Showing posts with label neocolonialism. Show all posts
Showing posts with label neocolonialism. Show all posts

Sunday, 10 February 2019

በ«ቤተሰብ ምጣኔ» ስም የሚፈጸመው ጉዳት



 

በ«ቤተሰብ ምጣኔ» ስም በአማራ ክልል እየተፈጸመ የነበረው ማህበረሰባዊ ጉዳት ይህ ደብዳቤ / መመርያ ይገልጻል። አንብቡት።

ከዚህ ደብዳቤ የምንረዳው ዋና ነገሮች እነዚህ ይመስሉኛል፤

፩፤ የመጀመርያ ነጥብ የድርጅቱ አንዱ ግብ (target) የወሊድ መቆጣጠርያ የሚጠቀሙ ሴቶች ቁጥር መጨምር እንደሆነ ግልጽ ያደርጋል። እነዚህ ግቦች የሚመነጩት ደግሞ ከጤና ጥበቃ ቢሮ ብቻ ሳይሆኑ በዋና ደረጃ ከለጋሾቻቸው ማለትም ከተለያዩ የውጭ ሀገር ለጋሾች እንደ ኢዩ እና ዩኤሴይድ (አንድ ምሳሌ፤ http://www.healthpolicyproject.com/index.cfm?ID=country-Ethiopia)። ይህ ማለት የክልሉ መንግስት፤ የጤና ጥበቃ ቢሮ ሃላፊዎች፤ እና የጤና ቢሮ በታቾች ለገንዘብ ብለውም እንደዚህ አይነት ጉዳት የሞላው ፖሊሲ ፈጽመዋል። አዲሱ ቅኝ ግዛት እንዲህ ነው የሚሰራው።

፪፤ እነዚህን ግቦች ለመምታት በጣም ግልጽ የሆኑ ስህተቶች ተፈጽመዋል። ለምሳሌ በሁለተኛ፤ ሶስተኛ እና አምስተኛ ነጥቦች እንደሚገለጸው በረጅም ጊዜ መቆጣጠርያ ላይ የማይሆን ትኩረት ተደርጓል። የጤና ተቋሙ ገንዘቡን ለማምጣት ጸንፈኛ የሆነ አቋም እና ፖሊሲ ለማራመድ ወደኋላ አላለም። ለምሳሌ ሁሉንም ሴቶች የወሊድ መቆጣጠርያ ተጠቃሚ የማድረግ ታርጌት እና ፖሊሲ ከጫፍ የያዙ ጽንፈኝነት በቀር ሌላ ቃል ሊሰጠው ያችልም።

፫፤ ነጥብ ሰባት የጤና ጥበቃ ቢሮው እንደ ተቋምም ሰራቶኞቹም ለገንዘብ ብለው የተለያዩ የወሊድ መቆጣጠርያ እንደሚያስተዋወቁ እና ሴቶች ላይ እንደሚጭኑ በግልጽ ያስረዳል። ፖሊሲው የሚመራው ለህዝቡ ጤንነት ምን ይበጃል በሚለው መርህ ሳይሆን ምን ገንዘብ / ጉቦ ያመጣልናል በሚለው ነው። ስለዚህ የፖለሲው እና የተግባሩ አለቆች እና ወሳኞች የውጭ ሀገር ለገሾች እና የወሊድ መቆጣጠርያ ሳጭ ኩባኒያዎች ናቸው ማለት ነው።

፬፤ ይህ የብሉሹ እና የበሰበሰ አሰራር የጤና ተቋሙ ሚስኪን ሴቶች ላይ የቅስቀሳ ዘመቻ እያካሄዱ የሴቶቹ ስነ ልቦና እና ጤና የሚጎዳ ነገሮች እንዲያደርጉ እንደሚያደርግ ነጥብ ስምንት ያረጋግጣል። የጤና ጥበቃ ቢሮ ቢሮው ገንዘብ እንዲአገኝ፤ ሰራተኞቹም ለግላቸው ገንዘብ / ጉቦ / ስኮላርሺፕ እንዲያገኙ ጉዳት እንደሚፈጽሙ ግልጽ ነው።

፭፤ የአማራ ህዝብ ልሂቃኑን በደምብ መፈተሽ እና ማስተካከል እንዳለበት ግልጽ ነው። ከላይ ደጋግሜ የገንዘብ ሚና እንዴት የአማራ ጤና ጥበቃ ቢሮ የውጭ ሀገር ለጋሾች እና የመድሃኔት ሻጮች መሳርያ እንዲሆን እንዳደረገ ገለጽኩኝ። ገን ከዚም አልፎ ተርፎ በርካቶች በርዕዮት ዓለም ደረጃ በዚህ ጸንፈኛ ፖሊሲ የሚያምኑ የአማራ «የተማሩ» ልሂቃን አሉ። ከሁሉም በላይ ይህ ነው የሚያሳዝነው። ልሂቃኖቻችን በበአድ አስተሳሰብ አዕምሮአቸው ተገዝቷል። ወደ ኋላ ብለው የጠጡትን ፕሮፓጋንዳ መፈተሽም አይችሉም። የህዝብ ቁጥር ምጣኔ ከሌላ አንጻር መመልከትም አይችሉም። ህዝቡ እራሱ የራሱን የቤተሰብ ምጣኔ መወሰን እንደሚችል፤ ሃብታም በሆነ ቁጥር እራሱ የሚወልደውን ቁጥር እንደሚቀንስ፤ የቤተሰብ ምጣኔ የህዝብ ቁጥርም መቀነስ ጉዳይ አለመሆኑ፤ ወዘተ መገንዘብ የማይችል ልሂቃን ተፈጥሯል። የህዝቡን ስነ ልቦና እና ማህበረሰባዊ እሴቶች የማያውቅ ልሂቃን ተፈጥሯል። በዚህ ላይ ብዙ ስራ ሊሰራ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

