Thursday 22 March 2018

የመሬት ፖሊሲ በጸንፈኛ ፖለቲከኞቻችን እጅ

English version: https://asfawdarguemeshal.blogspot.ca/2017/05/our-radical-politicians-land-to-ruler.html

በቅርብ ጊዜ ከዚህ ዓለም የተለዩት የኃይለ ሥላሴ የህግ አማካሪ የነበሩት ተሾመ ገብረማርያም በቃለ ምልልስ እነዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፤ «መሬት ለአራሹ» ነበር ያልነው፤ «መሬት ለመንግስት» ሆኖ ቀረ። የ«መሬት ለአራሹ» የሚባለው ፖሊሲ አላማው ከባላባት «ተከራይቶ» የሚያርሰውን መሬት ለጪሰኛው መስጠትና የመረቱ ባለቤት ማድረግ ነበር። የኃይለ ሥላሴ መንግስት ይህን ፖሊሲ ለማጽደቅ ቢሞክር በፖለቲካ በፍትህ በአፈጻጸም ደረጃ ችግሮች ያጋጥሙት ነበር። ሆኖም ለነበረው ኢፍትሃዊ ሥርዓትና ከነበረው የገበሬውችግር አንጻር ይህ «መሬት ለአራሹ» ፖሊሲ ትክክል ተገቢ አስተዋይና መጠነኛ እርምጃ ይሆን ነበር። በተቃራኒው ከደርግ ጀምሮ የዋለው «መሬት ለመንግስት» ፖሊሲ የመሬት ባለቤትነት ሙሉ በሙሉ ለመንግስት ማስተላለፉ ለነበረው የመሬትችግር የከረረና ጸንፈኛ መልሰ ነበር። የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን ተገቢውን መጠነኛውን እርምጃ ከመውሰድ አክራሪና ጸንፈኛውን እርምጃ ወሰዱ።

የሚያሳዝነው ነገር በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን ታሪቅ ልሂቃኖቻችን በቁልፍ ጊዜዎች በተደጋጋሚ ወደ ጸንፍ ማድላታቸው ነው። በተለይ የኃይለ ሥላሴ «ልጆች» የሆኑት በሳቸው ጊዜ ከ1950 ወዲህ የቀለም ትምሕርት የተማሩት ልሂቃን በተደጋጋሚ ጸንፈኛ የፖለቲካ ውሳኔዎች በመወሰን አገራችንን ወደ ከባድ ያልተጠበቁ አደጎች መርተዋታል። ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ለነዚህ አጉል ውሳኔዎች  ዋጋ እየከፈለች ነው።

ከዚህ ጽሁፍ የኢትዮጵያን ህዝብ የጎዳው እስካሁንም እያሰቃየው ያለው የመሬት ባለቤትን መንግስት ያደረገው የፖሊሲ ውሳኔን እንመልከት። ይህ ፖሊሲ ባጭሩ ስድስት ችግሮች ፈጥሯል አባብሷል፡

1. የህዝብ ቁጥርን ባልተጠበቀና በኢተፈትሮ ሁኔታ መናር
2. አሁን ያለውን ታላቅ የገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት
3. ዝቅተኛ «የሰው አቅም» (human capital) በትለይ የግብርና ሙያ በገጠር ቦታዎች
4. ዝቅተኛ የእርሻ ምርት መጠን
5. ከፍተኛ የእህል የምግባ ዋጋ ግሽበት
6. የምግብ ዋስትና እጥሮትና ረኃብ

እነዚህ ችግሮች እንዴት ተፈጠሩ? በመጀመርያ መሬት የመንግስት መደረጉ ገበሬዎች መሬታቸውን መሸጥ መለወጥ ስለከለከላቸው የገጥር ህዝብን ከሞላ ጎደል እስረኛ አድርጓቸዋል። ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው ወደ ከተማ መዘዋወር እንዳይችሉ ከልክሏቸዋል። ይህ እንዴት እንደሆነ በምሳሌ ላስረዳ።

