Wednesday 21 March 2018

የፖለቲካ ውይይት ስልት፤ «ከጠንካራ ወገኑ ተሟገት»

የኛ የ«ተቃዋሚዎች» የፖለቲካ ችሎታችን፤ ብስለታችን፤ አቅማችን ምን ያህል ደካማ መሆኑን የቅንጅት ታሪክ አጉልቶ ካሳየን 12 ዓመት አልፎታል። አሁንም ደካማ ነን። ብዙኃኑ ንሯል ልሂቃኑ ኋላ ቀርቷል። ምክንያቱ ፖለቲካችንን ለማጠናከር የሚያስፈልጉን ባህሪዎች እንደ መወያየት፤ መተባበር፤ መተማመን፤ መስማማት፤ አብሮ መስራት፤ ቅራኔን መፍታት ወዘተ አሁንም ይጎሉናል። ይህ ጉድለት ነው ለሰላምና ፍትህ ትግላችን ዋና እንቅፋት የሆነው።

ዛሬ በነዚህ ዙርያ አንድ ነጥብ ላይ ማተኮር እወዳለው። ውይይት ሙግት ክርክር የፖለቲካም የማንኛውም የህብረት ስራም መሰረት ነው። የውይይት አንዱ አላማ ሀሳቦችን መፈተንና ማጣራት ነው። የትኛው ትክክል እንደሆነ፤ የትኛው የተሳሳተ እንደሆነ፤ የትኛው ጠቃሚ እንደሆነ፤ የትኛው ተጨማሪ መጠናት እንዳለበት፤ ወዘተ።

ስንወያይ የራሳችን ሀሳብ መናገር ብቻ ከሆነ የምናደርገው እና የሌሎችን ሀሳብ በትክክል የማናዳምጥ ከሆነ ውይይቱ ግቡን እንደማይመታ ግልጽ ነው። እያንዳንዳችን የራሳችን ሀሳብ ብቻ ነው ተቀባይነት የሚገባው ከሆነ ሀሳባችን ሊገመገምና ሊጣራ አይችልም ልንስማማም አንችልም። ሀሳቦቻችን ስላልተገመገሙ ደካማ ይሆናሉ ስላልተስማማን አብረን ደካማ ሆነን እንቀራለን። ስለዚህ ተጠንቅቀን የሌሎችን ሀሳብ ብቻ ሳይሆን አመለካከታቸውንም መረዳት አለብን።

እንደዚህ ለማድረግ የተሟጋቾቻችን ወይም የተቃራኒዎቻችን ሀሳቦች «ጠንካራ ወገንን» መመልከት አለብን። የውይይታችን ዓላማ ማሸነፍ ሳይሆን መገምገምና ማጣራት ስለሆነ። አልፎ ተርፎ የተቃራኒአችን ወይም ተሟጋችን አመለካከትና ሀሳብ ልክ እንደሱ አውቀን መከራከር መቻል አለብን። ከጥንት ዘመን እንደሚባለው ተቃራኒውን ወይም ጠላቱን ያላወቀ ይሸነፋል። ማወቅ ማለት ላይ ላዩን አባባሉን ድርጊቱን ማወቅ ሳይሆን ልከንደሱ ማሰብ ምቻል። ይህን የቻለ ሰው የተቃራኒውን ሀሳብና አቋም ከሱ በተሻለ መንገድ ማሳመን ይችላል! ተቃራኒን በደምብ ማወቅ ማለት ይህ ነው። ከዚህ ብኋላ የተቃራኒውን ሀሳብ በትክክል ሊሟገት ሊያሸንፍ ወይም ሊጠቀምበት ይችላል።

ስለዚህ ጉዳይ ከራሴ አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ። ለረዥም ዓመታት ከ«ጎሰኞች» ጋር ስሟገት የራሴ አቋም እውነት ነው ስነ መግባርና ፍትህ የተሞላ ብቸኛ ሀሳብ ነው ብዬ እነሱን አላዳምጥም ነበር። «ጎሰኝነት ዘረኝነት ነው» እያልኩኝ ከዚህ ሳላልፍ እንደመድም ነበር። ለኔ የሙግቴ አላማ እነሱን የራሴን ሀሳብ ማሳመን ብቻ ነበር። አልሰራም።

አንድ ወቅት ማዳመጥ ጀመኩኝ። እስቲ በነሱ ቦታ ሆኜ ላስበው አልኩኝ። እንደነሱ ሆኜ ከራሴ ጋር መሟገት ጀመርኩኝ። እንደዚህ ሳረግ የነሱ አስተሳሰብ አመጣጥና ሀሳብ እይገባኝ ሄደ። የነሱን አቋም ይዤ መከራከር ቻልኩኝ። ይህ የራሴን አቋም እንዳጠራው ጠቀመኝ። እነሱም እንደማዳምጣቸው ሲረዱ እኔንም ማዳመጥ ጀመሩ። መተማመን ጀመርን እንደ ጥላት መተያየት አቆምን። ብዚህ ምክንያት ጎሰኝነትን አሁን ከድሮ ይልቅ በደምብ እረዳለሁ ማለት እችላለሁ። የጎሰኝነትንም አጉል ወገን እንዴት ማስወገድና ማጥፋት እንደሚቻል ይበልጥ የገባኝ ይመስለኛል።

በተዘዋዋሪ ይህን «ማዳመጥ» ወይም ለሰው መቆርቆርና ራስን በሌላው ቦታ ማድረግ የደረስኩበት ከክርስትና ተልእኮአችን ነው። «አትፍረዱ» «ማሩ» «ራሩ» መሰረታዊ የክርስትና ትምሕርቶች ናቸው። አንዱ ታላቅ ቅዱስ ዮሐንስ «ዘመሰላል» እንደዚህ ብለዋል፤
«አስተዋይ ሰው ወይን ሲበላ የበሰሱትን ይበላል ያልበሰሉትን የሚጎመዝዙትን ይተዋል። እንዲሁም አስተዋይ አዕምሮ በማንድ ሰው የሚያየው (ትንሽም) ጥሩነት ተጠንቅቆ ይመዘግባል። አዕምሮ ቢስ የሆነ ድክመትና መጥፎ ባህሪያትን ይፈልግበታል… ሰው ኃጢአት ሲፈጽም በአይንህም ብታይ አትፍረድ፤ አይኖቻችንም ሊታለሉ ይችላሉና።»
ይህን መንገድ የሚከተል የሌሎችን አስተያየትና አመለካከትን አክብሮ በነሱ ቦቶ እራሱን አስቀምጦ ሁኔታውን ይገመግማል። «አትፍረዱ» «ማሩ» «ራሩ» ማለት እራስን በሌላው ቦታ አድርጎ ማሰብ መቻል ነው!

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!