ብዙዎቻችን በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን በሀገራችን ታልቅ የግብረ ገብ እጦት እየታየ ነው እንላለን። ለማ መገርሳም አብይ አህመድም ይህን ጉዳይ በተደጋጋሚ ያነሱታል። ባለ ስልጣን ይጨቁናል እና ይሰርቃል፤ የመንግስት ስራተኛ ጉቦ ይጠይቃል፤ ብዙሃኑ ያጭበረብራል፤ ስርቆት፤ ግድያ፤ ማጭበርበር፤ ለሰው ግድ ዬለሽነት፤ ዝሙት፤ ርክሰት፤ ሌብነት ወዘተ። ሁላችንም ሰምተነዋል አይተነዋልም።
መፍትሄውን ለማግኘት ለምን ይህ ሆነ ብለን መጠየቅ አለብን። ስንጠይቅ በቅርብ ያረፉት ታዋቂ የቻይና የፖለቲካ ተንታኝ እና እስረኛ ሊዩ ሺያዎቦ ጥሩ መልስ ይሰጡናል። የቻይና እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ አገዛዝ እና በማሀበረሰቡ ላይ ያሳደረው ጫና በተወሰነ ደረጃ ተመሳሳይነት አላቸው።
በቻይና አንድ አውራ ፓርቲ በሙሉ ስልጣን ይገዛል። የማይፈልጋቸውን ያስራል ይገላል (በአመት ወደ 2,000 ሰዎች በይፋ በሞት ፍርድ ይገደላሉ)። ማንም ሰው መማር ማደግ ወይንም ስልጣን መያዝ ከፈለገ ከገዥ ፓርቲው ጋር ጥሩ ወይም ቢያንሽ መልካም ግንኙነት ሊኖረው ይገባል። ከፓርቲው ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ከሌላው ሀብረተሰብ ሃብታም እና ባለ ስልጣን ይሆናሉ። ይህ ሃብት እና ስልጣን በስራ እና እውቀት የተገኘ ሳይሆን ከፓርቲ አባል እና መሪዎች ጋር በመሻረክ ነው የሚመጣው። በዚህ ምክንያት በርካታው የሀገሪቷ ሃብት በጥቂት ሰዎች የተቆጣጠረ ነው።
እንዲሁም ሆኖ የቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ ህዝቡ ከስልጣን በአመጽ እንዳያወርደው ብሎ ኤኮኖሚው የገበያ ኤኮኖሚ እንዲሆን እና በፍጥነት እንዲያድግ አድርጓል። ለብዙ ዓመት ኤኮኖሚው በየአመቱ ከ10% በላይ ነው እድገቱ። በርካታ ስዎች በፍጥነት ሃብታም ሆነዋል። መካከለኛ መደቡም አድጓል። ግን የእድገት ፍጥነቱ በሃብታም እና ድሃ ያለውን ልዩነት በጣም አስፍቶ ከዓለም አንደኛ አድርጎታል (30 ዓመት በፊት በእውነተኛ ኮምዩኒዝም ዘመን እኩልነቱ በዓለም አንደኛ ነበር)። ግን ብዙ ሰው ማደግ የሚችለው ሃብት ማከማቸት የሚችለው አጭበርብሮ፤ ጉቦ ከፍሎ ወይንም ወስዶ ወይንም በተለያየ መንገድ ህግን ጥሶ ወይን ስነ መግባርን ጥሶ ነው።
በአጭሩ የቻይና መንግስት ከህዝቡ ጋር ያለው ስምምነት እንዲህ ነው፤ በፖለቲካ እና ስልጣናችን አትምጡ ከመጣችሁ እናጠፋችኋለን፤ ግን እንደፈለጋችሁ ሃብታም ሁኑ ከፈለጋችሁ ከኛ ጋር ተሻረኩ እና ስረቁ። የቻይና «ልማታዊ መንግስት» እና «አውራ ፓርቲ» አገዛዝ ርዕዮእተ ዓለም እንዲህ ነው። በህወሓት ዘመን የነበረውን በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ የነበረውን አገዛዝ ሊያስታውሳችሁ ይገባል። አንድ ነው።
ወደ የቻይና የፖለቲካ ተንታኙ ሊዩ ሺያዎቦ እንመለስ። ሊዩ ይህንን ልማታዊ መንግስት ሲተቹ ይህ ስርአት የሚያመጣውን የስነ መግባር እጦትን በደምብ ተንትነዋል (https://www.nybooks.com/articles/2012/02/09/liu-xiaobo-he-told-truth-about-chinas-tyranny/)። ከዚህ ጽሁፍ የተወሰነውን ተርጉሜ ከታች አቀርባለሁ…
