Showing posts with label የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን. Show all posts
Showing posts with label የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን. Show all posts

Friday, 16 March 2018

ቤተክርስቲያን የፈውስ ቦታ ናት

«ወደ ቤተክርስቲያን ግባ እና ከኃጢአትህ ታጠብ። ቤተክርስቲያን የፈውስ ቦታ እንጂ የዳኛ ፍርድ ቤት አይደለችም እና። ወደ ቤተክርስቲያን በመግባትህ አትፈር። ኃጢአት ሰርተህ ንሰሐ ባለመግባትህ ግን እፈር።»

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

Thursday, 15 February 2018

ቤተ ክርስቲያን መቅደም አለባት!

ከትላንት ወድያ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙርያ ያልጠበቅናቸው መልካም አሳቢዎች እንደ ለማ መገርሳና አቢይ አህመድ ብቅ ማለት ጀመሩ። ትላንትና መንግስት ለረዥም ዓመታት የሚለመነውን ነገር አደረገ፤ ያለጥፋት የታሰሩትንና የተሰቃዩትን በርካታ እስረኞችን ፈታ። ዛሬ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃደኝነታቸው ስልጣናቸውን ከቀቁ። መልካ ለውጦች ይታያሉ፤ እግዚአብሔር መጨረሻውን ያሳምርልን።

ግን ከፖለቲካው ቤተ ክርስቲያናችን መቅደም አልነበረበትም? (ይህን ስል እኔም እንደ አንድ ምእመናን እራሴን እየወቀስኩኝ ነው።) የኛ ለማ መገርሳዎች፤ በትህትና አለመፍረድ፤ በፍቅርና በምሳሌ፤ የሚናገሩት የት አሉ? እርግጥ አሉ፤ ግን በሌሎቻችን ተከበው ድምጻቸው በአግባቡ አይሰማም። እስረኞችንን መቼ ነው የምንፈታው? በርካታ እስረኞች አሉን፤ ፍቅር፤ ሃላፊነት፤ እርቅ፤ ትህትና፤ ሰላም። እነዚህንንሁሉ አስረን ቁጭ ብለናል። መቼ ነው የምንፈታቸው? ደግሞ መቼ ነው ሃላፊነት ወስደን እራሳችንን ህዝብ ፊት ዝቅ የምናደርገው። እንዲህ የሚያደርጉ አሉ ግን በኔ አይነቱ ተከበው አይታዩም። እንቅፋትም ሆነናቸዋል።

ቤተ ክርስቲያናችን እንደ አቡነ ጴጥሮስ መምራት መጀመር አለባት። በፖለቲካው መመራት ወይም መቀደም እፍረት ነው። አሁን ከቤተ ክርስቲያን እርቅ በፊት በሃገራችን ፖለቲካ እርቅ ቢመጣ ታላቅ እፍረት አይደለም? ከዛ በሗላ መጀመሪያውኑ ፖለቲካ ነው ያስቸገረን ብለን ልናሳብብ ነው? እነ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮሜ ፖለቲካ እየተሰውዉ ደፍሮ ያላሉትን ልንል ነው?! ይህ ቢሆን እጅግ አሳሳዛኝ ነው።

ስለዚህ እንምራ! በሃገር ውስጥና በውጭ ያሉት ስይኖዶስ መካከል ፈጥነን እርቅ እናምጣ። ለኢትዮጵያ ህዝብ ምሳሌ እንሁን። ፈተናው ብዙ ነው። ገና እየበዛ ይሄዳል። ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ በሁሉም ቦታ ከኛ ጋር ነው። ይህን ካመንን ለፍቅር እንድፈር፤ አንፍራ!

