀት እንደሚገባው ያውቃል። የህዝብ ቁጥር እና አቅም እንዳለው ያውቃል። መደራጀት ያልቻለበት ምክንያት የራሱ ድክመት እና ጥፋት መሆኑም በተወሰነ ደረጃ ውስጡ ያውቃል። ጭቆናውን ችሎ መደራጀት እንደነበረበት ያውቃል።

ህወሓት ደጋግሞ እንድተጫወተበትም ያውቃል። ለኔ ስገዱ አለበለዛ ጎሰኞቹን ለቅባችኋለው እያለ ቆዬ። የአዲስ አበባ ህዝብ እራሱን አጠንክሮ ዞርበል ከማለት ፈርተን ዝም አልን። እውነታውን እንመን።

ይህ ነው የአዲስ አበባ ህፍረት የምለው። የተገዛው በትንሽ የምትባል ቡድን (ህወሓት) እንደሆነ ያውቃል። ህወሓት አንድ ለአምስት በሚባለው የቁጥጥር ዘዴ ሲፈጸምበት በራሱ ድክመት እንደሆነ የሚገዛው ህዝቡ አውቋል። ቄሮ እና ፋኖ ሲወራላቸው ዝም ብሎ ቁጭ እንዳለ ያውቃል። ይህ ለአዲስ አበባ ህዝብ ታላቅ የስነ ልቦና ቁስል ሆኗል። የዝቅተኛ መንፈስ እንዲያድርበት፤ አቅም የሌለው እንዲመስለው፤ የተዋረደ እንዲመስለው አድርጓል። ይህ ነው የአዲስ አበባ ህዝብ ሀፍረታችን።

ፍርሃት እና ህፍረት ስላለን ነው በቀደም ኦነግ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ ችግሮች የተፈጠሩት። ህዝቡ ፍርሃቱን በእውን አየው። የሚፈራው የሚፈራቸው ሲገቡ ደንግጧል። በሌላ በኩል ደግሞ እንዳልተደራጀ እና አቅሙን እንዳልሰበሰበ ያውቃል እና ታላቅ insecurity ተሰምቶታል። ሰለዚህም ነው በሰንደቅ አላማ እና አርማ ዙርያ ግጭቶች የነበሩት። ከፍርሃት የመነጨ ምላሽ ነው የአዲስ አበባ ውጣቶች የሰጡት።

እዚህ ላይ አንድ aside ያስፈልጋል። መደራጀት ማለት መዋጋት አይደለም። ውግያ እንዳይኖር ጠንክሮ ስልታማ ሆኖ መገኘት ነው። ግዙፍ አቅም እና ስነ ስረዓት ያላቸው የህዝብን አላማ የሚያስፈጽሙ መዋቅሮችን መፍጠር ማለት ነው። እነዚህ መዋቅሮች ብዙ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ለምሳሌ በከተማ አስተዳደር፤ በምሃበራዊ ኑሮ ጉዳዎች፤ በጸጥታ ዘርፍ፤ በፍትህ ወዘተ። እነዚህ ህዝብን የሚወክሉ መዋቅሮች ቢኖር ሁሉም የአዲስ አበባ ድርጅቶች በህዝብ ፍላጎት እንዲመሩ፤ ተጠያቂነት እና ግልጸኝነትት እንዲኖር ወዘተ ያደርጋሉ። በአጭሩ ህዝቡን አንድ ገልጽ ላይ ያደርጋል። እነዚህ መዋቅሮች ቢኖሩ ኦነግ ሲገባ ህዝቡ ምንም አይመስለውም ነበር። ምንም አይነት ኃይልን መቋቋም የሚችሉ መዋቅሮች እንዳሉት ስለሚያውቅ። ጭራሽ የኦነግ አርማ ይዞ ለመቀበል ይወጣ ነበር! መደራጀት ይህ ማለት ይህ ነው። በአጭሩ አዲስ አበባ በአዲስ አበባ ህዝብ ፍላጎት እንዲመራ ማድረግ ነው።

