Showing posts with label ምዕራባዊነት. Show all posts
Showing posts with label ምዕራባዊነት. Show all posts

Thursday, 17 May 2018

የ«አማራ ብሄርተኝነት» ትውፊታዊ ነውን?

የ«አማራ ብሄርተኝነት» ትውፊታዊ ነው ወይስ እንደ ሌሎች የጎሳ ብሄርተኞቻችን (ኤርትራ፤ ትግራይ፤ ኦሮሞ፤ ወዘተ) በፈረንጅ በምዕራባዊ በ«ተራማጅ» በማርክሲስት ፍልስፍና የተመሰረተ ነው?

እርግጥ ብዙ አይነት የአማራ ብሄርተኝነቶች አሉ፤ ለፖለቲካ ስልት ወይንም «ታክቲክ» ብቻ የሆነ አለ፤ በስመ አማራ ላለፉት 27/40 ዓመታት ለተበደሉት ፍትሕ መጠየቅያ የሆነ አለ፤ ዛሬ አማሮች ላይ የሚደርስባቸውን በደል ለመታገል የሆነ አለ፤ በሀገር ደረጃ በፖለቲካ ድርድር ለአማራ ህዝብ የሚቆም አለ፤ በሃሰት የታማው የአማራ ህዝብን ታሪክ እውነቱ እንዲታወቅ የሚንቀሳቀስ አለ፤ የአማራ ህዝብ ክብርና ማንነትን ለመመለስ የሚታገለው አለ፤ ወዘተ። ዛሬ እነዚህ ሁሉ አይነት እንቅስቃሴዎች በስመ አማራ ብሄርተኝነት ይጠራሉ።

ዞሮ ዞሮ ዋናው ነጥብ ይህ የፖለቲካና መሃበራዊ ንቅናቄ እራሱን የ«አማራ ብሄርተኝነት» ብሎ መሰየሙ ነው። አላማው ምንም ቢሆን በዚህ «አማራ ብሄርተኝነት» የሚለው ስም መጠራት ይፈልጋል። በዚህ ስም መጠራቱ ምን ይነግረናል? በተለይ በትውፊትና በተቃራኒው ምዕራባዊ ተራማጅነት ያለው ግንኙነቱ ምንድነው?

ደስ የሚለው ነገር የሁሉም አይነት የአማራ ብሄርተኝነት ምልክቶች ትውፊታዊ ናቸው። ለምሳሌ ዓፄ ቴዎድሮስ አንዱ ዋና የአማራ ብሄርተኝነት ንቅናቄ ምልክት ናቸው። የአማራ ታሪክን በትክክሉ ማስተዋወቅና መናገር ሌላው የአማራ ብሄርተኝነት አላማና ምልክት ነው። ግን ዓፄ ቴዎድሮስ እራሳቸውን ወይንም ሀገራቸውን ወይንም አገዛዛቸውን የአማራ ወይንም «አማራ ብሄርተኛ» ብለው ይሰይሙ ይሆን? የአማራ ታሪክ የምንለው በታሪክ ሰሪዎቹ እና በዘጋቢዎች ዘንድ የአማራ ታሪክ ይባል ነበር? የአማራ ብሄርተኝነትን ያንጸባርቅ ነበር?

ለነዚህ ሁለቱም ጥያቄዎች መልሱ «አይደለም» እንደሆነ ነው የማውቀው። ዓፄ ቴዎድሮስ እንደ ሁሉም ንጉሶቻችን በስመ ኢትዮጵያዊነት ነበር እራሳቸውን የሚመለከቱት። ታሪካችም እንዲሁ ኢትዮጵያዊነት ላይ ነው የሚያቶክረው አማራነትን አይደለም። ይህ ማለት «አማራ» የሚባል ህዝብ የለም አልነበረም ማለት አይደለም! መኖሩ በታሪክ በተለያየ ቦታ መመዝገቡ ይታወቃል። ግን እስከማውቀው ማንም በስመ አማራ አልተንቅሳቀስም። ትውፊታችንና ታሪካችን እንደዚህ ከሆነ እንዴት እራሱን «አማራ ብሄርተኝነት» ብሎ የሰየመ ንቅናቄ ትውፊታዊ ነው ማለት ይቻላል?

