Showing posts with label ትህትና. Show all posts
Showing posts with label ትህትና. Show all posts

Thursday, 5 April 2018

የአሜሪካ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ይሻላል?

ባለፉት 18 ዓመታት በተለያዩ የአሜሪካ ጦርነቶች ምክንያት ወደ አንድ ሚሊዮን አካባቢ ሰዎች ሞተዋል። በርካታ ሀገሮች ተበጥብጠዋል መንግስታት ተገልብጠዋል ህብረተሰብ ተጎሳቅሏል። ሆኖም በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ምሁራን ልሂቃን ሀገራችን «እንደ አሜሪካ በሆነች» እንላለን።

ይህ አባባላችን ምን ማለት እንደሆነ እንመርምር። በምርመራችን ሂደት ግረ መንገድ ስለ ራሳችን ስለ አቋማችን ማንነታችን አንዳንድ ቁም ነገሮች እንማራለን። ይህ ትምሕርት ለሰላምና ፍትሕ ያለንን ትግል አስፈላጊ ነው ያጠነክረዋልም።

እስቲ ስለ አንድ መጠነኛ የመርካቶ ነጋዴ የሆነ ኢትዮጵያዊ እናስብ። እድሜ ለህዝብ ብዛት ለኤኮኖሚ እድገት ንግዱም ገቢውም እያደገ ነው። ከመንግስትም ከሌላም ወገን እንቅፋቶች ቢያጋጥሙትም እንደ ጓዶቹ ብልህ ነውና ለንግዱ ለንብረቱ ብዙ ስጋት የለውም። ሆኖም አጋጣሚው ሲፈቅድ የተወሰነ ገንዘቡን ወደ ውጭ ሀገር ያወጣል። ኑሮው የተመቸ ቢሆንም ሀገሪቷ የሰላም የፍትሕ የፖለቲካ ችግሮች እንዳሏት ያቃል ያምናል። ግን ቱክረቱ የለት ኑሮው ላይ ነው። እንደማንኛውም ሰው ለኑሮ ይሯሯጣል ጥዋት እስከ ማታ ይሰራል። የሥርዓቱ ተበዳዮች የታሰሩትን የተገደሉትን መሬታቸውን የተቀማባቸውን አንዳንዴ ቢረዳም ብዙ ሊያያቸው አይፈልግም። እንዳሉ ቢያውቅም «ምን ይደረግ በተቻለ ቁጥር ከፖለቲካ መራቅ ነው» ብሎ ይኖራል።

እስቲ አንድ በአሜሪካ ያለ ኢትዮጵያዊ ስደተኛን እንመልከት። አሜሪካ መጥቶ ታግሎ በትምሕርቱ ገፍቶ ጥሩ ገቢና መአረግ ያለው ስራ ከያዘ ቆይቷል። የአሜሪካ «መካከለኛ መደብ» አባል ሆኗል። ባለቤቱም ትሰራለች ቤት መኪኖችም አላቸው ልጆቻቸው ይማራሉ በቅርብ ከፍተኛ ትምሕርትቤት ይገባሉ። ኑሮ ተመችቷቸዋል። አሜሪካ ተመችቷቸዋል። አዎ አንዳንዴ ስለ ዘረኝነት ስለወንጀል ይማረራሉ ግን እነዚህ ነገሮች ሕይወታቸውን አልነኩም። እንደ ፈረንጆች «አሜሪካ ታላቅ ሀገር ናት» ይላሉ። ስለ የኢራቅ ጦርነት ሰለቦች ወይም ሌሎች የአሜሪካ መንግስት ተጎጂዎች ብዙ አያስቡም፤ ምን አገባቸው። የለት ኑሮ በቂ ነው።

ግን ይህ «ኢትዮ-አሜሪካዊ» ኢትዮጵያ የሚኖረውን ነጋዴ ይተቸዋል። «እንዴት ዙርያህ ሰው እየተጭቆነ እየተገደለ እየተበደለ ዝም ዝም ብለህ ትኖራለህ» ይላል! እራሱ ግን  ለአሜሪካ መንግስት የሚሰጠው ቀረጥ ሀገሮችን ለመውረር ህዝብን ለመግደል ሲውል ዝም ይላል። እንቋን አሜሪካን መተቸት «አሜሪካ ጥሩ ሀገር ናት» ይላል። አልፎ ተርፎ «ኢትዮጵያ እንደ አሜሪካ ትሁን» ይላል!