ዛሬ የአዲስ አበባ ህዝብ እንደ መላው ኢትዮጵያ ህዝብ በፍጥነት በዚህ መልኩ መደራጀት አለበት። የፖለቲካ ፓርቲ መፍጠር አለበት ወይንም እንደ ግንቦት 7 አይነቱ ጋር ተባብሮ ለአዲስ አበባ መዋቅር መዘርጋት አለበት። ሚዲያ መመስረት አለበት። የባህላዊ ድርጅቶችን በአንድ ጃንጥላ ስር ማሰባሰብ አለበት። ህዝቡ የሚወያይበት መዋቅሮች መዘርጋት አለበት። በጥቅልሉ ህዝቡን በአንድ ገልጽ የሚያደርገው መዋቅሮች እና ድርጅቶች መፈጠር አለበት። ነጻነት ማለት እንደዚህ አይነት የፖለቲካ ሃላፊነትን መወጣት ነው።

ግን በመጀመርያ ፍርሃት እና ህፍረታችንን ማመን አለብን። ይህ መደበቅ የለበትም። ስለዚህ በይፋ ማውራት መቻል አለብን። እውነቱ ከሃሰቱ መለየት አለበት። ይህም በውይይት እና መመካከር ነው የሚመጣው። አንዴ ፍርሃት እና ህፍረታችንን ካመንን በኋላ ወደ መፍትሄ ለመሄድ ይቀለናል።

Tuesday, 14 August 2018

ተረት ተረት፤ አዲስ አበባ የሰፋችው ኦሮሞ ገበሬን በማፈናቀል ነው

እንደ አብዛኛው ውሸት «አዲስ አበባ የሰፋችው ኦሮሞ ገበሬን በማፈናቀል ነው» የሚለው የተወሰነ እውነታ አለው። አዎን በኢህአዴግ አገዛዝ በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ ገበሬዎች ለመሬታቸው ከሚገባው እጅግ ዝቅተኛ የሆነ ካሳ ተከፍሏቸው በግዴታ ከመሬታቸው ተባረዋል። ግን ይህ ሙሉ ታሪኩ አይደለም።

እንደሚታወቀው በሀገራችን መሬት የመንግስት ነው የሚል አሳዛኝ ህግ ነው ያለው። ይህ ህግ ሲተገበር ስናይ መንግስት ባሰኘው ጊዜ የከተማም ይሁን የገጠር መሬት ከነዋሪዎች ይወስዳል። ሲወስድ ደግሞ የሚከፍለው ካሳ የ«ገበያ» ዋጋ ሳይሆን መንግስት እራሱ የሚተምነው እጅግ አናሳ ካሳ ነው። ልምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ለ«ልማት» ተብሎ መሬትን መንግስት ሲወስድ የሚከፍለው ካሳ የቤትና የጊቢው አብሮ ዋጋ ሳይሆን የቤቱ (የግንቡ) ዋጋ ብቻ ነው። ለምሳሌ 100 ካሬ ላይ ቤት አለኝ ከሸጥኩት 500,000 ብር ያመጣል እንበል። መንግስት ሊወስደው ከፈለገ ግን የቤቱ ግምብ ዋጋ ብቻ እራሱ (ሶስተኛ ወገን ሳይሆን) ገምቶ ምናልባት 50,000 ብር ከፍሎኝ በግድ ይወስደዋል። በገጥር ደግሞ እንደ ክልሉ እና ዞኑ ቢለያይም አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ። መንግስት ከገበሬ መሬቱን ሲወስድ የሶስት ዓመት ገቢውን ለካሳ ይከፍለዋል። ገጠር መሬት መሸጥ ባይኖርም የዚህ መሬት ዋጋ ከዚህ በላይ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። የሶስት ዓመት ገቢ ሳይሆን ቢያንስ የአስር ነው መታሰብ የነበረበት።

ከዚም አልፎ ተርፎ ይግባኝ የለም። መንግስት አንዴ ትፈናቀላላችሁ ካለ ይህን ውሳኔ መታገል አይቻልም። ከመሬት ንትቅያው በስተጀርባ ያለው የገንዘብ እና የፖለቲካ ኃይል እጅግ ከባድ ነው። የኢህአዴግ ባለሟሎች አሉ፤ ኢነቬስተር ዩኖራል፤ ጉቦኛ መንግስት ሰራተኛው አለ፤ ባለ ስልጣን አለ። ባለ መሬቱ ከነዚህ ጋር መጋፋት አይችልም እና ተዛዙ ሲመጣ እሺ ጌታዬ ብሎ መንግስት የሚሰጠውን ካሳ ተቀብሎ መሄድ ነው።