Sunday, 11 December 2016

ተሃድሶ

ስለ «ተሃድሶ ኦርቶዶክስ» የሚባለውን ንቅናቄ አንዳንድ ሃሳቦች ለማቅረብ እወደለሁ። በመጀመርያ ትሃድሶ በትክክል ምን እንደሆነ አይታወቅም። በጾም ጊዜ አሳ መብላት አግባብ ነው የሚሉ ተሃድሶ ተብለው ሊሰየሙ ይችላሉ። እንደ ፒያኖ ወይም ኦርጋን አይነት የሙዚቃ መሳርያ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ መተቀም ይቻላል የሚሉም እንደዚሁ ተሃድሶ ተብለው ይሰየማሉ። ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጫማ ማድረግ ክልክል አይደለም የሚሉትም እንደዚሁ። በድንግል ማርያም አማላጅነት አምነው ግን በስብከታቸው ስለሷ ብዙ የማይናገሩ ተሃድሶ ይባላሉ። ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደ ክርስቶስ የሚያመልኩ አሉና ይህ መሆን የለበትም የሚሉም ሳይገባ ተሃድሶ ይባላሉ። የጋራ ጾም አያስፈልጉም የሚሉም ተሃድሶ ይባላሉ። በቅዱሳን አማላጅነት አናምንም የሚሉም ተሃድሶ ይባላሉ። ወዘተ። «ተሃድሶ» የሚባለው ስያሜ በተለያዩ አግባብ ያላቸውም የሌላቸውም ምክንያቶች እንጠቀማለን።

ከዚህ ጽሁፍ ግን ተሃድሶ ስል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትንም ስርዓትንም መቀየር - በትንሹም በትልቁም - የሚፈልግ አቋምን ነው። ጫማ ከቤተ ክርስቲያን እናድረግ እስከ የቅዱሳን አማላጅነት የለም የሚሉት። እነዚህ እጅግ የተለያዩ አቋሞች እንደሆኑ እራዳለሁ! ጫማ አለማድረግ የ«ትንሽ» ስረዓት ጉዳይ ነው - የእምነት ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ከግብጽ በተ ክርስቲያን ጋር እንለያይ ነበር። ትንሽ ስረዓት ቢሆንም ምክነያት አለው - ይህን ስርዓት ለመቀየር የሚጓጓው መንፈስ በቅዱሳን አማላጅነት አላምንም ከሚለው መንፈስ በተወሰነ ደረጃ ግንኙነት አለው። ላስረዳ...

የኦርቶዶክስ ክርስቲያን እምነት በሶስት መስፈርቶች ሊፈተሽ ይችላል። እምነቱ ከጥንት ጅምሮ ያለ ነው፤ እምነቱ በሁሉም ቦታ ይገኝ ነበር፤ እምነቱ በሁሉም ይታመን ነበር። እነዚህ መስፈርቶች ከክርስቶስ ቀጥሎ ከሃዋሪያቶቹ የወረስነውን እምነት አለማጠፍም አለ«ማደስ»ም ከመንፈቅ ትቆጥበን እምነታችንን እንደተሰጠን ይዘን እንድንጠብቅ የሚገልጹ ናቸው።

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሃሳብ እንደዚህ ነው። አዲስ ነገርን - ትንሽም ትልቅም - በቀላሉ አታስተናግድም። ቅዱስ አታናሲዮስ መጽሃፍ ቅዱስ የትኞቹን መጸሃፍት እንደሚያካትት ሲናገሩ አዲስ ነገር ነበር። መጸሃፍ ቅዱስ እነዚህ መጸሃፍቶች ናቸው ተብሎ ተሰይሞ አያውቅም ነበር። ታድያ ይህ አዲስ ነገር ነበር ወይ? በፍጹም፤ ቅዱስ አታናሲዮስ የነበረ ሁሉም በሁሉም ቦታ ከመጀመርያ የሚያምኑበትን ነው ያረጋገጡት። ሌሎች መጸሃፍቶችን የተተውበት ምክንያትም የቤተ ክርስቲያን እረኞች ህዝቡ እነዚህን መጸሃፍት በተሳሳተ መልኩ እያነበበ ወደ ኑፋቄ ሲገባ አይተው ነው።

የቤተ ክርስቲያን ስረዓትም በተመሳሳይ ቢጠበቅም ትንሽ ላላ ይላል። ስረዓትን «ታናሽ»ና «ታላቅ» ብለን መከፋፈል ይቻላል ግን ይህ ቅፍፍል ወጥ አይደለም - ታናሽና ታላቅ ዳሮች ሆነው ከመካከል ብዙ አሉ። ታናሽ ስረዓቶች ለምሳሌ ጫማ አለማድረግ፤ ታቦት፤ ወዘተ ከኛ ጋር አንድ ከሆነችው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የሉም። እነሱም የራሳቸው እኛ የሌለን ስርዓቶች አሏቸው። ሆኖም ስረዓትም በቀላሉ አይቀየረም። እንደ እምነት ያህል ባይሆንም ከእምነቱ ጋር እጅግ የተያያዘ ስለሆነ መቀየሩ እጅግ አስፈላጊ መሆን አለበት።