ከዚህ ምንድነው መማር የምንችለው? በመጀመርያ የሰው ልጅ «ሲመቸው» ሲደላው ያለውን ችግር የሀገርም የግለሰብም የባለንጀራውም ችግር አይመለከትም። ለሰው ልጅ ድሎቱ ያሳውረዋል። ይህ እውነታ በፖለቲካ ደረጃ ሲንጸባረቅ ዓለም ዙርያ ይታያል። የቻይና መንግስት ኤኮኖሚውን በማፋጠን ህዝቡን ዝም አሰኛለሁ በሚል መርህ (policy) ነው ላለፉት 35 ዓመታት የሰራው። በኢትዮጵያም ይህ የፖለቲካ መርህ በ«ልማታዊ አስተዳደር» ስም ይራመዳል። ግን በጎሳ ፖለቲካ ሥርዓቱ ምክንያት ህዝቡን ዝም አላሰኘም። ከላይ እንደጠቀስኩት በአሜሪካም ድሎት ህዝቡን የመንግስት ግፎችን እንዳይመለከት ያደርጋል። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ሰላምና ፍትሕ የምንፊልገው ይህን የሰው ባህሪ እና በፖለቲካ ያለውን ሚና አውቀን ነው መርህዎቻችን ስልቶቻችን መወቀር ያለብን።

ሁለተኛው ትምሕርት፤ የኢህአዴግ መንግስት ከሌሎች ያዓለም መንግስታት ተለይቶ «ሴጣን» አለመሆኑ ነው። አዎን መጥፎ መንግስት ነው ለ27 ዓመታት የፈጸመው ግፎች ተመዝግቧል። ሆኖም የኢህአዴግ ማንነትና አሰራር ውስብስብ ነው በቀላሉ «ሴጣን» ነው ማለት እውነቱን አለመገንዘብ ነው። ለዚህም ነው እንደ የ«ለማ ቡደን» አይነቱ ከኢህአዴግ ውስጥ ገብቶ ሰርቶ የደረሰበት ደረጃ የደረሰው። በጭፍን «ሴጣናዊ» መንግስት ቢሆን እንደዚህ አይነት ስራ ሊሰራበት አይችልም ነበር። ግን እንደማንኛውም መንግስት ስልጣን ዋናው አላማ ቢሆንም ለስልጣኑ ለፖለቲካ ህልውናው ያሉት ምርህዎች የሚያካሄደው ስራዎች ለሰላምና ፍትሕ ታጋዮች ከፍተት ፈጥሯል ይፈጥራልም። እነዚህን ክፍተቶች እንዳሉ ተገንዝበን መጠቀም አለብን።

ሶስተኛ ትምሕርት፤ ሀገራችን እንደ ማንም ሀገር «ትሁን» አንበል። አንድ፤ ማንም ፍፁም የለም። ከአሜሪካ እስከ ጀርመን እስከ ኮሪያ ሁሉም የራሳቸው ታሪክ የራሳቸው ችግሮች አሏቸው። ከሌሎች ሀገሮች ጠቃሚ ሃሳቦች መጠቀም አለብን ግን እነዚህ ሃሳቦችን ከኛ መሰረታዊ ማንነት ስር አድርገን ነው መጠቀም ያለብን። አለበለዛ እንደ ከላይ የጠቀስኩት ኢትዮ-አሜሪካዊ የገንዛቤ ድክመቶች ይኖርብናል።

በመጨረሻ መማር የሚገባን በፖለቲካ አስተያየት ትህትናና ለሰው መቆርቆር (empathy) ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ ነው። ከላይ የጠቀስኳቸው ምሳሌዎችን ለመጠቀም… እራሳችንን በሰዎቹ በኩል አድርገን ማሰብ አለብን። ኢትዮጵያ ያለው ነጋደ ሀገር ውስጥ በመሆኑ ምንድነው የሚያጋጥመው የሚያስበው የሚያደርገው። ማናልባት ዙርያውን ያለውን ህዝብ በተለያየ መንገድ እየጠቀመ ይሆናል። ኢትዮ-አሜሪካዊው ደግሞ እንደ ማንም አሜሪካዊ ስለ ሀገሩ ችግር በደምብ አይገነዘብም። የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው ልንፈርድበት አይገባም። ወዘተ። አይመስልም እንጂ ትህትና ዋና የፖለቲካ መሳርያ ነው ሁላችንም ተገንዝበነው ትሁት መሆን መሞከር ይገባናል።