ይህ ሁኔታ ያለው በመላው ሀገሪቷ ነው በአዲስ አበባ ብቻ አይደለም። ከመሬታቸው አለ አግባብ የሚፈናቀሉት ኦሮሞ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ሁሉ ናቸው። ገበሬዎች ብቻ ሳይሆን ከተሜዎችም ናቸው። አዲስ አበባን ከመሬታቸው የሚፈናቀሉትን ካየን ከአዲስ አበባ ዙርያ ካሉት ገበሬዎች ይልቅ የከተማው ተፈናቃይ ነው ይበልጥ መፈናቀል የሚጎዳው። ለምን? አራት ኪሎ 100 ካሬ ላይ የሚኖር ቤቱን ከነ ጊቢው ቢሸጠው አንድ ሚሊዮን ያገኝበት ነበር 50,000 ተሰጥቶ ይባረራል። ገበሬው ግን ሰፋ ያለ መሬት ቢኖረውም ከከተማ ሩቅ በመሆኑ ዋጋው ያን ያህል ውድ አይደለም በሚሰጠው ካሳ እና በመሬቱ እውነተኛ ዋጋ ያለው ልዩነት እንደ ከተማው መሬት አይሆንም። ስለዚህ አዲስ አበባ እና ዙርያ ሁሉም በመንግስት ከመሬታቸው የተፈናቀሉ ቢጎዱም በአማካይነት የከተማው ከገበሬው ይበልጥ ተጎድቷል።

በመጨረሻ ማን ነበር እነዚህን ገበሬዎች የሚያፈናቅለው ብለን ከጠየቅን የኦሮሚያ የኦህዴድ ቀበሌ እና ውረዳ ሰራተኞች እና የነሱ አዛዦች ናቸው። ለምሳሌ ባለ ሃብት ወይንም የአዲስ አበባ መንግስት በኢህአዴግ ድጋፍ መጥተው የለገጣፎን ባለስልጣኖች መሬት እንፈልጋለን ይላሉ። እነዚህ የኦህዴድ ባለ ስልጣኖች አላማቸው ትንሽ ካሳ ለገበሬው ሰጥቶ በትልቅ ዋጋ ለአዲስ አበባ ወይንም ለባለ ሃብት መስጠት እና በመካከል ከዋጋ ልዩነቱ ጉቦ መብላት ነው። አዲስ አበባ ውስጥም ይህ ነበር አሰራሩ። በጠቅላላ ላለፉ 27 ዓመት መሬት ለመንግስት ሹማምንት ታላቅ የጉቦ የገቢ ምንጭ እና ለኢህአዴግ ታላቅ የካድሬ መያዣ መንገድ ነበር። ስለዚህ አዲስ አበባ ሳይሆን የራሱ የኦህዴድ ካድሬ ነው አዲስ አበባ ዙርያ ያለውን ኦሮሞ ገበሬ አለ አግባብ ያፈናቀለው። አዲስ አበባ ናት ያፈናቀለቻቸው ማለት ሃሰት ነው።

ሙሉ እውነታው ይህ ነው፤ አዲስ አበባ ዙርያ ሳይሆን አዲስ አበባ ውስጥም ሀገር ዙርያም በየቀኑ ዜጎቻችን ከመሬታቸው አለ አግባብ እና አለ በቂ ካሳ ይፈናቀላሉ። የሚፈናቀሉት ደግሞ ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ነው። ችግሩ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ሳይሆን የመሬት የመንግስት ነው የሚለው ፖሊሲ (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_47.html) ነው። መሬት የግል ቢሆን እነዚህ ገበሬዎች በነፃነት በሚያስደስታቸው ዋጋ መሬታቸውን ሽጠው ነበር።

Friday, 13 April 2018

ብቸኝነት

ወደ 10-15 ዓመታት ይሆነዋል የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ስለ የለት ኑሮዋቸው ስለ ማህበራዊ ኑሮዋቸው መለወጥ መገንዘብና ማዘን ከጀመሩ። «ሰዉ እንደ ድሮ አይደለም» ይላሉ። «ጊዜ የለም። ወላጆቼን ዘመዶቼን በወር አንዴም አላገኛቸውም።» «ጥዋት በ12 ሰዓት ወጥቼ ማታ በሁለት ነው ቤት የምገባው። ልጆቼን ከቅዳሜና እሁድ በቀር አላገኛቸውም።» «ጎረቤቶቼን አላውቃቸውም። ዛሬ ማንም ለጎረቤት ጋር አይተዋወቅም። ችግር ቢያጋጥመን ማን እንደሚደርስልን አናውቅም።» «ለእድር ማህበር ቤተ ክርስትያን ጊዜ የለንም። ማህበራዊ ኑሮ የለንም።» «እንደ ድሮ እህል ወዘተ ማዘጋጀት አልችልም የምገዛው ደግሞ ጥራቱ አይታመነም ከየት እንደሚመጣም አላውቅም።» «ዛሬ ሰዉ አይታመንም ለገንዘብ ብሎ ሰው ይሸጣል ራስ ወዳድ ነው።» ወዘተ። ሁላችሁም እነዚህን አባባሎችን ሰምተናቸዋል።