በሁለተኛ (ወይንም አንደኛ!) ደረጃ ጠቅላላ የጎሳ ብሄርተኝነት የሚባለው ነገር የምዕራባዊ የፖለቲካ ፍልፍና እንደሆነ ይታወሳል። በትውፊታዊ ፖለቲካ «ሀገር» ነው ያለው፤ «ጎሳ» የለም። ይህ አባባሌ ብዙ ነገሮች ስለሚያከማች ሁሉንም በዚህ ጽሁፍ አልጠቅስም ግን በጠቅላላ የ«ጎሳ ብሄርተኝነት» የዘመናዊ የምዕራባዊ ጽንሰ ሐሳብ ነው።

የምፈራው ነገር ይህ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ልክ እንደ በፊቶቹ የኤርትራ፤ የትግራይ፤ የኦሮሞ፤ ወዘተ ብሄርተኝነቶች በብሶት እና በበአድ ምዕራባዊ ርዕዮተ ዓለም የተመሰረተ ኢተውፊታዊ ንቅናቄ ይሆናል ብሄ ነው። የኤርትራ እና የትግራይ ብሄርተኝነት በመሰረቱ ጸረ ትውፊት ናቸው። በቀላሉ ምሳሌ ለህዝባቸው መሰረት የሆነው ሃይማኖትና ባህልን የሚጠላ ርዕዮተ ዓለም ነው እነዚህ ብሄርተኝነቶች የተመሰረቱት። የኦሮሞ ብሄርተኝነት እንደዚህም ቢሆን ቢያንስ ወደ ኦሮሞ ትውፊት ለመመልከትና እንደ ገዳ አይነቱን ተውፊት ማክበር ሞክሯል። ሆኖም መሰረቱ የማርሲስት የጨቋኝ ተጨቋኝ የጎሳ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ ነው። የአማራ ብሄርተኝነትም እንደዚህ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርበታል። ግን እራሱን «አማራ» ብሎ ከሰየመ እዚህ ወጥመድ ውስጥ ቀድሞ ገብቷል ማለት ይመስለኛል።

ጎበዝ፤ ጠንካራ፤ ሀገር ወዳድ ምሁራን በተለይ ወጣቶች የአማራ ብሄርተኝነት ያቀፉ አሉ። ምክንያቱ ለሁላችንም ሊገባን ይገባል፤ ለብሶት መልስ ነው። የአስራት ወልደየስ ፖለቲካ የብሶት ሳይሆን እራሳቸው እንዳሉት የግዴታ ነበር። የዛሬው ግን የ27/40 ዓመታት ያመጣው ብሶት ነው። ብሶቱ በህወሓት ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም፤ በድሮ ምሁራን፤ ልሂቃን፤ ተቃዋሚ፤ ወዘተ ነው። እኔ እንደሚመስለኝ የተማሪው ንቅናቄ ወደ እንደ ማርክሲዝም አይነቱ ምዕራባዊ ፍልስፍና እና ርዕዮተ ዓለም በብሶት ምክንያት እንደገባው የዛሬው ትውልድ በብሶቶች ምክንያት እንደ ቀድሞው ተማሪ ንቅናቄ ወደ ኢ-ትውፊታዊ (ምን አልባት ጸረ ኢትዮጵያዊ) የማይሆን አስተሳሰብ እየገባ ነው። ስለ ተውፊቱ ስላልተማረ በምዕራባዊ የቀለም ትምሕርት የሚሰግድ ህብረተሰብ ውስጥ ስላደገ ሳያውቀው ብዙ ኢ-ትውፊታዊ አስተሳሰቦች አድረውበታል።

ስለዚህ ጉዳዩን ወደ ኋላ ወደ መሰረታችን ተመልሰን አመለካከታችንን በሙሉ ከ«ሀ» ብንገመግም ጥሩ ይመስለኛል። ከዛ በኋላ ነው የአማራ ብሄርተኝነት ትውፊታዊ ነው ወይ የሚለውን ጥያቄ በትክክሉ ልንመልሰው የምንችል የሚመስለኝ።


Wednesday, 21 March 2018

«ሴኩላሪዝም»

ትንሽ አመታት በፊት አንድ የመንግስት ስራተኛ የሆነ ዘመዴ የኦርቶዶክስ መዝሙር ከመስሪያቤት ኮምፕዩተሩ ላይ ማዳመጥ ክልክል እንደተደረገ ነገረኝ። ለምን ብዬ ስጠይቀው ክርስትያኑም ሙስሊሙም የሚፈልገውን መዝሙር፤ ስብከት፤ ትምሕርት እያዳመጠ እና ኮምፕዩተሩ ላይ ሥዕል እየለጠፈ የሰራተኞች እርስ በርስ ግጭት ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ተከለከለ አለኝ። የሚገርመው ነገር ግን 1) ከመስሪያቤቱ እንደዚህ አይነት ግጭቶች አልነበሩም እና 2) ክልከላው በተራ ትዛዝ ሳይሆን ከከፍ ያለ የአስተዳደር ደረጃ በመመርያ ምልክ የተላለፈ ነበር። የመመርያው ርዕስ ደግሞ «ሴኩላሪዝም» ነበር።

ይህን ታሪክ ስሰማ እጅግ አዘንኩኝ። መቼ ነው መንግስቶቻችን፤ ምሁሮቻችን እና ልሂቆቻችን የምዕራብ ዓለም ርዕዮት ዓለምና ፍልስፍና ይዘው አገራችን ላይ መጫን የሚያቆሙት? ካለፉት የ100 ዓመታት ታሪካችን አይማሩምን?

