ስለ አማራ ማንነት ይሆን ወይም በሌላም አርእስት ስነወያይ ነገሮችን በጥራት እንድናይ ለመወያየት ለመከራከር ለመተቻቸት ብቻ ሳይሆን ግብ ለመምታት ከሆነ ከውይይታችን ከአስተሳሰባችን በስተ ጀርባ ዙርያውን ያለውን ሁኔታ አስተሳሰባችን መመልከት አለብን። ይህን ለማድረግ ዘንድ እስቲ እነዚህን ነጥቦች በደምብ እንመልከታቸው።
1. ሁሉም ውይይት "context" (ዐውደ ሁኔታ?) አለው። ዛሬ ያለው ሁኔታ ምንድነው? 60 ዓመት በፉት ይህ ውይይት ይኖር ነበር ቢኖርስ ምን ይመስል ነበር። 2. ለውይይቱ ምን አይነት አመለካከት ርዕዮት ዓለም እምነት ወዘተ ይዘን ነው የምንከራከረው? በጎሰኝነት ("identity") ፒለቱካ እናምናለን? ወይም የአገር ብሄርተኖች ("nationalist") ነን? 3. የምንጠቀምበት ቋንቋ ቃላቶች ምን ትርጉም አላቸው? «ጎሳ» ምንድንደው? «ህዝብ» ምንድነው? «አማራ» ምንድነው? «ማንንነት» ምንድነው?
4. የውይይታችን አላማ ምንድነው? ውይይቱን ማሸነፍ ነው? መስማማት ነው? እውነት ላይ መድረስ ነው?
5. የጠቅላላ አላማችን ምንድነው? ከአገራችን ሽኩቻ አድሎ ኢፍትሃዊነት እንዲጠፋ ሰላምና ፍትህ እንዲኖር ነው? ህወሓትን ከስልጣን ማውረድ ነው? ስልጣን መያዝ ነው? ጥሩ የሚመስለንን ሥርዓትን ማስፈን ነው?
6. ውይይታችን አቋማችን ከህዝቡ ዝንባሌ ጋር በተወሰነ ድረጃ ብቻ ቢሆንም ይሄዳል ወይ? ይህ ታላቅ ጥያቄ ነው። የ«ፌስቡክ» ብቻ ውይይት ነው? የልሂቃን ብቻ ውይይት ነው? የአዲስ አበባ ብቻ ውይይት ነው? የተማሪዎች? ወይም ከብዙኃኑ ምካከል ይህ ጉዳይ እንደ ቁም ነገር ይቆጠር ይሆን?
ሁላችንም እራሳችንን እነዚህን ጥያቄዎች ጠይቀን በአግባቡ መልሰን ነው ፍሬአማ ውይይት ሊኖርን ይሚችለው።
እስቲ የኔን መልሶች ልስጣችሁ፤
1. ዛሬ የምዕራባዊ የማርክሲዝም የጎሳ ወይም ብሄሮች አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ በደምብ ሰክኗል። በ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ተማሪዎቻችን ወደ ውጭ አገር ትምሕርትቤት ሄድው ያመጡት ርዕዮት ዓለም አገር ውስጥ መሰረት ጥሎ ጭርሽ ህገ መንግስታችንን በክሎታል የፖለቲካ መዋቀራችንን በይኗል። በመሀበረሰብ ደረጀ በፊት ከ«ልሂቃን» ያልወጣ አስተሳሰብ አሁን አማራ ኦሮሞ ሲዳማ ትግሬ ብዙኃኑም ያውቀዋል። ግን በትክክሉ ምንድነው የሚያውቀው? ቋንቋ ነው? «ዘር» ነው? «ቦታ» ነው? ማንነት ነው? የፖለቲካ ክፍል ነው? ብዚህ ዙርያ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም አብዛኞቻችን «አማራ» የሚለውን ቃል ድሮ የማንጠቀምበት ዛሬ እንጠቀምበታለን። ድሮ የፖለቲካ ትርጉም ያልነበረው ዛሬ አለው። ዛሬ ሰዎች በአማርነት ይከሰሱበታል። ይወነጀሉበታል። አንዳንዱ አማራ በመሆኔ ተጎጂ ነኝ ብሎ ያስባል። እጨቆናለሁ መብት የለኝም የሚል አለ። ባጭሩ ይህ ሁኔታ ላይ ነው ዛሬ የምንገኘው።
