Monday 10 September 2018

«ብዛት ቀጥሎ ጥራት» መመሪያ ያመጣው የችልተኝነት እና ስነ መግባር እጦት

ለረዥም ዓመታት የኢህአዴግ መንግስት «ብዛት ቀጥሎ ጥራት» የሚለውን መፈክር ለመንግስት አገልግሎት በሙሉ ይጠቀም ነበር። በትምሕርት፤ ጤና፤ መሠረተ ልማት፤ ቴሌኮም፤ ውሃ፤ መብራት ወዘተ የመንግስት ቱክረት ለብዙሃኑ አገልግሎት በሰፊው ማቅረብ ነበር። እንደሚታወቀው «ብዛት» እና «ጥራት» ተፎካካሪ ናቸው፤ ብዛትን ለመጨመር ጥራትን መቀነስ ያስገድዳል ጥራትን ለመጨመር ብዛትን መቀነስ ያስገድዳል። የኢህአዴግ መንግስት ያደላው ወደ ብዛት፤ ወጪ መቀነስ አና ጥራት በመከነስ። ውጤቱ ብዛት እና አነስተኛ ጥራት ነው።

መንግስት ይህን የብዛት እና ጥራት ሚዛን ምን ይምሰል እና ወደ የትኛው እናዳላ ብሎ ሲገመግም ለግምገማው ብዙ ግብአቶች (መስፈርቶች) ታይተዋል ብዬ እገምታለሁ። ለምሳሌ 1) ህዝቡ ምንድነው የሚጎድለው፤ 2) ህዝቡ የተወሰነ አገልግሎት ነው ወይንም ዜሮ አገልግሎት ነው የሚያገኘው፤ 3) የሌሎች ሀገሮች ልምድ ምንድነው፤ 4) አቅማችን ምንድነው የሚፈቅደው፤ ዛሬውኑ ጥራት ማቅረብ እንችላለን ወይንስ አንችልም፤ 4) ለፖለቲካ የሚያዋጣን ምንድነው፤ 5) በጀታችን ምንድነው የሚፈቅደው፤ ወዘተ። እነዚህ የተለመዱ "textbook" ጥያቄዎች ናቸው።

ግን እንደሚመስለኝ አንዱ ያልተካተተ መስፈርት «ባህል» ነው። ባህል ስል ብዛት ላይ ስናተኩር እና ጥራት ለጊዜውም ቢሆን አያስፈልግም ስንል፤ ይህን ስንሰብክ እና እንደ ፖሊሲ ስናራምድ ምን አይነት የስራ እና ሌላ ባህል ነው ስራተኛው እና መላ ህዝቡ ላይ እያዳበርን ያለነው የሚለው ጥያቄ ነው። በስነ መግባር እና ግብረ ገብ በኩል ምን አይነት የባህል ጫናዎች ነው ይህ ፖሊሲ የሚያመጣው? ይህ ጉዳይ ምናልባትም ዋናው ቢሆንም የታየ አይመስለኝም።

እኔ እንደሚገባኝ ጥራትን ትቶ ብዛት ላይ ማተኮር ባለሞያዎቻችን ላይ የ«ችልተኝነት» ባህል እና ባህሪ እንዲያድርባቸው አድርጓል። በስራቸው ከመኩራት እና ለሞያቸው ክብር እንዳይኖራቸው አድርጓል። የስነ መግባር እጦትንም አስፋፍቷል። እነዚህ ጉዳቶች በሰው ስነ ልቦና እና አቅም (human capital) ዙርያ ስለሆኑ ከብዛት ለሚገኘው ቁሳዊ ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ እጅግ ከባድ ነው።

እስቲ ይህ «ችልተኝነት» እና ስነ መግባር እጦት» እንዴት እንደሚከሰት ምሳሌ ላቅርብ። አንድ ሐኪም ብዙ ቀዶ ጥገና ለማድረግ አቋራጭ  መንገዶች (short cut) ይጠቀማል። አንድ አንድ አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎችንም አያደርግም። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይህ ልምድ እና ባህል ይሆናል በሐኪሙ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሐኪም ቤቱ እና ባልደረቦቹ። ችልተኝነት ባህል ይሆንበታል። ለሐኪም ቤቱም የችልተኝነት እና የግድየለሽነት ባህል እንዲሰፍን ያደርጋል።  ከዛ በኋላ አንድ ቀን ይህ ሐኪም ወደ ጥራት ያለው አሰራር ተቀየር ቢባል መቀየር ያስቸግረዋል። ልምድ እና ባህል ለመቀየር ረዥም ጊዜ ይፈጃል።

አልፎ ተርፎ ይህ የችልተኝነት እና በፍጥነት አለ ጥንቃቄ መስራት ባህሪ ሐኪሙ ተካሚውን እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ቁጥር እንዲመለከት ያደርገዋል። 100 ሰው ከማክም ዛሬ 150 ነው የማክመው ብሎ እራሱን ቢያዝናናም ውስጡ የሚያደርገው ነገር ትክክል አለመሆኑ ስለሚያውቅ ታካሚውን እንደ ሰው አለማየት ይሞክራል ("objectify" ያደርጋቸዋል)። ህሊናችን 100 ሰው ክምንጠቅም አንድ ሰው ባንገድል እንደሚሻል ስለሚነግረን ("do no harm" እንደሚባለው) ማለት ነው። ሐኪሙ ቀዶ ጥገና ላይ ተገቢው ጥንቃቄ ባለማድረግ  ሰዎች ይጎዳሉ ወይንም ይሞታሉ። ሐኪሙ ይህ ጸጸት ህሊናውን ያስቸግረዋል።

«ብዛት ቀጥሎ ጥራት» የሚል ፖሊሲ ሲነደፍ ይህ ሁሉ መታሰብ ነበረበት። ግን አልታየም። ዛሬ የጠ/ሚ አብይ መንግስት ይህን መፈክር ትተነዋል እና ወደ ጥራት እንሄዳልን ብሏል። ጥሩ ውሳኔ ይመስለኛል። ይህ የፕሊሲ ለውጥ የሰው አቅምን (human capital) ከጊዚያዊ የቁስ ጥቅምን አብልጦ ያያል እና ትክክለኛ እና አዋጪ ነው። በዋናነት ሰውን ከራሱ ጋር ከህሊናው ጋር የሚያጣላ መርህውን ያስቆማል። ቀጥሎ ሰራተኛም አዛዥም በስራው እንዲኮራ እና የ«ሙያ ስነ መግባር» እንዲኖረው ያደርጋል። የአገልግሎት ተጠቃሚ ጉዳትን እንዲቀንስ ያደርጋል። ሙያተኛው በስራው እና በሙያው ሲኮራ፤ ህሊናው ንፁ ሲሆን፤ ለተስተናጋጁ ሲቆረቆር ወዘተ ስራው ጥሩ ይሆናል፤ እየተሻሻለ ይሄዳል እና ለኤኮኖሚው ዘለቀታ ያለው መሻሻል ያደርጋል።

ግን የተበላሸ ባህልን መቀየር እጅግ ከባድ ነው። ቁሳቁስ መስራት እና መገንባት ቀላል ነው። ግን የሰው ልጅን መጠገን እና ማጎልበት ከማድ ነው። በዚህ ምክንያት ወደ ፊት ፖሊሲዎች ሲዋከሩ በሰው አቅም እና ስነ ልቦና ያላቸው ጫናዎች በጥንቃቄ መታየት የሚኖሩባቸው ይመስለኛል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!