Thursday, 10 January 2019

አቶ አበረ አዳሙን አዳምጡት!


https://www.youtube.com/watch?v=43jAqrS4F_g

«(አብዛኛው ያየኋቸው የሀገራችን ፖለቲከኞች) የሚናገሯቸው እና የሚያስተላለፉት መልእክቶች ተመሳሳይ ሆነው ከአንድ መጸሃፍ የተቀዱ ሆነው ግን ደግሞ ምን እንደሚአላያቸው በማይገባህ መንገድ እርስ በርሳቸው ሲለያዩ ታያለህ።»

«ከነ አቢይ ቡድን (ቲም ለማ) በቀር የኢትዮጵያን ተጭባጭ ሁኔታ እና ታሪካዊ እሴቶቿን የተረዳ ያለ (ፖለቲከኛ) ያለ አይመስለኝም።»

Tuesday, 1 January 2019

የአማራ «ልሂቃን» እና የአማራ ህዝብ ቅነሳ

ማንም በማይክድበት ደረጃ በአማራ ክልል የተካሄደው የወሊድ ቅጥጥር (በተዘዋዋሪ የህዝብ ቁጥር ቅነሳ) ዘመቻ ከሁሉም ክልል በላይ በደምብ «ተሳክቷል»። ማለት የህዝብ ቁጥር ጭማሬ በደምብ እንዲቀንስ አድርጓል።

ይህ ለኔ እጅግ የሚያሳዝን ክስተት ነው። የአማራ ክልላዊ መንግስት በአማራ ልሂቃን ተደግፎ ያልተሟላ እና ኋላ ቀር የህዝብ ብዛት መጥፎ ነው የሚል ፍልስፍና ተሸክሞ የአማራ ክልልን ህዝባዊ አቅምን መንምኖታል። ህዝቡም በመርፌ የሚወገ የወሊድ መቆጣጠርያ መድሃኔት በmarketing እና coercion ኃይል እንዲጠቀም በማድረግ ከባህሉ፤ ከጤንነቱ እና ከራሱ (ከህሊናው) ጋር እንዲጣላ አድርጓል። ሌሎቹ ክልሎች ይህንን መርዛማ አካሄድ ላለመከተል ሲታገሉ የአማራ መንግስት እና ልሂቃን አዋቂ እና ተምረናል ባዮች ሙሉ በሙሉ capitulate አደረጉ። እውነትም «የተማረ ገደለን» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/12/blog-post_7.html)።

ዛሬ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር የህዝብ ብዛት አይደለም። ከመሰረታዊ ችግሮች መካከል የመሬት ፖሊሲው (መሬት የመንግስት መሆኑ) እንደ ችግር ይበልጠዋል። የህዝብ ብዛት እንዲህ እንዲጨምር ያደረገው ገበሬው መሬቱን ሽጦ ወደ ከተማ መምጣት ስለማይችል የኢትዮጵያ ህዝብ ለ40 ዓመታት artificially ገጠር እንዲቆይ ተደርጓል። ገበሬው በነጻነት መሬት መሸጥ መለወት ቢችል ኖሮ ዛሬ 80-85% የገጠር ነዋሪ ከሚሆን ወደ 60% ደርሰን ይሆን ነበር። የገጠር ህዝብ ስድስት ልጅ ይወልዳል የአዲስ አበባ ህዝብ ሁለት ልጅ ይወልዳል። 40% የከተማ ነዋሪ ሆኖ ከስድስት ፋንታ ሁለት ልጅ በአማካኝ ሲወልድ የህዝብ ቁጥራችን እንዲህ አይጨምርም ነበር። ስለዚህ ልክ እንደ ቻይና በማኦ ዘመን የመሬት ፖሊሲው ነው የዝብ ቁጥራችንን artificially እንዲንር ያደረገው። አሁን ታድያ መሰረታዊ ችግሩን አምኖ ለመቅረፍ ከመሞከር symptomኡን ለማከም እንሞክራለን። ይህ ታላቅ ጥፋት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ አንድ ህዝብ የሚወልደውን ልጅ መጠን እራሱ የራሱን ጥቅም አይቶ በholistic እና organic መንገድ ቢቆጣጠር ነው የሚሻለው (በስነ ልቦና እና ማህበራዊ ሰላም ደረጃ)። ከተሜ ሲሆን፤ ቆይቶ ሲያገባ፤ ወዘተ እራሱ አስቦ መወሰን ይጀምራል። በመንግስት እና ኤንጂኦ ኃይል በግፊት እና ጫና በቅኝ ግዛት መልክ ከተመጣበት ችግሩን በደምብ ሳያውቀው ወደ አደገኛ የወሊድ ቁጥጥር ይገባበታል። ከዛ ዛሬ የምናየው backlash ይመጣል። ሴቶች መውለድ አቃተን ይላሉ። ልጆች ጠፉ ይባላል። ወዘተ። የብአድ መፍትሄ ብዙ ጊዜ መፍትሄ አይደለም።

