https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_97.html
የለገጣፎ ነዋሪዎች መፈናቀል ድርጊት በምንም ሚዛን እጅግ አሳፋሪ እና ለሁላችንም ጎጂ መሆኑ ግልጽ ያልሆነለት... ይቅርታ አድርጉልኝ እና የድሮ የፖለቲካ ደንቆሮ ነው።
ሆኖም እንደዚህ አይነት መፈናቀል እና ተመሳሳይ ክስተቶች ለ27 ዓመታት ሲካሄዱ ቆይተዋል። ወደ ኋላ ከሄድንም ደርግ የ«ከበርቴዎችን» ቤት እና መሬት አለ ፍትህ፤ ሚዛን፤ እና ርህራሄ ቀምቷል።
የአዲስ አበባ ህዝብ ይሁን ሁሉ ያትዋል አሳልፏልም። በርካታ ሰለቦች አይተናል። ግን አንዴም ጣታችንን አንስተን እንርዳችሁ፤ ይህ ክስተት እንዳይደገም ተደራጅተን ለእርስ በርሳችን እንቁም ብለን አናቅም። ይሉቅንስ ወይ ተባብረናል፤ አንገታችንን ደፍተናል፤ ወይንም ለተጎጂዎች ከመራራት ፋንታ ፈርደንባቸዋል።
በዚህ ምክንያት አሁንም ባለንጀሮቻችን፤ ጎረቤቶቻችን፤ ወንድም እህቶቻችን እጣ ፈንታቸው ከሆነ መሬት እና ቤቶቻቸውን ይነጠካሉ። ዛሬ ለገጣፎ ነው ነገ ሌላ ቦታ። የኦሮሚያ መንግስት ተወካዮች ይቀጥላል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ህዝብ እንደዚህ አይነት ኢ-ሰባዊ ድርጊቶች እንዲቆሙ ከፈለገ ከመደራጀት በስተቀር ምንም ማድረግ አይችልም። መቾህ፤ ቂም መያዝ፤ ማዘን ወዘተ ብዙ ዋጋ የለውም። አንድ እና አንድ ምርጫ ብቻ ነው ያለው፤ መደራጀት።
ምን ማለት ነው መደራጀት? መቼስ ፖለቲከኞቻችን ሊያውቁ እና ሊያስተምሩን ይገባል ግን እስቲ ለኛ ብዙሃን በምሳሌ መልኩ ልዘርዝረው። ልብ፤ እውቀት፤ እና ገንዘብ ያላቸው «የአዲስ አበባ ዜጎች ድርጅት» የሚባል ያቋቁማሉ። የድርጅቱ ተዕልኮ የአዲስ አበባ ህዝብን ፍላጎትን እና ደህንነትን ለማስከበር መሟገት ይሆናል። ድርጅቱ በየ ቀበሌው፤ በየ ህዝብ ዘርፍ (ነጋዴ፤ ሞያተኛ፤ አስተማሪ፤ እናቶች፤ ወዘተ) አባላት እና ገንዘብ ይመለምላል። ትምሕርት ያስተምራል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ይሰበስባል። እነዚህ አባላት በዬ ህብረተሰብ ክፍል እና መንግስት መስርያቤቶች ያሉ ይሆናሉ እና በይፋም በህቡም ለድርጅቱ እና ለአዲስ አበባ ህዝብ ተጽዕኖ ማድረግ የሚችሉ ይሆናሉ። እንድነ ለገላፍቶ አይነት ክስተት እንደሚካሄድ ሲታወቅ ይህ ድርጅት በሁሉ ዘርፍ ተጽዕኖ ያደርጋል። እንደዚህ አይነት የማፈናቀል እና ሌላ ህዝቡን የሚጎዳ እቅድ እንዳይታሰብ ያደርጋል።
አሁን የደረደርኩት ምሳሌ አዲስ እንዳልሆነ መቼስ ሁላችንም እናውቃለን። ዓለም ዙርያ ለሺ ዓመታት ፖለቲካ በዚህ መልኩ ነው የሚካሄደው። እንኳን የሰላም ፖለቲካ የጦር/ኃይል ፖለቲካም እንዲሁ ተደራጅቶ ነው የሚሰራው። ስለዚህ የአዲስ አበባ ህዝብ ማድረግ ያለበት የተለየ እና በተለየ መልኩ ከባድ ነገር አይደለም። ለአካባቢ ጥቅም መደራጀት ቀላል እና የተለመደ የሰው ልጅ አካሄድ ነው።
ታድያ ለምንድነው የአዲስ አበባ ህዝብ እስካሁን ያላደረገው? በነ ግምት የአዲስ አበባ ህዝብ ይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ (ሀገር) ብሄርተኞች ከ66 አብዮቱ እና ሽብሮቹ እስካሁን አላገገመም። አብዮት ተከታታይ ትውልዶች እንደሚያተፋ ይታወቃል በሀገራችንም እንዲሁ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራውን እርስ በርስ አፋጅቶ ድምጥማጡን አጥፍቷል። ስለዚህ የአዲስ አበባ እና ጠቅላላ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ፖለቲካ አሁንም እጅግ ደካማ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_38.html)።
ይህ እንደሆነ እውነታው የአዲስ አበባ ህዝብ ካልተደራጀ እንደ ለገጣፎ አይነት ኢ-ሰባዊ ክስተቶችን ማቆም እንደማይቻል ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ ደጋግሞ ይረገጣል። ከመደራጀት በቀር ምንም መፍትሄ የለም። ለመድገም ያህል እሮሮ ማሰማት፤ ማልቀስ፤ መርገም፤ መለፍለፍ ወዘተ ዋጋ የለውም። ከባዱ የመደራጀት ስራ ግድ መሰራት አለበት።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!