Thursday 18 April 2019

ገንቢ ትምሕርት ክሙስታፋ ምሐመድ ዑመር

ይህንን ቪዲዮ እንድትመለከቱ በትህትና እጠይቃለሁ። ሙስጠፋ መሐመድ ዑመር (የሱማሌ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር)  ታላቅ የመሪ ትህምሕርት በሚገባ ቋንቋ ነው የሰጡት።

ሁለት ዋና ዋና ነጥቦች፤

፩) በፖለቲካ ፍፁምነት የለም። ፍፁም እውነት እና ፍፁም ውሸት የለም። ፖለቲካ እንደ ሃይማኖት አይደለም። የሁሉም ሃሳብ የተወሰነ እውነት ሊኖረው ይችላል። ስለዚህም የሌላውን ሃሳብ እና አቋም በደምብ መረዳት አለብን። እራሳችንን በሌሎች ቦታ አድርገን በርህራሄ ማሰብ አለብን። ምናልባት ልክ ሊሆኑ ይችላሉ ብለን ማሰብ አለብን። መገተር የለብንም። ለመስማማት መወያየት እና መደራደር አለብን። ይህን ተመልክቶ «ፖለቲካ ሃይማኖት አይድለም» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/10/blog-post.html) የሚለውን ጽሁፍ ያንብቡ።

በተዘዋዋሪ በፖለቲካ ተደራድሮ ተስማምቶ መኖር ሲቻል በሃይማኖት ረገድ አይቻልም ብለው ሲአስረዱ በሃይማኖት ግን ተቻችሎ፤ ላለመስማማት ተስማምቶ አብሮ መኖር ይቻላል ብለዋል። ግን «ተቻችሎ» ብቻ ሳይሆን ተፋቅሮ መኖር ይቻላል። «ሃይማኖታዊ መቻቻል» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/04/blog-post_3.html) የሚለውን ጽሁፍ ያንብቡ።

፪) ይህንን ተከትሎ ርዕዮት ዓለምን እንደ ፍፁም ማየት የለብንም። ርዕዮት ዓለም ሰው ስራሽ ነው እና ስህተቶች እንዳሉት ማወቅ አለብን። ርዕዮት ዓለምን እንደ ጣኦት ካመለክን ወደ እልቂት እናመራለን። አቶ ሙስታፋ ብዙዎቻችን «የምናመልከው» ዴሞክራሲም እንደ ጣኦት ከተቆጠረ ታላቅ አደጋ እንደሚያስከትል አስረዳ። በዚህ ዙርያ «ዴሞክራሲ» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_8.html) የሚለውን ጽሁፍ ያንብቡ።

አልፎ ተርፎ በርዕዮት ዓለም ፍፁም እውነት ወይንም ፍፁም ስህተት የለም ስንል ይህን አባባል በኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ስንተገብር አንዱ መደምደምያ የጎሳ ብሄርተኝነት ፍፁም ስህተት አይደለም የሚለው ይሆናል። እኔ የጎሳ ብሄርተኝነት በተለይ የጎሳ ፌደራሊዝም ባልወድም የጎሳ ብሄርተኝነት እና ፌደራሊዝም «ክፋት» ናቸው አራማጆቹም «ክፉ» ናቸው ማለት ተገቢ አይደለም። በነሱ ቦታ ሆኖ አስቦ ተቆቁሮ ነው ወደፊት መራመድ የሚቻለው። በዚህ ረገድ «ተረት ተረት፤ ጎሰኝነት ዘረኝነት ነው» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_6.html) የሚለው ጽሁፍ ይመልከቱ።

፫) በመጨረሻ የጎሰኝነትን አደጋ (ይህ የሀገር ብሄርተኝነትንም ሊመለከት ይችላል) «የኔ ጎሳ ሰዎች ንጹ የሌሎች ክፉ» አድርገን መቁጠር ምን ያህል ሃሰት እንደሆነ አቶ ሙስታፋ አስተማሩ። በኔም በሌላም ጎሳ ደጎች እና ክፉዎች እንዳሉ ለማንም ግልጽ ነው። ጥሩ እና ክፉን የሚለየው መስመር በጎሳዎች መካከል አይደለም የሚሄደው፤ በጎሳዎች ውስጥ ነው።

አቶ ሙስታፋ እዚህ ላይ አቆሙ፤ በሃሳቡ አልቀጠሉበትም። መሰረታዊው ነጥብ ይህ ነው፤ ጥሩን እና ክፉን የሚለየው መስመር የሚያልፈው በጎሳዎች መካከል ሳይሆን በያንዳንዶቻችን ልብ መሃል ነው። እነዚህን ሁለት ጽሁፎች ያንብቡ፤ https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/blog-post_21.html እና https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_30.html

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!