ሶስተኛ፤ መላ ኢትዮጵያም አማራም ለህዝብ ቁጥር እድገት በቂ ቦታ አላት። አልተጨነቀችም። ሌሎች የመንግስት ፖሊሲዎች ናቸው ችግሮቹ። አልፎ ተርፎ አንዱ ላለፉት አመታት የኤኮኖሚ እድገት ያመጣው ግበአት የህዝብ ብዛት ነው። የ100 ሚሊዮን ገበያ እና ሰራተኛ ኃይል ቀላል አይደለም። ጥቅም አለው። ይህ በአማራ ክልል እና ልሂቃን የታሰበበት አይመስለኝም። ውሳኔዎችን በ one track mind ሆነው ነው የወሰኑት።

አራተኛ፤ በዛሬው የጎሳ ችግር ሁኔታ ዴሞግራፊ ወሳኝ ነገር ነው። የአማራ ክልል ህዝብ ቁጥር ቀነሰ ማለት በአንድነት የሚያምነው ህዝብ ቁጥር ቀነሳ ማለት ነው (አማራው ከሞላ ጎደል እንዳለ ከአንድነት ኃይሉ ውስጥ ስለሆነ)። ዛሬ ይህን ሃቅ መካድ አይጠቅምም። ይህ ፖለቲካዊን ይቀይራል። መሃሉን ያደክማል ጎሰኝነትን የሚያራምድ ፖለቲካን ያጠነክራል። ፖለቲካው ይዛባል። የአማራ ክልል መንግስት እና ልሂቃን ይህን እንደ አንድ ግበአት አለማሰባቸው እጅግ ያሳፍራል። ወይ ክፋት ወይንም ጅልነት ነው፤ ይቅርታ አድርጉልኝ። ነባራዊ እውነታን አለመቀበል ነው። ለጎሳ ፖለቲካ ተብሎ የህዝብ ቁጥር እንዲንር ይደረግ ማለቴ እንዳልሆነ መችሄስ ግልጽ ይመስለኛል። ግን ሁሉ ነገር መታየት አለበት እና ሚዛናዊው መንገድ መከተል አለብን ነው የምለው።

መፍትሄው ምንድነው? የወሊድ መቆጣጠርይ ይከልከል ወዘተ አይነት የማይሆን ነገር አደለም የምለው፤ ከአንዱ ጸንፍ ወደ ሌላው! መንግስት ለወሊድ መቆጣጠርያ marketing እና እርዳታ ይተው ነው የምለው። በዚህ ዘርፍ የሚሰሩ ኤንጂኦዎች ይከልከሉ። የታወቁ ጉዳታቸው ያነሰ የወሊድ መቆጣጠርያ መንገዶች ይሸጡ ግን ህዝቡ ላይ አይጫኑ። ህዝቡ አለ ጫና እና ግፊት በorganic እና holistic መንገድ የራሱን ግላዊ ውሳኔ ያድረግ። አለ ጫና እና ግፊት። ይህ መፍትሄ ሁለት ግቦች ይኖሩታል፤ 1) የህዝቡ ስነ ልቦና እና የማህበረሰቡ ስነ ልቦና ይገጋጋል እና ይጠበቃል እና 2)  የህዝብ ቁጥር ጭማሬ ከፍ ይላል፤ ወደ naturally መሆን ያለበት ደረጃዎች ይሄዳል እና ከሌሎች ክልሎች ብዙ አያንስም። በአጭሩ የክልሉ ፖሊሲ ከጫፍ ወደ ሚዛን ይመለሳል ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/04/blog-post_6.html)።

Saturday, 29 December 2018

ልሂቃኖቻችን ዛሬም የምዕራባዊነት እስረኞች…

እምብዛም ልሂቃን እና ምሁራኖቻችን ዛሬም በምዕራባዊነት አምልኮ የተለከፍን ነን። እንግሊዝን፤ ጀርማንን፤ አሜሪካንን ገልብጦ እንዳለ ወደ ኢትዮጵያ ከማምጣት ውጭ ሃሳብ የለንም። ምናልባት የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ለሙሉ እንደ ምዕራብ ሀገር ለመሆን ዝግጁ ባለመሆኑ ጉዞውን ቀስ በ ቀስ እንጀምራለን እንል ይሆናል። ግን ግቡ አንድ ነው፤ ኢትዮጵያን እንደ «ፈረንጅ» ሀገር ማድረግ ነው።

