Tuesday 20 February 2018

ታሪክን አንድገም፤ ሀገርን እንገንባ

አሳፋሪና አገር አፍራሽ ታሪካችንን እንዳንደግም ነው ይህን ጽሁፍ የምጽፈው። ታሪክ እንደመዘገበው ከኢህአዴግ ውጭ ያለነው ምሁራን፤ ፖለቲከኞችና ብዙሃን በፖለቲካ ረገድ ቁም ነገር ለማድረግ እድል ባጋጠመን ቁጥር እልዳችንን አበላሽተናል። በተደጋጋሚ ጊዜ ለአገራችን የፖለቲካ መስተካከል ከኢህአዴግም ይበልጥ እንቅፋት ሆነን ተገኝተናል።  ይህን ደፍሬ መናገር የምችል ይመስለኛል።

አንዱ የድክመታችን ምክንያት ተልዕኮአችንን አለማወቃችን ወይም መርሳታችን ነው። ተልዕኮአችን የአገር ፖለቲካ ግንባታ ነው እንጂ የፖለቲካ ውድድር አይደለም። የአገር ፖለቲካ ስርዓት ግንባታ ሲባል ሁላችንም ስለ ህገ መንግስትን ማርቀቅ ነው የምናስበው። ግን ከዚህ ህገ መንግስት ማርቀቅ ስራ በፊት  የልብ ለልብ መተዋወቅ፤ በተወሰነ ደረጃ መተማመን፤ መግባባትና መስማማት ያስፈልጋል። እነዚህ ለአገር ግንባታ የፖለቲካ ድርድር ቀድሞ ሁኔታዎች ናቸውና። አለነዚህ ማንኛውም በወረቀት ያለ ህግ፤ ምንም አይነት ወርቅ የሆነ ህግ ቢሆነም፤ በስራ ሊተገበር አይችልም

ቀጥሎ በነዚህ ተመስርቶ ህገ መንግስትና ሌሎች የርዓይና የህግ ሰነዶች ይደነገጋሉ። ቅራኔ ወይም አለመግባባት ካለ በህግ መሰረት ይፈታል ህጉ ደግሞ በቂ ካልሆነ ያለው መተማንና ስምምነት ለፍትህ ይረዳል። የአገር የፖለቲካ ግንባታ ሂደት እንደዚህ ነው መሆን ያለበት።

የፖለቲካ ውድድር ደግሞ የሚጀምረው የፖለቲካ ስረዓቱ ከተዋቀረ በኋላ የሚመጣው የፖለቲከኞችና ሌሎች ለመሪነት እርስ በርስ በህጉ መሰረት መወዳደር ነው። በምእራብ «ዴሞክራሲዎች» እንደዚህ አይነቱ ውድድር በርካታ ክርክር፤ ክስ፤ ዘለፋም ወዘተ ያካትታል። የህጉን ገደብ ዳር ዳር እየነኩ ግን ሳያልፉ እነዚህን አይንቶች ባህሪዎችን ያንጸባርቃሉ። ይህ ስልጣን ለመያዝ ሊበጃቸው ይችላል ግን ምንም አይገነባም። እርግጥ መተማመንንና ውይይትን ይጎዳል ግን ከምርጫው በኋላ የደረሰውን ጉዳት ይጠግኑና የአገር ማስተዳደር ስረአቸውን ይጀምራሉ። ይህ ነው በተለምደው የምናውቀው የፖለቲካ ውድድር።

የፖለቲካ ውድድር ደግሞ የፖለቲካ ስርዓቱ ከተዋቀረ በኋላ የሚከተለው የፖለቲከኞችና ሌሎች ለመሪነት እርስ በርስ በህጉ መሰረት መወዳደር ነው። በምእራብ «ዴሞክራሲዎች» እንደዚህ አይነቱ ውድድር በርካታ ክርክር፤ ክስ፤ ዘለፋ ወዘተ ያካትታል። የህጉን ገደብ ዳር ዳር እየነኩ ግን ሳያልፉ እነዚህን አይንቶች ባህሪዎችን እያንጸባርቁ ይወዳደራሉ። ይህ ስልጣን ለመያዝ ሊበጃቸው ይችል ይሆናል ግን አገርን አይገነባም ይጎዳልም። ሰልዚህም ነው ውድድሩ ምርጫው ካለፈ አሸናፊዎቹ ውድድሩ ያደረሰውን ንዴት፤ ቂምና ጉዳት ይጠግን ዘንድ ትሸናፊዎቹንም መላው የአገሪቷን ህዝብ አንድ የሚያረግ እርቃዊ ንግግርና ተግባር የሚአደርጉት። ይህ ነው በተለምዶ የምናውቀው የፖለቲካ ውድድር።

ስለዚህ አገርን መገንባትና የፖለቲካ ውድድር የተለያዩ ባህሪያት፤ ተግባራትና ልምድ ያስፈልጋቸዋል። የአገር ግንባታ ሂደት እንደ መተማመን፤ ስምምነት፤ አንድነት፤ መግባባት፤ ህብረት፤ ቅራኔን መፍታት፤ ውይይት ወዘተ አይነቱ ባህሪያትና ልምዶች ያስፈልጉታል። የፖለቲካ ውድድር ግን ክርክር፤ ውድድር፤ ፉክክር፤ መካሰስ፤ ህግና ስረዓትን ዳር ዳሩን መጣስ፤ ወዘተ አይነቱን ልምዶች ያካትታል። በአገር ግንባታ ሂደት መካከል እነዚህን የፖለቲካ ውድድር ባህሪያትና ልምዶች ይዘን ከገባን አገርን መገንባት ሳይሆን ማፍረ ነው የምናደርገው።