2. ማንነት የሰው ተፈጥሮ ባህሪ ነው ብዬ አምናለው። በመንደር ካልሆነ በጠቅላይ ግዛት ካልሆነ በጎሳ ካልሆነ በአገር ሁላችንም አንዱ የማንነታችንን ክፍል ይህ ነው። እስቲ አንድ ምሳሌ እናስብ። አንድ ኢትዮጵያዊ አሜሪካ ለ20 ዓመት ኖሮ ዜግነት ተቀብሎ አሜሪካው ነኝ ይላል። ኢትዮጵያዊ ነኝም ይላል። ለምን ኢትዮጵያዊነቱን አይተወውም። ልም ልጆቹን የኢትዮጵያ ቋንቋ ያስተምራል ቢችልም የኢትዮጵያ ትምሕርትቤት ይልካል? ለመሆኑ አሜሪካና ኢትዮጵያ በሆነ ጉዳይ ቢቃረኑ ማንን ይሆን የሚደግፈው? ኢትዮጵያን ቢደፍግ ሌላው አሜሪካዊ ከሃዲ አይለውም ይሆን? ለሌላው አሜሪካዊ «ኢትዮጵያዊ-አመሪካዊ» ማለት ጎሳ ነው። አያችሁ የጎሳ ስሜት እንዴት የተፈጥሮ እንደሆነ። የተፈጥሮ ቢሆንም ብዙ ጎሳዎች ያሉበት አገር ውስት የጎሰኝነት ስሜት ከአገር ብሄርተኝነት ስሜት ከበለጠ የጎሳ ፉክክር ("ethnic competition") በፖለቲካ ምድር ውስጥ ያበዛና ለአገሪቷ ህልውና ለሰላም ለፍትህ አደገኛ ነው ይሚሆነው። ይህን ነው ዛሬ በኢትዮጵያ የምናየው። ይህ ምክነያት የአገር ብሄርተኛ ነኝ። ማለት ለሁላችን ሰላምና ለአገሪቷ ብልጽግና የጎሰኘት ስሜት ከአገር ስሜት በታች መሆን አለበት ብዬ ነው የማምነው። «ኢትዮጵያዊ ነኝ ቀጥሎ ኦሮሞ» ትሩ ነው። «ትግሬ ነኝ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ» ወደ ችግር ይመራል።
3. «ጎሳ» «ህዝብ» «ማንንነት» «አማራ» ለሁላችንም የተለያዩ ትርጉሞች አላቸው። ከላይ እንዳልኩት ለኔ የሰው ልጅ ማንነት ውስጥ አንድ የአገር ወይ ጎሳ ወይ መንደር ወዘተ ክፍል አለ። ስለዚህ ለኔ ይህ የማንነት ክፍል በ«ኢትዮጵያዊነት» ወይም «ኦሮሞነት» ወይም «ኦሮሞ-ኢትዮጵያዊነት» ወይም «ኢትዮጵያ-አማራነት» ወይም «ጎጃምነት» ወይም «አፍሪካነት» ሊሞላ ይችላል። ግን ሰውው «ጎሳ» እና «ህዝብ» እና «አገር» ሲለይ የፖለቲካ አቋምን ነው የሚገልጸው። ለምሳሌ አውሮፓ ከትናንሽ የንጉስ ግዛቶች «ጎሳዎች» ወደ አገሮች ("nation state") ሲቀየር «ጎሳ» የኋላ ቀር ነው ብለው ሰየሙ። ግን በጎስኝነት ዘመን የሚያራምዱት ጥላቻን ጦርነትን አሁን በ«አገር» ደረጃ በከፍ ያለ አቀም አራመዱት! ወደ «አማራ» የምንለው ቃል እንምጣ። የቃላቱ ትርጉም በመቶዎች ዓመታት እነደተቀየሩ ግልጽ ነው። የታሪቅ መጽሐፍቶች የድሮ አጠቃቀም ካሁኑ እንደሚለው ያሳያሉ። በቅርብ ዓመታት እራሱ ለምሳሌ ከሃረር እስከ ሸዋ መካከል «ነባር» ሙስሊም ኦሮሞዎች በቀር ሌላው «ክርስትያን» ነበር የሚባለው። ግን ነገሮች ይቀየራሉ። አሁን ከላይ እንደጠቀስኩት የማርክሲዝም ፖለቲካ ሰፍኖ ሁላችንም አማራ እንላለን ወይም ታግለን እራሳችንን እንቆጥባለን።
4. ስወያይ በተቻለ ቁጥር እውነት ላይ ለመድረስ ነው የምወያየው። አዎን አንድ አንድ ጊዜ ፍተናው ያሸንፈኛልና ትቢት ተሞልቼ ማሸነፍ ፈልጋለው አቋሜ ትክክል ቢሆንም ባይሆንም። ውይም ፈርቼ ወይም ለይሉኝታ መስማማት እፈልጋለሁ ስምምነት በውሸት የተመሰረተ ቢሆንም። ግን ደካማ ወገኔን ትቻ አላማየ እውነት ነው። ባልወደውም። ለምን እውነንት? እውነት ነው ለሁሉም የሚበጀው። አላማ እውነት ነው ማለት ለታክቲክ ወይም ለጊዜያዊ ሰላም ቁስል እስኪድን ወዘተ ተብሎው ዝም አይባልም ወይም አይዋሽም ማለት አይደለም። ገን የመጨረሻ ግቡ እውነት ነው።