ዐምዴ የሚባል አንድ ገበሬ በ1968 በቂ የሆነ ወደ ሰባት ሄክታር የሚሆን እርሻ ነበረው። ዐምዴ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ከተማ መዘዋወር ይፈልጋል። ግን ይህን ለማድረግ የመቋቋምያና ስራ መጀመርያ ገንዘብ ያስፈልገዋል። ይህን ገንዘብ ለማግኘት መሬቱን በሙሉ ወይም በከፊል መሸጥ አለበት መሬቱ ዋና ንብረቱ ስለሆነ። ያኔም አሁንም የኢትዮጵያ ገበሬዎች ከመሬታቸው ሌላ ብዙ ዋጋ ያለው ንብረቶች የላቸውም።

ግን የዐምዴ መሬት የመንግስት ነው ተብሎ ስለተሰየመ መሸጥ መለወጥ በሱ መበደርም አይችልም። ስለዚህ ለከተማ ኑሮ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት አልቻለም። በተጨማሪ መሬቱን ትቶ ቢሄድ ደግሞ ይወሰድበታል። ስለዚህ በተዘዋዋሪ ዐምዴ ወደ ከተመ መዘዋወር እንዳይችል ተከለከለ ማለት ነው። 1) መሬቱን ሽጦ ወደ ከተማ ለመሄድ ገንዘብ ማግኘት አይችልም። 2) እንደምንም አድርጎ ገንዘብ አግኝቶ ቢሄድም ሀሳቡን ቀይሮ ልመለስ ቢል ምሬቱ ተወስዶበት ነው የሚያገኘው! ይህን ሁሉ ስለሚያውቅ ዐምዴ ወደ ከተማ መሄድን አያስበውም። ሌሎቹም የኢትዮጵያ ገበሬዎች እንደ ዐምዴ ከተማ መሄድ ቢፈልጉም ገጠር ቁች ብለዋል። በዚህ የመሬት ፖሊሲ ምክነያት ከ1975 እስከ ቅርቡ ጊዜ ገበሬዎች በሚገባው ቁጥር ወደ ከተማ አልፈለሱም።

በዐምዴ ታሪክ እንቀጥልና የለት ኑሮው እንዴት ነበር ብለን እንጠይቅ። እንደ አብዛኛው የገጠር ነዋሪ ዐምዴ ብዙ ልጆች ወልዷል። ሰባት ልጆች ወልዷል። በ2000ዓ.ም. በገጠር የሚኖሩ ሴቶች በአማካኝ 6.5 ልጆች ነበር የሚወልዱት በአዲስ አበባ 2.2 ነበር። ይህ በከተማና በገጠር ያለው የልጅ መውለድ መጠን ልዩነት ዓለም አቀፍ ያለ ነው፤ የገጠር በአንጻሩ ብዙ ይወልዳል የከተማ አይወልድም። ደሃ ባንጻሩ ብዙ ይወልዳል ሃብታም አይወልድም። ይህ ዓለም በሙሉ የሚታይ ሁኔታ ነው።

የዐምዴ ልጆች ሲያድጉ መሬቱን ከፋፍሎ ለእያንዳንዳቸው አንድ ሄክታር አወረሰ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ልጆቹም እያንዳንዳቸው ሰባት ልጆች ወለዱና አንድ ሄክታር መሬቶቻቸው ጠበቡ። ይህ ችግር በአገር አቀፍ ደረጃ እየባሰ ሄዷል። ዛሬ በኢትዮጵያ የአማካኝ የእርሻ ይዞታ ከአንድ ሄክታር በታች ነው። የገጠር መሬት ተጨናንቋል።