አዲስ አበበ ባለፉት ቅርብ ዓመታት በህዝብ የመብዛትና በኤኮኖሚው ፈጣን እድገት ምክንያት የ«ብልጽግና» ("development") የ«ዘመናዊነት» ("modernity") ችግሮችን ይታዩባታል። አንዱ ችግር በ«ያደገው» ወይም በ«የለጸገው» ዓለም ለረዥም ዓመታት የሚታየው የህብረተሰባዊ ችግር ነው። ብዙዎች ይህን ችግር የማኅበራዊ ኑሮን ማጣት ይሉታል። ግን ጠልቀን ካየነው በሌላ ቃል ልናጠቃልለው እንችላለን፤ «ብቸኝነት» (loneliness)። ይህ ለሰው ልጅ ኢተፈጥሮ የሆነው ብቸኝነት ኢትዮጵያንም ዓለምንም ለማጥፋት ከባድ ስራ እየሰራ ነው።

የበለጸገና ዘመናዊ ህብረተሰቦችና ሀገሮች የብቸኛ ርዕዮት ዓለም (individualism) የሰፈነባቸው ናቸው። ልክ የአዲስ አበባ ሰዎች እንደሚሉት እነዚህ ሀገር ሰው አይተዋወቅም ጊዜ የለውም ማህበራዊ ኑሮ የለውም ጓደኝነት የለም የሚደግፈውም የሚገድበውም ማህበረሰብ የለውም። እራሱ ይወስናል ለራሱ ይኖራል በራሱ ይተማመናል በሚዲያ ጫና በማስተዋወቂያ ካልሆነ ከማህበረሰቡ ምንም ሀሳብ ድጋፍ አያገኝም። እግዚአብሔርም የለውም ወይም እራሱ የፈጠረው የሰየመው በራሱ የሚወሰን አምላክ ነው ያለው።

በአዲስ አበባም አሁን ይህ ቀስ ብሎ እየገባ ነው። ልጅ ተወልዱ በሕፃንነቱ ወደ ሕፃናት ማቆያ ይላካል። እናትም አባትም መስራት አለባቸው ከዋጋ ግሽበት ጋር ለመወዳደር። ምናልባትም ለትንሽ ቤት ለማጠራቀም። ልጁ ጥዋትና ልተኛ ሲል ነው ወላጆቹን የሚያገኘው፤ ያውም ካገኛቸው። ቤተሰቡ ከዘመድም ከማንም ጋር አይገናኝም ጊዜ የለምና። ወደ አያቶቹ ለመሄድ የአንድ ሰዓት መንገድ ነው በታክሲ። የአክስቱ ቤት የሁለት ሰዓት መንገድ ነው። የጎረቤት ልጆችን በደምብ አያቃቸውም ከቅዳሜ እሁድ በቀር ከቤት አይወጣምና። ልጁ ከወላጅና እህት ወንድም በቀር ከሌሎች ተገሎ ነው የሚያድገው።

ልጁ ጎበዝ ተማሪ ነው ሁለተኛ ትምሕርት ቤት ጨርሶ ከአዲስ አበባ ሩቅ የሆነ ዩኒቨርሲቲ ይሄዳል። ትምሕርቱን አጠናቆ አሁንም ከአዲስ አበባ ሩቅ የሆነ ከተማ ለስራ ይበደባል። ከተወሰነ ዓመታት በኋላ እንደምንም አድርጎ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ጥሩ የኪራይ ዋጋ በማግኘቱ ከወላጆቹ ሩቅ ቦታ ቤት ይከራያል።

ትዳር ይመሰርታል ልጅ ይወልዳል ልጁ አያቶቹን በሁለት ሶስት ወር አንዴ ነው የሚያገናቸው። እነዚህ አያቶች አሁን እያረጁ ነው የሚጦራቸው ያስፈልጋቸዋል። ልጆቻቸው ሁሉ ከነሱ ርቀው ነው የሚኖሩት። ጊዜም የላቸውም። ሰራተኛ ጠባቂም አይገኝም። እንደ ምዕራቡ ዓለም የአዛውንት ማረፍያ (ወይም «መጣያ») የለም። ምን ይደረግ! እነዚህ አያት የሆኑ አዛውንቶች የመጨረሻ እድሜአቸውን ከልጆቻቸው የልጅ ልጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ተለይተው ሊኖሩ ነው። ይህ ነው የዘመኑ የብቸኝነት ኑሮ።

