Friday 21 September 2018

የተረሳው ጉዳያችን፤ የመሬት ፖሊሲ ሚና በጎሳ ፖለቲካ

ከዚህ በፊት ደጋግሜ ስለ የኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲ ችግር ጽፍያለሁ (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_47.html)። መሬት የግል ወይንም የአካባቢ ("local community" ለምሳሌ ወረዳ) ከመሆኑ ፋንታ የመንግስት መሆኑ ለህዝባችን እጅግ ጎጂ ፖሊሲ ነው ብዬ ነው የማምነው። ለዝርዝሩ ከላይ የጠቀስኩትን ጽሁፍ አንብቡ፤ ግን በአጭሩ መሬት የመንግስት መሆኑ የፈጠረው ችግሮች እንዲህ ናቸው፤

1. ገበሬው ለ«ጎበዝ ገበሬ» የሆነው ጎረቤቱ መሬቱን ሽጦ ወደ ከተማ መሄድ ባለመቻሉ ገጠር ቀርቶ በገጠር የመውለድ መጠን (birth rate፤ በገጠር አማካኙ ከስድስት ልጅ በላይ ነው) ልጅ ወለደ። ከተማ ቢሄድ ኖሮ ሁለት ልጅ (ሁለት አማካኙ ነው ለከተማ ነዋሪ) ይወልድ ነበር። ይህ ማለት የህዝብ ቁጥርን ባልተጠበቀና በኢተፈጥሮዊ (artificial) መንገድ ንሯል። ኢተፈጥራዊ ማለት ህዝቡ ወደ ከተማ እንዳይሄድ ነፃነቱ በመገደብ የጠፈጠረ ሁኔታ ስለሆነ ነው። ከግዳጅ የመጣ ክስተት ስለሆነ ነው።

2. የገጠር ህዝብ ቁጥር ንሮ የገበሬ መሬት አንሶ ልጆች የሚወርሱት አጥተው አሁን ታላቅ የገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት ተከስቷል። ለ40 ዓመት ቀስ በቀስ ፍልሰት ከመሆኑ ፋንታ የገጠሩ ሰው ለ40 ዓመታት ከገጠር ተጠራቅሞ አሁን ባንዴ ወደ ከተሞች እየመጣ ነው። ይህ ሁኔታ ከተሞቻችንን አስጨንቋል።

3. ገበሬዎች ቢጎብዙም ገንዘብ ቢኖራቸውም መሬት መግዛት ባለመቻላቸው የግብርና ስራውን ማስፋፋት አልቻለም። ማደግ አልተፈቀድለትም። በዚህ ምክንያት «የሰው አቅማቸው» (human capital) እንዳያድግ ተደርጓል። ለምሳሌ እንደ የግብርና የሙያ፤ የንግድ ሙያ፤ የአስተዳደር ችሎታ አይነቱን እንዳያዳብር ተደርጓል።

4. ገበሬው ሽጦ መሄድ ባላመቻሉ መሬቱን ለትውልድ እያከፋፈለ መሸንሸን ሆነበት። መሬቱ ተሸንሽኖ የያንዳንዱ ገበሬ መሬት አንሶ አንድ ቤተሰብም ማስተዳደር የማይችል ሆኗል። በዚህ ምክንያት ገበሬዎች ለድርቅ እና ርሃብ ተጋለጡ። የምግብ ዋስትና እጥረት እንዳለ ነው።

5. ጎበዝ ገበሬዎች መሬት ገዝተው መስፋፋት ባለመቻላቸው እና ደካማ ገበሬዎች ለጎበዞቹ መሸጥ ባለመቻላቸው የእርሻ ውጤት ዝቅተኛ ሆኖ ቈርቷል። ይህ ደግሞ የእህልና የምግባ ዋጋ ግሽበት አምጥቷል።

ከላይ የጠቀስኳቸው ባብዛኛው በኤኮኖሚ ዙርያ የሆኑ ነጥቦች ናቸው። ግን የመሬት ፖሊሲው ሌላ ታላቅ የፖለቲካ እና ማህበረሰባዊ ተጽዕኖ አለው።

ባጭሩ፤ የመሬት ፖሊሲው አንዱ የጎሳ አስተዳደሩ ምሶሶ ነው። መሬት የ«ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች» ነው ሲባል ለ27 ዓመት የተተረጎመው የአማራ ክልል መሬት የ«አማራ ብሄር» ነው፤ የኦሮሚያ ክልል መሬት የ«ኦሮሞ ህዝብ» ነው ወዘተ እየተባለ ነው። ትርጉሙም የህገ መንግስቱን ጽሁፍም መንፈስም የተከተለ ነው።

«መጤ» እና «ነባር» የሚሉት ጽንሰ ሃሳቦች በማህበረሰቡ በዚህ መሬት ፖሊሲ ይደገፋሉ። የ27 ዓመታት የመፈናቀል ዘመቻዎች የተካሄዱትም በዚህ ምክንያት ነው። ግን ህጉ የመሬት ባለቤትነት የግለሰብ ወይንም የቅርብ አካባቢ ሰዎች ቢያደርግ ኖሮ የ«መጤ» እና «ነባር» አስተሳሰብን ይቀንስ ነበር ነአ ቀስ በቀስ ያጠፋ ነበር። ለዚህ አስተሳሰብ የህግ ሽፋን እንዳይኖረው ያደርጋል። ተፈናቃዮች ለመብታቸው በፍርድ ቤት መታገል እንዲችሉ ያደርጋቸው ነበር።

ስለዚህ ዛሬ ያለውን ጎሰኝነትን ለመታገል እና ቀስ ብሎ ከጎሳ ፌደራሊዝም ወደ ህብረ ባህላዊ አገዛዝ ለመሄድ ይህን የመሬት ፖሊሲ መመልከትና መቀየር ጠቃሚ ይመስለኛል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!