በ1968 የመሬት አዋጁ ሲታወጅ ከ28 ሚሊዮን የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ 85% የገጠር ነዋሪ ነበር። 40 ዓመት በኋላ በ2008 ከ97 ሚሊዮን ጠቅላላ የህዝብ ቁጥር 80% በገጠር ይኖራል። በ40 ዓመት በገጠር የሚኖረው የህዝብ መጠን ከ85% ወደ 80% በአምስት ብቻ ነው የቀነሰው። ግን የገጠር ነዋሪዎች ከላይ እንደጠቀስኩት በአማካኝ 6.5 ልጅ ስለሚወልዱ ጠቅላላ የገጠር የህዝብ ቁጥር ናረ። ለምን? ለ40 ዓመት ገበሬዎች ሲፈልጉ መሬታቸውን ሽጠው ወደ ከተማ መዘዋወር ስላልቻሉ ከሚገባው በታች ቁጥር ነው ወደ ከተማ የፈለሰው። የመሬቱ ፖሊሲ ባይኖር ኖሮ የገጠሩ ሰው ዓለም ዙርያ እንደሚታየው በራሱ በተፈጥሮና በነፃነት መንገድ ቀስ በቀስ ውደ ከተማ ይፈልስ ነበር። ይህ የተፈጥሮ መጠነኛ ፍልሰት በመሬት ፖሊሲው ምክነያት ባይታገድ ኖሮ የገጥር የህዝብ ቁጥር ዛሬ ከ80% ፋንታ ምናልባት ወደ 65% ወይም ከዛም ዝቅ ብሎ ይወርድ ነበር።

በዚህ መልክ የገጠሩ የህዝብ ቁጥር ቅስ በቅስ እየወረደ ቢሄድ የከተማ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ የአገሪቷ የጠቅላላ የህዝብ ቁጥር እንዳሁኑ አይንርም ነበር። ምክነያቱ የከተማ ሰው እንደ ገጠሬው ያህል አይወልድም። በዐምዴ ምሳሌ ከቀጠልን ወደ ከተመ ቢዘዋወር ኖሮ ልጆቹ እያንዳንዳቸው ሰባት ልጆች ከሚወልዱ ከተማ ስለሚኖሩ እንደሌሎች የከተማ ነዋሪዎች ሁለት ይወልዱ ነበር። ግን ወደ ከተማ እንዳይመጣ «ተከልክሎ» ዐምዴ ከገጠር ታስሮ ቆየ። በዐምዴ ምሳሌ እንደምናየው ይህ «የገጠር እስርቤት» መተንፈስ ስላልቻለ የህዝብ ቁጥሩ በ40 ዓመት ከ24 ሚሊዮን ወደ 77 ሚሊዮን ገባ። ይህ የገጠር/ከተማ የህዝብ መጠን አላግባብ ከፍ ያለ በመሆኑ ነው የኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር በኢተፈጥሮ መንገድ የናረው እስካሁን የሚንረው።

ወደ ዐምዴ ቤተሰብ እንመለስ። ልጆቹ እያንዳንዳቸው ሰባት ልጆች ወልደው የአንድ ሄክታር መሬታቸውን ለሰባቱ መከፋፈል አይችሉም አንድ ሰባተኛ ሄክታር ለአንድ ቤተሰብን በቂ ስላልሆነ። ስለዚህ መሬታቸውን ለአንድ ልጃቸው ያወርሱትና ሌሎቹ ስድስት ልጆቻቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ጨርሰው ግድ ወደ ከተመ መዘዋወር ይኖርባቸዋል። አሁን በአገራችን የምናየው ሁኔታ ይህ ነው። የጠበቅነው ግን መንግስቶቻችን ችላ ያሉት የመሬት መጥበብ ደርሷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎች ለአንድ ወራሽ ብቻ የሚበቃ መሬት ነው ያላቸውና ሌሎች ልጆቻቸው ወደ ከተማ እየፈለሱ ነው። አሁን ያለውን ታላቅ የገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት ይህ ነው ምክነያቱ። ለ40 ዓመት የተጠራቀመ ፍልሰት ነው አሁን ባንዴ የሚታየው። ግና ይቀጥላል።