ስለዚህ ፖለቲካ ውስብስብ ነው። በተራ ግንዛቤ ብቻ የምናይ ከሆነ አሜሪካ ገነት ኢትዮጵያ ሲኦል ኢህአዴግ ሴጣን ይመስለናል። ግን እውነቱ እንደዚህ ቀላል አይደለም። ትክክለኛ ሀሳብና ተግባር እንዲኖረን ይህን መገንዘብ አለብን።

Friday, 16 March 2018

ስለ ትህትና

እግዚአብሔር ክፉ መናፍስትን የማስወጣት ጸጋ የሰጣቸው አንድ ባሕታዊ ነበሩ። በአንድ ወቅት ጋኔኖቹን የሚያስፈራቸውና ከሰዎች እንዲለቁ የሚያደርጋቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት ፈልገው ጠየቁ።

«ጾም ይሆን?» ብለው አንዱን ጠየቁት።

«እኛ መቼም አንበላም አንጠጣምም» ብሎ ክፉ መንፈሱ መለሰላቸው።

«የለሊት ሙሉ ጸሎት ይሆን?»

«እኛ አንተኛ።»

«ዓለምን ትቶ መመንን?»

«ይህ እንደ ትልቅ ነገር ይቆጠራል። ግን እኛ አብዛኛው ጊዜአችንን በየ በርሃው እየዞርን ነው የምናጠፋው።»

«ታድያ ምንድነው ይዞ ሊቆጣጠራችሁ የሚችለው፤ እባካችሁ ንገሩኝ» ብለው ታላቁ አባት ደግመው ጠየቁ።

ክፉ መንፈሱ በተአምራዊ ኃይል ጥያቄውን እንዲመልስ ተገደደ፤ «ትህትና ነው። ይህን መቼም ልናሸንፍ አንችልምና።»

Thursday, 15 February 2018

ቤተ ክርስቲያን መቅደም አለባት!

ከትላንት ወድያ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙርያ ያልጠበቅናቸው መልካም አሳቢዎች እንደ ለማ መገርሳና አቢይ አህመድ ብቅ ማለት ጀመሩ። ትላንትና መንግስት ለረዥም ዓመታት የሚለመነውን ነገር አደረገ፤ ያለጥፋት የታሰሩትንና የተሰቃዩትን በርካታ እስረኞችን ፈታ። ዛሬ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃደኝነታቸው ስልጣናቸውን ከቀቁ። መልካ ለውጦች ይታያሉ፤ እግዚአብሔር መጨረሻውን ያሳምርልን።

ግን ከፖለቲካው ቤተ ክርስቲያናችን መቅደም አልነበረበትም? (ይህን ስል እኔም እንደ አንድ ምእመናን እራሴን እየወቀስኩኝ ነው።) የኛ ለማ መገርሳዎች፤ በትህትና አለመፍረድ፤ በፍቅርና በምሳሌ፤ የሚናገሩት የት አሉ? እርግጥ አሉ፤ ግን በሌሎቻችን ተከበው ድምጻቸው በአግባቡ አይሰማም። እስረኞችንን መቼ ነው የምንፈታው? በርካታ እስረኞች አሉን፤ ፍቅር፤ ሃላፊነት፤ እርቅ፤ ትህትና፤ ሰላም። እነዚህንንሁሉ አስረን ቁጭ ብለናል። መቼ ነው የምንፈታቸው? ደግሞ መቼ ነው ሃላፊነት ወስደን እራሳችንን ህዝብ ፊት ዝቅ የምናደርገው። እንዲህ የሚያደርጉ አሉ ግን በኔ አይነቱ ተከበው አይታዩም። እንቅፋትም ሆነናቸዋል።

ቤተ ክርስቲያናችን እንደ አቡነ ጴጥሮስ መምራት መጀመር አለባት። በፖለቲካው መመራት ወይም መቀደም እፍረት ነው። አሁን ከቤተ ክርስቲያን እርቅ በፊት በሃገራችን ፖለቲካ እርቅ ቢመጣ ታላቅ እፍረት አይደለም? ከዛ በሗላ መጀመሪያውኑ ፖለቲካ ነው ያስቸገረን ብለን ልናሳብብ ነው? እነ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮሜ ፖለቲካ እየተሰውዉ ደፍሮ ያላሉትን ልንል ነው?! ይህ ቢሆን እጅግ አሳሳዛኝ ነው።