ይህ አካሄድ ለኔ unimaginative ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን የማይሆንም ነው ብዬ አምናለሁ። የኢትዮጵያዊነት ምሁራ ዶናልድ ሌቪን እንደሚያስታውሱን፤
"The vitality of a people springs from feeling at home in its culture and from a sense of kinship with its past. The negation of all those sentiments acquired in childhood leaves man adrift, a prey to random images and destructive impulses…"
ለኔ፤ በግሌ፤ ኢትዮጵያን እስክስታ፤ እንጀራ፤ ወዘተ ያላት ፈረንጅ ሀገር ማድረግ ትርጉም የለውም። ማንነትን ማጣት ነው። ባህላዊን እሴቶችን ማጣት ነው። አብሮነትን አጥተን ብጨኞችን መሆን ነው። ፍቅር አጥተን ነግ በኔዎች መሆን ማለት ነው። እምነት አጥተን እምነት የለሾችን መሆን ማለት ነው። ለኔ ይህ ትሩጉም የለውም።

ግን ልሂቃን እና ምሁራኖቻችን የሀገር ወጋችን ገብቷቸው አክብረውት መራመድ ያቃተን ምክንያት ይገባኛል። በመጀመርያ ወጋችንን በደምብ አላከበርንም። በጃንሆይ ዘመን የነበረው የፍትህ እጦት እና ጭቆና (በምንም ደረጃ ቢሆንም) የመጀመርያ ሀገር በቀል ፈረንጆቻችን እንዲወለዱ አደረገ። በሃይማኖት ተቋሞቻችን የነበረው ግብዝነትም እንዲሁ ጥላቻ ፈጠሮ ምሁራን ወደ ማርክሲዝም እንዲሄዱ ጋበዘ። ይህ ለምሁራኖቻችን ፈረንጅ አምላኪነት አንዱ ምክንያት ነው።

ሌላው ምክንያት ዘመናዊ ትምሕርት አሰጣጡ ነው። ሶሻል ሳየንስ ተማሪዎቻችን ከሞላ ጎደል የሚማሩት የዘመኑ ርዕዮት ዓለም ነው። ርዕዮት ዓለሙ እንደ እውነት ነው የሚሰበክላቸው አብዛኞቹ አለ ጥያቄ ይቀበሉታል። እንደ ምሁራን መቀጠል ከፈጉ ደግሞ ምርጫ የላቸውም። ከዘመኑ ርዕዮት ዓለም የተለየ አስተሳሰብ በባልደረቦቻቸው እንዲናቁ እና እንዲዘለፉ ነው የሚያደርጋቸው። ስራቸውንም ያጣሉ ማንም ዩኒቨርሲቲ ወይም ሌላ ተቋም አይቀጥራቸውም። ስለዚህም የዘመኑን ርዕዮት ዓለምን እንደ ጣኦት ያመልኩታል።

ሶስተኛው ምክንያት የኢትዮጵያ ነባራዊ ችግሮች ናቸው። አስተዋይ ያልሆነ ሰው ሃብታሙ እና ምቾት የተሞላውን ምዕራብ ዓለም ከኢትዮጵያ ጋር አወዳድሮ ምዕራብ ነው ትክክል ይላል። ማስተዋል የማይችል። ጠልቆ ማሰብ እና ማየት የማይችል። መሳደቤ አይደለም፤ እኔም ወደ እንደዚህ አይነት ቀላል ድምዳሜ ተስቤ አውቃለሁ።

ስለዚህ ዛሬ በኢትዮጵያ ታላቅ የምሁራን እና ልሂቃን እጥረት (deficit) አለ። እምብዛሙ ውጭ ሀገር የሚያየውን ፎርሙላ ወደ ሀገር ማምጣት ብቻ ነው የሚታየው። ማንነቱን አጥቷል። ማርክሲዝም ይሁን፤ «ሊበራሊዝም» ይሁን፤ ሶሻሊዝም ይሁን፤ «ማርኬት ኤኮኖሚ» ይሁን፤ ሴኩላሪዝም ይሁን፤ ፌሚኒዝም ይሁን፤ ዴሞክራሲ ይሁን ለምሁራኖቻችን ጣኦት ሆነዋል። ለምን ኢትዮጵያዊነት እንደሚያሰኝንም አላውቅም። አሜሪካዊ መሆን ይሻለናል ማንነታችን አሜሪካዊ ከሆነ።

ፋንታሁን ዋቄ እንዳለው ታላቅ paradigm shift ያስፈልገናል። አቢይ አህመድም ደጋግመው እንደሚሉት የሀገራዊ እሴቶቻችንን ተምረን አቅፈን እንራመድ። እሴቶቻችንን እንፈተሽ እና እናሟላ። አንድ አጭር ምሳሌ ልስጥ፤ ሃይማኖታዊ መቻቻል (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/04/blog-post_3.html)። የሀገራችንን ወግ የማያውቅ የሀገራችን ሃይማኖቶች መቻቻልን አያውቁም ይላል። ወይን መቻቻል የሚችሉት መሰረታቸውን ትተው ባህል ብቻ ሲሆኑ ነው ይላል። ግን ከላይ እንደጠቀስኩት ጽሁፌ በኦርቶዶክስ ክርስትና ለምሳሌ ከመቻቻል አልፎ ፍቅር ነው ዋናው መርህ! ሙስሊሙን መቻል (አሉታዊ ነገር ነው tolerate) የለብኝም መውደድ ነው ያለብኝ! ግን አብዛኞች ምሁሮቻችን መቻቻልን ከምዕራባዊነት እና ሴኩላሪዝም ያያይዙታል! ይህ ትንሽ ምሳሌ ነው። ወጋችንን እንፈትሽ። የምዕራብ ርዕዮት ዓለም እስረኞች አንሁን። ለራሳችን ማንነት ክብር እና ፍቅር ይኑረን። እራሳችንን እንወቅ።

Thursday, 11 October 2018

የፌደራል መንግስት ዘመን አቆጣጠራችን (calendar) ይቀየር ይላሉ አቶ አብዱ አሊ ሂጅራ?!

