Thursday, 8 September 2016

ሙባረክና መለስ

2008/13/2 ዓ.ም. (2016/9/7)

ስልጣን ላይ በነበሩበት ግዜ ፕሬዘዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከሃይማኖት ጋር ያልተያያዙ (“secular/liberal”) የግብጽ የዴሞክራሲ ተቀናቃኞችንና ደጋፊዎቻቸውን ለማስፈራራትም ለመተንኮስም «እኔ ከስልጣን ብወርድ የሙስሊም አክራሪዎቹ ይገዟችኋል፤ የምትጠሉትን የሙስሊም ሃይማኖት አገዛዝ የሸሪያ ህግንም ይጭኑባችኋል» ይሏቸው ነበር። ከዛ ደግሞ ወደ ሙስሊም ወንድማማቾች የሚባሉት ትንሽ «ከረር» ያሉ የሙስሊም ፖለቲካ ፓርቲና ደጋፊዎቹ ፕሬዘዳንት ሆስኒ ዞር ብለው «እኔ ባልገዛ ኖሮ እነዚህ ሃይማኖታችሁን የማያከብሩ፤ ሃይማኖት የሌላቸውና ክርስቲያኖች ይገዟችሁ ነበር» ይሏቸው ነበር! ሁለቱም ሙባረክን የሚጠሉትና ዴሞክራሲ እንፈልጋለን ባይ የሆኑት ከሃይማኖት ውጭ ዴሞክራሲ ተቀናቃኞችና የሙስሊም ወንድማማቾች ተፈራርተው አንዱ ሌላው ስልጣን እንዳይዝ ብለው ሙባረክ በስልጣን ላይ እንዲቆይ ፈቀዱ።

ሆኖም ግን አንድ ቀን ሁለቱ የዴሞክራሲ ተቀናቃኝ ጎራዎች በአምባገነኑ ሙባረክ መገዛት በቃን አሉ። ፕሬዘዳንት ሆስኒ ሙባረክን ከስልጣን ለማውረድ ተባበሩ። የሁለቱ ድጋፍ ተደምሮ የሙባረክ መንግስት ከነበረው ድጋፍ እጅግ ከፍተኛ ስለነበር በ2011 እ.ኤ.አ. ወደ 1000 አካባቢ ሰው በሞተለት «የአረብ ፀደይ» ተብሎ በተሰየመው ዓብዮት የሙባረክን መንግስት ገለበጡ። የምዕራብ ዓለም ሚዲያዎች በሙሉ አጨበጨቡ።

የሙባረክ መንግስት ከወረደ በኋላ አዲሲቷ ግብጽ ምን መምሰል አለባት በሚለው ጉዳይ በርካታ ፓርቲዎች ተወያዩ ተስማሙና  አገሪቷንም ለነፃ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አበቋት። ምርጫውን የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ በትንሽ ልዩነት አሸነፈ። የቀሩት የፓርላማ መቀምጫዎች በሌሎቹ በበርካታ የዴሞክራሲ ተቀነቃኝ ፓርቲዎች ተያዙ።

ልክ የሙልሲም ወንድማማቾች ስልጣን ከያዘ በኋላ ችግሮች መታየት ጀመሩ። በመጀመርያው ሌሎቹ ፓርቲዎች የሙስሊም ወንድማማቾች ከሃምሳ በመቶ በላይ ድምጽ አገኝቶ ሙሉ ስልጣን ማግኘቱን ቅር ብሏቸው ነበር። ከዛም ቀጥሎ የሙስሊም ወንድማማቾች መሪ መሃመድ ሞርሲ የፓርቲያቸውን ኃይል የሚያጠነክርና ቀስ ብሎ የሸሪያ ህግ ለማምጣት የሚያመቹ እርምጃዎች መውሰድ ጀመረ። እርግጥ አላማቸው የሸሪያ ህግ ላይሆን ይችል ነበር፤ ነገር ግን የሌሎቹ የፖሊቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ጥርጣሬ ይህ ነበር። በተጨማሪም የሙስሊም ወንድማማቾች ቀስ በቀስ ስልጣኑን እየጨመረ እራሱን ሰዎች በየቦታው እየሾመ የሌሎችን ስልጣን እየሸረሸረ ነበር።

