Friday, 13 April 2018

ብቸኝነት

ወደ 10-15 ዓመታት ይሆነዋል የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ስለ የለት ኑሮዋቸው ስለ ማህበራዊ ኑሮዋቸው መለወጥ መገንዘብና ማዘን ከጀመሩ። «ሰዉ እንደ ድሮ አይደለም» ይላሉ። «ጊዜ የለም። ወላጆቼን ዘመዶቼን በወር አንዴም አላገኛቸውም።» «ጥዋት በ12 ሰዓት ወጥቼ ማታ በሁለት ነው ቤት የምገባው። ልጆቼን ከቅዳሜና እሁድ በቀር አላገኛቸውም።» «ጎረቤቶቼን አላውቃቸውም። ዛሬ ማንም ለጎረቤት ጋር አይተዋወቅም። ችግር ቢያጋጥመን ማን እንደሚደርስልን አናውቅም።» «ለእድር ማህበር ቤተ ክርስትያን ጊዜ የለንም። ማህበራዊ ኑሮ የለንም።» «እንደ ድሮ እህል ወዘተ ማዘጋጀት አልችልም የምገዛው ደግሞ ጥራቱ አይታመነም ከየት እንደሚመጣም አላውቅም።» «ዛሬ ሰዉ አይታመንም ለገንዘብ ብሎ ሰው ይሸጣል ራስ ወዳድ ነው።» ወዘተ። ሁላችሁም እነዚህን አባባሎችን ሰምተናቸዋል።

አዲስ አበበ ባለፉት ቅርብ ዓመታት በህዝብ የመብዛትና በኤኮኖሚው ፈጣን እድገት ምክንያት የ«ብልጽግና» ("development") የ«ዘመናዊነት» ("modernity") ችግሮችን ይታዩባታል። አንዱ ችግር በ«ያደገው» ወይም በ«የለጸገው» ዓለም ለረዥም ዓመታት የሚታየው የህብረተሰባዊ ችግር ነው። ብዙዎች ይህን ችግር የማኅበራዊ ኑሮን ማጣት ይሉታል። ግን ጠልቀን ካየነው በሌላ ቃል ልናጠቃልለው እንችላለን፤ «ብቸኝነት» (loneliness)። ይህ ለሰው ልጅ ኢተፈጥሮ የሆነው ብቸኝነት ኢትዮጵያንም ዓለምንም ለማጥፋት ከባድ ስራ እየሰራ ነው።

የበለጸገና ዘመናዊ ህብረተሰቦችና ሀገሮች የብቸኛ ርዕዮት ዓለም (individualism) የሰፈነባቸው ናቸው። ልክ የአዲስ አበባ ሰዎች እንደሚሉት እነዚህ ሀገር ሰው አይተዋወቅም ጊዜ የለውም ማህበራዊ ኑሮ የለውም ጓደኝነት የለም የሚደግፈውም የሚገድበውም ማህበረሰብ የለውም። እራሱ ይወስናል ለራሱ ይኖራል በራሱ ይተማመናል በሚዲያ ጫና በማስተዋወቂያ ካልሆነ ከማህበረሰቡ ምንም ሀሳብ ድጋፍ አያገኝም። እግዚአብሔርም የለውም ወይም እራሱ የፈጠረው የሰየመው በራሱ የሚወሰን አምላክ ነው ያለው።

በአዲስ አበባም አሁን ይህ ቀስ ብሎ እየገባ ነው። ልጅ ተወልዱ በሕፃንነቱ ወደ ሕፃናት ማቆያ ይላካል። እናትም አባትም መስራት አለባቸው ከዋጋ ግሽበት ጋር ለመወዳደር። ምናልባትም ለትንሽ ቤት ለማጠራቀም። ልጁ ጥዋትና ልተኛ ሲል ነው ወላጆቹን የሚያገኘው፤ ያውም ካገኛቸው። ቤተሰቡ ከዘመድም ከማንም ጋር አይገናኝም ጊዜ የለምና። ወደ አያቶቹ ለመሄድ የአንድ ሰዓት መንገድ ነው በታክሲ። የአክስቱ ቤት የሁለት ሰዓት መንገድ ነው። የጎረቤት ልጆችን በደምብ አያቃቸውም ከቅዳሜ እሁድ በቀር ከቤት አይወጣምና። ልጁ ከወላጅና እህት ወንድም በቀር ከሌሎች ተገሎ ነው የሚያድገው።

ልጁ ጎበዝ ተማሪ ነው ሁለተኛ ትምሕርት ቤት ጨርሶ ከአዲስ አበባ ሩቅ የሆነ ዩኒቨርሲቲ ይሄዳል። ትምሕርቱን አጠናቆ አሁንም ከአዲስ አበባ ሩቅ የሆነ ከተማ ለስራ ይበደባል። ከተወሰነ ዓመታት በኋላ እንደምንም አድርጎ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ጥሩ የኪራይ ዋጋ በማግኘቱ ከወላጆቹ ሩቅ ቦታ ቤት ይከራያል።