ለምሳሌ የቅዳሴአችን ዜማ የተጻፈው በ6ኛው ክፍለ ዘመን በቅዱስ ያሬድ ነው። ከዛ በፊት የነበረው ዜማ የተለየ ነበር ወይም ዜማ አልነበረም። የቅዳሴ ዜማ የስረዓት ለውጥ በቅዱስ ያሬድ ጊዜ ተካሄደ። ይህ የሚያሳየው ስርዓት መቀየር እንደሚቻል ነው። ግን ከዛ በኋላ እስካሁን ለ15 ክፍለ ዘመን አልተቀየረም። ይህ ደግሞ የሚያሳየው ስረዓት መቀየር ቢቻልም (እንደ ስረዓቱ አይነት) እጅግ በጣም ጥቂት ጊዜ ነው የሚቀየረው። የኦርቶዶክስ አስተሳሰብ ለውጥ ስለማይወድና ጥንቱን ስለሚያስቀድም።

ስረዓት ይቀየር ሲባል ለምን ብለን እራሳችንን መጠየቅ አለብን። ኦርቶዶክሳዊ ለውጥ የሚከላከለው አንዱ ታላቅ ምክነያት አብዛኛው ጊዜ ለውጥ የሚፈለገው ለማይሆን ምክነያት ስለሆነ ነው። እንደዚህ አይነት ምክነያቶች ምሳሌዎች እንደ የመንፈቅ አስተሳሰብ፤ ፖለቲካ ወይም የስልጣን ሹኩቻ፤ ፍርሃት አይነቱ ናቸው።

በዛሬው ዘመን - «ዘመናዊነት» ግዥ ርዕዮተ ዓለም በሆነበት ዘመን - የስረዓት ለውጥ (የእምነትም ለውጥ) የሚገፋፋው ከዘመኑ ጋር አብሮ ለመሄድ ነው። ቅዱስ ያሬድን ያነሳሳቸው ጾም ጸሎትና የዳዊት መዝሙርን በመድገም እግዚአብሔርን ይበልጥ ለማመስገን ፈልገው ነው። በዛሬው ዘመን ግን ብንወድም ባንወድም ብናውቀውም ባናውቀም ከዘመኑ ጋር አብሮ የመሄድ ሃሳብ ተጽእኖ ያሳድርብናል ሳናውቀውም ይገፋፋናል። በዚህ ምክነያት ከበፊት ዘመናት - ከቅዱስ ያሬድም - ይበልት ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ምንም አይነት ስርዓትን እንኳን ለመቀየር በጥያቄ ምልክት ውስጥም ማድረግ የለብንም።

ብለላው ቋንቋ እላይ የጠቀኩትን የቤተ ክርስቲያናችንን አስተሳሰብን መርሳት የለብንም - ለውጥን በታቻለው ምከላከልንና መፈተሽን።

ይህ ብዬ ወደ ተሃድሶ እንመለስ። በቤተ ክርስቲያናችን ስንት የሚሰራ ስራ እያለ ለምንድነው ማደስ የሚታሰበው። ንስሃ ገብተናልን? እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን እንድወደዋለን? ያለንን በሙሉ እንሰጠዋለን? በሰው ላይ አንፈርድምን? ገና እንድወድቃለን እንነሳለን መውደቃችን እጅግ ቢበዛም። እረኞቻችን ታድያ ድሮም እንደነበራቸው ዛሬም እንድንነሳና ለክርስቶስ ለመቅረብ ያለንን ፍላጎት ለማዳበር ብዙ ስራ አላቸው። ይህ ሁሉ ስራ እያለ ስለማደስ ማሰብ ምን አስፈለገ?

እንዳልኩት የዘመኑ ርዕዮተ አለም በፍጹም ሳናውቀው ከባድ ተእጽኖ ያደርግብናል። ካቶሊኩንና ፕሮቴስታንቱን እያየን ሳናውቀው በአፋችን እንደተሳሳቱ እየተናገርንም በልባችን አንዳንድ ነገሮቻቸው በነበር ብለን እንመኛለን። ስነ ስረዓት፤ ንጽህና፤ ፍልስፍና፤ ሃብት፤ ብልጠት፤ ስነ መግባር ወዘተ። ቤተ ክርስቲያናችን ትታደስ ስንልም እንደነዚህ ትንሽ ትሁን ማለታችን ነው። ምንጩ ይህ ነው አደጋውም ይህ ነው።

