Sunday 4 November 2018

ጥብቅ ማህበራዊ ኑሮ ለሰው ልጅ ተፈጥሮው ነው

ስለ ብቸኛ (individualist) እና ማህበራዊ (collective) ማህበረሰብ ወይንም ባህል ብዙ ተተንትኗል። የቃላቶቹ ትርጉም በጣም ጥብቅ ባይሆንም ከሞላ ጎደል ግልጽ ነው። እነ አሜሪካ እና አውሮፓ የብቸኛ ማህበረሰብ ባህል አላቸው። በርካታው ሶስተኛ ዓለም የማህበራዊ ባህል ነው ያለው። የብቸኛ ኑሮ የግል መብትና ራስን በራስ መቻል ላይ ነው የሚያተሩረው። የማህበራዊ ኑሮ የሰው ልጅ ይበልጥ ለማህበረሰቡ ህገጋት እንዲገዛ ያደርጋል እና መደጋገፍ እንዲኖር ያደርጋል። ወዘተ።

አብዛኛው ጊዜ ስለ ብቸኛ እና ማህበራዊ ባህሎች ሲተነተን ባህሪአቸው፤ ጥቅም እና ጉዳታቸው፤ በፖለቲካ እና ኤኮኖሚ ያላቸው ተፅዕኖ ወዘተ ነው የሚጠቀሰው። ሰው እንደ ርዕዮት ዓለሙ ወይንም እንደ ግል ምኞቱ ይህ ከይህ ይሻላል ይላል። የአስተሳሰብ እና ፍላጎት ጉዳይ ነው የሚደረገው። ግን በዚች ዓለም ዘመናዊነት ሁሉንም መግዛቱ ስለማይቀር በርካታ ተንታኞች ሁሉ ቦታ የብቸኛ ኑሮ እንደሚሰፍን ያምናሉ።

ግን ጥንታዊው ክርስትና እነዚህን ብቸኛ እና ማህበራዊ የምንላቸውን አኳኋን እንደ እኩል አማራጭ አያቆጥራቸውም። ክርስትና የሚለው የማህበራዊ አኗኗር የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው (ontological)። የሰው ልጅ ህይወት ከባለንጀራው ጋር የተቆራኘ ነው። እርስ በርስ አንድነት አለን። ከኢግዚአብሔር አንድነት (communion) አለን። በዘር፤ በትውልድ፤ በሀገር፤ ከቤተሰብ ወዘተ የወረስነው ሁሉ እራሳችን በራሳችን በምኞት እና ፍላጎት ከምንወስነው ይልቅ እጅግ ግዙፍ ነው።

ዛሬ እንደ በርካታ የሶስተኛ ዓለም ሀገራት በኢትዮጵያም የብቸኛ ኑሮ በ«ዘመናዊነት» እና «ልማት» በኩል አድርጎ እየመጣ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/04/blog-post_13.html)። በተለይ በአዲስ አበባ እና በተወሰነ ደረጃ በትናንሽ ከተሞች ህብረተሰቡ ይህ የብቸኛ ኑሮ ተዕፅኖ እየተሰማው ነው። ሰው አይጠያየቅም፤ አይተዋወቅም፤ አይደራረስም፤ ልጆቹንም በደምብ አያገኝም፤ ባለመተዋወቅ ምክንያት ወንጀል ይበዛል፤ ፍቅር የለም፤ ከሰው ይልቅ ገንዘብ ወዳድ ሆኗል፤ ለባለንጀራው ግድ የለውም፤ አዛውንቶች አይጦሩም፤ ወዘተረፈ ደጋግሞ ሲባል ሁላችንም እንሰማለን። ጥሩ ነገር እንዳልሆነ እናውቃለን ግን እንደ መዓበል መቶብን በትክክል ምን እንደሆነም ችግሩን ለመቅረፍ ምን ማድረግ እንዳለብን አናውቅም።

በዚህ አጭር ጽሁፍ ማለት የምፈልገው «ይህን ችግር አንንቀው» ነው። ወጋችንን ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው ልጅ ማንነታችንንም የሚያጠፋ ነገር ነው። በ«ሰለጠነው ዓለም» የብቸኛ ኑሮ ያመጣውን ልባዊ ቀውስ እያየን ነው። ኪስ ሙሉ ደስታ (እውነታዊ ደስታ) የለም። የሰው ልጅ ለብቸኝነት አልተፈጠረምና። ጠ/ሚ አቢይ ይህንን በተወሰነ ደረጃ እንደ ገባቸው አመልክተዋል። ግን እሳቸውም ሁላችንም ጠልቀን እንመርምረው። በታቻለ ሁኔታ በግል ኑሮዋችንም በመንግስት ፖሊሲም የብቸኝነት ኑሮ እንዳይሰፍን እንስራ። የህልውና ጉዳይ ነውና።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!