እስቲ «ሴኩላሪዝም» ባጭሩ ምን እንደሆነ እንመልከት። «ሴኩላሪዝም በዓለማችን እግዚአብሔር የለም/አይሳተፍም ብሎ ማሰብ ነው»። ሴኩላሪዝም እግዚህብሔር ሊኖር ላይኖርም ይችላል ግን ከዓለማችን ከሕይወታችን ከለት ኑሮአችንም አይሳተፍም የሚለው አመለካከት ነው። እግዚአብሔር ካለ እዛው ከዙፋኑ ወይንም ገነቱ ተቀምጦ ይመለከተናል። በሃይማኖት እና በእግዚአብሔር በግል ምርጫችን ልናምንባቸው የምንችል የእምነት ሥርዓቶች ናቸው። በሀሳብ ደረጃ ነው የምናምንባቸው ካላሰኘን ደግሞ ከሀሳባችን እናስወግዳቸዋለን!

ይህ አስተሳሰብ በተለያየ መንገድ ወደ ክርስትያን የሆነውን አስተሳሰብ ገብቷል። «ዓለማዊ» እና «መንፋሳዊ» የምንላቸው ቃላት በተሳሳተ መንገድ እንጠቀማለን። ዓለማዊ ስንል ስራችን፤ ትምሕርታችን፤ ገበያችን፤ ንግዳችን ወዘተ ነው። እግዚአብሔር እነዚ ነገሮች ውስጥ እንዳለ አናምንም። ስለዚህም ነው በነዚህ የህይወት ዘርፎቻችን ኢ-ክርስትያናዊ ነገሮች እያደረግን እያለን አማኞች ነን የምንለው። እሁድ እሁድ ግን ቤተ ክርስትያን ሄደን ወደ መንፈሳዊስ ዓለም እንሸጋገራለን። እዛ ጨዋ ነን፤ ጥሩ ስነ መግባር አለን፤ ጭንቀቶቻችንን አስተንፍሰን ወደ ዓለማችን እንመለሳለን።

ይህ ግን የውሸት ክርስትና ነው። በእምነታችን እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ በሁሉም ነገር አለ። «እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም። ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር።» ኤር 23:23-24።

ስለዚህ ትምሕርት ቤት ብሄድ፤ መስሪያ ቦታ ብሄድ፤ እርሻዬ ላይ ብሆን፤ ትራንስፖርት ላይ ብሆን፤ መጠጥ ቤት ብሄድ፤ በሁሉም ቦታ እግዚአብሔር አለ። ሕይወታችንን እግዚአብሔር ያለበትና የሌለበት ብለን ልንከፋፍለው አንችልም። በሁሉም ቦታ በሁሉ ደቂቃ ከኛ ጋር ነውና።

ይህ የሚያሳየን የሰው ልጅ ክርስትያንም ሴኩላሪስትም አብሮ ሊሆን አይችልም። ብዙዎቻችን ወደዚህ ስህተት ብንገባም ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ለክርስትያኖች እግዚአብሔር ልኬት የለውምና። በተጨማሪ ሴኩላሪዝም እግዚአብሔርን ከለት ኑሮአችን ማጥፋት ስለሚፈልግ የክርስትና ተቃራኒ ብቻ ሳይሆን ጠላት እንደሆነ ግልጽ ነው።

«እናንተ ኦርቶዶክሶች፤ ሙስሊሞች፤ ፕሮቴስታንቶች አብሮ መኖር አትችሉም። ስለዚህም (እግዚአብሔራን ተክቼ!) ከላያችሁ ሆኜ አስተዳድራችኋለሁ» ይላል ሴኩላሪዝም / ሴኩላሪስቱ። «እኔ ነኝ ስልጡኑ፤ ከማንም ጋር የማልጋጨው፤ ከሁሉም ጋር የምግባባው፤ ሁሉንም የማከብረው» ይላል። እውነቱ ግን ሴኩላሪስቱ እንደዚህ ሲል ሁሉንም በሰላም ለመጠበቅ ሳይሆን አላማው ይህን አስመስሎ «እግዚአብሔር የለም» የሚባለውን ሃይማኖትን ለማስፋፋት ነው። እግዚአብሔር ከአዕምሮአችን ብቻ ነው ያለው እንጂ ከስራ ቦታችን፤ ገበያ ቦታችን፤ መንገዶቻችን፤ ሚዲያዎቻችን፤ ከለት ኑሮአችን የለም ብለን ካመንን ቀጥሎ እግዚአብሔር የትም የለም ማለት የሚቀጥለው ቀላል እርምጃ ነውና!