ኅብረተሰብን በመቀየር አገዛዙን እንቀይር» በሚል ጽሁፉ ሊዩ ሺያዎቦ ለቻይና ያሉትን ተስፋዎቹን ዘርዝሯል። የፖለቲካ አንባገነንነቱ ቢቀጥልም ህዝቡ ድንቁርናውን እና መከፋፈሉን ያሸንፋል። ህዝቡ ያለውን ኢፍትሃዊ አሰራር ለመታገል አስፈላጊ የሆነውን ህብረት ይረዳል እና መተባበርን ይጀምራል። ህዝቡ አይን ያወጣ ሙስናውን እና ሹማምንቱ የሚሰራውን አድሎአዊ ስራዎችን አብሮ በህብረት እንደሚቃውም ተረድቷል። ማህበራዊ ጥንካሬ እና ስለ ህዝብ መብት ማወቅ ይስፋፋል። ዜጎች የኢኮኖሚያዊ ነፃነት ሲያገኙ መረጃ ለማግኘት እና ለመቀያየር ይቀላቸዋል።
ህዝቡ በቀላሉ መንግስት መቆጣጠር በማይችልበት መንገድ ሃሳብ እንዲቀያየር ኢንተርነት ይፈቅዳል ያጎላብታል። የምነግስት የመረጃ አፈናን አቅመ-ቢስ እያደረገ ይሄዳል። የቻይና ህብረተሰብ ነፃ መሆን የሚችለው ህብረተሰቡ ከታች (ከብዙሃኑ) ወደ ላይ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ ሲሄድ ነው። ይህ ቀስ በቀስ የህብረተሰብ ለውጥ አገዛዙን በግድ እንዲቀየር ያደርገዋል።
ሊዩ እነዚህን ተስፋዎች እየዘረዘርም በተቃራኒው የቻይና ህብረተሰብ የመንፈሳዊ ድኻነት በአሳዛኝ መልኩ ይገልጻል። መንግስት ህዝብ ታሪክን እንዲረሳ አውጆ ለማስረሳት ትልቅ ስራ እየሰራ ነው። የቲዬንአንሜን ጭፍጨፋ (Tiananmen Massacre) ታሪክ ከአዲሱ ትውልድ አዕምሮ እንዲጠፋ ተደርጓል (ለኢትዮጵያ ተመሳሳዩ ክስተት ምርጫ 97 እና የተከተሉት ጭቆናዎች ናቸው)። የቻይና መንግስት ወጣቱ ይህን ትዝታ እንዲረሳ በጭፍን ብሄርተኝነት ይተከዋል ወጣቱ ያሉትን እውነታዊ ችግሮችን እንዲረሳ (በኢትዮጵያ context መንግስት ወጣቱን በ «ልማት» ፕሮፓጋንዳ ነው የሚሞላው) ነው። ሥን ጽሑፍ፤ መጽሔት፤ ፊልም እና ቪዲዮዎች ሁሉ በዝሙት እና ሁከት (violence) የተሞሉ ናቸው «የህብረተሰባችን የግብረ ገብ በርሃነትን» ያንጸባረቃል።
«ቻይና የተስፋ መቁረጥ እና ጥርጣሬ ዘመን ውስጥ ገብታለች ማንም በምንም አያምንም… የኮምዩኒስት ፓሪቲ መሪዎቹም አባላቶቹም በራሳቸው ፓርቲ ፕሮፓጋንዳ ማመን ትተዋል። በመርህ፤ ስነ መግባር፤ እምነት መመራት ትተን አሁን በገንዘብ እና አለማዊ ነገር ሆናል «እምነታችን»። የቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ ልክ የለሽ የማያቋርጥ ፕሮፓጋንዳ ትዝታ እና ታሪክ የለለው ትውልዶች ፈጥሯል…አንዳንድ ምዕራባዊ ሊበራሎች የማኦ ጥብቅ ዘመን ሲፈርስ የዝሙት ነፃነት ይመጣ እና እንደ ቦምብ የህብረተሰባዊ እና ፖለቲካዊ ነፃነት ያመጣል ብለው ይገምቱ ነበር። አሁን ግን ሊዩ እንደሚለው የ«ዝሙት ፌሽታ» ሀገሪቷን አጥለቅልቆታል። ሀገሪቷን በዝሙት፤ ሁከት እና ስግብግብነት ሞልቶታል። ህብረተሰቡ በረዥም ዓመታት ጭቆና እና ውሸት ፕሮፓጋንዳ ምክንያት የግብረ ገቡን ማጣት ነው ይህ ሁሉ የሚያሳየው። «ድሮ ለፖለቲካዊ አብዮት ያበደው ዛሬ ለገንዘብ እና ዝሙት አብዷል» ይላል ሊዩ።
