Friday 13 July 2018

በረከት ስምዖን ይዙር!

በረከት ስምዖን አማራ ክልልን እየዞረ ገንዘብ እያደለም ድጋፍ እየሰበሰበ ነው ይባላል? ታድያ ምን አለ ይህን ቢአደርግ። ምንድነው የምንፈራ። ሰዎቻችንን ይገዛል ብለን ነው? ያሳምናል ብለን ነው?

በረከት በገንዘብ እና ሀሳብ የራሳችንን ሰዎች ከገዛ ካሳመነ ይህ ስለኛ ምን ይነግረናል። ምን አይነት ህዝብ ነን ማለት ነው? በገንዘብ እና ውሸት የምንገዛ ህዝብ ነን? እንዲህ ከሆነ ደግሞ መሰረታዊ እና መታረም ያለው ችግር የበረከት መዞር ነው ወይንም የኛ በገንዘብ እና በ ውሸት መገዛት ነው? 

ግልጽ ነው፤ ችግሩ እኛ ነን መፍትሄው እራሳችንን ማስተካከል ነው። አለበለዛ የኛ ህዝብ በገንዘብ እና ውሸት ሀሳብ ስለሚገዛ በረከትን እናባረው ከሆነ መሰረታዊ ችግራችንን አንፈታም። በርከት ቢጠፋ ሌላ ደግሞ ይመጣል። ሌላ ተቃዋሚ፤ ሌላ የ«አማራ ጠላት»፤ ሌላ ሽብርተኛ ወዘተ። የራሳችንን ችግር ካልፈታን ለአደጋ እና ክህደት ሁልጊዜ የተጋለጥን እንሆናለው። ልድገመው፤ የራሳችንን ችግር ካልፈታን ለአደጋ እና ክህደት ሁልጊዜ የተጋለጥን እንሆናለው።

ለኔ ስለ በረከት ዙረት መቸገር እጅግ እጅግ አሳፋሪ ነው። አንድ ህዝብ የማይወደው አማራ ነኝ ኤርትራዊ እየዞራ ሊበጠብጣችን ይችላል ማለት እኛ እጅግ ደካማ እና ቀሽም ነን ማለት ነው። ባሁኑ ጊዜ ያውም ሰፃነት የሰፈነበት በረከት ምንም ጡንቻ የሌለበት እንዴት ነው የምንፈራው? ያስንቃል። 

ወንድሞች እህቶች እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ያስንቃል። ያስንቃል። እንደዚህ ነው እነ ህወሓትን ያሞላቀቅናቸው። ትንሽ ሆነው በቀላሉ ሊገዙን እንደሚችሉ ያመኑት ገና አንዳቸውን ስናይ ሊበጠብጠን ነው ብለን ስንሸማቀቅ ሲያዩ ነው። ይህን ውሸት ማድረግ አለብን። በረከት ስምዖን እየዞረ ሰውን እያሳመነ ከሆነ እኛ ያን ሰው አንዳያምን ማድረግ አለብን። የክህደት መንፈስ፤ የመታለል መንፈስ፤ የመገዛት መንፈስ ከኛ እንዲጠፋ ማድረግ አለብን።

ድሮ ኩሩ ህዝቦች ነበርን። አንድ ሽፍታ ያጠፋናል ብለን አንፈራም ነበር። በራሳችን በራሳችን ህዝብ እንኮራ እንተማመን ነበር። አንድ ወቅት ግን እርስ በርስ መፈጃጀት ስንጀምር በራሳችን መተማመኑን ያቆምን ይመስለኛል። ከዛ ወዲህ በአንድ ክፍል ውስጥ 100 ሆነን ተግኝነት አንድ «ጠላት» ከመጣ ያንን አንድ ጠላት እንደ 100 ሃይል መፍራት ጀመርን። ይህን አስተሳሰብ ካልቀየርን ኢትዮጵያም አማራም አዲዮስ። በተዘዋዋሪ ለዚህ ነው እነ ሻ'ዕብያ እና ወያኔ አንዳችን የ10 አማራ ዋጋ አለው የሚሉት። ትንሽ ሆነን እናሸማቅቃቸዋለን የሚሉት።

ስለዚህ በረከት ስምዖን ይዙር። ከተማ ለከተማ ይዙር ጉቦ ይስጥ ወሬውን ያውራ። መብቱ ነው። እኛ ለህልውናችን ግዴታ የሆነውን ራሳችንን እናስተካክል እናስተምር አንድነት እናምጣ። ልድገመው፤ አንድነት እናምጣ። አንድ ከሆንን እንደ ብረከት አይነቱ 10,000 ሆነውም እየዞሩ ጉቦዋቸውን ቢያድሉ ዋጋ አይኖረውም። ይህ አይነት አንድነት ከሌለን ለዘላለም በቀላሉ የምንሸነፍ ሰዎች ነው የምንሆነው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!