Tuesday 20 November 2018

የደርግ ኢሰባዊ ድርጊቶች በአግባቡ ለህዝብ ቢገለጽ ኖሮ ታሪክ (ብሶ) እንዳይደገም ይረዳ ነበር...

በደርግ ዘመን የሚካሄዱት ኢሰባዊ ድርጊቶች እንደ ግድያ፤ እስር፤ ማሰቃየት ወዘተ ለኢትዮጵያ ህዝብ በበቂ ደረጃ በይፋ አልቀረበም። «የእርቅ እና ሰላም» እና የፍትህ ሂደት በታላቅ መድረክ ለህዝብ አልቀረበም። መቀረብ ነበረበት። ህዝቡ ከተጎጂዎች ታሪኮቸውን በደምብ መስማት ነበረበት። የጨቋኞችን የፍርድ ሂደት በደምብ መስማት ነበረበት። ይህ ሳይደረግ ቀርቶ ጉዳዩ ላይላዩን ብቻ ታይቶ ህዝቡ «የደርግ ባለስልጣኖች ታሰሩ ቀጥሎ ተፈረደባቸው» ተብሎ ጉዳዩ በዛው ተዘጋ። ለስነልቦና የሚያስፈልገው ግልጽ የሆነ የእርቅ፤ ሰላም እና ፍትህ ሂደት አልተካሄደም።

በዚህ ምክንያት ዛሬ ብዙ ሰው ስለ ደርግ፤ ነጭ ሽብር እና ቀይ ሽብር አያውቅም። የለማወቅ ብዛቱ ይገርማል፤ አዲሱ ትውልድ ብቻ ሳይሆን የደርግ ዘመነን የሚያውቁትም በአግባቡ ታሪኩን አያውቁትም። ይህ «ማህበራዊ መርሳት» አንዱ ምክንያት ይመስለኛል ኢህአዴግ የደርግን ጭቆና በባሰ ሁኔታ እንዲደግም እድል የተሰጠው።

ሰሞኑን ከአንድ ዘመዴ ጋር ስለ ቅርብ ቀናት የደህንነት፤ የፖሊስ እና የሌሎች «መርማሪዎች» እና ሥቃይ አዛዥ እና አስፈጻሚዎች መታሰር እየተወያየን ነበር። ይህ ዘመዴ በደርግ ጊዜ ታስሮ ነበር። በታሰረበት ጊዜ እሱ እና ሌሎች ላይ የደረሰባቸውን የእስር ስቃይ በትንሹ አካፈለኝ/አስታወሰኝ፤
1. ዘመዴ ብዙ ከተገረፉት አንዱ ቢሆንም የደረሰብኝ ከሌሎች ይሻላል ይላል፤ ቆሻሻ ካልሲ ከአፍ ውስጥ ወትፈው ነው ለሳምንታት የገረፉት።  
2. አሰቃዮች ሴቶችን በሲጋራ መለኮሻ ነበር «እንትናቸውን» የሚያቃጥሉት። 
3. ጥፍር መንቀል ወዘተ ተራ እና የተለመደ ነበር። 
4. አንድ የታወቀ ዘመዴ የሚያውቀው አሰቃይ ነበር። ለሊቱን በየ እስር ቤቱ እየዞረ አንዳንድ እስረኞችን መርጦ አውጥቶ በሚኪና ይወስዳቸዋል። ሜዳ ላይ ለቆ «ሩጡ» ብሎ ያዛቸው እና በካላሹ ተረከዛቸውን መሬት መሬቱን ይተኩስባቸውል። «ጨዋታው» ሲያልቅ ይገላቸዋል። ይህ አሰቃይ መጨረሻ ላይ ደርግ እራሱ አስሮት ወደ ዘመዴ ያለበት እስር ቤት ገባ። አዕምሮውን ክፉኛ ሳተ፤ ጨርቁን ጣለ።
እንደዚህ አይነት ታሪኮች ብዙ ናቸው ግን ህዝባችን በደምብ አልተነገረውም። አስቀየሚ ዝርዝሮቹ  በይፋ ይነገሩ አደለም የምለው። ላያስፈልጉ ይችላሉ። ግን ክስተቶቹ፤ ተጎጂው፤ ወንጀለኛው፤ ወዘተ በህዝብ መደረክ በሚገባው ደረጃ መቅረብ አለበት። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይህን አሳፋሪ ታሪካችንን ማወቅ አለበት።

ለምን የደርግ ጭካኔ ታሪክ በደምብ አይልተነገረም? እንደሚመስለኝ ኢህአዴግ እራሱ ለሰው ልጅ የሚሰጠው ዋጋ ትንሽ ስለሆነ ነው። እራሱ እንደ ደርግ ህዝብን እንደሚረግጥ ስለሚያውቅ ይመስለኛል። ስለዚህ ኢህአዴግ በደርግ ግፎች ትልቅ የፖለቲካ ትርፍ ማትረፍ ቢፈልግም የራሱ እምነቶች እና ስራዎች ይህን እድልም እንዳይጠቀም አድርጎታል።

አሁን የ«እርቅና ሰላም» ኮሚሽን ሲቋቋም ያንን የደርግንም ታሪክ እንዲያካትት እና እንዲያሰማ መደረግ ያለበት ይመስለኛል። ኮሚሽኑ የ44 ዓመታት ግፍን ያስተናግድ። እኛ ኢትዮጵያዊያን ለረዥም ዓመታት ወንጀለኞች፤ ገዳዮች፤ አሰቃዮች ወዘተ እየወለድን እያሳደግን ወደ ስልጣን እያመጣን መቆየታችንን ማየት አለብን። የዚህ ቀጥታ ሰለቦች ታሪካቸውን የመናገር እድል ማግኘት አለባቸው። ሌሎቻችን ጥፋት እና ሃላፊነታችንን በነሱ በደረሰባቸው ማየት እና ማመን አለብን።

ይህ የንስሀ ሂደት ባለፈው 27 ዓመት ብቻ ከተገደበ እራሳችንን በሚገባው እንዳንወቅስ ይረዳናል። «እነሱ ናቸው ጥፋተኞቹ» ብለን የራሳችንን ሃላፊነት እንዳናይ ያረገናል። ግን ከደርግ ጀምሮ ታሪክን ካየን ሙሉ ግንዛቤ ይኖረናል። የኛ የማህበራዊ ጉድለታችንን እንድናምን ይረዳናል። አንድ ህበረተሰብ በተደጋጋሚ ጨቃኞች ሲወልድ እራሱን ምፈተሽ አለበት።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!