ብስመ አብ! የፌደራል መንግስት ዘመን አቆጣጠራችን (calendar) ይቀየር ይላሉ አቶ አብዱ አሊ ሂጅራ?!

ከመአዛ አሸናፊ ጋር 10 ቀን በፊት ያደረጉትን ቋሚ ቃለ ምልልስ አሁን አዳመጥኩት (https://www.youtube.com/watch?v=s-ve5RiImNc)። ባጭሩ የቀን መቁጠርያችን እንደ ባህል እንጠብቀው፤ ለምሳሌ አዲስ አመትን አሁን እንደሚደረገው በመስከረም 1 ይከበር፤ ግን official ወይንም የመንግስት የቀን አቆጣጠር ወደ «ፈረንጁ» (Georgian calendar) አቆጣጠር ይቀየር። ምክነያቱ አብዛኛው ሀገራት በፈረንጁ አቆጣጠር ስለሚጠቀሙ በኢትዮጵያ አቆጣጠር መጠቀም ለበርካታ ስራ አይመችም። ሁልጊዜ ከአንዱ ወደ አንዱ መቀየር (convert) ስራን ያስተጓድላል አሉ አቶ አብዱ አሊ።

ይህ በብዞዎች ተቀባይነት ያለው አስተሳሰብ ነው። ግን ትክክል አይደለም… አይመስለኝም። ማንኛውም ትውፊታዊ ነገር እንደ ቀን መቁጠርያ እንደ «ባህል» ብቻ ይዘን በስራ ላይ ካልዋለ ቀስ ብሎ ይጠፋል! ለዚህም ነው ሀገራት የራሳቸውን ቋንቋ የሚጠብቁት። ከጃፓንኛ ወደ እንግሊዘኛ መከያየር ከባድ ስራ ነው። አብዛኛው የቴክኖሎጂ ነክ ነገሮች በእንግሊዘኛ ናቸው። ሆኖም ጃፓን በጃፓንኛ ቀልቋል። ያን ሁሉ ቴክኖሎሂ ነክ ስራዎችም ሲሰራ በጃፓንኛ ነው ያደረጉት። ድሮ የኮምፕዩተር ስራ በሌላ ቋንቋ መስራት በጣም ከባድ በሆነበት ዘመንም በጃፓንኛ ነበር የሰሩት። የማንነት ጉዳይ ስለሆነ እንደ ባህል አልትውትም። ሰሩበት አሁንም ይሰሩበታል። ይህ አስተያየት ለቋንቋ ብቻ ሳይሆን ለቀን መቁጠርያም ይሆናል።

በተዘዋዋሪ ኤርትራ የመንግስት የቀን መኩጠርያውን ሲቀይር እጅግ አዝኜ ነበር። ውጤቱ ዛሬ እና ነገ ይታያል እነ እንቁጣጣሽም እየተረሱ ይሄዳሉ።

ትንሽ ቃል ስለ ሃሳቡ ጠቅላላ መንፈስ ልጻፍ… ጣልያን ሀገር ብትሄዱ ሰንበት ሱቅ መከፈት የለበትም፤ እንደነ «ዎልማርት» አይነት ግዙፍ ሱቆች ሊኖሩ አይገባም፤ አማዞን ገደለን ወዘተ ይባላል። እነዚህ ነገሮች በማህበራዊ ኑሮ (including social capital)፤ ግለኝነት እና ብቸኝነት (individiualism and loneliness)፤ የትናንሽ ከተማ እና ሰፈር ህልውና፤ ወዘተ ላይ ያላቸው ሚና ይተቻሉ። ሁሉን ነገር 'rationalise' ማድረግ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳትም እንዳሉእው ይታወቃል። በዚህ ምክንያት localism የሚባለው ርዕዮት ዓለም ባለፉት አስርት ዓመታት ወደ ልሂቃን መገናኛ ተመልሷል። ስለዚህ እንደዚህ አይነቱን ጉዳይ ላይላዩን ሳይሆን ጠልቀን መመርመር ይኖርብናል።

Wednesday, 21 March 2018

«ሴኩላሪዝም»

ትንሽ አመታት በፊት አንድ የመንግስት ስራተኛ የሆነ ዘመዴ የኦርቶዶክስ መዝሙር ከመስሪያቤት ኮምፕዩተሩ ላይ ማዳመጥ ክልክል እንደተደረገ ነገረኝ። ለምን ብዬ ስጠይቀው ክርስትያኑም ሙስሊሙም የሚፈልገውን መዝሙር፤ ስብከት፤ ትምሕርት እያዳመጠ እና ኮምፕዩተሩ ላይ ሥዕል እየለጠፈ የሰራተኞች እርስ በርስ ግጭት ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ተከለከለ አለኝ። የሚገርመው ነገር ግን 1) ከመስሪያቤቱ እንደዚህ አይነት ግጭቶች አልነበሩም እና 2) ክልከላው በተራ ትዛዝ ሳይሆን ከከፍ ያለ የአስተዳደር ደረጃ በመመርያ ምልክ የተላለፈ ነበር። የመመርያው ርዕስ ደግሞ «ሴኩላሪዝም» ነበር።