ከዐምዴ ጋር እንቀጥል። ዐምዴ እግዚአብሔር ይባርከው እንጂ ጎበዝ ገበሬ አይደለም። ሙያውም ፍላጎቱም የለውም ግን ቤተሰቡን ለማስተዳደር ብሎ ያርሳል። ጎረቤቱ ገመቹ ግን እጅግ ጎበዝ ገበሬ ነው። የግብርና ንግዱን ማስፋፋት ይፈልጋል። ግን በመሬት ፖሊሲው ምክነያት እንዴት አድርጎ ተጨማሪ መሬት ይግዛ። ዐምዴ በደስታ መሬቱን ይሸጥለት ነበር ገመቹም ችሎታውን ተማምኖ ጥሩ ዋጋ ይሰጠው ነበር ግን አይፈቀድም። ስለዚህ የሚፈቀደውን አደረጉ ገመቹ ከዐምዴ የተወሰነ መሬት በየዓመቱ እየተከራየ ማረስ ጀመረ። ገመቹ ጉድጓድ መቆፈር ዛፍ መትከልና ተመሳሳይ የረዥም እቅድ ስራዎችና ኢንቬስትሜንቶች ማድረግ ይፈልጋል ግን መሬቱ የሱ ስላልሆነ ኪራዩም በየዓመቱ የሚታደስ ስለሆነ ስለረዥም እቅዶች ማሰብ አይችልም። ገመቹ ከሌሎች ጎረቤቶቹ ተጨማሪ መሬት ገዝቶ ስራውን አስፋፍቶ ምናልባት በትራክተር ማረስ፤ ሙያውንም ማዳበር፤ ስለ ፍራፍሬ ማምረት መማር፤ ወዘተ ያልማል። ግን ችሎታ ቢኖረውም በመሬት ፖሊሲው ምክነያት ምኞቶቹን በተግባር መዋል አልቻለም።

ገመቹ ከዐምዴ በተከራየው መሬት 20 ኪንታል በሄክታር ጠፍ ያመርታል። ዐምዴ 10 ነበር የሚያመርተው። ገመቹ የዐምዴ መሬት ሙሉ በሙሉ ሰባቱንም ሄክታር ገዝቶ ጠፍ ቢተክልበት ኖሮ በዐምዴ 70 ኪንታል የሚያበቅለው መሬት በገመቹ እጅ 140 ኪንታል ያበቅል ነበር። የአካባቢው የምርት መጠን ይጨምር ነበር። ገመቹ ደግሞ የሚያገኘውን ትርፍ ተጠቅሞ መሬቱ ላይ ኢንቬስት አድርጎ የግብርና ንግዱን የምርት መጠኑን ይበልጥ ያሻሽል ነበር። የአካባቢው የጠፍ ምርት ይጨምር ነበር የጤፍ ዋጋ ደግሞ ይቀንስ ነበር። ዐምዴ ከተማ ገብቶ ጠፍ በመጠነኛ ዋጋ ያገኝ ነበር።

ገመቹ ላይ የደረሰው የስራ ክለላ ወይም የማስፋፈትና ማደግ ክለላ የኢትዮጵያ መንግስታት በአገሪቷ ገበሬዎች ላይ ያሳደሩት አሳዛኝ ድርጊት ነው። ገበሬዎች ስራቸውን እርሻቸውን ንግዳቸውን እንዳያሰፋፉ በማገድ መንግስት የገበሬዎቻችን «የሰው አቅም» (human capital) አፍነዋል። ይህ የኤኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የሥነ ልቦና የፖለቲካ የማኅበራዊ ተጽዕኖ ገበሬዎች ላይ አሳድሯል። ከሁሉም የግል ነጋዲዎች ተለይተው ገበሬዎች ነፃነት እንዳይኖራቸው ንግዳቸውን ማስፋፋት እንዳይችሉ ተደርገዋል። በዚህ ምክነያት በሙያ ችሎታም በሙያ ትምሕርትም እንዳይሻሻሉ ተደርገዋል። እንደነበሩት እንዲቆዩ ተደርገዋል። እስቲ አንድ ሜካኒክ ስራውን ንግዱን ከማስፋፋት በህግ ቢከልከል እናስበው። ከአንድ መኪና በላይ የሚችል ቦታ ሊኖርህ አይችልም ቢባል። ይህ ሜካኒክ መቼም የችሎታውን አቅም ሳያሟላ ይቆያል። ወይም አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር ስራ መቀየር አትችልም ከአንድ ርዕስ ውጪ ጥናት ማካሄድ አትችልም ቢባል። ይህ መምህር በሙያው የተም አይደርስምና እራሱን ለማሻሻል አይጥርም። ስራውም እየሰለቸው ይሄዳል። ስለዚህ የመሬት ፖሊሲው ለገበሬዎች ኮምዩኒዝም ለሌሎች ካፒታሊዝም ነው ያደነገገው።