እግዚአብሔር ሲፈጥረን በቤተሰብ እንድንኖር ነው። ሚስት እንደ ቤተ ክርስትያን ባል እንደ ክርስቶስ አንድ ሆነው ልጆች ይወልዳሉ። የዚህ ቤተሰብ አንዱ ተልዕኮ መማርያ ማስተማርያ ነው። የእግዚአብሔርን ፍቅር እንድንማር እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ፍፁም ፍቅርን እንድንማር ትዳርና ልጆች ሰጠን። ባለቤታችንን ልጆቻችንን በመውደድ ለነሱ መሥዋዕት በማድረግ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ትንሽ ልንረዳ እንችላለን። ከዛ አልፎ እንደሱ አይነት ፍቅር እንዲኖረን መሞከር እንችላለን እንደሱ መሆን መሞከር እንችላለን።

እንዲሁም እግዚአብሔር ሲፈጥረን ከህብረተሰብ ማህል አድርጎ ነው። ግለሰብ ብቻ ወይንም አባት እናት ልጆች ብቻ አድርጎ አልፈጠረንም። አንዱ የቤተ ክርስትያን ተልዕኮ ይህ ነው፤ ህብረት እንዲሆነን ነው። ይህ ህብረተሰብንም እንደ አባት እናት ልጆች የእግዚአብሔር ፍቅር መማርያ ይሆነናል። ስለዚህም ነው ከጥንት ጀምሮ ክርስትያኖች በደብር ዙርያ እንደ አንድ ህብረተሰብ የምንኖረው። ይህ አኗኗር ከአባቶቻችን የወረስነው ነው። በተዘዋዋሪ የገዳምም አኗኗር እንደዚሁ ነው።

ስለዚህ ቤተሰባዊና ማህበራዊ ኑሮ እግዚአብሔር የሰጠን አኗኗር ነው። አኗኗራችን በዚህ መልክ ካልሆነና የብቸኝነት ኑሮ ከያዝን ኢተፈጥሮ ነውና እንጎዳልን። እንጓደላለን። እንታመማለን። እናጣለን።

ግን «ብልጽግና» እና «ዘመናዊነት» ይህን ኢተፈጥሮአዊ የሆነውን የብቸኝነትን ኑሮ ነው የሚያመጡት የሚያራምዱት። ታድያ እንዴት አድርገን ነው ይህን መከላከልና መቀየር የምንችለው? ወደ መፍትሄ ከመሄድ መጀመርያ ችግሩን በትክክል መረዳት አለብን። ለዚህ ገና ነን። ለምን ቢባል ብልጽግና ዘመናዊነት ከ«ካፒታሊዝም» ጋር አብሮ ከብቸኝነት የሚመጡርን የጠቀስኩትን ጉዳትና ህምምን የሚያስታግስ ዕፅ ይሰጡናል። ገንዘብ ምቾት መዝናኛ ጨዋታ። ቤት ትልቅ ቤት መኪና ትልቅ መኪና ቴሌቪዥን ፊልም ዘፈን ስፖርት/ቴያትር  ዝነኞች አሉባልታ ወሬ ከፍልስፍና እስከ ሙዚቃ እስከ መዝናኛ የተለያዩ ጣዖቶች። እነዚህ ዕፆች የኢተፈጥሮ አኗኗራችንን ብቸኝነታችንን የማደንዘዝ ስራ ብቻ አይደለም የሚያደርጉት በመጀመርያ አኗኗራችን ኢተፈጥሮ እንደሆነ እንዳንረዳ ነው የሚያደርጉን። እንዳመመን እንዳናውቅ እያመመን ምክንያቱን እንዳናውቅ ነው የሚያረጉን።

ስለዚህ እስቲ ሁላችንም አኗኗራችንን እንድንመለከት እጋብዛለሁ። ባል ሚስት ልጆች ቢኖሩንም ብቸኞች አይደለንምን? የሚጦርን አይኖርምን? ልፋታችን ከንቱ አይሆንምን? እስቲ እራሳችንን እንጠይቅ።