ይህን ታሪክ ስሰማ እጅግ አዘንኩኝ። መቼ ነው መንግስቶቻችን፤ ምሁሮቻችን እና ልሂቆቻችን የምዕራብ ዓለም ርዕዮት ዓለምና ፍልስፍና ይዘው አገራችን ላይ መጫን የሚያቆሙት? ካለፉት የ100 ዓመታት ታሪካችን አይማሩምን?

እስቲ «ሴኩላሪዝም» ባጭሩ ምን እንደሆነ እንመልከት። «ሴኩላሪዝም በዓለማችን እግዚአብሔር የለም/አይሳተፍም ብሎ ማሰብ ነው»። ሴኩላሪዝም እግዚህብሔር ሊኖር ላይኖርም ይችላል ግን ከዓለማችን ከሕይወታችን ከለት ኑሮአችንም አይሳተፍም የሚለው አመለካከት ነው። እግዚአብሔር ካለ እዛው ከዙፋኑ ወይንም ገነቱ ተቀምጦ ይመለከተናል። በሃይማኖት እና በእግዚአብሔር በግል ምርጫችን ልናምንባቸው የምንችል የእምነት ሥርዓቶች ናቸው። በሀሳብ ደረጃ ነው የምናምንባቸው ካላሰኘን ደግሞ ከሀሳባችን እናስወግዳቸዋለን!

ይህ አስተሳሰብ በተለያየ መንገድ ወደ ክርስትያን የሆነውን አስተሳሰብ ገብቷል። «ዓለማዊ» እና «መንፋሳዊ» የምንላቸው ቃላት በተሳሳተ መንገድ እንጠቀማለን። ዓለማዊ ስንል ስራችን፤ ትምሕርታችን፤ ገበያችን፤ ንግዳችን ወዘተ ነው። እግዚአብሔር እነዚ ነገሮች ውስጥ እንዳለ አናምንም። ስለዚህም ነው በነዚህ የህይወት ዘርፎቻችን ኢ-ክርስትያናዊ ነገሮች እያደረግን እያለን አማኞች ነን የምንለው። እሁድ እሁድ ግን ቤተ ክርስትያን ሄደን ወደ መንፈሳዊስ ዓለም እንሸጋገራለን። እዛ ጨዋ ነን፤ ጥሩ ስነ መግባር አለን፤ ጭንቀቶቻችንን አስተንፍሰን ወደ ዓለማችን እንመለሳለን።

ይህ ግን የውሸት ክርስትና ነው። በእምነታችን እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ በሁሉም ነገር አለ። «እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም። ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር።» ኤር 23:23-24።

ስለዚህ ትምሕርት ቤት ብሄድ፤ መስሪያ ቦታ ብሄድ፤ እርሻዬ ላይ ብሆን፤ ትራንስፖርት ላይ ብሆን፤ መጠጥ ቤት ብሄድ፤ በሁሉም ቦታ እግዚአብሔር አለ። ሕይወታችንን እግዚአብሔር ያለበትና የሌለበት ብለን ልንከፋፍለው አንችልም። በሁሉም ቦታ በሁሉ ደቂቃ ከኛ ጋር ነውና።

ይህ የሚያሳየን የሰው ልጅ ክርስትያንም ሴኩላሪስትም አብሮ ሊሆን አይችልም። ብዙዎቻችን ወደዚህ ስህተት ብንገባም ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ለክርስትያኖች እግዚአብሔር ልኬት የለውምና። በተጨማሪ ሴኩላሪዝም እግዚአብሔርን ከለት ኑሮአችን ማጥፋት ስለሚፈልግ የክርስትና ተቃራኒ ብቻ ሳይሆን ጠላት እንደሆነ ግልጽ ነው።

«እናንተ ኦርቶዶክሶች፤ ሙስሊሞች፤ ፕሮቴስታንቶች አብሮ መኖር አትችሉም። ስለዚህም (እግዚአብሔራን ተክቼ!) ከላያችሁ ሆኜ አስተዳድራችኋለሁ» ይላል ሴኩላሪዝም / ሴኩላሪስቱ። «እኔ ነኝ ስልጡኑ፤ ከማንም ጋር የማልጋጨው፤ ከሁሉም ጋር የምግባባው፤ ሁሉንም የማከብረው» ይላል። እውነቱ ግን ሴኩላሪስቱ እንደዚህ ሲል ሁሉንም በሰላም ለመጠበቅ ሳይሆን አላማው ይህን አስመስሎ «እግዚአብሔር የለም» የሚባለውን ሃይማኖትን ለማስፋፋት ነው። እግዚአብሔር ከአዕምሮአችን ብቻ ነው ያለው እንጂ ከስራ ቦታችን፤ ገበያ ቦታችን፤ መንገዶቻችን፤ ሚዲያዎቻችን፤ ከለት ኑሮአችን የለም ብለን ካመንን ቀጥሎ እግዚአብሔር የትም የለም ማለት የሚቀጥለው ቀላል እርምጃ ነውና!