በተጨማሪ እግዚአብሔር ከለት ኑሮአችን ከሌለ የማህበረሰብ የአገራችን ድንጋጌዎች ከየት ሊመጡ ነው? ከሴኩላሪዝም ርዕዮት ዓለም ከ«እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖት ሊመጡ ነው! አያችሁ ሴኩላሪዝም እራሱን ገለልተኛ አድርጎ እንዴት «እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖትን ሰተት ብሎ እንደሚያሰፍን።

ኢትዮጵያ የሃይማኖት አገር ናት። ታሪካችን ትውፊታችን ከዚህ የተያያዘ ነው። ማንነታችን ይህ ነው። ሴኩላሪዝም ደግሞ የህን አፍርሶ «እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖትን ነው ማስፈን የሚፈልገው። ይህ ሂደት እንዴት እንደሚሰራ ለማወቅ የምዕራብ ዓለሙን ያለፈውን 400 መቶ ዓመት ታሪክ መመልከት ነው። ስለዚህ ሴኩላሪዝም ኢ-ኢትይጵያዊ እንደሆነ ተረድተን ወደ አገራችን ሰተት ብሎ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን። በተለይ ደግሞ ወደ ልባችን ሰተት ብሎ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን።

Friday, 2 March 2018

የምዕራባዊያን አገራት አምልኮ

የአባቴ ትውልድ የምዕራባዊያን አገሮችን የሚተቹባቸው በርካታ ጉዳዮች ነበሩ። ዘረኛ ናቸው። ታላቂቷ ምዕራባዊ አገር አሜሪካ አሁንም በጥቁር ዜጎቿ ታላቅ ግፍ እያደረሰችባቸው ነው። ዓለምን በቅኝ ግዛት አሰቃይተዋል። ቅኝ ግዛታቸውን እየተውዉ ቢሆንም አሁንም በ«አዲሱ ቅኝ ግዛት» መርህ ዘንድ ጥቅማቸውን የማያስከብሩ መንግስታትን በመፈንቀለ መንግስትና የተለያዩ ዘዴዎች ያፈርሳሉ።

የአሁኑ ትውልድ ደግሞ የምዕራባዊያን አገሮችን እንደ ጣዖት የሚያመልክ ይመስላል። ነፃነት ከነሱ ጎራ ነው የሚገኘው። ተራማጅነት ከነሱ ነው። ሀብት ከነሱ። ዴሞክራሲ ከነሱ። ቴክኖሎጂ ከነሱ። ስነ መግባር ከነሱ። ወዘተ።

በኔ ኢይታ ይህ አምልኮ ለአገራችን ለያንዳንዳችንም አደገኛ ነው። ለምን ብትሉኝ ይህ አመለካከት ከባህላችን፤ ትውፊታችን፤ ማንነታችን ነጥቆ እንደ ስሩ የተነቀለ አትክልት ነው የሚያደርገን።

ስለዚህም ቢዚህ ርእስ ዙርያ የተወሰኑ ጽሁፎች ለማዘጋጀት አቅጅያለሁ። የኢትዮጵያዊነት፤ የሰውነት፤ የማንነት ጉዳይ የተሳሰረበት ርእስ ነው። የምዕራባዊው ፕሮፓጋንዳ እጅግ ከባድ ነው። በመሰረታዊ አስተሳሰባችንን፤ አስተያየታችንን፤ አስተነፋፈሳችንንም ታላቅ ሚና ተጫውቷል። መሰራታዊ ሃሳቦቻችንና ቋንቋችንም ቀይሯል መቀየሩንም አናውቀውም! ይህ ሁሉ በደምብ ልናየው ይገባል።

ጽሁፎቼን ስጽፍ በተለምዶ በመጀመርያ እንደ ክርስቲያን በማቀው ክርስቲያናዊ አመለካከት ነው የምጽፋቸው። እምነቴ በሁሉ ነገር ኢግዚአብሔር አለ ብሎ ሰለሚያስተምር እንቋን የማንነት ጉዳይ ምንም ነገር ከዚህ መነጽር ውጭ ማየት አይቻልም።

ለጽሁፎቼ እንደ መግብያና ሀሳብ ማንሸራሸርያ እስቲ እነዚህን ቃላቶችን እናስባቸው፤

ዘመናዊነት (modernity)
መሻሻል ወይም እድገት (progress)
ዴሞክራሲ (democracy)
ነፃነት (freedom)
ሰው (Man)
ፍትህ (justice)
ልማት (development)
አገር (nation)
ጎሳ (tribe - in the neutral sense)
ተፈጥሮ (nature)
ፍቅር (love)
ስልጣኔ (civilization)
ሴኩላሪዝም (secularism)