5. እኔ ሰላምና ፍትህ ነው የምወደው። (አድሎ ሙስና አይኖር ማለት ፍትህ ይኑር ነው።) ሰው እንዳይጎዳ። ሰው ሌላውን ጉዳ እንዳይባል መጉዳት ከመጎዳት ይበልጥ ጎጂ ነውና። ከዛ ውጭ ማን ይግዛ ምን ሥርዓት ይኖር ግድ የለኝም። እንደ ኦርቶዶክስ ክርስትያንነቴ ወደ ንጉሳዊ አገዛዝ አደላለው ከሰው ወይም ሰዎች ይልቅ እግዚአብሔር መሪ ቢሾም ይሻላል ስለሚመስለኝ። ግን ይህ ሀሳብ ለ«ዘመናዊ» ሰው አይገባውም እንተወው። ለማንኛውም ሰላም ፍቅር ፍትህን የሚያበዛ ትልና ሽኩጫን የሚያሳንስ ሥርዓት ከተባለ ከሞላ ጎደል ምን መምሰል እንዳለበት እናውቃለን።
6. እውነቱን ለመናገር ይህ ሀአማራ ማንነት ጉዳይ ከዲያስፖራና ፌስቡክ ውች ያን ያህል ትኩረት ያለው አይመስለኝም። በኔ እይታ (በኢህአዴግም ይመስለኛል!) ያለፉት ሶስት አራት ዓመት የህዝብ ተቃውሞ በመጀመርያ ደረጃ አድሎን በተለይ የ«ትግሬ አድሎን» ተመስርቶ ነው። ይህ በአማራ ክልል የተካሄደውን ተቃውሞንም ያካትታል። መፈከሩ ትግሬ አይግዛን ነው እንጂ አማራ ይከበር አይመስለኝም። በግሌ ያየሁት የሰማሁት እንደዚህ ነው። እንደሚመስለኝ ዛሬ አማራ የምንለው ህዝብ አሁንም በጣም ወደ ኢትዮጵያዊነት ያመዝናል ከአማራነት ይልቅ። ነገ አማራ ክልል በንዚን ቢገኝ ለአማራ ክልል ብቻ ይውል የሚል ጥቂት መሰለኝ። ትግሬ ምንም አያገኝ የሚሉ ብዙ ይኖራሉ ያሳዝናል እንጂ። ጥቃት ያመታው ችግር ነው። ግን አብዛኛው አማራ በለጸገች ከማለት ኢትዮጵያ በለጸገች ነው የሚለው።
እሺ በመጨረሻ ለ«ትግሉ» ተብሎ በአማራነት መታገሉ አይሻልም ወይ የሚለው ከመምህር ሐዚም አስራት ወልደየስ ዘመን ጀምሮ ያለ ጥያቄ አለ። ያኔ አልሰራም ከላይ እንደጠቀስኩት «አማራ» የሚባለው ስሜቱ ከአማራነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነት እጅግ ስለሚበልት። አናሳ ብሄርም ስላልሆነ። የተጭቋኝ ስሜትም ስላልነበረው። ዛሬ ሁኔታው ጠቀይሯል በተወሰነ ደረጃ ግን አሁን ስኬታማ የ«አማራ የጎሳ» ትግል ለማካሄድ የህዝቡ ሁኔታ የሚፈቅድ አይመስለኝም።
እውነት ነው እንደዚህ አይነቱ ትግል ያስጎመዣል። እነ ሻዕብያ ህወሓት ኦነግ እንዳረጉት ስኬታማ ትግል ማድረግ ነው። የጎሳን የተፈጥሮ የማሰባሰብ ኃይል መጠቀም ነው። ግን ሁኔታው ካልፈቀደ ህዝቡ ማንነቱ ከዚ አይነት አስተሳሰብ ጋር የማይሄድ ከሆነ አሁንም አይሳካም። ሰከን ብሎ ማሰብ ነው።
በመጨረሻ ላስታውሳችሁ የምወደው ምሳሌዎቹ ወይም "template" የሆኑት እነ ሻዕብያ ህወሓት እጅግ አናሳ ስለሆኑ ለማሸነፍ ጎሰኝነትን ግድ መጠቀም አለብን ብለው ያምኑ ነበር። ግን እስካማውቀው ኢ-ህወሓት የሆንነው ወይም «ተቃዋሚ» የሆንነው የአገሪቷ 90% ወይም 80% ወይም 70% ነን። የጎሰኝነት የፖለቲካ ኃይል መሰብሰብያ "ethnic leverage" አስፈላጊ ነው ልንል አይገባም። ትንሽ የፖልቲካ ብስለት ትብብር አብሮ መስራት መተማመን ጉዳዩን ትላንት ይጨርሰው ነበር።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!