Wednesday 5 September 2018

ልማት ሀገርን አይገነባም!

እስካሁን በሰው ልጅ ታሪክ አንድ ሀገር በ«ልማት» ተመስርቶ ተገንብቶ አያውቅም። ሰዎች ከአንድ መንደር ሲሆኑ፤ የጋብቻ እና የደም ትሥስር ሲኖራቸው፤ ባህላቸው አንድ ሲሆን፤ ለመተባበር እና ለመረዳዳት ብለው በተፈጥሮአዊ በአዎንታዊ መንገድ «ሀገር» ይሆናሉ። ሃብት ፍለጋ፤ ጦርነት፤ ግጭት ወዘተም በአሉታዊ መንገድ በሀገር ምስረታ ሚና ይጫወታል። ግን «ልማት» ሀገር አይገነባም። ትሥሥር አይፈጥርም። ዝምድና አይፈጥርም። ፍቅር የለውም። ከልብ መረዳዳት አይጠይቅም። ሀገር አይገነባም።

ለማስታወስ ያህል የተወሰነ ዓመት በፊት ህዝብን የምርጫ 1997 ችግርን ለማስረሳት፤ «ጠባብ» የጎሳ ብሄርተኝነትን ለመዋጋት፤ መንግስትን ሊጥል የሚችል መሃበረሰባዊ ክፍፍልን ለማስወገድ ኢህአዴግ «ልማታዊ መንግስት» ብሎ አወጀ። ኦሮሞ፤ አማራ፤ ትግሬ፤ ሲዳማ ወዘተ ብሄር ብሄረሰቦች አንድ መሆን ባይችሉም በ«ልማት» ዙርያ አንድነት ይፈጥራሉ ወይንም ግጭት ይቀንሳሉ ተብሎ ነው «ልማት» የታወጀው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/10/ethnic-federalism-kills-meles.html)። የዚህ የልማት ዘመቻ ደግሞ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ነው ተብሎ የሳቸው ምስሎች ከነ ልማት ምስሎች ጋር በማርክሲስት አይነት ስዕሎች በየቦታው ተለጠፉ።

ልማቱ መጣ ኤኮኖሚው በፍጥነት አደገ። ግን ህዝቡ ይበልጥ ተከፋፈለ። ግጭቶች እየጨመሩ እየጠነከሩ ሄደ። ሰላም እና ፍቅር እየጠፋ ሄደ። የግብረ ገብ እጦቱ በአስፈሪ መልክ በዛ አገሩን አጠለቀለቀ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_31.html)። «ልማት» ወደ «ገንዘብ» ተተርጉሞ ለገንዘብ ብለን እናታችንን የምንሸጥ ስባዊነት-ቢስ ማህበረሰብ ሆንን። ይበልጥ ተከፋፈልን። «ልማት» የሚለው መፈከር አልሰራም።

ግን አሁንም ስለ «ልማት» እንሰማለን። «ለምን አንድ ሆነን ተፋቅረን ሁላችንም ወደ ልማት አንሄድም?» ይባላል። «ሀገራችንን በጋራ እናሳድጋት» ሲባል እንሰማለን። «አንድ ከሆነን ሀገራችን እንደ ሌሎች ሀገራት ትበለጽጋለች!» ይባላል።

አዎን ልማት እና እድገት አይከፋም። ግን ልማት ሀገር እና ህዝብ አያደርግም ወደፊትም ሊያደርግ አይችልም። ሀገር እና ህዝብ የሚያደርገን «ፍቅር» እና «ሰላም»፤ «እውነተኛ ዝምድና እና ትሥስር»፤ «መደጋገፍ» እና «መረዳዳት»፤ «አባቶችንና ተውፊትን በጋራ ማክበር» ወዘተ። እነዚህ ጊዜያዊ ሳይሆኑ ዘላቂያዊ ነገሮች ናቸው። ልክ እንደ ሃብት ቤተሰብን እንደማይፈጥር እንደማይገነባ ሀገርንም አይፈጥርም አይገነባም።

ይህን ስለተረዱ ነው ጠ/ሚ አብይ አህመድን ታላቅ የሚያረጋቸው። የሳቸው ትኩረት በጊዜያዊ አላፊ ትናንሽ ነገሮች ሳይሆን በከፍ ያሉት (higher) ነገሮች ነው። ህዝባችን ከልማት በላይ ደስታ እንዲኖረው ነው የምፈልገው ብለዋል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያው ትውፊታዊ አመለካከት ነው። ኢትዮጵያዊ ከገንዘብ፤ ምቾት፤ ሃባት ወዘተ ይልቅ ፍቅር፤ ሰላም፤ ፍትህ ወዘተን ያስቀድማል በሃይማኖትን እና ትውፊቱ ምክንያት። ለዚህም ነው የጠ/ሚ አብይ መልዕክት ምዕራቢያዊያንን በሚያስገርም ሁኔታ ህዝባችንን ያስደሰተው።

ስለዚህ የኛ መሪዎች እና ፖለቲከኞች እንዲሁም እኛ ብዙሃን «ልማት» የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ላሁን ብንተወው እና ትክክለኛ ቦታው ብንሰጠው ጥሩ ይመስለኛል። ፍቅር እና ሰላማችንን እናዳብር። ክፍፍሎቻችንን በግልጽ እና በትህትና እንወያይ። ይቅርታ እንባባል እርስ በርሳችን እንቆርቆር። ሀገርን እንገንባ። እዚህ ላይ እናተኩር። ከዛ በኋላ ልማት እንደ ሁለተኛ ምርት (byproduct) ይመጣል። ባይፈጥንም ፍቅራችን ያኖረናል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!