ታድያ እንደዚህ ስንል ሌላው አብዛኞቻችን በተለይ ካህናቶቻችን በተለይ እናድስ የሚሉት የማናውቀው ነገር ምህ ያህል ካቶሊኩና ፕሮቴስታንቱ - በተለይ ፕሮቴስታንቱ - ችግር ውስጥ እንዳለ ነው። «ፔንጤ» የምንላቸው በትክክሉ «ኤቫንጄሊካል» የሚባሉት ለምሳሌ ባለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያድጉም ባሁኑ ጊዜ በምንጫቸው ሃገር አሜሪካ እየመነመኑና ታላቅ አደጋ ላይ ናቸው። መሰረታው እምነታቸው የግል ስለሆነ - ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ግለ ሰብ ነው ሃይማኖቱን ብቻውን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እይሚያውቀው ብለው ስለተነሱ - አሁን እስከ 30,000 አይነት ክፍፍሎች አላቸው። ስንቶቻችን ነን ይህን የምናውቀው። የቆዩት ፕሮቴስታንቶች (በኢንግሊዘኛ «ሜይንላይን» ይባላሉ) እንደ አንግሊካን ደግሞ ከሁሉም ክርስቲያን ከሚባሉት የመነመኑና ምእመናን ያጡ ናቸው። ይህን ስንቶቻችን ነው የምናውቀው? አሜሪካን ሀገር ትልቁ የክርስቲያን ፍልሰት ከፕሮቴስታንት ወደ ኦርቶዶክስ እንደሆነ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው? ባንዳን የኦርቶዶክስ ሃገረ ስክበቶች አብዛኛ ካህናት ከፕሮቴስታንትነት ውደ ኦርቶዶክስ የተቀየሩ እንደሆነ ስንቶቻችን እናውቃለን? ኦርቶዶክእነሱ ወደ ኦርቶዶክስ ይመጣሉ እኛ ደግሞ ወደነሱ መሄ እንፈልጋለን!

ክሃገራችን ውጭ ብንመለከት ይበጀናል። ውጭ ሃገር ያለነው - በተለይ ካህናት - ስራችን ብለን ዙርያችን እንመልከት። የክርስትና ድርጅቶች አካሄድን እንመልከት። ዛሬ ከምንጩ አሜሪካ እየጠፋ ያለው ፕሮቴስታንት ሃይማኖት ነገ ኢትዮጵያ በዚሁኑ ምክነያት እንደሚጠፋ እንወቅ። ባለፉት ዓመታት በሃገራችን የተከናወነው የኦርቶዶክስ ወደ ጴንጤ ፍልስትን ብቻ አንይ። ሃገራችን ውስጥ እራሱ እነዚህ ድጅጅቶች እንዴት ቀንበቀን እየተፈረካከሱ እንደሆነና እየተባዙ እንደሆነ እንይ።

ምን አልባት ዞር ዞር ብለን ይህን ሁሉ ካየን የፕሮቴስታንት አደጋም የዘመኑ ፈተናንም ልንረዳው እንችላለን። ይህን ተረዳነው ማለት ደግሞ እንታደስ የሚለው ስሜት ይቀንስልናል። አስተያየታችንን ያስተካክላል ሚዛናዊም ያደርጋል።

Tuesday, 8 November 2016

የሲኖዶሱ ጉዳይ በ2009

2009/2/29 .. (2016/11/8)

(pdf)

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን ሁለት የተወጋገዙ ሲኖዶሶች አላት፤ በኢትዮጵያ ያለው ሲኖዶስና ስደተኛው ሲኖዶስ። ይህ ሁኔታ የተፈጠረው ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ የቤተ ክርስቲያናችን ፓትሪያርክ አቡነ መርቆርዮስ በመሰደዳቸው ነው። ስለ መሰደዳቸው ሁኔታ በዛን ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ከመንበር እንዲወርዱ ያዘዝኩት እኔ ነኝ ብለው እንደመሰከሩ ይታወሳል። ምንም ቢሆን በአቡነ መርቆርዮስ መሰደድና በአቡነ ጳውሎስ መሾም መካከል ጳጳሳቱ የመንግስት ጫና አድሮባቸው እንደነበረ ግልጽ ነው። ሆኖም መንግስት በቤተ ክርስቲያን ላይ ጫና ሲያደርግ ይህ የመጀመርያ ጊዜ አልነበረም። በደርግ ጊዜም እንዲሁ ነበር፤ በኃይለ ሥላሴም፤ ከዛም በፊትም በነግስታቱ ዘመን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጳጳሳቶችዋ ይህ ፈተና ሁልጊዜ ዪደርስባቸው ነበር። ሆኖም የዛሬው ክፍፍል ምንጭ ይሄው የመንግስት ጫና በሲኖዶሱ ላይ በመሆኑ ነው።

