Tuesday 24 July 2018

የጠ/ሚ አብይ ነፃ ምርጫ ፍላጎት

በቅርብ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ለምሁራን ባደረጉት ውይይት የነፃ የመድበለ ፓርቲ ምርጫ በሁለት ዓመት ውስጥ ማካሄድ እወዳለሁ ብለዋል። ምሁራኑ ቆሞ አጨበጨበ ተብለናል። እውነትም ነፃ ምርጫ ጥሩ ነው አብዛኞቻችን የምንመኘው ነው። ነገር ግን በቂ ቀድሞ ዝግጅቶች ካልተደረጉ ምርጫው የግጭት መፍትሄ ሳይሆን የግጭት ምንጭ እና ማባባሻ ይሆናል (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_8.html)።

በተለመደው የፖለቲካ «ቴኦሪ» የሀገር ራእይ በህገ መንግስት ይገለጻል። ስለዚህ አንድ አዲስ ሀገር ሲፈጠር (እንደ ኤርትራ 24 ዓመት በፊት) ወይንም ወደ «ዴሞክራሲ» ሲሸጋገር አንድ የሽግግር ውየንም ሽማግሌዎች ቡድን ይቋቋም እና የህዝቡን እና የልሂቃኑን አስተያየት እና ራእይ ይሰበስባል። በዚህ ሂደት መሰረት ህገ መንግስት ይደነገጋል (ወይንም ያለው ይታደሳል)። ህገ መንግስቱ እንደ ሀገሩ ህዝብ የመሃበራዊ ስምምነት ይሰራል። ይህን ተመስርቶ ምርጫ ይቃሄዳል ውጤቱም ይከበራል። ይህ ነው የቴኦሪው አካሄድ።

ግን አብዛኛው ጊዜ እንደዚህ አይሳካም! የቅርብ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ታሪኮች ይመሰክራሉ። ህገ መንግስት ተደንግጎ «ዴሞክራሲ» አልመጣም። ሌላ ጥሩ ምሳሌ የግብጽ ሀገር የቅርብ ታሪክ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_8.html)። ታሪኩ ባጭሩ እንዲህ ነው። ተቃዋሚዎች ለረዥም ዓመታት እርስ በርስ ባለመተማመን እና ባለመስማማት በጦር ስራዊቱ የሚደገፈው የሙባረክ (የሳዳትም) መንግስት በስልጣን ቆየ። ተቃዋሚዎች የማይስማሙበት ምክንያት ህብረተሰቡ የተከፋፈለ ስለሆነ ነው። «ለዘብተኛ» ሙስሊም፤ «አክራሪ» ሙስሊም»፤ ክርስቲያን፤ ሃብታም፤ ደሃ፤ ኮምዩኒስት፤ ነጋዴ እያለ ተከፋፍሏል ክፍፍሉ በፖለቲካ ፓርቲዎች ይንጸባርቃል። ሙባረክም ሲገዛ አንዱን ጎራ ከአንዱ ጎራ እያጣላ ወይንም ባላቸው ጥል እየተጠቀመ ነበር።

ከዓመታት በኋላ በ2003 ተቃዋሚዎቹ ተስማሙና ይህ ስምምነታቸው የህዝብ አብዮትን ለማካሄድ እና ለማሳካት አበቃቸው። የተቃዋሚው ልሂቃን እና ብዙሃን የሙባረክን በጦር ኃይሎች የተመሰረተውን መንግስትን ገለበጠ። ዓለም አጨበጨበ። ተቃዋሚዎች ተሰብስበው ምርጫ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ቀድሞ ስምምነቶች አድርገው ምርጫ አካሄዱ። «ለዘብተኛ/አክራሪ» የሚባለው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አሸነፈ እና በፓርቲዎቹ ስምምነት እና ባለው ህገ መንግስት መሰረት ስራ ጀመረ። ግን ሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሙስሊም ወንድማማቾች አገዛዝን እየተጠራጠሩ እየተቃወሙ መጡ። ወደ የከረረ እና የማይፈታ ግጭት ገቡ። መጨረሻ ላይ እነዚህ ፓርቲዎች እና ተከታዮቻቸው ይህ የሙስሊም ወንድማማቾች መንግስት ከሙባረክ መንግስት አይሻለንም ብለው ደመደሙ። መጀመርያ ላይ የገለበጡት ጦር ኃይልን እባካችሁ ተሳስተን ነበር ይህን መንግስት ገልብጡልን ብለው ጠየቋቸው። «ዴሞክራሲ» በግብጽ አበቃ። ዛሬ የግብጽ ጦር ኃይሎት ተመልሰው የአምባገነን ስርአት መስርተዋል።