ለዚህ ደግሞ በርካታ ታሪካዊ ምሳሌዎች አሉን። እስቲ ወደ 15 ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሰን የ«ተቃዋሚ» ምሁራን፤ ጋዜጠኛና ፖለቲከኞች እያደረጉ፤ እየተናገሩ፤ እየጻፉ ምን እንደነበር እናስታውስ። ስራቸውን ባጭሩ ለመግለጽ «እርስ በርስ መበላላት» ማለት ይቻላል! ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ ከሚተቹት ይበልጥ እርስ በርስ ነበር የሚፋጁት። ጋዜጣ ላይ ቁም ነገር ሳይሆን ስድብና የመንደር ወሬ ነበር የሰፈነው። ከሞላ ጎደል ስራቸው 90% አፍራሽ 10% ገምቢ ነበር። ስለዚህም ነው ተቃዋሚው ጎራ ምርጫ '97 በግንቦት ሆኖ እሰከ የካቲት አካባቢ የትብብር መዋቅሮች ያላደራጀው! ለዚህም ነው ከምርጫው በኋላ ተቃዋሚዎች በቀላሉ የተበታተኑት። በበፊቱ ዓመታት እዱሉ እያለን ቅስ ብለን በትብብር ጉዳይ ተወያይቶ ትብብርን ከመፈጸምና ጠንካራ መሰረት የሆነ መዋቅርን ከመገንበት እንደ ምርጫ ተዋዳዳሪዎች እየተሰዳደብን ዋልን። ችግር ሲመጣ ለመቋቋም አቅሙ አልነበረንም። እርስ በርስ ተፋጅተን አለቅን። የግንባታ ስራ ያልተሰራባቸው ቅንጅትና ህብረት በቀላሉ ፈረሱ። የፖለቲካ መዋቅር ግንባታንና የፖለቲካ ውድድርን መለየት ያልቻሉትም ከፖለቲካ ወጡ። የህዝብም ትዝብት አደረባቸው።

በርካታዎቻችን በምዕራብ የሚዲያ ዜና፤ ትምህርትና ፕሮፓጋንዳ ስላደግን የነዚህ አገራት ፖለቲካ ስናይ ፖለቲካ እንደዛ መሆን እንዳለበት ይመስለናል። የናየው ደግሞ የፖለቲካ ውድድራቸውን ነው። ክርክሩን፤ ዘለፋውን፤ ስድቡን፤ ሴራውን ወዘተ። እኛም እንደነሱ ማድረግ እንወዳለን መሰለኝ። ግን ኢትዮጵያ ያለችበት ቦት፤ ለረዥም ዓመታት ያለችበት ቦታ፤ ገና የአገር ፖለቲካ ግንባታ ላይ ናት። ብዙሃኑም ልሂቃኑም የፖለቲካ መደቦቻችን እስካሁን በእምነት የተመሰረተ አገራቷን ምን መምሰል አለበት የሚል ሰፊ ስምምነት ላይ አልደረስንም። አሁንም ያለው ዋና ስራችን የህ ነው። አዎን ህገ መንግስት አለን ግን ሰፊው ርአይና ስምምነት የለንም። ነገ ኢህአዴግ ከስልጣን ቢወርድም ይህ ስምምነቱ ስለሌለ ሁከትና አብዮት ይከተላል።

በዚህ ምክንያት ሁላችንም፤ ምሁራን፤ ብዙሃን፤ ፖለቲከኛ፤ የመንግስት ሰራተኛ፤ ወዘተ ትኩረታችን ወደ አገር ግንባታ መቀየር አለበት። ይህ ማለት ከታች የተጠቀሱትን ለአገር ግንባታ አስፈላጊ የሆኑትን ብሃሪያት፤ ተግባሮችና ልምዶች ከራሳችን ጋር መዋሃድና በዚህ አስተሳሰብ ወደ ፊት መራመድ።

ስምምነት፤ አንድነት፤ መግባባት፤ ህብረት፤ መተማመን፤ በስነ ስረዓት መነጋገር፤ ውይይት፤ ቅራኔን መፍታት።

የሚቀጥለው ጊዜ አንድ ሰውን ወይም ቡድንን መዝለፍ ወይም መስደብ ካሰኘን ቆመን እናስብ። የፖለቲካ ውድድር ውስጥ አይደለንም። እንደዚህ አይነቱ ባህሪያት ታሪካችን እንደሚያረጋግጠው ሁላችንንም ጠርጎ ገደል ውስጥ ያስገባል አገራችንን ያፈርሳል። በሰላም እየተከባበርን እየተማመንን ነው መወያየት ያለብን። ይህ የሁላችንንም ጥቅም ያስከብራልና። ይህንን ብቻ ተግባራዊ ካደረግን አለ ምንም ጥርጣሬ ታላቅ አገር እንገነባለን ጠላት የምንላቸውም ምንም ሊጎዱንም አይችሉም።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!