በግብጽ ከሃይማኖት ነጻ የሆኑት ፓርቲዎችና እንደ የሙስሊም ወንድማማቾች አይነት የሃይማኖት ፓርቲዎች መካከል ያለው ጥርጣሬና ጥላቻ እንደገና መታየት ተጀመረ። ሙባረክን ለመጣል ብቻ ነበር የተስማሙት እንጂ ከዛ በኋላ ለሚመጣው የግብጽ የፖሊቲካ ሁኔታ ከልባቸው አልነበረም የተስማሙት። የዓመታት ጥርጣሬና አለመስማማታቸውን አላስወገዱም ነበር። በአንድ አገር በሰላምና ሁሉንም በሚያስማማ ህግ ስር አብሮ ለመኖር አልተስማሙም ነበር። ትንሽ አለመግባባት ሲመጣ ወዲያው ወደ ድሮው ጥርጣሬና ጥላቻቸው ተመለሱ።

የዚህ ታሪክ የመጨረሻው ክፍል እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ነው። አስተማሪም ነው። ከሃይማኖት ነጻ የሆኑት ፓርቲዎች ሁለተኛ አቢዮት አስነሱ። ሙባረክን በስልጣን ላይ ያቆየውን ኃይል የግብጽ ጦር ሰራዊትን የሞርሲን መንግስት እንዲገለብጡ ለመኑ! የሞርሲ መንግስት በዴሞክራሲ ከሚገዘን አምባገነኑ ጦር ሰራዊት ይግዛን አሉ! ይህም የመንግስት ግልበጣ ተካሄደና ይባስ ብሎ ሞርሲና በርካታ ባልደረቦቹ ታሰሩ፤ የሞት ፍርድም ተፈረደባቸው!

ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዘናዊም በስልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን ህወሓት ወክለው ደጋግመው አማራውን «እኛ ከስልጣን ብንወርድ ኦሮሞ ብሄርተኛው ያርዳችኋል»፤ ኦሮሞውን ደግሞ «እኛ ከስልጣን ብንወርድ ነፍጠኛው አማራ መሬታችሁን ይነጥቅና ባርያ ያደርጋችኋል» እያሉ ይዘፍኑ ነበር። ሁለታችሁ አትስማሙም ልትስማሙም ስለማትችሉ እኛ ህወሓት መግዛት አለብን ይሉ ነበር። ዛሬም በርካታ የህወሓት አክራሪዎች በዚህ አስተሳሰብ እንደተመረዙ ያሉ አሉ።

ሆኖም ይህ የህወሓት ዘፈን የተወሰነ እውነታ እንዳለው እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ማመን አለብን። ችግራችንን ለመፍታት ችግራችንን ማመን አለብን። በአማራና ኦሮሞ ፖለቲከኞች መካከል ብቻ ሳይሆን በስመ ኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ፖሊቲከኞች መካከል እጅግ ከባድና አሳፋሪ ቅራኔ፤ ሽኩቻ፤ አለመተማመንና አለመስማማት አለ። ባለፉት የተወሰኑ ዓመታት ግን እነዚህ ቅራኔዎች እየቀነሱ ሄደዋል። ይህ መሻሻልና ለውጥ አስፈላጊና ለሁላችንም ህልውና ግዴታ ነው።

አንድ ምሳሌ ልስጥ፦ በዛሬ በአማራ ክልል ያለው ንቅናቄ ምክንያት ኢህአዴግ ኦሮምኛን የአዲስ አባባ ቋንቋ አደርጋለሁ ብሎ ጭምጭምታ እያሰማ ነው። ይህ የተለመደው የኢህአዴግ ዘፈን አማራንና ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚሉትን የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን «ኦሮሞ ሊገዛችሁ ነው» በማለት ለማስፈራራት ነው! ህዝቡ ግን ይህ ማስፈራሪያ አሁን አይሰራም፤ ኦሮምኛን ጭራሽ የኢትዮጵያ ሁለተኛ ብሔራዊ ቋንቋ አድርጉት እያለ ነው። ኢህአዴግ ምን ይበጀው ይሆን!

ይህ ምናልባት ህልም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ህልም በተግባር እንዲውል የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ነን የምንለው ወገን ታላቅ ሃላፊነት አለብን። የኛ የፖለቲካ ጎራ በመጀመሪያ እርስ በርሳችን አንድ ሆነን ሽኩቻን አስወግደን ጠንካራ ሆነን ከዛም በዚህ ጉዳይ ላይ መስራት አለበን፤ ከኦሮሞ ፖለቲካ ወገን ጋር በደምብ ስምምነት ላይ ባስቸኳይ መድረስ አለብን። እንደ ግብጽ አገር በመጨረሻ ደቂቃ እንስማማ ማለት ውድቀትን መጋበዝ ይሆናልና።



No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!