ይህ ታሪክ የሚያስተምረን ሁለት ነበር ነው። 1) «ዴሞክራሲ» እና «ምርጫ» በራሱ ፍቱን አይደለም በሀገሩ ራእይ ቀድሞ መስማማት ያስፈልጋል። 2) የሀገሩን ራአይ የሚገልጽ ህገ መንግስት ወይንም ሌላ ቀድሞ ስምምነት ቢራቀቅም የልብ ስምምነት ከሌለ በወረቀት የተጻፈ ዋጋ የለውም። ለምን ብነል ይህን ስምምነት የሚያስከብር የበላይ ኃይል የለም። ሀገ መንግስቱን በግድ አክብሩ የሚል የዓለም የበላይ መንግስት የለም! ከስምምነቱ በኋላ የልብ ስምምነት ባለመኖሩ አንዱ የስምምነቱ (ግዙፍ) አካል ሌቀዳደው ከፈለገ ምንም ማድረግ አይቻልም። ስምምነቱ የሚደነገገው ሁሉም የተስማሙበትን እንዲያቁ ነው እንጂ በግድ ለማስከበር አይደለም።

ይህን ሁሉ ተገንዝበን ጠ/ሚ አብይ ነፃ ምርጫ ላማካሄድ መጀመርያ ሀገር አቅፍ ራእይ እንዲመሰረት ማድረግ አለባቸው። ቴኦሪው እንደሚለው የተለያዩ ህዝብ ወቃዮችን ሰብሰበው ስለ ህገ መንግስቱ እና ምርጫው አካሄድ ስምምነት እንዲኖር ማድረግ አለባቸው። የልብ ስምምነት እንዲኖር ማድረግ አለባቸው። ልድገመው፤ የልብ ስምምነት ማድረግ አለባቸው። ይህን በተወሰነ ወራት ማድረግ ይችላሉ ወይ ነው ጥያቄው።

አንዱ ትልቅ እንቅፋት የሚመስለኝ በአሁኑ ኢትዮጵያ በቂ ህዝብን የሚወክል ተቋማት የሉም። ተቃዋሚ ፓርቲዎች እጅግ ደካማ ናቸው። ማንን እንደሚወክሉ እነሱም እኛም ለማወቅ ይከብደናል። አቅምም መዋቅርም የላቸውም። ተከፋፍለዋልም። በተጨማሪ ሁለቱ ትልቅ የፖለቲካ ጎራዎች የኢትዮጵያ ብሄርተኞች እና የጎሳ ብሄርተኞች የተራራቁ ናቸው። እንኳን እርስ ብሰር ውስጣቸውም አይስማሙም አንድ ሀገራዊ ራእይ የላቸውም።

በኔ እየታ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ስራ ይጠበቃል። ተቃዋሚዎች መጎልበት አለባቸው። ምናልባት 1500 ፊርማ ፋንታ 100,000 ፊርማ ነው የሚያስፈልፈው እንደ ተቃዋሚ ለመመዝበብ ማለት ያስፈልግ ይሆናል በግድ ትብብረና አቅም ለማጎልበት። ምናልባት ከመንግስት የተወሰነ ድጎማ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ዋናው ግን የመወያያ መድረክ እና ጊዜ፤ በተለይም ጊዜ፤ ያስፈልጋቸዋል። ምናልባት መጀመርያ የከተማ እና የክልል ምርጫዎች እንደ ሙከራ ማካሄድ ያስፈልግ ይሆናል። እንደዚህ አይነት ብዙ ነገሮች መታሰብ አለባቸው። ይህን ሁሉ ስል ደግሞ የኢህአዴግ ውስጣዊ ጉዳይ አለ…።

ስለዚህ ነፃ ምርጫ ሁላችንም የምንፈልገው ነገር ቢሆንም እዛ ለመድረስ ሂደቱ ትልቅ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። ቀድሞ ሁኔታዎች በደምብ በማያሻማ ሁኔታ እስኪሟሉ ምርጫ አለማካሄድ ነው የሚመረጠው። ዋናው ነበር ምርጫው ሳይሆን የህዝብ ለህዝብ በሀገራችን ራእይ ያለ ስምምነት ነው። ያንን ስምምነት በትክክሉ ገደረስንመት ሌላው ሁሉ በቀላሉ ይሳካል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!