ስለዚህ እንምራ! በሃገር ውስጥና በውጭ ያሉት ስይኖዶስ መካከል ፈጥነን እርቅ እናምጣ። ለኢትዮጵያ ህዝብ ምሳሌ እንሁን። ፈተናው ብዙ ነው። ገና እየበዛ ይሄዳል። ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ በሁሉም ቦታ ከኛ ጋር ነው። ይህን ካመንን ለፍቅር እንድፈር፤ አንፍራ!

Thursday, 1 February 2018

ትህትና

አባ ቲኾን በጻፉት መጸሃፍ "Everyday Saints" አባ ቲኾን አንድ ታላቅና ጀግና መኖክሲት፤ በሶቪዬት መንግስት ደጋግመው የታሰሩ የሆኑ፤ ስለ ገዳም ኑሮ ሲጠይቋቸው እኚህ መኖክሲት እንደዚህ አልዋቸው፤ «ዋናውና መጀመርያው ነገር ይህ ነው፤ ማንንም ላይ አትፍረድ»

አለመፍረድ ማለት አለመኮነን ነው። ይህ መፍረድ ድርጊትን ወይም አቋምን ጥሩ ነው ወይ መትፎ ነው ማለት አይደለም። እንደዚህ አይነት ፍርድ ተገቢም አስፈላጊም ነው። አትፍረዱ ማለት አትኮንኑ፤ ሰውን ከድርጊቱ ጋር አታቆራኙ። ሰውየው እራሱ መጥፎ ነው፤ ሃጥያተኛ ነው፤ እኔ ከሱ እሻላለሁ፤ እሱ ወደ ገሃንም ይገባል አይነቱ ነው አትበሉ አታስቡ የምንባለው። ስለዚህ ለክርስቲያን በድርጊት መፍረድ ተገቢ ነው ግን በሰው ማንነት መፍረድ ትክክል አይደለም።

በሰው መፍረድ ኢክርስቲያናዊ የሆነው አንዱ ምክነያት መፍረድ ወደ ተዕቢት ስለሚመራ ነው። ተዕቢት ደግሞ የመጀመርያውና ዋናው እግዚአብሔርን ያጣንበት ምክንያት ነው። አዳምና ሄዋን በትዕቢታቸው ምክንያት መልአክት ለመሆን አስበው ነው እጸ በለሱን የበሉትና። ስለዝህ እንደ ክርስቲያን ከትእቢት ርቀን ወደ ተቃራኒው ትህትና ነው መጠጋት ያለብን።

አዎን ትህትና አንድ ክርስቲያን ከሚፈልገው ዋና ጥሩ ባህርይ ነው። «ትህትናና ፍርሃ እግዚአብሔር ከሁሉ መልክአ ምግባር በላይ ናቸው» ትብሏል። ትህትና የሰው ልጅን ዋና ተልኮ፤ ማለት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ፤ ለማሟላት ግድ ነው። እራሱን እንዲገመግም፤ ከፈተናና ሴጣን እንዲርቅ፤ ሌሎችን ላይ ከመጠቆም እራሱን ላይ መጠቆም። እነዚህ በሙሉ ትህትና ይጠይቃሉ።

እንደዚህ ሆኖ ማንም ሰው፤ በተለይ መሪ፤ ትህትናን ሲያንጸባርቅ ደስ ይለኛል። እራሱን ወይም ወገኑን የማያሞገስ፤ እራሱን አጥፊና ሃላፊ የሚያደርግ፤ እራሱን ጥልቆ የሚገመግም፤ ሌሎችን በፍርድ ሳይሆን በመቆርቆር አይን የሚያይ ሰው ደስ ይለኛል። ይህ ባህሪዎች ለራሱም ለዙርያው ላሉትም እጅግ ይበጃል።

እኔ አቶ ለማ መገርሳን አላውቋቸውም ግን ያዳማጥኳቸው ንግግሮቻቸው በትህትና የተሞሉ በመሆናቸው ተደስጭያለው። በዚህ ረድፍ ለሁላችንም ታላቅ ምሳሌ መሆናቸው ነው ከሁሉም በላይ ያስደሰተኝ።

