Tuesday 18 September 2018

ኦኤምኤንን ከመክሰስ ሌላ ሚዲያ አቋቁመን እንብለጠው

በርካታ ጽሁፎቼ ስ«ለሃላፊነት» መውሰድ ነው። የሰው ልጅ ችግሮች ሲያጋጥሙን ሌሎችን ከመውቀስ እኛ ምን ብናደርግ ነው፤ ምን ብንሳሳት ነው፤ ምን ቀድሞ ዝግጅት ባናደርግ ነው ብለን እራሳችንን መጠየቅ አለብን። በዚህ አካሄድ ብቻ ነው ችግሮቻችንን መፍታት የምንችለው።

ሌሎችን መውቀሱ ዋጋ የለውም። ለምን ብትሉ ችግርን የሚፈጥሩ ሰዎች አውቀው የሚያደርጉት ከሆነ የኛ እነሱን መውቀስ በሃሪና ተግባራቸውን አይቀየርም። ይቀየራሉ ብለን ስንጠብቅ ችግሮቻችንን እያባባሱ ይቀጥላሉ! እኛ እየተጠቃን እንቀጥላለን። በራሳችን ያለን መተማመን እየቀነሰ ይሄዳል። የሰለባ አስተሳሰብ (victim mentality) እና የዝቅተኝነት መንፈስ (inferiority complex) እያደረግን እየጠነከረብን እንሄዳለን። አሉንታዊ እና ብሶታዊ ሰዎች እንሆናለን።

ግን ችግር ሲያጋጥመን ሃላፊነት ወስደን ምን ብናደርግ ባናደርግ ነው ይህ ችግር ያጋጠመን ካልን እራሳችንን የችግሩ መፍትሄ እናደርጋለን። እራሳችንን እናጎለብታለን (empower)። ችግሩን ሰፋ አድርገን እናያለን። ኃይል እንዳለን ይገባናል እና በራሳችን እንድንተማመን (confidence) ያደርገናል። አዎንታዊ እርምጃዎች ወስደን ከችግራችን እራሳችንን እናወጣለን። ደግሞ ችግር እንዳይገጥመን ደግሞ እራሳችንን እናጠነክራለን። ለደህንነታችን ሌሎችን መለመን እንደማያስፈልገን ይገባናል ስለዚህም በማንነታችን በተገቢው እንኮራለን።

በቅርቡ በቡራዩ እና ዙርያ በተከሰተው የጎሳ ማጥፋት (ethnic cleansing) ክስተት በርካቶች ኦኤምኤን ተለቪዥን ጣብያን እንደ አንድ ጥፋተኛ ከሰዋል። ኦኤሜን ላይ የሚቀርቡ ተንታኞች የዘር ማጥፋት ቅስቀሳ ስለሚያደርጉ ነው አንዱ ምክንያት እንደዚህ አይነት ክስተት የሚከሰተው ይባላል። ኦኤምኤን ነው ችግራችን እና ይዘጋ ወይንም እስከሚስተካከል ይታገድ ይባላል።

ጥሩ ነው። አጥፊ አጥፊ ነው ተብሎ መንግስትን ህግን አስከብሩ ማለትም የዘር ማጥፋት ቅስቀሳን አቁሙ ማለት ተገቢ ነው። ግን በዚ ላይ ብቻ ማተኮር እራስን አቅመ-ቢስ ማድረግ ነአ ማዋረድ ነው። አንዴ መንግስት ተነግሯል፤ መንግስት ያውቃል፤ ይበቃል። ኦኤምኤንን ደጋግሞ መክሰስ ኦኤምኤንን ማጎልበት ነው። በኛ ላይ ብዙ ኃይል አለህ እና ጫና መፍጠር ትችላለህ ማለት ነው። እኛ የአንተ ሰለቦች ነን ብሎ ማለት ነው። ይህ አካሄድ ኦኤምኤንን ያጎለብታል እኛን ደግሞ አቅመ-ቢስ ያደርጋል። የሰለባ እና የዝቅተኝነት ስሜት እንዲአድርብን ያደርጋል። በዋናነቱ ደግሞ ችግሩ እንዲቀጥል እንዲባባስ ያደርጋል።

መሆን ያለበት አንዴ መልዕክታችንን ለመንግስት ካስተላለፍን በኋላ እና ለህዝቡ የኦኤምኤንን ጥፋት ካገለጽን በኋላ ወደ ራሳችን ስራ መግባት ነው። 10% ጊዜአችን ስለ ኦኤምኤን እውነቱን መናገር ካጠፋን 90% ጊዜአችንን እራሳችን በራሳችን መፍትሄ በማግኝነት ነው ማድረግ ያለብን።

በዚህ በሚዲያ የዘር ማጥፋት ጉዳይ ምንድነው እኛ ማድረግ የምንችለው? ብዙ ነገሮች አሉ ግን አንዱ ቀላሉ ጠንካራ የኦሮምኛ ሚዲያ ማቋቋም ነው። ይህን ነው ኢሳት ረዥም ዓመታት በፊት የመከረው ግን ይህ ሙከራ አቅሙ እጅግ ደካማ ነው። ስለዚህ ያልንን አቅም (resources) ሰብስበን ኦኤምኤንን የሚበልጥ ሚዲያ በማቋቋም መስራት አለብን። ይህን ካደረግን እና ከተሳካ ግማሹ ችግር ይጠፋል። ስለ ኦኤምኤን ማልቀስ ይቀራል። ይህ አካሄድ አሉታዊ ከመሆን አዉንታዊ ያደርገናል።

ሁሉ ጉዳዮቻችንን በዚህ መልኩ ብናያቸው ጥሩ ይመስለኛል። ጣት ከመጠቆም እራስን ማየት እና እራስን አጎልብቶ መፍትሄ በራስ ባግኘት። እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ቢኖረን ኖሮ ስንት ያለፍንባቸው ችግሮች አይኖሩም ነበር። በጥቂት ድጋፍ ያለው ህወሓትም አንገዛም ነበር! ስለዚህ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ እናተኩር፤ ከህጻንነት ወደ ሃላፊነት የምንወስድ አዋቂዎች እንቀየር።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!