Friday 14 September 2018

ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ…

…ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?

ሌላ ሰውን በኛን ሃሳብ ለማሳመን ስንሞክር ከአንደበታችን ይልቅ ስራችን ማለትም ምሳሌአችን ነው ዋና ሚና የሚጫወተው። ምንም ጥሩ ሃሳቦች ቢኖሩን፤ ምንም ጥሩ አቀራረብ ቢኖረንም፤ ሃሳባችንን በተግባር የምናውል ጥሩ ምሳሌ ካልሆንን ማንም አይሰማንም፤ አያምነንም፤ አይከተለንም።

በ«ኢትዮጵያዊነት» ወይንም በ«ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት» የምናምነው ይህን ነጥብ ጠንቅቀን ብናሰብበት ጥሩ ይመስለኝም። የኛም የኢትዮጵያም ህልውናን ይመለከታልና። የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ፖለቲካ ታሪካችን የእርስ በርስ (አለ ጥሩ ምክንያት) መቃረን እና መጋጨት ነው (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_31.html)። በኃይለ ሥላሴ ዘመን ሹማምንቶቹ እየተጣሉ ለፍርድ እና ለዳኝነት  ጃንሆይ ደጅ ረዥም ሰልፍ ይሰለፉ ነበር። ዛሬም የፖለቲካ ድርጅቶቻችን ከሚገባው ማለትም ብዙሃን ደጋፊዎቻቸው ቁጥር አንጻር እጅግ ደካማ ናቸው የመሰባሰብ፤ መወያየት፤ መስማማት እና መተባበር አቅማችን ደካማ ስለሆነ። ይህ የሚያሳየው የኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች የረዥም ዓመታት የንትርክ፤ የመጣላት፤ የአለመተማመን ወዘተ ታሪክን ነው።

ይህን ታሪክ ሁሉም አይቶታል እና ያውቀዋል። በተለይም የጎሳ ብሄርተኞች (ጸንፈኛም ለዘብተኛም) የሚባሉት ከኛ «ተቃራኒ» የፖለቲካ አቋም ያላቸው ይህንን የኛ ደካማ የፖለቲካ ጠባይ አይተውታክ። ንቀውናልም ማለት ይቻላል። በአንጻሩ እኛ እነሱን «ዘረኛ አትሆኑ»፤ «በግለሰብ እኩልነት እና መብት እመኑ፤ «ከኛ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ አቋም ተማሩ» ወዘተ እንላቸዋለን። ግን በጎሳ አስተዳደር የሚያምኑት እኛን የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ሲያዩ እርስ በርስ ስንጣላ እና ስንለያይ ነው የሚያዩት። ከኛ ጥሩ ምሳሌ አያዩም። ታድያ እንዴት እኛ የምንለውን ሊያምኑ እና ሊከተሉ ይችላሉ። ይከብዳቸዋል።

ግን እኛ ጥሩ ምሳሌ ብንሆን፤ የፖለቲካ ጎራችን ንፁ ቢሆን፤ እርስ በርስ ያለን ግንኙነት በፍቅር እና በሰላም የተሞላ ቢሆን የጎሳ ብሄርተኞችም ሌሎችም ወደኛ አቋም ይበልጥ ይሳቡ ነበር። «የነሱ አስተሳሰብ ይህንን ሰላም እና ስልጣኔ የሚያመጣ ከሆነ እኛም ወደነሱ እንጠጋ እና ከዚህ ብልጽግና እንካፈል» ይሉ ነበር። «እውነትም ፖለቲካ አቋማቸው ልክ መሆን አለበት» ይሉ ነበር።

ስለዚህ አሁን ባለው እና በሚመጣው የፖለቲካ ግንባታ እና ውድድር በደንብ ከመግባታችን በፊት እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች መጀመርያ እራሳችንን መፈተሽ አለብን። ቀጥሎ የነ ጠ/ሚ አብይን ምሳሌ ተከትለን ንስሃ ገብተን ይቅርታ መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል በህዝቡ ዘንድ እምኔታ ለማግኘት እና ህሊናችንን ለማርካት። እኛ ፍፁም ነን ችግሩ ከኢህአዴግ፤ ህወሓት፤ ደርግ ወዘተ ነበር ማለቱ ልክ አይደለምም አዋጪም አይደለም። እውነታ የሆነውን የኛ ታሪካዊ ጥፋቶችን ልክ እንደ ጠ/ሚ አብይ አምነን፤ ተቀብለን መናገር አለብን። ከዚህ በኋላ ነው የፖለቲካ እንቅስቃሴአችን ውጤታማ መሆን የሚችለው።



No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!