ስለ ዴሞክራሲ ብዙ ተጽፏል። በንደፈ ሐሳቡ ደረጃ ምንም መጨመር አልፈልግም። በዚህ ጽሁፍ አሁን ባለን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ዙርያ ስለ«ዴሞክራሲ» ያለን አመለካከት ምን ቢሆን ይበጀናል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ነው የምወደው።
እንደ እስክንድር ነጋ አይነቶቹ በርካታ (ጀግና) የነፃነት ታጋዮቻችን የችግራችን መፍትሄ ዴሞክራሲ ነው ይላሉ። በአንድ ወቅት እኔም እንደዚሁ ይመስለኝ ነበር። ግን ጉዳይ ከዛ እጅግ ውስብስብ እንደሆነ ተረድችያለሁ።
ዛሬ ባለን ህገ መንግስትና ጠቅላላ የመንግስታዊ አወቃቀር የነፃ ምርጫ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቢካሄድ ችግሮቻችን ይፈታሉ ብለን እንገመታለን? አሸናፊዎቹ፤ ተሸናፊዎቹ፤ ጦር ሰራዊቱ፤ የክልል መንግስታት ወዘተ ውጤቱን ተቅብለው ተስማምተው ይሰራሉ ብለን መገመት ኢንችላለን? አዲሱም መንግስት ሰላምና ፍትህ ያመጣል ወይም የፓርላማ ስልጣንና ኃይሉን ተጠቅሞ ግፍና ጭቆና ያሰፍን ይሆን? ህገ መንግስቱን ይቀየር የምንለውሳ? በቂ ድምጽ ካለን አናሳ ድምጽ ያላቸውን የራሳችሁ ጉዳይ ብለን በዚህ ድምጽ ኃይል እንቀይረውና አዲስ ህገ መንግስት እንጭንባቸው ይሆን? ዛሬ እነዚህ አይነቶቹ ከባድ ጥያቄዎች ጥሩና የተሟላ መልስ አላቸው ብዬ እርግጠኛ መሆን አልችልም። ለእነዚህ ጥያቄዎች በሚገባው መልስ ሳይኖረን ወደ ዴሞክራሲ የምንለው ምርጫ ከገባን ደግሞ አደጋ ነው የሚሆነው።
ስለዚህ እንደኔ እንደኔ በመጀመርያ ሰፊ ውይይት በተለያዩ ደረጃዎች ያስፈልጋሉ። የዚህ ውይይት ግብ በርካታ ባለጉዳዮቹ ከብዙሃን እስከ ልሂቃን የአገራችን ማንነትና ፖለቲካ ምን መምሰል አለበት በሚለው ጥያቄና መልስ አንድ ገጽ ላይ እንዲሆኑ ነው። ሰፊ ስምምነት እንድውል ነው። አሁን ያለንበት ደረጃ አገር መገንባት ላይ ነው። በህዝቡም በልሂቃኑም የፖለቲካ መተማመንና መሰረታዊ ስምምነት የለምና። ከላይ የጠቀስኳቸው አይነቶች መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎች እንኳን ሊመለሱ አልተጠየቁም አልተወያየንባቸውም። ይህን የውይይት ሂደት ሳንጨርስና መሰረታዊ ስምምነት ላይ ሳንደርስ ወደ ምርጫ መሄድ አደገኛ ይመስለኛል። እንደ ግብጽ፤ ኢራቅ፤ እና ሌሎች ምርጫ ያላቸው ወይም የነበራቸው ግን ሰላምና ፍትህ የሌላቸው አገሮች እንድንሆን አይፈለግምና።
እሺ፤ በርካታና አስፈላጊዎቹ ባለጉዳዮች አንድ ገጽ ላይ መሆናቸውና ስምምነት ላይ መድረሳቸው እንዴት ልናውቅ እንችላለን? አንዱ ዋና ምልክት የሚመስለኝ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በስል ማለት ነው። ጠንከር ያለ ተቃዋሚ ፓርቲ ከሌለ ወይም ፓርቲዎቹ በጎሳ ብቻ የተመሰረቱ ከሆነ ይህ ጥሩ ምልክት አይመስለኝም። ተመሳሳይ የሆኑ አቋም ያላቸው ተቃዋሚዎች የመዋኸድን ሂደት ለማሟለት ብቃት ከሌላቸው ጥሩ ምልክት አይሆንም። ይህን ያልቻሉ እንዴት አብረው መንግስት ይሆናሉ ወይም እንዴት የአስተዳደሩን ህግ ያከብራሉ? የጎሳ ፓሪቲ ብቻ ካለ ደግሞ እንዴት ነው ፖለቲካ ስረአቱ የማይቀረውን የጎሳ ውድድሩን በሰላም ማስተናገድ የሚችለው? አሁንም ከባድ ጥያቄዎች። እንደምናየው ወደ ምርጫ ከመግባታችን በፊት ብዙ ስራ አለ ቀድመሁኔታዎችም መሟላት አለባቸው።