በተጨማሪ እግዚአብሔር ከለት ኑሮአችን ከሌለ የማህበረሰብ የአገራችን ድንጋጌዎች ከየት ሊመጡ ነው? ከሴኩላሪዝም ርዕዮት ዓለም ከ«እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖት ሊመጡ ነው! አያችሁ ሴኩላሪዝም እራሱን ገለልተኛ አድርጎ እንዴት «እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖትን ሰተት ብሎ እንደሚያሰፍን።

ኢትዮጵያ የሃይማኖት አገር ናት። ታሪካችን ትውፊታችን ከዚህ የተያያዘ ነው። ማንነታችን ይህ ነው። ሴኩላሪዝም ደግሞ የህን አፍርሶ «እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖትን ነው ማስፈን የሚፈልገው። ይህ ሂደት እንዴት እንደሚሰራ ለማወቅ የምዕራብ ዓለሙን ያለፈውን 400 መቶ ዓመት ታሪክ መመልከት ነው። ስለዚህ ሴኩላሪዝም ኢ-ኢትይጵያዊ እንደሆነ ተረድተን ወደ አገራችን ሰተት ብሎ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን። በተለይ ደግሞ ወደ ልባችን ሰተት ብሎ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን።

Thursday, 8 March 2018

ዴሞክራሲ

ስለ ዴሞክራሲ ብዙ ተጽፏል። በንደፈ ሐሳቡ ደረጃ ምንም መጨመር አልፈልግም። በዚህ ጽሁፍ አሁን ባለን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ዙርያ ስለ«ዴሞክራሲ» ያለን አመለካከት ምን ቢሆን ይበጀናል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ነው የምወደው።

እንደ እስክንድር ነጋ አይነቶቹ በርካታ (ጀግና) የነፃነት ታጋዮቻችን የችግራችን መፍትሄ ዴሞክራሲ ነው ይላሉ። በአንድ ወቅት እኔም እንደዚሁ ይመስለኝ ነበር። ግን ጉዳይ ከዛ እጅግ ውስብስብ እንደሆነ ተረድችያለሁ።

ዛሬ ባለን ህገ መንግስትና ጠቅላላ የመንግስታዊ አወቃቀር የነፃ ምርጫ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቢካሄድ ችግሮቻችን ይፈታሉ ብለን እንገመታለን? አሸናፊዎቹ፤ ተሸናፊዎቹ፤ ጦር ሰራዊቱ፤ የክልል መንግስታት ወዘተ ውጤቱን ተቅብለው ተስማምተው ይሰራሉ ብለን መገመት ኢንችላለን? አዲሱም መንግስት ሰላምና ፍትህ ያመጣል ወይም የፓርላማ ስልጣንና ኃይሉን ተጠቅሞ ግፍና ጭቆና ያሰፍን ይሆን? ህገ መንግስቱን ይቀየር የምንለውሳ? በቂ ድምጽ ካለን አናሳ ድምጽ ያላቸውን የራሳችሁ ጉዳይ ብለን በዚህ ድምጽ ኃይል እንቀይረውና አዲስ ህገ መንግስት እንጭንባቸው ይሆን? ዛሬ እነዚህ አይነቶቹ ከባድ ጥያቄዎች ጥሩና የተሟላ መልስ አላቸው ብዬ እርግጠኛ መሆን አልችልም። ለእነዚህ ጥያቄዎች በሚገባው መልስ ሳይኖረን ወደ ዴሞክራሲ የምንለው ምርጫ ከገባን ደግሞ አደጋ ነው የሚሆነው።

ስለዚህ እንደኔ እንደኔ በመጀመርያ ሰፊ ውይይት በተለያዩ ደረጃዎች ያስፈልጋሉ። የዚህ ውይይት ግብ በርካታ ባለጉዳዮቹ ከብዙሃን እስከ ልሂቃን የአገራችን ማንነትና ፖለቲካ ምን መምሰል አለበት በሚለው ጥያቄና መልስ አንድ ገጽ ላይ እንዲሆኑ ነው። ሰፊ ስምምነት እንድውል ነው። አሁን ያለንበት ደረጃ አገር መገንባት ላይ ነው። በህዝቡም በልሂቃኑም የፖለቲካ መተማመንና መሰረታዊ ስምምነት የለምና። ከላይ የጠቀስኳቸው አይነቶች መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎች እንኳን ሊመለሱ አልተጠየቁም አልተወያየንባቸውም። ይህን የውይይት ሂደት ሳንጨርስና መሰረታዊ ስምምነት ላይ ሳንደርስ ወደ ምርጫ መሄድ አደገኛ ይመስለኛል። እንደ ግብጽ፤ ኢራቅ፤ እና ሌሎች ምርጫ ያላቸው ወይም የነበራቸው ግን ሰላምና ፍትህ የሌላቸው አገሮች እንድንሆን አይፈለግምና።