ይባስ ተብሎ መንግስቶቻችን የመንግስት ያልሆኑት ድርጅቶችም (ንጂኦ) ገበሬዎችን ወደታች አድርገው በንቀት ይመለከታሉ። እንደ ሞግዚት የሚያስፈልጋቸው ደንቆሮች ያይዋቸዋል። ከላይ እንዳልኩት ይህ የሆነው ገበሬዎች አቅማቸውን እውቀታቸውን ከማሻሻል ስለተገደቡ ነው። መንግስት እራሱ በነፃነት እንዳይሰሩ ስለከለከላቸው ነው። እንደ ጥሩ ኮምዩኒስቶች መንግስት ዋናውን የምርት ግበዓት የሆነውን መሬት አፍኖ ሌሎችን ግብአቶች እንደ ምርጥ ዘር ማዳበርያ ተባይና አረም ምጥፍያ የ«ኤክስቴንሽን» ትምሕርት ወዘተ በመጨመር የአገሪቷ የምርት መጠንን መጨመር ሞከረ። ግን አልሰራም።

ዛሬም በኢትዮጵያ የሰብል መርት በሄክታር ዝቅተኛ ነው። የምግብ ዋጋ ከሌሎች ታዳጊ ዓገሮች ውድ ነው። ወተት እንቁላል ቂቤ ሥጋ ማር ከአደጉ አገሮች ይልቅ ኢትዮጵያ ይወደዳሉ። የሰብል ዋጋ ውድ ቢሆንም የግብርና የንግድ ክፍል ተስፋፍቶ ያለውን ፍላጎት በአግባብ ማስተናገድ አልቻለም። ፈላጊ እየበዛ ሲሄድ አቅራቢ በቂ ማቅረብ አቅቶታል። ገበሬው ኢንቬስት ማድረግ አልቻለም። ለዚህ ነው የእህል የምግባ የዋጋ ግሽበቱ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሆነውና መንግስትን የሚያስጨንቀው።

ወደ ዐምዴ እንመለስ… ኢትዮጵያ በ10 ዓመት አንዴ የሚደርስባት ድርቅ መጥቶ የዐምዴ ልጆች በአንድ ሄክታሮቻቸው በጣም አነስተኛ መርት ያገኛሉ። ዐምዴ ሰባቱን ሄክታር በሚያአርስበት ጊዜ ድርቅ ቢኖርም የሰባት ሄክታሩ ምርት ብዙ ስለነበር ለድርቅ ጊዜ በቂ የተከማቸ እህል ነበረው። አሁን ግን የዐምዴ ልጆች በአንድ ሄክታር እጅ ወደ አፍ ስለሚኖሩ የአንድ ዓመት ምርታቸው ከቀነሰ በቂ አይኖራቸውም። ስለዚህ ሰባቱም የዐምዴ ልጆችና ቤተሰቦቻቸው ወደ ምግብ እርዳታ ተሸጋሸጉ።

ታሪኩ በዚ ይጠቃለላል፤ የህዝብ ቁጥርን ባልተጠበቀና በኢተፈትሮ ሁኔታ መናር አሁን ያለውን ታላቅ የገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት ዝቅተኛ «የሰው አቅም» (human capital) በትለይ የግብርና ሙያ በገጠር ቦታዎች ዝቅተኛ የእርሻ ምርት መጠን ከፍተኛ የእህል የምግባ ዋጋ ግሽበት የምግብ ዋስትና እጥሮትና ረኃብ። ሁሉም ችግሮች ብያንስ በከፊሉ የ1968 የመሬት አዋጁ ውጤቶች።

የዚህ ፖሊሲ ጎጂ ውጤቶች ያልበሰሉ ጸንፈኛ የፖለቲካ ልሂቃን በችኩልነታቸው አገሪቷ ላይ ሊያመጡ የሚችሉትን ጉዳት ያሳያል። ከጽንፈኝነት መካከለኛውን መንገድ መያዝ ይሻላል። የዛሬም ግዥዎቻችን ከዚህና ሌሎች ታሪኮች ተምረው ሌላውን ጸንፈኛ የአገራችን ፖሊሲ የጎሳ አስተዳደርን እንደገና ቢያስቡበት ይሻላል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!