ታድያ መፍትሄው ምንድነው? እንደሚታወሰው በሲኖዶሶቹ መካከል እርቅ ለማምጣት በተለያየ ጊዜ ግለሰቦችም፤ ሽማግሌዎችም፤ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ሃላፊዎች ሞክረዋል። አንዳንዱም ሙከራ ጥሩና ያልተጠበቀ የማቀራረብ ውጤቶችን አሳይተዋል። ግን እስካሁን ጉዳዩ አልተቋጨም።

በዚህ ጽሁፍ የጉዳዩን ጠቅላላ ይዞታ አልተችም፤ ጉዳዩና የእርቅ ስራው እጅግ ከባድና ውስብስብ ናቸውና። በዚህ ጽሁፍ ከጉዳዩ አንዱን ንብርብር ለመላጥ ነው የምሞክረው፤ ይህ ደግሞ ሲኖዶስ ሊሰደድ ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ ነው።

ይህን ጉዳይ ለዘብ ባለ መንገድ ከታየ ስምምነት ላይ እንደሚደረስና ችግሩም መፍትሄ አንደሚያገኝ እርግጠኛ ነኝ። ነገር ግን አክራሪ አስተያየቶች ናቸው የሰፈኑት። እነዚህ «ሲኖዶስ ሊሰደድ አይችልም» እና «መንግስት ሲኖዶስ ላይ ጫና ካደረገ ፓትሪያርኩ ግድ መሰደድ አለባቸው ስለዚህ ሲኖዶሱ ውጭ ይሆናል ማለት ነው» የሚሉት ናቸው።

በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በማንም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ሲኖዶስ መንቀሳቀስ አይችልም የሚል ህግ የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ጣልያን ኢትዮጵያን ወርራ ከአንድ በስተቀር ጳጳሳቱን በሙሉ ረሽና ቢሆን እኚህ አንድ የቀሩት ጳጳስ ተሰደው ቤተ ክርስቲያኑን ካሉበት ቢመሩ ህገ ወጥ ነው? በፍጹም። ግን ዋናው ጥያቄ ህገ ወጥ ነው ወይ ሳይሆን ክርስቲያናዊ አይደለም ወይ? ቤተ ክርስቲያን በዚህ መንገድ እራስዋን ማዳንና በጎቿን መጠበቅ አለባት። አንዳንድ ሁኔታ መሰደድን ያስገድዳልም ይመክራልም።

እነዚህ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ አስቀድሞ አይታወቅም፤ ጊዜው ሲደርስ ሁኔታው ተጠንቶ ነው መወሰን የሚቻለው። ለዚህም ነው ከላይ ስለ ሲኖዶስ መሰደድ ቤተ ክርስቲያናዊ ህግ ሊኖር አይችልም ያልኩት። እንደ ሁኔታው፣ እንደ አደገኛነቱና እንደ አስፈላጊነቱ ውሳኔው ይለያያል።

ለዚህ እውነታ ጥሩ ምሳሌው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ በ1910 በሩሲያ ኮምዩኒስት አብዮት ምክንያት መሰደዱ ነው። የሶቪዬት ኮምዩኒስት መንግስት በቤተ ክርስቲያንዋ ላይ ያደረሰው ጥቃት እጅግ ከባድ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ካህናትና አማኞች በህሊናም ቢሆን ለማሰብ ያስቸግራል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ያህል ካህናት ናቸው በተለያየ መንገድ የተገደሉት። ሌሎቹ በሞት እስር ቤቶች ታሰሩና አብዛኞቻቸው ሞቱ።