እሺ፤ በርካታና አስፈላጊዎቹ ባለጉዳዮች አንድ ገጽ ላይ መሆናቸውና ስምምነት ላይ መድረሳቸው እንዴት ልናውቅ እንችላለን? አንዱ ዋና ምልክት የሚመስለኝ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በስል ማለት ነው። ጠንከር ያለ ተቃዋሚ ፓርቲ ከሌለ ወይም ፓርቲዎቹ በጎሳ ብቻ የተመሰረቱ ከሆነ ይህ ጥሩ ምልክት አይመስለኝም። ተመሳሳይ የሆኑ አቋም ያላቸው ተቃዋሚዎች የመዋኸድን ሂደት ለማሟለት ብቃት ከሌላቸው ጥሩ ምልክት አይሆንም። ይህን ያልቻሉ እንዴት አብረው መንግስት ይሆናሉ ወይም እንዴት የአስተዳደሩን ህግ ያከብራሉ? የጎሳ ፓሪቲ ብቻ ካለ ደግሞ እንዴት ነው ፖለቲካ ስረአቱ የማይቀረውን የጎሳ ውድድሩን በሰላም ማስተናገድ የሚችለው? አሁንም ከባድ ጥያቄዎች። እንደምናየው ወደ ምርጫ ከመግባታችን በፊት ብዙ ስራ አለ ቀድመሁኔታዎችም መሟላት አለባቸው።

ይህን ካልኩኝ በኋላ እስቲ ይህን ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ ዴሞክራሲ ቢኖር ሰላምና ፍትህ ይኖራል ማለት ነው? እስቲ አንድ አንድ እውነታዎች እንመልከት። በዓለም ታላቅ የሚባለው ዴሞክራሲ አሜሪካ ነው። በጦሩ ኃይል በርካታ የዴሞክራሲ አገርዎች በሰላም እጠብቃለሁ እሸከማለሁ ባይ ነው። ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አሜሪካ ወደ 20 ሚሊዮን ሰዎች በተለያዩ ጦርነቶች ገድሏል ይባላል። አጭር ትዝታ ያለን መቼም ስለ ኢራቅ፤ ሊብያ፤ ሶርያ እናውቃለን። ኢህአዴግ  ከዚህ ጋር ሲወዳደር መለአክ ነው ማለት ይቻላል! ግን አሜሪካ ለኑሮ ጥሩ አገር ነው። ገንዘብ አለ፤ ከሞላ ጎደል ፍትህ አለ፤ የተወሰነ ነፃነት አለ። ሁላችንም ወደዛ ለመሄድ እንሻለን። ግን ገንዘቡ ባይኖር በአሜሪካ ምን ይሆን ነበር?

ምናልባት አውሮፓ ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን ለምን አሜሪካን እንደ ምሳሌ ትጠቀማለህ ትሉ ይሆናል። ሰላማዊዋ ስዊድንሳ? እውንቱን ለመናገር የስዊድን የጦር መሳርያዎች በዓለም ዙርያ ምን ያህል ሰው እንደተገደለ የተቆጠረ አይመስለኝም። ግን ትንሽ አይመስለኝም። ደግሞ ከሳውዲ አራቢያ ያላቸው ጓደኝነታቸው እንዴት ፍቅር የተሞላ ነው?!

ዴሞክራሲ ለሰላምና ፍትህ ሊበጅ ይችላል፤ ይህ ጥያቄ የለውም። ግን ሰላምንና ፍትህን ለማስፈን ሥርዓቱ በራሱ አይበቃም።  ብዙሃኑም ልሂቃኑም ቀድሞ በትወሰኑ መሰረታዊ ጉዳዮችና አስተሳሰብ መስማማት አለባቸው። ከህግና የሂደት ደምብ አስተሳሰብ ይቀድማል። አሰተሳሰቡ ካለ ህጉ ይመጣል በሚገባውም ይተገበራል። ህጉ ካለን አስተሳሰቡ ከሌለ ዋጋ የለውም። ብዙ ነገር በጽሁፍ ላይ የዋለ ህገ ደምቦች ሊካታቱ ይችላሉ ግን አስተሳሰብ በጽሁፍ ሳይሆን በልብ ውስጥ የሚሰክን ባህል ነው መሆን ያለበት። ከዛ በኋላ እንቅፋት ሲያጋጥም ይህ አስተሳሰብ፤ ስምምነትና አንድነት ናቸው ከወረቀት ላይ ከሰፈረው ህግ ይልቅ ወደ መፍትሄ የሚመሩን።

ስለዚህ ዴሞክራሲን እንደ ዋና ግብ ወይንም እንደ ጣዖት አንመልከተው። ዋናው ግብ ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ ነው። እነዚህ እንዲሰፍኑ ዴሞክራሲ አንዱ መሳርያ ሊሆን ይችላል። በዴሞክርሲ ዘንድ ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ ሊሰፍኑ ይችላሉ። ግን ቀድሞ ዝግጅቶች ካልተደረጉ፤ ግባችን እነዚህ እንደሆኑና ዴሞክራሲ መንገድ ወይም ሂደት ባቻ እንደሆነ ካልተረዳን ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ የሌለው ዴሞክራሲ ሊሰፍን ይችላል። እንደዚህ አይነቱ ዴሞክራሲ ደግሞ በበርካታ አገራት ልምድ እንደምናየው አይበጅም።