ከአቶ ለማ ሌሎችን በሰሞኑ አይቻለሁ። ብአዴን በደብረ ብርሃን የጠራው የምሁራን ስብሰባ ላይ አንድ ወጣት ምህሩን በጥህትና እጅግ እጅግ አስደሰተኝ። እኛ ምሁራን ባንኖር ገበሬው (ብዙሃኑ) በሰላም አብሮ ይኖር ነበርና እኛ ነን ችግሩ። ለችግሩ መፍትሄ እናገኝለታለን ከማለት መጀመርያ እራሳችንን እንፈትሽ ብሎ ታላቅና አስደናቂ ንግግር አቀረበ። እንደዚህ አይነቱ የምላስ ሳይሆን የመንፈስ ጀግና ነው ሁላችንም የሚያስፈልገን።

ሁላችንም በሌላ ላይ ከመጠቆም፤ ችግርሮቻችንን ብሌላ ከማሳበበ፤ መፍትሄም ከሌሎች ነው የሚመጣው ብለን ከምናሰብ፤ እራሳችንን ወድቅ (disempower) ከማድረግ፤ ውስጣችንን መርምረን ሌሎች ላይ ሳንፈርድ ብንራመድ ለሁላችንም መልካም እንሆን ነበር።

እግዚአብሔር ትህትና ይስጠን። ከትዕቢት ፈተና ያርቀን። የእርስበርስ ሰላም እንድሽ ይርዳን።

Thursday, 28 December 2017

ስለ የለማ መገርሳ ምሳሌ የሆነ ንግግር

ለማ መገርሳን አላውቃቸውምም ባውቃቸውም ስለማንነታቸው ምንም ማለት አልችልም፤ ይህ የእግዚአብሔር ጉዳይ ነውና።
ሆኖም አቶ ለማ ይሚሰጡትን ንግግሮች አድምጬ እጅግ ጥሩና አስተማሪ እንደሆኑና ለሉላችንም አስፈላጊ መልክቶች እንደሚያስተላልፉ ተገንዝብያለው።

ከባህር ዳር በበአዴን ስብሰባ የተናገሩትን እኚህን ዋና ነጥቦችን ላተንትን፡

1. ትህትና፡ አቶ ለም አንድም እሳቸውም ድርጃታቸውም የሰራውን ነገር አልወደሱም። አንድች። በአንጻሩ ያሉትን ችግሮች አለ ህፍረት ሙሉ በሙሉ ዘርዝረው በተዘዋዋሪ ሙሉ ሃላፊነት ተቀብለዋል። ማን ፖለቲከኛ ነው እንደዚህ የሚለው? ይህ ለሁላችንም እጅግ ታላቅ ምሳሌ ነው። ጣት ከመጥቆም ወደ ራስ ማየት ነው የችር መፍቴ።

2. ሃላፊነት፡ ላሉት ችግሮች ሃላፊነት ወሰደው ለመፍትሄውም ሃላፊነት ወስደዋል። እንደዚህ መደረግ አለበት ወይም እነዛህ እንደዚህ ማድረግ አለባቸው ሳይሆን እንደዚህ ማድረግ አለብን ነው ያሉት። ታልቅ ምሳሌ የሆነ አባባል ነው።

3. ኢትዮጵያዊነት፡ አቶ ለማ የኢትዮጵያዊነት እንዳለና እንዳልጠፋ፤ ለሰላምና ብልጽግና እንደሚያስፈልግ አስረግጠው ተናገሩ። 20 ዓመት በፊት ነውር የነበረውን «ኢትዮጵያዊነት» አኩሪ እንደሆነ ገለጸ። ይህ አባባል፤ በተለይ ከአንድ ኦህዴድ መሪ፤ እጅግ ጥንካሬንና ለእውነትና ሰላም መሻትን ያሳያል። ሌሎቻችንም እንደዚህ ብናስብ ይበጅ ነበር!

