በዚህ ዘመን የቃላቶች ትርጉም ተተንቅቀን ነጣጥለን ማየት አለብን።
እስቲ በመጀመርያ «መቻቻል» ምን ማለት እንደሆነ እንመርምር። ሰው የሚወድውን ነገር «ቻለው» ይባላል? አይባልም! የማይወደውን ግን በተለያዩ ምክንያቶች ስለነገሩ ምንም ማድረግ የማይችለውን ወይም ማድረግ የማይፈልገውን ነገር ነው «ቻለው» የሚባለው።
ለምሳሌ… ሙስሊም ጎረቤቴ በየጊዜው ድምጽ የበዛው የጸሎት ዝግጅት ያካሄዳል ከበቱ። ጩኸቱን አልወደውም ግን ለሰላም ብዬ ዝም እላለሁ። ይህ የመቻቻል አንድ ምሳሌ ነው።
እዚ ጋር አንድ ነገርን ልብ እንበል። ጎረቤቴን ዝም ያልኩት ስለምወደው ወይም ጥሩ ልሁንለት ብዬ አይደለም። «ነግ በኔን» አስቤ ነው። ለራሴ ጥቅም ብዬ ነው። እኔም ዝግጅቶችህን ተው ብዬ አላስቸግረውም እሱም እኔ እንደዚሁ አይነት ፕሮግራም ባዘጋጅ ዝም ይለኛል። አልፎ ተርፎ ጸብ ስለሌለን ግንኙነታችን ሰላማዊ ስለሆነ ወደ ፊት በተለያዩ የሚጠቁሙን ጉዳዮች መተባበር መረዳዳት ቀላል ሊሆን ይችላል።
ስለዚህ «መቻቻል» የአብሮ መኖር ስልት ነው። የጥሩነት ወይም በጎ መግባር ውጤት አይደለም የመዋደድ የፍቅርም ውጤት አይደለም።
መቻቻል እንዲህ ከሆነ ለኛ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች ምን ማለት ነው? መቻቻል አለብን ወይ? የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችን «መቻል» አለብን ወይ? «የሃይማኖት መቻቻልን» መተግበር አለብን ወይ? በፍፁም! በመጀመርያ እንደ ክርስትናችን «መውደድ» ነው ያለብን። አምላካችን እንዳለን እሱ እንደሚወደን ያህል ባለንጀራችንን መውደድ አለብን። የኛ የክርስትያኖች ተዕልኮ «ፍቅር» ነው እንጂ «መቻቻል» አይደለም! ማንም ሰው ከልምድና ምቾት አንጻር መቻቻል ይችላል፤ ግን ክርስትያኖች መውደድ ነው ያለብን።
ወደ ቅድሙ ምሳሌአችን ከተመለሰን የሙስሊም ጎረቤቴን ስለ ጸሎት ዝግጅቶቹ የማላስቸግረው ምክንያት «መቻቻል» ሳይሆን «ፍቅር» ነው መሆን ያለበት። ስለ ዝግጅቱ ካላማረርኩኝ አለማማረሬ ከፍቅር የመነጨ መሆን አለበት እንጂ ለራሴ ጥቅም ብዬ መሆን የለበትም። እሱም ይሉኝታ ኖሮት ዝም ይለንኛል ብዬ ከሱ ጠብቄ ሳይሆን ምንም ሳልጠብቅ ምሆን አለበት። ስለዚህ ክርስትያኖች መቻቻልን መተግበር አለባቸው ማለት ትርጉም የለውም። ከመቻቻል በላይ ሰማይ ጠቀሱን ፍቅር መተግበር ነው ያለን።
እንግዲህ አንዳንዶቻችሁ «አምላካችሁ ውደዱ ቢላችሁም አትሰሙትም» ትሉኝ ይሆናል። «እናንተ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች ድሮም አሁንም ፍቅርን አታውቁም።» አልክድም፤ እውነት ነው፤ እኔ ኦርቶዶክስ ክርስትያን ብሆንም ኃጢአተኛ ነኝ ፍቅር ይጎለኛል። ፍቅር የሆነውን ተልዕኮኤን ሁል ጊዜ እየሳትኩኝ ነው የምኖረው። ይህ ኃጢአተኝነቴ ግን የሚስተካከለው ወይንም በትክክሉ ቋንቋ የሚታከመው መቻቻልን መተግበር በመሞከር አይደለም። ፍቅርን በመተግበር ነው። ካልቻልኩኝ ከወደቅኩኝ ተመልሼ መሞከር መነሳት ነው። ይህ ነው የክርስትና ኑሮ። እንጂ መውደድ አልችልም ብዬ ተስፋ ቆርቼ እስቲ መቻቻልን ልሞርክ ማለት ውድቅ ሀሳብ ነው።
ስለዚህ ፕሮቴስታንት ወንድሜ፤ ሙስሊም እህቴ፤ ሴኩላሪስት ወንድሜ፤ ካስቀየምኩህ ካስቸገርኩህ ከጎዳሁህ እኔን ኃጢአተኛውን ይቅር በለኝ። መሻሻል እሞክራለሁ። ልችልህ ሳይሆን በእግዚአብሔር እርዳታ ልወድህ እሞክራለሁ።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!