በዚህ ሁኔታ በ1913 የሩሲያ ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ ቅዱስ ቲኾን ቤተ ክርስቲያንዋ ታላቅ ችግር ላይ መሆንዋንና የሶቪዬት መንግስት ካህናት እየገደሉ የራሱን ካድሬዎች ካህን አድርጎ ወደ ቤተ ክርስቲያን እያስገባ እንደሆነ ተገንዝበው በውጭ ያሉት የተሰደዱት ጳጳሳት እራሳቸውን እንዲያስተዳደሩ አዘዙ። ያሉበትን ሁኔታም ለመገምገምና ይህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሶስት አመት ፈጀባቸው። ሲኖዶሱ፣ ማለትም ጳጳሳቱ በመንግስት ቁጥጥር ስር እንደሆኑ ሲያውቁ ነው ፓትሪያርኩ ውጭ ላሉት ጳጳሳት ካሁን ወዲያ በኛ መተማመን አትችሉምና እራችሁን ቻሉ ያሏዋቸው።

ሆኖም የውጩ ፓትሪያርክ ወዲያው አልተሾመም። ፓትሪያርክ ቲኾን ከተሰዉ (አሁን ቅዱስ ቲኾን ናቸው) በኋላና የሩሲያ (ሞስኮብ) ሀገረ ስብከት ከመጠን በላይ የካድሬ ግዛት ሲሆን የውጭ ሲኖዶሱ ፓትሪያርክ ሾመ። ከዛ ቀጥሎ እስከ 1999 የሩሲያ የውጭ ሲኖዶስ (ROCOR) እና የሞስኮብ ሲኖዶስ ተለያይተው እንዲሁም ሲወጋገዙ ቆዩ።

1999 ሁለቱ ሲኖዶሶች ተታረቁ። የውጭ ሲኖዶሱ ከማን ጋር ነው የትታረቀው፤ የሩሲያው ሲኖዶስ በካድሬ የሞላ አልነበረምን ብላችሁ እያሰባችሁ ይሆናል። በሚገርም ሁኔታ ካድሬ ያልሆኑ ታላላቅ አባቶችና መነኮሳት አንገታቸውን ደፍተው ከፖለቲካ ራሳቸውን አርቀው እየሰሩ እየተፈቱ እየተደበቁ የሶቪዬት ኮምዩኒስት ዘመንን ያሳለፉ ነበሩ። አንዳንዶቹ ጭራሽ ራሳቸውን እንደ ካድሬ አስመስለው ሌሎች ወንድሞቻቸው ካህናትን ክጥቃት የመጠበቅ ስራ ይዘው ነበር። አሁንም በሀገራችን ኢትዮጵያ ከጳጳሳቱና ሀገረ ስብከቱ የካድሬ መንፈስ፤ የካድሬ ብቻ ሳይሆን ሲብስ የተራ ሙስናና ሐጥያት መንፈስ፤ ቢኖርም ከዛ መካከል እጅግ ብፁ የሆኑ አገልጋዮች እንዳሉ እናውቃለን። ካድሬ የሚባሉት ውስጥም እንደሁላችንም ከራሳቸው ጋር እየተሟገቱ ንስሀ እየገቡ እየወደ እየተነሱ የሚኖሩ አሉ። በሩሲያም ሲኖዶስ እንዲሁ ስለነበር ነው እርቅ ላይ ሊደርሱ የቻሉት

በተዘዋዋሪ በዚህ በሩሲያ ታሪክ ሌላ አስደናቂ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። በሁለተኛ የአለም ጦርነት ጀርመኖቹ ለተወሰነ ጊዜ ምእራብ የሶቪዬት ህብረትን ተቆጣጥረው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ሀገረ ስብከት የተዘጉትን በሺህ የሚቆጠሩ ቤተ ክርስቲያኖችን እንደገና እንዲከፍት ፈቀዱ። ከግድያ የተረፉት እውነተኛ የሆኑት ካህናት ይህን ነፃነት ተጠቅመን ህዝቡን እናገልግል ወይስ የሀገራችን ወራሪ የሰጠንን ነፃነት ለክርስቶስም ቢሆን ልንጠቀምበት አይገባም በሚለው ጥያቄ ልባቸው ተከፋፍሎ ነበር። ምእመናኑ ሃይማኖቱ እጅግ ጠምቷቸው ስለነበር በርካታ ካህናት ወደ ቤተ ክርስቲያኖቻቸው ተመልሰው አገለገሉ። ጦርነቱ ሲይበቃም የሶቬት መንግስት እንደዚህ አይነት ካህናትን እንደጠበቁት እስር ቤት ላካቸው ወይም ረሸናቸው። (ስለዚህ ታሪክ «ካህኑ» የሚባለውን የሩሲያ ፊልም እንድታዩ እጋብዛችኋለው፤ እጅግ አስተማሪ ነው።)

የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመሰደድ ታሪክ የሚያሳየን የሲኖዶስ መሰደድ ጉዳይ እንደ በርካታ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጉዳዮች «ጥቁርና ነጭ» አይደለም። እንዲህ ቢሆን ይሰደዳል እንዲህ ቢሆን አይሰደድም የሚል አስቀድሞ ሁሉንም ሁኔታ የሚያካትት ህግ የለም። እንደ ሁኔታው ነው ውሳኔ የሚወሰነው።

ታድያ በኢትዮጵያ በ1983 የነበረው ሁኔታ አቡነ መርቆርዮስ የሲኖዶስ መንበራቸውን ይዘው እንዲሰደዱ ያስገድዳቸው ነበር? ይህ ጥያቄ እውነት ወይ ውሸት የለውም፤ እንደ እያንዳንዱ ሰው አመለካከት ነው። አዎን መንግስት በጳጳሳቱ ላይ ጫና እያደረገ ነው ግን ያን ያህል ስላልሆነ መሰደድ አያስገድድም፤ ጳጳሳቱ ጫናውን ሊቋቋሙ ይገባል ማለት ይቻላል። ወይም ጫናው የቤተ ክርስቲያኑን መሰረት አናግቶታልና በነፃነት ምእመናኑን ለማገልገል ሲኖዶሱ ከሀገር ውጭ መሆን ነበረበት ማለት ይቻላል። ሁለቱም አስተያየቶች ያስኬዳሉ።

ከዚህ መማር የምንችለው ታላቅ ትምህርት ሁሉም ነገር እንደ ሃይማኖት ዶግማ ወይም ቀኖና ማየት የለብንም። በነዚህ ታሪኮች አንድ እውነት ብቻ ነው ያለው። ስለሆነም እነዚህን የመሰሉ ችግሮችን እንደ ዶግማ እና ቀኖና እንደ አስፈላጊነቱ የማይሻሻሉ አድርገን ማየት የለብንም። ከሃይማኖታችን መሰረተ ትምህርትና ስርዓት በቀር ሌላውን ጉዳይ በሙሉ በትህትና ነው ማየት ያለብን። አቋሞቻችንንም በትህትና መያዝና ሃሳቦቻችንን መቀየር መቻል አለብን። ጥሩ ክርስቲያን አንድ አምላክ እግዚአብሔርን እንጂ ሃሳቡን፣ የሚከተለውን ርዕዮት አለም፤ ወይንም አቋሙን አያመልክም።

በመጨረሻ አንደ ልጠቅስ የምፈልገው ነገር አለ፤ ሁለቱ ሲኖዶሶቹ ቢታረቁ ለሀገራዊ እርቅ ሰላምና የመንፈሳዊ ደስታና መረጋጋት ታላቅ ድል ይሆናል። በዛሬ ኢትዮጵያ ህዝቡ ያጣው መሪ ነው የሚባለው እውነት ነው። ልጄ ሲያድግ እንደ ከሌ ቢሆንልኝ የሚባል መሪ በየትኛውም በመንግስትም በሃይማኖትም በመሃበራዊም ዘርፍ የለም። ከግዥ መደቡ ጥሩ ምሳሌ የሚባልና የሚደነቅ የለም፤ ጭሽ ህዝቡ ሙስናና ተመሳሳይ መትፎ ስነ መግባር ውስጥ ሲገባ መሪዎቻችንም ያረጉታል ለምን እኛም አናደርገውም እያለ ነው። ስለዚህ እንደ ሲኖዶስ እርቅ አይነቱ ዜና ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቢመጣ ለህዝባችን ታላቅ ምሳሌና ለሀገራዊ እርቅ ታላቅ ድል ነው የሚሆነው። ይህ እርቅን ለማምጣት ደግሞ በሃይማኖታዊም በፖለቲካውም አቅጣጫ ቢታይ ከባድ ያልሆነ ጥቅሙ ከጉዳቱ እጅግ ከፍ ያለ ነግር ነው። ከሌሎች ጉዳዮች ይልቅ ብዙም ከባድ አይደለም። እግዚአብሔር ይህንን እርቅ ለማድረስ ልቦናውን ይስጠን።