4. መልካም አስተዳደር (ሙስና)፡ የመንግስት ሹማምንት «ብቸኛይ ስልጣን» ስላላቸው ነው ችግሩ ብለዋል አቶ ለማ። ሚዛን ከህዝብ ወደ ሹማምንት ከመጠን በላይ አመዝኗል አሉ። ይህ ኢሃዴግን በተለይ የ100% ውሳኔውን የሚተች አነጋገር ነው። ኢህአዴግ ብችኛ ስልጣን ሊኖረው አይገባም። ወይም የፖለቲካ ውድድር በተወሰና ደረጃ ቢሆን ግድ ነው ማለቱ ነው። ከአንድ የኢህአዴግ አመራር አስደናቂ አባባል ነው።

5. ስለ ወጣቶች ሲናገሩ ከፖለቲካ ወደ ማህበራዊ ጉዳይ ከፍ አሉ። ወጣቱን ለቴለቪዥንና ኢንተርኔት መተው ሳይሆን ማሳደግ እንዳለብን አስታወሱን። ከዛም በላይ ግን የወደኩላቸው ቤተሰብ ዋና መሆኑን ማስረዳታቸው ንው። ማንም ኢትዮጵያዊ ምህር ቤተሰብን ከትምህርት በዚህ ማንገድ ሲያስቀድም ስምቼ አላውቅም። ትምህርት ትምህርት ትምህርት ነው የሁላችንም ጭህወት። ግን ትምህርት መሳርያ ነው ቤተሰብ ማንነት ነው የሚለውን  ከዚህ በፊት ማንም ሲል ሰምቼ አላውቅም። እጅግ ጠንካራ ምልክት ነው ያስተላለፉት፡

6. በእህአዴግ ዘመን በተለያየ መድረክ የተዘለፉት ምሁራን እንዳ ማንኛውም የህዝብ ዘርፍ ለሃገሪቷ አስፈላጊ እንደሆኑ ሲያሳስበን አቶ ለማ አንድ ጉዳትን ያመጣ ቁስል አዳነ።

7. የጎሰኝነት ለሁሉም ያለው አደጋ አስረግጠው ተናገሩ። ያመጣው ጥላቻና ቅሬታ ለሁሉ ሰውና ለሃገሪቱ ጎጂ መሆኑን ማስረገጣቸው ለሁላችንም ታላቅ ማስተንቀቂያና ምሳሌ ነው። አንድነት ደግሞ የሁሉ ችግራችን ቀድሞ መፍቴ መሆኑን ገለጹ። እውነት ነው። ማንም ችግር አለአንድነት ሊፈታ አይችልም፡

8. በታሪካችን ማፈር ሳይሆን ኮርተን ጥሩውን እንደምሳሌ ወስደን መጥፎውን አስወግደን ግን ሃላፊነቱን በጋራ ተቀብለን መኖራለብን። ይህ ታላቅ የአንድነት መንገድ ነው። ታሪቅ የኔ ወይም የሱ ሳይሆን የጋራ አድረግን መያዝ አንድነትን ይየሚያዳብር ነው።

እግዚአብሄር አቶ ለማ እንዳለው ያድርግለት። ከባድ ስራ ነው ያለው። የኦህዴድ መሪነት ከባድ ስራ ነው ከጎሰኞች ጋር የሚያጋፍጥ ነውና ሚዛን ጠብቆ ነው መራመድ የሚችለው። በዚህ ጉዞአው ሁላችንም ፍርድ ሳይሆን ድጋፍ እንድንሰጠው ይገባል ብዬ አስባለው።

Wednesday, 5 October 2016

ፖለቲካ ሃይማኖት አይደለም!

2009/1/24 .. (2016/10/4)

(pdf)

ዛሬም ጠንካራ፤ ህዝብን የሚወክል፤ ኢህአዴግን በመጠኑም ቢሆን ሊጋፈጥ የሚችል የተቃዋሚ ድርጅት በኢትዮጵያ የለም። (ደህና የሚባለው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስም በምንም ሚዛን እነዚህን መስፈርቶች አያሟላም።) ይህ እውነታ ሁላችንም የምናውቀው ነው፤ የዛሬው የህዝብ እንቅስቃሴ ከቀጠለና ከጨመረ አለመሪነትና ድርጅት እንዴት ይሆናል ብለን እንሰጋለን።

ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ለ25 ዓመት ደህና ተቃዋሚ ድርጅት ኖሮ አያውቅም። የነበሩትም ያሉትም ደካማ፤ በቀላሉ የሚፈሩና የሚበታተኑ፤ እርስ በርስ ተጣልተው እራሳቸውን ከጥቅም ውጭ የሚያደርጉ ወዘተ ናቸው።

