Wednesday, 21 March 2018

«ሴኩላሪዝም»

ትንሽ አመታት በፊት አንድ የመንግስት ስራተኛ የሆነ ዘመዴ የኦርቶዶክስ መዝሙር ከመስሪያቤት ኮምፕዩተሩ ላይ ማዳመጥ ክልክል እንደተደረገ ነገረኝ። ለምን ብዬ ስጠይቀው ክርስትያኑም ሙስሊሙም የሚፈልገውን መዝሙር፤ ስብከት፤ ትምሕርት እያዳመጠ እና ኮምፕዩተሩ ላይ ሥዕል እየለጠፈ የሰራተኞች እርስ በርስ ግጭት ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ተከለከለ አለኝ። የሚገርመው ነገር ግን 1) ከመስሪያቤቱ እንደዚህ አይነት ግጭቶች አልነበሩም እና 2) ክልከላው በተራ ትዛዝ ሳይሆን ከከፍ ያለ የአስተዳደር ደረጃ በመመርያ ምልክ የተላለፈ ነበር። የመመርያው ርዕስ ደግሞ «ሴኩላሪዝም» ነበር።

ይህን ታሪክ ስሰማ እጅግ አዘንኩኝ። መቼ ነው መንግስቶቻችን፤ ምሁሮቻችን እና ልሂቆቻችን የምዕራብ ዓለም ርዕዮት ዓለምና ፍልስፍና ይዘው አገራችን ላይ መጫን የሚያቆሙት? ካለፉት የ100 ዓመታት ታሪካችን አይማሩምን?

እስቲ «ሴኩላሪዝም» ባጭሩ ምን እንደሆነ እንመልከት። «ሴኩላሪዝም በዓለማችን እግዚአብሔር የለም/አይሳተፍም ብሎ ማሰብ ነው»። ሴኩላሪዝም እግዚህብሔር ሊኖር ላይኖርም ይችላል ግን ከዓለማችን ከሕይወታችን ከለት ኑሮአችንም አይሳተፍም የሚለው አመለካከት ነው። እግዚአብሔር ካለ እዛው ከዙፋኑ ወይንም ገነቱ ተቀምጦ ይመለከተናል። በሃይማኖት እና በእግዚአብሔር በግል ምርጫችን ልናምንባቸው የምንችል የእምነት ሥርዓቶች ናቸው። በሀሳብ ደረጃ ነው የምናምንባቸው ካላሰኘን ደግሞ ከሀሳባችን እናስወግዳቸዋለን!

ይህ አስተሳሰብ በተለያየ መንገድ ወደ ክርስትያን የሆነውን አስተሳሰብ ገብቷል። «ዓለማዊ» እና «መንፋሳዊ» የምንላቸው ቃላት በተሳሳተ መንገድ እንጠቀማለን። ዓለማዊ ስንል ስራችን፤ ትምሕርታችን፤ ገበያችን፤ ንግዳችን ወዘተ ነው። እግዚአብሔር እነዚ ነገሮች ውስጥ እንዳለ አናምንም። ስለዚህም ነው በነዚህ የህይወት ዘርፎቻችን ኢ-ክርስትያናዊ ነገሮች እያደረግን እያለን አማኞች ነን የምንለው። እሁድ እሁድ ግን ቤተ ክርስትያን ሄደን ወደ መንፈሳዊስ ዓለም እንሸጋገራለን። እዛ ጨዋ ነን፤ ጥሩ ስነ መግባር አለን፤ ጭንቀቶቻችንን አስተንፍሰን ወደ ዓለማችን እንመለሳለን።

ይህ ግን የውሸት ክርስትና ነው። በእምነታችን እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ በሁሉም ነገር አለ። «እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም። ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር።» ኤር 23:23-24።

ስለዚህ ትምሕርት ቤት ብሄድ፤ መስሪያ ቦታ ብሄድ፤ እርሻዬ ላይ ብሆን፤ ትራንስፖርት ላይ ብሆን፤ መጠጥ ቤት ብሄድ፤ በሁሉም ቦታ እግዚአብሔር አለ። ሕይወታችንን እግዚአብሔር ያለበትና የሌለበት ብለን ልንከፋፍለው አንችልም። በሁሉም ቦታ በሁሉ ደቂቃ ከኛ ጋር ነውና።

ይህ የሚያሳየን የሰው ልጅ ክርስትያንም ሴኩላሪስትም አብሮ ሊሆን አይችልም። ብዙዎቻችን ወደዚህ ስህተት ብንገባም ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ለክርስትያኖች እግዚአብሔር ልኬት የለውምና። በተጨማሪ ሴኩላሪዝም እግዚአብሔርን ከለት ኑሮአችን ማጥፋት ስለሚፈልግ የክርስትና ተቃራኒ ብቻ ሳይሆን ጠላት እንደሆነ ግልጽ ነው።

«እናንተ ኦርቶዶክሶች፤ ሙስሊሞች፤ ፕሮቴስታንቶች አብሮ መኖር አትችሉም። ስለዚህም (እግዚአብሔራን ተክቼ!) ከላያችሁ ሆኜ አስተዳድራችኋለሁ» ይላል ሴኩላሪዝም / ሴኩላሪስቱ። «እኔ ነኝ ስልጡኑ፤ ከማንም ጋር የማልጋጨው፤ ከሁሉም ጋር የምግባባው፤ ሁሉንም የማከብረው» ይላል። እውነቱ ግን ሴኩላሪስቱ እንደዚህ ሲል ሁሉንም በሰላም ለመጠበቅ ሳይሆን አላማው ይህን አስመስሎ «እግዚአብሔር የለም» የሚባለውን ሃይማኖትን ለማስፋፋት ነው። እግዚአብሔር ከአዕምሮአችን ብቻ ነው ያለው እንጂ ከስራ ቦታችን፤ ገበያ ቦታችን፤ መንገዶቻችን፤ ሚዲያዎቻችን፤ ከለት ኑሮአችን የለም ብለን ካመንን ቀጥሎ እግዚአብሔር የትም የለም ማለት የሚቀጥለው ቀላል እርምጃ ነውና!

በተጨማሪ እግዚአብሔር ከለት ኑሮአችን ከሌለ የማህበረሰብ የአገራችን ድንጋጌዎች ከየት ሊመጡ ነው? ከሴኩላሪዝም ርዕዮት ዓለም ከ«እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖት ሊመጡ ነው! አያችሁ ሴኩላሪዝም እራሱን ገለልተኛ አድርጎ እንዴት «እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖትን ሰተት ብሎ እንደሚያሰፍን።

ኢትዮጵያ የሃይማኖት አገር ናት። ታሪካችን ትውፊታችን ከዚህ የተያያዘ ነው። ማንነታችን ይህ ነው። ሴኩላሪዝም ደግሞ የህን አፍርሶ «እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖትን ነው ማስፈን የሚፈልገው። ይህ ሂደት እንዴት እንደሚሰራ ለማወቅ የምዕራብ ዓለሙን ያለፈውን 400 መቶ ዓመት ታሪክ መመልከት ነው። ስለዚህ ሴኩላሪዝም ኢ-ኢትይጵያዊ እንደሆነ ተረድተን ወደ አገራችን ሰተት ብሎ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን። በተለይ ደግሞ ወደ ልባችን ሰተት ብሎ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!