ይህን ካልኩኝ በኋላ እስቲ ይህን ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ ዴሞክራሲ ቢኖር ሰላምና ፍትህ ይኖራል ማለት ነው? እስቲ አንድ አንድ እውነታዎች እንመልከት። በዓለም ታላቅ የሚባለው ዴሞክራሲ አሜሪካ ነው። በጦሩ ኃይል በርካታ የዴሞክራሲ አገርዎች በሰላም እጠብቃለሁ እሸከማለሁ ባይ ነው። ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አሜሪካ ወደ 20 ሚሊዮን ሰዎች በተለያዩ ጦርነቶች ገድሏል ይባላል። አጭር ትዝታ ያለን መቼም ስለ ኢራቅ፤ ሊብያ፤ ሶርያ እናውቃለን። ኢህአዴግ ከዚህ ጋር ሲወዳደር መለአክ ነው ማለት ይቻላል! ግን አሜሪካ ለኑሮ ጥሩ አገር ነው። ገንዘብ አለ፤ ከሞላ ጎደል ፍትህ አለ፤ የተወሰነ ነፃነት አለ። ሁላችንም ወደዛ ለመሄድ እንሻለን። ግን ገንዘቡ ባይኖር በአሜሪካ ምን ይሆን ነበር?
ምናልባት አውሮፓ ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን ለምን አሜሪካን እንደ ምሳሌ ትጠቀማለህ ትሉ ይሆናል። ሰላማዊዋ ስዊድንሳ? እውንቱን ለመናገር የስዊድን የጦር መሳርያዎች በዓለም ዙርያ ምን ያህል ሰው እንደተገደለ የተቆጠረ አይመስለኝም። ግን ትንሽ አይመስለኝም። ደግሞ ከሳውዲ አራቢያ ያላቸው ጓደኝነታቸው እንዴት ፍቅር የተሞላ ነው?!
ዴሞክራሲ ለሰላምና ፍትህ ሊበጅ ይችላል፤ ይህ ጥያቄ የለውም። ግን ሰላምንና ፍትህን ለማስፈን ሥርዓቱ በራሱ አይበቃም። ብዙሃኑም ልሂቃኑም ቀድሞ በትወሰኑ መሰረታዊ ጉዳዮችና አስተሳሰብ መስማማት አለባቸው። ከህግና የሂደት ደምብ አስተሳሰብ ይቀድማል። አሰተሳሰቡ ካለ ህጉ ይመጣል በሚገባውም ይተገበራል። ህጉ ካለን አስተሳሰቡ ከሌለ ዋጋ የለውም። ብዙ ነገር በጽሁፍ ላይ የዋለ ህገ ደምቦች ሊካታቱ ይችላሉ ግን አስተሳሰብ በጽሁፍ ሳይሆን በልብ ውስጥ የሚሰክን ባህል ነው መሆን ያለበት። ከዛ በኋላ እንቅፋት ሲያጋጥም ይህ አስተሳሰብ፤ ስምምነትና አንድነት ናቸው ከወረቀት ላይ ከሰፈረው ህግ ይልቅ ወደ መፍትሄ የሚመሩን።
ስለዚህ ዴሞክራሲን እንደ ዋና ግብ ወይንም እንደ ጣዖት አንመልከተው። ዋናው ግብ ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ ነው። እነዚህ እንዲሰፍኑ ዴሞክራሲ አንዱ መሳርያ ሊሆን ይችላል። በዴሞክርሲ ዘንድ ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ ሊሰፍኑ ይችላሉ። ግን ቀድሞ ዝግጅቶች ካልተደረጉ፤ ግባችን እነዚህ እንደሆኑና ዴሞክራሲ መንገድ ወይም ሂደት ባቻ እንደሆነ ካልተረዳን ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ የሌለው ዴሞክራሲ ሊሰፍን ይችላል። እንደዚህ አይነቱ ዴሞክራሲ ደግሞ በበርካታ አገራት ልምድ እንደምናየው አይበጅም።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!