የዚህ ሁኔታ ያልሆነበትን ምክንያት ተጠንቅቀን እናውቃቸዋልን። ኢህአዴግ ጠንካራ ስለሆነ አይደለም። ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ ጥቂት ህዝብ ነው የሚወክለው እያልን በዛው ትንፋሻችን ጠንካራ ነው ማለት አንችልም!! ኢህአዴግ በኃይሉ ሳይሆን በፈቃዳችን እንደሆነ የሚገዛው እናውቃለን፤ እራሳችንን አናታልል።

ታድያ ለምንድነው ተቃዋሚው ለመደራጀትም የሚያቅተው። እንደምናቀው አንዱ ዋና ችግር የተቃዋሚ ፖለቲከኖችም ህብረተሰብም የአለመስማማት፤ እርስ በርስ መጣላት፤ እሩቅ ማሰብ አለመቻል፤ ወዘተ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ተጽፏል። ሆኖም ከዚህ ጽሁፍ አንድ ሌላ ተቃዋሚን የሚያደክመው ምክንያት ላቀርብ እወዳለሁ፤ ይህ ፖለቲካን እንደ ሃይማኖት ማየትና የሚከተለው ግትርነትና አለመቻቻል።

ሃይማኖት በአንድ እውነት የተመሰረተና የማይቀየር ነው። ለምሳሌ እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያንነቴ ክርስቶስ ሞተና በሶስተኛው ቀን ተነሳ ብዬ አምናለው ከዚህ እምነትም ዝንፍ አልልም፤ ይህ ፍፁም እውነት ነውና።

ግን ይህንን ዝንፍ አለማለትን ወደ ፖለቲካ ወይም ሌላ የህይወት ዘርፍ ማምጣት የለብኝም። ቅንጅት ፓርላማ ይግባ አይግባ ፍፁም እውነት ያለው የሃይማኖት ጉዳይ አልነበረም፤ ከሁለቱም አቋሞች ጥሩ የሆኑ የሚያስኬዱ ምክንያቶች ነበሩ። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ጎሳን ያካትት አያካትት፤ ይህም የድርድር ጉዳይ ነውንጂ እውነትና ውሸት የለበትም። ወዘተ። በፖለቲካ ወይም በስራ ወይም በቤተሰብ ኑሮ መደራደር፤ የሌላውን አስተያየት መረዳት፤ ለሌላው መቆርቆር፤ ላለመስማማት መስማማት፤ ወዘተ አስፈላጊ ነው።

ለምሳሌ ስንቶቻችን ነን የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞቻችንን ቀይረን የማናውቀው? አንዳንዶቻችን የኃይለ ስላሴን መንግስት በግዜው እንደግፍ ነብር ዘሬ ግን ዴሞክራሲአዊ አለመሆኑን አንወድም እንላለን። ስንቶቻችን በኮምዩኒዝም በኢህአፓ ወዘተ እናምን ነበር ዛሬ ግን ተሳስተን ነበር እንላለን። ስንት የደርግ ደጋፊ የነበሩና አሁን ንስሃ የገቡ አሉ። እርግት ኢህአዴግንም በአንድ ወቅት የደገፉ አሉ!

ታድያ ሃሳባችንን ሲያስፈልግ የምንቀይር ከሆነ ለምንድነው ከኛ ፖለቲካዊ ሃሳብ ጋር የማይስማማ ባልደረባ ሲያጋጥመን ከሱ ጋር ጦርነት የምንገባውም የጋራ ፖለቲካ ድርጅታችንንም የምናፈርሰው?! ይህ የሚሆነው ፖለቲካን እንደ እምነት ምንም ድርድር የማይደረግበት ነው ብለን ስለምንቆጥር ነው።

በፖለቲካ ደረጃ መስማማት፤ አለመከፋፈል፤ አንድ መሆን ከፈለግን የሃሳብ ልዩነቶችን በሚገባው በትህትና መቀበልና ማስተናገድ አለብን። የግትርነትና አጉል እረግጠኝነት መንፈሳችንን ማስወገድ አለብን። እንደዚህ ማድረግ ስንችል፤ በተለይ የፖለቲካ ትህትናችንን ማዳበር ስንችል ነው የተቃዋሚ ድርጅቶቻችንን በቂ አቅም እንዲኖራቸው ማድረግ የምንችለው።

ትህትናና ግትር አለመሆን፤ እነዚህን ብቻ እናስታውስ።