በደህና የኑሮ ሁነታ ያደገው ከ«ቲዬንአንሜን» ቀጥሎ የተወለደው ትውልድ አሁን እንደ አላማ ያለው የመንግስት ሹም መሆን (አስፋው፤ በጉቦ ሃብታም ለመሆን)፤ ሃብታም መሆን ወይንም ውጭ ሃገር መሄድ… ስለ ታሪካዊ ስቃዮች መስማት አይፈልጉም ትዕግስቱ የላቸውም… «ታላቁ እርምጃ» (ወደ 40 ሚሊዮን የሞቱበት ማኦ የፈጠረው ርሃብ "The Great Leap Forward")፤ «ባህላዊ አብዮት» (አንዱ የቻይና ቀይ ሽብር "Cultural Revolution")፤ የቲዬንአንሜን ጭፍጨፋ። ለአዲሱ ትውልድ እነዚህን የመንግስት ጥፋቶች ማንሳት እና የህብረተሰባችን «ጭለማ ወገን» ማሳየት አስፈላጊ አይደለም። የራሳቸውን የሞልቃቃ አኗኗር እና የመንግስትን ፕሮፓጋንዳ ተጠቅመው ቻይና ታላቅ ተራምዳለች ማለት ይሻላቸዋል።»
አንዳንድ የግራ ፖለቲካ አማኞች የዛሬ የቻይና የግብረ ገብ እና መንፈስ እጦትን በገበየ ኤኮኖሚው (market economy) እና ግሎባላይዛሽን (globalization) የመጣ ነው ብለው ያሳብባሉ። እነዚህም ናቸው የቻይናን ግዙፍ የሙስና ችግር ያመጡት ያላሉ። ግን ሊዩ በተቃራኒው የዛሬው ተስፋ መቁረጥ፤ ጥርጣሬ፤ እምነት ማጣት፤ ርክሰት፤ ብልግና እና ጥቅላላ የግብረ ገብ እጦትን በማኦ ዘመን ያሳብባል። የዛ የ«ንፁ» የኮምዩኒዝም ዘመን ነው የሀገሪቷን መንፈስ የዘረራት ይላል። ያ መንግስት፤
«ኢ-ሰባዊ እና ገብረ ገብ የሌለው ነበር። የማኦ አምባገነናዊ መንግስት ሰዎችን መንፈሳቸውን እንዲሸጡ ሰውነታቸውን እንዲከዱ አድርጓል። ባለቤትን መጥላት፤ አባትን ማውገዝ፤ ጓደኛን መካድ፤ ተጎጂን ይበልጥ ምጉዳት፤ ጥሩ ኮምዩኒስት ለመባል ማንኛውም ነበር ማለት። ልክ እና ገደብ ያልነበረው አለማቆም ጨፍላቂ የሆነው የማኦ የፖለቲካ እርምጃዎች መሰረታዊ የሆኑትን የቻይና ህዝብ ስነ መግባሮችን አጠፋ።»ከማኦ በኋላ ይህ አካሄድ ቢቀንስም አለ። ከቲዬንአንሜን ጭፍጨፋ በኋላ መንግስት ህዝቡ እንዲረሳው ጣላቅ ፕሮፓጋንዳ እና ሽብር አራመደ (አስፋው፤ ልክ እንደ ኢህአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ እንዳረገው ሰውው ትዝታ እንዳይኖረው ስለ «ልማት» ብቻ እንዲያስብ)። ህዝቡ ህሊናውን ክዶ ለምንግስት ተገዢነቱን እንዲያሳይ ተገደደ። «ቻይና ህዝቧ ለህሊናው የሚዋሽ ሀገር ከሆነች በምን ተዓምር ነው ጤናማ ግብረ ገብ ያለው ህብረተሰብ መገንባት የሚቻለው?» ሊዩ ይቺን ምዕራፍ እንደዚህ ደመደመው፤
«ቻይናን ያረከሳት ዛሬ የምናየው በሀገሪቷ ዙርያ የሰፈነው የግብረ ገብ እጦት ምንጩ የማኦ ኢ-ሰባዊ ዘመን ነው። በዚህ ዘመን የዝሙት ማሳደድ ዘመቻ ለአምባገናናዊ ስረዓቱ እጅግ ይጠቅመዋል። ህዝቡ በልማት እየተጠቀመ ቢሆንም ወደ ፖለቲካ እንዳያስብ ያደርገዋል። የዝሙት «ነፃነት» ዴሞክራሲን ከማምጣት ይልቅ የድሮ የመሳፍንቶቻን የዝሙት ጥንቅን ነው የሚመልሰው… ይህ የዛሬዎቹን አምባገነኖችን በጣም ይመቻቸዋል። ከዘመናት ግብዝነት ያመጣውን ገብረ ገብ መበስበስ እና የፖለቲካ ጭቁና ጋር አብሮ ይሄዳል። ህዝቡ የፖለቲካ ነፃነት ከመጠየቅ በርክሰት እንዲጨማለቅ ያረገዋል።»በሌላ ጽሁፍ ይህ እንዴት ኢትዮጵያን እንዲሚመለከት እወያያለሁ።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!