ትዳር ይመሰርታል ልጅ ይወልዳል ልጁ አያቶቹን በሁለት ሶስት ወር አንዴ ነው የሚያገናቸው። እነዚህ አያቶች አሁን እያረጁ ነው የሚጦራቸው ያስፈልጋቸዋል። ልጆቻቸው ሁሉ ከነሱ ርቀው ነው የሚኖሩት። ጊዜም የላቸውም። ሰራተኛ ጠባቂም አይገኝም። እንደ ምዕራቡ ዓለም የአዛውንት ማረፍያ (ወይም «መጣያ») የለም። ምን ይደረግ! እነዚህ አያት የሆኑ አዛውንቶች የመጨረሻ እድሜአቸውን ከልጆቻቸው የልጅ ልጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ተለይተው ሊኖሩ ነው። ይህ ነው የዘመኑ የብቸኝነት ኑሮ።

እግዚአብሔር ሲፈጥረን በቤተሰብ እንድንኖር ነው። ሚስት እንደ ቤተ ክርስትያን ባል እንደ ክርስቶስ አንድ ሆነው ልጆች ይወልዳሉ። የዚህ ቤተሰብ አንዱ ተልዕኮ መማርያ ማስተማርያ ነው። የእግዚአብሔርን ፍቅር እንድንማር እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ፍፁም ፍቅርን እንድንማር ትዳርና ልጆች ሰጠን። ባለቤታችንን ልጆቻችንን በመውደድ ለነሱ መሥዋዕት በማድረግ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ትንሽ ልንረዳ እንችላለን። ከዛ አልፎ እንደሱ አይነት ፍቅር እንዲኖረን መሞከር እንችላለን እንደሱ መሆን መሞከር እንችላለን።

እንዲሁም እግዚአብሔር ሲፈጥረን ከህብረተሰብ ማህል አድርጎ ነው። ግለሰብ ብቻ ወይንም አባት እናት ልጆች ብቻ አድርጎ አልፈጠረንም። አንዱ የቤተ ክርስትያን ተልዕኮ ይህ ነው፤ ህብረት እንዲሆነን ነው። ይህ ህብረተሰብንም እንደ አባት እናት ልጆች የእግዚአብሔር ፍቅር መማርያ ይሆነናል። ስለዚህም ነው ከጥንት ጀምሮ ክርስትያኖች በደብር ዙርያ እንደ አንድ ህብረተሰብ የምንኖረው። ይህ አኗኗር ከአባቶቻችን የወረስነው ነው። በተዘዋዋሪ የገዳምም አኗኗር እንደዚሁ ነው።

ስለዚህ ቤተሰባዊና ማህበራዊ ኑሮ እግዚአብሔር የሰጠን አኗኗር ነው። አኗኗራችን በዚህ መልክ ካልሆነና የብቸኝነት ኑሮ ከያዝን ኢተፈጥሮ ነውና እንጎዳልን። እንጓደላለን። እንታመማለን። እናጣለን።

ግን «ብልጽግና» እና «ዘመናዊነት» ይህን ኢተፈጥሮአዊ የሆነውን የብቸኝነትን ኑሮ ነው የሚያመጡት የሚያራምዱት። ታድያ እንዴት አድርገን ነው ይህን መከላከልና መቀየር የምንችለው? ወደ መፍትሄ ከመሄድ መጀመርያ ችግሩን በትክክል መረዳት አለብን። ለዚህ ገና ነን። ለምን ቢባል ብልጽግና ዘመናዊነት ከ«ካፒታሊዝም» ጋር አብሮ ከብቸኝነት የሚመጡርን የጠቀስኩትን ጉዳትና ህምምን የሚያስታግስ ዕፅ ይሰጡናል። ገንዘብ ምቾት መዝናኛ ጨዋታ። ቤት ትልቅ ቤት መኪና ትልቅ መኪና ቴሌቪዥን ፊልም ዘፈን ስፖርት/ቴያትር  ዝነኞች አሉባልታ ወሬ ከፍልስፍና እስከ ሙዚቃ እስከ መዝናኛ የተለያዩ ጣዖቶች። እነዚህ ዕፆች የኢተፈጥሮ አኗኗራችንን ብቸኝነታችንን የማደንዘዝ ስራ ብቻ አይደለም የሚያደርጉት በመጀመርያ አኗኗራችን ኢተፈጥሮ እንደሆነ እንዳንረዳ ነው የሚያደርጉን። እንዳመመን እንዳናውቅ እያመመን ምክንያቱን እንዳናውቅ ነው የሚያረጉን።

ስለዚህ እስቲ ሁላችንም አኗኗራችንን እንድንመለከት እጋብዛለሁ። ባል ሚስት ልጆች ቢኖሩንም ብቸኞች አይደለንምን? የሚጦርን አይኖርምን? ልፋታችን ከንቱ አይሆንምን? እስቲ እራሳችንን እንጠይቅ።


No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!